እንደ ይሁዳ ከዱ ልጆችሽ ሸፈጡ
እንደ ኤሳው ሆኑ ቡክርናቸውን ሸጡ
በመታመን ፋንታ ኑፋቄን መረጡ።
እንደ ባህር አሸዋ – እንደ ሰማይ ከዋከብት
ምነዋ ኢትዮጵያ… በዛብሽ ጠላት?…
አፈርሽ ‘’ሰለሰ’’ ሜዳሽ ‘’አሜክላ’’ እሾክ አበቀለ
ተራራ ሸለቆሽ ‘’ጃርት’’ ተራባበት – ተራብቶም ፏለለ፤
ባላና ማገርሽ፣ ምሰሶሽ ተማሰ
ዞብ አምባሽ ተናደ፣ ወንዝሽ ደፈረሰ
ደም እንደ ጎርፍ ውሀ፣ በገላሽ ፈሰሰ
ውጭ ውስጥሽ ነቀዘ፣ ቤት አጉራሽ ፈረሰ
ምነዋ ኢትዮጵያ… ምፅአት ለአንች ደገስ?
የሚታመን ጠፋ፣ ለሰው ልጅ ያደረ
ውሸት ገኖ ናኘ፣ በቀየሽ ከበረ
ዘብጥያ ወረደ፣ እውነትም ታሰረ
ታሪክ ተረት – ተረት ብስራት ተበሰረ፤
የውርጃ ‘’አደፍ’’ ቅሪት – ጭንጋፍ አሳድገሽ
‘’ቃልቻ ዘር – ጎጥን’’ ደም ተጠማልሽ
ጉድ ውልዶ ‘’አነበረ’’ ጊዜ ማህፀንሽ
ምነዋ እናት ምድር… ያልታየ ታየብሽ?
በቆብ ደፊ ‘’ሻሻም – ቀሳሽ መሳይ ኮከብ ቆጣሪ ‘’
በቀን ሰባኪ፣ ማታ ጎፈሬ አበጣሪ
በደብተራ፣ ረጅም ተላባሽ፣ ካባ ተሞሻሪ
በዘንግ ተውረግራጊ – ወገብ አሳሪ፤
ማህደረ ቅርስ ‘’ፅባወተ – መምበርሽ’’ ታምሶ
በዛር ፈረስ ደመ ነውጠኛ፣ መቅደስሽ ‘ረክሶ፤
የዓምላክ ጻድቅ – ሰማአታትሽ ማደሪያ
ተቸበቸበቸበ ወ’ቶ ባደባባይ ደርቶ በገብያ
ታበዩ በእግዚአብሔር ምነዋ ኢትዮጵያ…?
አንድ ቀን ለተለበሰ ‘’ጥቁር ካባ’’ ለተደፋ ‘’ጥቁር ቆብ’’ በሚሉ ከ’ኔ ወዲያ የለም፣ ልሂቅ – አዋቂ ለሀገር የሚያስብ በሚመስላቸው እነሱ ብቻ የሆኑ ህዝብ፤ እየተራበ ያጠገባቸውን – እየታረዘ ያለበሳቸውን ሳይማር ያስትማራቸውን – ሳይከፍሉት የከፍላቸውን እየናቁት ያከበራቸውን – እየሞተ ያኖራቸውን በረሱት – በከዱት የገዛ ማንነት ወገናቸውን፤ በ’ነ ከረባት ….. ማ’ረጋቸው
በ’ነ ሆድ ….. አምላካቸው፤
በነሰለጠን ባይ ደንቁረው አደንቋሪ፣ ውስጠ ‘’አንኮላዎች’
ያልሆኑትን ለመሆን፣ በመስሎ አዳሪ፣ ህሊና ቢስ ሸፍጠኞች
በጥራዝ ነጠቅ ‘’ርዕዬት አለም’’ ሰባኪዎች
ያዩትን ያላዩትን ናፋቂ፣ በብልጭልጭ ኰተት ጎታች፣ ተሸካሚዎች
የሀገር ርዕይ በሌላቸው – በቅዥታም ተቀጥላ ጅራቶች፤
ተገዘገዝሽ!… ተቦረቦርሽ!… ተከፋፈልሽ!…
እንደ ቅርጫ ስጋ ገነጣጠሉሽ – ቸበቸቡሽ!
ምነዋ ኢትዮጵያ …?
ምነዋ ኢትዮጵያ …?
ባጠባሽ ተነከስሽ – ባጎረስሽ ተበላሽ
አመድ አፋሽ ሆነ የዚህ ዘመን እጅሽ።
ወግ ነው ሲዳሩ እንዲሉ ‘’ተማሪ’’ ነኝ በሚሉ
ይይዙትን አ’ተው ይጨብጡትን በዋለሉ
በመማሪያ የብዕር ደም ብልቃጥ፣ ውሀ በሞሉ፤
በኮሌጅ – ዩኒቨርስቲው በየትምህርት ቤት
የሚማሩት የሚያገኙት፣ የእውቀታቸው አይነት
የአድማሳቸው ልዕልና፣ የ’ርካታቸው ጥማት
የወጣትነት ህይወታቸው፣ የጥበባቸው እድገት፤
አባትን ሳያውቁ አያትን መጠየቅ
ሱሪ በአንገት ማጥለቅ – በጎጥ እድር መድረቅ፤
ዲስኮ …ጫት …ሀሽሽ ‘’ፓሪ’’ መንጎድ
ምነዋ እናት ሀገር …. ምነው ጠፋ ትውልድ።
እንደ ይሁዳ ከዱ ልጆችሽ ሸፈጡ
እንደ ኤሳው ሆኑ ቡኩርናቸውን ሸጡ
በመታመን ፋንታ ኑፋቄን መረጡ።
እንደ ባህር አሸዋ – እንደ ሰማይ ከዋከብት
ምነዋ ኢትዮጵያ… በዛብሽ ጠላት?…
ባህር-ወደብሽን፣ ልጆችሽን አ’ተሽ
ዙሪያሽ እሾህ ሆኖ፣ በጠላት ተከበሽ፤
እንድነት ተረስቶ፣ መደማመጥ ጠፍቶ
የባዕዳን መሳሪያ፣ አገልዩ በዝቶ፤
ርሀብ – እርዛት፣ ሰቆቃና ስደት
ስም መጠሪያሽ ሲሆን፣ አንች ባለሽበት፤
እርስ-በርስ መባላት፣ ትውልድን ሲጨርስ
የፍትህ ያለህ ባይ፣ ዓለምን ሲያዳርስ
እኛ ማለት ቀርቶ ‘’እኔ ብቻ’’ ሲነግስ፤
ወገኑን – ወገኑ ገሎ ሲፎክር
ሀውልት ሲገነባ፣ በአንች ምድር አፈር
ምፃ’ተኛ ሲኮን በገዛ ሀገር፤
ትንሳኤሽ ደረስ ብለን ስናናፍቅ
ጥላ ሲሆንብን ፣ ስቀርበው ሲርቅ፤
ጥቂቶች ሲስቁ፣ ብዙሀን ሲያለቅስ
ኃጢአት ተትረፍር፣ፎ ፅዋው ሞልቶ ሲፍስ
ዘመን አልፎ ዘመን- ዛሬም ደም ስናፈስ
ምነዋ ኢትዮጵያ…?
ምነዋ እናት ምድር… ዝም አለ የአ’ች ነፍስ?
ፍርድ ስጭ ዝም አትበይ፣ ተይ አትታበይ
ዋጋ ይከፈለው፣ በዳይ – ተባዳይ
ይቅርም አባብይን ወደፊት እ’ድናይ።…
የነፃ ህዝብ መልኩ ሰንደቅ አላማቸው
ባላደራ እናት ነሽ ቅርስ ያ’ርነታቸው።
አለሁ ካልሽ አለው በይ መስክሪ በራስሽ
ከአንገቱ ተቃንቶ ማየት የሚሽ ይይሽ።…
ታላቅ እንደነበርሽ፣ ታላቅ ትሆኛለሽ
ኑሪ ለዘላ’ለም ፣ ዓለም ኢትዮጵያ ነሽ።
—–//—— ፊልጶስ
e-mail: philiposmw@gmail.com
***ይህ ”ምነዋ ኢትዮጵያ ” የተሰኘ ግጥም የጻፍኩት ከአስር ዓመት በፊት ሲሆን በአንድ ወቅት ለብዙሃን መገናኛ ቀርቦ ሲዘዋወር ነበር። አሁን እንዳንድ ጓደኞቸ እንደገና እንዳቀርበው ስለጠየቁኝና እኔም ስለአምንኩበት፣ መጠነኛ ማስተካከያ አድርጌ ለእንባቢዎች አቅርቢያለሁ።****