ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ክብር ብለው “ጣሊያንን ተቀበሉ ብዬ አልሰብክም፣ እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ ምድሪቷም ጣሊያንን እንዳትቀበል አውግዣለው” በማለታቸው በፋሺስት ኢጣሊያ በግፍ በጥይት ተደብድበው የተገደሉበት ዕለት ነው።
<< ሰምዓቱ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ >>
የአገር ጽናት፣ እምነትና ጥንካሬ በአንድ እርሳቸው ሕይወትና ሰማዕትነት ውስጥም ተጽፎ ይገኛል። የ20ኛው ዘመን ታላቅ ሰማዕት ናቸው ይሏቸዋል፤ አቡነ ጴጥሮስን። እድገታቸውና ልጅነታቸው እንዲሁም ወጣትነትና ጉልምስናቸው በሃይማኖት አጸድ የተከበበ ነው። በአብነት ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ዘልቀዋል። አልፈውም የቅኔ እና የመጻሕፍት መምህር ነበሩ። በመረጡት የምንኩስና ሕይወትም የጵጵስና ሹመት አግኝተዋል። በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሃያ ስምንተኛው ዓመት፤ ጣልያን ፋሽት ጦሩን አግተልትሎ ኢትዮጵያን የወረረበት ጊዜ ነው። አርባ ዓመታትን ቆይቶ በበቀል ጥማት የመጣው የጣልያን ጦር ሕዝቡን በግፍ ይገድል፣ ሕዝቡ የእኔ ያለውን ቅርስና ሀብት ያጠፋና ይዘርፍ ነበር።
በዚህ ጊዜ አርበኞች ከውስጥም ከውጭም መታገል ጀመሩ። ከእነዚህ ብርቱ የአገር አርበኞችም ጋር አንድ አባት አይጠፉም ነበር፤ አቡነ ጴጥሮስ። አርበኞችን እንደሚያበረቱና ከእነርሱም ጎን እንደቆሙ የሰማው የጣልያን ጦር በሥራቸው ደስተኛ አልሆነም። ኃይልና ጠብመንጃን ፈርቶ ሰጥ ለጥ ብሎ ሕዝቡ እንዲገዛና መንፈሱ እንዲዳከም እንጂ እንዲበረታ አይፈልጉምና ነው። አስቀድመውም አቡነ ጴጥሮስን ሊገድሏቸው ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ተሰሚነታቸውን አይተው ለራሳቸው ተመኟቸው፤ በጣለያን ጎን ቆመው ሕዝቡ እንዲታዘዝ እንዲያደርጉና በዛም ፋንታ ጥሩ ካሳ ምቹ ኑሮ እንደሚያገኙ ተነገራቸው።
አቡነ ጴጥሮስ ከጣልያን በላይ የራሳቸው ሰው ሆኖ በባንዳነት ጣልያንን የሚያገለግለው ሳያሳዝናቸው ይቀራል? እርሳቸውማ እንዲያ ባለ ነገር ውስጥ እንደማይገኙ ያውቁት ነበር። ከወገኔ ጋር ስለአገሬ እሞታለሁ እንጂ አይሆንም ብለው አሻፈረኝ ያሉትም ከዚህ የተነሳ ነው። በዚህም ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም በአደባባይ ሰማዕትነትን ተቀበሉ። ክስተቱን የተለያዩ ጸሐፍት በተለያየ አገላለጽ አስፍረውታል። ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን መጽሐፍ እና ስምዐ-ጽድቅ የተሰኘ ጋዜጣ እንዲሁም ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ ክስተቱን በተለያየ መንገድ ተርከውታል።
ከዚህ መካከል ‘ኮርየርዴላሴራ ‘(corriere della sera) የተባለው ጋዜጣ ወኪል እና የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረ ‘ፖጃሌ’ የተባለ ጋዜጠኛ የጻፈው እንዲህ ተጠቅሶ ይገኛል፤ «ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ። በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው ‘ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ አንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም’ ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት።
አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው ነበር። ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብጽ ከአዲስ አበባ ውጭ እንኳ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም መመሪያ አስተላላፈ። «ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ፣ መልካቸው ጠየም፣ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ፤ የጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ልብስ የለበሱ ሰው ወደችሎት ቀረቡ፤ አቡነ ጴጥሮስ። ለፍርድ የተሰየሙት ዳኞች ሦሰት ሲሆኑ፤ አቡነ ጴጥሮስ የቀረበባቸው ወንጀል ‘ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል’ የሚል ነበር። «ዳኛውም ‘ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?’ ሲል ጠየቃቸው። ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም በቆራጥነት የሚከተለውን መለሱ፤ ‘አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ።
እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ’ አሉ። «በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲመለከት ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ መልዕክት አስተላለፉ፤ ‘አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው እንጂ በጎ ለመሥራት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ። ስለውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ። ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን’ ብለው አወገዙ» አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነትን የመቀበላቸው ነገር መቅረቡን ሲያረጋግጡ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱስ ተሳለሙት፣ በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፣ የኪሳቸውን ሰዓት አውጥተው ከተመለከቱ በኋላ መልሰው ወደኪሳቸው አስገቡት…ያኔም ወታደሮቹ ጥይት አከታትለው በመተኮስ ገደሏቸው። እንደው በስጋ ሞት አይቀርምና ገደሏቸው አልን እንጂ አቡነ ጴጥሮስ የበለጠ በየሰው ልብ ያበቡትና ያበሩት ሕያው ሆነውም የቆዩት ከዛ በኋላ ነው።
ክብር ሀገራን ለነፃነት ላቆዩልን አርበኞች