እንዲመለከቱን ሰማእታት ተምድር፣
ፖለቲካ ስሌት ቁማር ስንቆምር፣
እንደ ትንሳዔው ለት ተከፈት መቃብር፡፡
አሳደን አሲዘን በይሁዳ አስጠቁመን፣
ወንጀልን ለጥፈን ባሰት አስመስክረን፣
ተጲላጦስ ችሎት ቀፍድደን አቅርበን፣
ተሁለት ሺ በፊት ጌታን እንደሰቀልን፣
ዛሬም ሰማእትን ሙልጭ አርገን ክደን፣
ሰበብ እየፈጠርን ተገዳዮች ጋር ቆምን፡፡
እንደ ንጋት መስኮት ተከፈት መቃብሩ፣
ሰማእት በዓይን አይተው እርምን እንዲያወጡ፣
እነ ህሊና ቢስ እነ ሆድ አምላኩ፣
ተገዳዮቻቸው ዝሙት ሲፈጥሙ፡፡
ይህ አድግ ገዳይ ነው ስንል እንዳልነበር፣
ዛሬ በፍቅር አብደን ገባን ተጭኑ ሥር!
መደመርና ሱስ አብረው እያዜሙ፣
እርኩስን ተቅዱስ እያቀላቀሉ፣
ጥንቡን ተንጡሁ እያደባለቁ፣
ያችን የእምነት ምድር ጭምልቅ አደረጉ፡፡
መለኮት ፍጡርን በግብሩ ሲለየው፣
ብሩኩን ገነቱ ክፉን ሲኦል ሲለው፣
እርሱ ተስንት ጋኔን ውል ቢዋዋል ነው፣
ተኮናኙን ተጻድቅ አብሮ እሚደምረው?
ተከፈት መቃብር አሰፋን የዋጥከው፣
ተከፈት መቃብር አስራትን የያዝከው፣
ተከፈት መቃብር የሳሙኤል አወቀው፣
ተከፍት መቃብር ጎቤን የበላሃው!
የከሀዲውን ጉድ አጥንታቸው ይየው፡፡
የትግል ጓደኛ የቃል ሰዎች መስለው፣
ጀግናን በትግል ወቅት ተፊት አሰውተው፣
የተረፉትንም ተመንገድ ወርውረው፣
ማተብን እንደ ክር ቡጭቅጭቅ አድርገው፣
መሽኮርመም ጀመሩ ይህ አድግ ወሽመው!
ተከፈት መቃብር በደኖ ያለኸው፣
ተከፈት መቃብር የባሌ አርባ ጉጉው፣
ተከፈት መቃብር የአሩሲ ነገሌው፣
ተከፍት መቃብር ወልቃይት የራያው፣
ተከፈት መቃብር መተከል የሸዋው፣
አፈሩን ፈንቅሎ ይየን አጥንታቸው፣
ለኛ እንዲመች ብለን ዳግም ስንሰዋቸው!
ተከፈት መቃብር ጋንቤላ አዲሳባው፣
ተከፈት መቃብር የጎዴ የአዋሳው፣
ተከፍት መቃብር ብራዩ የጋሞው፣
በጅምላ በጅምላ እሬሳን የዋጥከው፣
አደራ እንደበላን ይረዳ አይምሯቸው፣
ዛሬም ጨፍጫፊዎች ተወንበር ላይ ናቸው፡፡
ተከፈት መቃብር ማጀቴ የቆምከው፣
ተከፈት መቃብር ጎንደር የተናስከው፣
ተከፈት መቃብር ወልዲያ ያለኸው፣
ተከፈት መቃብር ባህር ዳር የዋጥከው፣
ተከፈት መቃብር ታቦር የበላኻው፣
ተከፈት መቃብር ቡሬ የተማስከው፣
ሰማእት ይታዘቡ አንገት ቀና አድርገው፣
ስንጨፍር ስንደልቅ ተገዳዮቻቸው!
ሰማንያ ስድስት ነፍስ ስልቅጥ ያደረከው፣
ተከፈት መቃብር በቅርብ የተማስከው፣
ግንዙን ከፈኑን ተራስ አንሳላቸው፣
የሚዶፈውን ግፍ እንዲያየው ዓይናቸው፣
ደማሪው ገዳዩን በጦር ሲያሳጅበው!
በአጣና አስጠብሰህ ሥጋ የበላኻው፣
ቤተክሲያን ሰው አርደህ ደሙን የጠጣኻው፣
ተከፈት መቃብሩ ይጠና ዘራቸው፣
አቢይ አወርሞ የዘረዘራቸው፡፡
የሞተን አትርሳን ቀርጥፈን እንደ ሳር፣
ሙታንን አሲዘን ቁማር ስንቆምር፣
በወገናችን ደም ሊጥ እርሾ ስንጥል፣
በአጥንት መቆስቆሻ እንጀራ ስንጋግር፣
የፖለቲካ ትርፍ ዝሙት ስንመንዝር፣
ሰማእታት እንዲያዩን ተከፈት መቃብር!
ተከፈት መቃብር!!
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ታህሳስ ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.