ሲዳሩ ማልቀስ አሁንም፤ ወግና ማረግ ሆኖብን፣
አሩግ መሆኑን እያወቅን፤ ታዲሱ ዘመን ገባን አልን፡፡
የጷጉሜ ጠበል ሳይነካን፤ ያደፈ ቆዳ ለብደን፣
ዛሬም እንደ ትናንቱ ተሻገርን፤ የሰው ደም በእግር እረግጠን፡፡
ፍትህ ተምድር ተቀብራ፤ ነፍስ አጥፊ አገር ሲገዛ፣
ቀኑ እንደ ደመና ጨልሞ፤ ተሰደን ገደል ስንገባ፣
ሌሊቱን እንዴት አልፈነው፤ ነጋና መስከረም ጠባ?
እምነት ሳይሽረው ክህደትን፤ ሱባኤ ሳያጥብ ወንጀልን፣
ንስሀ ሳይጠርግ ሐጥያትን፤ እርቅ ሳይፍቀው ጥላቻን፣
እንዴት ተሻግረን ክረምቱን፤ መስከረም ጠባ እልል አልን?
እንደ ቅድመ-አያት ሳንቆርጥ፤ ወጉ ባህሉ ሳይገባን፣
ደረስክ ደረስሽ ተባባልን፤ ቤተክሲያን ሲነድ ጪጭ እያልን፡፡
ሆ ሄ በላቲን ተፍቆ፤ ቤተ-ክርስትያን ተደፍሮ፣
የምን ከበሮ ድለቃ፤ ቆብን ቆልሎ ሻሽ አስሮ፡፡
በሳጥናኤል እግር ተጉዘን፤ ሰማእታትን ዘንግተን፣
ስንባባል አናፍርም፤ እንኳንስ አብሮ አደረሰን፡፡
የአድራሹን ትዕዛዝ በጥሰን፤ በይሁዳ ጫማ ተጉዘን፣
መልካምን ዘመን መመኘት፤ ቆዳና ልብን አጉድፈን፡፡
አሮጌው ዓመት ቀፍድዶን፤ አዲሱ ተሰማይ እርቆን፣
ተመንዘላዘል የማንድን፤ ማወቅ የማንችል እባብን፣
በቀትር ፀሐይ የምንሄድ፤ ቅቤ ታናት ላይ አኑረን፣
አድሮ ቃሪያዎች ትሉሎች፣ ማሞ ቂሎዎች ከብቶች ነን፡፡
መሞት ማለፍን ዘንግተን፤ ሰማእታትን የረሳን፣
ተገዳዮች ጋር የደለቅን፤ ደመ-ነፍስ እንኳን ያልገታን፣
እንሰሳም ሊሉን የከበድን፣ አምላክ ያስቸገርን ፍጡር ነን፡፡
ሆድና ስስት ማርከውን፤ አድርባይነት አጣሞን፣
ሰውን ተበላው ይህ አድግ፤ አብረን ዶልተን የጨፈርን፣
ለእኛ ሲል የሞተው ሁሉ፤ መቃብር ከፍቶ የሚያየን፣
ታሪክ ሲወቅሰን የሚኖር፣ የእሳት ልጅ አመድ ከንቱ ነን፡፡
በመድረሳችን ተሳክረን፤ ያልደረሱትን የረሳን፣
ጡት እንደሚጠባ እምቡቅል፤ ክፉና ደጉን ያለየን፣
የሚያስት እባብ የማናውቅ፤ ዓይኖች ያልገለጥን ድመት ነን፡፡
በላይነህ አባተ ([email protected])
መስከረም አንድ ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.