ይሄን ጥያቄ የማነሳው መሠረታዊ ነገሮችን እንዳናስብ በቲፎዞ እያደነዘዙ አገርንና ሕዝብን ቀጥሎ ለመዝረፍ እየተፎካከሩ በሚመስል ሁኔታ የፖለቲካ ቡድን ነን የሚሉት ነገር በየትኛውም መለኪያ እድል ቢያገኙ አደገኛ እንደሆኑ ለሕዝብ መጠቆም ግዴታ ስለሆነብኝ ነው፡፡ ኢዜማ አንዱ ማሳያ አደረግኩት እንጂ ኢትዮጵያ ላይ እየተሰራ ያለው የፖለቲካ ቁማር በዋናነት ኢሕአዴግ የተባለ የዘረፋ ቡድን ነው የሚከውነው፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ተፎካካሪ ነን ከሚሉት አንዳቸው እንኳን የአገርና ሕዝብ ጉዳይ ሊሰማቸው የሚችል ሆነው አይታዩም፡፡ እንግዲህ አገራችንን በቅብብል ወንበዴዎች ላይለቀቋት ሁሉም እንደ አንድ ቡድን ይሰራሉ፡፡ አሁንማ እርስ በእርስ እየተሞከሻሹ የሚቀጥለውን የዘረፋ ምእራፍ በጋራ ሊያደርጉት የተዘጋጁ ነው የሚመስለው፡፡
የሰሞኑን የኢዜማ ለዲያስፖራ እቅዱን ለማስተዋወቅ ጉዞ እንደሚያደርግ በየ ፌስቡኩ ተሰራጭቶ ያለውን ማስታወቂያ ሳይ ብዙ ነገር ወደ አእምሮዬ መጣ፡፡ አገርን በቡድን ተደራጅቶ ለመዝረፍ እንጂ ለአገርና ሕዝብ በቁጭት የሚሰራ አንድም እንኳን አለመኖሩ እጅግ ያሳዝናል፡፡ እንግዲህ ይሄ የኢዜማን እንቅስቃሴ እንደማሳያ ልጠቁማችሁ፡፡ መራጩ ሕዝብ ያው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ራሱን ማስተዋወቅ ከአለበት እቅዱን እዛው ለሚመርጠው ሕዝብ ማስተዋወቅ ግድ ይላል፡፡ የሽርሽር ፖለቲካን ሁሉም የተካነበት ይመስላል፡፡ አሜሪካም ሆነ ካናዳ አብዛኛው የአበሻ ዘር የሆነ በዜግነት እንኳን ኢትዮጵያዊ አደለም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ግን ዜጋ ሳይሆኑ በቀጥታ የፖለቲካ ቡድን ውስጥ በዋናነት የሚሳተፉ ቢያንስ አንዳርጋቸው ጽጌና ኤርሚያስ ማዴቦን እንደማሳያ መውሰድ ይቻላል፡፡ እንግዲህ የዜግነት ክብርን እንኳን ጠንቅቆ የማያውቀው ዛሬ ራሱን ኢዜማ በማለት የዜጎች ፖለቲካ ብቸኛ አራማጅ ነኝ የሚለው ቡድን አሁን ደግሞ በአብዛኛው ዜጋም ባልሆኑ ቢሆኑ አንኳ በመራጭነት ለመሳተፍ ትንሽ እድል ላላቸው በዋናነት ፕሮገራሜን አስተዋውቃለሁ እያለን ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንን ማን ከቁም ነገር ይቆጥራል? ምጽዋትና ቲፎዞ የሚሆኑትን ማሳመን እንጂ፡፡ ዜጋ ላልሆነው ዲያስፖራ ራሴን አስተዋውቃለሁ የሚለው በዜግነት የሚቀልደው 100 ሚሊየን ዜጎች አብዛኛው ከነመኖሩም አያውቅም፡ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ሕዝብ ግልጽ የሆነ የውንብድና ሴራ ሲሰራበት ዝም ማለታቸው ሳያንስ የዜጎች ራሳቸውን ከወሮበሎች እንዲከላከሉ የሚቀሰቅሱትንም ሲያወግዙ የነበሩ ናቸው እንግዲህ ዛሬ ስለዜጋ ከእኛ ውጭ የለም የሚሉን፡፡ አንዱ እስክንድር ለዜጋ እያደረገ ያለውን ማየት በቂ ነው ዜግነት ማለት ከገባን፡፡ ዛሬ በእስክንድር ላይ ሁሉም በትብብር የሚዘምቱበት ግልጽ የሆነ የፍትህና የዲሞክራሲ መርህ ላይ ቆሞ የእነሱን ነገር እያበላሸባቸው ስለሆነ ነው፡፡ እንጂማ በምን መስፈርት ቤት እያፈረሰ ዜጎችን ሜዳ ላይ የሚጥል ወንበዴ ቡድን ሳይወገዝ፣ በጠራራ ጸሐይ ዜጎች ስንት አመት ለፍተው ያገኙትን ቤት በጉልበት አይሰጥም ያለን ትንፍሽ ሳይሉ እነዚህ ወሮበሎች ለመከላከል ራስህን አደራጅ ብሎ ሕዝብን እየቀሰቀሰ ያለውን ያወግዛሉ፡፡ በየትኛው አመክንዮ ነው ይሄ ትክክል የሚሆነው?
የዜግነት ክብር ይከበር! ሥርዓት ይከበር! መንግስታዊ አደረጃጀት እንዲመጣ እንጂ ከአንዱ ቁማርተኛ ወደሌላው ለመሸጋገር አደለም፡፡ ሕዝብን የንግድ እቃ ማድረግ ይቁም! ኢትዮጵያ ቁርጠኛ ልጆች ትሻለች፡፡ ገንዘብና በቲፎዞነት የሚደግፉትን በማሳመን በሕዝብ ላይ ዳግም ሸክም ለመሆን ለሚጥር ቡድን እደል ሊሰጠው አይገባም እላለሁ፡፡ ሁሉም ራሱን ይመርምር፡፡ ጊዜ የለም! ተሳስቼ ከሆነ እታረማለሁ፡፡ ገብቶናል የምትሉ ልሰማችሁ ዝግጁ ነኝ፡፡ በደንብ ማሰብን ይጠይቃል! በሆያሆዬ ሕዝቡን እያደነዘዙ አገር እየወደመች ነው!
ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ! አሜን!