አደባባዩ ምን ያህል ይርቃል? – ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
እነሆ ይቺ ሀገር ኢትዮጵያ ናትና የመብት (የለውጥ) ጥያቄዎች፣ እንደ አህጉር ተጋሪዎቿ ሁሉ መልስ የሚያገኙት ከአደባባይ ጩኸት ብቻ ይሆን ዘንድ ባህል ሆኖአል፡፡ ትውልድ ተሻጋሪ ታሪኳም የሚነግርህ በየወቅቱ ከተፈራረቁ ገዥዎቿ አንዳቸውም እንኳ ለህዝብ ፍላጎትና ውሳኔ ተገዝተው አለማወቃቸውን ነው፤
ጠመንጃ አሊያም ተፈጥሮ ወደ ግብአተ መሬት ካልሸኛቸው በቀር፡፡ የሩቁን (የጨለማውን ዘመን) ትተን፣ የቅርቡን እንኳን ብንመለከት በወጡበት መንገድ፣ ቁልቁል ተምዘግዝገው መውደቃቸውን መረዳቱ አይቸግርም፡፡ አዛውንቱ አፄ ኃይለስላሴ፣ ‹‹ቆራጡ›› ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም እና ‹‹ታጋዩ›› አቶ መለስ
ዜናዊ እጅ የሰጡት ለህዝብ ፍላጎት ሳይሆን ለጠመንጃና ለተፈጥሮአዊ ኃይል ነው፡፡ የሶስቱም የአመፃ ‹‹የዳቦ ስም›› ደግሞ ተመሳሳይ ነበር፡- ‹‹ለሀገርና ህዝብ ጥቅም››፡፡
ንጉሰ ነገስቱ ልጅ እያሱን ያስወገዱበት ምክንያት ‹‹ሀገርን ከሚያጠፉ ጋር በማበሩና ህዝብን ከማስተዳደር ይልቅ፣ ለግላዊ ምቾት ጊዜውን በዋል ፈሰስ በማዋሉ ነው›› የሚል ሰበብ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በግልባጩ እርሳቸውም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ አደባባይ ባናወጠ ንቅናቄ ተገፍተው፣ ገደል አፋፍ በቆሙባት በዛች ዕለት፣ የሠራዊቱን መለዮ ባጠለቀ አንጋች የተነበበላቸው የክስ ደብዳቤ፡- ‹‹ሀገርን ለቆሞ-ቀር፣ ሀብትን ለቤተሰብና ለግለሰቦች ጥቅም መመዝበር፣ ህዝብን ለከፋ ጭቆናና ሰቆቃን ላዘነበ ረሀብ መዳረግ…›› የሚል እንደነበረ ስናስታውስ ‹ታሪክ ራሱን ደገመ› ያሰኛል፡፡ በዚህ መልኩ ‹‹በደልና ግፍ ከምሽግ አስወጣን›› ባሉ ወታደራዊ መኮንኖች የተመሰረተው የደርግ መንግስትም አስራ ሰባት ዓመት ሙሉ እንዳሻው ሲገድል፣ ሲፈልጥ፣ ሲሸልል… ቆይቶ ‹‹ብሶት ከትምህርት ገበታ አፈናቀልን›› ባሉ በረኸኞች ፍፃሜው ይሆን ዘንድ ግድ ሆነበት፡፡ ታሪክም የሚነግረህ ይህንኑ ነው፤ ሌላ የለም፡፡ ያገዛዝ ጭቆናና መከራ ያስመረረው አደባባዩን በኃይል ሲነጥቅ-ሲነጥቅ ዛሬ ላይ መድረሱን፡፡ በርግጥ ይህ እርግማን አይደለም፤ ለጨቋኞች በልክ የተሰፋ ፍትሀዊ ፍርድ የሚተላለፍበት አማራጭ መንገድ እንጂ፡፡
የሆነው ሆኖ ዛሬም ቢሆን ትውልድ እንጂ ታሪክ አልተቀየረምና፣ የለውጥ መንገዶች በሙሉ ሄደው ሄደው ወደ አደባባይ የሚገፉ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ‹የነፃነት በር በብላሽ አይከፈትም› ያለው ማን ነበር? …ርግጥ ነው መለስ ዜናዊም በርሃ ሳለ ‹‹ምኹሕዃሕ ዘይፍለዮ ማዕፆ›› (ማንኳኳት ያልተለየው በር) በተሰኘ ታንክ ተደግፎ በፃፈው መፅሀፉ ላይ የደርጉን ፋሺስትነት ከመተንተኑ በተጨማሪም ከጓደኞቹ ጋር ተስፋ ሳይቆርጥ ባደረገው ትግል ነፃነቱን ተቀዳጅቷል፡፡ ይሁንና በለስ ቀንቶት በትረ-ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ግን፣ የአስተዳደር ዘይቤውን የወረሰው ታግሎ ከጣለው ስርዓት ዶሴ እንደነበር ለመረዳት ብዙ አላስጠበቀም፤ ቀድሞ
የተተገበረውን አሻሽሎ፣ በከፋ መልኩ ደጋግሞ ተግብሮታል፡፡ የመፅሀፉ ዋና ገፅ-ባህሪ ‹‹እነይ ስላስ›› በእንባ እንደታጠቡት፣ በድህነት እንደጎበጡት ሁሉ ዛሬም የኢትዮጵያ እናቶች በደህነት አጥንታቸው ገጥጧል፤ ለእስርና ለስደት በተዳረጉት ልጆቻቸው ጉልበታቸውን ታቅፈው በሀዘን እንዲወዛወዙ ተፈርዶባቸዋል፤ ሥራ-አጥ ጎረምሳ ልጆቻቸውን ለመቀለብ ላይ-ታች ከመማሰን አልተገላገሉም፤ ‹‹ለግርድና›› ወደ አረብ ሀገር የተሰደዱትን ሴት ልጆቻቸውን እያሰቡ በስጋት እየተናጡ ነው… እናም በኢህአዴግና እነርሱ ‹‹ፋሺስት›› በሚሉት በደርጉ ስርዓት መካከል የታየው የአስተዳደር አይነት የጊዜና የሰዎች ልዩነት ብቻ እስኪመስል ድረስ የአንድ ሳንቲም ግልባጭ
መምሰሉ ‹‹ነፃ አውጪ››ነቱን ምፀት አድርጎታል፡፡ በበረሃ የተደረሰው መዝገበ ቃላትም ‹‹ህዝብ በሁለት ይከፈላል›› ይላል-በ‹‹ደጋፊ›› እና ‹‹ተቃዋሚ›› ጎራ፡፡ ተቃዋሚ የተባለውንም የምድር እርግማን ሁሉ ይፈፀምበት ዘንድ ያዝዛል፤ ጭቆና፣ ግፍ፣ ጭካኔን… በህዝብ ደህንነትና ሰላም ስም ማንበር፤ በህገ-መንግስት ትከሻ ማንጠልጠል፤ ህልምን፣ ምርጫን፣ ህዝበ-ውሳኔን… በክንደ-መሳሪያ መተርጎም… በዚህ የተነሳ የለውጥ ሃዋርያት ወደ አደባባዩ ይጎርፉ ዘንድ ወቅቱ ግድ ብሏል፤ በርግጥም ስርዓቱ በደልን ዘርተው፣ በደልን በሚያፀድቁ፤ ጭቆናን ከዳር ዳር በሚያዳርሱ፤ በፍትሕ በሚዘባበቱ፤ ከመልካም አስተዳደር በእጅጉ በራቁ፤ በሀገር ሀብት ራሳቸውንና ዘመዶቻቸውን ባበለፀጉ፤ ስቃይንና መከራን የአገዛዝ ስልት ባደረጉ፤ በአማላይ ዕቅድና ፖሊሲ በሚሸነግሉ፤ የምርጫን ውጤት እንደፍቃዳቸው ማገለባበጥ በተካኑ… የተዋቀረ በመሆኑ እነሆ ሕዝቡ ለድፍን ሃያ ሁለት ዓመታት አሳር መከራውን እንዲቆጥር ተፈርዶበታል፡፡
መቼስ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በሥልጣን ስለቆየው የኢህአዴግ አስተዳደር ክስረትና ሽንፈት በእንዲህ አይነቱ የመፅሄት ፅሁፍ ተንትኖ ለመጨረስ ቀርቶ፣ ጠቅሶ እንኳን ማለፍ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የድርጅቱ ገመና በዜጎች መሀል አለመተማመን ከመፍጠር አንስቶ በሀገር ጥቅም መደራደር፣ ህግን የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ፣ ሰላዮችን አለቅጥ በሕዝብ መሀል መሰግሰግ፣ የሠብዓዊም ሆነ የፖለቲካ መብቶችን መጨፍለቅ፣ የሀገር ሀብትን መዝረፍና ማዘረፍ፣ በሥልጣን መባለግ፣ የልማት አጀንዳን ለፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት ብቻ መጠቀም፣ በዚህም የሥራ-እጥ ቁጥርን ማናር፣ የኑሮ ውድነትን ማሻቀብ፣ ዜጎችን ማፈናቀል፣ በሠላማዊ ህዝብ ላይ የታጠቀ ኃይል ማዝመት፣ ፍርሃትን ማንገስ… እያለ ይቀጥላልና ስንቱን ዘርዝሮ መጨረስ ይቻላል? ይህ ተቆጥሮ የማያልቅ ሃያ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ አሳረ-መከራም ነው ብዙሃኑን ‹አደባባዩ ምን ያህል ይርቃል?› የሚል ጥያቄ እንዲያንሰላሰል ገፊ ምክንያት የሆነው፡፡ ተቀራራቢው መልስም ከሚከተሉት አንዱ ሊሆን ይችላል፡- የሞትን ያህል፣ በእስር ቤት የመበስበስን ያህል፣ በስደት የመንከራተትን ያህል ወይም ለተጨማሪ ሃያ፣ ሰላሳ፣ አርባ… የጭቆናን ዓመታት ያህል? ካገዛዙ ባህሪይ አንፃር ከላይ የተዘረዘሩት በሙሉ ለጥያቄው መልስ ሊሆኑ እንደሚችሉ አንድ እንኳ የሚጠራጠር ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የስርዓቱ ስር የሰደደ ሴራ ‹ግደል› ሲባል የሚገድል፣ ‹ተኩስ› ሲባል የሚተኩስ፣ ‹አፍን› ሲባል ‹ለምን?› ብሎ የማይጠይቅ የታጠቀ ኃይልን ማሰልጠኑ እና በሀሰት ለመክሰስ የማያመነታ ህሊና ቢስ ዓቃቢ ህግን፣ በሀሰት ለመፍረድ የማያቅማማ ዳኛን፣ በአጠቃላይ ሰጥ-ለጥ ብሎ የሚገዛ ሎሌ ትውልድ… ለመፍጠር አቅዶ መስራቱ ነውና፡፡
በአናቱም የምሁራኖቻችን አድርባይነትም ሆነ ዝምታ ለከፋፋይ አገዛዙ ጉልበት ሆኖታል፡፡ አብዛኛዎቹም ነገን አጥብቀው የሚፈሩ፣ ከሀገርና ህዝብ ጥቅም በላይ የግል ምቾታቸው የሚያስጨንቃቸው መሆንን መርጠዋል፡፡ የተቀሩት (ገቱ ያላቸው) ጥቂት ታላላቆችም ቢሆኑ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፤ ወይም ሞክረው አልተሳካላቸውምና ለዛሬቷ ኢትዮጵያ ‹‹የቁልቁለት መንገድ›› የድርሻቸውን ማንሳታቸው አከራካሪ አይሆንም፡፡
ሌላው ትልቁ እንቅፋት ደግሞ የአገዛዙ ቂመኝነት ከዕለት ዕለት፣ ከዓመት ዓመት እየከፋ መምጣቱ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአስከፊዎቹ የሀገሬ እስር ቤቶች የከረቸመባቸውን እነዛን (ራሳቸውን መከላከል የማይችሉትን) የህሊና እስረኞች ‹ማኪያቬላዊ በቀል› በተሰኘው መፅሀፉ ምሪት ፍዳቸውን ከማስቆጠር አልተመለሰም፡፡ እስክንድር ነጋ፣ አንዱአለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፣ ርዕዮት አለሙ፣ ውብሸት ታዬ… የድርጊቱ ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ ርግጥ ነው መንግስት ሰዎቹን ያሰረው ለሕዝብ ጥቅም ሲል እንደሆነ ዛሬም ድረስ ለማሳመን እየለፈለፈ ነው፤ ይሁንና እስካሁን ያልነገረን ማሰቃየቱ፣ ፍትህ መንፈጉና ጠያቂ መከልከሉ… ለማን ጥቅም ሲባል እንደሆነ ነው፤ ለሕዝብ ይሆን?
ከሁሉም በላይ ግራ የሚያጋባው ነገር ደግሞ የእስረኞቹ ጠባቂዎች ልበ-ደንዳናነት ነው፤ የእነርሱን ያህል የተጎሳቆሉ፣ የእነርሱን ያህል የተገፉ፣ የእነርሱን ያህል የተበደሉ ታሳሪዎችን ለማንገላታትና ለማሰቃየት ያላቸው ሞራል የበዛ ነውና፡፡
መቼም በዚህ ዘመን የእኛዎቹን እስር ቤቶች ያህል አስከፊ የሰቆቃ ቦታዎች በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ አይመስለኝም (ለካስ! እንዲህ ዘመን የተጣላት፣ ታሪክ የተቃረናት ሀገር ዜጋ መሆን የከፋ ስቃይ ኖሯል!!) …ይህ ሁኔታም ይመስለኛል ከስርዓቱ አጋፋሪና አጫፋሪዎች ይልቅ ጨካኙን በሽር አልአሳድን በሶሪያ ጎዳናዎች የሚፋለሙት ነፃነት ናፋቂዎች በሥጋ የተዛመዱህ ያህል እንድትቆረቆርላቸው ያደረገው፤ ከጨቋኝ የሀገርህ ገዥዎችም ይልቅ፣ በየትኛውም ክፍለ ዓለም ያሉ ጭቁን ህዝቦችን ‹ወገኔ› እንድትል ያደረገው፤ ከእነርሱ የመንፈስ አንድነትን፣ የነፍስ ትስስርን በፅኑ ስለምትጋራ ነው፡፡ አንተም ጭቁን ነህና የተጨቋኞች አበሳ ይቆጠቁጥሀል፤ አንተም
መብትህና ክብርህ ተገፏልና፣ ተመሳሳዩ ከተፈፀመባቸው ሕዝቦች ጎን መቆምህ ግድ ነው፡፡ …ከዚህ በተረፈ ‹እንመራሀለን› የሚሉህ ወንድሞችህ፣ ልብህን በጩኸት ከማሸበር፣ ዘመንህን ካለፉትም በላይ የከፋ ከማድረግ፣ ለዓመታት ቀጥቀጠው ከመግዛት ያለፈ የፈየዱት ቁም-ነገር የለምና ለእነርሱ ቀረቤታና ሀዘኔታ ከቶም ሊሰማህ አይችልም (በነገራችን ላይ አንዳንድ ለውጥ ናፋቂዎች ስርዓቱን ከመላው የትግራይ ተወላጆች ጋር ደርበው መውቀሳቸውና መክሰሳቸው ስህተትና ለሀገር አንድነት ጠንቅ መሆኑን አምነው ካልተቀበሉ የትግሉን ዕድሜ ከማራዘሙም በላይ ለከፋ ችግር መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ መልኩም ተሰልቶ የሚመጣ ውጤትም የኢህአዴግን ስህተት በእጥፍ መመንዘር ነው የሚሆነው፡፡ እናም ምርጫው ሁለት ይመስለኛል፤ ይህ አይነቱን ሸውራራ /ጨለምተኛ/ አተያይ አስተካክሎ ታላቂቷን ኢትዮጵያ በጋራ መገንባት፣ አሊያም የህወሓትን መንገድ በመከተል ለውጡን በዜሮ አባዝቶ ሀገርን እንደአንባሻ ዘጠኝ ቦታ ለሚከፋፍል አደጋ ማጋለጥ)
የመነቃቃት መንፈስ…

ጥያቄው ይህ ነው፡- ህማማቱ ስንት ቀን ይፈጃል? የማራኪና ተማራኪ አስተዳደር ዕድሜው ምን ያህል ይረዝማል? ስለምንድር ነው ባለስልጣናት አስፈራሪ፣ ቀለብ ሰፋሪ ህዝብ ደግሞ ተስፈራሪ የሆኑት? ማን ነውስ መብታቸውን የሚጠይቁ የሃይማኖት መሪዎችን-አክራሪና አሸባሪ፣ ተቃዋሚዎችን-በሀገር ላይ የሚያሴሩ፣ ጋዜጠኞችን-የጠላት ሀገር ተላላኪ ያደረገው? በየትኛው ህግስ ነው ስርዓትን መደገፍ-ሀገር ወዳድ፣ መቃወም-ይሁዲነት የሆነው? …ግና እመነኝ ውንጀላው በጉልበታም ገዥዎች ዘንድ የተለመደ የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ በተቀረ ነፃነትን ያጣጣሙ ነባር ሀገራትን ትተህ፣ የቅርቦቹን እነቱኒዚያን ብትወስድ እንኳ፣ አደባባዩ ሽንፈት ያወጀባቸው ገዥዎቻቸው ተመሳሳዩን ይፈፅሙ እንደነበር ድርሳናቶቻቸው ይነግሩሀል፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ ታሪክ ቢሆኑም፡፡
ያንተም ጨቋኝ ገዥዎች ታሪክ የሚሆኑት፣ ይህ ሁሉ አሳረ-ፍዳ ከእነጦስ ጥንቡሳሱ ሊወገድ የሚችለው ዋጋን በሰማይ በሚከፍለው ‹‹ንሰሃ›› አይደለም፣ ጎዳናዎችን በሚያጥለቀልቅ ህዝባዊ ቁጣ እንጂ፡፡ እናም የአደባባዩን ርቀት ከጭቆናው ጋር እያለካኩ፣ የፍርሃት ሰንሰለትን አየበጠሱ፣ በሁከተኛው ስርዓት ላይ የሚጮኹ የነፃነት ድምፆችን ማስነሳቱ አማራጭ አልባ መፍትሄ ነው፤ እነዛ ጎበዛዝቶች፣ በሚከፍሉት ዋጋ ታጋይ እንጂ ትግል እንደማይሞት እያስመሰከሩ፣ መንገዶቹን የሚያንቀጠቅጡ ፋኖዎች ከቁም እንቅልፍ የሚባንኑበትን ዕለት ማሳጠር የግድ ይላል፡፡
በዚህም አለ በዚያ ይህ ኩነት ይለወጥ ዘንድ ስደት መፍትሄ አይሆንም፤ ማሳደዱን፣ ማስፈራራቱን፣ ማደህየቱን፣ ማሰር፣ መግደሉን… ከቶም ቢሆን ሀገር ጥሎ በመሄድ ማሸነፍ አይቻልም፤ ምክንያቱም የስርዓቱም ፍላጎት ይኸው ነውና፤ የተቃወመውን፣ በስልጣን አደገኛነት የጠረጠረውን ከሀገር በማባረር፣ ከአደባባዩ ይበልጥ ማራቅ፣ ከአይን መሰወር፣ በዚህም ለውጥ ያረገዘውን የቁጣ ቀን ማዘግየት፡፡ ለዚህም ነው ‹እኔ ምን አገባኝ›ም ሆነ ስደት መፍትሄ አይሆንም የምለው፡፡ አዎን! ሀገሪቱን የጥቂቶች ብቻ ለማድረግ የተያዘውን ግብግብ ማጨናገፍ የምትችለው መሬት በሚያርድ ሠላማዊ ቁጣ ብቻ ነው፤ የሰብዓዊ መብት አፈናም ሆነ ሥራ እጥነትና ድህነት የሚያሰድዳቸው ወንድም እህቶቻችን የባሕር ሲሳይ የሚሆኑበትን አሳዛኝ ዕጣ መለወጥ የምትችለው በአደባባይ ቁጣ ነው፤ የህሊና እስረኞችን ነፃነት ማወጅ የምትችለው እጅ ለእጅ ተያይዘህ የጎዳና ቁጣን በማሰማት ነው፤ ረሀብና ድህነትንም ማጥፋት የምትችለው በቅድሚያ በሰንካላ ፖሊሲና ደካማ አስተዳደር በሚመራው ስርዓት ላይ መቆጣትና ማምረር ስትችል ነው፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው ኢትዮጵያ የአንተም ሀገር የምትሆነው፡፡
የጥሪው ድምፅ
‹‹ሰላም ይሉናል፣
ጥርሳቸውን እያፋጩ በጥል
ቤት እያፈረሱ በበቀል
ኑሮን እያደረጉ ገደል
ሰላም ይሉናል፣
እኛ እንግዛ፣ እናንተ ተገዙ
እኛ እንዘዝ፣ እናንተ ታዘዙ
እኛ እናስብ፣ እናንተ ደንዝዙ
ንገሯቸው እባካችሁ
ሰላም ነፃነት ነው ብላችሁ
ዝም አትበሉ
እሪ በሉ
ጠመንጃቸውን እስቲጥሉ፡፡›› (ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም ‹‹ዛሬም እንጉርጉሮ›› የግጥም መድብል)
እነሆም የሀገሬ ጀግኖች ከአንቀላፉበት አዚም ይነቁ ዘንድ ጩኸቱ በርክቷል፤ የደውል ድምፁም አስተጋብቷል፤ አምነት የሚጣልበት የአርነቱን ‹ሙሴ›ም፡- ‹‹ጥሩት አያ’ገሌን ያሳየን መንገዱን መሪ ነው ያጣነው፣ ስናቋርጥ ዱሩን›› (አንዱአለም አባተ ‹‹የረዘመ ትንፋሽ›› የግጥም መድብል) የሚሉ ድምፆች እያፈላለጉት ነው፡፡
እውነት እውነት እልሀለሁም፡- ይህ ሲሆን ነው በነብያቶች አንደበት የተነገረው በኢትዮጵያ ‹‹ታህሪር›› ታሪክ የሚሰራበት፣ ጭቆና-ድባቅ የሚመታበት፣ ያጎነበሰ አንገት-የሚቃናበት፣ የተሰበረ ልብ-የሚጠገንበት፣ የደከመ መንፈስ-የሚበረታበት፣ ነፃነት የሚዋጅበት፣ በምኩራቦቹ ፍትህ-የሚሰበክበት፣ ህግ-የሚከበርበት፣ አድሎአዊነት-የሚወገዝበት… ይሆናል፤ ደጀ ሰላሞቹም የሰብዓዊ መብት የሚከበርባቸው፣ የመኖር ዋስትና የሚረጋገጥባቸው…፤ አውደ ምህረቶቹም ያለቀሱ የሚስቁበት፣ የአዘኑ የሚፅናኑበት… ይሆናል፡፡ ይህ ነው ነብያቶቹ የተናገሩት የተስፋው ቀን፤ የተስፋው ምድር፡፡ … እነሆም በገዥዎች ላይ ሰቆቃንና ዋይታን ከሚያዘንበው የመጨረሻዎቹ
ቀናት በፊት እንዲህ ማለትን ወደድኩ…
አንድ ምክር-ለጓዶች
ደጋግማችሁ የአደባባይ ተቃውሞን፣ ሕዝባዊ ንቅናቄን ለማውገዝ እንደ ምክንያት የምትጠቀሙበት ‹‹ሀገሪቱን በልማት ጎዳና አከነፍናት፣ እድገታችን ለተከታታይ ዓመታት ከሁለት ዲጂት በላይ ከሆነ ሰነበተ›› የሚለው ሀቲት፣ተራ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ የታወቀ ቢሆንም እስቲ ‹‹ይሁን›› ብለን ብንቀበለው እንኳ እንደምኞታችሁ የተቃውሞው ድምፆች ይዘጉ ዘንድ የግድ እንዲህ የሚሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች መመለስ ይኖርባችኋል፡- የፖለቲካ ነፃነት አለመኖሩስ? በስርዓቱና በአምሳሉ የተቀረፁ ተቋማት ተአማኒነት ማጣታቸውስ? ጎሳን እየነጠሉ ለፖለቲካ ጥቅም ማዋሉስ? አዋጅና ፖሊሲ ከመፅደቃቸው በፊት ሀቀኛ ተቀናቃኞች፣ ገለልተኛ ምሁራን እና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በድፍረት እንዲተቹበት አለመደረጉስ? (‹ሰው በእንጀራ ብቻ ይኖራል!› የሚል እምነት አራማጅ የሆኑትን የኢቲቪ ሸንጋይ ‹‹ምሁራኖች››ን እርሷቸውና ማለቴ ነው)፣ ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ የሚያበረታ መደላድል አለመኖሩስ? ማንም ሰው ባመነበት ሃሳብ መደራጀት አለመቻሉስ? የህግ የበላይነት ከወረቀት አለመዝለሉስ? መከላከያ ሠራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስና የደህንነት ተቋሙ ተጠሪነታቸው ከህገ-መንግስቱ ይልቅ ለፓርቲ መሆኑስ? …እናም ‹ህዝብን ከፍ ከፍ አድርጎ ያከበረ መንግስት መንበሩ የፀና ይሆናል!›› እንዲል ጠቢቡ፣ የረዣዥም ተራሮቻችንን አናት ሳይቀር ለማንቀጥቀጥ በማስገምገም ላይ ያለው ይህ ብርቱ የቁጣ ድምፅ የሚረግበው፤ የፈረሱ ቅፅሮችን በጋራ ለማነፅ በመሀከላችን መተማመን የሚሰፍነው፤ ‹ባቢሎናውያን›ነት ሰክኖ፣ እርስ በእርስ መደማመጥ የሚቻለው እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የለውጥ ፈላጊው ወሳኝ ጥያቄዎች በአስቸኳይ ሁሉንም ወገን በሚያሳምን መልኩ መፍትሄ የተሰጣቸው እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ መፍትሄ የለም -ታሪክን በከፋ መልኩ ከመድገም በስተቀር፡፡
መልካም ዕድል!

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአማራ ብሄር ተወላጆች እና በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለዉ የዘር ማጥፋት ወንጀል ይቁም!!!

1 Comment

Comments are closed.

Share