. የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የጫነብን የዘር ክልል አስተዳደር – አንዱዓለም ተፈራ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ – ፲ ፱ ፻ ፹ ፫ እንደገና

የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የጫነብን የዘር ክልል አስተዳደር፤

አሁን ለተዘፈቅንበት የፖለቲካ አረንቋ ምክንያቱ ነው? ወይንስ መፍትሔው?

አንዱዓለም ተፈራ፣ ረቡዕ፣ መስከረም ፲ ፮ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፩ ዓ. ም. (Wednesday, September 28, 2018)

ሀገራችን አሁን በአስጊ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች። በዓለም ዙሪያ ተደናቂነትን ያገኘው አሁን የተጀመረው የለውጥ ሂደት፤ ከፍተኛ አደጋ አንዣቦበታል። በፖለቲካ መድረኩ ላይ እየተጫወቱ ያሉት አንዳንድ ድርጅቶች፤ አጀንዳውን ወደየ ፍላጎታቸው እያንጋደዱ ለመውሰድ፤ የለውጡን ሂደት ስጋት ላይ የጣለ፤ ግብግብ ላይ ናቸው። ይህ የሀገራችንን ሕልውና በንጥልጥል አስቀምጦታል።

ግንቦት ፲ ፱ ፻ ፹ ፫ ዓመተ ምሕረት፤ ሶስት ነፃ አውጪ ግንባሮች፤ ከኤርትራ፣ ከትግራይ እና ከኦሮምያ፤ የሰው በላውን አምባገነን መንግሥቱ ኃይለማርያም ሥልጣን ወረሱ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፤ እኒህ ሶስቱ ድርጅቶች፤ ሀገራችን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ያለፈችበትን ሂደት ወስነውታል። የኤርትራዊያን ነፃ አውጪ ግንባር (ህግሓኤ)፤ በቀሪዎቹ በሁለቱ ድጋፍና እውቅና፤ ሀገሪቱን በመገንጠልና ወደብ አልባ በማድረግ፤ የራሱን ሀገር መሠረተ። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፤ ባጣዳፊ የፈለጉትን የዘር ክልል ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ መሠረቱ። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ የሀገሪቱን 6% ብቻ የሚሆኑትን ትግሬዎችን እወክላለሁ በማለት፤ ቀሪውን 94% የሚሆነውን የሀገሪቱን ወገን ለመግዛት፤ አመቺ የሆነ ሕገ-መንግሥት በቦታው ማስቀመጥ ነበረበት። በሜዳ ውስጥ የኳስ አቀባይነት ሚና የተጫወተው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፤ የሥልጣን ጉርሻ አገኛለሁ በማለት፤ ጓጉቶ ተሳተፈ።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መሪዎች፤ አንድም ዕውቀቱ ጎድሏቸው ነበር፤ አለያም በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር የተመሠረተው የኦሮሞዎች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ይጠፋል! ወይንም በኦሮሞዎች ፊት በሚደረገው ምርጫ፤ የሕዝቡን ልብና አእምሮ እኛ እንወስዳለን! ብለው አምነው ነበር። ነገር ግን፤ ኦነግ በሁለቱም በኩል ባዶ ቀረ። ጨካኙ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ይህ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፤ ኦነግን ለማጥፋት፤ ቀን ተሌት ተሯሯጠ። እናም ያንኑ ድርጊት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎችን በመግደልና በአስርት ሺዎች የሚቆጠሩትን ለእስር በመዳረግ አጠናቀቀ። በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባሩ የተመሠረተው ኦሕዴድ፤ በትሕነግ መንግሥት እርዳታና በአካባቢው ባቋቋመው መዋቅር፤ ቀስ እያለ እያደገ ሲሄድ፤ በትሕነግ የተደቆሰው ኦነግ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ተከፋፈለ።

በቅርቡ የዐማራና የኦሮሞ ወጣቶች፤ “የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግፍና በደል በቃን!” ብለው ተነሱና ይሄ ገዢ ቡድን ሀገሪቱን እንዳፈተተው መግዛት እንዳይችል አደረጉት። አረመኔው ዘረኛ የትሕነግ ገዢ ቡድን፤ በጁ ያገኘውን ማንኛውንም ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ በማከሄድ ሊቆጣጥር ሞከረ። አልተሳካለትም። ይልቁንም ኦሕዴድና ብዐዴን በመካከላቸው ያቆመባቸውን አጥር አፍርሰው፤ ወዳጅነት በመፍጠር፤ ጉልበታቸውን አፈረጠሙ። የቀጥታ ግንኙነታቸውን አጠንክረው፤ ግልጥ የሆነ የአንድነት ዓርማ አውለበለቡ። ከዚያ ቀጥለው፤ አረመኔው ትሕነግ፤ በሕዝቡ ላይ የለቀቀውን ያልተገራ ወታደራዊ እርምጃ፤ መጠየቅ ጀመሩ። የተርበተበተው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር የቀድሞ አጋሮቹን ከቀበረበት ቦታ መቆፈር ያዘ። በኤርትራ በኩል በማያዳግም ሁኔታ ድሮ ድልድዩን አፍርሷል። በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በየቦታው ሆ! ብሎ ሲነሳበትና የኢሕአዴግን መሠረት ሲያናጋው፤ የኦሕዴድና የብዐዴን አመራር ለውጥ ፈላጊ ቡድን፤ ከሕዝቡ ጋር ወገነ። በዚያ ሰዓት የሀገሪቱ አመራር በለውጥ ፈላጊዎች እጅ ወደቀ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አቶ አብርሃም ያዬህ የምላስዎትን አፈሙዝ በአቶ ገ/መድኅን አርአያ ላይ አያዙሩ!

በቅርብ ጊዜ፤ በአረመኔ አምባገነን መሪዎች ሥር የነበሩ የተለያዩ ሀገሮች ያደረጓቸውን ለውጦችና ከዚያ የተከተለውን ስንመለከት፤ ምንም ዓይነት ቀመር እንደሌለና ተከታዩ ይሄ ነው ብለን የምንተነብይበት መሣሪያ እንደማናገኝ እንረዳለን። እስኪ አስቡት፤ የምሥራቅ አውሮፓዊያን ሀገራትን የቀለም አብዮት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የአረብ ሀገራት ፀደይና በሊቢያ፣ ግብጥና የመን የተከተለው፣ የአይሲስ መነሳትና ወርዶ መከስከስን ማን ከመከሰታቸው ከጥቂት ዓመታት በፊት ገምቶ ነበር? ይህ ያስተማረን፤ የአንድን ሀገር ክስተት፤ ቀደም ብሎ በመመርመር፤ በታወቀ ቀመር አስገብቶ፤ የሚሆነው እንዲህ ነው ብሎ መገመት አዳጋችነቱን ነው። በያንዳንዱ ሀገር ያለው የኅብረተሰብ ኡደት ወሳኝና የተለያየ ነው። እናም በሀገራችን የሚከተለው ምን እንደሚሆን ማወቁ አስቸጋሪ ነው። ብዙ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎች አሉ። አንዳንዶቹ እንቅልፍ ይነሳሉ። ሌሎች ደግሞ ትንፋሽ ያረጋጋሉ።

እስካሁን የታወቀው ይህ ነው። ለውጥ ፈላጊ በመንግሥት ቁንጮ ላይ ተቀምጧል። ይህ ለውጥ ፈላጊ ክፍል በአብዛኛው ሕዝብ የተፈቀረና የተደገፈ ነው። በመንግሥቱ ውስጥ ያሉ አንዳንዶችና በውጪ ያሉ አንዳንድ ቡድኖች፤ ቀን ተሌት ለውጡን አቅጣጫ ለማሳት ወይም ለማቆም እየጣሩ ነው። የዚህ የኋለኛው ክፍል ዋና መሪ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ሲሆን፤ እሱ ያሰማራቸው ቅጥረኛ አባሪዎቹና የሱ ዓይነት አጀንዳ ያላቸው አብረው አድመዋል። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ምንም እንኳን በመንግሥቱ አናት ላይ ባይቀመጥም፤ ቁልፍ የሆኑ ቦታዎችን በጦሩ፣ በደህንነቱና በምጣኔ ሀብት ሥምሪቱ መንግሥታዊና ከመንግሥት ውጪ በሆኑ ክፍሎች፤ አባላት አሉት። በተጨማሪም፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር የሀገሪቱን ሀብት መዝብሮና ጢም ያለ የመሣሪያ ክምችት ትግራይ ውስጥ ስብስቧል።

አሁን በሀገራችን ውስጥ ያለውን መንግሥት ስንመለከት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ እጃቸው ከኋላቸው ታስሯል። መቼም ያለ ሕግ-መንግሥትና መንግሥታዊ መዋቅሩ፤ ብቻቸውን እንዳሻቸው መንግሥትን መምራት አይችሉም። ኃላፊነቱን የሠጣቸውና ወካያቸው፤ ኢሕአዴግ ነው። የሚገዙት በኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት ነው። የሚንቀሳቀሱት፤ መንግሥታዊ መዋቅሩ ውስጥ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ላይ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ባስቀመጠላቸው የጦሩ፣ የደህንነቱና የየክፍሎቹ ኃላፊዎች ነው። በተጨማሪም አብረው የሚሠሩት የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መርጦ ባስቀመጣቸው አባላት ከተሞላው ፓርላማ ጋር ነው። በሌላ በኩል፤ ጉልበታቸው፤ ለውጡና የሚወዳቸው ሕዝብ ነው። ይህ አጣብቂኝ ሁኔታ፤ የግድ ኦሕዴድ የሚመርቅላቸውን ሰዎች በየቦታው እንዲመድቡ አስገድዷቸዋል። ኦሕዴድ ደግሞ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና የኦሮሚያ ፕሬዘዳንት አቶ ለማ መገርሳ የሚመሩት አንድ ወጥ ድርጅት አይደለም። በዚህም ምክንያት፤ በየከተማው ሰልፉን በሚያካሂደውና ለውጡ ፈላጊው ሕዝብና ለውጡን በሚመሩት የመንግሥቱ ክፍል መካከል ክፍተት ተፈጥሯል። ለምሳሌ፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር በሰንደቅ ዓላማችን ላይ ያስቀመጠውን ምልክት ጥለው፤ አረንጓዴ፣ ብጫና፣ ቀይ ቀለማት ብቻ ያሉትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ድረስ፤ ሕዝቡ እያውለበለበ፤ “ተደምሬያለሁ!” እያለ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ስም እያሞገሰ ወጥቷል። ነገር ግን፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባርን ሰንደቅ ዓላማ ለማስከበር፤ መንግሥታዊ መዋቅሩ፤ እኒህን አውለብላቢዎች እያሰረ ነው። ሕዝቡ ቀድሞ፤ “አንለያይም!” “አንድ ነን!” “በዘር አጥር መከፋፈሉ ያብቃ!” “ኢትዮጵያዊ ነን!” እያለ ነው። አሁንም በየክልሉ ያሉትን መሪዎች ይሄ የሚጋፋቸው ሆኗል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ህዝበ-ሙስሊሙን ያለአግባብ በስጋት መፈረጅ፤ ማዋከብና መግደል በአፋጣኝ ይቁም!!

ከዚህ ላይ ግልጥ የሆነው ነገር፤ የተለየ አጀንዳ ያላቸው ክፍሎች፤ በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ጭፍሮቻቸውን ሰግስገው በማስገባት፤ ምናልባትም በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር እርዳታ፤ ለውጡን ለማደናቀፍ እየሠሩ መሆናቸው ነው። ይህ ደግሞ ባደባባይ የዋለው፤ የዐማራ ወጣቶችንና የኦሮሞ ወጣቶችን ለማጣላት፤ የሌለ አጀንዳ በማራገብና በመካከላቸው ክፍተት በመፍጠር ነው። ባሁኑ ሰዓት ሀገራችን ማተኮር ያለባት፤ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ጉዞ ማፋጠን ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው፤ የክልል አስተዳደሩ የተዋቀረው፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባርን አጀንዳ ለማራመድ እንጂ፤ ሌሎችን ማንኛቸውንም ለማስደሰት አይደለም። የክልል መስመሮቹ ማንንም አላረኩም! ትክክል አይደሉም። ምክንያቱም ትክክል የሚባል የክልል ወሰን የለማ! ዐማራው በመላ ኢትዮጵያ ይገኛል። ኦሮሞው በመላ ኢትዮጵያ ይገኛል። ጉራጌውም ሌላውም። የትኛውም ቦታ ቢሆን በተለይ ለአንዱ ወገን ተብሎ ሊከለልና ሊሠጥ አይችልም። እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊትና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የራሷ እና የራሱ የሆነ ንብረት፤ በየሚገኙበት ቦታ አላቸው። ሀገሪቱን ደግሞ በአንድነት ከቀድሞዎቹ ወርሰናታል። ቀጥለን ደግሞ ለመጪዎቹ እናወሳታለን። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት። ትናንት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስሟ በረራ ነበር። ዛሬ አዲስ አበባ ተብላ ተጠርታለች። ታሪኩን ለተመራማሪዎች በመተው፤ እኔ እማራለሁ። ባሁኑ ሰዓት፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር፤ በአዲስ አበባ ለሚኖረው ሕዝብ መተው አለበት! ለሐረርም እንዲሁ! የአካባቢውን አስተዳደር የአካባቢው ሕዝብ መምረጥና መመደብ ይኖርበታል።

በሌላ በኩል፤ ኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል መባረራቸውና መገደላቸው ትክክል አይደለም። ዐማራዎችም እንዲሁ። ጋሞዎችም በቡራዮ የተፈጸመባቸው ግፍ ትክክል አይደለም። ጉራ ፈርዳ፣ ሐረር፣ አርሲ፣ ወለጋ፣ ቤንሻንጉል፣ ወልቃይት፣ ጠለምት፣ ራያ በዐማራው ላይ የተፈጸመው በደል፤ ግድያው፣ መፈናቀሉ፣ መባረሩ፣ ሀብታቸው መዘረፉ፣ ትክክል አይደለም። ባጠቃላይ በትውልድ ሐረግ የተመሠረተ ማንኛውም አጀንዳ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አጀንዳ እንጂ፤ የኢትዮጵያዊያን አጀንዳ አይደለም። ይሄን አጀንዳ አንግበው በሕዝቡ መካከል ጠብ የሚጭሩ፤ ፀረ-ሕዝብ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባርና አባሪዎቹ ናቸው።

በሕዝቡ መካከል የሚፈጠር የጎሳ ግጭት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ቅንብር ነው። ይሄም ሕዝቡ በአንድነት እንዳይቆም የሚያደርግ መርዛማ ሴራ ነው። ይሄን በማድረግ ብቻ ነው፣ አናሳው ክፍል ብዙኀኑን ሊገዛ የሚችለው። ይህ የዐማራው ወይንም የኦሮሞው አጀንዳ አይደለም። ይህ ደግሞ ለመላ ሰማንያ ሁለት ጎሳዎች የሚሠራ ነው። ቅመ አያቶቻን እና ቅድመ አያቶቻችን፤ አያቶቻችን እና ወላጆቻችን፤ ባጽምና በደማቸው የገነቧትን ሀገራችንን፤ በአንድነት ኢትዮጵያዊ ሆነን እንኖርባታለን። ያለን ምርጫ ያ ብቻ ነው። ይህ አብሮ ያሠረን ዜግነታችን ነው። አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነን፣ በኦሮሚያ ፕሬዘዳንት ለማ መገርሳና በዐማራ ፕሬዘዳንት ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራውን የለውጥ ሂደት የምንደግፍ በሙሉ፤ የአንድነቱን አጀንዳ አንግበን፤ ከለውጡ ጋር መራመድና ለውጡ እንዳይስተጓጎል ዘብ መቆም አለብን። አዎ! ጉድለቶች ይኖራሉ። ነገር ግን መገንዘብ ያለብን፤ አሁን በሽግግር ላይ ነን። እኔም ቢሆን፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነቀርሳ ዛሬውኑ ከሥሩ ተመንግሎ ቢወገድ ደስ ይለኛል። ይህ ግን ምኞት ነው። ተጨባጭ ሀቅ ደግሞ ለእውነት እንድገዛ ያደርገኛል። ለፍላጎታችን ቅደም ተከተል ማበጀት አለብንና ሀገራችን እናስቀድም። የግለሰብና የቡድን አጀንዳችንን ወደኋላ በማለት፤ ሀገራችን እና የአንድነት ሰንደቃችንን በማሰቀደም፤ ወደፊት መሄድ አለብን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሰይጣን ግዛትም ሥላሤዎች አሉ - እንተዋወቃቸው፡፡ - ወልደ ማርያም ዘገዬ

የለውጡን ሂደት እደግፋለሁ፣ አንድነትን እወዳለሁ ብሎ፤ አዲስ አበባ የኦሮሞዎች ናት ማለት አይቻልም! ቀድሞ ነገር ይህ ምን ማለት ነው? ሁመራ የኦሮሞው አይደለችም? ጂጂጋስ? መቀሌስ? ይህ ያስተወሰኝ፤ ጭራቁ ሟች የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መሪ፤ “አክሱም ለወላይታው ምኑ ናጥ?” ሲል ያላገጠበት ንግግር ነው። አሁን የሰፈሩት የትግሬዎቹ እንጂ፤ የቀሪዎቹ ኢትዮጵያዊያን አይደለም ሲለን! ይህ የክልል አስተዳደሩ ጋር መጥፋት ያለበት ጉዳይ ነው። ለአሁኑ፤ ከላይ እንዳሰፈርኩት፤ አዲስ አበባ ከክልሎቹ አንዷ በመሆኗ፤ የክልሏ ነዋሪዎች ናቸው አስተዳደሯን የመርጡትና የሚያካሂዱት። ጠባብ ብሔርተኝነት የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር እና ያራገበውና አሁን ከሱ ጋር የቆሙ የሚያራምዱት አጀንዳ ነው። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ዐማራውን ለማጥፋት፤ በዘር ላይ የተመሠረተ የዘር ማጽዳት በዐማራው ላይ አካሂዷል። ይሄንን ማንኛውም ዐማራ ከአእምሮው አያወጣውም። አሁን ደግሞ አምስት የኦነግ አካሎችን የሚወክልና ኢትዮጵያዊያንን በኢትዮጵያ አብረን እንድንኖር የማያስችል ንግግር፤ ከአቶ በቀለ ገርባ ሰምቻለሁ። ይህ በጣም አደገኛ ነው።

በጎንደር የተሰለፉት የዐማራ ወጣቶች፤ አቶ በቀለ ገርባን በትከሻቸው ጭነው፤ የራሳቸው መሪ አድርገው፤ “የኦሮሞዎች ደም የኛ ደም ነው!” “የእስልምና ተከታይ ወገኖቻችን ጉዳይ የኛም ነው!” “በቀለ ገርባ መሪያችን ነው!” ብለው ሲጮኹ፤ ኢትዮጵያ በወቅቱ የምትፈልገውን የመዳኛ ገመድ ፈተሉ። አቶ በቀለ ገርባ፤ “እኔ ጎንደሬ ነኝ!” “እኔ ዐማራ ነኝ!” “አመሰግናችኋለሁ!” ማለት ነበረባቸው። ይሄንን አላደረጉም። እኒያ ኩሩ ጎንደር ያሉ የዐማራ ወጣቶች፤ በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ምንም ዓይነት ቅሬታ የላቸውም። ያን ያደረጉት ከኦሮሞ ወገናቸው ጋር አብረው በመቆም፤ “ኦሮሞ ወጣቶች መሪያችን ያሉት የኔም መሪ ነው!” ብለው ኢትዮጵያን ለማዳን ነበር። ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት። ይህ ነው ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የጸዳ ኢትዮጵያዊነት። “አዲስ አበባ የኦሮሞዎች ናት!” በማለት፤ አቶ በቀለ ገርባ በጎንደር የተሰለፉትን የዐማራ ወጣቶች በጣም አሳዝነዋቸዋል። ጥረታቸውንም ዋጋ አሣጥተውታል።

አዎ! በዘር ላይ የተመሠረተው ፌዴራሊዝም ይወድማል። አዎ! በዚህ አጀንዳ በደል የፈጸሙ፤ የትም ይገኙ፣ ከየትም ይምጡ፤ ለፍርድ ይቀርባሉ። አዎ! እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል፤ የመኖር፤ ሀብት የማፍራት፤ በቦታው የኅብረተሰብ ክንውን ሙሉ ተሳትፎ የማድረግ መብታችን ይከበራል። ይህ ነው ለውጡ እየገሰገሰበት ያለው ግብ።

መወያየት ለሚፈልጉ፤ eske.meche@yahoo.com

4 Comments

  1. የዛሬን አያርገውና ድሮ ድሮ ሰው ሰው እያለ አንድ ባነበው ባነበው እስከአሁን ሚስጢሩ ያልገባኝ መጽሃፍ አለ። መጽሃፉ “አደፍርስ” ሲባል ጸሃፊው እውቁ ዳኛቸው ወርቁ ነው። የተጫነው አፈር ይቅለለውና ላነሳ የፈለኩት የመጽሃፉን መታሰቢያነት ነው።
    መታሰቢያ ይልና የሚከተሉትን ሰዎች ይዘረዝራል።
    ለልዑል ራስ መኰነን ወልደ ሚካኤል
    ለራስ አርአያ (የአጼ ዮሐንስ አጎት)
    ለፍታውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ
    ለደጅአዝማች ባልቻ ሳፎ
    እና
    ለራስ ቢትወደድ እንዳልካቸው መኰነን ይላል… አንባቢ ምን ይህን ሁሉ አስቀባጠረህ ደግሞስ አቶ አንድዓለም ተፈራ ከጻፉት ሃሳብ ጋር ምን አገናኘው ይል ይሆናል። ረጋ በሉ ሃሳቤን አንብቡት። የጫካ ፓለቲካ የመኖሪያ ብልሃት ሳይሆን በፊት ከላይ በመታሰቢያነት የተዘረዘሩት ሰዎች ለሃገራቸው ማለፊያ ተግባር የሰሩ ሲሆን በአሁኑ የዘር አሰላለፍ ደንብ አብረው ሊወሱ ባልቻሉ ነበር። የድሮ ስርአት ናፋቂዎች እያለ የሚያላዝነው የወያኔ ጥርቅም ሰውን በሰውነቱ ማየት ትቶ በዘር እና በጎሳ በመከፋፈል በብሄርና የብሄር ብሄሮች ነጻነት በማለት ሃገርን ያፈረሰና ለጠላት የሸጠ ቡድን ነው። እኔ ለውጡን ለውጥ ብየ ከበፊትም አልተቀበልኩትም። ያው ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እንጂ። ይህን ስል የዶ/ር አብይ መንግሥት መልካም እርምጃዎችን አላደረግም ማለቴ አይደለም። በጎ ነገሮች አሉት። ግን እየቆየ ወያኔን እየመሰለ እየመጣ ነው። አንድ ጊዜ አቶ መለስና የያኔው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት በሃሳብ ይጋጫሉ። እውኑን በመናገር የሚታወቁት ትውልደ ወለጋዊው ኢትዮጵያዊ አቶ መለስን እንዲህ አሉት። “አሁንስ መንግስቱ መንግስቱን ትመስለኛለህ”። አዎ እኛ ሰው ዛሬ በህይወት የሉም። ወያኔ፤ ሻቢያ እና በኦሮሞ ህዝብ ነጻነት ዙሪያ ጠበንጃ ያነገቱ ሁሉ ተማሩ፤ አልተማሩ ጥላቸው ከሁለት ነገር ብቻ ነው። በውሸት ራሳቸውን ግተውና ህዝባቸውን አሳምነው የሚመሩበት የጥላቻ ምርኩዞች አንድ አማራ ጠላትህ ነው ሲሆን ሌላው ኢትዮጵያን ከመጥላት የመነጨ ነው። ሌላ ምንም የለውም። ምሳሌ ልስጥ – ሻቢያ ከ 14 በላይ የፓለቲካ ድርጅቶችን በሃገሩ ላይ አቅፎና ደግፎ እያስታጠቀ ሲያሰለጥን በዶ/ር አብይ ጥሪ መሳሪያ ፈትተው ሃገር ገቡ ተብለናል። በተቃራኒው የአስመራውን መሪ የሚቃወሙ ሃይሎችን ደግሞ ወያኔ በመሃል ሃገር ሲያስታጥቅ፤ በአዋሳና በሌሎች ከተሞች ሲሰበስብ ነበር። አሁን እነዚያ የሻቢያ ተቃዋሚ ሃይሎች ድመት እንደመጣችበት አይጥ ለነፍሳቸው ሲራወጡ ማየት የፓለቲካን ጠማማነት አጉልቶ ያሳያል። በሻቢያ የውስጥና ድንበር ዘለል የስለላ መረብ ላለመጠለፍ ስራቸው ሁሉ ነፍሴ አውጪኝ ሆኖአልና። የዶ/ር አብይ መንግሥትም ለእነዚህ ሰዎች ቀዳሚ ከለላና ውል ባለማድረጉ በየቀኑ እየታፈኑ ወደ አስመራ እንደሚጋዙ አመላካች ነገሮች አሉ። የሻቢያ ሰላዮች በሃገሪቱ መዲናና በመላ የሃገሪቱ ክፍል ባለሃብት በመሆን፤ የመኖሪያ ፈቃድ በማውጣት ልክ በደርግ ጊዜ አፍንጫችን ላይ ቁጭ ብለው እቁብ እያዋጡ የሻቢያን ፊልሚያ ይረዱ እንደነበሩት ዛሬም አሰራራቸው ረቀቀ እንጂ አልመከነም። በዚህ ሁሉ ግን የሚጎዳው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ሃገራችን መስቀለኛ መንገድ ላይ የሆነቸው ዛሬ አይደለም። ቆየ። የወደፊት እድል ፈንታዋም የጨለመ ነው። ማንም ህዝብ በብሄርና በቋንቋ ተከፋፍሎ አብሮ መኖር አይችልም። በመሰረቱ ክልል የሚለው ቃል የእኔ አለ፤ መስመር አበጀ፤ አጠረ ከሚለው ሃሳብ ጋር ይያያዛል። እንዲህ ባለ የምስቅል ፓለቲካ ሃገር ሃገር ሆና ትቀጥላለች ብሎ ማመን ይከብዳል። መካሪዎችና አስታራቂዎች እንዳይኖሩን አፈር መልሰንባቸዋል። ወና በቀረ ሃገር ላይ ዲስኩረኛና ጦረኛ በየሜዳው እያቅራራ ሰው ለሰላም ጆሮውን ሰጥቶ አርፎ ይቀመጣል ማለት ከምኞት አያልፍም። በዛ ላይ የአረብ ሃገሮች፤ በተለይም ግብጽ፤ ሳውዲ፤ እና ሌሎችም እሳትና ገንዘብ የሞላው ኮሮጆ አሸክመው ሂድ በለው ማለታቸው እውን ነው። የጠባቦች እይታ ከአፍንጫቸው አይርቅም። አዲስ አበባ የኦሮሞ ከተማ ናት እያሉ የሚለፉ ጉዶች የአለምን የፓለቲካ ታሪክና ስሬት መለስ ብለው ቢያዪ ስንቱ ነገር የእኔ ነው በተባለ ነበር። ግን አይቻልም። አብሮ መኖር አማራጭ የማይገኝለት በመሆኑ። ዳኛቸው ወርቁ በአደፍርስ ላይ ለመታሰቢያነት የጠራቸው ስሞች ለሃገራቸው አንድነትና ልዕልና የተፋለሙትን ነው። ቆንጨራ ይዞ የወገኑን ቤት በእሳት የሚያጋይ፤ አንገት የሚቀላ፤ በዘር በተሰመረ እይታ የሰው ቤት የሚያፈርስ ጠባብ የዘር ፓለቲከኞችን አይደለም። ግን እኮ ፓለቲካ ነፋስ ነው፡፤ የዛሬው አንጋች የነገ ነጭ ለባሽ ሆኖ አፈር ይመለስበታል፡ አይተናል። የጊዜ ድንፋታ በጊዜ ይገታል… ጊዜ የሰጣቸው ዛሬ በህዝባችን ላይ የሚያደርሱት ግፍ ግን በጊዜው ተበቃይ ይኖረዋል። ያኔ እናንተን አያርገኝ!

  2. ትክክል ነህ የኛ ነገር። ዘሃበሻ ያርመዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የላኩላቸውን ጽሑፍ በድረገጻቸው ላይ በሚጭኑበት ወቅት፤ ርዕሱን ብቻ አስቀምጠው፤ የቀደመ ፅሁፌን ጭነውታል።የላኩላችሁ ጽሑፍ፤ የለውጡ ጎራ በግልጥ እየጠራ መጥቷል የሚለውን አልጫናችሁትምና፤ ከይቅርታ ጋር ተመልሳችሁ ብትመለከቱት እወዳለሁ።

  3. ዘሀበሻ፤ የሚገርምህ ነገር፤ ብዙ ድረገጾች ካንተ ወስደው በራሳቸው ድረገጽ ላይ እንዳለ ስለሚለጭኑት፤ ስህተቱ ተዛምዷል። እባክሁን በተጻለ መጠን ቶሎ አስተካክለው። በጣም አመሰግናለሁ።

Comments are closed.

Share