ማነው? እንዴትስ ነው? (ተገናው ጎሹ)

April 9, 2017
19 mins read
ማነውእንዴትስ ነው?

አዎ!

    የረጅሙ ታሪክ የተጋድሏችን፣

    ነፃ የራስ አገር የማቆየታችን፣

    ለትውልድ ትውልድ ማስተላለፋችን፣

    የጋራ ኩራት ነው የጋራ ክብራችን።

    ዋጥ አድርገን ችለን የቤት ብሶታችን፣

    የጭቆናን ቀንበር የገዢዎቻችን፣

    በደም በአጥንት ዋጋ አገር ማኖራችን፣

    እንደ ሕዝብ እንደ አገር አብረን መዝለቃችን፣

    የተገነባ ነው በምስጢረ አብሮነት በውህድ ደማችን።

ግን

    የእብደት ፖለቲካን መልክ ማስያዝ ተስኖን፣

    አብሮነትን  ሳይሆን ጥላቻና ቂምን እየተገባበዝን፣

    ለከፋፋይና ለጨካኝ ገዢዎች እየተመቻቸን፣

    ከረዥሙ ታሪክ ከደጉም ከክፉም ባለመማራችን፣

    ነፃ ባቆየናት በገዛ ምድራችን፣

    ስንቀበልባት ስቃይ መከራችን፣

    ማነው እሚፈታው፣ እንዴት ነው እሚፈታው እንቆቅልሻችን?

አዎ!

     የዚያ ባለ ታሪክ ልጆች፣ የልጅ ልጆች እንደመሆናችን፣

    ጥልቅ ነው ሰፊ ነው ክብር ኩራታችን።

ግን

    በአያት፣ በቅድመአያት በተሰራ ታሪክ ዘፈን እየዘፈን ወይም እየፎከርን፣

    ልማድ እስኪመስል ዘመን እየቆጠርን፣ ቀንን እየዘከርን፣

    ከተሰቀለበት ጦር ጋሻ እያወረድን፣

    ጧሪና ቀባሪ በሌለው ደረት ላይ ሜዳሊያ አንጠልጥለን፣

    ታሪክን ለከዱ ሸፍጠኛ ገዢዎች አጃቢዎች ሆነን፣

    ጎንበስ ቀና ብለን እነሱን ደጅ ጠንተን፣

    ከነሱ ያደረን ፍርፋሪ ለቅመን፣

    ደግሞም ሲሳካልን ኢንቬስተሮች ሆነን፣

    በዝርፍያው በቅሚያው አብረን ተሰማርተን፣

    ዘመን መቁጠራችን፣ እዚህ መድረሳችን፣

    እንዴት ነው እሚፈታው፣ ማንስ ነው እሚፈታው እንቆቅልሻችን።

አዎ!

    የውጪ ወራሪዎች እንደተመኙልን፣ እንደዘመቱብን፣

    የዉስጥ ገዦቻችን እንዳጎሳቆሉን፣

    በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባሕል ልዩነት እንደመብዛታችን፣

    ቤት አልባ ያልሆነው አፍርሰን ቤታችን፣

    በመዋሀዱ ነው ለአገር የከፈልነው መስዋዕቱ ደማችን።

    የሩብ ምዕተ አመቱ የጎጠኞች እብደት፣ የዘረኞች ፅልመት፣

    ፍርስርስ ያረገው የስንቱን ቤት ንብረት፣

    እርግፍግፍ ያረገው የስንቶቹን ህይወት፣

    ታሪክ የለወጠው ወደ ተረትነት፣

    ምስቅልቅል ያረገው ያገርን ምንነት፣

    እስኪጠፋን ድረስ ትርጉሙ የዜግነት፣

    መወገድ አለበት በላቀ ትብብር፣ በማይፈርስ አንድነት።

    ይሄ እውን ሆኖ ለዉጥ መምጣት ካለበት፣

    የውድቀታችን ምንጭ የሩብ ምዕተ አመት፣

    አስተሳሰባችን መለወጥ አለበት።

    እኛው ችግር ፈጥረን፣ እኛው አወሳስበን፣

    ጥበቡ ጠፍቶብን፣ ቅንነቱ ጎሎን፣ ትግሥት አልባ ሆነን፣

    በሕዝብ ለሕዝብ ሳይሆን፣

    በቡድን ለቡድን እየተደራጀን፣

    የግል ጥቅምንና ዝናን እያሰላን፣

    የቆጠርነው እድሜ፣ ያሳለፍነው ዘመን፣

    እስቲ ይጸጽተን ሕመሙ ይሰማን።

    አዎትክክል ነው፣

    ጠንክሮ እንዲወጣ የምንፈልገው፣

    የዜግነት መብት ኢትዮጵያዊነት ነው።

    ይህ ግን የሚሆነው፣

    ሌሎች ማንነቶች በጥበብ በትግሥት ሲስተናገዱ ነው።

ግን

    አሁንም በዚህ ወቅት፣ ዘረኛ ገዢዎች ፍፁም ባበዱበት፣

    በሀሳብ የተለየን በሚያሰቃዩበት፣

    ቀጭን ትእዛዝ ሰጥተው በሚያስገድሉበት፣

    ገዳይ ሀይላቸውን ጭራሽ ጀግና ብለው በሚያወድሱበት፣

    ስቃይ፣ ሰቆቃውን፣ ነፃ እርምጃዉን በአዋጅ ባወጁበት፣

    አልተጸየፍነውም ክፉውን ልዩነት፣

    የተጓዝንበትን ለሩብ ምዕተ አመት።

    ይሄ ክፉ አዙሪት እሽክርክሪታችን፣

    እንዴት ነው እሚፈታው፣ ማንስ ነው እሚፈታው እንቆቅልሻችን?

አዎ!

    የእምነታችን ታሪክ በዉን ያኮራናል፣

    እስላም ክርስቲያኑን በአንድ ላይ አኑሯል፣ በፍቅር አጣምሯል።

    የአገር ፍቅርና ሐይማኖቶቻችን፣

    ጣምራ እሴቶች ናቸው ያኩሪዉ ታሪካችን።

    የወገን መከራ ግድ ይለናል ብለው፣

    ባለጌ ገዦችን የገሰፁ ደፍረው፣ 

    መስዋት የከፈሉ በቃላቸው አድረው፣

    በታሪክ ጉዟችን ታላቅ ሥፍራ አላቸዉ።

ግን

    አሁን ባለንበት በዚህ ዘመናችን፣

    ካንጀት ሳይሆን ካንገት ሆኖ ፀሎታችን፣

    ዝና አድርገነው መብዓ ማቅረባችን፣ ምጽዋት መስጠታችን፣

    ለእንጀራ ማብሰያ ኑሮ ማሻሻያ ሲሆን ስብከታችን፣

    ወደ ቤተ አምልኮ መመላለሳችን፣

    ተራ ልማድ ሲሆን ያልገባ ዉስጣችን፣

    ድነን ማዳን ሲያቅተን አገር ወገናችን፣

    እግዚኦ አድነን እያልን መጮሀችን፣

    እንዴት ነው እሚፈታዉ፣ ማንስ ነው እሚፈታው እንቆቅልሻችን?

    መከራ ሲነግስ ገዝፎ ስንፍናችን፣ ገኖ ፍራታችን፣

    የእግዜር ቁጣ ነዉ ብለን መስበካችን፣ ወይ ማስተማራችን፣

    ድርጊት አልባ ፀሎት የማነብነባችን፣

    ከመድረክ አላልፍ ሲል ዜማ መዝሙራችን፣

    ማነው እሚፈታው፣ እንዴት ነው አሚፈታው እንቆቅልሻችን?

    የፈጣጠርነውን መከራና ስቃይ እኛዉ እራሳችን፣

    የተጫነብንን የሰቆቃ ቀንበር በገዢዎቻችን፣

    አንተ (ፈጣሪአቅለው ብለን የመተኛታችን፣

    መከራና ስቃይ የጽድቅ ስንቅ ነው እያልን መስበካችን፣

    የእንችላለንና የድርጊት መንፈስን የማኮስመናችን፣

    ማጠር ያለበትን የመከራ ዘመን የማራዘማችን፣

    ማነው እሚፈታው፣ እንዴት ነው እሚፈታው እንቆቅልሻችን?

    ያደንቁሮ ገዢዎች ተባባሪ ሆነን፣

    ሰብአዊ ማንነት እንዳልሆነ ሲሆን እየተመለከትን፣

    እንዴት ለምን ሲሉን ፖለቲካ እያልን የመቀለዳችን፣

    እንዴት ነዉ እሚፈታዉ፣ ማንስ ነው እሚፈታው እንቆቅልሻችን?

    በቁሙ እያለ ያልደረስንለትን፣ አይዞህ ያላልነውን፣

    በረሀብ ሲቀጡት ያልተቆጣነዉን፣ ያላመረርነውን፣

    በጥይት ሲመትሩት ጋሻ ያልሆነዉን፣

    በቆሻሻ አኑረው ቆሻሻ ሲያለብሱት መቁረጥ ያቃተንን፣

    ምን አርግ ነው እምንለዉ በሰማይ ያለውን?

    ዝም ጭጭ ብለን ቆመን አስገድለን፣

    በየቤተ እምነቱ ዙሪያ ተደርድረን፣

    በማኀሌት ሆነን ቤተመቅደስ ገብተን፣

    እባክህን ማረዉ፣ እባክህን ማራት ብለን እንጮሀለን፣

    ደግሞም እንደልማድ ከበሮ እንመታለን፣

    ድምፁን ከፍ አድርገን ፅና እናንሿሿለን፣

    በዜማ በንባብ ሙሾ እናወርዳለን፣

    ከከንፈር የማያልፍ የመጽናኛ ዲስኩር እንደሰኩራለን።

    ይሄ እንቆቅልሽ፣ ይሄ የሰቆቃው፣

    እንዴት ነው እሚፈታው፣ ማንስ ነው እሚፈታው።

    ረቂቅ አእምሮ ብቁ አካል የሰጠን፣

    እንድኖር አደለም የታምር ነፃ አውጪ እየተጠባበቅን።

    እኛ ግን አሁንም ድርጊት አልባ ጩኸት እናስተጋባለን፣

    ማገናኘት አቅቶን ቃልና ድርጊትን፣

    ታምር አዉርድ እያልን እግዚኦ እንላለን።

    ደሞ የሚገርመው እጅግ የሚቆጨዉ፣

    ባለንበት ቆመን ዘመን ስንቆጥር ነው።

    አዎበታላቁ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው፣

    ወደ ፈጣሪዋ እጅ የዘረጋችዉ፣

    የኛ አገር መሆኗ ትልቅ ትርጉም አለው።

    ሁሌም ተዘርግተው አቤት ሐያሉ አምላክ የሚሉት እጆቿ፣

    ስጥልኝ ስትል ነው ፍቅርና አብሮነት ለመላዉ ልጆቿ፣

    እኛ ግን እየተለያየን፣

    እየተጠላለፍን አብረን እየወደቅን፣

    ፍቅርን እየጠላን ጥላቻን አፍቅረን፣

    ለወገን መዘርጋት ተስኖት እጃችን፣

    ግሩም ነዉ እንላለን በታላቁ መጽሐፍ በመጠቀሳችን፣

    ታዲያ ይህ ክፉ አዙሪት እሽክርክሪታችን፣

    ማነው እሚፈታው፣ እንዴትስ ይፈታል እንቆቅልሻችን።

አዎ!

    እንደኛ ስንፍና እንደ ክፋታችን፣

    እየተጠላለፍን እንደመዉደቃችን፣

    የመከራ ዘመን እንደማርዘማችን፣

    ጀግና አልባ አልሆነችም ኢትዮጵያ አገራችን።

    ቅድስት ማሀፀኗ ጨርሶ እማይነጥፈው፣

    ዛሬም ጀግኖች ወልዷል መቼም አይሳነው።

    በዉብ ማሀፀኗ በተሸከማቸዉ፣

    በእናትነት ክንዷ አቅፎ ባሞቃቸው፣

    በጡቶቿ ወተት በመገበቻቸው፣

    በቃል ኪዳን ፀንተዉ በእምነት ተሳስረው፣

    በዉስጥም በዉጪም ከየመኖሪያቸዉ፣

    ነፃነት በነፃ አይገኝም ብለው፣

    የቁርጥ ቀን ልጆች ፍልሚያው ቦታ ናቸዉ።

    አዎእዚያ ትግል ሜዳ ድምጽ ያስተጋባል፣

    አድማሱን አቋርጦ አየሩን ሰንጥቆ ኢትዮጵያን አዳርሷል።

    ድምበርን ተሻግሮ ውቅያኖስ አልፎ ይሄዳል ይነጉዳል፣

    ወገን ያገር ልጅን በአዋጅ ይጣራል፣

    እንዲህ ይናገራል።

    መደማመጥ አቅቶን መከባበር ጠልተን እዚህ የደረስነው፣

    የጨካኝ ዘረኞች ሰለባ የሆነው፣

    የዕለት ምግብ እንኳ ዋስትና ያጣነዉ፣

    የተመፅዋችነት እስረኛ የሆነው፣

    በመዝገበ ቃላት የረሀብ ፍቺ መፍቻ ምሳሌ የሆነዉ፣

    በማንነታችን የተሸማቀቅነዉ፣

    ከየት ነህከየት ነሽየሚልን ጥያቄ በእጅጉ እምንሸሸዉ፣

    ደፍረን እንቀበል ችግሩ ከኛዉ ነዉ።

    እናም ይሄ እሽክርክሪት እንቆቅልሻችን፣

    መፈታት አለበት በኛዉ በራሳችን።

    ደግሞም ያስተጋባል በአፅንኦት ያዉጃል፣

    እንዲህም ይለናል።

    መሆኑን ካመንን የመፍትሔው ቁልፉ ከኛዉ ከራሳችን፣ 

    እንዴት ነው እምንፈታው እንቆቅልሻችን?

    ይክበድም ይቅለልም መልሱ አንድ ብቻ ነው፣

    የድል፣ የነፃነት ጠበቃ ዋስትናዉ፣

    እጅ ለእጅ ተያይዞ መታገል ብቻ ነዉ።

    እጅግ ዘግይተናል፣ መከራዉም በዝቷል፣

    የተናጠልና የሽኩቻው መንገድ ከእንግዲህ ይበቃል። 

 

     

 

 Tegenaw Goshu (ጐሹ ) 

 

April 7, 2017

1 Comment

Comments are closed.

Previous Story

ኢትዮጵያዊነትን ማን ነካክሶ አቆሰለው (ክፍል ሁለት) – ያየያየ ይልማ

Next Story

እጃችሁን ከአማራው ላይ አንሱ! – ግርማ በላይ

Latest from Blog

አትዮጵያ ያን ዕለት

ግም ሞት 20’ 1983 .ዓ.ም. ለህወሀት /ኢህአዴግ ልደት ለኢትዮጵያ እና ለብዙዉ ኢትዮጵያዉያን የዉድቀት ፣ጥልመት እና ሞት ዕለት መሆኑን ያ ለሁለት አሰርተ ዓመታት ከፍተኛ ዕልቂት እና ደም መፋሰስ የነበረበት ጦርነት አዲስ አበባ በደም

አቢይ አህመድ ታላቁን አሜሪካንና የተቀሩትን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ማታለል ይችላል ወይ? የአሜሪካ “ብሄራዊ ጥቅምስ ኢትዮጵያ ውስጥ“ እንዴት ይጠበቃል? የአሜሪካ እሴቶችስ(Values) ምንድን ናቸው?

ለመሳይ መኮንና ለተጋባዡ የቀድሞ “ከፍተኛ  ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት” በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን የስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ተቀጥሮ ለሚስራው ኢትዮጵያዊ ሰው የተሰጠ ምላሽ!   ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ግንቦት 19፣ 2016(ግንቦት 27፣ 2024) መሳይ መኮንን በአ.አ በ17.05.2024 ዓ.ም አንድ እሱ  የቀድሞው “ከፍተኛ የኢትዮጵያ

ጎንደር ሞርታሩን እስከ ጄነራሉ ተማረከ | ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | ብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን

ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | “ፋኖ ከተማውን ቢቆ-ጣ-ጠር ይሻላል” ከንቲባው |“አብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን” ኮ/ሉ |“በድ-ሮን እንመ-ታችኋለን እጅ እንዳትሰጡ” ጄ/ሉ
Go toTop