July 6, 2022
19 mins read

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ የምሥረታ ወርቅ ኢዮቤልዩ ሲፈተሽ (ፕሮፈሶር ኀይሌ ላሬቦ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዘንድሮ የምሥረታውን የወርቅ ኢዮቤልዩ ማለትም ዐምሳኛውን ዓመት [በአ.አ. 1972-2022] በማክበር ላይ ይገኛል። በዓሉ የሚገልጥልን ነገር ቢኖር፣ የአገራችን ሕዝብ ከታሪክ መማርም ቀልብ መግዛትም እንደተሳነው ነው ብል ስሕተት አይመስለኝም። ገለልተኝነትን በተላበሰ የታሪክ መነጽር ብናየው፣ ኢሕአፓ ልክ እንደሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይና [ሕወሓት]  የኦሮሞ ነጻነት ግንባር [ኦነግ]፣ ዛሬ መወገዝ፣ መሰደድና ከሥረመሠረቱ መጥፋት ያለበት ሽብርተኛ ድርጅት እንጂ እንደዚህ በአደባባይ ስሙ በክብር መጠራት የሚገባው አይደለም። አዞ የተባለው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ቡድን አካልና ጭንጋፍ እንደመሆኑ፣ ከ፲፱፻፷ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ በኢትዮጵያ በየዘርፉ ለተከሠተው የሐሰት ታሪክ ስርጭትና የርእዮተዓለም ቀውስም ሆነ ላስከተለው ኢሰብኣዊ ተግባር፣ ማለትም አሁን በኦሮሚያም ሆነ በትግራይ በሌሎችም ክልሎች ጭምር፣ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠየቁት ዋነኞቹ አንዱ ኢሕአፓ እንደሆነ አይካድም።

EPRP 1

የአዞም የኢሕአፓም የጡት አባቶቻቸው የኤርትራው ነፃ አውጪ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ የነዚህን ሕልም እውን ያደረጉት ደግሞ ኢሕአፓና ሕወሓት እንደሆኑ አይካድም። ኢሕአፓ በኅብረብሔርነት፣ ሕወሓት በጐሣነት ላይ የተመሠረቱ የማይጣጣሙ ድርጅቶች መስለው ቢታዩም፣ በዓላማቸውና በርእዮታቸው ግን የማይለዩ መሆናቸው ማወቅ ያስፈልጋል። ዋና ዓላማቸው ሥልጣን ሲሆን፣ የተጠቀሙትም  የጡት አባቶቻቸውን የመገንጠል ጥያቄ በኢትዮጵያ የጭቁን ብሔሮች ሽፋን ለማስፈጸም እንደሆነ ድርጊታቸው ይመሰክራል። ሁለቱም ከተማሪዎች እንቅስቃሴ በተዋሱት፣ “ብሔር፣ ብሔረሰቦች  የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት እስከመገንጠል” በሚል መርህ ዙርያ የተሰባሰቡ ሲሆኑ፣ ልዩነታቸው የትኛው አስቀድሞ ይተግበር በሚለው ላይ ብቻ ነው። ኢሕአፓ “ትግሉ ሊሠምር የሚችለው በኅብረብሔራዊ ድርጅት ሲመራ ነው” ሲል፣ ሕወሓቶች፣ “የለም፤ በቀዳሚነት የተለያዩ ጭቁን ብሔር፣ብሔረሰቦች በየራሳቸው ድርጅት አማካኝነት ትግላቸውን ጀምረው፣ ከዚያ በኋላ የኅብረት ግንባር ሲፈጥሩ ነው” ይላሉ። ስለዚህ ሁለቱ የሚለዩት በስልት እንጂ በርእዮተ ዓለም ወይንም በእኩይ ተግባራቸው አይደለም።

ሁለቱም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንቋሽሹ፣ አባቶችንና ታሪክን የሚያዋርዱ፣ በአጉል ትምክህትና ትዕቢት ያበጡ፣ የማይስማማቸውን በጭካኔ ከማረድም ወደኋላ የማይሉ፣ ለሥልጣንና ለገንዘብ ሲሉ አገር ከመሸጥ ወይንም ከጠላት ጋር ወግነው የገዛ አገራቸውን ከመውጋት ዐይናቸውን የማያሹ፣ ብዙ ‘ኢሰብኣዊ” ወይንም “አሬመኔኣዊ”ና “ባንዳዊ” ተግባሮች የፈጸሙ እንደሆኑ ደጋግሞ ታሪካቸው ይመሰክራል። ከኢሰብኣዊ ተግባራት መካከል የጌታቸው ማሩ አገዳደል ሊጠቀስ ይችላል። አቶ ክፍሉ ታደሰና አቶ ተስፋይ ደበሳይ የሽብር ተግባራቸውን የተቃወመውን የድርጅቱ የፓለቲካ ቢሮ ተለዋዋጭ አባል የነበረውን አቶ ጌታቸውን ከገደሉት በኋላ፣ ራሱን፣ እጁንና፣ እግሩን፣ ሌላውን አካላቱን ቈራርጠው በጆንያ ከትተው ይዘውት ሲሄዱ ተይዘው ሁለቱም ሸሽተው እንዳመለጡ ሻምበል ተስፋዬ ርስቴ በ“ምስክርነት” መጽሐፋቸው ይነግሩናል። ይኸ ዐይነት ጭካኔ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሬት ሲፈጸም፣ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም። የኢሕአፓን ባንዳነት ድርጅቱ በሱማሌ ወረራ ወቅት የፈጸመው ክህደት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ወረራውን መደገፍ ብቻ ሳይሆን፣ በወቅቱ ከሱማሌው መሪ ሲያድ ባሬ ወደዐምስት ሚሊዮን ብር ወደድርጅቱ እጅ እንደገባ ይነገራል። ኢሕአፓ ይኸንን አስነዋሪ ድርጊት እንደለመደው ቢክድም ዓለም ያወቀው ፀሓይ የሞቀው የአደባባይ ምስጢር ከመሆን አላመለጠም።

ኢሕአፓና ሕወሓት በኢትዮጵያ ጥንታዊነትና ታላቅነት አያምኑም። በነሱ አስተያየት፣ ዓለም የሚደነቅበት፣ የመላው ዓለም ጥቊር ሕዝብ የሚኰራበት፣ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው፣ ከአፄ ምኒልክ ሲሆን፣ ሌላው ትርክት የደብተሮች ፈጠራ ነው። ከስድስት ሺ ዓመታት በላይ ያስቈጠረውን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የርስበርስ መወላለድ፣ በአምቻና በጋብቻ መገማመድ፣ በባህልና በሀብት መቋደስ፣ በቋንቋና በሃይማኖት መተሳሰር ምንም ዋጋ አይሰጡም። ኢትዮጵያ ለነሱ፣ “አንድ አማራ በተባለ ጨቋኝ ብሔረሰብ ወረራ የተቋቋመች፣ መቶ አምሳ ዓመት የማይሞላ ታሪክ ያላት አገር ናት። በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ፣ አማራው በሁሉም ዘርፍ የበላይነቱን ይዞ የሚገዛባት፣ አማራ ያልሆነው ብሔረሰብ ግን፣ በግፍና በገፍ የሚማቅባት እስር ቤት በመሆኗ፣ ፈርሳ፣ጨቋኝና ተጨቋኝ በሌለበት መልኩ፣ እነሱ በምናባቸው በቃዡት አምሳል በአዲስ መልክ መገንባት ይኖርባታል” ይላሉ።

በዚህም አቋማቸው ኢሕአፓና ሕወሓት የጠቅላላው ጥቁር ሕዝብም ሆነ እንደነጻነቱ አረቦን ትታይ የነበረችው የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው የአውስትሪያ ቄሣራዊ ሥርዐት አቀንቃኝ (ኢምፔርያሊስት) የባሮን ፕሮቻስካ ታማኝ ደቀመዛሙርት መሆናቸውን ያስረዱናል። የፓለቲካ ቋንቋቸውም ሆነ፣ ራእያቸውና ስልታቸው እንዳሉ የተቀዱት እሱ ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ለተዘረጋው ለነጭ ዘር የበላይነትና ዐምባገነንነት ስጋት እንዳትሆን ነጮች አገሪቷን እንዴት አድርገው ማጥፋት፣ ግዛቶቿንም መበታተን ይገባቸዋል ሲል ከደረሰው “ኢትዮጵያ የባሩድ ቤርሚል” ከሚለው መጽሐፉ እንደሆነ አያጠራጥርም።

ይሁንና፣ ኢሕአፓ በነዛው የሐሰት ወኔ ቀስቃሽ ስብከቱ፣ በአገር ፍቅር ስሜት የነደደውን፣ ዘመናዊ ትምህርቱን ከአገራችን ነባር ታሪክም ሆነ፣ ሥርዐትና ወግ ማጣጣም ያቃተውን፣ የቦዘኔውንና የሕልመኛውን፣ እንዲሁም የግልቱንና የገልቱን ወጣት ቀልብ በሰፊው ሊስብ እንደበቃ አይካድም። እልፍ አእላፋት ንጹሓን ኢትዮጵያውያንም ድርጅቱ ለሥውር ዓላማው ሲል በፈጠረው ነጭ ሽብር የተባለ የግድያ መፈክሩ ሰለባ ሁነዋል። የራሱም ተከታዮች ክፉ ድርጊታቸው ባስከተለው በቀይሽብር ጦስ ለእንግልትና ለእልቂት ሲዳረጉ፣ከመሪዎቹ መካከል ጥቂቶቹ ራሳቸው በከፈቱት ጦርነት ቢሞቱም፣ ብዙዎቹ ግን፣ዕቅዳቸው ሲባክንና ሲመክን፣ እንደምንደኛ እረኛ ጀሌዎቻቸውን በጠላላ ሜዳ ጥለው፣ ጓዛቸውን ጠቅልለው፣ ወደውጭ አገር እንደፈረጠጡ፣ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ስለሆነ እዚህ መድገም ተገቢ አይመስለኝም።

ኢሕአፓ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም፣ ቢቻልም ለማጥፋት፣ ከተነሡት ድርጅቶች አንዱ ቢሆንም፣ የቋመጠው ሥልጣን ግን የውሃ ሽታ ሁኖ ቀርቶበታል። በለስ የቀናለት ልክ እንደኢሕአፓ፣ በኤርትራ ነፃ አውጭ ድርጅቶች፣ በተለይም በሻቢያ ትዝላትና እንክብካቤ ያደገው ሕወሓት ቢሆንም፣ የማታ ማታ እሱንም ለአፄ ምኒልክ ቤተመንግሥት ያበቃው በቀዝቃዛ ጦርነት ፍጻሜ ላይ በአዲሱ የዓለም ኀይሎች አሰላለፍ ብቸኛዋ የዓለም ዘበኛ ሁና የቀረችው አሜሪቃ ናት። ሕወሓት መላዋን ኢትዮጵያን የመግዛት ዕድል እንደገጠመው፣ በጌታው በአሜሪቃና በተጨባጭ በአገሩ ሁናቴ ተገፋፍቶ፣ የኅብረብሔርነት ሽፋን ለመስጠት ሲል ኢሕአዴግ የተባለ የዳቦ ስም በመስጠት የመርሀግብሩ አስፈጻሚዎች እንዲሆኑ በየክልሉ የየብሔራቸው ምስለኔዎቹ እንዲሆኑለት አስተማማኝ ናቸው ያላቸውን መልምሏል። ይኸ የወያኔ አወዳሽና አጐንባሽ የጐጠኞች፣ የአገርና የወገን ካጆች ክበብ የሞላው በሌላ ሳይሆን በኢሕአፓ አባላት እንደሆነ ለመረዳት ሌላውን ሁሉ ትቶ እነታምራት ላይኔን የመሳሰሉ ያሉበትን ግዙፉን የአማራን ክልል ብቻ መመልከቱ ይበቃል።

ኢሕአፓዎችና ጀሌዎቻቸው ብዙውን ጊዜ አጉራ ሲጠናባቸው፣ እንደመከላከያ የሚያነሡት ለእምነቱ ሲል የደርግን መድፍ ሳይፈራ በመቋቋም በጦር ሜዳ ላይ ሕይወቱን የሠዋውን የወጣት ብዛት ነው። የዚህን አስተሳሰብ ፈር ከተከተልን መዘዙ አስፈሪ መሆኑ አይካድም። ከፍተኛ ጥፋትና ውድመትም ሊያመጣ ይችላል። በአሜሪቃን የርስበርስ ጦርነት ጥቁሮች ጭንቅላታቸው ከዝንጀሮው ስለማይበልጥና ከሰው ልጅ በታች ስለሆኑ ከነጭ ዘር እኩል ሊታዩ አይችሉም ብለው ጦርነት የቀሰቀሱት የጥምረት መንግሥት (ኮንፌዴራሲ – Confederates) ኀይሎች፤ የአንድመቶ ዐሥርሺ አንድመቶ (110,100)  ሰዎችን ሕይወት በከንቱ በጦር ሜዳ ላይ ሠውተዋል። የሟቾቹ ቁጥር በመላው የአሜሪቃን ታሪክ ወደር የሌለው እንደሆነ ይታወቃል። ይኸም ሌላው ከፍተኛ ውድመትና ምስቅልቅል ሳይቈጠር ማለት ነው። ታዲያ የአንድነት (ዩኒዮኒስት – Unionists) ኀይል መድፍ ስላላስፈራቸውና ብርቅ ሕይወታቸውን ስለሠው ብቻ የባለጥምረት መንግሥት ኀይሎች በራእያቸውና በዓላማቸው ትክክል ነበሩ ማለት ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ከሚሉት ዐይነት ወግ ይመሳሰላል። የኢሕአፓም ሁናቴ ከዚህ አይለይም።

ኢሕአፓዎች የተካኑበት ሌላም መስክ አለ። ሐቁ ሲነገራቸው አንዲት ብጣሽ ዐረፍተነገር እንኳን መዝዞ በማውጣት ሐሰቱ ከምን ላይ እንደሆነ ሳይገልጡ ጽሑፉን በጭፍኑ የውሸት ታሪክ ነው በማለት ማጥላላትና መኰነን አንዱና ዋነኛው ነው። ከዚያም ባለፈ ጸሓፊውን መሳደብ፣ ያልሆነ ስም በማውጣት ወይንም ከወራዳ ድርጅት ጋር በማያያዝ ማሸማቀቅ እንደሃይማኖታቸው ቀኖና አድርገው ይዘውታል፤  ሁለተኛ ባሕርያቸው እስከሚመስል ድረስ። ርግጥ፣ እውነት ትመርራለች። አንጐልና ቅንነት ያለው ሰው ግን በሆነ ባልሆነ መመጻደቁን ትቶ ብትመርም፣ ብታሳዝንም ብትከብድም እውነቱን በጀ ብሎ ይቀበላል፤ ይማራል፣ ይታረማልም። አጉራ ሲጠናበት አጠናና ተጠያቂነት የጐደለው ግልብ ሐተታ የሚጠበቀው ከጅልና ከጥራዘ ነጠቅ ብቻ ነውና።

በገዳይነቱና በጭካኔው ኢሕአፓ ከሕወሓት አያንስም። በማንኛውም መመዘኛ ከደርግ ይከፋል እንጂ አይሻልም ማለት ይቻላል። ይሁንና ሕወሓት ሥልጣን እንደጨበጠ ለቀድሞ የሽብር አጋሩ ለኢሕአፓ የዋለው ከፍተኛ ውለታ ቢኖር የቀይ ሽብር ፈጻሚዎችን ለፍርድ አቅርቦ ሲቀጣ፣  በኢሕአፓ ለተጨፈጨፉት የነጭ ሽብር ሰለባዎች ግን ደንታም አልሰጠም። ታሪክ ረስቷቸው ደማቸው ደመከልብ ሁኖ ቀርቶ ዛሬም የፍትህ ያለህ እያሉ እንደጮሁ ናቸው። ፍትህ የአሸናፊዎች ደንገጡር ናት ካልተባለ በስተቀር ለነሱም መልስ ሊሰጣቸው ይገባል። እነዚህ የሞቱት ኢሕአፓ በራሱ ቀስቃሽነት በጀመረው በነጭ ሽብር መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ ኢሕአፓ ቅንጣት የምታክል ልቦና ካለው፣ በዚህ የውደመት ተግባሩና ታሪኩ ማፈርና መጸጸት ሲገባው መኩራትና ሽር ጒድ ማለት ለትዝብት፣ ከዚያም ባሻገር በድርጅቱ ሰለባዎችና እሱም ባደረሰው በአገሪቷ ቊስል ዕንጨት ስደድበት ለማለት ካልሆነ በስተቀር ፋይዳው ግልጥ አይደለም።  የፍልስፍና አባት እንደሆነ የሚነገርለት ሶቅራጢስ “ያልተፈተሸ ሕይወት መኖር ብላሽ ነው” ያለው ዘይቤ የኢሕአፓና የተከታዮቹ  ዕጣ ፈንታ ሁኖ ከቀረ ቈይቷል። ከታሪኩና ከድርጊቱ ጋር ለመታረቅና ለመጣጣም የማይፈልግ ድርጅት ዐቅመቢስ ከመሆን ባሻገር ፋይዳቢስም እንደሆነ የሕይወት አመክሮ ይነግረናል። በዚህ ዕይታ ኢሕአፓ እያከበረ ያለው የሕያዌነቱን የወርቅ ኢዮቤልዩን ሳይሆን የሞት ተዝካሩን ነው ማለት ይቻላል። ገና ከጥንስሱ የሞተ ነበርና። ይኸም የድርጅቱ ህልውናና ማንነት ትክክለኛ መግለጫ መሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም።

“ከታሪክ መድረክ – ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትናንትናና ዛሬ” ከተሰኘው መጣጥፌ የተቀነጨበ። መሉዉን መጣጥፍ ለማንበብ ከፈለጉ በዚህ ያገኙታል። ማስፈንጠርያውን ይጫኑት።  https://www.academia.edu/82676278

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop