ከታሪክ ማኅደር: ዐድዋና አንድምታው (ኀይሌ ላሬቦ)

Haile Larebo 2
Dr Haile Larebo

ኀይሌ ላሬቦ

በየካቲት ኻያሦስት ቀን ሺስምንትመቶ ሰማንያስምንት ዓ. ም. ረፋዱ ላይ ዓለም ካንዲት ስሟ ካልታወቀ ኰሳሳ መንደር በፍጹም ያልተጠበቀ አስደናቂ ዜና ሰማ። ሰፈሯ ዐድዋ ትባላለች። ዜናውም  የዓለምን ታሪክ ሂደት የቀየረው፣ አዝማሚያና ቅርጽ የለወጠው በመንደሯ ተራራ ላይ የተፈጸመው ኢትዮጵያ በቅኝ ወራሪው ኢጣሊያን ላይ የተጐናፀፈችው አቻ የሌለው ድል ነበር። ከዚያን ቀን ጀምሮ፣ ዐድዋ በዓለም ታሪክ መዝገብ ለዘለዓለም በማይፋቅ የወርቅ ቀለም ስሟን አጽፋለች። ብዙዎች ከተሞችና መንደሮች ስማቸው በታሪክ ቢጠቀስም፣ እንደዐድዋ የጐላና አስደናቂ ሚና አልተጫወቱም። ይኸ ድል በተጠራ ቊጥር፣ የሚነሣው የዐድዋ ስም ብቻ ሳይሆን፣ የድሉ መሪዎች፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፣ የአገሩ ሰንደቅ ዓላማ፣ የሕዝቡም ቋንቋና ታሪክ ናቸው።

የዐድዋ ድል ዛሬ መቶኻያ ሰባተኛ ዓመቱን አስቈጥሯል። እንደታላቅነቱና ታሪክነቱ ከሆነ፣ ድሉ ያንድ ቀን ብቻ በዓል መሆን የለበትም። የየትኛውንም አገር ታሪክ ብንመረምር፣ መዛግብታቸውን ብንገለባብጥ፣ የዐድዋን ዐይነት ታሪክ የሠራ ሕዝብም አገርም የለምና። እንግዴህ ይኸንን ድል ከማንኛውም ልዩ የሚያደርገው ምን እንደሆነ እስኪ በዐጭሩ እንቃኝ።

መጀመርያ፣ ዐድዋን ከአገር አኳያ ስንመለከተው፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ልዕልናዋንና ልዑላዊነቷን ለመላው ዓለም በማያፋልም ሁናቴ ያስመሰከረችበት ነው። ከዐድዋ በፊት የተለያዩ ቄሣራውያን አገሯን ሊቦጫጭቋትና ሊቈራርሷት ሲሉ ለኻያ አምስት ዓመታት ያህል ሳያቋርጡ ወርሯታል። በልማት ሥራ እንዳትሰማራ ፋታ ከልክሏት ነበር። ግብጾች፣ ሱዳኖች፣ ኢጣሊያኖች፣ ይኸንን ልዕልናዋን በተከታታይ ጦርነቶች ፈታትነውታል። ሁላቸውም በልጆቿ ጠንካራ ጡንቻ ተመትተው ወደየመጡበት ቢመለሱም፣ ዘመኑ የነጮች የበላይነት ወቅት ስለነበር፣ ኢጣሊያኖች ከዕብሪታቸው የተነሣ፣ በጉልበታቸው፣ በብልሃታቸውና በመሣርያቸው ተማምነው፣ በዲፕሎማሲ ሊበገሩ፣ በልመና ሊታገቱ አልፈለጉም። የበላይነት ስሜቱ ዘመናት ያስቈጠረ፣  አውሮጳውያን አዲሱ አህጉር በተባለው በአሜሪቃ መስፈር እስከጀመሩበት የዘለቀ ስለሆነ፣ ማንኛውንም አውሮጳዊ ያልሆነውን የሰው ዘር በቀላሉ እንደሚያሸንፉ በተደጋጋሚ አረጋግጠውታል። ከዚህ ጥብቅ እምነት በመነሣት ነው እንግዴህ፣ ጦርነቱን በብልሃትና በጀግንነት እንዲመራ የተላከው አዲሱ የጦር መኰንንና የኤርትራ ገዢ የነበረው ጀኔራሉ ባራቲየሪ ወደኢጣልያን አገር ተመልሶ በሄደ ጊዜ፣ “የኢትዮጵያን ጦር በአጭር ጊዜ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ምኒልክን ራሱን በቀፎ ውስጥ ይዤው አመጣዋለሁ” እያለ፣ በየቦታው እየዞረ ሲፎክርና ሲደነፋ፣ ሕዝቡም አምኖት በየደረሰበት በእልልታ፣ በሆሆታ፣ በዘፈንና በጭብጨባ እየተቀባበለ ሲያጅበውና ሲሸኘው የሰነበተው። ሐቁ ግን እሱ እንደሰበከው ስብከት፣ እንደነዛው ጒራ አልሆነም። ይልቅስ የጓዶቹ የነአልበርቶኔና ዳቦርሚዳ የመሳሰሉት ጄኔራሎች ሕይወታቸው በጦር ሜዳ የሰማይ አሞራና የዱር አውሬ ሲሳይ ሁኖ ሲቀር፣ እሱ ግን ያንን ሁሉ ጒራና ድንፋታ ረስቶ፣ እሾህና ጒድጓድ ሳይለይ፣ እግሬ አውጭኝ እያለ ወታደሩን ጥሎ በመሸሽ አመለጠ። ለኢጣልያን ሕዝብ “ምኒልክን በቀፎ ውስጥ ይዤላችሁ እመጣለሁ” ብሎ ቃል የገባው ታላቁ የጦር መኰንን፣ ብዙም ሳይቈይ ከሥልጣኑ ተሽሮ፣ ወዳገሩ ተጠርቶ እግሩ መሬቱን እንደረገጠ፣ የጠበቀው ክስና ፍርድ ቤት ነበር።

እውነቱን ለመናገር፣ የአውሮጳውያንን ጦር ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ብቻ አልነበረችም። በ፲፰፻፳፫ ዓ.ም. አሁን የጋና መንግሥት አካል የሆነው አሻንቴ በመባል ይታወቅ የነበረው አገር፡ ዓለምን ከጫፍ እስከጫፍ ድረስ ከመቈጣጠሩ የተነሣ፣ “ፀሐይ የማይጠልቅበት መንግሥት” እየተባለ የሚነገርለትን የእንግሊዝን ጦር ደምሰሶ፣ የጦር መሪዎቹን ቸብቸቦ ለሰለባ ዳርጓል።  እንዲሁም በጥር ፲፰፻፸፰ ዓ.ም. የዙሉ ንጉሥ ሴትዋዮ፣ እንደገና የእንግሊዝን ወራሪ ጦር በእስንድህልዋና ጦርነት ድል አድርጎ፣ ለወሬ እንኳን የሚሆን ሳያስቀር ድምጥማጡን አጥፍቶታል። ሁኖም ብዙም ጊዜ ሳይቈይ፣ ባላንጣቸው በደምብ ተደራጅቶ ተመልሶ ሲወጋቸው፣ አሸናፊዎቹ የተቀዳጁት አኩሪው ድል ከንቱ ሁኖ ቀርቷል። በአንጻሩ የዐድዋ ድል ከመጀመርያውኑ የለየለት ነበር። የኢጣሊያን ጦር ተመልሶ መቋቋም በማይችልበት ሁናቴ ተመቷል። ጦርነቱን የቀሰቀሰው የአገሩ መሪ አቶ ፍራንቼስኮ ክሪስፒም ከሥልጣኑ ተወግዷል። የአገሩም ሕዝብ ዐምጾ “ምኒልክ ለዘላለም ይኑር፤ ክርስፒ ግደል ይግባ።” እያለ የከተሞቹን መንገዶች በጩኸቱ አጥለቀልቋቸዋል። የዐድዋ ድል “አውሮጳውያን በዕውቀት አቻ የሌላቸው፣ በትምህርት የተራቀቁ፣ በሀብት የበለጸጉ በመሆናቸው በጥቁርና በብጫ ሕዝብ በፍጹም ሊሸነፉ አይችሉም” የሚለውን ዘመናት ያስቈጠረውን እምነትና አስተሳሰብ ውድቅ ለማድረግ በቅቷል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ የዐድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን የማንነታቸው መግለጫ ሲሆን፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ከመላው አፍሪቃም ሆነ ከሌላው  ዓለም የምትለየው፣ ሕዝቧም ከየትኛውም አገር ነዋሪ በሚጻረር መልኩ ባህሉን ጠብቆና ኰርቶ፣ አንገቱን አቅንቶ፣ ደረቱን ነፍቶ፣ ትከሻውን ደርበብ፤ ሰውነቱን ሰፋ አድርጎ የሚሄደው፣ ጉንጩን ሞልቶና ነፍቶ የሚናገረው፣ ጀግኖች  አባቶቹና እናቶቹ በዐድዋ ባጎናፀፉት ድል ምክንያት እንደሆነ የማይካድ ሐቅ ነው። አለበለዚያ ስማቸው “ቀጀላ መርዳሳ” መሆኑ ቀርቶ “ሮቤርቶ በቪላኳ” በሆነ፣ እኅቶቻቸውና እናቶቻቸውም በ “ጽጌ”ና “ወለተ” ፋንታ “ማርያ”ና “ጆቫና” እየተባሉ በተጠሩ። ዋናው ምግባቸው የሆነው ክትፎ፣ ዶሮ ወጥና እንጀራ፣ በ”አሮስቶ”ና “ፓስታ” በተተኩ፤ ፊደላቸው የላቲን፣ ልብሳቸውም እንደዚሁ የተውሶ ሁኖ በቀረ።

ሌላው ብዙ ጊዜ የማይነሣ ጉዳይ ቢኖር፣ ብሔራዊ ቋንቋን በተመለከተ ሲሆን፣ ይኸም ግልጽ የሚሆነው ጦርነቱ የተቀሰቀሰው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋና ፊደል የተጻፈው ስምምነት ዋጋቢስ ሁኖ፣ የተተረጐመበት የአውሮጳዊው ፊደልና ቋንቋ እንደአስተማማኝና ሐቀኛ ሰነድ ሁኖ በመወሰዱ ነው። በዚህ የቅጥፈት ትርጒም ሰለባ በመሆን ኢትዮጵያ ብቸኛ አይደለችም። የዛሬይቷ ዚምባብዌ በእንግሊዝ እጅ ልትወድቅ የበቃችው፣ አባ ሄልም የተባለው ሚሲዮናዊ ቄስ፣ የአገሩ ገዢ ንጉሥ ሎበንጉላ ከማዕድን አዳኙ አቶ ሴሲል ሮድስ ጋር የገባውን ስምምነት ሆን ብሎ በቅጥፈት አሳስቶ ስለተረጐመው ነው። ሎበንጉላ ለጽሕፈት የሚበቃ ቋንቋ ስላልነበረው በቀላሉ ሲታለል፣ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ግን የኢጣልንያኛው ትርጒም ስሕተት ስለሆነ በማስረዳት፣ “በአማርኛችን የተጻፈው ይከበር፤” አለበለዚያም ከሱ ጋር ይስተካከል በማለት አውሮጳዊ ስለሆነ ብቻ በአገራቸው ቋንቋ ምንም ዐይነት የበላይነት እንደሌለው አስታወቁ። የኢጣሊያን መንግሥት ወኪል የነበረው አንቶኔሊ በበኩሉ፣ እቴጌ ጣይቱን አማርኛውን ትተው፣ በኢጣሊያንኛ የተጻፈውን ውል ይመልከቱ ቢላቸው፣ ኀይለኛዋ ንግሥቲቷም፣ “እኛ እምናውቀው በቋንቋችን በአማርኛ የተጻፈውን ነው እንጂ የፈረንጅ ቋንቋ አናውቅም። አንተ ግን ቋንቋችንን ስለምታውቅ እየው” ቢለው ቢመልሱለት፣ አንቶኔሊ የውሉን ወረቀት ቀዶ ሲያበቃ፣ “የኢጣሊያ መንግሥት ውሉን በጦር ኀይል ታስከብራለች” በማለት ስሕተቱን የኢጣሊያንኛውን የበላይነት በጉልበት ለማጽደቅ መረጠ። ዐድዋ ለኢትዮጵያውያን አማርኛ ቋንቋቸውና የተጻፈበት ፊደላቸው፣ እንደቈዳ ቀለማቸው ከሌላው እኩልና የከበረ መሆኑን በጀግኖቹ ደምና ዐጥንት አስመሰከረ።

የዐድዋ ድል፣ በጦርነት ስልቱም ሆነ ጦሩ ከጠላት ለተማረኩት ባሳየው ሰብኣዊነትና እንክብካቤ፣ ኢትዮጵያ በተግባረእድ (ቴክኖሎጂ) ወደኋላ የቀረች አገር ብትሆንም፣ በሌላው ግን ከሠለጠነው ዓለም በምንም እንደማታንስ አረጋገጠ። ከድሉ በፊት በንቀትና በትዕቢት እንደአገር ሊያዩዋት እንኳን ዝግጁ ያልነበሩ የአውሮጳ ታላላቅ መንግሥታት፣ አላንዳች ኀፍረት ወደመናገሻ ከተማዋ ለመድረስ መሽቀዳደም ጀመሩ። አገሪቷ በልማት ሥራ እንዳትሰማራ ዕንቅፋት ሁነው የነበሩትም፣ ብሔራዊ ግንባታው ላንዱ አውሮጳዊ ተሰጥቶ እሱ ባዶ እጁን እንዳይቀር፣ ሌላው ቢቀር ትራፊ እንኳን እንዳያመልጥባቸው፣ በለማኞች ወኪሎቻቸው የአፄ ምኒልክን ግቢ አጥለቀለቁት።

ሌላው የዐድዋ ድል ትሩፋት፣ በቅርቡ ተመልሶ የተቋቋመው የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ነው፤ የተዋጋውና ለዚህ አስደናቂ ድል ያበቃው ይኸ ሕዝብ ስለሆነ። ስለዚህ ድሉ የሕዝቡ የአንድነቱና የውህደቱ መግለጫ፣ የማንነቱ ማረጋገጫ ሆነ። ሠራዊቱ ከሩቅም ከቅርብም፣ ከተለያየ ኅብረተ-ሰብ የመጣ ብቻ ሳይሆን፣ ከያንዳንዱ መንደር የተወጣጣ ጦር ነበር። በዚህ የመጀመርያው የአንድነቱ፣እንዲሁም የአገሩ ነፃነትና ልዕልና ፈታኝ ጦርነት ላይ ያልተሳተፈ አካባቢም ብሔረሰብም አልነበረም ማለት ይቻላል። ጐጥና ጐሣ፣ ቋንቋና ሃይማኖት፣ ጨዋና ባለጌ፣ ዕድሜና ፆታ ሳይለይ፣ ወንድና ሴት፣ ወጣቱና ጐልማሳው፣ ተራውና መኰንኑ፣ ባለዳባውና ባለካባው በልዩነቱ ሳይገደብ፣ ከያንዳንዱ ማዕዘን ማለትም ከሰሜኑና ደቡቡ፣ ከምሥራቁና ምዕራቡ፣ ከመስዑና አዜቡ፣ ከባሕሩና ሊባው፣ ሁሉም ከየመጣበት ቀዬው በኢትዮጵያዊነቱ፣ በአገር ልጅነቱ ጐንና አቋም ብቻ ተሰልፎ ቁሞ፣ ደረቱን ለጦር፣ እግሩን ለጠጠር በመስጠት፣ በዠግንነት ተዋግቶ አጥንቱን በመከስከስ፣ ደሙን በማፍሰስ፣ ኅብረቱንና አንድነቱን፣ ወንድማማችነቱንና ቤተሰብነቱን ያጸደቀበት ድል ነው። አንድ መድፈኛ የኢጣሊያን ጋዜጠኛ በማጋነን መልክም ቢሆን የተዋጊውን ጦር ኅብረትና ትብብር ሲገልጥ፣ “ሕዝቡ ከሁሉም ብሔረሰብ የተወጣጣ ነው። ይዋጋ የነበረው ፈረሱም፣ በቅሎውም፣ አህያውም ባንድነት ከሰው ጋር ሁነው ነው። በጦርነት የገጠመን መደበኛ ጦር አልነበረም። ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ቄሶችና ቈማጣዎችም ሳይቀሩ ይዋጉን ነበርና።” ይላል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ በተወለደችበት ማግስት፣ አንድነቱን በደሙ ጥምቀት አጽንቶታል ማለት ይቻላል። ለሚወዱት አገርና ሕዝብ የራስን ሕይወት አሳልፎ ከመስጠት የበለጠ ነገር የለም ብቻ ሳይሆን ማድረግም አይቻልም።

በጾታና በአገር ደረጃ ካየነው፣ በዐድዋ ጉልህ ሁኖ የሚታየው የሴቶች ሚና ታላቂነት፣ የአንድ አካባቢና ጐሣ ፋይዳቢስነትና ደካማነት፣ የመላው አገር  ሕዝብ ጥንካሬና ወሳኝነት ነው። ይኸንንም ለመገንዘብ ሁለት ምሳሌዎችን ላንሣ። አካባቢንና ብሔረሰብን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያውያን በመጀመርያ ላይ በጦር ሜዳ የገጠሙት የትግራዩን ገዢ፣ ራስ መንገሻን በኰዓቲት፣ በሰንዓፈና በደብረ-ሐይላ በተባሉ ሰፈሮች በተደረጉት ጦርነቶች ሦስቴ አከታትሎ  ያሸነፈውን የኢጣሊያን ጦር ነው። በዘመኑ የትግራይ ጦር በመሣርያም ሆነ በጦርነት ልምድ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሻለ እንደሆነ ይነገርለት የነበረ መሆኑን ማስመር ይገባል። ይኸንን ጦር ኢጣሊያኖች በጥቂት ጊዜ ውስጥ ስላሸነፉ ከፍተኛ ዕብሪት፣ ታላቅ ኩራትና በራስ መተማመን ቢሰማቸው በጣምም አይገርምም። ከዚህም የተነሣ ነው እንግዴህ ጄኔራል ባራቴርም ሆነ፣ ራስ መንገሻን ድል ያደረገው ኮሎኔል ቶሴሊ፣  መላውን የኢትዮጵያን ጦር በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ዐመድ አድርገነው ባንዴ እመዳፋችን ውስጥ እናስገባለን በማለት የኢትዮጵያን ጦር ያጣጥሉ የነበሩት።

ይሁንና ኢትዮጵያውያን ኢጣልያንን ድል ያደረጉት አንዴና ሁለቴ ብቻ ሳይሆን አከታትለው በሦስት በተለያዩ የጦርነት ዐውድማዎች ነው። መጀመርያ ራስ መንገሻን ያሸነፈው ቶሴሊ፣ በአምባ አላጌ ላይ ሁኖ፣ የሰሜኑን ሕዝብና ባላባቶቻቸውን ካፄ ምኒልክ ጭቈና ነፃ አወጣለሁ ብሎ ሊያሳምፅ ተራራውን ይዞ ነበር። ሕልሙ አልተሳካም ብቻ ሳይሆን፣ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ጦሩ ተደምስሶ ወሬ ነጋሪ ሳይቀር ዐለቀ። ጨቋኙ ጣሊያን እንጂ ምኒልክ እንዳልሆነ ሊያስተምሩት ደግሞ፣ እርሱን ራሱን ነፍሴ አውጭኝ ብሎ ሲሸሽ የአገሩ ሕዝብ አሳድዶት ይዞት ለሞት አበቃው። የትግራይን ጦር የደመሰሰው፣ ጠንካራውና አይበገረው የኢጣሊያን ሠራዊት፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጦር በጥቂት ሰዓት ውስጥ ኢምንት ሁኖ ቀረ። ይኸ ድል የኢትዮጵያውያኖችን መንፈስ አጠናከረ፤ ወኔአቸውን ይበልጥ ቀሰቀሰ።

ቀጥሎ የመጣው የመቀሌው ጦርነት፣ የሴቶችን ሚና ምን ያህል ወሳኝ እንደነበረ በጉልህ ይመሰክርልናል። ኢጣሊያኖች፣ የአምባላጌ ዐይነት ውድቀት እንዳይገጥመን ብለው፣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የማይደፈር፣ ጠንካራ ዕርድ በመቀሌ ሠርተው ጠበቁ። የምሽጉ መግቢያ ዙርያውን የጠርሙስ ስብርባሪ ተነሰንሶበታል፤ ከዚያም በማከታተል ወፍ እንኳን የማያሳልፉ ሹል ዕንጨቶችና ድቡልቡል የእሾኽ ሽቦ አጥር ተተክለውበታል፤ ቀጥሎ ደግሞ የሦስት ሜትር ስፋት ያለው ካብ ተገንብቶበታል። የኢትዮጵያ ጦር የሚዋጋ አለጫማ በሌጣ እግሩ ቢሆንም፣ጋሻውን እያነጠፈ የጠርሙሱን ስብርባሪ ዐለፈ። ግን ወደዕንጨቶቹና ወደእሾኻማ የሽቦ አጥሩ ሲደርስ፣ አብዛኛው በነዚሁ እየተዘነጠለ፣ ከነሱም ያመለጠው የኢጣሊያን መትረየስ እየተርከፈከፈበት፣ እንደወፍ ሬሳ በሹል ዕንጨትና፣ (ያን ዐልፎት የሄደ ደግሞ) በድቡልቡሉ የእሾህ ሽቦ እየተንጠለጠለ ቀረ። የመቀሌ ምሽግ በሰው ብዛት፣ በወንዶች ጀግንነት፣ ባገር ወኔ፣ በመሣርያ ጥቃት የማይፈታ ሁኖ ተገኘ። የኢትዮጵያን ጦር እየለቃቀመ በጭካኔ በላው፤ ወሽመጥ ቈራጭ፣ ወኔ አቅላጭ ሆነ። ኢጣሊያኖችም በምንም መልክ የማይሸነፉ መሰላቸውና ከፍተኛ እብሪት ተሰማቸው።

ባለቀው ጀግና ብዛት በሐዘን ተውጠው የነበሩት የኢትዮጵያ ፀሐይ በመባል የሚታወቁት እቴጌ ጣይቱ፣ የወንዶቹን ጀግንነት በሴቶች ብልሃት ባይተኩ ኖሮ፣ ወደዐድዋ መጓዙ ሕልም ሆኖ ሊቀርም በቻለ። ይሁንና እሳቸው ለሞተ ተዝካሩን ለማውጣት፣ ልጁን ለማሳደግ፣ ለቀረ ደግሞ ለመሸለም ቃል ገብተው፣ ኢጣልያኖች ለውሃቸው የሚጠቀሙትን ምንጭ፣በራሳቸው አምስትሺ ጦር ካስያዙ በኋላ ነው፣ ኢትዮጵያኖች ከከፋ ዕልቂትና ከመንፈስ ውድቀት ድነው ወደዐድዋ የተጓዙት።

እቴጌም ለውሃ ጠባቂዎቹ፣

“ጠጅ በብዙ ቀንድ እየተሞላ፣ በማለፊያ ወጥ እንጀራ እየተፈተፈተ በመሶብ ሁኖ፣ ፍሪዳው ታርዶ ሥጋው በእንቅብ እየሆነ ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት ይሰዱላቸው ነበር። ትጥቃቸውን ሳይፈቱ፣ እንቅልፍ ሳይተኙ፣ ለአንድ ቀን የሚያስመርረውን ጦርነት ዐሥራ-ዐምስት ቀን ሙሉ ሌትና ቀን እየተዋጉ፣ ውሃውን ከልክለው፣ በጭንቅ ኢጣሊያኑን ከዕርዱ እንዲወጣ አደረጉት።”

ኢጣሊያኖቹ ከውሃ ጋር ሲጨነቁ፣ ራስ መኰንን ዕድሉን ተጠቅመው ሽቦውን ቈረጡ። ከራስ አሉላም ጋር ከካቡ ሁነው ሠራዊታቸውን ቈሉት። ያ የተማመኑበት ምሽግ ዋጋ-ቢስ ሆነና ኢጣሊያኖች እጅ ከመስጠት ሌላ ምርጫ እንደሌላቸው ሲረዱ ሁሉም ተማረኩ። እንዲህ ሁኖ በሴቶቹ ጥበብ የተጠናቀቀው የመቀሌ ድል ወደዐድዋው መራ። በዚህ ጦርነት ከዐሥር ሺ እስከዐሥራሁለት ሺ ሴቶች በተለያየ ሙያ፣ ሠራዊቱን በማበረታታት፣ ፈርቶ የሚፈረጥጠውን በማሳፈር፣ ምግብና ውሃ በማቅረብ፣ በማከም በሌሎችም እነኚህን በመሳሰሉት መስኮች ተሰማርተው ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ እንረዳለን።

በመጨረሻም፣ በማንኛውም ጦር ወሳኙ መሪ መሆኑን ታሪክ በተደጋጋሚ ይመሰክራል። ታላቁ እስክንድር፣ በአስደናቂ ድል የወቅቱን መንግሥታት አሸንፎ እንደሞተ፣ የጦሩ ኀይል በጥንካሬው እንዳለ ሁኖ ቢቀርም፣ ብዙም ሳይቈይ ብትንትኑ ወጣ። የአፄ ዮሐንስ አራተኛ ሠራዊት በመተማ በደርቡሾች ላይ ድል ተጐናፅፎ እያለ፣ ንጉሡ ነገሥቱን በማጣቱ እግሬ አውጭኝ ብሎ ሲሸሽ፣ አብዛኛው በተሸነፈው የጠላት መልሶ ጥቃት ማለቅ ብቻ ሳይሆን፣ የጌታቸውን ሬሳ ለተፋላሚው አስረክቦ ለመሸሽ ተገደደ። እንደዛሬ ዘመናዊ መሣርያ ባልዳበረበት ዘመን፣ ሁሌም ባይሆን አብዛኛውን ጊዜ የጦርነቱን ውጤት ወሳኝ መሪው ነው ቢባል ስሕተት አይደለም።

ዛሬ ለመተቸት አፋቸውን ከማሽሞጥሞጥ ውጭ ምንም ዐይነት ፋይዳ ያለ ሥራ ያልሠሩ ጽንፈኞችና፣ የብሔረሰባችን ነፃ አውጪዎች ነን በማለት ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙት ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ አፄ ምኒልክ በዐድዋ በመሪነት የተጫወቱትን ሚና ማንኳሰስና ማብጠልጠል ሙያቸውና መለዮአቸው አድርገውታል። ይሁንና እነሱ ዕውቅና ሰጡም አልሰጡም፣ ንጉሠነገሥቱ ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፂዖ መላ ዓለም ያወቀው፣ እንደጠራራ ፀሓይ ግልጥ ስለሆነ፣ በድርጊታቸው የሚጨምሩትም የሚቀንሱትም ነገር የለም። ይልቅስ ጅልነታቸውንና አክራሪነታቸውን አጉልቶ ከማጋለጥ ውጭ፣ የንጉሥነገሥቱን ሥራ ለመፍረድ ብቃትም ችሎታም፣ ዕውቀትም ያላቸው አይደሉም።

የዐድዋ ጦር ባፄ ምኒልክ ባይመራ ኖሮ፣ የኢትይጵያ ዕጣ ከሌሉቹ የአፍሪቃ አገሮች ባልተለየም ነበር ማለት ይቻላል። ካፄ ምኒልክ በፊት አፄ ዮሐንስ፣ ከሳቸውም ቀጥሎ ልጃቸው ራስ መንገሻ በየጊዜአቸው ጣሊያንን ተጋፍጠውታል። አፄ ዮሐንስ ኢጣልያኖች ስማቸው ብቻ ሲጠራ እንኳን የሚያበረግጓቸውና የሚያንቀጠቅጧቸው ራስ አሉላን የመሰሉ ታማኝ የጦር መኰንን ቢኖሯቸውም፣ በብልሃት፣ ዐሪቆና አራቅቆ በማየት እንደአፄ ምኒልክ አልታደሉም። እውነት ነው ጀግንነታቸውም ሆነ አገር-ወዳድነታቸው፣ እንዲሁም ሃይማኖተኝነታቸው በፍጹም የሚያጠያይቅ አይደለም። አፄ ዮሐንስን በቅርቡ ያውቃቸው የነበረው እንግሊዛዊው አውጉስቱስ ብላንዲ ዋይልድ ለምሳሌ፣ አፄ ምኒልክን በጣም የሚደነቅ ራዕይ ብቻ ሳይሆን፣ ዐሪቆና ሰፋ-አድርጎ የማሰብ ችሎታ አላቸው ብሎ ሲያሟግሳቸው፣ አፄ ዮሐንስን ግን ከሳቸው ሲነጻጸሩ “እንደልጅ ናቸው” ብሎ ያጣጥላቸዋል። የጽሑፌ ዓላማ አፄ ዮሐንስ ባለመሆናቸው፣ ንጉሠነገሥቱ በተግባርም ያስመሰከሩት በትክክል የአቶ ዋይልድን ግምገማ ነው በማለት ስለርሳቸው ያለኝን አስተያየት በዚሁ ልቋጭ።

በዐድዋ ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያ እንደአፄ ምኒልክ መሪ በማግኘቷ በጣም ዕድለኛ ናት ያሰኛል። በዚህ አንጻር ስናይ፣

“ምኒልክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ፣

ግብሩ ዕንቊላል ነበር ይኸን ጊዜ አበሻ።”

የሚለው አነጋገር ዝምብሎ እንዳልሆነ አያጠራጥርም።

አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ዘመናዊ አንድነቷን ባደላደሉ በሰባት ዓመት ውስጥ ነው እንግዴህ፣ ሕዝቡን በአስገራሚና ሊታመን በማይቻል መንገድ ተባብሮ ባንድነት እንዲዋጋና ድል እንዲቀዳጅ ያበቁት። ሠራዊቱ የተዋጋው ላገሩ ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ በአፄ ምኒልክም ፍቅር ተነሽጦ ነበር ማለት ይቻላል። ንጉሠነገሥቱ ባስተላለፉት የክተት ዐዋጅ፣

ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ደግሞ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ርዳኝ።”

ሲሉ ሕዝባቸው የአስተዳደራቸውን ቅንነትና ጥሩነት ዐይቶ፣ ለርሳቸውም ሆነ፣ ከልብ ለሚንሰፈሰፍላቸው ብርቅ ነገሮች፣ ማለትም ለአገር፣ ለሃይማኖት፣ ለልጅና ለሚስት ፍቅር ሲል፣ እስከጦር ሜዳ እንዲከተላቸውና ሕይወቱን እስከመስጠት እንዲዋጋላቸው ነው የተማጠኑት። አስቀድመው እንደተማመኑበት ሕዝባቸውም በተግባሩ አላሳፈራቸውም።

እስኪ ያለፈውን፣ በጭካኔው የታወቀውን፣ የደርግን መንግሥት በጐን እንተወውና፣ “ሕዝብን እወክላለሁ፣ በሕዝብ ተመርጫለሁ” እያለ፣ በየጊዜው የሚለፈልፈው ያሁኑ መንግሥት፣ ደፍሮ “ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም።” ሊል ይችላል ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። በብዙዎች ግምትና እምነት በፍጹም የሚታሰብ አይመስልም። ቢልም ካይነ-ዐውጣነትና ከትዝብት በስተቀር ሌላ ትርፍ ሊኖረው አይችልም።

አፄ ምኒልክ ግን በጥበብና በፍቅር እንደሚያስተዳድሩ፣ ሕዝቡም በጥብቅ እንደሚወዳቸው፣ ሌላው ቀርቶ ጠላቶቻቸው በመሆናቸው ስለርሳቸው ጥሩነት አይናገሩም ተብለው የሚታሙት አውሮጳውያን እንኳን ሳይቀሩ፣ በአድናቆትና በሙገሳ ደጋግመው ይመሰክራሉ።

ንጉሠ-ነገሥቱ ደግ ብቻ አይደሉም፣ ብልጥም ነበሩ። እሳቸውም መኳንቶቻቸውም የዐድዋን ድል ሊቀዳጁ የቻሉት፣ ፈረንጆች በተንኰልና በሽንገላ ቢመጡባቸው፣ ተንኰልን በተንኰል፣ ጦርነትን በጦርነት ዐጸፋውን በመመለስ ነበር። የወቅቱ የለንዶኑ ዘታይምስ የተባለው ጋዜጣ፣ “ኢጣሊያኖች ንጉሡን ያሳመኑ መስሏቸው ሲታለሉ፣ እርሱ ግን በመሣርያ እየተዘጋጀ ቈይቶ፣ ዐጸፋውን ሰጣቸው” ሲል፣ የንጉሠ-ነገሥቱ ሥራቸው በዘዴና በዐሪቆ አሳቢነት የተመራ ነበር የሚለውን አስተያየት ያጠናክራል። ጣሊያኖችም ሲጽፉ፣ “ምኒልክ ከቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ነገሥታት የሚለየው ነገር ቢኖር፣ ሁካታ ባለበት በድል ሰዓትም ቢሆን፣ በተሸናፊዎቹ ላይ አይጨክንም ብቻ ሳይሆን የምሕረት እጁንም ለጠላቱ መዘርጋቱ ነው” ብለው ጽፈዋል። እንግዴህ ንጉሡ እንደልበ-ሰፊ መሪ ተብለው የሚደነቁት በወዳጆቻቸው ዘንድ ብቻ አይደሉም፤ በጠላቶቻቸውም ጭምር እንጂ። በዐድዋ ያሳለጡት ድል ትሩፋትም ከኢትዮጵያ ተንዘግዝጎ ጩራውን በመፈንጠቅ  በቀረው ዓለም ለማንቦግቦግ በቅቷል። ተወደደም ተጠላም ሐቁ ይኸ ነው።

ስለዚህ የዐድዋ ድል ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ብቻ አይመለከትም። ለሌላውም ዓለም ተርፏል። በዚያን ዘመን ጨቋኝ ለነበረው ለነጩ ዘርም ሆነ፣ ለተጨቋኙ ያለም ሕዝብ የነፃነት ፋና ነበር። ድሉን ተከትሎ፣ ጥቁር ሕዝብ በያለበት ሁሉ “ኢትዮጵያዊነት”ና “አኃዜኲሉ አፍሪቃ” (ፓናፍሪካኒስም)  ለተባሉ፣ ጠንካራ የሃይማኖትና የፖሊቲካ እንቅስቃሴዎች መነሻ፣ መቀስቀሻ፣ መነቃቂያ ሁኖ አገልግሏል። ለነጩ ከኢሰብኣዊነቱ ጭካኔ የሚላቀቅበት፣ ነጭ ላልሆነው ደግሞ ከሚማቅቅበት ከምዕራባውያን የባርነት ቀንበር ነፃ የሚወጣበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ያበሠረ ድል ነው። የድሉ ወሬ እንደደረሰው ዘታይምስ ጋዜጣ ይኸንን በማያወዛግብ ሁኔታ ጥርት አድርጎ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል።

“ኢጣልያኖች በጀብድነትም ሆነ በጦር ስልት ከሌሎቹ አውሮጳውያን በምንም መልክ አያንሱም። .. ድሉ የመላ [ጥቊር] አፍሪቃ ድል መሆኑ አይካድም። ይኸም አስተያየት ወደፊት እያየለ ሄዶ በግልጽ የሚታይ ነው። ወሬው በነፋስ ክንፍ በረኻውን አቋርጦ እየበረረ በመጓዝ በነዚህ አገሮች ከጫፍ እስከጫፍ ተዛምቶ ሲያበቃ፣ አፍሪቃውያን አውሮጳውያንን ማሸነፋቸው አይቀርም የሚለውን ስሜት አነቃቅቷል። ነገሩ አስጊ በመሆኑ በኢጣልያኖች መሸነፍ መደሰት [ለነጮች] ተገቢ አይደለም። ሽንፈቱ የሁላችንና የሌሎችም ጭምር ሽንፈት ነው። ዛሬ ቅኝ ገዢ የሆነችውና የመላዋ የነገዪቷ አውሮጳ ሽንፈት ነው።”

ዘታይምስም ሆነ፣ በዘመኑ በጋዜጤኝነት ሙያው ዝናን ያፈራው ሞርቶን እስታንለይን የመሳሰሉ ጸሓፊዎች፣ ኢጣሊያ በጥቁር ሕዝብ ተሸንፋ ራሷ ኀፍረትን ተከናንባ፣ ነጭንም ዘር አዋርዳ መቅረት የለባትምና፣ በርካታ ጦር ልካ፣ የጦርነት ስልቷን አሻሽላ፣ እንደገና ቶሎ ብላ ተመልሳ እንድትዋጋ እያበረታቱ ነበር የጻፉትና፣ ጩኸታቸውንም ያስተጋቡት። ግን ሁሉም ከንቱ ሆነባቸው። ከላይ እንዳየነው ሽንፈት ዕጣዋ የሆነባት ኢጣልያን እንኳን ተመልሳ ተደራጅታ ባዲስ ኀይልና ብልሃት ልትዋጋ ይቅርና፣ ጦርነቱን ያስጀመረው መንግሥት ራሱ ከሥልጣኑ ወድቆ ከሥራው መባረር ጽዋው ሆኖ ቀርቷል።

በአሜሪቃ ግዩራን (ዳያስፖራ) ዘንድ የተመሠረተው የ“ኢትዮጵያዊነት”ና የአኃዜኲሉ አፍሪቃ (ፓናፍሪካኒስም) እንቅስቃሴዎች ዓላማቸው የተበታተነችውን አፍሪቃን አንድ በማድረግ፣ የአውሮጳን ቅኝግዛትንና የነጭ የበላይነትን ለማስወገድ ሲሆን፣ ከላይ እንዳልሁት ስሜቱና አስተሳሰቡ ራሱ የፈለቀውና የተነቃቃው የዐድዋ ድል በአፍሪቃ ብቸኛ ልዑል አገር ካደረጋት፣ ከአውሮጳ የፖለቲካ ተገዢነት ነፃ ሁና፣ የራሷን ባህል ጠብቃ ከኖረችው ኢትዮጵያ ነው። ለነሱም  ወደፊት እንድትፈጠርና እንድትወለድ ለሚፈልጓት አፍሪቃ ኢትዮጵያ በአእምሯቸው ውስጥ ፅንስና ንድፍ ሁና አገልግላለች። ስለዚህም የአብዛኞቹ ሰንደቅ ዓላማቸው ኢትዮጵያን በዐድዋ ድል ያጐናፀፈውን፣ ከምዕራቡ ዓለም የበላይነት ነፃ መሆኗን ያረጋገጠውን፣  የኢትዮጵያን ባለሦስት ቀለማት ማለትም አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ ቀለማት የራሳቸው አድርገውታል።

በመጨረሻም፣ ዐድዋ በምዕራባውያን ዘንድ ለዘመናት እንደማያፋልም እምነት ሁኖ የቈየውን፣ “ኀይል መብት ነው።” የሚለውን ዘይቤ አኰላሽቶ፣ የሰው ልጅ በዘር፣ በቀለም፣ በእምነት፣ በብሔርና በጾታ እንዲሁም በዕውቀት ደረጃ የተለያየ ቢሆንም፣ በሰብኣዊነቱ ግን እኩል መሆኑን አስተምሯል። ኢትዮጵያውያንም ለሕይወታቸው ሳይሣሡ፣ ጀግንነታቸውን ለዓለም ያስመሰከሩት፣ ይኸንን መብት ለማስከበርና ለማረጋገጥ ሲሉ ነው።

እንግዴህ በዓሉ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይወሰን፣ ቢቻል በመላው ዓለም፣ ካልሆነም በአፍሪቃ አህጉር ደረጃ እንዲከበር ቢጣር ተገቢ ነው። ይኸንን ግብ ለመምታት ግን ኢትዮጵያውያን አስቀድመው ቤታቸውን ማጥራት፣ የዐድዋ ድል ያመጣላቸውን ክብር፣ እንዲሁም የአንድነታቸውን መለዮችንና መታወቂያዎችን፣ አሁን ካሉበት አሳዛኝ ሁናቴና ደረጃ አንሥተው  ማሳደስና ከፍከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop