ሸንጎ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጣይነት እያካሄደ ካለው ትግል ጎን እንደሚቆም አስታወቀ

ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ. ም

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ዕሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ. ም በጎንደርና በደሴ ከተሞች የተካሄዱትን ትዕይንተ-ሕዝቦች ይደግፋል። ”የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!” በሚል መሪ ሃሳብ ሥር በአንድነት ፓርቲ አቀነባባሪነት የተጀመረው የሕዝብ እንቅስቃሴ፤ የተጋረጠበትን እንቅፋት ሁሉ አልፎ እነሆ በደሴና በጎንደር ከተሞች በከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ የፍራቻ ድባብን ሰብሮ በይፋ ለመግልጥ መቻሉ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ ተግባር ነው።

ሃሳብን በሰላማዊ መንገድ መግለጥ የሰው ልጅ የተፈጥሮ መብት ነው። ይህ መብት ደግሞ ሰው በሰውነቱ ሊከበሩለት ከሚገቡት በርካታ መብቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን በዓለም አቀፍ ሕግጋትም የተደነገገ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶቶች እጅግ ብዙ ናቸው። በኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት መሰቃየት፣ ከዚህም የተነሳ ስብዕናውን የሚያዋርዱ ተግባራት ውስጥ እንዲሰማራ መገደዱ፤ የሕግ የበላይነት ተደፍጥጦ የሕዝቡ በሆነ ባልሆነው ምክንያት መደብደብ፤ መታሰር፣ መሰቃየት፤ መገደልና ለስደት መዳረግ ዕለታዊ ተግባራት መሆናቸው፤ ሙስና በስፋት መንሰራፋቱ፤ የመፃፍ፤ የመናገር፤ በነፃነት የመደራጀት መብቱ ሊከበርለት አለመቻሉ፤ በሃይማኖቱ ውስጥ የአገዛዙ ጣልቃ ገብነትና አያደረሰበት ያለው ሰቆቃ፣ ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት ቀየው ያላግባብ መፈናቀሉ፤ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ድምፁን ሊያሰማ አለመቻሉ፣ በሚናገረው ቋንቋ ምክንያት በገዛ ሀገሩ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ተዘዋውሮ ለመሥራትና ለመኖር አለመቻሉ፣ ሕዝብ የሚፈልገውን መንግሥት ሊመርጥ አለመቻሉ…ወዘተ በዚህ ሥር የሚጠቃለሉ ሰቆቃዎች ናቸው፡

ከላይ የተጠቀሱትን ሰቆቃዎች አስወግዶ መብቶችን ለማቀዳጀትና እንደሰው ለመኖር የፍራቻ ድባብን ወርውሮ በመጣል አጠንክሮ መታገል የግድ ነው። ተደጋግሞ እንደሚነገረው፤ ያለትግል ድል የለምና።

አዎ ያለው አገዛዝ በጭካኔ የተሞላ ነው። ያለው አገዛዝ ሕዝብ በፍርሃት ተሸብቦ ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ የማያደርገው ነገር የለም። አገዛዙ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ይረዱኛል የሚላቸውን እርምጃዎች ሁሉ ቢወስድም፤ ለመብቶቹ መከበር የሚታገልን ቆራጥ ሕዝብ ግን ለረጅም ጊዜ አንበርክኮ መግዛት አይችልም። ይህን ሃቅ ከራሳችን የትላንትና የትላንት በስቲያ ታሪካችን፤ እንዲሁም ዛሬ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚታየው እውነታ ትምህርት መውሰድ ይቻላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሃዋሳ 3 የአንድነት አመራርና አባላት ታሰሩ - “እስሩ ቅስቀሳውን አያስተጓጉለውም”

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ፤ አሁን ደግሞ (ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ. ም) በጎንደርና በደሴ ከተሞች የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፍራቻ ድባብን ሰብሮ በመውጣት መብቶቹን ለማስከበር ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ይህ በቁርጠኝነት እየተካሄደ ያለው አበረታች ትግል ውጤታማ እንዲሆን ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደጎን በመተው በአንድነትና፣ በቀጣይነት የሕዝቡን ትግል ማስተባበር ይጠበቅባቸዋል። ስለሆነም ይህንን ታሪካዊ ግዳጅ ለመወጣት ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ድርጅቶች ተባብረው እንዲታገሉ አሁንም ጥሪውን ያቀርባል። ሸንጎው ከምሥረታው ጀምሮ በተደጋጋሚ እንደገለጸው ሁሉ ዛሬም ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።

የተባበረና የቆረጠን ሕዝብ ፍላጎት የሚገታ ምንም ኃይል ከቶውንም አይኖርም!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

1 Comment

  1. I for one don’t agree with these multiple parties for the sake of one target which is to throw away the current junta eprdf my wish will be all of you parties I don’t care if you content is 5,10,or millions unite together be one and act like one then we will see the result otherwise it won’t go far, names of the different parties it won’t take us any where. medrek,andnet,semayawi,ehapa,oneg,obneg shengo etc……………….. find a way to be one for the sake of one nation ETHIOPIA.
    Thank you

Comments are closed.

Share