March 16, 2013
26 mins read

ኧረ የፍትህ ያለህ !! ያለ ነፃነት መኖር በቃን! በቃን መኖር ሰለቸን ! ለውጥ ያስፈልጋል!

ከዘካሪያስ አሳዬ
ዘካሪያስ አሳዬ
(ኖርዌይ)
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖር እና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ዜጎች በእኩልነት ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ የሚያስቡ፣ የሚናገሩ፣የሚፅፉና የሚቆረቆሩ በጠቅላላው ለእነዚህ ፅንስ ሐሳቦች ዘብ የሚቆሙ በሙሉ የስርዓቱ ጠላቶች ተደርገው በመቆጠር ላይ ናቸው::
ለአገሪቱ አንድነትና ሉአላዊነት ብልፅግና በጣም ከሚቆጠሩ መሪዎቿና የፓርቲአቸው ጠባብ ጎሰኛ ፖሊሲ የተለየ የሚያስቡ ዜጎችና ቡድኖች ሁሉ ጠላትና ሽብርተኞች ወይንም አሽባሪዎች ወይም በዘመኑ አባባል ጽንፈኛ ተደርገው ይቆጠራሉ።

በመሆኑም ህውሃት/ወያኔ <<ሽብርተኞች>> የሚላቸውን ለማሽበር ለማፈን ያወጣው ህግ አገርንና ዜጎችን በማሸበርና ንጹሓንን በየእስር ቤቱ በመወርወር ላይ ከመገኘቱም በላይ ሕገ መንግስቱንና የአገሪቱን የፍትህ ስርዓት ለጊዜአዊ ስልጣንና ጥቅሙ በመርገጥና በማዋረድ ላይ ይገኛል::
ሕዝብ አመኔታ ያልሰጠው መንግስት በምንም መመዘኛ ታማኝ ሊሆን፣አገርን ሊያስተዳድር አይቻልም። በዜጎች ድምፅና ፈቃድ ሳይሆን በጦር መሳሪያና በማጭበርበር ስልጣኑ እንደተቆጣጠረ ስለሚያውቀው እንደ መንግስትለሚያስተዳድረው ሕዝብ እምነትና ፈቃድ አይጨነቅም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማሕበራዊ ዘርፍ የሚከተላቸው ፖሊሲዎች… የሚያፀድቃቸው አዋጅና ህጎች የሚያወጣቸው ደንቦችና መመሪያዎች የሚሰይማቸው አስፈጻሚ አካላት… በህዝብ ፈቃድ ላይ የተመረኮዘና ለህዝብ ዘለቄታ ጥቅም እንዲአበረክቱ የሚታሰብላቸው አይደሉም።
አምባገነኖች ከስልጣን ወንበራቸው ውጭ አርቀው መመልከትም ሆነ ማየትም አይሹም አንድም ከስህተቶቻቸው ሁለትም ከቀደም ቢጤዎቻቸው ውድቀትና ውርደት በመማር እራሳቸው ለመለወጥ ከህዝባቸውና ከፖለቲካ ተጠቃሚዎቻቸው ጋር እርቅ ለመፍጠር ቅንነትና ፍላጎት የላቸውም::
የዛሬውን እንዴት እንደተቆናጠጡት ስለሚያውቁት ነገ የእነሱ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደሉም ወደዱም ጠሉም ትተውት በሚያልፉት ስርዓት ዉስጥ የፈጸሟቸው እኩይ ተግባራት ሊያስከትሉ የሚችሏቸው አገራዊ ቀውሶች በግልም ሆነ በጋራ ተጠያቂነት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ግን አያጡትም። ዋጋም መክፈላቸው የት ይቀርና !!
ነገ በታሰባቸው መጠን ዘወትር ዉስጣቸው ይረበሻል። የዛሬው ማን አለብኝነት ሕገ_ ወጥነትና የበላይነት ከነገው ተጠያቂነት ውርደትና ቅሌት
አንፃር በሩቅ እየታየ ሠላም ይነሳቸዋል፣ ይረብሻቸዋል፣ ያሻብራቸዋል በመሆኑም ዘወትር ሕዝቡን ሰላም ይነሳሉ ያሸብራሉ በየጊዜው እየበረገጉ እንደሚኖሩ ሁሉ ሕዝብን በፍርሃት ለማስበርገግ እንቅልፍ ያጣሉ::
ይህ የአምባገነኖች የጋራ ባህሪ ነው ነገ የነሱ እንዳልሆነ ተስፋ በቆረጡ መጠን ለነገ ብሩህ ተስፋ የሰነቀ ሁሉ ሰላም የሚያሳጣቸው የሚረብሻቸው ፀረ ሰላም አሸባሪ ጠላት የሆነ ኃይል ነው መስሎ የሚታያቸው። በመንግስት ላይ የሚንፀባረቀው የተስፋ መቁረጥ ባህርይ ከኢትዮጵያ አልፎ ጎረቤት ሐገሮችን ተሸብረው እንዲያሸብሩ ምክንያት መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም። አይቀሬው ውድቀትና ውርደት የሚያባንነው አገዛዝን ሕዝብን በፍርሃት እያሽማቀቀ ቀን ከመግፋት ባሻገር አርቆ ማየት አልቻለም ስለ ውድቀታቸውና በምትኩ ነገ ሊኖር ስለሚገባው የህግ የበላይነት ግልፅነት ተጠያቂነት በስውርም ይሁን በግልጽ የሚያስቡ የሚናገሩ የሚጽፉ ሁሉ የስርአቱ ጠላቶች ናቸው። ስለሆነም የስርዓቱ ጠላት እና ሽብርተኞች ወይንም አሽባሪዎች ተደርገው ሊከሰሱ የሚችሉበት ጭፍን ህግ ተረቅቆና በመለስ አሻንጉሊት ፓርላማ ጸድቆ የስርዓቱ ዘብ በመሆን ያገለግላል።
የፀረ ሽብር ሕጉ በአፈፃፀም ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከመነሻውም ዓላማው ህውሐት/ወያኔ ተቃዋሚዎቹንና በተሳሳተ ፖሊሲዎቹ ላይ ነፃ አስተያየት የሚሰነዝሩበትን ተቺዎች ለማሽበርና ለማፈን ያወጣው በራሱ መንግስታዊ ሽብርን ለማስፋፋት የተረቀቀና የፀደቀ ነው።
ሕጉ ዜጎች ሃሳብን በነፃነት ለገንቢ ዓላማ መግለጽ እንዳይችሉ ለማፈን በሕገ መንግስት የተቀመጡ የዜጎች ማህበራዊና ግላዊ ነፃነቶች የሚጋፉ አስገዳጅ ሁኔታዎች …የሐገር ብሔራዊ ደህንነት…የሕዝብ ሰላም…በሚሉ ግልፅነት በጎደላቸው አንቀፆች እንዳሻው ሊተረጎም በሚችል ገደብ ባጣ መልክ መንግስት ሊያፍናቸውና ሊያጠቃቸው የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች ቡድኖች ብቻ ሳይሆን የሐገሪቱ የበላይ የሆነውን ህገ መንግስት በመርገጥ የፍርድ ቢቶችንና የአስፈፃሚ አካላትን መብት በመጣስ የፍትህ ስርዓቱን የጠባብ ዘረኛ ቡድን ፍላጎት ማስፈፀሚያ መሣሪያ ለማድረግ የታለመ ነው።
በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ አመለካከታቸው በህብረተሰቡ ተቀባይነት ያላቸውን የህዝብ ወገኖች ለማዳከም፣ በጠባብ ዘረኝነት ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ ስርአቱ አገልጋዮችን ስልጣን ጥቅም ለማስጠበቅና ሐገራዊና ብሔራዊ ተቆርቋሪነት ለማጥፋት የተረቀቀ ነው።
በሰላማዊ መንገድ መስተናገድ የሚገባን የህዝብን ድምፅና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማፈን በሐሰት ሽፋን የሚመሰረቱት ተራ ወንጀሎች በሂደት ትርጉም አተው ሐገርን የሐሰተኞች፣ የወንጀለኞችና በሃይል እርምጃ ድምፃቸውን ለማሰማት ፍላጎታቸውን ከግብ ለማድረስ የሚቆሙ ዜጎች መፈልፈያ እንዳያደርጋት ያስፈራል::
ህጋዊነትን ያልተከተለ አካሔድ ህገ ወጥነትን እንደሚያስከትል ግልፅ ነው። ህወሃት/ወያኔ እንደ መሳሪያ የሚገለገልበት የፀረ ሽብር ህግ የፍትህ ስርአቱን ሙሉ በሙሉ እያሽመደመደው እንደሆን በጽናት ቆመው መናገር ያለባቸው ከማናችንም ይልቅ በቅድሚያ የህግ ባለሞያዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል። የፍትህ ስርዓት አለኝታ የማይሆነው ህብረተሰብ ኑሮው አንድም እስር ቤት ተፈርዶበት ሁለትም ሸሽቶ በፋኖነት ከመኖር ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም።
ይህ በየጊዜው በመበርገግና በመሸበር በደንቆሮ ግምት እነ ወያኔ/ህውሃት በህግ የሚመሩ ለማስመሰል የሚወስዱት እርምጃ የሐገሪቱን የፍትህ ስርአት አደጋ ውስጥ እንደጣለው እንረዳለን ።
በሃሰት ክስ ወንጀለኛ ለማድረግ የሚፈፀመው የተሳሳተ ተግባር የዜጎች በጋራ አብሮ የመኖርና የመከባበር መሰረት በሆነው ፍትህና ዳኝነት ላይ ይቅር የማይባል ከፍተኛ ወንጀል እየፈፀመ መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል።
በእርግጥ << እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል >>በሚል እምነት የታወሩ መሪዎች የዛሬን እስከ ታደጋቸው ድረስ ነገ የእነሱ ባለመሆኑ የፍትህ ስርአቱ ሊገጥመው የሚችለው አደጋ ደንታ አይሰጣቸውም።
በመፈጸም ላይ የሚገኙት ወንጀል ነገ የሚኖረው ማህበረሰባዊ ጉዳት በሃገርና በወገን የወደፊት ሚዛናዊ ህይወት ላይ የሚያሳርፈው አንድምታ እና ትቶት የሚያልፈው ጠባሳ በቀላሉ እንደ ማይታይ በትክክል መገንዘብ የሚችሉት በህግ የሚያምኑ ኃይሎች ብቻ ናቸው።
የፍትህ ስርአቱ መሳቂያና መሳለቂያ የሆነበት ዜጋ ዋስትና የሌለው ነው ህይወትና ትርጉም የማይሰጡት ዜጋ ነው። መብቱን የሚያስጠብቅለት ጥቃቱን የሚከላከልበት ኃይል የሌለው ዜጋ መሸሸጊያ ካጣ ከዱር አውሬ
ተለይቶ ላይታይ ይችላል። ኃይልና ጡንቻ ፣ዉሸትና ቅጥፈት በሚገዙት ህገ ወጥ ስርዓት ውስጥ እንዲኖር የተፈረደበት እስረኛ አድርጎ ራሱን እንዲቆጥር ይገደዳል።
በሐሰት በ << አሸባሪነት >> ከተከሰሱት ከነ አንዱአለም አንዳርጌ እስክንድር ነጋ ሌሎች በሐገር ዉስጥም ዉጭም ያሉ ተከሳሾች በላይ ዛሬ ወያኔ/ህውሃት ለስልጣን እድሜአቸውን ማራዘሚያ እንዲያገለግሏቸው ክብር የሚያሰጧአቸው ዳኞችና የፍትህ አካላት ወንጀል እየተፈፀመባቸው እደሆነ በህግ የበላይነት የሚያምን ሁሉ ልብ ይለዋል።
የፀረ ሽብር አዋጅን በመጠቀም በፍትህ ላይ የሚፈፀመው ይህ ወንጀል ከተራው ዜጋ ይልቅ በቅድሚያ ሊያስጨንቅና ሊያሳስብ የሚገባው ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩትን ባለሞያዎች መሆኑ አያጠያይቅም።
ከፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ ታች በዘርፉ የሚያገለግሉትን የህግ ባለሞያዎቻችን ሁሉ ህሊናቸው በፈቀደ መጠን በቅንነት ለማገልገል በምህላ የተቀበሉት ክቡር የስራ መስክ ነው። አንፃራዊ በሆነ እኩልነት የዜጎች ማህበራዊ ግንኙነት እንዲጠበቅ ሃላፊነት የተቀበሉና የሞራል ግዴታ የተጣለባቸው ዜጎች ተደርገው ስለሚቆጠሩ…………
ወያኔ/ ኢህአዲግ መንግስት ቀናቸው ደርሶ ከመንበራቸው ሲወርዱም ሆነ ሲዋረዱ ዳኞቻችን እንደደረቡት ካባ አውልቀው የሚጥሉት ሙያ አይደለም።
ዛሬ በሃሰት የወንጀል ክስ የተሰየሙት ዳኞችና አቃብያን ህጎች ከህወሃት\ኢህአዲግ ስርአት ዉጭ ነገ ሞያቸውን መተዳደሪያችን አይሆንም በማለት ሌላ የሙያ ስልጠና ወስደው ሌላ ሙያተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ላንጠራጠር እንችላለን ። ይሁንና የህግ እውቀታቸው በተሰየሙበት መንበር የሰጡትን ብይን የፈፀሙትን ተግባር በየአጋጣሚው እያነሳ የራሳቸው ህሊና ዳኝነት እየሰጠ ሰላም እንደሚነሳቸው ግልፅ ነው ። በማህበራዊ ህይወታቸው ውስጥ የትም ይሁኑ የት የህግ ሰዎች ናቸውና የተዛባ ዳኝነትና ሚዛናዊ ያልሆነ ዉሳኔ በገጠማቸው ቁጥር በድፍረት<< ይህ ዉሳኔ ትክክል አይደለም>> ብለው ለማለት የሞራል ብቃት አይኖራቸውም። እንደ ሰው የሚያስቡ እስከ ሆነ ድረስ ዘወትር ህሊናቸው ይሞግታቸዋል። እስከ እለተ ሞት በህሊና ባርነት ዉስጥ ከመውደቅ በላይ የሚሰቀጥጥ የፍርድ ዉሳኔ የለምና።

ህወሃት/ወያኔ ጠባብና ዘረኛ የፖለቲካ አላማውን ከግብ ለማድረስ ላለፉት 21አመታት በመንግስት ስልጣን ላይ ተቀምጦ በፈፀማቸውና ዛሬም በሚፈጽማቸው መንግስታዊ የሽብር ተግባሮች ምክንያት የሐገሪቱ አንድነትና ሉአላዊነት እንደተሸረሸረ ፣ ሐብትና ታሪካዊ ቅርሶቹ አለ አግባብ እንደተዘረፉ ዜጎቿ እስራት፣ እንግልት፣ ድብደባ ፣ሰቆቃና ግድያ እንደደረሰባቸው አለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች በየጊዜው ይፋ ያደረጉት ሃቅ ነው።ከጥቅማጥቅም ታግዶ የንብረት ባለቤትነቱን ተነጥቆ…. የገጠሩ አነስተኛ ገበሬ ለባእዳንና ለባለ ሐብቶች…..ጥቅም ከይዞታው ያለ ፈቃዱ ያለ መጠጊያና ያለ ዋስትና ተፈናቅሎ… .ረሀብ ድህነት እና ግፍ ያስመረረው በሌላ በኩል ቤተሰቡን ወገኖቹን የሚወደውን አካባቢና ታሪካዊ ሐገሩን ጥሎ መሰደዱን የባዕድ መሬትና ድንበር ሲያቋርጥ በማያውቀው ምድር ለእስር መዳረጉን በባህርና በየበረሃው ወድቆ መቅረቱን በጠቅላላው በዜጎቿ ላይ ስለደረሰውና በመድረስ ላይ ስላለው ግፍና በደል ከኛ ይበልጥ በርካታ የውጭ ምሁራንና አለም አቀፍ ድርጅቶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ያለ ነፃነት መኖር በቃን! በቃን መኖር ሰለቸን ለውጥ ያስፈልጋል ??? አረ የፍትህ ያለ !!!

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በግል የስልጣን ጥቅምና ጠባብ የጎሰኝነት አላማ በታወሩ መሪዎች ስንገዛና ውርደት ሲደርስብን በወያኔ/ ህውሃት አምባገነን አገዛዝ በታሪካችን የመጀመሪያው ነው።
ይህ ሁሉ ህገ መንግስቱን በመርገጥ የሚፈጸመው … ዜጎችንና አገርን የሚጎዳ አካሄድ የህግ አግባብነት እንዲኖረው ፍትህና ርትእ የሚነግሱባት ስርአት እውን እንዲሆን… በኃይል ሳይሆን በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ… ከማናችንም በላይ በቅድሚያ እንደ ዜጋ ድምፃቸውን
ማሰማት በተለያየ ዘዴ ቁጣቸውን መግለፅ የነበረባቸው የሃገራችን የህግ ባለሞያዎች ናቸው ቢባል ስህተት አይሆንም ከነሱ ውጭ ለሕግ ጥብቅና ሊቆም የሚችል ኃይል ከቶው ሊኖር አይችልምና።
በፓኪስታን፣ በህንድ፣ በቱኒዚያና በግብፅ የህግ ባለሞያዎች የህዝብን አመፅ በግንባር ቀደምትነት መርተዋል የሙያ ማህበራቸውን ጊዜያዊ የዜጎች መብት ማስከበሪያ ተቋም በማድረግ አደራጅተዋል… በሕዝባዊ አመጾች ወቅት የመንግስት ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸሟቸውን የህግ ጥሰቶች መዝግበው ይዘዋል… ለሰብአዊ መብት አስጠባቂ ድርጅቶችና የውጭ አገር የዜና ማሰራጫዎች ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል።በተለያዩ የውጭ አገሮች ውስጥ የሕግ አውጪ አካላት ከሕዝባቸው በተሰጣቸው ህጋዊ ውክልና መሰረት የዜጎችን ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር መንግስታቸውን ይነቅፋሉ ይተቻሉ።ከዚህ አልፈው ተርፈው ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው በፓርላማ ውስጥ እስከመደባደብ የደረሱበትን ሁኔታ ታዝበናል።
በርግጥ እኛ ለዚህ አልታደልንም ፓርላማችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰነዝራቸው ያልታረሙና ስነ ምግባር የጎደላቸው አባባሎች የሚያስፈነድቋቸው ለህዝብ ሳይሆን ለመለስና ድርጅታቸው ተጠሪ የሆኑ የአሻንጉሊቶች ስብስብ መሆኑ አይጠፋንም።አሁንም ያሉት ጠ/ሚኒስተር ተብየው እሳቸው መስለው ቁጭ!
የህግ ባለሞያዎቻችን ለህጉ አተረጓጎምና አፈጻጸም አገራዊ ሃላፊነት ስላለባቸው ስብእናቸው ፈተና ውስጥ መውደቅ ነበረበት። የስርዓቱ ተጠቃሚ በመሆናቸው በህሊና ባርነት የሚታሰሩበትን ምክንያት ሊኖር ባልተገባ ነበር።
የደረቡት ካባ የተሰየሙባት ችሎትና የተጣለባቸው ማኅበረሰባዊ ግዴታ ከፊት ለፊታቸው በተከሳሽ ሳጥን ውስጥ በሰንሰለት ታስረው ለሚቆሙ ፍትህ ፈላጊ ወገኖች ሚዛናዊ ዳኝነት ለመስጠት የሚያስችላቸውን የአእምሮና የሞራል ጽናት ሊያድላቸው በተገባ ነበር። ግን ለዚህ አልታደልንም ከህሊና ነፃነት ይልቅ ባርነትን ከሞራል ፅናት ይልቅ ውድቀትን የመረጡ የህግ ባለሙያዎች ለፍትህ ስርዓታችን ዘብ መቆም አልቻሉም።
ሚዛናዊ ፍትህ ለማግኘት ፍርሀት እልህና ሲቃ እየተናነቀው ….. ዓይን ዓይናቸውን እየተመለከተ ታስረው በማእከላዊ እስር ቤት ግፍ ተፈጽሞብኛል። ከወንጀል ምርመራ ሃላፊ እስከ ታችኛው ወንጀል መርማሪ ሰራተኛ ድረስ ያሉት አንድ ላይ ሆነው ልብሴን ሙሉ በሙሉ አስወልቀው ውሃ እየደፉብኝ ለ23ቀናት አሰቃይተውኛል ። እነሱ የሚፈልጉትን እንድናገር ጠይቀውኝ አልናገርም በማለቴ 7 ቀን ምግብ እንዳልበላ እነሱ የሚሉኝን የማልናገር ከሆነ አትቀመጥም አትተኛም ብለው በቁም እንድሰቃይ አድርገውኛል እጄን ወደ ኋላ አስረው አሰቃይተውኛል ድብደባና ግርፋት ደርሶብኛል…..በደልና ግፍ ተፈጽሞብኛል……በማለት ቤተሰብና ህዝብ ታዛቢ በሆነበት ችሎት ላይ አቤቱታ እየቀረበ ……..
የአቃቤ ህግ ምስክር <<……እንዲህ ብለህ ተናገር ተብዬ ነው የመጣሁት…… ፖሊስ እንዲህ ብለህ መስክር አለኝ….አሳየኝ ጠቆመኝ…. >> በማለት….ቅን ህሊና ያስገደደው ወጣት አዛውንት የቤተሰብ አስተዳዳሪ የልጆች እናት የከበዱና ምራቃቸውን የዋጡ በእድሜ የገፉ አረጋዊ የተማረ በሃላፊነት ላይ የነበረ ለሃገር ህልውና የተሰለፈ የጦር መኮንን …….. የገጠመውንና የደረሰበትን እውነት በአደባባይ ሲናገር ሲመሰክር…..በፍትህ መንበር ላይ ተቀምጦ በችሎቱ አዳራሽ ሁሉንም እያየና ጆሮው እየሰማ ለቀረበው አቤቱታም ሆነ ለተፈጸመው ህገ ወጥ ተግባርና ምስክርነት ህሊናው ኮርኩሮት አንዳች እልባት ካልሰጠ እሱ ከአምባገነን አዛዦቹ በከፋ መልኩ ህግ እያወቀ ፍትህን በመርገጥ ላይ እንደሚገኝ በድፍረት መናገር ይቻላል::
ክሱ የወንጀሉን አፈጻጸም ቦታና ጊዜ አያመለክትም ህገ መንግስታዊ መብትንና ሃገሪቱ የተቀበለችውን አለም አቀፍ ድንጋጌ ይጻረራል በማለት
የተከሳሽ ጠበቆች ለሚያቀርቧቸው የክስ መቃወሚያዎች ምንም አይነት ግንዛቤ የማይሰጥ ዳኛ አካሉ እንጂ ህሊናው በችሎት ወንበሩ ላይ ተሰይሟል ለማለት አስቸጋሪ ነው።
በዚህ ፍትህ ባጣ ህዝብ ላይ የገዢው መንግስት ሲጫወትበትና ሲቀልድበት ማየት የተለመደ ሆኗል <<ኧረ የፍትህ ያለህ! >> በዚህም ምክንያት የፍትህ ስርአቱ ሲዋረድና ፣አልፎ ተርፎ የህግ አዋቂዎቻችን ለፍትህ ስርዓቱ ዘብ በመቆም ፈንታ ደንታ ቢስ ሲሆኑ መመልከት እጅግ ያሳስበናል ነገ የሚያስተዛዝበን ሌላ ቀን እንደሆነ እናውቃለንና…… ነገ ደግሞ በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም!
ለውጥ ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

ከዘካሪያስ አሳዬ( edenasaye@yahoo.com)

Go toTop