February 15, 2023
22 mins read

ከታሪክ ማህደር: ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ እና የትምህርት ሚኒስትር

ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ

ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮችን ሾማ ማሰራት ከጀመረችበት ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ አሁን በቅርቡ እስከተሾሙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ድረስ 30 (ሰላሳ) በላይ በሚኒስትር ማእረግ ያሉ ሰዎች ሃገራችንን በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።

እ.ኤ.አ ከ 1907 እስከ 1910 የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው ካገለገሉት ከነጋድራስ ሃ/ጊዮርጊስ ወ/ሚካኤል የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሹመት አሃዱ ተብሎ ከተጀመረ በኋላ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ አስራ ስምንተኛው የኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር (አንዳንድ መረጃ ምንጮች ሃያ አንደኛው ሚኒስትር እንደሆነ ይናገራሉ) ተደርገው የተሾሙና ሃገራቸውን በቅንነት ለሶስት አመታት ያክል በሚኒስትርነት ማእረግ ያገለገሉ ጠንካራ ዲፕሎማትና ቆፍጣና ወታደር ናቸው።

ዶክተር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ተወልደው ያደጉት በያኔው ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ጎሬ በተባለች አነስተኛ ከተማ እንደሆነ የቅርብ ወዳጆቻቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ። የያኔው ወጣት ጎበዝ ተማሪ ጎሹ መደበኛ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በመግባት የህግ ትምህርቱን በከፍተኛ ነጥብ በማጠናቀቅ እንደተመረቀና እስከዛሬም ድረስ ሰቅሎ ያስመዘገበው ነጥብ እስካሁን እንዳልወረደም ይወራለታል። ጎሹ ከዚህ አስከትሎ ያመራው ወደያኔው ስመገናና የሃረር ጦር አካዳሚ ገባ። ከዚያም በመኮንንነት ተመርቆ እንደወጣ በንጉሰ ነገስቱ አስተዳደር ውስጥ በተለያየ ቦታ እንዳገለገለ በሙያውና በስነ ምግባሩም እጅግ የተመሰገነ ሰው እንደነበር አብረው የሰሩ የቀድሞ ባለስልጣናት ምስክርነት ሰጥተዋል።

የ 1966 የኢትዮጵያ አቢዮትን ተከትሎ በትረ ስልጣኑን ከተቆናጠጠው የደርግ መንግስት ጋርም ወጣቱ ጎሹ ተቀራርቦ ለመስራት በንጉሰ ነገስቱ ዘመን ያሳየው ብቃትና ተወዳጅነት ረድቶት ኖሮ የጠቅላይ ጦር ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ሆኖ ሊሾም በቃ። ኮሎኔል ጎሹ መንግስት ከሰጠው የአቃቤ ህግ ሃላፊነት አንስቶ ታጠቅ የጦር ሰፈር ወስዶ ሲሾመው የሚሰጠውን ምልምል ወታደሮች የማሰልጠን ሃላፊነት በቀላሉና በብቃት እንደሚወጣው በመተማመን ነበር።

ቀደም ሲል በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ቆይቶ ደግሞ በ 1969 ዓ.ም በዚያድባሬ ይመራ የነበረው የሶማሌ መንግስት ኢትዮጵያን በመውረር የሃገሪቱን ቀላል የማይባል ግዛት ተቆጣጥሮ ስለነበርና ወደ ስልጣን ከወጣ ገና ጥቂት አመት ብቻ ያስቆጠረው የደርግ መንግስትም በስንቅም በትጥቅም በፖለቲካዊ አመራር ብቃትም ከፍተኛ የሆነ የልምድና የአቅም ማነስ ይስተዋልበት ስለነበር ሳይሆን አይቀርም እንደነ ኮሎኔል ጎሹ አይነቶቹን ምሁራንና ቆፍጣና ወታደር ወደ አሳሳቢው የጦርነት ቀጠና የሳባቸው።

በሰለሞናዊው ስርወ መንግስት የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት በመሆን ኢትዮጵያን ለ 44 አመታት ዘውድ ጭነው ያስተዳደሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ በንግስና ዘመነ መንግስታቸው የዉጭ ጉዳዩን፣ የመከላከያውን፣ የደህንነቱን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩንና የመሳሰሉ የሃገር ሁለንተናዊ ስልጣኖችን ለሌሎች ባለስልጣናት ሰጥተው እንዲያስተዳድሩ ካደረጉ በኋላ ከንጉሰ ነገስትነታቸው ደርበው የያዙት ስልጣን የትምህርት ሚኒስትርነትን ስልጣን ነበር።

እናም ይሄ ከንጉሱ ግዜ ጀምሮ ትልቅ ስፍራ ትርጉም ያለው የመንግስት ስልጣን “በማን የአስተዳደር እዝ ስር ይሆናል?” የሚለው ጥያቄ ብዙዎች ሲያነሱ ሲጥሉት የነበረ ጉዳይ ሆኖ ሲያበቃ በመጨረሻ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ እንዲይዙት ተደረገ

➛ በመሬት ለአራሹ የገጠርና የከተማ መሬት ድልድል በርካታ ጭሰኞችና ቤት አልባዎች የመሬት ባለቤት ሆነዋል።

ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ

➛ ከዚህ በተሻለና በበለጠ ደግሞ መሃይምነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ባለመው የእድገት በህብረት ዘመቻ ኢትዮጵያ ከምንግዜውም የላቀና ታይቶ የማይታወቅ ምሁራንን ማፍራት ከመቻሏም አልፋ ተርፋ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ የነበሩ በጣታቸው ቀለም ነክረው ይፈርሙ የነበሩ መሃይማን በአመዛኙ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ሆኗል።

➛ ወራሪውን የሶማሊያ መንግስት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ እስከ ዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ድረስ አሯሩጦ የተረከበውን የሃገራችንን ሉአላዊነት በአደራ አስረክቧል

— በአፍሪካ ወደርና አቻ የማይገኝለት ግዙፍ ጦር ሰራዊት ገንብቶ ሃገራችን ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ተፈርታና ታፍራ እንድትኖር አድርጓል….ወዘተ።

ይህም ደርጎች ወይንም የስርአቱ የቀድሞ ባለስልጣናት “ያኔ የሰራነው” ብለው ከሚመኩበት ስራዎቸው በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ጉዳዮች ናቸው።ፐከእነዚህም መካከል መሃይምነትን ከሃገራችን ለማጥፋት ታቅዶ በተካሄደው የእድገት በህብረት ዘመቻ ላይ አንቀሳቃሽ ሞተሮች ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ኢትዮጵያ ፈጽሞ ስማቸውን ልትዘነጋው ከማይገባ መሃይምነትን ከገጠሪቷ ኢትዮጵያ ጠራርገው ካጠፉ ጉምቱ ባለስልጣናት መካከል ኮሎኔል ጎሹ ወልዴን ሳይጠቅሱ ማለፍና ታሪክን አውሸልሽሎ ለመመዝገብ መሞከር በሽንቁር ገንቦ ውስጥ ውሃ ለማስቀመጥ እንደመሞከር ሳይሆን አይቀርም። ለዚሁ ስኬታማ ዘመቻ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት “መሃይምነትን ለማጥፋት ባደረግሽው ትግል” ተብላ ለሶስት ግዜ ያክል ተሸላሚ እንድትሆን ከማድረጋቸው አልፈው ተርፈው የመምህራኑ የኑሮ ደረጃና ገቢ እንዲጨምር የደረጃ እድገትና የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እንዲሰጣቸው ስለማድረጋቸው በስፋት ይነገርላቸዋል።

ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ሲበዛ ደፋርና የመሰላቸውን ለመናገር አንዲት ስንዝር ታክል ወደኋላ ንቅንቅ የማይሉ የግንባር ስጋ የሚባሉ አይነት ተጋፋጭ አንደበተ ርቱእ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ምሁር ናቸው። አንዳንዶች እንደሚሉት ደርግ በወቅቱ የወታደሮች ስብስብ ከመሆኑና በመሃከሉ ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው ምሁር በማስፈለጉ ነበር ኮሎኔል ጎሹን በቅድሚያ ወደ ትምህርት ሚኒስትርነት በመቀጠልም ወደ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እንዲመጡ ያደረጉት። ይህ ማለት እንግዲህ እንደነ ባሮ ቱምሳ እንደነ ሃይሌ ፊዳ አይነቶቹ ኮሎኔል መንግስቱን የሶሻሊስቱን ርእዮተ አለም ሀ ሁ አስጠንተዋል እንደሚባለው አይነት ሳይሆን አይቀርም።

የኢትዮጵያን በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ከሰላሳ በላይ ሰዎች መርተዉታል። ከነዚህም መካከል ከጦር አዋቂው ፊትአውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ አንስቶ በቅርቡ በሞት እስከተለዩት ተስፋዬ ዲንቃ፤ ከያኔው ራስ ተፈሪ (ኋላ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ)አንስቶ ዛሬ ጣልያን ኤምባሲ ተሸሽገው እስከሚገኙት ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ ከጸሃፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ አንስቶ እስከ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከልጅ ሚካኤል እምሩ እስከ ስዩም መስፍን ከዶክተር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ አንስቶ እስከ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ድረስ ይጠቀሳሉ። በመሆኑም ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ሹመት ከነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ኢትዮጵያዊያን ጋር በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እየተሰባጠረ ብሎም እየተነጻጸረ መቅረቡ የማይቀር ጉዳይ ነው።

ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ
ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ

ኮሎኔሉ አንደበታቸው የጣፈጠ ንግግራቸው ማራኪ ከመሆናቸውና ፍጹም የእንግሊዝ አፍ ነው በሚባልላቸው የተዋጣለት የእንግሊዝኛ ንግግራቸውን ተጠቅመው ሃገራችን ኢትዮጵያን በብዙ አለም አቀፍ መድረክ ወክለው ለሶስት አመት ያክል በአስደናቂ ብቃት አገልግለዋል።

ደርግ ኢትዮጵያን በመራበት አስራ ሰባት አመታት ውስጥ የነበረው ልዩነት በመንግስት ሹማምንት እና በህዝብ መካከል ብቻ ሳይሆን በመንግስት ባለስልጣናት እርስ በርስም ጭምር ነበር። በዚህ አንዱ አንዱን ለመጥለፍ አንዱ አንዱን ለመጣል አንዱ በአንዱ ትከሻ ላይ ተንጠላጥሎ አንገቱን ለማስገግ በነበረ ዉትብትብ የፖለቲካ ጨዋታ ጎሹ ወልዴ ድንገት ባላሰቡትና ባልገመተዠቱት መልኩ ከጠላቶቻቸው ወጥመድ ውስጥ ከኮሎኔል መንግስቱ ጥርስ ውስጥ ዘው ብለው ገቡ።

ጎሹ ሃገር ለቀው ከወጡ በኋላ ስም እየጠቀሱ የተቿቸው ባለስልጣናት የእርሳቸውን ቦታ ማለትም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ሲመኙ እንደነበር ለሊቀመንበሩ ስማቸውን ጥላሸት እየቀቡ ያቀርቡ እንደነበር በተለይ በተለይ እነ አሻግሬ ይግለጡ (አሻጥሬ ይላቸዋል)እነ ካሳ ከበደ እነ ፍቅረስላሴ ወግደረስ እና ሌሎችም እርሱን ለመጣል የተንኮል ሸማ ሲያሸምኑ እንደ እንደነበር ይገልጻል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጎሹ በተለያየ ጊዜያት ሃገራችንን ወክሎ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መድረክ ላይ በመቆም ብስለታቸውን በሚያስመሰክር መልኩ ንግግሮችን በሚያደርጉበት ግዜ የተወሰኑ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በሸረቡት ሴራ በልኡካን ቡድን መሪነት ስም ጎሹን ሲሰልሉ ዉጭ ሃገር ሄዶ ምን እንደሚያደርጉ ከማን ጋር እንደሚያወሩ ወሬ እየለቃቀሙ ለሊቀ መንበር መንግስቱ ሹክ ይሉ እንደነበር ዛሬ ዛሬ እየታተሙ እየወጡ ያሉ የቀድሞውን ስርአት ምንነት የሚያሳዩ መጽሃፍ በስፋት እያብራሩት ይገኛሉ።

የኮሎኔል ጎሹና የደርግ መንግስት የተሳሰሩበት ጅማት የመበጠሻዋ ቢላ መሞረድ የጀመረችው ቀደም ብላ ቢሆንም ነገሩ የተካረረውና አንዳንዶች እንደሚሉት ጎሹ የተጠመደላቸው ወጥመድ ዉስጥ የገቡት ብራስልስ ላይ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጉባኤ መነሻነት ነበር። የዛን ግዜ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ በተገኙበት የብራስልሱ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኮሎኔል ጎሹ እነርሱን ወክለው ንግግር እንዲያደርጉ ይመርጥዋቸዋል።

በጉባኤው ላይ ንግግር እንዲያደርጉ የተመረጡት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴም የንግግሩ ፍሬ ሃሳብ የነበረው “አሜሪካ በሁለተኛው የአለም ጦርነት የተጎዳውን የምእራብ አውሮፓ በማርሻል ፕላን እንደታደገችው ሁላ አፍሪካንም በተመሳሳይ ፕላን ልትታደጋት ይገባል” የሚል ይዘት ነው የነበረው።

እንደሚታወቀው ማርሻል ፕላን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (SECRETARY OF STATE) በነበረው በጆርጅ ካትሌት ማርሻል የሃሳብ አመንጪነት የቀረበ እቅድ ሲሆን የእቅዱም አላማ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ለተጎዱት የምእራብ አውሮፓ ሃገራት አሜሪካ ለአራት አመት ፕሮጀክት 13 ቢሊየን (በዛሬው ስሌት 120 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ) ለአውሮፓ ሃገራት የመልሶ ግንባታ እንድታበድር: እግረመንገዷንም የምስራቅ አውሮፓ የሶሻሊስት ተስፋፊ ሃገሮችን እንድታዳክም የተነደፈ ፕላን ነበር። እናም በጉባኤው ላይ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በመንኮታኮት ላይ ስለነበረው የአፍሪካ ምጣኔ ሃብት የመልሶ ግንባታና የኢኮኖሚ ድቀት ማገገሚያ ይሆናል ብሎ እንደ ሃሳብ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ያቀረበው ንግር ይህንኑ የማርሻል ፕላን አይነት እቅድ አሜሪካ እንድታደርግ ነበር በዚህ ግዜ የኮሎኔል ጎሹን ንግግር ሰበዝ በሰበዝ እየሰነጠቁና የተባለውን ካልተባለው የታሰበውን ካልታሰበው እያቆራኙ ለሊቀመንበሩ ከጎሹ ወልዴ ድንቅ የእንግሊዝኛ ንግግር ክህሎት ጋር እያጣመሩ “ወትሮም የሲአይኤ ቅጥር ነው ስንልዎ አልሰሙንም ነበር ይሃው አሁን በአደባባይ አሜሪካ አፍሪካን እንድታጥለቀልቅና ኢምፔሪያሊዝም እንዲስፋፋ ይማፀናል።

ይህ እና ሌሎች የተንኮል ድሮች የወታተቧቸው ኮሎኔል ጎሹ ለአንድ የስራ ጉዳይ ወደ ዉጭ ሃገር ከሄዱ በኋላ ዳግመኛ ወደ ትውልድ ሃገራቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል። ኮሎኔል ጎሹ በወቅቱ አልመጣም ቀረሁኝ የሚልና “አብዮታችን ወደ ፍጹም አምባገነናዊነትና ጭካኔ ዘቅጧል”የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤን ጨምሮ የዉሎ አበላቸውን ዶላር የጉዞ ቲኬት እንዲሁም ጠቃሚ ዶክመንታቸውን ለሊቀበንበሩ በአድራሻቸው እንዲሰጥ ማድረጋቸው እጅግ መነጋገሪያ ሆኖ በወቅቱ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በተደጋጋሚ ሲነገር ነበር።

ጎሹ ወልዴ ስርአቱን ተቃውመው ከመውጣታቸው የተነሳም ይሁን ወይም በግል ስብእናቸው ወይንም በሃቀነታቸው የተነሳ ስርአቱን ይቃወሙ የነበሩትም ይደግፉ የነበሩም በተመሳሳይ መልኩ በአመዛኙ መልካም አስተያየት እየሰጡ በምሳሌነት ያነሷቸዋል። በስንዴ መሃል እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁላ በእንክርዳድ መሃልም ስንዴ ላይጠፋ ይችላል። ደርግ ራሱ በኋላ ቀርነቱና በበዝባዥነቱ ከሚወቅሰው ከአጼ ሃይለስላሴ መንግስት ካቤኔ ውስጥ እነ ልኡል ራስ እምሩንና ሚካኤል እምሩን እንዲሁም እነ ራስ መንገሻ ስዩምንና በተራማጅነት ይጠቅሳቸው ነበር።

ገና በሃያዎቹ መጨረሻ እድሜያቸው ጀምረው ወደ መንግስት ከፍተኛ የስልጣን ኮርቻ ላይ ጉብ ያሉት ኮሎኔል ጎሹ የደርግን ስርአት በቃኝ ብለው ሃገር ጥለው ሲወጡ እድሜያቸው ገና በሰላሳዎቹ መጨረሻ ላይ ነበር። ምንም እንኳ የደርግ ስርአት ቁንጮ ከነበሩ ሰዎች አንዱ ቢሆኑም በቀይ ሽብርና በዘር ማጥፋት በመሳሰሉት ወንጀሎች ጠቅላይ አቃቤ ህግም ይሁን የወንጀሉ ሰለባዎች የኮሎኔሉን ስም ሲያነሱት እምብዛም አይሰማም ወይንም ተሰምቶ አይታወቅም (ከኑግ ጋር የተገኘ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ካልሆነ በቀር ማለት ነው):።

ኢትዮጵያ ስማቸውን በበጎ ከምታነሳቸው ዲፕሎማት ወታደርና ሚኒስትሮች መደዳ ያሉት ጎሹ ዛሬ ኑሯቸውን በሃገረ አሜሪካ አድርገው እየኖሩ ነው።

#ታሪክን_ወደኋላ

ዳንኤል እንግዳ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop