የወያኔ ራዕይ ቅዠት ሆኖ የሚቀረው ሥርአቱን ተረክቦ የሚያስቀጥል ትውልድ ስለማያገኝ ነው | ከይገርማል

የሀገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ በተደጋጋሚ የሚነገረው የፖለቲካ ድርጅቶች በዋናነት የአንድነት ኃይሎችና የጎሣ ኃይሎች በሚል በሁለት እንደሚከፈሉ ነው:: ልዩነታቸው የአይዲዮሎጂ ወይም የፖለቲካ ፕሮግራም ሳይሆን ባረጀ ባፈጀ የማርክሲስት ሌኒንስት አስተምህሮ ላይ በተመረኮዘ እሳቤ በዘርና በቋንቋ በተቧደኑ ጠባቦችና በአንድነት ኃይሎች መሀከል ባለ የመበተንና የመሰብሰብ ፍቅር ላይ የተመሰረተ ነው:: የጎሳ ኃይሎች የሚባሉት አንድን ጎሣ ወይም አካባቢ የትኩረት ማዕከል አድርገው የተደራጁትን ሲሆን የአንድነት ኃይሎች የሚባሉት ደግሞ ጎሣና አካባቢ ሳይገድባቸው ሁሉንም በእኩል ዐይን እናያለን ለሕዝብ አንድነትና ለሀገር ግንባታ እንሰለፋለን የሚሉትን ነው:: 

ኢትዮጵያ ከውጪ ወራሪ ኃይል ጋር ጦርነት በገጠመችባቸው ጊዜያት ሁሉ ከየትኛውም ጎሣ ለጠላት ያደሩ ሰዎች እንደነበሩ ከታሪክ እንረዳለን:: ያም ሆኖ ተበታትኖ በየትናንሽ ባህላዊ የሰፈር አስተዳደሮች ይተዳደር የነበረውን ሕዝብ በማሰባሰብ የተጠናከረች ኢትዮጵያ ዕውን እንድትሆን የታገለው የአንድነት ኃይል አሸንፎ ዛሬ እንዲህ እናፍርሳት: አይ እናድሳት: የለም አፍርሰን እንስራት የምንላትን ሀገር ለእኛ ማስረከብ ተቻለ:: 

ይህች ሀገር እንዲህ በቀላሉ እዚህ የደረሰች አይደለችም:: የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ሁልቆ መሳፍርት የሌለው የአንድነት ኃይል ደምና አጥንት ከፍሎ አላማውን አሳክቷል:: ሁልቆ መሳፍርት የሌለው የሀገር ባንዳና የውጪ ወራሪ ኃይል ፍላጎታቸውን ከዳር ሳያደርሱ አልፈዋል:: በዚች ታሪካዊት ምድር ለአንድነቷ እና ለነጻነቷ የሞቱላትም ሆኑ ሊበታትኗትና ቅኝ ሊገዟት ጎራዴ መዝዘው በጦር ሜዳ የተገደሉት ሁሉም ስራቸውን ለታሪክ ትተው አርፈው አፈሯን ለብሰዋል:: 

ከ1969-1970 ቀጥተኛ የሶማሌ ወረራ ወዲህ ሀገራችንን በቀጥታ የሚተነኩስ የውጭ ወራሪ ኃይል አልታየም:: ይሁን እንጅ የውጪ ወራሪ ኃይሎች ከፈጸሙት የበለጠ ጭፍጨፋና ጥፋት በሀገር በቀል ጸረ-አንድነት ኃይሎች ተፈጽሟል: አሁንም እየተፈጸመ ነው:: የኢትዮጵያ ጠላቶች ቀጥተኛ ወረራ ለመፈጸም እንደበፊቱ ጦር ሰብቀው ጐራዴ መዘው አይምጡብን እንጅ አሁንም ቢሆን ልባቸው ለነዋይና ለስልጣን ተሸናፊ የሆኑትን ወይም በተለያየ ምክንያት አኩርፊናል የሚሉትን ሀገር በቀል አጋሚዶወች በመላክ ጉዳት ከማድረስ አልቦዘኑም:: ራሳቸውን በጎሣና በሐይማኖት ድርጅቶች ያደራጁ ወገኖች ኢትዮጵያን በታትነው ራሳቸውን ችለው ሊቆሙ የሚከብዳቸው ትናንሽ መንግሥታትን ለመመስረት እንዲታገሉ ስልጠና የሚሰጣቸውም ሆነ ትጥቅና ስንቅ የሚያገኙት ከነዚህ ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ነው:: እነዚህ ራሳቸውን በጎሣና በሐይማኖት ያደራጁ ኃይሎች የእኛ ጎሳ አባል አይደለም/ የእኛ ሐይማኖት ተከታይ አይደለም ባሉት ሰላማዊ ዜጋ ላይ ለመናገርም ሆነ ለመስማት የሚከብድ ዘግናኝ ግፍ ሰርተዋል:: 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደብረጺዮን በሁመራ ዋሉ

በመሰረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰውን አክባሪ: ከራሱ ሸንጉቶ ለእንግዳ የሚያጎርስ: ለሥጋው ሳይሆን ለነፍሱ ያደረ: በአንድ አምላክ የሚያምን ሕዝብ ነው:: የተቸገረን በመርዳት: የታመመን በማስታመም: የተጣላን በማስታረቅ: የሚሄድን በመሸኘት: የሚመጣን በመቀበል: ችግሩንም ደስታውንም ተካፍሎ የሚኖር በይሉኝታና በሞራል የተገነባ ሕዝብ ነው:: “የመሸብኝ የእግዜር እንገዳ ነኝ” ብሎ ለመጣ መንገደኛ የጎሣና የሐይማኖት አጥር ሳይገድበው “ቤት ለእንገዳ!” ብሎ ያለውን ሳይሰስት አቅርቦ ጠብ እርግፍ ብሎ የሚያስተናግድ የደከመን የሚያበረታ: ጣመንን የሚያፍታታ: ርሀብን የሚያስታግስ ድንቅ ሕዝብ ነው:: 

ሀገራችን ከየትኛውም ሀገር በተለየ የሀይማኖት ችግር የማይስተዋልባት: ዘረኝነት የማይታሰብባት ሀገር ነበረች:: ጠዋት አደም ይባል የነበረው ከሰዐት በኋላ አዳም የሚባልባት ወይም ጠዋት አዳም ይባል የነበረው ከሰዐት በኋላ አደም የሚባልባት ጽድቁንም ኩነኔውንም ለአምላክ አሳልፈው የሰጡባት ከስልጣን ጥያቄ ውጪ ባሉት ነገሮች በብዙ ጎኑ ያልታወቀላት ዴሞክራሲያዊት ልትባል የምትችል የግለሰብ መብት የተከበረባት ሀገር ነበረች:: እስላምና ክርስቲያኑ በአንድ ዕድር የተሰባሰበባት: በሰርግ: በቀብር: በተዝካር: በሀይማኖት በዐላት የማይለያዩባት: በዘርና በቋንቋ የማይጎሻሸሙባት “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” እንዲሉ ከምንም በላይ ፍቅር የነገሰባት የጋራ ቤት ነበረች:: 

እንደሚታወቀው ይህች አለም የምትዘወረውም ሆነ የምትበጠበጠው በብዙሀኑ ሳይሆን በጥቂቶች ነው:: ጥቂቶች ናቸው የሚያለሙትም የሚያጠፉትም:: ብዙሀኑ ሕዝብ እግዜር እስከፈቀደለት ጊዜ በሰላም ሰርቶ መኖር የሚፈልግ ተሳስቦ የሚኖር ለአምላኩ የተመቸ ሕዝብ ነው:: ከማሕበረሰቡ መሀል የተለየ ፍላጎት ያላቸው ጥቂት ግለሰቦች ናቸው ለጥሩም ለመጥፎም ድርጅት በመመስረት አላማቸውን ለማሳካት የማሳሳቻ ቃላትን እየተጠቀሙ በሕዝብ ሰላም: ሀብትና ሕይወት ላይ እንደፈለጋቸው የሚጫወቱት::

ወያኔ ወደስልጣን ሲመጣ ፍቅርና መተሳሰብ ጥለውን ጠፍተው ጥላቻና መለያየት በቦታቸው ተተኩ:: የክርስቲያንና የእስላም ዕድሮች ተለዩ: ክልሌ ከሚሉት ውጪ ወጥቶ መኖር ጥፋትን አስከትሎ ለቁጥር የሚታክት ሰላማዊ ሕዝብን እንደቀልድ ጠፋ:: ጎሰኞች በአንድነት ኃይሎች ላይ የበላይነት ተቀዳጅተው የሚያስተሳስሩንን ማህበራዊ እሴቶች በመበጣጠስ ስለልዩነታችን ይተረክ ያዘ:: የሦስት ሽህ አመት አኩሪ የነጻነት ታሪካችን ተሰርዞ የ100 አመት አሳፋሪ የኢትዮጵያ ታሪክ ተፈጠረልን:: ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በጎሰኞች ፈጠራ ተታለው የማይረሳ በደል ፈጸሙ:: 

ተጨማሪ ያንብቡ:  በእነሀብታሙ አያሌው ጉዳይ ማረሚያ ቤት ላይ ክስ ቀረበ

ሀገር ዳር እስከዳር ሽብር ውስጥ ገብታ ሁሉም በፍርሀት ቆፈን በሚርገፈገፍበት ጊዜ ወያኔወችና ግብረበላወቻቸው ከድሀው አፍ እየሞጨቁ ለልጅ ልጆቻቸው የሚተርፍ ሀብት አካበቱ:: ለጭቁን ብሔር-ብሔረሰቦች እንታገላለን ብለው የጭቁኖችን ጥሪት አሟጠው ወሰዱ:: በሕዝብ ስም እያለቀሱ የሕዝቡን ደም አፈሰሱ:: የነአጼ ቴወድሮስ: የነአጼ ሚኒሊክ: የእነ ራስ አሉላ አባነጋ: የነራስ ጎበና ዳጬ: የነሱልጣን ዐሊ ሚራህ: – – – ልጆች አንገታቸውን ደፍተው የነ ራስ ስሁል ሚካኤል: የነኃይለሥላሴ ጉግሳ ልጆች ነገሱ:: የነአቡነ ጴጥሮስ የመንፈስ ልጆች ተገፍተው የነአቡነ ጳውሎስ የምግባር ልጆች የሀይማኖት አባት ሆኑ:: በሀገራችን እንደሰው ባንታይ: ግፉ ቢበዛብን በአፋችን የመጣልንን እርግማን አዥጎድጉደን ላንመለስ ድንጋይ ጥለን ተሰደድን:: ነገር ግን የወደቀብን የመከራ ሸክም አልወርድ ቢለን ካሰብነው ሳንደርስ በየበረሀው ወደቅን:: ኧረ ስንቱ ይነገራል! 

በአንድ ወቅት አብርሀ ደስታ መታሰሩን የሚገልጽ ጽሁፍ በአቡጊዳ ላይ አንብቤ በአስተያየት መስጫው ላይ ያስቀመጥሁት አስተያየት ነበር::  በዚያ አስተያየቴ ላይ ወያኔና አስከፊ ስርአቱ የሚወድቁት በተቃዋሚው ጥንካሬ ሳይሆን አሮጌውን አስተሳሰብ ተሸክመው የሚዞሩ ሱቅ-በደረቴወች ለመሆን በማይፈቅዱ ታዳጊወች እንደሚሆን ነበር:: ልዩነትን የሚያራግቡ የአንድነት ብሎችን እኩይ ባህሪይ ሊጋሩ በማይፈልጉ ወጣቶች እንደሚሆን ነበር:: የወያኔና ጀሌወቹን የተበላሸ አስተሳሰብ ሊረከቡ በማይፈልጉ ትውልዶች ምክንያት የወያኔና መሰሎቹ የተበላሸ እይታ አይሻገርም ብየ በማሰብ ነበር::  

በጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ ባነቀፋቸው ቁጥር ወድቀው የሚቀሩ: ባዳለጣቸው ቁጥር የሚንሸራተቱ ቢኖሩም አሁንም የአባቶቻችንን መስዋእትነት ከንቱ ለማስቀረት የማይፈቅዱ የትኛውም ፈተና የማያሸንፋቸው ጽኑ የሀገር ልጆች አልጠፉም:: ከደምና ከቋንቋ በላይ ሀገሬ ያሉ ኢትዮጵያውያን አሁንም ሞልተዋል:: ከእውነተኛ የትግራይ ልጆች እነ ገብረመድህን አርአያን የመሳሰሉ ቃላቸው የማይታጠፍ: ጊዜ የማይለውጣቸው የእውነት ተሟጋቾች የአንድነት ማተቦች እጅ አልሰጡም:: በፌስቡክ የማውቃቸው የነ አብዲሳ አጋ: የነጎበና ዳጬ ልጆች ምስራቅ ተስፋየ: መስፍን የመሳሰሉት እንደነ ጂጂና ጃዋር መሀመድ ለመሳሰሉት የዳውድ ኢብሳና የኦቦ ሊበን ዋቆ ልጆች አልተንበረከኩም:: ዛሬም እጅግ ብዙ የቴወድሮስ: የሚኒሊክ: የአሉላ: የጎበና: የበላይ ዘለቀ: የጃጋማ ኬሎ: የባልቻ አባነፍሶ: የሱልጣን ዐሊ ሚራህ _ _ _  ልጆች የሀገራችንን ታሪክና አንድነት ለመከላከል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እየጮሁ ነው:: የነዚህ ወገኖች ጩኸት ከምንም በላይ ገዝፎ አንድነት: ፍቅርና ሰላም መለያው የሆነውን ወጣት ከየማዕዘኑ የሚጠራ ይሆናል:: ይህን ተከትሎ ጥላቻ በፍቅር መለያየት በአንድነት ይሸነፋሉ:: አዲሱን ችግር በአሮጌ አስተሳሰብ ለመፍታት የሚዳክሩ ጐሰኞች የሻገተ አስተሳሰባቸውን ተቀብሎ የሚያራምድ አዲስ ትውልድ ስለማያገኙ ሳይወዱ በግድ ቀስ በቀስ በሽንፈት እጃቸውን ይሰጣሉ:: ልዩነታችን ውበታችን አንድነታችን ህልውናችን ነው የሚሉ ወጣቶች ያለጥርጥር ቤታችንን ከተባይ አጽድተው የዱሮውን ፍቅራችንን እና ኩራታችንን ይመልሱልናል:: 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለቸኮለ! ማክሰኞ መስከረም 18/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!

Share