August 17, 2022
26 mins read

ኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስና የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ፕራይቬታይዜሽን ሴራ!!!

(ክፍል 2) ሚሊዮን ዘአማኑኤልና ፂዮን ዘማርያም (ኢት-ኢኮኖሚ)

677668788በዶክተር ኢዮብ ተስፋዬ በሪፖርተር ጋዜጣ እሁድ ሰኔ 17 ቀን 2010ዓ ም በፁሁፍ ያቀረቡት ‹‹ኢኮኖሚው ያጋጠሙትን የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ለማቃለል የቀረበ የመፍትሄ ሐሳብ….(1)

በዶክተር ኢዮብ ተስፋዬ፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ ከአራት ዓመታት በፊት ለብልጽግና መንግሥት ምክረ ሃሳቡን አቅርበው መንግሥትባለመቀበሉ የተነሳ የሃገራችን የኢኮኖሚ ቀውስ እለት በእለት በሚጨምር የዋጋ ግሽበት ተመታ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የፋይናንስ ሥርዕት ቀውስ፣ አላስፈላጊ የገንዘብ ህትመት፣ ለአመታት የተዛባ የውጭ ንግድ ገቢና የገቢ ንግድ ወጪ የንግድ ሚዛኑን ማዛባት ተመዝግቦል፡፡ ባሳለፍነው የጦርነት ኢኮኖሚ የተነሳ በሁሉም ወገኖች ግማሽ ሚሊዮን ወጣቶች ተሰውተዋል፣ አካላቸው ጎሎል፡፡ እንዲሁም አንድ ትሪሊየን ብር የሚገመት መሠረተ ልማቶች ወድሞል፡፡ በዚህም የተነሳ የውጭ ሃገር ኢንቨስተሮች ቀንሰዋል አሊያም ኮብልለዋል፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍስት ቀንሶል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች በብልፅግና መንግሥት እምነት በማጣት የሃዋላ የገንዘብ ፍሰት እያደር በመቀነስ ላይ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የጦር አበጋዞች መንግሥት የድንበርና ወሰን ግጭት ወደ ማያባራ ጦርነት ውስጥ አገሪቱን ስለከተታት ተወያይቶ ከወዲሁ ህገመንግሥቱን ማሻሻል፣ የዘር ፌዴራሊዝምን የክልሎች ድንበርና ወሰን በማጥፋት እውነተኛ ፌዴራሊዝም በመገንባት ራስን በእራስ የማስተዳደር መብቶች የሚከበርባት ኢትዮጵያን በሠላም መገንባትና ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር መብቶችና ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብቶች በማስከበር ዘለቄታዊ የሠላም መፍትሄ እንሻለን፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በአስተማማኝና ዘለቄታዊነት ባለው ሰላም ላይ መሠረቱን መጣል ይኖርበታል፡፡ በውጭ ምንዛሪ የተገነቡትን መሠረተ ልማቶች እያፈረስን መኖር የድንቁርና የድህነት መንገድ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ የዶክተር ኢዮብ ተስፋዬን ከአንድ እስከ ስምንት ቁጥር የቀረቡትን የመፍትሄ ሃሳብን አቅርበን ባለፈው አራት አመታት የተከወኑትን አንኳር ጉዳዬች የእኛን ሃሳቦች ከስሩ በቡሌትድ ሊስት አካተናል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ፡፡

የማክሮኢኮኖሚተግዳሮቶችን ፈትቶ፣ የኢኮኖሚ የመዋቅር ለውጥ በቀጣይነትለማመጣትምንመደረግአለበት?

{1} የማክሮኢኮኖሚ ሪፎርም ማካሄድ፡-

‹‹ የአንድ አገር ማክሮ ኢኮኖሚ የተረጋጋና ጤናማ ነው የሚባለው የተረጋጋ ዋጋ (Price stability)፣ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ (Stable exchange rate)፣ ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት (Sound financial system) ሲኖር ነው፡፡በዚህ ረገድ የዋጋ ግሽበትን ከተሰቀለበት ትርጉም ባለው ደረጃ ለማውረድ መንግሥት የሚወሰን ከሆነ ሊከተለው የሚገባው መንገድ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ (Tight monetary policy) መሆን አለበት፡፡ ይህ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲዎችን (Direct and indirect monetary policy instruments) በሥራ ላይ በማዋል ኢኮኖሚው ሊሸከመው የሚችለውን የገንዘብ አቅርቦት መንገድ መወሰን የወለድ መጠንና የመጠባበቂያ ገንዘብን በጥብቅ እየተከታተሉ እንደአስፈላጊነቱ መጠኑን በመለወጥ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የብር የመግዛት አቅም እንዳይዳከም ይረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዋጪነትን፣ ብሔራዊ ባንኩም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተቀመጠለት አካሄድ መጎዙን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

ይህ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ለተወሰነም ጊዜም ቢሆን የኢኮኖሚ እድገቱን ፍጥነት ለዘብ የሚያደርገው ቢሆንም በቀጣይ ጊዜያት በአመቺ ሁኔታ እንዲያድግ መደላደል ይፈጥራል፡፡ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው የዋጋ ግሽበትን ሊያወርድ የሚችለው በገንዘብ አማካይነት ብቻ የተፈጠረውን የዋጋ ግሽበት በመሆኑ በአቅርቦት ማነሰ የሚፈጠረውን ወይም የተፈጠረውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር የሚቻለው የአቅርቦት መጠን በማሳደግና በመጨመር በመሆኑ መንግሥት አቅርቦትን በፍጥነት ሊጨምሩ የሚችሉ (Aggressive supply side measures) መወሰድ ይኖርበታል፡፡ የገንዘብ አቅርቦት ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ጋር ተጣጥሞ ሲያድግና የምርት አቅርቦት ሲጨምር ህብረተሰቡን ያማረረ የዋጋ ግሽበትን ማረጋጋት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ህብረተሰብ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ ነው፡፡››

  • ከመጋቢት 2010 እስከ መጋቢት 2011ዓ/ም፤በብልፅግና ፓርቲ በዶክተር አብይ አህመድ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የማዕከላዊመንግሥት ዕዳ7 (አራት መቶ አርባ ዘጠኝ ነጥብ ሰባት) ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
  • በ2013 ዓ/ም የአገርውስጥ የመንግሥት ዕዳ 945 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተጠቅሷል። ከዚህ ውስጥ 525 (አምስት መቶ ሃያ አምስት) ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቆማት ያበደረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡
  • የኮነሬሉ አብይ መንግሥት በሦስት አመታት በትረ ስልጣኑ ከመጋቢት 2010 እስከ 2013ዓ/ም የአገርውስጥ የመንግሥት ዕዳ ከ449.7 ቢሊዮን ብር ወደ 945 ቢሊዮን ብር ደረሰ፡፡ መንግሥት ተጨማሪ 495.3 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከብሔራዊ ባንክ፣ በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ፣ ከመንግሥት ሠራተኞችና ከግል ሠራተኞች የጡረታ ፈንድና ተወስዶ ያልተከፈለ ዕዳ መሆኑን ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል፡፡
  • የኮነሬሉ አብይ መንግሥት የአራት አመት አገዛዝ ዘመን ከመጋቢት 2010 እስከ 2014ዓ/ም የአገር ውስጥ ውዝፍ ዕዳ መጠን 1.14 (አንድ ነጥብ አስራ አራት) ትሪሊዮን ብር መድረሱ ተገልፆል፡፡ የአገርውስጥ የመንግሥት ዕዳ ከ449.7 ቢሊዮን ብር ወደ 945 ቢሊዮን ብር ብሎም ወደ 14 (አንድ ነጥብ አስራ አራት) ትሪሊዮን ብር ደረሰ፡፡ መንግሥት ተጨማሪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከብሔራዊ ባንክ፣ በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ፣ ከመንግሥት ሠራተኞችና ከግል ሠራተኞች የጡረታ ፈንድና ተወስዶ ያልተከፈለ ዕዳ መሆኑን ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል፡፡
  • የመንግሥትልማት ድርጅቶች የአገር ውስጥ ዕዳ8 (ሦስት መቶ ሰማንያ ስድስት ነጥብ ስምንት) ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንዳለባቸው መረጃው በዝርዝር ያመለክታል፡፡ ብድሩ የተሰጠው ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከኢትዮ ቴሌኮም ወጭ ያሉትን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የሚመለከት እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል፡፡ ከመንግሥት ልማት ድርጅቶቹን የተናጠል ዕዳ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ያለባቸው የአዲስ አበባ የቤት ልማት መርሃግብር 50 (ሃምሳ) ቢሊዮን ብር እዳ፣ የስኳር ኮርፖሬሽን 70 (ሰባ) ቢሊዮን ብር እዳ፣ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል 300 (ሶስት መቶ) ቢሊዮን ብር እዳ፣ የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ወዘተ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ያለባቸው ድርጅቶች ናቸው፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከጥቂት ወራት በፊት ይህንኑ ሁኔታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስረዳታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም መንግሥታቸው ተግባራዊ ማድግ የጀመረውየኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም ፈጥኖ ባይደርስ ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመውደቅ አደጋ ተጋርጦበት ነበር ማለታቸው አይዘነጋም። መንግሥት እያደረጋቸው ከሚገኙ ሪፎርሞች መካከል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልከፈሉትን ዕዳ ቀስ በቀስ ወደ መንግሥት ማዘዋወር አንዱ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ የመፍትሄ አማራጭ መሆኑን ታውቆል፡፡›› ኮነሬል አብይ መንግሥታቸው ዋናው ተበዳሪ ሆኖ እያለ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ያልተከፈለ የተቆለለ እዳ ቀስ በቀስ ወደ መንግሥት ማዘዋወር አንዱ አማራጭ ተደርጎ ተቀምጦል፡፡ የመንግሥት የትየለሌ እዳ እያለበት እየታወቀና ያለገደብ ከብሔራዊ ባንክ ያለህግ እየመነተፈ የልማት ደርጅቶችን እዳ ወደ መንግሥት ማጠቃለል ማለት እዳቸውን መሠረዝ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

{2} የውጭ ምንዛሪ አቅምን ማጎልበት:-

‹‹አሁን በሥራ ላይ ያለው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ ከኤክስፖርት ይልቅ በእጅጉ የሚያበረታታው ኢምፖርትን ወይም የገቢ ንግድ ነው፡፡ ኦፊሴል በሆነው የውጭ ምንዛሪ ገበያና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ተመን ሰፊ በመሆኑ ለነጋዴዎች ተመራጭ የሆነው በሃያ ሰባት ብር አንድ ዶላር በሚመነዘር ተመን ዕቃ በማስገባት በ35 ብር መሸጥ ተመራጭ ሆኖል፡፡ በመሆኑም የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲውን ድክመቶች በሚገባ መፈተሸና ማስተካከል እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ሐዋላ ወይም ሬሚታንስ በከፍተኛ ሁናቴ ለመጨመር ብሔራዊ የሐዋላ የሬሚታንስ ስትራቴጂ መንደፍ የአጭር ጊዜ ተግባራት ናቸው፡፡ በመካከለኛ ጊዜ ደግሞ የኤክስርት ስትራቴጂ በመንደፍ የኤክስፖርት ሴክተሩን መደገፍ፡፡ እንዲሁም የውጭ አንቨስተሮች ሲመጡ እውነተኛ ከእውነተኞቹ ኢነቨስተሮችን ነጥሎ በማውጣት ድጋፍ ማድረግና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስመንትን ሥራ አጠናክሮ በቀጠል በ ምንዛሪ ላይ የተፈጠሩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ከውጨ ንግድ በተጨማሪ ኢምፖርት ስብስቲትዩሽን (በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት) ጉዳይም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡››

  • የአገሪቱየውጭ ምንዛሪ ተመን ከአመት ወደ አመት እየረከሰ መሄድ ማለትም፣ የአንድ ዶላር የብር ተመን በ1991 እኤአ 2.05 ብር የነበረ ሲሆን፣ ከ1992 እስከ 1994 እኤአ ወደ 5 ብር፣ ከ1995 እስከ 1999 እኤአ 5.88 ብር፣ ከ2000 እስከ 2004 እኤአ 8.15ብር፣ ከ2005 እስከ 2008 እኤአ 8.65 እስከ 9.67 ብር አንድ አሃዝ እየረከሰ ሄድ፡፡ ከ2009 እስከ 2015 እኤአ የአንድ ዶላር የብር ተመን ወደ ሁለት አሃዝ እየረከሰ ከ12.39 ብር ወደ 21.83 ብር፣ ከ2016 እስከ 2022 እኤአ የአንድ ዶላር የብር ተመን ወደ ሁለት አሃዝ እየረከሰ ከ22.39 ብር ወደ 51.00 ብር (Dollar to Ethiopian Birr Exchange Rate Today, Live1 USD to ETB = 52.9561) በአራት አመት ከሃያ ሰባት ብር ወደ ሃምሳ ሦስት ብር መድረሱ የሚያመላክተው የብራችን የመርከስና የብር የመግዛት አቅም መውደቅ ዋና ምክንት የተደላደለና የረጋ የውጭ ምንዛሪ ተመን አለመኖሩን በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በጥቁር ገበያ አንድ ዶላር ከ82 እስከ 84 ብር ይመነዘራል፡፡

{3} የገንዘብና የካፒታል ገበያን ማቌቌምና ማስፋት፡-

ከላይ ከተጠቀሱት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እርምጃዎች በተጨማሪ የገንዘብ ገበያን ማለትም የመንግሥት የግምጃ ቤት ሠነድ ገበያን (Treasury bils market) የካፒታል ገበያ ማስፋፋት ለኢንቨስትመንት ማደግ አማራጭ የገንዘብ ምንጭ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የገንዘብ ፖሊሲውን አተገባበር እንዲሁም የተሳለጠ ፕራይቬታይዜሽን እንዲኖር የሚረዱ በመሆናቸው መንግሥት ለገንዘብ ገበያና ለካፒታል ገበያ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡

{4} ብሔራዊ ባንክን እንደገና ማዋቀርና ማደራጀት:-

‹‹የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመምራት የሚወጡ ፖሊሲዎችን ለማስፈፀም የፋይናንስ ሴክተሩን ጤናማ ሆኖ እንዲጎዝና ለቀጣይ ውድድር አቅም እንዲገነባ ለማድረግ የኢኮኖሚውን የወደፊት ወርድና ቁመና የሚመጥን ማዕከላዊ ባንክ (Central bank worthy of its name) ሊኖር ይገባል፡፡ ይህን ባንክ ሊመሩ የሚችሉ ሰዎችይህን ያህል ብር አትም ሲባሉ የለም ያንሳል ጨምሬ ላትም የሚሉ ሳይሆኑ ለህሊናቸው ብቻ ተገዥ የሆኑና ለሙያቸው ክብር ያላቸው የፖሊሲ ማስፈፀም አቅማቸው ደካማ ያልሆነና ማንኛውንም ሐሳብ የሚያስተናግድና ከምርምር ተቌማትና ከአካዳሚው ጋር በትብብር ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎች መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ጥበቃም ቢሆን የሚለውን የነጭ ፈረስ ፍለጋ መሥፈርት ውድቅ አድርጎ ባንኩን በጥንቃቄ ማዋቀር ያስፈልገዋል፡፡

በነገራችን ላይ ለዋጋ ግሽበቱ መባባስ ዋነኛው ምክንያት ካለፈው መንግሥት ጀምሮ መንግሥት በብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን የገዘብ መጠን ገደብ እንዲነሳና እንደ ልብ እንዲዳብር በመፈቀዱ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በትክክል እንዲያስፈፅም ከውሸት የጸዳ የገንዘብ፣ የክፍያ ሚዛንና የምንዛሪ መጣኝ (Monetary balance of payments, exchange rate) ዳታ ቤዝ እንዲሁም ጠንካራ የጥናትና የምርምር ክንፍ እንዲኖረው ማድረግ ለባንኩ ጥንከሬ ወሳኝ ነው፡፡ ባንኩ ልክ እንደ ሌሎች ማዕከላዊ ባንኮች ሁሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በትክክል መሥራታቸውን ችግሮችና ሥጋቶች ሲፈጠሩ ፈጥኖ የማስተካከያ የፖሊሲ እርምጃዎችን የሚወስድ የሞኒተሪ ፖሊሲ ኮሚቴ (Monetary policy committee) ሊኖረው ይገባል፡፡››

  • የብልፅግና መንግሥትየአገር ውስጥ ዕዳ፣የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማክሰር ሴራ ላይ የተመሠረተ ነው፣ የብልፅግና መንግሥት የአገር ውስጥ ዕዳ ከ449.7 (ከአራት መቶ አርባ ዘጠኝ ነጥብ ሰባት) ቢሊዮን ብር በ2010ዓ/ም የነበረ ሲሆን በ2014 ዓ/ም ወደ 14 (አንድ ነጥብ አስራ አራት) ትሪሊዮን ብር ተመንድጎል፡፡ የአብይ አህመድ መንግሥት በአራት አመታት ውስጥ 690.3 (ስድስት መቶ ዘጠና ነጥብ ሦስት) ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድሮል፡፡
  • መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ መውሰድ የሚችለው የቀጥታ ብድር ጣሪያ በ2000ዓ.ም. እንዲነሳ ከተደረገ በኋላ፣ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ያለ ገደብ እየተበደረ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በብሔራዊ ባንክ ሥራ ጣልቃ በመግባት ትቶ መንግሥት መውሰድ የሚችለው የቀጥታ ብድር ጣሪያ ዳግም መከበር ይኖርበታል እንላለን፡፡.መንግሥት ካለበት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ብድር ውስጥ 182 (መቶ ሰማንያ ሁለት) ቢሊዮን ብር ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ የተበደረው መሆኑ ይታወቃል፡፡ መንግሥት ያለ ገደብ ከብሔራዊ ባንክ የሚበደርበት ሥርዓት አለ ማለት፣ ውጤቱ ገንዘብ እንደማተም እንደሚቆጠር ይህም ኢኮኖሚው ያላመነጨው ተጨማሪ ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲሽከረከርና የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
  • ለዚህ ነው የአንድ ዶላር የውጭ ምንዛሪ 52.83 በባንክ ቤት ህጋዊ ምንዛሪ ሲሆን በጥቁር ገበያ ከ80 እስከ 84 ብር ይመነዘራል፡፡ አይኤም ኤፍና የዓለም ባንክ ብር እንዲረክስ ጫና በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡በሃገሪቱ በጦርነት ኢኮኖሚ ውስጥ በመገኘቶ የተነሳ የኑሮ ውድነት በፋብሪካ ሽቀጦችና የግብርና ምርቶች የዋጋ ግሽበት አስከትሎል፡፡ በሃገሪቱ በታወጀ የጦርነት ኢኮኖሚ በክልሎች ኮማንድ ፖስት ሥር በወታደራዊ አገዛዝ ቀንበር ሥር ወድቆል፡፡ መንግሥትያለ ገደብ ከብሔራዊ ባንክ የሚበደርበት ሥርዓት አለ ማለት፣ ብሔራዊ ባንክ ማክሮ ኢኮኖሚውን ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ማስተዳደር አለመቻሉን እንደሚያሳይ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት ካለበት 945 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ዕዳ ከፍተኛው መጠን ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ ብድር የተወሰደ፣ እንዲሁም በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አማካይነት ከሁለቱ የሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና (የጡረታ) ኤጀንሲዎች፣ ማለትም ከመንግሥት ሠራተኞችና ከግል ሠራተኞች የጡረታ ፈንድና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወስዶ ያልተከፈለ ዕዳ መሆኑን ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ማዕከላዊ መንግሥት ዕዳ በብሔራዊ ባንክ ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በህግ መወሰን ይኖርበታል ካለዛ የጡረተኞች ተቀማጭ ገንዘብ በመንግሥት ተወስዶ ጡረተኛው የሚከፈለው እንዳያጣ ያስጋል እንላለን፡፡

ምንጭ

(1) https://online.fliphtml5.com/qhkn/nmft/(ቅጽ 23 ቁጥር 1894 / እሑድ ሰኔ 17 ቀን 2010)

ሪፖርተር ጋዜጣ እሁድ ሰኔ 17 ቀን 2010ዓ/ም በዶክተር ኢዮብ ተስፋዬ

(2) መንግሥት ከአገር ውስጥና ከውጭ የተበደረው ውዝፍ የዕዳ መጠን 2.4 ትሪሊዮን ብር ደረሰ/ ሪፖርተር ጋዜጣ / 1 ሴፕቴምበር 2021

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop