ሸበረኸ እንቁጣጣሽ! – በላይነህ አባተ

/

ወፍ አሞራው የሚያደምቅሽ፣
ጅረት ወንዙ የሚያዜምሽ፣
ሜዳ ጋራው የሚያጅብሽ፣
ሁሉ እሚልሽ እንኳን መጣሽ፣
ጨለማ ክረምትን ፈንቅለሽ፣
ሸበረኸ  እንቁጣጣሽ፣
ዛሬም ዳግም እንኳን መጣሽ፡፡

 

ምድሩ በመስክ ተለብጦ፣
ሶሪት ላባ ከውስጥ ሽጦ፣
ፍንትው ብሎ ተንገልጦ፣
እንግጫ አድጎ ወጥቶ ወጥቶ
በፍልሰታ ተንሰራርቶ፣
ችብሃ መስሎ ወዙን ተፍቶ፣
ሸበረኸ ፊቱ ፈክቶ፡፡

 

ሸበረኸ እንቁጣጣሽ፣
ባለም አምሳል ያላገኘሽ፣
ለየት ብለሽ የተሠራሽ፣
ልጅ አዋቂው የማይጠግብሽ፣
ሸበረኸ እንቁጣጣሽ፣
ዛሬም ዳግም እንኳን መጣሽ፡፡

 

ወፏ በራ እየወጣች፣
ክረምት ቤቷን እየተወች፣
ስለት ፉጨት እያሰማች፣
ሸበረኸን ታዜማለች፣
ለእንቁጣጣሽ ትዘፍናለች፡፡

 

ወኔአም ጎብዝ ሃይ ሎጋው ሲል፣
ልባም ቆንጆ በለው ስትል፣
ዳገት ጋራው ያስተጋባል፣
ሸበረኸን ያዳምቃል፡፡

 

ምድሩ ጪቃን አወላልቆ፣
አደይ ለብሶ ባደይ ደምቆ፣
ከላይ እታች ፈነዳድቆ፣
እያሳቀ እሱም ስቆ፣
ይህን ከዚያ አንፀባርቆ፣
ጉብላልት አስደልቆ
ከንፈር ወዳጅ አስተዋውቆ፡፡

 

ወንዙ እንዲሁ ተጠራርቶ፣
አፈር ኮረት ማፈስ ትቶ፣
ዘና ብሎ ፊቱ ፈክቶ፣
ልጅ አዋቂ አስደስቶ፣
ኃጥያት አጥቦ አነጣጥቶ፣
እያዜመ በዋሽንቱ፣
ዳግም ያምጣሽ በያመቱ፣
ሸበረኸ የኛይቱ፡፡

 

ቤተክሲያኑ ባበባ አምሮ፣
በአገር ልጆች ዙሪያው ታጥሮ፣
ዓለም ሲቀልጥ በከበሮ፣
ካህን ቄሱ ሻሹን አስሮ፣
ፀናፅሉን ሿ! ሿ! አርጎ፣
ወረብ ሲያደርስ ዘንጉን ሰብቆ፣
ሸበረኸ ሲል ሁሉ አብሮ፡፡

 

እንግጫውም ተጎንጉኖ፣
በአደይ ሶሪት ተሽቆጥቁጦ፣
ኮረዳ አንገት በዚያ አጊጦ፣
የጎበዝ ልብ አስደንግጦ፣
በሎሚ ኳስ ደረት መቶ፣
ከንፈር ወዳጅ ከዚያው ቀልጦ፡፡

 

እሸት ቆንጆ ተደጅ ወጥታ፣
ስትል ዘፍና ውብ አበባ፣
ተው አብራልኝ ሶሪት ላባ፣
ጎበዝ ወጥቶ ሲያስተጋባ፣
የፍቅር ችቦ ሲያበራ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢህአዴግ ጣና በለስን ለምን አፈራረሰው? “በሩ ይከፈት፣ በአባይ ጉዳይ አገራዊ አቋም እንያዝ”

 

የኢቶጵ ልጅ ጥርን ንቆ፣
ከመስከረም ተቆራኝቶ፣
ዘመን ሲቆጥር በራስ ኮርቶ፡፡

 

ያበባ ዓይነት ወጥቶ ፈክቶ፣
አደይ በምድር ፈነዳድቶ፣
የሶሪት ዘር ነቂስ ወጥቶ፣
ተእንግጫ ጋር ተዋህዶ፣
እንደ ድሪ በአንገት ገብቶ፣
ሸበረኸን አስጨፍሮ፣
ከንፈር ወዳጅ አስገብይቶ፣
በእንቁጣጣሽ ምኑ ቀርቶ!

 

የእኛ እመቤት እንቁጣጣሽ፣
እኛ እንደዚህ ስንወድሽ፣
አሲረዋል ጠላቶችሽሽ፣
ተመስከረም ሊያባርሩሽ፣
ተጥር ወር ሊወሽቁሽ፡፡

 

ቀናተኛ ቢንጨረጨር፣
ሸበረኸን ቆርጦ ሊጥል፣
ራስ ዳሽን እምቢኝ ይላል፣
ላሊበላ ማት ያወርዳል፣
ያባይ ጋራ ይናወጣል፣
ቢጫ መልበስ አልተው ይላል፣
ጎበዝ ቆንጆን ያስጨፍራል፣

አበባዬን ያዘፍናል፡፡

 

ከሀዲያን ቢታገሉሽ፣

ግን አትወድቂ ተሸንፈሽ፣

መረጃዎች እስካሉልሽ፣

ሶሪት አብቃይ ሜዳዎችሽ፣

እንግጫ አጠጪ ወንዞችሽ፣

ሻደይ መጋቢ ጅረቶችሽ፣

አደይ ለባሽ ተራሮችሽ፣

ሸማይዋነ እንቁጣጣሽ፣

ሸበረኸ እንቁጣጣሽ፤

ከርሞም ደሞ ትመጫለሽ!

 

በዓለም አምሳል ያላገኘሽ፣

ለየት ብለሽ የተሰራሽ፣

ልጅ አዋቂው የማይጠግብሽ፣

በደስታ የሚያዜምሽ፣

ዛሬም ዳግም እንኳን መጣሽ፣

ወሰን የለሽ ይሁን ዕድሜሽ፣

ሸማይዋነ እንቁጣጣሽ፣

ሸበረኸ እንቁጣጣሽ፡፡

 

                                በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

                                                                       

መጀመርያ ነሐሴ ሰማንያ ዘጠኝ ዓ.ም. እንደገና ነሐሴ ሁለት ሺ አስራ አንድ ዓ.ም.

Share