ሳትዋጋ ንገሥ ቢሉት “የለም፤እምቢ ተዋግቼ!” – በገ/ክርስቶስ ዓባይ  

ነሐሴ 5 ቀን 2019 ዓ/ም

ዓለማችን ከፍጥረት ጀምሮ ሊታመኑ የማይችሉ እጅግ ድንቅ ድንቅ ነገሮችን አስተናግዳለች። ከታላቁ መጽሐፍ እንደምንረዳው ዮሴፍ በገዛ ወንድሞቹ ወደ ግብጽ ከተሸጠ በኋላ የፈርዖን ባለሟል ለመሆን እንደበቃና በወቅቱ በአካባቢው በተፈጥረው ድርቅ ምክንያት ሰው ሁሉ በረሃብ ቸነፈር ሲያልቅ፤ ወንድሞቹንና አባቱን ማለትም የአሥራ ሁለቱን ነገደ አሥራኤል አባት ያዕቆብን እንደታደጋቸው።

ከግብጽ ሠራዊት ግድያ እንዲተርፍ ከደንገል በተሠራ አገልግል፤ ዓባይ ወንዝ ላይ ተጥሎ ሳለ በልዕልቲቱ የተገኘው ሙሴ፤ በንጉሡ ቤት እንደ ልዑል ከአደገ በኋላ በከፍተኛ ጭቆና ላይ የነበሩትን እሥራኤላውያን ወገኖችን ነፃ ለማውጣት በእግዚአብሔር እንደተመረጠ፤ ሳዖል፤ የጠፋ አህያውን ፍለጋ በሔደበት የእሥራኤል ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ፤ ንጉሥ ዳዊትም ከበግ ጠባቂነት ወጥቶ ንጉሥ ሆኖ እንደተቀባ፤ እንረዳለን።

ከዚያም ወደ ሀገራችን እንኳ ብንመለስ፤ ሻለቃ መንግሥቱ ኃ/ማርያም 3ኛ ክ/ጦርን ወክለው ወደ አዲስ አበባ እንደመጡና በአጋጣሚ የደርግ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ለመሆን በቅተው በዚያው ሰበብ አገር የመምራት ዕድል እንዳጋጠማቸው፤ ሟቹ መለስ ዜናዊም እንዲሁ ከተራ አማፂነት (አጋሚዶነት) የኢትዮጵያ መሪ የመሆን ዕድል አንዳጋጠማቸው የሚዘነጋ አይደለም። በማስቀጠልም አቶ ኃይለ ማርያም ደሣለኝም እንዲሁ ሰው በጠፋበት ወቅት ተገኝተው ጠ/ሚንስትር የመሆን ዕድል አጋጥሟቸዋል። ሁሉም ግን የሚመሩትን ሕዝብ በማይመጥን ተግባር ላይ በመሠማራት ሕዝባቸውን በመግደል፤ በእሥራት፤ በግርፋትና በስደት፤እንዲሁም በፍርድ መጓደል ሲያስመረሩ ቆይተው፤ከሕዝቡ ምንም ዓይነት ክብርና ሞገስ ሳያገኙ እንደተጠሉ ከኃላፊነት ተነስተዋል።

ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እንዲሉ ዶ/ር ዓቢይ አህመድም ከላይ ከተገልጸው ባልተለየ መልኩ በኢሕአዴግ መካከል በተፈጠረ ድንገተኛ የሥልጣን ክፍተት፤ እጅግ በጣም በሚገርም ተዓምር ወደ ኃላፊነት መጥተዋል። ዶ/ር ዓቢይ ለዚህ ሥልጣን ከመብቃታቸው በፊት ታዋቂ ሰው አልነበሩም። ምናልባት የሚታወቁ ቢሆን እንኳ ለነበረው አገዛዝ ታማኝ አገልጋይ በመሆን፤ የንጹሐን ዜጎችን ገመና እጅግ በረቀቀ መሣሪያ እየተከታተሉ በመመረጅ፤ለእሥር፤ ለአሰቃቂ ግርፋትና ግድያ በመዳረግ፤ ኑሯቸውንና የሕይወታቸውን መሠረት ሲያናጉ እንደነበር የሚረሳ አይደለም።

ይሁንና ወጣቱ ዶ/ር ዓቢይ በበዓለ ሹመታቸው ለፓርላማውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል ኪዳን በፈጸሙበት ወቅት ያደረጉትን ማር የተቀባ ማደንዘዣ ንግግር በማዳመጥ፤ ልጅ አዋቂው፤ መሃይም ምሁሩ፤ ሴት  ወንዱ፤ ነጋዴው ፤ ገበሬው፤ ተማሪና አስተማሪ፤ ላብ አደሩ ወታደሩ፤ ሸኪውና ፓስተሩ፤ ቄሱና ጳጳሱ፤ አገሬውና ዲያስፖራው፤ በአጠቅላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚባል መልኩ የደስታ ሲቃ ይዞት ዕልል እያለ አጨበጨበላቸው። ከዚያም እውን ቃልና ተግባር ይጣጣሙ ይሆን? በማለት በአንክሮ ሲከታተል ቆየ።

ዶ/ር ዓቢይ በቃል ኪዳናቸው ጸንተው ብዙም አልተጓዙም። በሆነ ኃይል ተጠልፈዋል ወይም ደግሞ በዘር ሥጥን ውስጥ ገብተው ታፍነዋል። ሰውየው የቃል ኪዳን ትርጉሙም የገባቸው አይመስልም። እመኑኝ ግን “ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ!” ዓይነት፤ ነግሮችን እንደማያውቁ በመምሰል ቀስ በቀስ አንዳንድ አጠራጣሪ ውሳኔዎችን ማስተላላፍ ጀመሩ። ይኸውም በጃዋር መሐመድ የሚመራው OMN ኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ ከሁሉም በፊት በአስቸኳይ በአዲስ አበባ እንዲቋቋም የማድረጋቸው እርምጃ የፖለቲካ ሀሁ የሚያውቁትን አንዳንድ አክቲቪስቶች ‘እንዴት?’ የሚል ጥያቄ አጭሮባቸዋል። ቀጠሉና  ለእርሳቸው ሥልጣን ላይ መውጣት ምክንያት የሆነላቸውን  ሕዝብ ያልፈለገውን ሕገ መንግሥቱን የማማሻሻል ጥያቄ በተቃራኒነት በመቆም እንዲያውም ተከራካሪ ሆነዋል።

በአንፃሩም እርሳቸው የሚፈልጉትን ደንብ በማሻሻል ከተለመደው አሠራር ውጭ ኢንጂነር ታከለ ኡማን የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ አድርገው ሾሙ። በዚህ አላቆሙም፤ ቁልፍ ቁልፍ የመንግሥት ሥልጣኖችን በኦሕዴድ ቁጥጥር ሥር ለማድረግ የሄዱበት እርቀት ሌሎችን የኢሃዴግ ዓባል ድርጅቶችና አጋር ፓርቲዎች ተዋጽዖ ያላመጣጠነ እየሆነ ሔደ።

አሁንም ቀጠሉና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በአሸባሪነቱ የተመዘገበውን ኦነግ፤ ያለ ሠፊው ሕዝብ ዕውቅና እና በይፋ የሚታወቅ አንዳች ቅድመ ሁኔታና ስምምነት ሳይኖር፤ ወደ አገር ቤት እንዲገባ ፈቀዱ። በሰበቡም ከአገራቸው ተገፍተው በስደት ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ቢሆንም፤ ግን ዋናው ዕቅዳቸው ኦነግን ለማስገባት መሆኑ ይሠመርበት።

በዚህም አላበቁም፤ በርካታ ባንክ አስዘረፉ፤ ኅልቆ መሣፍርት የሌለው ሠራዊት አሰልጥነው በእጅ አዙር አስታጠቁ፤ የአካባቢውን ዴሞግራፊ ለመቀየር በሚል ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኦሮሞዎችን በስልታዊ መንገድ በአዲስ አበባ ዙሪያ እንዲሠፍሩ አስደረጉ። በቡራዩና በለገጣፎ የተካሄዱትን ጭፍጭፋ፤ እና ዘር ተኮር የሆነ ቤት በዶዘር እያፈረሱ ንጹሐን ዜጎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ማፈናቀልን አስተገበሩ። ሆኖም እሳቸው ግን ይህን ሁሉ አላውቅም በማለት ሽምጥጥ አድርገው በአደባባይ ካዱ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአማራ ህዝብ የዘር ማጥፋት ተጠያቂዎች ወያኔ፣ ኦነግ፣ ጉሙዝና ብልፅግና በሄግ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ!

በመሠረቱ በአዲስ አበባ ዙሪያ ቀደም ሲል ጀምሮ የሚኖሩ ኦሮሞዎች እንዴት በዚያ አካባቢ መኖር ጀመሩ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያለብን ይመስለኛል። በአዲስ አበባ አካባቢ ወይም በቀድሞው አጠራር የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ንብረትነቱ የአማራ ባላባቶች አንደነበረ አጠያያቂ አይደለም። እነዚህ ባላባቶች በርካታ የሆኑ ግብርና ተኮር ሥራዎችን ያከናውኑ ነበር። ታዲያ በነዚህ የግብርና ዘርፎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሰዎች ያስፈልጉ ነበር።

እነዚህ ተቀጣሪዎች በአብዛኛው የሆኑት ኦሮሞዎች፤ መኖሪያቸውን በዚያው አድርገው እንዲሠሩ፤ ለቤተሰቦቻቸው የሚሆን ቤት ጭምር በአሠሪው ባላባት ተሠርቶ ይሰይጣቸው ስለነበር ግንኙነታቸው እንደ ቤትሰብ እንጅ እንደ ቀጣሪና ተቀጣሪ አልነበረም። እንዲያውም አንዳንዶቹ የእነዚህ ሠራተኞች ልጆች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ሲገቡ ባላባቶች እንደ ልጆቻችው አድርገው ያስተምሯቸው እንደነበር ይታወቃል። በዚህ ሁኔታ የተማሩ ሰዎች ወጥተው ሐቁን ቢናገሩ አገራችን አሁን ለወደቀችበት የሐሰት ትርክት እውነተኛ ማስረጃ ሊሆን ይችላል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በ1960ዎቹ ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ፤ ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ በውጭ ኃይሎች በተሠራጨው የ ‘መሬት ላራሹ’ ጽንሰ ሐሳብ እንደ ሰደድ እሣት መስፋፋት ጀመረ። ይህም ሐሳብ በተማሪዎች አማካይነት ወደ ወላጆችና ሌሎችም ኃይሎች በስፋት ተዛመተ። ከእነዚህም ውስጥ የመለዮ ለባሹ ይገኙበታል። ከዚያም ሐሳቡ ለተወሰኑ ዓመታት በሕዝብ ውስጥ ሲብላላ ቆይቶ በየካቲት ወር 1966 አብዮቱ መፈንዳቱ አይዘነጋም።

ቀጥሎም የጉዳዩ አሳሳቢነት እጅግ ያሰጋቸው ሻለቃ አጥናፉ አባተ፤ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣቱ በፊት ሥርዓት ለማስያዝ፤ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት በአደረጉት አስተዋጽዖ፤  በቅድሚያ እሣት በእጁ ያለውን ማለትም የጦር መሣሪያ የታጠቀው ኃይል ጸጥታ የማስከበሩን ኃላፊነት በጥራትና ብቃት እንዲወጣ ማስቻል እንዳለባቸው አመኑ።

ከዚያም ይህንን እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ፤ የተለያዩ መለዮ ለባሾች በመናበብ እንደ አንድ ኃይል ሆነው በመግባባት እንዲሠሩ በማሰብ፤ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ልዩ ልዩ ክፍሎች ተወካዮቻቸውን በመምረጥ ወደ አዲስ አበባ እንዲልኩ መመሪያ አስተላለፉ። በዚያም መሠረት መሿለኪያ አካባቢ በነበረው የአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ እንዲገቡ በማድረግ ደርግ የተባለው ወታደራዊ ቡድን ተመሠረተ።

ደርግ ከአሥር አለቃ ጀምሮ እስከ ሻለቃ ማዕረግ ድረስ ያላቸው የ120 ዓባላት ስብስብ እንደነበር ይታወቃል። ታዲያ ደርግ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ታማኝ መሆኑን እየገለጸ ቀስ በቀሰ ታላላቅ የመንግሥት ሹማምንትን እያደነ ወደ ከርቸሌ አስገባ፤ ቀጥሎም ያለ ፍርድ በኢትዮጵያ ታሪክ አሰቃቂ የሆነውን ጅምላ ርሸና ፈጸመ። ከዚያም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በሕዝቡ ውስጥ ሲብላላ የቆየውን ጥያቄ ለመመለስ ሲል የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ/ም ምንም ዓይነት ጥልቅ ጥናት ያልተደረገበትን ‘የመሬት ላራሹን አዋጅ’ በግብታዊነት አወጀ። በማከታተልም ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ/ም የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅን ያለምንም ጥልቅ ጥናት እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ በግብታዊነት አወጀ።

ከዚያም እነዚህ ሠራተኞች የሠፈሩበትን ቦታ እንደያዙ ጸኑ። በተለይ በአዲስ አበባ አካባቢ የነበሩት ገበሬዎች ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት መሐንዲሶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር መሬታቸውን ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር እንዳይጋጭ አስደርገው በማስቀየስ ከአሸነሸኑ በኋላ፤ በወቅቱ በነበረ የመሬት ዋጋ እየቸበቸቡ ተጠቃሚ ሆነዋል።ኑሯቸውም በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል። በዚህ አጋጣሚ አንጋፋው አርቲስት ዓለማየሁ እሻቴ ከኢልካ አለፍ ብሎ በሚገኝ ሠፊ የእርሻ ቦታ ይኖር እንደነበር ይታወቃል። በአጋጣሚ በሕይወት ስለአለ በእንዴት ያለ ሁኔታ መሬቱን እንዳገኘው ቢጠየቅ ሐቁን ግልጥልጥ የሚያደርግ ይመስለኛል።

ወያኔ በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜም የኦሕዴድ ዓባላት ከገበሬው ጋር እየተመሳጠሩ መሬቱን በመሸንሸን በወቅቱ በነበረ የመሬት ዋጋ ሲሸጡና ሲካፈሉ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። አሁን ደግሞ እንደገና ያንኑ ሽጠው የበሉትን መሬት፤ መልሰው በኃይል ለመውረስ የሚያደርጉት እሩጫ የግፍ ግፍ ነው። እንዲህ ያለውን ሥርዓት አልበኝነት ከጀርባ ሆነው ሽፋን በመስጠት የሚያስፈጽሙት ወናፉ ጠ/ሚንስትር ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ አዋጆች፤ ጥንታዊ የሆነውን የባላባትነትን እና የእርስትን ሥርዓት፤ ያለ በቂ ጥናት ያፈረሱና የዘረፉ በመሆኑ፤ አገራችን አሁንም ሆነ ገና ለወደፊት ለሚያጋጥሟት ውጥንቅጥ ችግሮች እንደ መሠረታዊ ምክንያት ሆኖ ይቀጥላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አብይ አህመድ ሀገራችን ኢትዮጵያን ገደል ለመክተት በከፍተኛ ፍጥነት እየተንደረደረ ነው

እዚህ ላይ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ስለባላባታዊና የእርስት ሥርዓት ትንሽ ማብራሪያ መስጠት ተገቢ ይሆናል። የባላባት ሥርዓት ማለት እንደ አሁኑ ዘመናዊ የጦር ሠራዊት ባልተደራጀበት ዘመን፤ አገር በተወረረች ጊዜ የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት መንግሥት፤ የግዛት ሉዓላዊነትን የሚፈታተን የባዕድ ኃይል በተከሰተ ጊዜ፤ ነጉሠ ነገሥቱ ነጋሪት ያስጎስማል የጦር ክተት አዋጅ ያውጃል።

ለምሳሌም የበኦቶማን ቱርክ የታገዘው የግራኝ አሕመድ ወረራ ከ1526-1555 ዓ/ም ድረስ አፄ ልብነ ድንግል የተሰውበት በ1521 ዓ/ም የተደረገው የሽምብራ ኩሬው ጦርነት፤ የደርቡሽ ወረራ በ1891፤በጄኔራል ናፒር የተመራው የ1860 ዓ/ም የእንግሊዝ ወረራ፤ በስዊዙ የጦር ጄኔራል ሙዚንገር አማካይነት፤ በእስማኤል ፓሻ መሪነት የተካሄደው የግብጽ ወረራ በ1868 ዓ/ም የተካሄደው የጉራዕ ጦርነት፤ ለአፄ ዮሐንስ ሞት ምክንያት የሆነው ከመሀዲስቶች ጋር መተማ ላይ 1881 ዓ/ም የተደረገው ጦርንርት፤ እንዲሁም በተደጋጋሚ ጊዜ ከጠሊያን ጋር የተደርጉትን ጦርነቶች ዶጋሊ ላይ በ1879ዓ/ም እና አድዋ ላይ በ1888 ዓ/ም የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።

በእነዚህ ዓይነት ጦርነቶች ቤተሰቦች በስራቸው ከሚገኙ ለአቅመ አዳም የደረሱትን ሰዎች አስከትለው፤ በራሳቸው ስንቅና ያላቸውን የጦር መሣሪያ ታጥቀው ይዘምታሉ። እንደሚታወቀው ጦርነት ሠርግ አይደለምና የመግደልም የመሞትም ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። ታዲያ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ጉዳት ለደረሰባቸው የጀግና ቤተሰቦች መተዳደሪያ የሚሆን መሬት ተከልሎ በመንግሥት ይሰጣል። እንዲህ ያለው የመሬት ሥሪት የጀግና ቤተሰብን የሚያመለክት፤ የቁርጥ ቀን ጀግና ሰው የተገኘበት ቤተሰብ መሆኑን ያመለክታል።

ባላባት ማለት የጀግና ዘው ዘር ማለት ሲሆን፤ እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ ስም አይደለም። አሁን ግን በዘራቸው እንዲህ ዓይነት ስም የሌላቸው፤ ነገር ግን በባለባቶች ደም ነፃነታቸውን የተጎናጸፉት፤ ለሀገር ምንም አስተዋጽዖ ያላበረከቱት ልጆች፤ አስጸያፊ እንደሆነ አድርገው ሲያራክሱት ማየት ኅሊናን ያቆስላል። ዳሩ ምን ያደርጋል እንዲህ ያለውን ክቡር መስዋዕትነት የሚያራክሱትና የሚያጥላሉት ሀገርን በመክዳት ለጠላት ያደሩ እንደ መለስ ዜናዊ ያሉ የባንዳ ዘሮች ናቸው።

እርስት ማለት ግን በምሪትም ይሁን በወርቅ ማለትም በገንዘብ የተገዛ ወይንም በዘር የሚተላለፍ ከአያት ከቅድመ አያት የተወረሰ መሬት እርስት ይባላል።

የጠ/ሚንስትሩ የቂልነት ጨዋታ አሁንም አላበቃም። መላውን ኢትዮጵያ ያስተዳድሩ ተብለው ኃላፊነቱ ተሰጥቷቸው፤ ሥልጣኑን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው እያለ፤ ሆን ብለው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የጥላቻ ትርክት እየፈጠሩ ተራራ እየቧጠጡ ድንጋይ እየፈነቀሉ ያሉትን፤ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ገቢሣን፤ ጃዋር መሐመድን እና በቀለ ገርባን ልዩ ፈቃድ በመስጠት፤ እንደ ቁራ በየቦታው እያስጮሁ፤ የዳውድ ኢብሳን ድርጅት፤ የኦነግን የመገንጠል አጀንዳ ለማስፈጸም፤ አደናጋሪ የሕዝብ አመለካከት ብረዛዎችን በማራገብ ላይ ይገኛሉ።

እጅግ በጣም የሚያስተዛዝበው ጉዳይ ደግሞ የሕወሃት (ትሕነግ) መሰል የግዛት ማስፋፋት ላይ መጠመዳቸው ሲሆን፤ ቤተ አማራ በመባል የሚታወቀውን ወሎን ወደ ኦሮሞ ለማጠቃለል በእጅ አዙር እያካሄዱት ያለው እንቅስቃሴ አገራችንን ወዴት እየመሯት እንደሆነ ለመገመት አይከብድም።

ዶ/ር ዓቢይ የጥቃትን ኃይል የተረዱ አይመስልም፤በዓለም ላይ ከአሉ አረመኒያዊ እርምጃዎች ውስጥ ጥቃት ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል። የጥቃት የመጨረሻው አማራጭ እራስን እስከ ማጥፋት ድረስ ይሄዳል። ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በገዛ እጃቸው ሕይወታቸውን ያጠፉት ጥቃትን ላለመቀበል በወሰዱት ውሳኔ ነው። በጠላት እጅ ወድቆ መዘባበቻ ከመሆን የማይቀረውን መራራ የሞት ጽዋ በመጎንጨት እስከወዲያኛው በክብር ማሸለብን መርጠው ነው።

እንግዲህ የጥቃት ኃይል ይህን ያህል የሚያስጨክን ከሆነ፤ ጥቃት የበዛበት ሰው ለጠላቱ ይመለሳል ብሎ ማሰብ የጅል ጅል መሆን ነው። ጥቃት እየባዛባቸው ያሉት ማኅበረሰቦች የኋላ ኋላ ወደ አንድነት ከመጡ ደግሞ የሚመልሳቸው ምድራዊ ኃይል ፈጽሞ አይገኝም። ምንም ማድረግ ባይቻል እንኳ አጥፍተው በመጥፋት ለቀጣዩ ትውልድ ቤዛ ሆነው ማለፍን ይመርጣሉ። በዚህ አኳኋን የሚገኝ ጥቅም የለምና ሰላማዊ ሕዝቦችን እየገፋፉ ለመጥፎ ነገር ማነሳሳት ለማንም አይበጅም።

ስለሆነም የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት በትኩረት ሊሠራበት ይገባል። በተለይ የአማካሪነት ደረጃ ላይ ያሉ ሐቀኛ ባለሥልጣናት እንዲህ ያለውን አስከፊ ገጽታ አስቀድሞ በመገንዘብ ሁኔታዎችን በጊዜው ማረም ይጠበቅባቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እኔና ስርጉተ--  አልተግባብቶም        ይገረም አለሙ

የበጀት አመዳደቡንም ስንመለከት ሆነ ተብሎ ሕጸጽ እንዳለበት እና የመሠረተ ልማቱ ዕቅድም ለአለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት የበይ ተመልካች ሆኖ ሳያልፍለት የቆየውን የአማራ ሕዝብ ጥቅም በወጉ ያላገናዘበ ነው። ሌላው አማራው ጠንካራ ተቆርቋሪ መሪ እንዳይኖረው መሪዎቹን እንዲያጣ ከተደረግ በኋላ፤ ሕዝቡ ከፍርሃትና ሰቆቃ ሳይላቀቅ በሥጋት እንዲኖር በማሰብ ወጣቱን በጅምላ በማፈስ ወደ እስር ቤት እየጨመሩ መሆናቸው ነው።

የአማራው ሰላማዊ ወጣት በግድ ወደ ጫካ እንዲገባ እየተገፋ መሆኑን የተገነዘቡ አይመስሉም፤ ወይም ከፍተኛ የሆነ ንቀት አሳድረዋል። እንዲህ ያለው ኃላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።

‘ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ’ እንዲሉ አማራው ለዚህ ሁሉ መከራና ግፍ እንዲዳረግ ምክንያት የሆኑት ከራሱ አብራክ የወጡት፤ በምንም መመዘኛ ለአማራው የሚመጥን የመሪነት ብቃት የሌላቸው፤ ደካሞችና የበታችነት ስሜት የተጠናወታቸው፤ እበላ ባይ የአዴፓ ባንዳዎች መሆናቸውን ሕዝቡ ጠንቅቆ ተረድቶታል። ነገር ግን ከዛሬ ነገ ቁጭት አድሮባቸው ይለወጣሉ በሚል በትዕግሥት ቢጠብቅም እየባሰ እንጂ እየተሻለ አልመጣም።  በአሁኑ ሰዓት አማራው ተገፍቶ ተገፍቶ ከገደል አፋፍ ላይ እንደቆመ አውሬ ሊመሰል ይቻላል። ያለው አማራጭ ከሰውነት ወጥቶ ወደ አውሬነት መቀየር ብቻ ነው። ያኔ ግን ለማንም የሚበጅ አይደለም።

ኢትዮጵያ አገራችን በዓለም መድረክ ላይ የተከበረች እንዳልነበረችና ሰላም ያጡ ሌሎች ሀገሮችን ስትሸመግል እንዳልነበረች አሁን ሰው በጠፋበት ወቅት፤ በራሷ ጊዜ ግን ‘ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሲሆኑ’ ተቻችሎ በመኖር ፋንታ፤ ሕዝብ እርስ በእርሱ በግድ እንዲጠፋፋ ግፊት እየተደረገ ይገኛል። እጅግ በጣም ፈታኝና አሳዛኝ ወቅት ነው። የአስተዳደር ልምዱም ሆነ ችሎታው ሲያንስ፤ ጉራ፤ ግለኝነትና ስግብግብነት በየተራ ይፈትናሉ።

እንዲህ የሚሆነው አይቶ ለማያውቅና በቂ ተሞክሮ ለሌለው ሰው ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ ለሚያደርጉት ለማናቸውም ጥቃቅን ነገር በፎቶና በቪዲዮ እንዲቀረጹ ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጡ የድብቁን እና የእጅ አዙር ትዕዛዛቸውን ግን በይፋ የሚያወጣባቸውን እንደጠላት የሚቆጥሩ ናቸው።

የዚህን ስውር ጠባያቸውን አደባባይ ያወጣው በታላቁ ኢትይጵያዊ ዜጋ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራው የባልደራስን የማያወላውል አቋም ከአዩ በኋላ ነው። ሁላችንም እንደምንረዳው የባልደርስ እንቅስቃሴ የአዲስ አበባ ሕዝብ ተወካይ ስሌለው ከፍተኛ የሆነ የአስተዳደር በደልና ግፍ እየተፈጸመበት ስለሆነ ድምጹን የሚያሰማለት፤ ፍትሕ የሚያሰፍንለት፤ ዕትብቱ ከተቀበረበት፤በሕጋዊ መንገድ በምሪት፤ ወይም ንብረቱን አፍ ስሶ በወርቅ ከገዛው ቦታው ላይ ያለአግባብ እንዳይፈናቀል፤ መብቱን የሚያስከብርለት፤ በነዋሪው ሕዝብ የተመረጠ መማክርትና ከንቲባ እንዲኖረው ለማስቻል ነው።

እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ለጠ/ሚንስትሩ የሚዋጥላቸው አልሆነም። ይህንን አስመልክቶ በአንድ ወቅት በንዴትና ስሜታዊ በመሆን በሰጡት መግለጫ ባልደራስ ምናምን እያሉ በሚጮሁ ላይ እንቅስቃሴያቸውን የማያቆሙ ከሆነ ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን በማለት አቋማቸውን አሳውቀዋል።  ከዚህ የምንረዳው ዶ/ር ዓቢይ ኦነግ መሆናቸውን ነው።

ሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላይ ሚንስትሩ ያለው እምነት ቀን በቀን እየተሸረሸረ ሄዷል። ከዚህ አኳያ የተፈጠረባቸውን እምነት የማጣትና የነበረው ጭብጨባ እየቀነሰ መምጣቱን አስመልክቶ፤ በተለይ ወጣቱን እያፈሱ ወደ እሥር ቤት መጨመር ዋነኛ ተግባር አድርገው ይዘውታል። እንዲህ ያለው አካሄድ ለዶ/ር ዓቢይ የአገዛዝ ዘመን ማጠር ዋነኛ ምልክቶች ናቸው። በፍቅርና በእኩልነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠ/ሚንስትር ሆነው ያገልግሉ ቢባሉ፤ ‘የለም እኔ የኦነግ ዓባል እንደመሆኔ መጠን የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ጠ/ሚንስትር ነኝ፤ ይሁን እንጂ እናንተንም በኃይል አስተዳድራለሁ’ በሚል እየተመጻደቁ ናቸው።

ዶ/ር ዓቢይ  የኢትዮጵያን ሕዝብ በሰላም በፍቅርና በእኩልነት አስተዳድር ቢባሉ፤ ምን ታመጣላችሁ? እኔ በአልኩት መንገድ ብቻ በአፈሙዝና እሥር ቤት በማጎር የፈለግሁትን አደርጋለሁ የሚል አቋም መያዛቸውን መገንዘብ ይቻላል። በእንዲህ ያለ ውጥረት ደግሞ ዕድገት የሚታሰብ አይደለም። በዚህ አካሄድ ምርጫም ቢሆን ሲያምረን ይቀራል እንጂ፤ የምርጫ ነገር ጉም እንደመዝገን ይቆጠራል። ዞሮ ዞሮ  የሕዝብ ይሁንታን አግኝተው ሳትዋጋ ንገሥ የተባሉት ዶ/ር ዓቢይ ‘የለም ተዋግቼ!፤ እንዲሉ የአምባ ገነን መንግሥታቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ።

ያዛልቃቸው ይሆን? እንደጸሐፊው ግምግማ ከሆነ እንኳን የመንግሥታቸው የእሳቸውም ዕድሜ አጭር እንደሚሆን ነው። ለማንኛውም ፈጣሪ አምለክ ማስተዋሉን ይስጣቸው።

-//-

Share