ቴዎድሮስ – ፋሲካ ገ/ጻዲቅ ወ/ሰንበት

ከስም የተጣሉ፡ ስሙ ያስጨነቃቸው

ስማቸው የጠፋ፡ ያደ’ፈ ስማቸው

ስሙን አንስማ  አሉ፡ ስሙ እያስፈራቸው።

አንዳንድ ስም አለ፡ ጥንቱን ያልታደለ

ከክፉ የዋለ

አንዳንድ ስም አለ፡ ባህሪን ያዘለ

በመልዐክ ተመርጦ

በወላጅ አንደበት፡ ይሁን የተባለ።

 

ከስሞች መሀል ታዲያ

በመልዐክ ከተመረጡት

በወላጅ ከጸደቁት፤

ቴዎድሮስ  ካሣ  ቴዎድሮስ ካሣ

ካሣ  ቴዎድሮስ  ቴዎድሮስ ካሳሁን

አይጥማቸውም አሉ

እኒህ ባለክፉ ስሞችን።

 

ካሣ ሊሆን ዐጼ ቴዎድሮስ

ቢነሣ ለሀገሩ ሊሆን ዋስ

የጠላቶቹ መበርከት፤

ግን ደግሞ  መይሣው ካሣ

ኮሶም ጠጥቶ ቢያገሣ

ያሽራል እንጂ ትንፋሹ

የወገንን አንጀት አራሹ።

ለጠላት ግን ውጋት ሆነ

ለአንድነት ሲል ጨከነ

ለሀገሩ እያደላ

የጠላቶቹን አንገት ቀላ።

 

 

ቴዎድሮስ ቴዎድሮስ

አይሆንም አለ ቴዎድሮስ

አትንኩብኝ ሀገሬን

ሀገሬን አትንኩብኝ

አፈሯን አትድፈሩብኝ።

እንኳን የውጪውን ጠላት

የውስጡንም አልምረውም

በሀገሬ  አንድነት ከመጣብኝ።

 

የቋራው አንበሳ

መይሣው ካሣ

መቅደላ  ላይ ሆኖ

በጀግንነት እያገሳ፤

ሞቼ ነው ቆሜ

ሞቼ ነው ቆሜ

ይፈሳል እንጂ ደሜ፤

እንዳለ አልቀረም እንደፎከረ

ደሙ መሬት ፈሶ

ሽጉጡን በአፉ ጎርሶ

ነው በጠላት የተደፈረ።

 

ቴዎድሮስ ቴዎድሮስ

እምቢ አለ ሳልሣዊው ቴዎድሮስ

አልቀበልም በቁሜ

የኢትዮጵያን መፈራረስ።

አይሆንም አለ ሳልሣዊው ቴዎድሮስ

ዘመናትን አልፎ ሲነሣ

ዘጸዐት ለኢትዮጵያ እያለ

ስለትንሣኤዋ ሲያወሳ።

 

ስለ ይቅርታ ፍቅር

ስለ ሀገር ኩራት ክብር

ስለ ንጉስ ስለ ንጉስ

እንጥሉ እስክትበጠስ፤

ኡኡ  ኡኡ ኡኡ አለ

ደግሙ በዚህ በኛ ዘመን

ትንፋሽ ከጎራዴ ከተሻለ

እጮሀለሁኝ አለ።

 

ምናለ ልሙት ምናለ

በቁሜ ግን ይቺ ሀገር

በቁሜ አታጣም ክብር

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ክልሎች ንፁሀን የአማራ ተወላጆች ላይ ለሚደርሰው ተደጋጋሚ የዘር ጥቃት መንግሥት ለምን ደንታ-ቢስ ሆነ?

ሳልሞት አይርቅም ፍቅር።

እያለሁኝ በህይወት

በቁሜ አይፈርስም አንድነት።

 

ስሜ ቴዎድሮስ ነውኮ

ቴዎድሮስ ካሣ ነው ስሜ

አደራ ነው ትዕዛዝ አለው

‘ምጠራበት ስያሜ።

የመይሳው ሞክሼ

አልቀርም ጥርሴን ነክሼ።

 

ኡኡ እላለሁ ኡኡ ኡኡ

ትንፋሼ እስካለ እጮሃለሁ

አልፈራም ሞትን የማይቀረውን

በቁም መፍረስን እንጂ

መለያየትን እንጂ ‘ምፈራው

ልቋቋመው ‘ማልችለው።

 

ሀገሬ ወይ ሀገሬ

እምዬ እናት ሀገሬ

ተሸራርፈሽ አታልቂም

እኔ ሳለሁ አትፈርሺም

ልጆችሽን ወንድሞቼን

እናት አባት እህቶቼን

አስታርቄ አስማምቼ

አመጣልሻለሁ አግባብቼ።

በስሜ የጠሉኝ ቢኖሩም

ሞቴን ውድቀቴን ቢመኙም

ሀገሬ ላይ ሆኜ እጣራለሁ

አልፈራም አልሸሽም።

 

ሀገሬ እናቴ ሀገሬ

እኔ ልግባ  መቃብሬ

ውርደትሽን ከማይ ቆሜ

እንደመይሳው ይፍሰስ ደሜ።

 

ስሜ ስሜማ ቴዎድሮስ ካሣ

በመልዐክ የወጣልኝ ነው

ከእናት ከአባቴ ስጋ ሳልነሣ።

 

ቴዎድሮስ የሞተላት ምድር

ሌላ ቴዎድሮስ እያለ

አንድነቷ እንዴት ይደፈር

ያውም በገዛ  ልጆቿ

እንደምን ትጣ ክብር።

 

ቴዎድሮስ የሞተላት ምድር

ተሸጠች አሉ ለደርቡሾች

ቋራ  ሁመራ  አርማጭሆ

ለደርቡሽ ተሸጡ አሉ

ገበሬ  አላዳናቸው ጮሆ።

 

ምን ይል ይሆን መይሳው

የእትብቱን መቀበሪያ

ባዕድ ጠላት ሲገዛው።

 

 

 

ሳልሳዊው ቴዎድሮስ

ለሞክሼው ዓላማ  በተቆረቆረ

ለአንድነት ባቀነቀነ

እወህኒ ተወረወረ።

 

 

ስመ ጥፉ ባገር ሞልቶ

 

ጥሩ ስም ያለው አልታደለ

ቴዎድሮስ ካሣ የተባለ።

 

 

 

በዚያ ላይ ዛሬ በሀገራችን

መልካም ስም የወጣለት

ሰውማ ከወደደውማ

የሰው ፍቅርን  ካከለበት

ሰው ካገነነውማ

አለለት መከራ ፍዳ

ስቃይ እንግልት አለበት

ወየውለት ወየውለት

መከራውን ማን አየለት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እባክህ አማራ የሚያስጨፈጭፍህን የምሳር እጀታ ከትከሻህ አውርድ (በላይነህ አባተ)

 

 

May 7, 2008

ቴዲ አፍሮ  ታስሮ

ፋሲካ  ገ/ጻዲቅ  ወ/ሰንበት

ቶሮንቶ፤ ካናዳ

 

 

 

 

 

 

 

 

Share