September 14, 2019
17 mins read

ሳይቃጠል በቅጠል! ቁማር ትውልድ ገዳይና አገር አጥፊ ካንሰር! – ገ/ክርስቶስ ዓባይ

ገ/ክርስቶስ ዓባይ
መስከረም 3 ቀን 2012 ዓ/ም

ቁማር ለሰው ልጆች ሕይወት ጠንቅ ከሆኑ መጥፎ ልማዶች አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ይታወቃል። ቁማር ሲጋራ ከማጨስ ወይም የተለያዩ አንደንዛዥ እፆችን፤ ከመጠቀም በከፋ መልኩ የሚመደብ ሱስ የሚያስይዝ መጥፎ ልማድ ነው። በቁማር ሱስ የተለከፈ ሰው የተማረም ይሁን ያልተማረ የእራሱን ክብር የማይጠብቅ ፍጹም ተራ ሰው ይሆናል ። አንድን የቁማር ሱሰኛ በዚህ መልኩ ከገለጽነው፤ ለአገር ደግሞ ከፍተኛ ጠንቅና የማኅበራዊ ችግርን የሚጋብዝ፤ አልፎ ተርፎም ትውልድ የሚገድል፤ እንደ ካንሰር ያለ መድኃኒት የሌለው በሽታ ነው።

ቁማር ከጣሊያን ወጥቶ ወደ ኢትዮጵያ መቼ እንደገባ በውል ባይታወቅም አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በዚህ ሱስ ተለክፈው እስከ ሞት ለሚደርሰ የከፋ ጉዳት የተዳረጉ ሰዎች እንደነበሩ ይነገራል። የራሥ አበበ አረጋዊ ልጅ የነበረው ዳንኤል አበበ ባለግል አውሮፕላን ባለቤት እንደነበረ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በዚህ በቁማር ሱስ ተለክፎ ስለነበር በዚሁ ሳቢያ ከሚተዋወቀው ጣሊያናዊ ጓደኛው ጋር ወደ አሥመራ ሄዶ ሲመልስ ወሎ ላይ በመከስከሱ ለህልፈት እንደተዳረገ ይነገራል። በወቅቱ ለአደጋው መንስዔ ተብሎ የተወሰደው መላምት ከፍተኛ ገንዘብ ከከሰረው ጣሊያናዊ ጋር አየር ላይ በተደረገ ግብግብ አውሮፕላኗን የሚቆጣጠራት በመጥፋቱ በራሷ ጊዜ ከሰማይ ወርዳ ምድር ላይ እንደ ተከሰከሰች በስፋት ሲወራ እንደነበር አይዘነጋም።

ቁማር በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በ1960 ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት፤ በከፍተኛ ደረጃ ማቆጥቆጥ ጀምሮ እንደነበር በሕይወት የሚገኙ ሰዎች የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው። ከዚህም የተነሳ የቁማር ማሽኖች በአዲስ አበባ ከተማ በየቡና ቤቱ እየተተከሉ ስለነበር ብዙ ሰዎች ገንዘብ እናገኛለን በማለት ሲጫወቱ፤ ያላቸውን አያስረከቡ ባዶ እጃቸውን ይሄዱ እንደነበር ይታወቃል። አንዳንዶቹም ከንዴት የተነሳ ማሽኑን ለመስበር ሲጋበዙና አምባጓሮ ሲፈጥሩ ጸጥታ በመረበሽ እየተከሰሱ በፖሊስ ይታሠሩ እንደነበር ይገለጻል።

ቀስ በቀስም የችግሩ ስፋትና ጥልቀት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ በየቦታው መሆኑ ቀርቶ በአንድ ማዕከል ብቻ እንዲቋቋም ተደረገ። በዚህም ግዮን ሆቴል አካባቢ ካዚኖ የሚባል የቁማር መጨዋቻ ማዕከል ተቋቁሞ በይፋ ይሠራ እንደነበር ይታወሳል። ነገር ግን ታላቅ ምስጋና ለደርግ መንግስት ይሁንና እንዲህ ያለው ትውልድ ገዳይ ተቋም እንዲዘጋ መደረጉም አይዘነጋም።

በስፋት እንደሚወራውና እንደሚታወቀው በአሜሪካ ላስቬጋዝ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የቁማር ማዕከል፤ የተገነባው ሰው በማይኖርበት በርሃ ላይ እንደነበር ይነገራል። ይሁን እንጂ ሰዎች ቦታውን ለማየትም ሆነ ቁማር ለመጫወት ወደዚህ ቦታ መጉረፍ በመጀመራቸው በአሁኑ ሰዓት የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን እንደቻለም በይፋ ይተረክለታል። ይህንኑ ተከትሎ ሰዎች ሥራ ፍለጋ ቀስ በቀስ ወደ ላስቬጋዝ በመጓዛቸው በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የሚኖርበት ከተማ ለመሆን በቅቷል ይባላል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የቁማር ጨዋታ በስፋት እንደሚዘወተር ግልጽ ነው። በተለይ በሐዘን ጊዜ ሰዎች ከማስተዛዘን ይልቅ ቁማር ለመጫወት ይሰባሰባሉ። አንዳንዴም በሚፈጠረው አለመግባባት ከፍተኛ ጠብና አምባጓሮ እንደሚነሳ ታዛቢዎች በጸጸት ይናገራሉ። እንዲህ ዓይነቱ የማኅበራዊ ጠንቅ የሆነው ልማድ እንደ ባህል ሆኖ ለትውልድ እንዳይሸጋገር መከላከል አግባብ ነው።

የኤስያ አገር ሰዎች በከፍተኛ የቁማር ሱስ ልክፍት የተያዙ በመሆናቸው እንደ ታታሪነታቸውና ሠራተኛነታቸው መጠን የኑሮ ደረጃቸው ከቶውኑ ሊሻሻል አልቻለም። በፊሊፒንስና በኢንዶኔዥያ፤ አውራ ዶሮዎችን ፉክቻ (ትግል) በማሠልጠን ዶሮዎች ሲናከሱ ሰዎች ዙሪያውን ከበው ገንዘብ በማስያዝ ቁማር ይወራረዳሉ። በጣም የሚዘገንነው ነገር ደግሞ ከዶሮዎች እግር ላይ ምላጭና ስለት ነገር በማሠር ተወዳዳሪ ዶሮዎችን እየተለተሉ ደም በደም አድርገው እንዲሸነፉ ማድረጋቸው ነው። ከዚህም የተነሳ እጅግ ወደ ነፍስ ግድያ፤ ዘረፋና ወደ ተራቀቀ የስርቆት ወንጀል ድርጊት ውስጥ ተዘፍቀዋል። ቁማርተኞች ከአሁን አሁን አገኛኛለሁ በሚል ያልተጨበጠ ተስፋ ያላቸውን ሀብት በሙሉ ከአስረከቡ በኋላ፤ ተስፋ ሲቆርጡ ሕይወታቸውን ያጠፋሉ፤ ወይም ከሕግ ውጭ ገንዘብ ለማግኘት ከፍተኛ ወንጀል ይፈጽማሉ።

በበለጸጉ ሀገሮች እንኳ ሳይቀር ቁማር መልኩን ቀይሮ አገርና ትውልድ እያጠፋ ይገኛል። የሶሎግ ውሻ (ግሬይ ሀውንድ) ሩጫ ውድድር እና የፈረስ ግልቢያ ውድድር ያደርጋሉ። በዚህ ሁሉ ከመዝናናት አልፎ የገንዘብ ውርርድ በማድረግ ከፍተኛ ቁማር እየተካሄደ ይገኛል። በተለይ በስፖርት ክለብ ሽፋን የቁማር ቤቶች እየተከፈቱ ማኅበረሰቡ ዕድሜ ልኩን ሲለፋና ሲገነባ የቆየውን አንጡራ ሀብቱን እጥብ በማድረግ ሰላሙን ነስተው ከጥሪት ውጭ እያደረጉት ነው። በደርግ ዘመነ መንግሥት የቢንጎ ጨዋታም በቴሊኮሙኒኬሽን፤በአውራ ጎዳና እና በመብራት ኃይል ክበቦች፤ እንደ መዝናኛ ሆኖ ይሠራበት እንደነበር አይዘነጋም።

 

በእርግጥ ሎተሪም ከቁማር ዘርፍ የሚመደብ ቢሆንም፤ አንደኛ የቲኬቱ ዋጋ ዓነስተኛ ከመሆኑም በላይ አሸናፊው ዕድለኛ በእርግጠኝነት ገንዘቡን እንደሚያገኝ ይታወቃል። በተጨማሪም በመንግሥት ተገቢው ቁጥጥር ስለሚደረግለት የሚገኘው ትርፍም ተመልሶ ለማኅበራዊ አገልግሎት እንደሚውል የሚያጠራጥር አይሆንም። ቁማርን ከዚህ የተለየ የሚደርገው ግን የተዘረፈው ገንዘብ ሁሉ የሚገባው ወደ ግለሰብ ኪስ መሆኑ ነው።

የቁማር መጥፎው ነገር አንደኛ እልክ ያስይዛል፤ ይኸውም አንድ ሰው የተበላውን ገንዘብ አስመልሳለሁ በማለት ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲከስር፤ እርኩስ አስተሳሰብ ይፈጥራል። በዚህ የእልክ እንቅስቃሴ ውስጥ ደግሞ ወደ ሱስ እንዲገባ ይሆናል። ስለሆነም በሱስ የተጠመደ ሰው የሥራ ሰዓትም አያከብርም፤ በዚህም ምክንያት ከሥራ የመባረር ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል። ትዳር ያለውም ከሆነ ለቤተሰቡ የሚሰጠው ምንም ጊዜ ስለማይኖረው ትዳሩ ይፈርሳል፤ ልጆችም ስለሚበተኑ ለማኅበራዊ ቀውስ አደገኛ ምክንያት ነው። ውሎ አድሮም የጎዳና ተዳዳሪ የመሆን፤ ወይንም ተስፋ በመቁረጥ፤ ከገባባት የጭንቀት አዙሪት ለመውጣት ቁማርተኛው የሚወስደው አማራጭ እራሱን ማጥፋት ይሆናል። አለበለዚያም ከፍተኛ ወንጀል ፈጽሞ ወደ ወኅኒ የመግባት ዕድሉ ከፍተኛ ነው።

በአጠቃላይ እንዲህ የመሰለው ትውልድ አጥፊና አገር አውዳሚ የሆነ ተግባር በኢትዮጵያ ምድር እንደ ሥራ መስክ ተወስዶ እንኳን የንግድ ፈቃድ ሊሰጠው ይቅርና፤ በስውር እንዲህ ያለውን ተግባር የሚያካሂዱና የሚያስፋፉ ሰዎች ከሽብር ባልተናነሰ መልኩ፤ በሀገር ክኅደት ወንጀል ተከሰው ከፍተኛ ቅጣት ሊሰጣቸው ይገባል።

በተጨማሪም ሀገርን ከከፍተኛ ወንጀል የመከላከልና ትውልድንም ከጥፋት የመጠበቅ ቁርጠኝነት የሚሰማው መንግሥት ቁማርን በአዋጅ የማገድ ኃላፊነት አለበት እንላለን። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለሀገርና ለወገን ከሚገቧቸው ቃል ኪዳኖች ውስጥ እንደዋነኛ የፖሊሲ መርህ አድርገው መውሰድ ይኖርባቸዋል። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን፤ የአረጀ፤ ያፈጀ እና የከሰረ ‘የሊበራል ዲሞክራሲን አስተሳሰብ’ መመሪያቸው እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ።

የሊበራል ዲሞክራሲን ጽንሰ ሐሳብ በጥልቀት የተረዱት አይመስልም። ሊበራል ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ የሚመጥን የፖለቲካ መርህ እንዳልሆነ በበዙ መልኩ ማስረዳት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ከሌላው ዓለም የሚለያቸውና የሚያስተባባራቸው ሰብአዊነትን መሠረት ያደረጉ እሴቶች አሏቸው። እነዚህ እሴቶች በተለያየ መልኩ ሲተነተኑ፤በማኅበራዊ የጋራ ጥቅም ግንኙነት፤ ማለትም በዕድርና በዕቁብ፤ እንዲሁም በኅዘንና በደስታ ጊዜ የሚደረጉ ግንኙነቶችን መጥቀስ ብቻ ይበቃል። ለምሳሌ አንድ ሰው ከማኅበራዊ ሥነ ሥርዓት ወጭ ሆኖ ከተገኘ ማኅበረሰቡ ‘የራሱ ጉዳይ ነው፤ ወይም ምርጫው ስለሆነ ነው’ ብሎ አይተወውም።

የቅርብ ዘመዶቹ ወይም ጓደኞቹ፤ ሰውየውን ወደ ጤናማው ደረጃ እንዲመለስ የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጉለታል እንጂ ፊታቸውን አያዞሩበትም። የሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ እንደዚህ ያለውን የማኅበረሰብ እሴት እንደ ኋላ ቀርነት በመቁጠር፤ በሰው ፍላጎት ጣልቃ እንደመግባት አድርጎ ይወስዳል። ስለሆነም አንድ ሰው ቁማር መጫወት  ከፈለገ መብቱ ነው በማለት ይከላከላል። ውሎ አድሮ በቤተሰቡ የሚደርሰውን ችግርና ሥቃይ፤ አልፎ ተርፎም  ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈውን መጥፎ ልማድ ከግምት ውስጥ የሚያስገባ አይደለም። በአጭሩ የግለሰቦችን መብት እናስጠብቃለን ወይም እናስከብራለን ከሚል የመነጨ በመሆኑ ለኢትዮጵያ  የሚጠቅም የፖለቲካ መርህ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ከማኅበረሰቡ ያፈነገጠውን ሰው ለመርዳት፤ በሐኪም የሚድን ከሆነ በሐኪም፤ በጸበል የሚድን ከሆነም በጸበል ለማዳን የሚቻለው ሁሉ ይደረግለታልና! ሊበራል ዲሞክራሲ እንዲህ ዓይነቱን እሴት የሚያደፋፍር አይደለም።

ለማንኛውም ቁማርን እንደ ንግድ ሥራ አድርጎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ቢኖር አገር የማውደም ስውር ተልዕኮ ያለው እንደሆነ መጠርጠር ተገቢ ነው። ገና ለገና የግለሰብን መብት በማስጠበቅ ሰበብ ትውልድ አጥፊ የሆነ ተቋም በአገራችን ሲስፋፋ እያዩ ዝም ማለት አግባብ አይሆንም። ‘ተንጋሎ ቢተፉ፤ ተመልሶ ባፉ!’ እንዲሉ አሁን እንደቀላል ነገር የታየው ጉዳይ፤ ነገ ችግሩ የማኅበረሰቡ ብቻ ሳይሆን የመንግስትም የጸጥታና ደኅንነት ራስ ምታት እንደሚሆን መረዳት ያስፈልጋል። እንዲህ የመሰለውን ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ተቀብሎ ሕዝብን እንዲያወድም፤አገርንም እንዲያጠፋ መፈቀድ የለበትም።

ስለዚህ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንዲህ ያሉ ግለስቦችን ወይም ቡድኖችን በመከታተልና በማጥናት በቁጥጥር ሥር በማዋል፤ ሀገርንና ትውልድን ከጥፋት መታደግ አለባቸው የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ለነገ የማይባል ነው። መንግሥትም ነገ ከነገ ወዲያ ቸግሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ አስቀድሞ ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ እንዲሉ አሁኑኑ በዕንጭጩ የማስቆም ኃላፊነትም፤ ግዴታም አለበት እንላለን።

-//-

 

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop