በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪዎቹን ሕወሓትና ሸኔ የመቃወም እና ለመከላከያ ድጋፍ የሚሰጥ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው፡፡
ነዋሪዎቹ ለመከላከያ ሰራዊቱና አብረውት ለቆሙት የፀጥታ ኃይሎች ያላቸውን ድጋፍ በመግለፅ፤ የሕወሓት የሽብር ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች እፈፀመ ያለውን ድርጊት የሚያወግዝ ሰልፍን ነው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እያካሄዱ ያሉት፡፡
ሰልፎቹ በመላ ኦሮሚያ በመካሄድ ላይ ሲሆኑ ሁለቱ የሽብር ቡድኖች (ሕወሓትና ሸኔ) አገርን ለማፍረስ ይዘው የተነሱትን እንቅስቃሴ እንደሚታገሉትና ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንደሚሰለፉ የሚገልጹ መፈክሮችን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
“የአገር መከላከያ ሰራዊታችን ሕዝባዊ ነው፤ ከሰራዊቱ ጎን መሆናችንን በድጋሜ እናረጋግጣለን፤ ኢትዮጵያ በልጆቿ መሰዋዕትነት ትቀጥላለች፤ ጣላቶቻችንን ደምስሰን የኢትዮጵያን ትንሳኤ እናረጋግጣለን” በማለት ሰልፈኞቹ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።
እንዲሁም ‹‹የወያኔ እና ሸኔ የጭካኔ እርምጃዎችን አጥብቀን እናወግዛለን፤ አሸባሪውን ቀብረን የኢትዮጵያን እድገትና ብልፅግና እናስቀጥላለን›› ሲሉም ተደምጠዋል።
ከእንግዲህ ኢትዮጵያዊያን የአሸባሪን ቡድን ግፍና መከራ የሚሸከሙበት ትከሻ የላቸውም ያሉት ሰልፈኞቹ ቡድኖቹን ዳግም እንዳያንሰራሩ አድርገን እንቀብራለን ሲሉም ቃል ገብተዋል።
በደረሰ አማረና ሚልኪያስ አዱኛ
ዋልታ