በሸፍጥ ፖለቲካ ያልተበከለው ነገራችን የቱ ነው? — ጠገናው ጎሹ  

August 11, 2019

ጠገናው ጎሹ

ባሳለፍነው የሐምሌ ወር የመጨረሻው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ  ያለ እርሳቸው ዘማችነትና አዝማችነት  ስለችግኝ ተከላ እቅድ የሚያወጣና የሚያስተባብር  ባለሙያ መሥሪያ ቤት እና  ለዚህም ተግባራዊነት  የሚተባበር ዜጋ  በአገሩ የጠፋ እስኪ መስል ድረስ እንደ ህዝብና እንደ አገር የመኖር ህልውና ላይ አደጋ የጋረጠውንና ጨርሶ ጊዜ የማይሰጠውን የፖለቲካ እብደት አደብ የማስገዛቱንና  ጤናማ አቅጣጫ የማስያዙን ሥራ አንድ ቀን ሙሉ እርግፍ አርጎ በመተው “የችግኝ ተከላ ሪኮርድ ሰበራ” ላይ መዋላቸው ይታወሳል። በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት አስተባብሮና መርቶ ወደ ዴሞክራሲያዊና ዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት የሚያሸጋግረው የፖለቲካ ድርጅትንና ይህኑ እውን ለማድረግ የሚያግዙ  የሲቭል ማህበራትን ወልዶ ማጎልበት ያልተሳካለት ህዝብ  ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር ለዘመናት ከኖረበት ልክ የሌለው የመከራና የውርደት ሥርዓት ቀንበር የተገላገልኩ እየመሰለው መሬት ላይ ጠብ በማይል የፖለቲከኞች ዲስኩር ነገ የተሻለ ይሆናል ብሎ ተስፋ ቢያደርግ የሚገርም አይደለም። ታዲያ  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ከሰማይ የተላኩለት ነፃ አውጭው አድርጎ የተቀበለ የዋህ ህዝብ ፖለቲከኞችና አሽቃባጮቻቸው የችግኝ ተከላ ዘመቻው ከሸፍጥ የፖለቲካ ጨዋታ ጋር ግንኙነት የለውም ሲሉት አሜን ብሎ ቢቀበል ለምን ይገርመናል ?

የህወሃት/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች  ህዝብ የእለት ከእለት ህልውናውን ሥጋት ላይ በጣለ ድህነት ውስጥ  እየማቀቀ “የእድገትና ልማት ገድላቸውን” ትርክት ያለምንም ሃፍረትና ይሉኝታ  በመከረኛው ህዝብ ላይ ሲያራግፉበት አያሌ ዓመታት ተቆጥረዋል ። በእንዲህ አይነት  ቁጥርን እየቀቀሉና ወደ መቶኛ (%) እየቀየሩ በህዝብ መከራና ውርደት እርካሽ የፖለቲካ ትርፍ በማጋበስ የተካኑ ፖለቲከኞች የችግኝ ቁጥርን ቀቅለው በማቅረብ  ዓመት ሳይሞላው ገመናው የተጋለጠውን ኢህአዴጋዊ  የተሃድሶ (የጥገና) ለውጥ ቆንጆ ለማስመሰል መሞከራቸው የማይጠበቅ አይደለም።  ይህን “ሪኮርድ ሰባሪ አረንጓዴ ዘመቻ” የአገርን ህልውና እና የህዝብን አብሮነት አደጋ ላይ ለጣለው የፖለቲካ እብደት የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ከመስጠት አንፃር ለሚታዘብ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ ለሆነ  የአገሬ ሰው ግን የአገራችን የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ አዙሪት በቀላሉ የሚቀረፍ እንዳልሆነ ለመረዳት አያስቸግረውም  ።

እዚህ ላይ አንድ  አስፈላጊ ጉዳይ የገባኝን ያህል ግልፅ ላድርግ የሰሞኑን “የዓለምን ሪኮርድ ሰባሪ” የችግኝ ተከላ ዘመቻ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተንሸራሸሩ ቢሆንም በአንድ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ግን ጨርሶ ልዩነት የለም።  ሊኖርም አይገባውም ። ያ መሠረታዊ ጉዳይ ችግኝ በማንምና በምንም ቢተከል “ለምን ተተከለ?” ብሎ ደምሳሳ  የተቃውሞ መከራከሪያ ማንሳት የጤናማ አእምሮ ባለቤትነት ሊሆን እንደማይችል በእርግጠኝነት ለመናገር የመቻል እውነትነት ነው።  ምክንያቱም እንኳን ህልውናቸው ከህልውናችን ጋር በጥብቅ የተቆራኘውን እፀዋትን በዚች ምድር ላይ የሚገኙ ጠቃሚ ነገሮችን ሁሉ የመንከባከብንና በአግባቡ የመጠቀምን አስፈላጊነት የማይፈልግ ወይም የሚቃወም ጤናማ አእምሮ ያለው የአገሬ ሰው ከቶ አይኖርምና ነው ። በሌላ አገላለፅ በአሳዛኝ ሁኔታ ተመልሶ ወደ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መሣሪያነት የገባው የመንግሥት ሚዲያና አፍቃሬ የለውጥ አራማጅ የግል ሚዲያዎች እንደሚነግሩን  ልዩነት ያለው ችግኝ መትከል ወይም አለመትከል ከሚል የለየለት የድንቁርና ወይም ጨርሶ ስሜት የማይሰጥ ደምሳሳ እሰጥ አገባ ላይ አይደለም።

ልዩነት ያለው በሚከትሉት  ጥያቄዎች ዙሪያ በምክንያታዊነት ፣ በጥሞና ፣በቅንነት ፣ በሃቀኘነት፣ በገንቢነት  እና አካፋን አካፋ ብሎ ለመጥራት በማይሽኮረመም ፖለቲካዊና ሞራላዊ  ሰብእና ላይ የተመሠረተ የሃሳብ ልውውጥ ለማድረግ ፈቃደኛና ዝግጁ ከመሆን ወይም ካለመሆን ላይ ነው።

  • አሁን መሬት ያለው ግዙፍና መሪር ሃቅ ለዓመታት ከዘለቅንባቸው በሸፍጥና በሴራ የተለወሱ  የፖለቲካ ዘመቻ ተውኔቶች ምን ያህል የተሻለ እርቀት ተጉዟል?
  • ሰላማዊ ፣ ቅን አሳቢና አድራጊ የሚመስሉ ነገር ግን በአደገኛ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ የተካኑ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች በተሃድሶ (reform) ሽፋን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ የአገዛዝ ሥርዓታቸውን ከሞት አፋፍ መልሰው ነፍስ እንዲዘራ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ግልፅና ግልፅ እየሆነ ከመጣ ብዙ ወራት ተቆጠሩ ። ታዲያ በዚህ እጅግ ፈታኝ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ችግኝ ተካይነት ከፖለቲካ ጋር ማያያዝ አይገባም ወይም ነውር ነው ብሎ መከራከር ምን የሚሉት ክርክር ነው?
  • ለመሆኑ የአገራችን ፖለቲካ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያልበከለው ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ሥነ ልቦናዊ ፣ መንፈሳዊ (ሃይማኖታዊ) እና ሞራላዊ እሴት የት ይገኛልና ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ ተከላ ዘመቻ ከፖለቲካዊ ሂስ ጋር ለምን ተገናኘ  በሚል ያዙኝና ልቀቁኝ የሚያሰኘን ?  የለውጥ ሽታ በሸተተን ቁጥር ሽታውን  በስሎ ለሚበላ ፍሬነት ለማብቃት ይቻል ዘንድ  ለዘመናት አደንቁረው ሲገዙን የኖሩትን ፖለቲከኞች ሂሳዊ  በሆነ አቀራረብና ድጋፍ ቃላቸውን እንዲጠብቁ ከማድረግ ይልቅ የእራሳችን ግዙፉና መሪር እውነት በመሸሽ መላልሰን የውድቀት አዙሪት ውስጥ የምንዘፈቅበት የፖለቲካ ታሪክ  ማብቃት ይኖርበታል ብሎ መከራከር እንዴት ሁሉን ነገር ፖለቲካ ከማድረግ  ጋር ሊያያዝ ይችላል ?
ተጨማሪ ያንብቡ:  የተቃዋሚ ጎራዉ የወያኔ መዉደቂያ ደረሰ የሚለዉ ወቅታዊ አጀንዳ መሰረቱ ምን ይሆን?

 

  • የለውጥ አራማጆች የምንላቸው ኦዴፓ/ ኢህአዴጋዊያን እንደማነኛውም የለውጥ አራማጅ ነኝ ብሎ እንደሚነሳ  ፖለቲከኛ ቡድን ሥልጣነ መንበሩ ይረጋጋላቸውና ይጠናከርላቸው ዘንድ ለዓመታት አደንቁረውና አጎሳቁለው ሲገዙት የቆዩትን መከረኛ ህዝብ በችግኝ ተከላና ሌሎች መሰል ዘመቻዎች እጅግ አሳሳቢ የትኩረት ወይም የቅድሚያ  ቅድሚያ አቅጣጫውን ለማስቀየር  መሞከር ሲያልፍም አይነካቸው  ብሎ መከራከርስ ምን ያህል ወደ እውነትነት ይጠጋል ?  በእንዲህ አይነት እጅግ የኮሰመነ አስተሳሰብ በሸፍጥና በሴራ በእጅጉ ከተበከለው የፖለቲካ አዙሪት ለመውጣትና የምንመኘውን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ እንዴት ይቻለናል?
  • ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበት ሥርዓት እንደ ሥርዓት መቀጠል ብቻ ሳይሆን ይበልጥ ሸፍጥ ወደ ተሞላበት አዙሪት ውስጥ እየተዘፈቀ ያለበትን መሪር ሃቅ በችግኝ ተከላ ዘመቻ ፕሮፓጋንዳ በተበከለ መዋዕለ ዜና እና ትርክት ለማካካስ መሞከር መከረኛውን ህዝብ የማያስብ ፣ የማያገናዝብና የማይታዘብ አድርጎ መገመት (dehumanization) አይሆንም እንዴ?
  • ከሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች በተለየ ኦነግን አሥመራ ድረስ ተጉዞ በመጎናበስ ለህዝብ ባልተገለፀ ስምምነት መሠረት ቀይ ምንጣፍ አንጥፎ የተቀበለና ትጥቅ ፈትቷል የተባለው ሠራዊት አገርን ሲያመሰቃቅልና በአሥራዎች የሚቆጠሩ ባንኮችን ሲዘረፈፍ ከቆየ በኋላ እንደ መንግሥት በህግ አግባብ ከማስተናገድ ይልቅ በሽምግልና /በገዳ ስም ( በአሁኑ ጊዜ እውን እውነተኛ ሽምግልና አለ ወይ የሚለው እንደተጠበቀ) በክብር እየተቀበሉ አሠልጥኖ የመንግሥት ሠራዊትና የፀጥታ አካል ለማድረግ  እየተሠራ መሆኑ ግልፅ ነው። ታዲያ ይህ እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ጨዋታ  እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ውስጥ እና  የራሳቸውም ሆነ  የወገናቸው መሠረታዊ  መብት ይከበር ዘንድ የሚጠይቁ ንፁሃን ዜጎች በሚዋከቡበትና  የቁም ስቃይ ሰለባ እየሆኑ ባሉበት መሪር እውነታ ውስጥ  የችግኝ ተከላውና ሌሎችም በጎ የሚመስሉ ዘመቻዎች ከፖለቲካ ሸፍጥ ነፃ ናቸው ብሎ መከራከር እንዴት የመልካም ዜጋ ባህሪ መገለጫ ሊሆን ይችላል?
  • በብሄራዊ እርቅና ሰላም ጉዳይ፣ በወሰንና የማንነት ጉዳይ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚነሱና ለለውጥ አራማጅ ተብየ የኢህዴግ ፖቲከኞች ፈታኝ የሆኑ ጥያቄዎችን ለማርገብና ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ በሚመች ሁኔታ ለማስኬድ  የተቋቋሙትን ኮሚሽኖች ከምር ለሚከታተልና የመሠረታዊ ዴሞክራሲዊ  የሥርዓት ለውጥን እውን መሆንን ተስፋ ለሚያደርግ የአገሬ ሰው የችግኝ ተከላ ዘመቻውን ከሸፍጥ የፖለቲካ ተውኔት ነፃ ነው ብሎ ለመቀበል እንዴት ይቻለዋል  
  • ከበሰበሰውና ከከረፋው ኢህዴጋዊ ሥርዓት ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የሚያስችል የሰው ሃይል በተገቢው የሥልጣንና የሃላፊነት ቦታ ላይ ከማስቀመጥ ይልቅ የሃምሳ ፐርሰንት የሴቶች ተሳትፎ ትርክትን ልክ ለሌለው የግልና የቡድን የፖለቲካ ዝና ማድመቂያነት የተጠቀመ ጠቅላይ ሚኒስትር የችግኝ ተከላ ዘመቻን ለተመሳሳይ ዓላማ ለማዋል አይሆንለትም ብሎ መከራከር ምንያ ህል  ሚዛን የሚደፋ አሳማኝነት ይኖረዋል?
  • የበሰበሰውንና የከረፋውን የኢህአዴግ ሥርዓት የተሸከሙት እጅግ ወሳኝ ምሰሶዎችና መረቦች እንዳሉ በቀጠሉበት የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ በነበራቸውና ባላቸው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ እውቅና ምክንያት የፖለቲካ ትርፍ ያስገኙልኛል የሚላቸውን ግለሰቦች (ወ/ት ብርቱካን ሜዴቅሳንና ዶ/ር ዳንኤል በቀለን) የምርጫ ቦርድ እና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የበላይ አለቆች አድርጎ በመሾም የሸፍጥ ፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ያደረገ ጠቅላይ ሚኒስትር የችግኝ ተከላ ዘመቻውን ለተለየ ተልእኮ ይጠቀምበታል ብሎ ማሰብ ወይ የድንቁርና ወይም ደግሞ የለየለት የአሽቃባጭነት የፖለቲካ ሰብእና ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል ?
  • ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥርሳቸውን ነቅሎ ያሳደጋቸው ህወሃት/ኢህአዴግ በህገ መንግሥት ደረጃ ደንግጎ ሥራ ላይ ባዋለው የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ የሃይማኖት ተቋማትን ሳይቀር በማዳረሱ ምክንያት ጎራ ለይተው ሲናቆሩ የኖሩ የሃይማኖት መሪዎች የተጀመረውን አወንታዊ ለውጥ በመጠቀም በራሳቸው ተነሳሽነትና ነፃ ፍላጎት እርቀ ሰላም እንዲፈጥሩ ማሳሰብና ማበረታት ከአንድ የፖለቲካን (የመንግሥትን) እና የሃይማኖትን ግንኙነት በአግባቡ  ከሚያውቅና ይህንኑ ግንኙነት መስመሩን ሳያልፍ እንዲቀጥል ማድረግ ከሚችል  የአገር መሪ የሚጠበቅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  ያደረጉት ግን ከዚህ አልፎ የሄደ ነበር (ነው)። ከሁሉም በላይ የሆነውን (የሚበልጠውን)  መንፈሳዊ ተልእኮ እንደተሸከሙ የሚያስተምሩ (የሚሰብኩ) የሃይማኖት መሪዎች የለውጡን ጅማሮ ጊዜ ወስደው  በጥሞና እና በቅንነት በመገምገም ያለ ፖለቲከኞች ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ወደ አንድነት የሚመልስና ከፖለቲካ ንፋስ ጋር አብሮ የማይዋዥቅ እርቀ ሰላም እንዲያወርዱ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ዋጋና ክብር በሚሰጠው ሃይማኖታዊ እምነት በኩል በመሄድ የፖለቲካ ተቀባይነትን ከዓለማዊው አልፎ ሰማያዊ ገፅታ ለማላበስ የተሞከረ ፖለቲካዊ ጨዋታ ጨርሶ አልነበረበትም ማለት እውነትነት የለውም ።
ተጨማሪ ያንብቡ:  "የኦነግ ጭፍጨፋ ተብለው ከሚጠቀሱ ትራጄዲዎች መካከል አብዛኛዎቹ በኦነግ የተፈጸሙ አልነበሩም" - ከአፈንዲ ሙተቂ

የሁለቱን ተቋማት (መንግሥታዊ እና የእምነት) የግንኙነት ገደብ በተቻለ መጠን ሚዛኑን ጠብቆ እንዲሄድ አለማድረግ ምን ያህል አስቀያሚ ሁኔታ እንደሚፈጥር በመሬት ላይ እየሆነ ካለው መሪር ሃቅ በላይ የሚነግረን የለም። እርቀ ሰላም አወረድን ያሉ የሃይማኖት መሪዎችና መምህራን (ሰባኪያን) የተጀመረው የለውጥ ጅማሮ ብዙም እርቀት ሳይሄድ የንፁሃን ዜጎች ህይወት ምስቅልቅሉ ሲወጣ እና አሁን ደግሞ “መፈንቅለ መንግሥት ተሞከረብኝ” በሚል የተንሸዋረረ የፖለቲካ ትርክት በርካታ ዜጎች እየተዋከቡና ኢሰባዊ በሆነ የእስር ቤት አያያዝ እየተጎሳቆሉ  በሚገኙበት ወቅት ያስታረቋቸውን ፖለቲከኞች ደፍረው ለመገሰፅ የሚያስችል  የሞራልም ሆነ የመንፈሳዊ ወኔ ማጣታቸው የሚነግረን ይህንኑ የሁለቱ ተቋማት የተሳሳተ ግንኙነት አስቀያሚነት ነው።

ታዲያ እንዲህ አይነት የፖለቲካ ጨዋታ የሚጫወቱ ፖለቲከኞች የችግኝ ተከላ ዘመቻን የሸፍጥ ፖለቲካ ኢላማ ለማድረግ አይደፍሩም ማለትን ወይ በየዋህነት ወይ በድንቁርና ወይም ደግሞ በአድር ባይነት ልክፍት ካልሆነ በስተቀር በሌላ በምን ሊገለፅ ይችላል ?

ይህ ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴ ለበርካታ ወገኖች ስሜት አስቸጋሪ ሊሆንባቸው እንደሚችል በሚገባ እረዳለሁ ። እንደ እኔ አረዳድና እምነት ግን ለስሜት በእጅጉ  የሚከብደው በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለሙዊው መንበረ ሥልጣን ላይ ተቀምጦ የተሸከመውን ሃላፊነትና ተልእኮ በአርበኝነት መንፈስና ቁመና ለመወጣት አለመቻል ወይም የሸፍጠኝነት ባህሪ ሰለባ ሆኖ መገኘት ነውና ከበርካታ ወገኖቼ ከቅንነትም ይሁን ከተቃራኔው መንፈስ የሚሰነዘር የውግዘት አስተያየት ቢኖር ጨርሶ አይገርመኝም ።

  • የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ከህግና ከሥነ ሥርዓት ውጭ ማስኬድ ብርቱ ቅጣት እንደሚያስከትል ከማስጠንቀቂያ ጋር በፓርላማ ተብየው ፊት የተናገረ ጠቅላይ ሚኒስትር  የሲዳማን ቀውስ  በአሥመራ አውራ ጎዳና ላይ (በሌላ አገር መሪ ሹፌርነት) መኪና እየሾፈረ በርቀት ሲከታተል እየተሸማቀቅንም ቢሆን ታዝበናል ። ይህ አይነቱ አስከፊ ቀውስ ሊከሰት በተቃረበ ቁጥር ለሥራ ወይም ለመተዋወቅ (ለመታወቅ) ወደ ውጭ  የመጓዝ ጉዳይ መደጋገሙን ልብ ብሎ ለታዘበ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ሰው ምነው ከሸፍጥ ፖለቲካ አዙሪት መውጣት አልሆንልን አለ ? የሚል መሪር ሃዘን ልቡን ቢሰብረው ምን ይገርማል ?

እንኳን ከባድ  የፖለቲካ ቀውስ ባለበት ሌላም ጊዜያዊና የተወሰነ ችግር በሚያገጥም ጊዜ ጉዞን ከይቅርታ ጋር ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ማስተላለፍ የተለመደና ተገቢም ነው ። ታዲያ  ከሌላው አገራዊ ችግር ላይ የሲዳማው ተጨምሮ አገርን ሲያመሰቃቅል እየተመለከቱ  ሲሆን ጉዞን ማስተላለፍ ፣ ያም ካልሆነ ጉዳይን በቶሎ ጨርሶ ወይም አቋርጦ  መመለስና አስቸኳይ የመፍትሄ እርምጃ በመውሰድ ቢያንስ የደረሰውን ጉዳት መቀነስ እንዴት አልተፈለገም (አልተቻለም)?

 

በሚገርም ሳይሆን (በአገራችን ፖለቲካ የሚገርም ነገር የተለመደ እየሆነ መጥቷልና)   በሚያሳዝን ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ከተመለሱም በኋላ  የመጀመሪያ ሥራቸውን የችግኝ ተከላ አዝማችና ዘማች በማድረግ  ተመልሶ ወደ ፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት አዙሪት የገባውን የመንግሥትና የአፍቃሬ መንግሥት የግል ሚዲያ በማሰማራት የለውጥ ሃዋርያነቱን ገድል ትርክት ለኢትዮጵያና ለዓለም ማህበረሰብ እንዲሰራጭ  ማድረግ ነበር ።

 

አቶ መለስ ዜናዊን “ታላቁ አፍሪካዊ መሪ” በሚል ሲያሞካሹ የነበሩት የውጭ አገራት መንግሥታትና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም “የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማሻሻያ (reform) ፍርፋሪ  ለኢትዮጵያ ህዝብ መች አነሰው” በሚል አይነት ንቀት የተነገራቸውን ወይም የሰሙትን ወይም ያነበቡትን “የችግኝ ተከላ ገድል”  እድሜ ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  በደቂቃዎች ውስጥ አስተጋብተውታል ።  ፖለቲከኞቻችንና ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር የአድር ባይነት ጭራቸውን የሚቆሉ ወገኖችም የስኬታማነታቸው ምስክር እያደረጉ በየዲስኩሮቻቸው በኩራት ማጣቀሻ አድርገውታል ። ለአገራቸው (ለእራሳቸው) እንኳን ችግኝ መትከል ተአምራዊ እድገት፣ልማትና ብልፅግና እውን ለማድረግ የሚችሉ ሚሊዮኖች  ከህፃናትና አቅመ ደካማ   ቤተሰቦቻቸው ጋር ከበቀሉበት የገንዛ አገራቸውና ቀያቸው እየተነቀሉ ለምድር ሲኦል የመዳረጋቸው መሪር እውነት ብዙም ጉዳያቸው አይደለም። ለነገሩ እኛ ጉዳያችን አድርገን ፖለቲከኞችን “ከዚህ አይነት የበሰበሰና የከረፋ የፖለቲካ ጨዋታ ውጡና የፖለቲካ ዲስኩራችሁ ማሳመሪያ ያደረጋችሁትን የንስሃና የይቅርታ ቃል ወደ መሬት አውርዳችሁ ትርጉም እንዲኖረው አድርጉ” ማለት የተሳነንን እነሱን (የውጭ አገራት መንግሥታትንና ሚዲያዎችን) መውቀስ በራሱ ብዙም ትርጉም አይሰጥም። ታዲያ እንዲህ አይነቱን በፖለቲካ ጨዋታ የተበከለውን ችግኝ ተካይነት የፖለቲካ ሸፍጥ የተጠናወተው መሆኑን በቀጥታና በግልፅ መግለፅ እንዴት ባዶ የፖለቲካ አኡታና  የጠቅላይ ሚኒስትሩን ክብር  መጋፋት ሊሆን ይችላል  ?

 

  • ሚሊዮኖች ንፁሃን ነፍሶች ከገንዛ ቀያቸው ተፈናቅለው ምድራዊ ሰቆቃ በሚቀበሉበት የነገ ህይወታቸው ከወላጆቻቸው ህይወት የተሻለ ይሆናል በሚል ከብርቱ ድህነት ጋር እየታገሉ ይማሩ የነበሩ ህፃናትና ታዳጊ ወጣቶች በወላጆቻቸው መፈናቀልና ለሰቆቃ ህይወት መዳረጋግ ምክንያት በሥነ ልቦና ቀውስ ሙሉ ሰው ሆኖ የመገኘት የነገ ተስፋቸው በእጅጉ በጨለመበት በጎሳ/በዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካና በሃሰት ታሪክ መሰል ትርክት ጨርሰው ያበዱ ወገኖች በተለይ የኦሮሞ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ነን ባዮቸ የህወሃትን እኩይና አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ ካልተጫወትን በሚል ያዙንና ልቀቁን በሚሉበት ብአዴን/አዴፓ የሚባል ድርጅት ከአሽከርነት ሥነ ልቦና እና የፖለቲካ ጨዋታ ለመውጣት ባልቻለበት ፣ ደህዴን የሚባለው ደግሞ መኖሩም ትርጉም የሌለው በሆነበት ህወሃት በእራሱ እጅግ እርኩስና አረመኔ በሆነ አገዛዝ ምክንያት የተፈጠረውን አገራዊ ቀውስ የራሱን “ገድላዊ ታሪክ” ተናፋቂ ለማድረግ በሚቅበዘበዝበት ከመቶ በላይ የሚቆጠር ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ተብየ በቅንነትና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ህብረት ወይም ቅንጅት ወይም ውህደት በመፍጠር የበሰበሰውንና የከረፋውን የኢህአዴግ ሥርዓት አስወግዶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት አማራጭ ከመሆን ይልቅ የለውጥ አራማጅ ከሚላቸው ፖለቲከኞች ጫማ ሥር በሚንደፋደፍበት እና  በአጠቃላይ ህዝብ ከሞቱት በላይ ካሉት ግን በታች በሆነ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ በሚገኝበት እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እየጓጎጡ  ይህን ያህል  ቁጥር ያለው ችግኝ አፈር ውስጥ በመሸጎጥ “የዓለምን  ሪኮርድ የሰበረ መሪነቴ ይታወቅልኝ” በሚል ልክ የሌለው የግል ዝናን  የማራመድ  ዘመቻ (excessesive self-agrandizemnt ) መጠመድ ከፖለቲካ ሸፍጠኝነት ውጭ በሌላ እንዴት ሊገለፅ ይችላል ?
ተጨማሪ ያንብቡ:  ህገ-ፓርቲ/ ኢህአዴግ  ህገ-ህዝብ አይደለም

 

 

 

ያሳለፍናቸውም ሆነ የወቅታዊው የፖለቲካ ተሞክሮዎቻችን የሚነግሩን መንበረ ሥልጣን  ላይ የሚወጡ ፖለቲከኞቻችን የሚያጋጥሙ ችግሮችን (ቀውሶችን)  በቀጥታ ፣ በግልፅ ፣ የቅድሚያ ቅድሚያን አስፈላጊነት በተከተለ አሠራር  ፣  ለራስም ሆነ ለህዝብ ታማኝ በሆነ  ፖለቲካዊ አቀራረብና ተግባር  ከማስተናገድ ይልቅ  በተለያዩ የኢትዮጵያን  ህዝብ እና የዓለም የወሬ አውታሮችን ቀልብ በሚስቡ ዘመቻዎች (ትእይንቶች) ሸፋፍኖ ለማለፍ የማያደርጉት ጥረት እንዳልነበረና አሁንም እንደሌለ ነው።  ይህንን ግዙፍና መሪር ሃቅ በተለያዩ ልፍስፍስ ሰበቦች ( clumsy excuses) ለማስተባበል መሞከር ወይ ድንቁርና ነው ፤ ወይ ከተሞክሮ የማይማር ክፉ አድርባይነት ነው ፤ ወይም ደግሞ  “የዛሬው በደልና በዳይ ከትናንቱ የተሻለ ስለሆነ የባሰ አታምጣ” የሚል እጅግ ከሰብዊ ፍጡር በታች የሚያውል ክፉ ልማድ ነው ።

የአገራችን ፖለቲካ ከድጡ ወደ ማጡ እየወረደ እንዲመጣ ካደረጉትና ይኸውና ከግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን በኋላም የባሰ ስፉት ጥልቀት ባለው ማጥ ውስጥ እንዲገኝ ካደረጉት አይነተኛ ምክንያቶች አንዱ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የግለሰብ ወይም የቡድን የሥልጣን ፍቅር/ጥም (voracious and dangerously excessive political power hunger) ስለመሆኑ ለመረዳት ወይም ለማስረዳት ቅንነትንና ለእውነት መቆምን እንጅ   ልዩ እውቀት አይጠይቅም ።

ፖለቲካችን የህዝብን የዴሞክራሲያዊ ፣ የሰብአዊና እንደ ዜጋ በነፃነት ሠርቶ የመኖር  መብት ጥያቄዎች  በተለያዩ የትኩረት ማዕከልንና አቅጣጫን በሚያስቱ (በሚያዘናጉ) የዘመቻ ውሎዎችና ትርክቶች (ፕሮፓጋንዳዎች) እጅግ በባሰ ሁኔታ ከተበከለ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል ።

ይህ የፖለቲካ ታሪካችን  የሚነግረን  ህዝብ ቀደም ባሉት አገዛዞች ላይ የነበረውን እጅግ የከረረና የመረረ  ብሶት (እሮሮ) ተጠቅመው ወደ ሥልጣን የሚወጡ  ፖለቲከኞች (ገዥዎች)  የህዝብን የእውነተኞ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጥያቄ የህዝብና ለህዝብ በሚመስሉ ዘመቻዎችና ፕሮግራሞች እያዘናጉ መንበረ ስልጣናቸውን ለማደላደልና ለማራዘም  የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንዳልነበር  እና አሁንም እንደማይኖር ነው።

እናም የአንድ ቀን  የችግኝ ተከላ ዘመቻው የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ መሆን እንደማይገባው ሂሳዊ አስተያየታቸውን የሚገልፁ ወገኖችን “በአሁኑ ጊዜ ችግኝ መትከል አያስፈልግም” ብለው እንደሚከራከሩ አይነት አድርጎ ለማሳየት ከአንዳንድ ወገኖች የሚሰነዘረው ትችት ወይ ከየዋህነትና  ከሂስ አልባ  የለውጥ ሃዋርያት አፍቃሪነት  ወይም ደግሞ ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር እየተገለባበጠ የእውነተኛ ዴሞክራሲዊያዊ ሥርዓት እውን እንዳይሆን በማድረግ በእጅጉ ከአስቸገረን  ክፉ የአድርባይነት  ልክፍተኝነት  የሚመነጭ ነው ።

ለዚህ ደግሞ ከገዥዎች ቀጥሎ በህግም ባይሆን በሞራልና በመልካም የዜግነት ውድቀት ተጠያቂው በዓለማዊው ወይም በመንፈሳዊው (በሃይማኖታዊው) እውቀት በልፅጊያለሁና ተመራምሪያለሁ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል ነው ።  ዘመን ያዘመነውን እውቀትና ክህሎት የህዝብን የነፃነትና የፍትህ ራእይ (ህልም) እውን ለማድረግ ወደ የሚያስችል  ተግባር ለመተርጎም የተሳነው ልሂቅ ወይም ሊቀ ልሂቃን  የሸፍጠኛ ፖለቲከኞችን የእዩልኝ የፖለቲካ ተውኔት ለምንና እንዴት ብሎ ይሞግታል ብሎ መጠበቅ ያስቸግራል ።

ገና በቅጡ ያልተገራው ፖለቲካችን ያልበከለው የህይወት ዘርፍና መስተጋብር  ከቶ የለም ። እናም ከእንዲህ አይነቱ ክፉ አዙሪት መውጣት ካለብን በግልፅና በቀጥታ እየተነጋገርንና ከትናንቱ አሳዛኝ ውድቀታችንና ከዛሬው ውሏችን በመማር ነገን የተሻለ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ የተሻለ ለማድረግ ለማንምና በማንም ሳይሆን ለራሳችንና በራሳችን ቃል መግባት ግድ ይለናል ።

 

 

 

 

 

Share