“ለውጡን ለመቀልበስ ከሚሰሩ ወገኖች በላይ እርስ በእርሳችን የምናደርገው ፍትጊያ የመጣውን ለውጥ ወደ ኋላ ይጎትታል” አቶ ለማ

“መሬት ወረራና ሕገ ወጥ ግንባታን ለመከላከል ስራዎች እየተሰሩ ነው”

ለሁለት ቀናት ይደረጋል የተባለው የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት 9ኛ መደበኛ ስብሰባ መካሄድ ሲጀመር የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በመክፈቻው ላይ የክልሉን መንግስት የ6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት አቀረቡ::  ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን;  እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል እንደ ሀገር የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል ሰፊ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል::

https://www.youtube.com/watch?v=14ql5rq_pMI

“ለውጡን ለመቀልበስ ከሚሰሩ ወገኖች በላይ እርስ በእርሳችን የምናደርገው ፍትጊያ የመጣውን ለውጥ ወደ ኋላ ይጎትታል:: ሰላም እና ህዝቡ በፖለቲካው ያገኘውን ድል እና መስመር እየያዘ የመጣውን የኦሮሞ ህዝብ ትግል በትእግስትና በብስለት በመምራት ኪራይ ሰብሳቢዎች እና ፀረ ዴሞክራሲ ሀይሎች በሚሸርቡት ሴራ ወደ ኋላ መመለስ በማይችሉበት መልኩ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሸጋገር ችለናል:: ጠላቶች የጥፋት አላማቸውን ከግብ ለማድረስ በአንድ በኩል የኦሮሞን እና የኦሮሚያን ጠላት በማብዛት በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሞን እርስ በእርስ ለማጋጨት ከፍተኛ ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድረስ በማቅረብ ሲሰሩ ነበር’ ያሉት አቶ ለማ “እነዚህ የጥፋት ሀይሎች ሲሸርቡት የነበረውን ሴራ ህዝቡ እና መንግስት ፊታቸውን ወደ ልማት እንዳያዞሩ ለማድረግ ሲከናወን በነበረው ስራ ውስጥ ጠላት ከሚሰራው ውጪ እርስ በእርስ የነበረው መከፋፈል ፈተና ሆኖ ቆይቷል::  በተለይም በአራቱ የምእራብ ኦሮሚያ ዞኖች እና በጉጂ ዞን የነበረው ግጭት ምክንያት ያልነበረው እና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተደረሰውን ስምምነት የተቃረነ ቢሆንም መንግስት ራሱን መስዋእት በማድረግ ህዝቡን ከጎኑ በማድረግ በትእግስትና በብስለት ወደ ሰላማዊ ትግል ለማምጣት ከፍተኛ ስራ ሰርቷል” ሲሉ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዘረኞች ጥላቻ እየፈረሰች ያለች ከተማ - አዲስ አበባ

“በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ ግጭቶችን ለመግታት ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመሆን ህብረተሰቡ ችግሮቹን በራሱ መንገድ እንዲፈታ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል::  በክልሉች መካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስቀረት በሚሰራበት ወቅትም የተለያዩ ግጭቶች ተፈጥረው” ነበር ያሉት አቶ ለማ  ለምሳሌም በጉጂ እና በጌዴኦ መካከል እንዲሁም በቡራዩ ከተማ ተከስቶ የነበረውን ግጭት አንስተዋ በቅንጅት በተሰራው ስራ በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ መኖሪያቸው የመመለስ እና አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።

“በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ በተነሳ ግጭት  በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው፣ የበርካቶች ህይወት አልፎ የመንግስትን መዋቅር እስከ ማፍረስ የደረሰ ቢሆንም፥ በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ ችግሩን የማስቆም እና አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራ ተሰርቷል::  የኦሮሚያ ክልልን ከሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ቦረና እና ሀረርጌ አካባቢዎች ግጭት እንዲፈጠር የተለያዩ ሴራዎች ሲሸረቡ ቢቆዩም የሁለቱ ክልሎች መንግስታት ችግሩ እንዳይፈጠር በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል” ያሉት አቶ ለማ “የሀይማኖት ግጭት ለማስነሳትም ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ በተቀናጀ መንገድ በጎባ እና በአሰላ ከተሞች እንዲሁም በአርሲ ዞን የነበረው እንቅስቃሴ በቀላሉ የሚታይ ባይሆንም የፀጥታ ሀይሎች እና ህብረተሰቡ ባደረጉት ጥረት እቅዱ መክሸፉን ተናግረዋል::

“በክልሉ አስተዳደር እና ሰላም ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ እንደ መሬት ወረራ፣ የኢንቨስትመንት ጉዳት፣ የደን ሀብት ዘረፋ እና ምንጣሮን ጨምሮ ሌሎች አደገኛ እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም፤ እልባት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው:: የመሬት ወረራና ሕገ ወጥ ግንባታን ለመከላከል ስራዎች እየተሰሩ ነው:: የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ የመንግስት ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ይቀጥላል ” ብለዋል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  አዲሱ ምስጢራዊ ሰነድ - ይህ ሰነድ ኦሮሚያ ውስጥ ሌላ መልክ ይዞ ቀርቧል

ክልሉ ከነበረበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የታቀደውን ስራ ሙሉ በሙሉ መስራት እንዳልቻለ በመክፈቻው ንግግር ላይ ያስቀመጡት አቶ ለማ በቀሪ ጊዜያት ያለውን የሰው ሀይል፣ እውቀት እና ገንዘብ በማቀናጀት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራ ገልጸዋል::

Share