ኪዳኔ ዓለማየሁ
መግቢያ፤
በጥንቱ ዘመን የአባይ ወንዝ ዋናዋ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗና ባለቤትነቱዋ ታውቆ የግብጽ መሪዎች በየዓመቱ ለሚጎርፍላቸው ውሀ ይከፍሉ ነበር። ባሁኑ ጊዜ ግን በተለይ ግብጽ የአባይን ወንዝ እንደ ግል ንብረቷ በመቁጠር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ለመጠቀም የምታከናውነውን ጥረት መቃወም ብቻ ሳይሆን ማስፈራራትም ይቃጣታል።
እንደሚታወቀው በየድረ-ገጹ በስፋት ከሚቀርቡት ሐተታዎች፣ ትችቶችና አስተያየቶች ውስጥ ሰፊ ስፍራ ይዞ የሚገኘው አንደኛው አርእስት ኢትዮጵያ ውስጥ በመገንባት ስላለው ታላቅ የአባይ ግድብ ነው። ስለ ግድቡ የተንጸባረቁት የተለያዩ አስተያየቶች እንዳሉ ሆነው የአባይ ወንዝ ባለቤትነት የማን እንደ ሆነ ውሱን በሆነ መንገድ ተነካ እንጂ በጥልቀት በተከናወነ ምርመራና በዓለም-አቀፍ ሕግ በተመሠረተ አስተማማኝ ማስረጃ የተደገፈ ጽሑፍ አልቀረበም። የዚች ጦማር ዓላማም ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር እንዲሁም ከሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር በምታከናውናቸው ውሎች ያሁኑንና የመጪውን ትውልድ ሁሉ መብት በሚጠብቅ ሥልት መጠቀሟን እንድታረጋግጥ ተገቢውን ቅድመ-ዝግጅትና ጥንቃቄ እንድታደርግ ለማሳሰብ ነው። በዚህ አጋጣሚም ተሞክሮው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ስለሚመስለኝ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት የለሶቶ (Lesotho) መንግሥት የሥራ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በነበርኩበት ጊዜ ስለዛች ሀገር ወንዝ በዓለም ባንክ ድጋፍ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጋር እኔ ራሴ በመራሁት የልዑካን ቡድን ስለ ተከናወነው ድርድርና ስለ ተገኘው ውጤትም ባጭሩ እገልጻለሁ።
የአባይ ወንዝ በረከት፤
አባይ፤ ኢትዮጵያ ካሏት እጅግ ታላቅና አኩሪ የተፈጥሮ ሀብቶች አንዱ ነው። ከልዩ ልዩ ወንዞች የተጠራቀመው ወደ 80 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር (cubic metre) ውሀ በአባይ አማካኝነት እየተዥጎደጎደ ሱዳንንና ግብጽን እያለማ አቋርጦ ከሚተነው ውሀ ጭምር የተረፈው ሚዲቴሬኒያን ባሕር ይገባል። አባይ ከኢትዮጵያ ሰንቆ የሚጓዘው ውሀ ብቻ ሳይሆን ለም አፈር ጭምር ነው። ስለዚህ ግብጽና ሱዳን የሚታየው ለም መሬት አብዛኛው በአባይ ወንዝ አማካኝነት ከኢትዮጵያ በሚጎርፍለት ውሀና ለም አፈር ችሮታ ነው። በተጨማሪም፤ እስካሁን ሳንጠቀምበት የቆየነውና አሁን ግን የተሰራው ግድብ 60 በመቶ ስራው በተጠናቀቀበት ወቅት ለኢትዮጵያና ለአካባቢዋ ከፍ ያለ የኤሌትሪክ ኃይል ሊያስገኝ የሚችለው ሌላው የአባይ ወንዝ በረከት ሊሆን ይችላል።
በአባይ ወንዝ በረከት የተጠቀመው ማን ነው?
አባይ (በእንግሊዝኛ Blue Nile) ከተሰኘው በዓለምና በታሪክ ታዋቂ ከሆነው ወንዝ ዋናዎቹ ተጠቃሚዎች ሱዳንና ግብጽ ናቸው። ከሌሎች ሀገሮች ጭምር ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚፈሰው ውሀ ሲታሰብ ከኢትዮጵያ የሚዘልቀው የአባይ ወንዝ አስተዋጽኦ ከጠቅላላው የውሀ መጠን 86% እንደ ሆነ ይታወቃል። የሚያሳዝነው ከባድ ጉዳይ ግን የአባይ ወንዝ ዋናዋ ምንጭ የሆነችው፤ ኢትዮጵያ፤ ለብዙ ዘመናት ተጠቃሚ ሳትሆን መቅረቷ ነው። ይህን ሁኔታ ከባድ የሚያደርገው ባንድ በኩል አባይን የመሰለ አኩሪ የውሀ ሀብት እያላት ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት በመደጋገም ረሀብና እልቂት የተፈራረቀባት ሀገር መሆኗ ነው። *
ለመሆኑ፤ የአባይ ወንዝ ባለቤት ማን ነው?
ዶር. ሚንጋ ነጋሽ፤ ዶር. ሰይድ ሀሰንና ዶር. ማሞ ሙጬ በቅርቡ ባበረከቱት “Misplaced Opposition to the Grand Ethiopian Renaissance Dam” በተሰኘው ጽሑፋቸው፤ ከታዋቂው ከሪቻርድ ፓንከርስት (Richard Pankhurst) በመጥቀስ በጥንቱ ቱርኮች ግብጽን በሚገዙበት ዘመን የአባይ ወንዝ የኢትዮጵያ መሆኑ ታውቆ፤ 50,000 (ሃምሳ ሺ) የወርቅ መሀለቅ (gold coins) ለሀገራችን በየዓመቱ ይከፍሉ እንደ ነበር ታውቋል።
ከላይ እንደ ተጠቀሰው፤ ምንም እንኳ ወደ ሱዳንና ግብጽ የሚነጉደው የአባይ ወንዝ ምንጭ ኢትዮጵያ ብትሆንም፤ በቅርቡ ዘመን የታየው ሁኔታ ለጊዜው ተጠቃሚ የሆኑት ሀገሮች እያንጸባረቁት የቆየው ተጨባጭ ሁኔታ ባለቤትነቱ የነሱ እንደ ሆነ ዓይነት ነው። ከላይ የተጠቀሱት ምሁራን እንደ ገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችባቸው ውሎች፤ (ሀ) እ.አ.አ በ1929 በእንግሊዝና በግብጽ መሀል በተፈጸመው ውል 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር ውሀ ለግብጽ፤ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር ውሀ ለሱዳን እንዲመደብ፤ በኋላ ደግሞ (ለ) በ1959 በግብጽና በሱዳን መሀል በተከናወነው ውል 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር ለግብጽ፤ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሚትር ውሀ ለሱዳን ተመድቧል። የሚያስገርመው፤ ዋናዋ የውሀው ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ መብት ምንም ዋጋ አልተሰጠውም።
ባሁኑም ጊዜ ተከስቶ ያለው ሁኔታ፤ ግብጽ “የአባይ ስጦታ” (“Gift of the Nile”) መሆኗን ስለምታውቅ በተለይ በቅርቡ ዘመን የለመደችውን ልቅ የሆነ በአባይ ወንዝ የመጠቀም ችሮታ ያለገደብ እንድትቀጥል መብቷ እንደ ሆነ እያስመሰለች ኢትዮጵያ በመብቷ ከተጠቀመች እርምጃ የሚያስከትል መሆኑን በመጠቆም የማስፈራራት ሥልት እያናፈሰች፤ በሌላ በኩል የዚህ ዓይነት አጉል ዘዴ የማያዋጣ መሆኑን ግንዛቤ ያለው በሚመስል ሥርዓት ለመደራደር ፈቃደኛነት ታሳያለች ። ኢትዮጵያውያን መብታቸውን ለማስከበር በቁርጠኛነት ከወሰኑ ማንም ሊገድባቸው እንደማይችል ግብጽም ብትገነዘብ መልካም ነው። በታሪክ እንደምናውቀው ግብጽ የሕልውናዋ ምንጭ የሆነውን አባይን በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ ከአሥር ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን ወርራ ሐረርን እስከ መያዝ ደርሳ፤ በመጨረሻው ግን ምኑም ሳይሳካላት ቀርቷል። በተቃራኒው ከታሪክ የምንማረው ኢትዮጵያ ከኃያሎቹ ሀገሮች አንዷ በነበረችበት ዘመን ግብጽንም ተቆጣጥራ ነበር። ለዚህ ማስረጃ ካስፈለገ የጥንት ግብጻዊ ነገሥታትን ታሪክ መመልከት ይበቃል። ስለዚህ ግብጽ ስለ አባይ ወንዝ ባለቤትነት የምትከተለው ሥልት የትም ስለማያደርሳት ይልቁንስ ሚዛናዊ በሆነ፤ የሁሉንም የወንዙን አካባቢ ሀገሮች መብት በትክክል ማስተናገድ የተሻለ ዘዴ ነው። ለኢትዮጵያ መብቷን የማስከበሩ ዋናው ኃላፊነት ግን የኢትዮጵያ የራሷ ነው። ሱዳንን በተመለከተ፤ ምንም እንኳ ከመገናኛ ብዙኃን መገንዘብ እንደሚቻለው በመገንባት ላይ ስላለው ግድብ ደጋፊ መሆኗ ቢገለጽም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ስላላት መብት አቋሟ ምን እንደ ሆነ በይፋ አልተገለጸም።
ስለ አባይ ወንዝ ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ ከሚነጉደው ውሀ 86% የምታበረክተው 110 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት ኢትዮጵያ ድርሻ በትክክል እንዲታይ ያስፈልጋል። የውሀ ሀብቷ እያለ፤ ኢትዮጵያ በድርቅና በረሀብ መሰቃየቷ መቀጠል የለበትም። ኢትዮጵያም የወንዝ ምንጭ እንደሆኑት እንደ ሌሎች ሀገሮች በአባይ ወንዝ በረከቷ፤ በውሀዋ፤ በነዳጇና በአፈሯ በስፋት እየተጠቀመች ልማቷን ማጣደፍና ማሳደግ መብቷ ነው። ይህም ሲባል ግን፤ የሌሎቹ ሐገሮች፤ ማለትም የሱዳንና የግብጽ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት አይኑር ማለት አይደለም። የዓለም-አቀፍ ሕግ መመሪያዎችን መሠረት ባደረገ ሚዛናዊ በሆነ የጋርዮሽ አጠቃቀም ሥልት ይከናወን ማለት ነው። ይህንንም ለማስገኘት በጥሞናና በመከባበር ለዘለቄታው ተቀባይነት በሚያስገኝ ዘዴ መደራደርና መዋዋል ያስፈልጋል ማለት ነው።
በወንዟ ሀብት የመጠቀም የለሶቶ (Lesotho) ተሞክሮ፤
በመግቢያው እንደ ገለጽኩት፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ለሶቶ (Lesotho) ሀገር እ.አ.አ በ1972-78 አገልግዬ ነበር። ለአራት አመቶች በፖስታ፤ ቴሌኮሙኒኬሽንና ሲቪል አቭዬሽን ዋና ዲሬክተርነት የሠራሁ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመቶች ደግሞ የሥራ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ በመሆን ሰርቻለሁ። የሥራ ሚኒስቴሩም የሚያጠቃልላቸው አገልግሎቶች የመንግሥት ሕንጻዎችና መንገዶች ግንባታዎችና ጥገናዎች፣ የውሀ ልማትና አቅርቦት፣ የኤሌክትሪሲቲ አገልግሎትና የትራንስፖርት አገልግሎት ነበሩ።**
ለሶቶ፤ ደቡብ አፍሪካ መሀል የምትገኝ አንድ ትንሽ ሀገር ናት። ትንሽ ብትሆንም እንደ ኢትዮጵያ የውሀ ሀብት በረከት ያላት ሀገር ናት። እኔ ለሶቶ በነበርኩበት ጊዜ የለሶቶ ወንዝ የሚፈሰው ለደቡብ አፍሪካ ለልማትና ሌላም ጥቅም እንጂ ወደምትፈልገው አቅጣጫ ስላልነበር፤ አስፈላጊው የማስተካከል ተግባር ተከናውኖ ሙሉ ተጠቃሚ እንድትሆን በለሶቶና በደቡብ አፍሪካ ድርድር ተጀምሮ ነበር። በዚህም ምክንያት በለሶቶው የሥራ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪነት ተግባሬ በድርድሩ ተካፍዬ ነበር። ከዚሁ በተለይ የማስታውሰው እ.አ.አ. በ1977 በኔ መሪነት ኬፕ ታውን (Cape Town) በመጓዝ የለሶቶ ባለሥልጣኖችና ከዓለም ባንክም ተወካይ የተገኘበት ልዑካን ከደቡብ አፍሪካ የሚመለከታቸው ባለሥልጣኖች ጋር ተደራድረን ነበር። የድርድሩ ጭብጥም ለሶቶ በውሀ ሀብቷ (ለኤሌትሪክ ኃይል ማፍለቂያ ጭምር) የመጠቀም መብቷ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ለደቡብ አፍሪካ ለሚፈሰው ውሀ ለሶቶ ተገቢው ክፍያ እንዲከናውንላት ለማድረግ ነበር።
ያ ሁሉ ድርድር ውጤቱ አምሮ፤ የለሶቶን ተራራ በመሸንቆር የወንዙን ፍሰት አቅጣጫ በማስለወጥ ለደቡብ አፍሪካ የሚያስፈልገው ውሀ በሚገባ እንዲቀርብ ለማድረግ ከቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሆነበት ሥራ ተጠናቆ ባሁኑ ጊዜ ለሶቶ በያመቱ በአማካኝ $50 ሚሊዮን በደቡብ አፍሪካ እየተከፈላት ነው። ለሶቶ ብሔራዊ መብቷንና ጥቅሟን ከላይ እንደ ተገለጸው ማስከበር ከቻለች ኢትዮጵያም ተመሳሳይ እድል እንዲገጥማት ብርቱ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ::
ማጠቃለያ፤
አባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ታላቅ የተፈጥሮ ሀብት ነው። ኢትዮጵያ የሱዳንንና የግብጽን ተገቢ መብት እያከበረች የራሷንም ጥቅም መጠበቅና ማስከበር ይኖርባታል። ለዚህም በወንዝ ውሀ አጠቃቀም መርሆ፤ ሥልትና እቅድ ባለሞያዎች በመታገዝ ዝርዝር ጥናቶች በማከናወን ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚከናወነው ድርድር የኢትዮጵያን የዘለቄታ ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ማረጋገጥና ስለ ሂደቱም ግልጽነትና ቁጥጥር የሰፈነበት እንዲሆን፤ የአባይ ወንዝ ዋናው ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሙሉ ግንዛቤ እንዲኖረውና ሙሉ መብቱ እንዲጠበቅ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ባሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን አመራር ሥልጣን ተረክበው የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ ክቡር ዶር/ አብይ አሕመድ ወደ ካርቱምና ካይሮ ተጉዘው ከአመራሮቹ ጋር ቅንነት የተላበሱ ውይይቶች ያከናወኑ በመሆኑ የአባይ ወንዝንም ብሔራዊ እሴትነት ጉዳይ አጥብቀው በመያዝ የኢትዮጵያ መብት እንዲከበር ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስዱ ይታመናል፡፡
ቸሩ አምላክ፤ ኢትዮጵያ በሕዝቧ ያልተቆጠበ ጥረት መብቷን፤ ክብሯንና ጥቅሟን እንድትጠብቅ ይርዳ!
*በዚህ አጋጣሚ አንድ የማልረሳው ነገር በተባበሩት የዓረብ ኤሚሬትስ እሠራ በነበረበት ጊዜ በዚያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) ባዘጋጀልን አንድ ስብሰባ አንድ ግብጻዊ የውሀ መሐንዲስ ጎኔ ተቀምጦ ስለ ነበር፤ በውይይታችን መሀል የአባይ ወንዝ ጉዳይ ተነሳና አብዛኛው ከኢትዮጵያ የሚመነጭ መሆኑን ሳስታውሰው፤ ወዲያውኑ የሚያስቆጭ መልስ ሰጠኝ፤ “አዎን፤ እኛ (ግብጽ) እንጠቀምበታለን።” “እኛም (ኢትዮጵያም)” የምልበት ጊዜ በሕይወት እያለሁ ይደርስ ይሆን?!
**በነገራችን ላይ፤ ስለዚህ ሥራዬና ስለ ሌሎችም አገልግሎቶቼና ጉዳዮች በቅርቡ በወጣው፤ “My Journey with the United Nations and Quest for the Horn of Africa’s Unity and Justice for Ethiopia” በተሰኘው መጽሐፌ በሰፊው ተገልጿል።