****************በዕውቀቱ ቡዳው በላን!*******************
***********ወፌ ቆመች እና ወደቀች፤ ከአሜን ያልተሻገረ ሐተታ*****************
በይድነቃቸው ሰለሞን (በደብረ ብርሃን የኒቨርሲቲ የእንግሊዘኛ ቋንቋና ሥነ-ፅኁፍ መምህር)
‹‹ቁም!›› ቡዳ ማለት የራሱን ድክመት ሳይመለከት ሌሎች ላይ የሚደፈድፍ ማለት ነው፡፡ ቃሉን ማህበረሰባችን ካንጠለጠለበት አሉዊ ትረጉም አውርደው በጎ እሴት በማልብስ ብቅ ያሉት አውቁ የአገራችን የፖለቲካ ሰው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አፍታተውታል፡፡ መመልከት ትችላለህ፡፡ የስነ-ጽሁፉ ሰው ቴዎድሮስ ገብሬ እንዲህ አይነቱን በማህበረሰቡ የተንጠለጠሉ ቃላትን አውርዶ በአዲስ እሴት በመሙላት መጠቀምን ግልብጥ ሃቲት (reverse discourse) ማቅረብ ይሉታል፡፡ ቃሉን በዕውቀቱም ተጠቅሞበታል፤ ስለ ጃርሶ ኪሩቤል (ደራሲ) ባወሳበት ገጽ 52 ላይ ‹‹የካሜራ ዓይን እንደ ቡዳ ዓይን ይፈራል›› ይላል፡፡ ስለዚህ የበዕውቀቱን የተለመድ የቃሉን አረዳድ ወደ ጎን ትተን፤ የመረራን ግልብጥ ሃቲት አዝለን እንቀጥል፡፡ በላን ስል በዘመኔ የአራዳ ቋንቋ ሰረቀን ማለቴ ነው፡፡ አሁን ሂድ!
******************** **************** ****************
ለኢትዮጵያ ምሁራን እና ለደራሲው ስብዕና በማይመጥን መለኩ በበዕውቀቱ ሥዩም ተደርሶ ለንባብ ያበቃው ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ዲስኩር የፌስ ቡክ ቅንጭብ አስተያየቶችን ጨምሮ በአመክኖ ጠንከርና ዘለግ ያሉ የመፅሃፍ ግምገማዎችን ለማንበብ በማስቻሉ ጥሩ የመነጋገሪያ መድረክ ፈጥሯል፡፡ ይህም ደራሲው አንድም ከአንባቢያን ጋር በቀደምት የግጥም ሥራዎቹ ስለሚታወቅ (ታዋቂ)፣ አንድም የመረጠው ጭብጥ ወቅታዊ፣ አንገብጋቢ፣ አስፈላጊ በመሆኑ (አስታዋይ) እና አንድም አቀራረቡ ለየት ያለና ለአንባቢ የማይሰለች የአጻጻፍ ሥነ-ዘዴን በመከተሉ (ብልጥ)የተፈጠረ ሁነት ነው፤ ብልህ ግን አይደለም!
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆኑኝ ሶስት መሰረታዊ ነጥቦች፤ አንድ፣ ምክንያታዊ አስተሳሰብ በውይይት እጅጉን ስለሚዳብር፤ በተለይም የማሰላሰል ውጤት በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉ መጽኃፍት ላይ የሚከወኑ ሂስ አዘል ውይይቶች የጎመራ ፍሬ እንደሚያበሉ የታመነ ነው፤ የበዕወቀቱም ድርሰት ይህን ቦታ በስህተት ስለወሰደ፤ ሁለት፣ በመፅሃፉና በመፅሃፉ ተቺዎች በቀረቡት ሃሳቦች እርካታ ማጣት ነው፤ ወይም ያልተነኩ ጉዳዮች ግን መታለፍ የሌለባቸው ነጥቦች ስላሉኝ ነው፤ ሶስት፣ የግሌን ምልከታና የመፀጽሃፉን አረዳድ ለማየትና ለማሳየት ነው፡፡
ይህን ፅሁፍ ከማሰናደቴ በፊት አንድ የደራሲውን ግብረ መልስና በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሃያስያን የቀረቡ ዲስኩሮችን አንብቤ’ለሁ፡፡ ከዚህም ሁለት መሰራተዊ ትዝብቶችን አስተዋልኩ፤ ስሜታዊነትና የሂስ አሰጣት እጥረት ግንዛቤ፡፡ ሁለቱን በቅድሚያ ላስረዳ፤ በእውቀቱ በመግቢያው ላይ የሱ ዲስኩር በግላዊ እይታው ላይ የቆመ እንደሆነ ቢገልፅም ለምን እና እንዴት የቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ፍሬ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የክብርና የታሪክ መታወቂያ ስም ገፈፋቸው፣ ለምን ንጉስ ቴዎድሮስን ዝቅ አድርጎ ተመለከተ፣ ለምንስ የቤተ-ክህነት ቄሶችን ስብዕና አቀጭጮ አቀረበ ወዘተ በሚል ስሜት ውስጥ ታቅፈው የተፃፉት ሂሳ-ሂሶች አልተመቹኝም፤ አንድም የቃላት ምርጫ እጅጉን የግል ዕይታ ውጤት ስለሆኑ፤ አንድም ከደራሲው የቃላት ምርጫ ባሻገር መታየት ያሉባቸው ጉዳዮች ስለአሉ፡፡ በተለይም በቡዳው ደራሲ ለዶ/ር ፍቅርተ የተሰጠው ‹‹የእሳት ጎርሳ፣ የዕሳት ለብሳ›› ምላሽ ምሁራዊውን ውይይት ያቀጨጨ ነው፡፡ ሌሎችን ግን መጽሃፉን ከበው መወያየትን ቀጥለዋል፡፡
እጅጉን የከበደው ትዝብት፤ በሃያስያን ዲስኩሮች የዘነጉት የደራሲውን እይታና የመጽሃፉን ጭብጥ፣ አላማና የአላማ ጠቀሜታ በግልጽ ሳያቀርቡ ወደ አስተያየት የመዝለል ነገር ምን ያህል ያነበቡት መፅሃፍ ከዳር እስከ ዳር አንብበውታል፣ ምን ያህልስ ተረድተውታል የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ ባልቀረበበት ሁኔታ ለማየስ ሂሳዊ የሆነ ጥልቅ ንባብ ስለመከወናቸው ያጠራጥራል፡፡ በዚህ እረገድ መክሸፍን ተከትለው ከመጡት ሁነቶችና በተለይም በፕሮፌሰሩ ከቀረቡት የሂሳ-ሂሶች ጭውውት አስፈላጊውን ትምህርት መውሰድ ያለብን ይመስለኛል፡፡
ለራሴ ዲስኩር የመረጥኩትን ርዕስ አስረዳለሁ፤ በዕውቀቱ ቡዳው የምትለዋ ሃረግ የመጣችሁ በዕውቀቱ በፋክት መፅሄት ላይ ‹‹ወረቁ ፈረደ›› በሚል የብዕር ስም? ያወጣቸውን ፅሁፎች ምንም አይነት የአቀራረብና የጭብጥ ማሻሻል ሳያደርግባቸው በመፅሃፍ መልክ መውጣቱ የኢትዮጵያን አንባቢያን ያታለለበት መንግድ እጅጉን ስላበሳጨኝ ነው፡፡ ያሳዝናል! ለማንኛውም ትክክለኛው ወርቁ ፈረደ የምናውቀው ገጣሚ በዕውቀቱ ስለመሆኑስ ምን ማስረጃ አለን፡፡ በትንሹ ያልታመነ፣ በትልቁ ብጠረጥረው ምን አለበት፡፡ ወፌ ቆመች ጨቅላው ከእናቱ እቅፍ አፈትልኮ ከመዳህ ለመራመድ የሚያደርገውን ሙከራ የምናበረታታበት ደስ የሚል ሞራል ሰጪ ስሜት የሚገለፅበት ቋንቋ መሆኑ ይታወስ፤ ይህም ለመፅሃፉ የምሰጠውን የመድረክ ስፋት ይጠቁማል፤ የበረታ ሃሳብ የታቀፈ መፅሃፍ ነው፤ ከዚህ ቀጥሎ የመጣው ከአሜን ያልተሸገረ ሃተታ፣ ፅሁፉ ያቀረበው የግል እይታ አመክኖ ከመሃይማን ወግ ያልወጡ ተረኮችን የታቀፈና ተቀባይነቱን ጥያቄ ላይ የሚጥሉ ትንታኔዎች ከመልካሙ ጋር አብሮ መቆለፋቸውን ይጠቁማል፡፡ ስለዚህ በዲስኩሬ ሶስት ቁምነገሮችን አሉ፤ አንድም የሚያወድሱ አንድም የሚያኮስሱ አንድም ስሜትን የታቀፉ (ያው ከስሜት ውጭ መኖር/መፃፍ አይቻልም፤ ከባድ ነው!)፤ ውደሳ የብዙ ነገሮች ጨመቅ ውጤት ስለሆነ በደምሳሳው ቀርበዋል፤ ወቀሳ በነጠላ የመጡ ክስተቶች ውጤት ስለሆነ በንፅፅር ነጥቦችን በመጥቀስ/በማውጣት የተከወነ ነው፤ ስሜታዊ የሆንኩት በዋናነት ይህ ፅሁፍ መባሰናዳበት ግዜ የተረዳሁት የወረቁ ፈረደ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አካሄድ የተመከረ የመፅሃፍ ሂስ አሰጣጥ ነው፣ ለስራው ይመጠናል፤ ደራሲውም የሄደበት መንገድ ስለሆነ ይመቸዋል የሚል ግንዛቤ አለኝ፡፡
አላማዬ ምሁራዊ ውይይቱን ባስቀጠለ መንገድ የበዕውቀቱ ዲስኩር ለእኔና በእኔ እይታ አመክኖ የሚዛነፍባቸውን ጉዳዮች ማውሳት ሲሆን በግብ ደረጃ በመፅሃፉ ዙሪያ የሚከወኑትን ውይይቶች አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ ይሆናል፡፡ የምከተለውም ሥነ-ዘዴ የበዕውቀቱን ሃሳብ በበዕወቀቱ ሃሳብ ማነፃፀርና የበዕወቀቱን ሃሳቦች በሌሎች የሃገራችን ፀኃፊያን መፈተን ነው፡፡
አገራችን እንደ አገር የመቆየት ከባድ ‹‹አደጋ›› ላይ እንዳለች መገንዘብ አለብን፤ የአንድ አገር ህዝቦች ታሪካቸው ላይ መስማማት ካልቻሉ ወይም የአገር ታሪክ በተለያዩ የሚጣረሱ መነጽሮች የሚተነተን ከሆነ እና ይህ ትንታኔ በህዝቡ ውስጥ ገብቶ ተቃባይነት ካለው ያ አገር መቀጠሉ ያጠራጥረኛል፡፡ ከቀጠለም ቀን የሚጠብቅ ነው የሚሆን ነው፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የህዝብ መንግስት መፍጠር አልተቻለም፤ በአገዛዞች ሲረገጥ የኖሮ ህዝብ በአገሩ የአገዛዝ ታሪክ ላይ ሊስማማ አይቻለውም፤ ዋናው ቁም ነገሩ የህዝብ ታሪክ ላይ መቆም መቻል ነው፡፡ የመጣንበት ዜጋ በመሆን ፈተና የወደቅንባቸው በቅርፅና በብዛት የተለያዩ የታሪክ፣ የፖለቲካና የሳይንስ ድምርምር ውጤት በእጅጉ እየተጫነን ነው፡፡ ይህ አገራዊ ፈታና የሚታለፈው በዜጋ ጥረት መሆኑ ይታወቃል፤ ጥረቱም እውነቱን የማውጣት ውጤት ሲሆን፤ በዕውቀቱም ይህ በአገር የመጣ ፈተና የታየው ዜጋ ነው፤ መፍትሄ ለማቅረብ የግሉን ጥረት ለህዝብ በማቅረቡ ምስጋና ያንሰዋል፡፡ ይህን የምለው የበዕውቀቱ ሃሳብ በቀጥታ እሱ በቅሎ ለጎለበት የዘመናችን የፖለቲካ ጉንፋን ውጤት ቢሆንም ኢህአዴግን በደፈናው ከሚተቹ መሰል መጽሃፍት በተሸጋገር መልኩ ውይይትን ወደ ሚጋብዝ የምሁራንን ስራዎች ይሁነኝ በማለት በመተኮር ታሪክን ቆፍሮ ሃሳቡን ለማስተላለፍ ሞክሮአል፡፡
በዕውቀቱ በዘመናችን ፖለቲካ የዘመመውን ታሪክ በታሪክ ለማቅናት ያደረገው ከተለመደው አገዛዝ መር የታሪክ ትንታኔ በወጣ መልኩ አንድም በግለ-ትርጓሜ፣ አንድም በማህበረሰብ ፈለቅ እሳቤዎች፣ አንድም ገጠመኞች በወለዱት ሃሳብ እሳቤውን አንሻራሽሯል፡፡ ምንም ነገር በራሱ ተጨባጭ አይደለም፤ ድንጋይን ድንጋይ የሚያደርገው ድንጋይ መባሉ ነው፤ እናም የግል አስተያየት የተጨባጭነት መሰረት በሆነብት ሁኔታ የደራሲው ጥረት የከበረ ቦታን ያሰጠዋል፡፡ ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳሳ የሚያደረጉ አኩይ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለማክሰም ያለመ ድርሰት ነው፡፡ በተለይም፣ የምንሊክን ታሪክ አጣሞ በማቅረብ ለሚበሩት ግሪሳዎች ማህበረሰባዊ ማረፊያ ለመንሳት ይረዳ ይሆናል፡፡ ሰው ሆነው ሳለ በብሄር መር የጋሪ ፈረስ አይኖች ታሪክን ለሚያቀርቡቱ ጥሩ መነፅር ነበር፤ ባይሰበር!
በብስክሌት ጎማ ቅርጽ ውስጥ የጥቁሩን ሰው ምስል ባጎፈረ አንበሳ አሳጅቦ አቀረበ፤ ይህም ባለአንድ ጎማ ብስክሌት የለምና ለአገራችን ሚዛን የጠበቀ ጉዞ በዘመናዊ መንገድ አስፈላጊውን ሃይል በመጠቀም ያዋቀሯትን ንጉስ ምኒልክ መቀበል አለብን ለማለት ነው፡፡ የመፅሃፉ የመጨረሻ ገጾች ይህን ታለሚ ያደረጉ ቢሆኑም ቅሉ አዲስ ግን አይደሉም፤ ከላይ እንደጠቆምኩት ፅሁፎቹ ወርቁ ፈረደ በተባለ ሰው በፋክት መፅሄት ወተዋል፡፡ ይህ ህቡዕ ሰው ነው እንግዲህ ‹‹ምኒልክ እና አርሲ›› (ፋክት ቅፅ 2 ቁ 47 ግንቦት 2006 ዓ.ም) ‹‹የፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ነገር!›› (ቅፅ 2 ቁ 58 ነሐሴ 2006) (ሌሎቹንም ማየት ይቻላል) እያለ ያወጣቸውን/ የወጡትን ጽሁፎች ምንም አይነት ጥቆማ ሳይሰጠን ኢ-ምሁራዊ ብልጠት በተሞላበት አታላይ አቀራረብ የበላን፤ ይህ ሰው የራሱን አያውቅም ቡዳ ነው፡፡ ምን አይነት ድፍረት እንደደፈረ፤ እንዴት ቢያንስ በቃለ መጠይቆቹ፣ በመፅሃፉ ምርቃት ወይም ቀጥለው በመጡ ውይይቶች አይነግረንም፡፡ እራሱን የሰረቀ ብቸኛው ሌባ ነው፡፡ አዝናለሁ ምንም አይነት ማመዛዘን ይህን ከማለት ሊያግደኝ አልቻለም፡፡ በዕውቀቱ ልደቱ! ወፌ ቆመች ስል ወደቀች!
በዕርግጥ በእኔ አረዳድ የትኛውም የኢትዮጵያ መሪ ወይም አስተዳደር የአሁኑን ወያኔ ጨምሮ ማለቴ ነው ዜጋን በዜጋነቱ የሚያስከብር ስርዓት ነበር ለማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም ዜጋውን ወደ ስልጣን ለሚያደርጉት ጉዞ ይጠቀሙበትና፤ ቀጥለው ይንቁታል፡፡ ዜጋ መናቅ ማለት ሃሳብ መናቅ ማለት ነው፤ ከትዕቢታቸው ብዛት ከዜጋ ያለፈ ህዝብ ሲነግራቸው አይሰሙም፡፡ የሆነው ሆኖ ተወቃሾቹ አጋዛዞቹ ብቻ ሳይሆኑ በእኩሉ በዛ ስርዓት ስር የሚኖረው ማህበረሰብ ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ማህበረሰቡም በራሱ ዜጋ አያከብርም፡፡ ለዜጋ ቦታ የለውም፤ ለዜጋ ሃሳብ ቦታ የለውም፡፡ ዜጋውን የሰብአዊነት ቦታ ነፍጎ ያሳብደዋል አንጂ፡፡ በዕውቀቱ እራሱ ለዚህ ትሩ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በሽታ እስካልተላቀቅን ድረስ መቼም በዲሞክራሲ ተከባብረን መኖር አንችልም፡፡ ሰውን ሰው ያደረገው ሃሳብ ነው፤ የበዕውቀቱ ይባስ የእራሱን ሃሳብ አያከብረም፤ ወዳጆቼ፡፡
ኃይለ ሥላሴ አንቱ የተባሉ አርበኞችን በአደባባይ አዋርደዋል፣ ገለዋል፤ ደርግ አበቦችን በበቀሉበት ሜዳ አርዷል፤ ወያኔ የሚያብቡ ምሁራንን ከአገራቸው በመንቀልና እንደ ግንድ የጠነከሩትን ወራጅና ምሰሶዎች ቋሚና ማገሮች እንዲሁም ፍልጥና ሳጋዎች እየረገጠ ነው፡፡ ትልቁን ምሳሌ እጠራለሁ፤ መረራ ጉዲናን እና ዳኛቸው አሰፋን (ጋዜጠኞቹን ሳንዘነጋ) በኢፍታዊነት አዋርዶአል፡፡ በግል፣ በአንድ አርብ ከጓደኟቼ ጋር ካለንበት ደብረ ብርሃን አዲስ አበባ ተገኝተን አይዞን ብለናቸዋል፤ ምን አሉን እነሱ? ማንም እንዲህ አላበረታንም አሉን፤ አባቶች ብለናቸዋል፤ ንጹህ አይኖችን ከመልካም ከንፈሮች ጋር አጣጥመናል፤ ዳኛቸው፣ ‹‹ከጎርፉ ተጠንቀቁ ለአገር እንድትበቁ›› ሲልን፤ መረራ፣ ‹‹ሚዛን ጠብቁ ሰው ሳይበላ አይኖርም ግን ይመጥናልና እናንተም መጥኑ›› በሎናል፡፡
ትግሉ የከበደው ሰው/ዜጋ ጠፍቶ ሳይሆን ማህበረሰብ እንደ ዜጋ ማሰብ ስላልቻለ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን በዕውቀቱ ጎንደር ሄዶ ጨጨሆ የሚወደውን ቅኔ የአዝማሪ ቅላጼ ከቢራ ጋር ላወራርድ ቢል አንድ ጎረምሳ ጭንቅላቱን በዳሽን ጠርሙስ ያጫውትለታል፤ ይህ ጎረምሳ የመንግስትና የማህበረሰብ ውጤት ነው፡፡ የጎረምሳው ምክንያት፣ በዕውቀቱ መይሳው ካሳን ማንጓጠጡና ምስኪኑን መስፍን በመናቁ ነው፤ በዕውቀቱ ደግሞ አላማው አገር ሊገነባ ነበር፤ መይሳውና በዕውቀቱ በግብ አንድ ናቸው፤ በማህበረሰብ ተቀባይነት ደረጃም ሁለቱም ከቤተ-ክህነት የተኳረፉ ሆነዋል፤ ታሪክ ቅን ፈረጃ ነው፤ ዛሬ መይሳው ሃውልቱን ፒያሳ መሃል ምንም እጅ ሳያጠፋ በማህበረሰቡ ተከብሮ እሱም ማህበረሰቡን አክብሮ ከመሃል ጎንደር ሃገር ይጠብቃል፤ የመይሳው አባይን አሻግሮ ሸዋ የምገኘውን እኔ በግርማ ሞገስ ያየኛል፤ እኔም በዐጸደ ነፍስ የሚገኘውን ንጉስ ስታዘዝ፤ በአጸደ ስጋው በግፍ የጨቀየውን ወያኔ አየሸፍትኩ ነው፡፡ ቴዲ ሲያየኝ እየዳኘኝ አለሁ፡፡
በዕውቀቱ ግን ይህን ስፋራ አያገኛትም! አሜሪካ ሆኖ ከጥርሙስ ቢያመልጥም ያታለለውን ህዝብ ይቅርታ ካልጠየቀ አያመልጥም፡፡
በዕውቀቱ ማጅራት መታኝ፤ መሃል ፒያሳ ከ40 በላይ መፅሃፉን ደርድሮ የሚሸጠውን ሰው ‹‹የበዕወቀቱን መፅሃፍ ስጠኝ›› ብለው፤ 90 ብር ይለኛል፤ ‹‹እንዴት አሁን በአሁን ከ70 ወደ 90›› እለዋለሁ፤ ‹‹እኔም እንደዛው ነው የገዛሁት››፤ ‹‹የመንግስት ቅጂ›› ብዬ ሳልገዛ ሄድኩ፤ ከጓደኛ ተውሼ ላንብ ብሞክር የወረደ ነው፤ በተለይ በአመክኖ አቀራረቡ፤ ሁለት የንጉስ ልጆችን ዳኝቶ አንዱን ሰማይ አወጣ፤ የአንዱን አይን አወጣ፤ የተመሰጌን ደሳለኝን ዕጮኛ ‹‹ጠርተህ አለምህን ቅጭ አልኩት›› ብሎን ስለኢትዮጵያ ሴቶች ጀግንነተ ተረከ፤ አንዷን እቃ ሌሎቹን አለቃ አደረገ፤ ይሁና፤ የዘመኔን የሰላም ታጋይ አርኛዬን ተመስጌን ደሳለኝን የዕርስ በዕርስ ጦርነት ቀስቃሽ ነው አለኝ፤ ይሁና፤ ይህንኑ ዲስኩር በልደቱ አንበብኩት ብሎኝ በኢነተርኔት ለቀቀ፤ አሳመመኝ፤ አንዴ ገደለው፤ የሞተውን ሰው ደግሞ ገደለው፤ ይሄስ አይሁን፤ ለተሜ እኔ እሞታለሁ! ተመስጌን ደሳለኝ ወንጀለኛ አይደለም፤ ወያኔ በግፍ አስሮ የሚጫወትበት የዘመኔ ታላቁ ዜጋ ነው! ተራ በተራ አስረዳሉ፤
በዕወቀቱ፤ ‹‹ወዝውዘው ወዝውዘው ጣሉት እንደ ዝሆን፤ ያው ወደቀላቸው ይበሉት እንደሆን›› በሚል መወድስ ጀመረና፤ ‹‹ ተሜ እኒያን በአብዮት ብሥራት የሰከሩ መጣጥፎችን በሚያሽጎደጉድበት ወቅት ይትብብር መንፈስ ከመቼውም በላ የተዳከመበት፤ ሁሉም ሰፈሩን ነጻ ለማውጣት የሚታገልበት ግዜ ነበር፡፡… ተሜ እንደገመተው ሆኖ አብዮት ደጃችን ላይ እያንኳኳ ሊበጀን ይሁን ሊፈጀን ማወቅ የሚቻል አይመስለኝም፡፡›› ቀጠለና ሃዲስ አለማየሁን ሲጠቅስ ‹‹ለውጥ በሰላም ለውጥ በደም›› ፤ እንግዲህ የተመስጌን በደም መሆኑ ነው፤ ምክንያቱም ‹‹መጣጥፎቹን አሜን ብዬ ተቀብያቸው እንደማለቅ መደበቅ አልሻም›› ይላል ገና ሲጀምር ጽኁፉን ያተነበት ፡፡
ይህ እንግዲህ በተመጌን ላይ የቀረበው ክስ ትክክል ነው ማለት ይሆናል፡፡ በዕውቀቱ ሳተ! የተሜ ሃሳብ ምክንያት ላይ የቆመ እና ሰላማዊ ለውጥን ለአገራችን የወጠነ ነው፡፡ ጠመንጃ አናነሳም ሲል ያቀረበው ሃተታ ብቻ ይበቃሃል፤ ተሜ ሌላው ሁሉ ቀርቶ በጦር የሚመጡ ለውጦች ሌላ ወያኔ ፈጣሪ ናቸው ባይ ነው፡፡ ተመስጌን ሰላማችን ነው!
ተመስጌን ዳሳለኝ፤ ፋክት ቅጽ 2 ቁ 59 ነሃሴ 2006 ገፅ 34
ይሁንና የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እና ነፃ የአደባባይ ክርክርን ባልተላመደ ማህበረሰብን አሁንም ለትጥቅ ትግል መጥራት ይህንኑ አሉታዊ ህዝባዊ ባህሪ ከማጠናከር የዘለለ አንዳች ፋይዳ እንደ ሌለው ለመሟገት የሚያስችሉ በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡… ይህ ሰላማዊ የመጫረሻ ሙከራ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ዳግም ነፍጥ እንዳይነሳ….በብረት የሚመጣ ለውጥ ተመልሶ ማህበራዊ ፍዘት ውስጥ እነደሚጥለን መረዳታችን መጪውን የአብዮት አማራጭ ….
ሌላው የቴዎድሮስ ነገር ተዛብቶበታል፤ በዕውቀቱ ከዚህ በፊት ከአለማየሁ ገላጋይ ጋር በንጉስ ቴዎድሮስ ጭካኔ ተከራክረው ነበር፤ ያን ክርክር ተመልሰን ማየት አለብን! ያ እንዳለ ሆኖ፣ በዕውቀቱ ንጉስ ቴዎድሮስ ‹‹መኝታ ቤት ግድግዳ ላይ ተለጥፈው የባልና ሚስቱን የግብረ ስጋ ግንኙነት ጭውውጥ ሲሰሙ ከቆዩ በኋላ ሚስት ስትረታ ሰምተው ሄዱ፡፡ ዝም ብለው ግን አልሄዱም፡፡ ያው ‹‹ዕየሳቁ ሄዱ›› በገፅ 133 ላይ፡፡ ይቀጥልና፣ በገፅ 137 ይህን የመንግስት የግለሰብ ገበናን በኢ-ሰባዊ መንገድ መድፈር ያዋሳበትን ጭብጥ ሲዛጋ፤ ‹‹በጎረቤት ግድግዳ ላይ ሽንቁር በስቶ ግብረ ስጋን መሰላል ግን ከወራዳነት ውጭ ምን ስም ሊሰጠው ይችላል በሚል አሳፈሪ ቃላት ይዘጋል፡፡
ይታይህ፤ ቴድሮስም አለበት እዝህ ‹‹ወራዳነት›› ውስጥ፡፡ ጥያቄዬ ሁለት ነው፤ አንድም የመረጃው እርቀት እውነታውን ማረጋገጥ ያከብዳል፤ ሁለትም ንጉስን በዚህ ደራጃ ዝቅ የሚደረጉ ናቸው ወይ፤ የዘመኑን መንፈስ አስቡት፤ ውሃም አያነሳ፡፡
በግሌ ንጉስ ዲሞክራሲያዊ ወይም ሰብዓዊ ናቸው ለማለት አልችልም፤ አንኳን በዛን ዘመን አሁን በወያኔ ዘመን እንኳ ኢ-ሰባዊነት ድንኳኑን በዜጎች ላይ ጥሏልና፤ ንጉሱ ግን በብዙ መንገድ ቡዳው የሰጣቸው ስያሜ አይመጥናቸውም፤ አንድም እጅጉን ለህዝባቸው ጥበብና ትምህርት የሻቱ ናቸው፤ ጥያቄያቸውን ማንም ዳግም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አልደገመውም፤ ሁለትም፤ የኢትዮጵያን ዳግም አንድ የማድረግ ህልም ያለሙና በደንብ የቻሉ ነው፤ ንጉስ ዮሃንስ ና ምንሊክ የቴዎድሮስ ወራሾች ናቸው፤ በአንድነት እረገድ፤ እንደውም ኢትዮጵያዊው ቢስማርክ ምንሊክ ሊሆን አይችልም፤ መክንያቱም ሃሳቡ የንጉስ ቴዎድሮስ ስለሆነ፤ ሶስትም በእውቀቱ የሚውደውን የንባብ ባህል ለመፍጠር ማለትም በዛን ዘመን መፅሃፍትን ያሳባሰቡ ብቸኛው ንጉስ ናቸው፤ አራትም ቴዎድሮስ የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ክብር ልዕልና የሰጠ ብቸኛው ንጉስ ነው፤ ስንቱ የሃገሬ ወታደር በቴዎድሮስ መንፈስ እራሱን በራሱ ጥይት መታ፡፡ ታዲያ በዕውቀቱ ፤፤፤፤፤፤ ይሁና!
አባቱን ገደለ፤ ልጁን ተበቀለ፡፡ በገፅ 50 እንዲህ ሲል ፃፈ፤
‹‹ባወጣ ባወርድ፤ የአለማየሁ ቴዎድሮሰን መቃብር የምጎበኝበት ምክንያት አልታይህ አለኝ፡፡ አለማየሁ ባጋጣሚ የንጉስ ልጅ ከመሆኑ ውጭ ለምርመራ ወይም ለጉብኘት የሚጋብዝ ምንም ብርቅ ነገር አጣሁበት፡፡›› ይግል እይታው ነው፤ መብቱ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ያለን ሰው በምን አእመክኖ ነው በእውቀቱ ስለ ጎበና እና ስለ ሸዋረገድ ምኒልክ ልጅ ስለሆነውና በአስራ አራት አመቱ ስላረፈው ወሰን ሰገድ ጎበና ሊያወራ የሚችለው፡፡ ምን ሰራ ወሰን ሰገድ በፎቶ ታጅቦ የቀረበው፡፡ በስራ ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ ቢያንስ መስፍኑ በአባቱ ጋዳዮች ስር ሲማቅቅ፣ሞ ሲናፍቅ፣ ሲሳቀቅ ነበር፤ ቢያንስ በበሽታ አልሞተም፤ በሃዘን፣ በናፍቆት፣ በብሶት ብዛት ነው፤ ምን አረገህ፤ አይነፋም፡፡
ምንም ብርቅ ነገር አጣሁበት ነው ያልከው አይደል፤ በጦብያ 7ኛ አመት ቁ 2 ሐምሌ 1992 በፍቃዱ ሃብቴ ከለንደን ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስነበበው ‹‹ባይተዋሩ መስፍን›› በተሰኘ ሃተታ ውስጥ ለመስፍኑ ቅርብ የነበረችውን የንግስት ዚክቶሪያን የመቃበር ላይ ፅኁፍ ነው የቀረበህ፤ ፅኁፉ ብርቅ ድንቅ ነው፤ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ባይተዋር እንደነበር ባይተዋር ሆኖ ሞተ፡፡ መስፍኑ አለማየሁ ቴዎድሮስ፤ የንጉስ ቴዎድሮስ ልጅ››፡፡ … ንግስቷ ተቀጥል ‹‹ የዓለማየሁን መሞት ዛሬ ጠዋት ሰማሁ፡፡ ጥልቅ ሃዘን ተሰማኝ፡፡ ባይተዋር እንደ ነበር ባይተዋር እነደሆነ ሞተ፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ ደስተኛ ልጅ አልነበረም፡፡ በወጣጥነቱ ካሳደጉት ዘመዶቹና ወገኖቹ እርቆ መኖር ለወጣት አለማየሁ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ … ወጣቱ አለማየሁ ቆንጅዬና ተናፋቂ ወጣት እንደ ነበር ቆንጅዬና ተናፋቂ ወጣት ሆኖ ሞተ፡፡›› ገፅ 21፡፡
ይሁና!
በዕውቀቱ ኢ-አማኒ መሆን የዕውቀት መገለጫ ያደርገዋል እየፈራ ሳያምነበት፤ ለምሳሌ በዕውቀቱ በቆንጨራ እመን ሳይሉት ያምናል፤ አይሎፕራን ሲነሳ፤ ግን ግን የዕጓለ ገብረ ዮሐንስን ያነበበ እውቀት ማለት በልጦ መሄድ እንጂ ፍሮይድን መገልበጥ እንዳልሆነ ይናራሉ፤ ለምሳሌ ፈላስፋው ዘዕረ ያዕቆ ኢትየጲያዊ ነው፤ ግን የሃሳብ ልዕልና በተላበሰ አመክኖ በማንኛውም እምነት ተከታይ አልነበረም፤ ለኛ የማያምን ሰው ብርቃችን አይደለም ማለቴ ነው፤ (እዚህ ጋር የፍሮይድን መፅኃፍ ያየው ሰውን አመሰግነዋለሁ)፡፡
ነጋድራስ ገብረ ሂዎት የተባሉትን የዘመናቸው አስተዋይ ቁንጮ የዕወቀት አባት (ገፅ 219)‹‹ኦሮሞን አሳንሶ›› ፃፈ ይላል፡፡ ይሁና! ሰውየው ‹‹ዕውቀት አላምን ይገዛ ዘንድ የማይናወፅ ህግ ነው!›› ያሉ፤ የተማሩ፣ ተመራመሩ ነበሩ፡፡ እኝህን ጎበዝ እንደዛ ለቃላት ምርጫ ተቸ፡፡ በእውነት ለእኔ ይህ ጠቀሳ ሃጢያት ነው የሚሆንብኝ፡፡
ድግሞ በጣም የበዛ ፍርሃትህ ከየት የመጣ ነው፡፡ ከሌብነቱ መሆን አለበት፡፡ እንዴት ሰው መታሰርን እንደዛ ይፈራል፤ እንዴት ነው ኢ-አማኒ በአውሮፕላን መሄድ የሚያስፈራው፤ እነዴት ነው እነዛን የመሰሉ ሰንገበገብላቸው የነበሩ ፅሁፎች ወረቁ ፈረደ በሚል ያወጣሃቸው፤ የሚገርምህ ሁሌ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ‹‹ማነ ነው እንላለን፡፡ አንተ ነህ ለካስ፤ አንደውም አንዴ ስንወያይ ወረቁ ፈረደ የሚባል የያ-ትውልድ የአልጂሪያ ክንፍ የሆነ ሰው ስም አንብበን እሱ ነው እስከማለት ደረሰን ነበር፤ ጀግናችን የታሰረው አንድም በአንተ ፅሁፍ ሃይለኝነትም ጭምር ነው፤ ቢገባህ፤ የታሰረው እሱ ስለፃፈቸው ኃሻቦች ብቻ አይደለም፤ ተመስጌን እጅጉን አምነው በወጡ ፅኁፎች ጭምር እንጂ!
ሳበቃ፤ ‹‹ከአሜን ባሻገር›› አንድ ቁም ነገር አለ፤ ናስተማሰለኪ ነው፡፡ ቀጥሎ የአመናችንን ነባረዊ ሁኔታ ማለት የቢራ ቤቶቹ ብዛትና የነገረ ወሲብ መስፋት በዕውነት ወዴት እይሄድን ነው ከማስባል አለፎ እንስሳ ሆንን ነን እንዴ ያስብላል፡፡ በዕወቀቱም የገለፀበጽ መንገድ ሐቅ አለው፡፡ እንዲህ ሲል ነው ማህበራዊውን ጉዳዩ ገልብጦ የመንግስት አስተዳደር ውጤጥ መሆኑን የፈረደው፡፡ ‹‹… የዜጎች ፀባይ ከአገዛዝ ስርዓት ጋር በትብቅ የተቆረኘ ነው፡፡ የፖለቲካ ጭቆና በበረታበት ሃገር ውስጥ፣ ወሲባዊ ልቅነት የመጨረሻው የነፃነጽ አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አመንዝራነት፣ ዜጎች ሌላው ቢቀር ብልታቸው በመንግስት ቁጥጥር ስር አለመሆኑን የሚያሳዩበት መንገድ ነው፡፡ ›› ገፅ 21፤ ይህ ብቻም አይደለም ጉዳዩ፣ ድህነቱ ወጣቱን ትዳር መስርቶ ከስጋት ውጭ እንድይኖር እድርጎታል፡፡ ሌለው፣ በስርዐቱ ውስጥ የተሰገሰጉት አዳሪዎች ዋንኛ ሴሰኛ መሆናቸው ይታወቃል! ደፈር በል! አንድም ሃገር ያረክሳሉ፤ አንድም እናት ሃገር ያረክሳሉ፡፡
በተራ ወሬ፤ በተራ ኢ-ምሁራዊ መነገድ፤ በኮንትሮባን ንግድ ከአሜሪካ ኢትዮጵያ የዘረፈው ብቸኛው ሰው ነው፤ በዕውቀቱ፡፡ መፅሃፉ ልንባብም ሆነ ለኢትዮጵያ አይመጥንም፡፡ በዶ ወረቀት ፅፎ ኢንጂነር እና ዶክቶቻችንን ሰራ አስፈታብን፤ በበኩሌ ካሳ እሻለሁ፡፡ አይቀርም፤ በፍትህ ዘመን ከሚጠየቁት አንዱ ነህ!
አሁን መወያየት ይቻላል!