June 20, 2019
16 mins read

ኢትዮጵያ 2011 ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዛ ዘመነ ሄሮድስ ደረሰች! – ነፃነት ዘለቀ

አንድ አባውራ የማይረባ እህል ገዛና ለሚስቱ ሰጠ አሉ፡፡ ያቺ የፈረደባት ሚስት ያን እህል ቂጣ ልርግህ – እምቢ፤ ገንፎ ላርግህ – እምቢ፤ እንጀራ ላርግህ – እምቢ፤ ንፍሮ ላርግህ – እምቢ … እያለ መከራዋን ሲያበላት የታዘበው ባል “ዕብድ እህል ገዝቼ ሚስቴን አሳበድኳት” አለ አሉ፡፡ እውቱን ነው፡፡ አንዳንድ እህልና መንግሥት ግራ ያጋባሉ፡፡

የዛሬ 2011 ዓመታት ገደማ የክርስትናው እምነት የማዕዘን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት ተወለደ፡፡ በዚያን ጊዜ ባለራዕዮቹ ሰብዓ ሰገል በኮከብ ምሪት ሕጻኑን ክርስቶስን አግኝተው ገጸ በረከታቸውን አቀረቡለት፡፡ ወደ ክርስቶስ ከመሄዳቸው በፊት ግን የወቅቱን የዚያችን ሀገር ንጉሥ የሕጻኑን አድራሻ እንዲነግራቸው ጠይቀውት ነበር፡፡ እርሱም አድራሻውን እንደማያውቅ ግን ባገኙት ጊዜ ለርሱ ለራሱም የሕጻኑን አድራሻ እንዲነግሩትና ሄዶም ስጦታ እንደሚያበረክትለት ነገራቸው፡፡ እነሱ ግን በእግዚአብሔር ምሪት በሌላ አቅጣጫ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ በትንቢቱ መሠረት የይሁዳ ንጉሥ በቤተልሄም በበረት ውስጥ እንደሚወለድ ቀድሞ ተነግሮ ስለነበር ሄሮድስ የተባለው ንጉሥ በቅናት ተመርዞ ሕጻን ኢየሱስን ሊገድለው ፈለገ – ሲያድግ ዙፋኑን የሚወስድበት መስሎት፡፡ ንጉሡ እነዚያን ሰዎች ወደርሱ መጥተው አድራሻውን እንዲነግሩት ቢያሳስባቸውና ቢያባብላቸውም የነሱን ወደርሱ አለመመለስ ሲረዳ እንዳታለሉት ተገንዝቦ ሌላ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ይህ ውሳኔ ከኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ ውሳኔዎች ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡

ሄሮድስ ሕጻን ኢየሱስን አፈላልጎ ማግኘት እንዳልቻለ ሲረዳ በግዛቱ ውስጥ የሚገኙ ከሁለት ዓመት በታች ዕድሜ የነበሩ ሕጻናት በሠይፍ አንገታቸው እየተቀላ እንዲሞቱ ፈረደባቸው፡፡ ቅልብ ወታደሮቹም እየዞሩ ትዕዛዙን ፈጸሙ፡፡ በዚያም ወቅት አሥራ አራት ዕልፍ ሕጻናት እንደተጨፈጨፉ መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ “የራሔል ዕንባ በራማ በረከተ፤ እግዚአብሔርም ሰማ” እየተባለ አሁን ድረስ በሃይማኖት መጻሕፍት ይወሳል – ሃይማኖተኛ ቢጠፋም ሃይማኖቱ አለ  – “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጠፋም” እንዲሉ፡፡ ያ የጭካኔ ተግባር ዘመን ሳይገድበው አሁን ድረስ እናስታውሰዋለን፡፡

የሕይወት መጥፋት ባይኖርበትም ሰሞኑን የአዲስ አበባ መስተዳድር ወሰነው የተባለው ውሳኔም ከዚያ ከሄሮድስ ውሳኔ የማይተናነስ ነው፡፡ ውሳኔው ሞተር ብስክሌቶች ከመጪው ሐምሌ 1 ጀምሮ በአዲስ አበባ እንዳይንቀሳቀሱ የሚል ነው፡፡ ፊደል ለቆጠረ ሰው ይህ ውሳኔ ትልቅ የሣቅ ምንጭ ነው – ችግሩ ለማይመለከተው ሰው በተለይ፡፡

በመሠረቱ የአንድን መንግሥት አቅመ ቢስነት ከምንመዝንባቸው በርካታ ጠቋሚዎች መካከል አንዱ ሕግን ማስከበር ያለመቻል ድክመቱ ነው፡፡ ደካማ መንግሥት ካለ ዜጎች የሚኖሩት በመሳቀቅ ነው፡፡ በሰላም ውሎ መግባታቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት አይኖራቸውም፡፡ ሽህ ሕግ ይወጣል – ግን አንዱም ተግባራዊ አይሆንም ወይም እየተንሻፈፈና እየተወለጋገደ ይተገበራል፡፡የኑሮ ውድነቱ ማንም ሊቆጣጠረው በማይችል ሁኔታ እያሻቀበ ዜጎች በከፋ ድህነት ውስጥ ለመኖር ይገደዳሉ፡፡ የሕግ የበላይት ይጠፋና ገንዘብ አፍ አውጥቶና እግር አብቅሎ በብዙኃን ምሥኪኖች  ላይ ሲዘባነን ይስተዋላል፡፡ አሁን በሀገራችን እየሆነ ያለው ይሄው ነው፡፡ ችግሮች በሕግ ጋጋታ የሚጠፉ የሚመስላቸው አላዋቂዎቹ ገዢዎቻችን ግን አስተዛዛቢ ደንቦችን በማውጣት ጭምር እኛን አልፎ ሌላውን ዓለምም እያስደነቁ ይገኛሉ፡፡

አንድ ዜጋ ላቡን አንጠፍጥፎ የገዛውን ንብረት ድንገት ሕግ አውጥቶ አታንቀሳቅስ ማለት ሕገ ወጥነትና የለዬለት ውንብድና ነው፡፡ ሕግንና መንግሥትነትን ከለላ በማድረግ እንደነሂትለርና ሙሶሊኒ በህግ ስም አገርንና ንጹሓን ዜጎችን ማሸበር ደግሞ ከአእምሮ ቢስ ጉልበተኞች እንጂ ማሰብ ይችላሉ ከሚባሉ አመራሮች የሚጠበቅ አይደለም፡፡ “ጌታውን ቢፈሩ ገበር ገበሩን” ወይም “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” ይባላል፡፡  የሥልጣን ወንበር ስለተያዘ ብቻ አንድን ህግ እንደፈለጉ ማውጣትና መሻር ተገቢነት እንደሌለው ማንም ይረዳዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ተናጋሪ እንጂ አድማጭ፣ ገዢ እንጂ መሪ፣ አሽቆጭቋጭ እንጂ አስተዋይ…. ባለመኖሩ የሚወጡ ህጎችና መመሪያዎች በአብዛኛው ከማሣቅና ከማሳቀቅ አልፈው አሁን አሁን የዜጎችን እንቅስቃሴ እስከመገደብ የሚደርሱ ሆነዋል፡፡ እግዚአብሔር ሆይ ወዴት አለህ!

በሞተር ወንጀል ይሠራል – እውነት ነው፡፡ በመኪናም ወንጀል ይሠራል – ይህም የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ታዲያ  ከሐምሌ ወር ጀምሮ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ ለምን አልተደረገም? ራሳቸው ባለሥልጣኖች ስለሚሄዱባቸው ነው? አንድ ሰው አንድን ነገር ማድረግ ስለቻለ ብቻ ቢያደርግ ግፍን ሠራ እንጂ ሕግን አልተከተለም፡፡ የፍትህን ዐይን ደነቆለ እንጂ ለዜጎች በእኩል አልቆመም፡፡ እጅግ በርካታ ከወንጀል የፀዱ የሞተር ብስክሌት ባለቤቶችና ተጠቃሚዎች አሉ፡፡ እንዲያውም እንደሌሎች ሀገራት ቢሆን ሞተር የሚበረታታ እንጂ የሚወገዝና እንቅስቃሴው በዐዋጅ እንዲቆም የሚደረግ አይደለም – በነዳጅ ቆጣቢነቱና በጊዜ ቆጣቢነቱ ሞተር ይታወቃል፡፡ ስለሆነም የውጭ ምንዛሬን በነዳጅ ከማባከን ይልቅ ብዙው ሰው በሞተርና በፑል ሲስተም እንዲጓዝ ቢመከር ብልኅነት እንጂ ክፋት የለውም፡፡ በተገላቢጦሹ ግን ገና ለገና ዘራፊዎች ሞተርን ይጠቀማሉ ተብሎ እንዲህ ዓይነት ፍርደ ገምድልነት በሀገር ላይ መወሰን ትልቅ ስህተት ነው፡፡

ወንጀለኛን መከታተልና መያዝ ሲያቅት እንዲህ ያለ የጅምላ ጭፍን ብያኔ ለማንም አይበጅም፡፡ ከበደ የሚባል ሰው ሚስቱን ገድሎ አምልጧልና ከበደ የሚባሉ ሰዎች ሁሉ እየተለቀሙ ይታሰሩ፤ አንድ ቀይ ሰው በዚህ ሲያልፍ እንትናን ተሳድቧልና እርሱ እስኪገኝ ቀይ ሰው ሁሉ እየታሰሰ እስር ቤት ይግባ፤ አጭር ቀሚስ ያደረገች ጠይም ሴት ዕቃ ሰርቃ አምልጣለችና አጭር ቀሚስ ያደረገች ሴት ሁሉ ከያለችበት እየታደነች ከርቸሌ ትውረድ፣ አንድ መነጽር ያደረገ ሰው ወንጀል ፈጽሞ ስላመለጠን መነጽር ያደረገ ሰው ሁሉ ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት ያድርግ…. ምን ዓይነት ድንቁርና ነው? እንዲህ ዓይነት ኋላ ቀር አስተሳሰብ አንዳንዴ የማስተውለው በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ሹፌሮች ሰው ወይም እንስሳ ገጭተው ሲያመልጡ ነው፡፡ ለምሣሌ በአፋር አካባቢ አንዲት ነጭ ፒካፕ መኪና በዚህ መልክ አንዲት ግመል ገጭታ ብታመልጥ ነጭ ፒካፕ መኪኖች ይቸገራሉ – ልብ አድርጉ ነጭ ፒካፕ መኪኖች ብቻ፡፡ ሌሎች መኪኖች ችግሩ እምብዝም አይመለከታቸውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ከዘላኖችም ባነሰ አንድ ወይ ሁለትና ሦስት ሞተረኞች ባጠፉ በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ በሞተር ተጓጓዦችና ተዳዳሪዎችን በአንዴ ጉሮሯቸውንና እግራቸውን ቆርጦ አስቀረው – አዎ፣ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው፤ ለአዛዥም አቀበት የለም፡፡ ይህን ነገር ማድረግ ጭንቅላት ሳይሆን ስሜት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ብስለትን ሳይሆን በሰው አምሳል የሚንቀሳቀስ ዐውሬ መሆንን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ የምትገርም ሀገር ናት፡፡ በዚህ የሀሙራቢ ህግ የት እንደምንደርስ ዕድሜ ሰጥቶን ማየት ነው፡፡

አሁንም ቢሆን ይህ ችግር ይታሰብበት፡፡ ጤነኛ ነን የምትሉ የመንግሥት አካላት ሰው ሁኑና ማሰብ መቻላችሁን ግለጡ፡፡ በዚህ መልክ ሀገር አትመራም፤ ሕዝብም አይተዳደርም፡፡

ዱላ የሚበዛበት ህግ ዘለቄታ የለውም፡፡ ይልቁንስ ከራስ ጀምሮ ወደ ሰውነት ደረጃ ለመምጣት መጣር ነው፡፡ በሙስና የተበከለ ቢሮክራሲና ሕግ አስፈጻሚ ይዘህ፣ ከላይ እስከታች በምዝበራ የከበረ ባለሥልጣን ይዘህ፣ በመኪናና በሞተር ቀርቶ በአውሮፕላን የሚሰርቅ ዜጋ አፍርተህ ባለህበት ሁኔታ ወንጀልን በዚህ መልክ እከላከላለሁ ማለት ግንጥል ጌጥ ከመሆኑም ባሻገር የትም የማያደርስ ጅልነት ነው፡፡ ሞተረሩን ብታሳጣቸው አንተን ቀድመው ሄደው ሌላ ዘዴ ይፈጥራሉ፡፡ ትልቁ ነገር ልብንና ኩላሊትን መግዛት ነው፡፡ አእምሮን ማሸነፍ ነው፡፡ ሥራን መፍጠር ነው፡፡ በየቀኑ የሚሰቀለውን የኑሮ ውድነት ማቀዝቀዝ ነው፡፡ ሀገርና ሕዝብ እንዲረጋጉ ማድረግ ነው፡፡ ዜጎችን ወደ ሰውነት ደረጃ ማድረስ ነው – ቅድሚያ ራስን ሰው አድርጎ በርግጥ፡፡ አንድ ንጹሕ ዜጋ ለማግኘት እየተቸገርን ሞተር ብታቆም፣ ፈረስ ብትገታ፣ መኪና ብትገትር፣… ወንጀል እንደሆነ አይቆምም፤ የአስተሳሰብና የባሕርይ ለውጥ እንዲመጣ መሥራት ነው ዋናው የችግራችን መፍትሔ፡፡ ሰዎች የቀደመውን ግብረ ገብና ሞራል እንዲላበሱ ሲደረግ ነው ወንጀልና ኢሞራላዊነት እየቀነሰ ሊመጣ የሚችለው፡፡

የመጨረሻ ምክሬ – ምስኪኖችን መውጫ ቀዳዳ እያሳጣችሁ በሚደርስባቸው በደልና ምክንያት በሚያነቡት ዕንባ እናንተው ራሳችሁ እንጦርጦስ እንዳትወርዱ ሰከን በሉ፡፡ ደግሞም ሕዝብንና አገርን እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል ለመረዳት አንብቡ፡፡ ማንበብ ሰውን ሰው ያደርጋል፡፡ ማተብም ይኑራችሁ፡፡ ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱና ይህን የተገፋና የተበደለ ሕዝብ ከእሳት ባህር ወደሜዳው አሻግሩት፡፡ ስታሻሩት ግን በብሶት ላይ ብሶት እየከመራችሁ እንዳይሆን ተጠንቀቁ፡፡ ዛሬ ሁሉም ነገር በጃችሁ ላይ ስላለ ሁሉንም – በስሜት ፈረስ እየጋለባችሁ የምትወስኑትን ሁሉ ማድረግ ትችሉ ይሆናል፡፡ ግን እመኑኝ ይህ ዕድል አያያዝን ይጠይቃል – ሊያመልጣችሁ ይችላልና በአስተውሎት ተራመዱ፡፡ በቃ፡፡

1 Comment

  1. What ahead of us is unfathomable. An apparent indication the man at the helm in Addis is doing nasty things. He has proved it many times in so many ways.

    Believe it or not we are back to square one. The change we are taking about is not taking root.I baffled and confused why the so called doctor PM is surrounding himself good for nothing people.

Comments are closed.

eri tigray
Previous Story

ትግራይ ማለት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለት ትግራይ ናት፡ – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Next Story

ኢዜማ የሚወዳደረው አሜሪካና ካናዳ ነው እንዴ? – ሰርፀ ደስታ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop