የቃሊቲ ዉሎ ከነእስክንድር ነጋ ጋር – በበትረ ያዕቆብ

ሐምሌ 3 ቀን 2005
ትናንት በማለዳ ነበር ተነስቼ ከሰሚት ወደ ሳሪስ ያቀናሁት፡፡ የሐምሌን ቀዝቃዛ የጠዋት አየር እየተመገብኩ ከጓደኞቼ ጋር ከተቀጣጠርኩበት ሐበሻ ካፌ ስደርስ ሰዓቴ ከጥዋቱ 1፡30 (7፡30 AM) ይል ነበር፡፡ ሁላችንም ከየአቅጣጫዉ በዚያች አነስተኛ ካፌ ከተሰባሰብን በኋላ ቁርስ ቢጤ እንደ ነገሩቀማምሰን የዕለቱን ዕቅዳችንን ለመፈፀም ተነሳን—በልባችን ስኬትን እየተመኘን፡፡ እናም ፍራፍሬ በየአይነቱ ሸማመትን ፤ ያስፈልጋሉ ያልናቸዉን ነገሮች ሁሉ አሟልተን ጉዞአችንን ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት (በርግጥ ማረሚያ ቤት የሚለዉ ቃል ፍፁም አይገባዉም) አደረግን ፤ ለኛ ሲሉ እራሳቸዉንአሳልፈዉ የሰጡ የጭንቅ ጊዜ ልጆች ማለትም አንዱአለም አራጌን ፣ እስክንድር ነጋን እና ርዕዮት አለሙን እንዲሁም ሌሎችን ለመጎብኘትና አይዞአችሁ ሁሌም ከጎናችሁ ነን ልንል፡፡

ይሁን እንጅ እዚያ ደርሶ እነዚያን ጀግኖቻችንን አይዟችሁ ማለት ዉጣ ዉረድ ነበረዉ፡፡ ምንም እንኳን ሁላችንም ከነርሱ ፊት ለመቆም በጣም ብንጓጓም ብዙ መሰናክሎችን ማለፍ ነበረብን፡፡

የመጀመሪያዉ ፈተና ያዉ የአዲስ አበባችን መታወቂያ ለመሆን የበቃዉ የትራንስፖርት ችግር ነበር፡፡ በጠዋት በስራ ቦታዉ በሰዓቱ ለመገኘት ከቤቱ በነቂስ የወጣዉን ህዝብ አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉት ታክሲወችና የአንበሳ አዉቶብሶች ሊያቃልሉት ስላልቻሉ አካባቢዉ በሰዉ ተጥለቅልቋል ፤ ሁሉም ከወዲያወዲህ ይሯሯጣል ፤ ይታመሳል፡፡ በዚያ ላይ ጭቃዉ፡፡ የሆነ ሆኖ ትንሽ ከተሯሯጥን በኋላ የመንገዱን አንድ ጠርዝ በመያዝ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ እንደጉንዳል መንጋ የተዘረጋዉን የሰዉ ሰልፍ ተቀላቅለን እድላችንን መጠበቅ ተያያዝን፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ለረጅም ሰዓት የታክሲ ያለህ ስንልቆይተን አይደርሱ የለምና በመጨረሻ አንዲት ታክሲ አግኝተን ወደ ጀግኖች መንደር ጉዞ ተጀመረ፡፡ ያም ሆኖ በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት በየመንገዱ እየቆምን ቃሊቲ ለመድረስ ብዙ ጊዜ ወሰደብን፡፡ ሆኖም ምንም አስቸጋሪ ይሁን ምንም ጊዜ ይፍጅ እዚያ መድረሳችን በራሱ ትልቅ ነገር ነበርና ሁላችንምበደስታ እየተሳሳቅን ወደ ማረሚያ ቤቱ አቀናን፡፡

አንዱአለም አራጌ ከሚገኝበት የዞን 2 በራፍ ላይ ስንደርስ ሁለት ወጣት የፖሊስ አባላት ተቀበሉን፡፡ ሁለቱም በእጃቸዉ የያዙትን ደብተር እየገለጡ ማን ናችሁ ፣ ወደየት ናችሁ…? ሲሉ አንድ ባንድ እየጠየቁ የሚፈልጉትን መረጃ ከመዘገቡ በኋላ መታወቂያችንን አይተዉ ወደ ዉስጥ እንድንገባ ፈቀዱልን፡፡ትንሽ አለፍ ከማለታችንም በአንዲት ትንሽ ቤት ዉስጥ ለሚገኙ የፖሊስ አባላት ሞባይል ፣ ቁልፎቻችንን ፣ ዋሌታችንን ፣ ባጠቃላይ ኪሳችን ዉስጥ የተገኘን ነገር ሁሉ እስክብሪቶና ወረቀት ሳይቀር አስረክበን ወደ ዉስጥ አለፍን፡፡ አዚህ ላይ እኔን በጣም የገረመኝ የስክብሪቶዉና የወረቀቱ ጉዳይ ነበር፡፡ አሁንእስቲ ምን ይሉታል ወረቀት መቀማት ፤ የጦር መሳሪያ መሆኑ ነዉ ፣ እንደሚመስለኝ ሰዉ እዚያ የሚፈፅሙትን ግፍ በተመለከተ መረጃ ይዞ እንዳይወጣ ለመከላከል ነዉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ሕዝቡ አሁንም የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ ዝግጁ ይሁን" ዶክተር ይልቃል ከፋለ

የሆነ ሆኖ ወደ ዉስጥ እየተገረምን ዘለቅን፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም እንድንቆም ተጠየቅን፡-ለፍተሻ፡፡ ከዚያማ ምን ልበላችሁ ከእጅ ጥፍራችን እስከ እግራችን ድረስ ተፈተሽን ሳይሆን ተበረበርን ፣ ተዳበስን፡፡ በቃ! ምንም የቀረ ነገር የለም ፤ እንትናችንም እንኳ ቢሆን ከዳበሳ አላመለጠም ፤ ያዉም ጠበቅ ካለዳበሳ፡፡ እኔማ ግራ ቢገባኝ ጠባቂዉን በጥንቃቄ ተመለከትኩት ፤ ምን ላድርግ አሁን አሁን በከተማችን የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት አልፎ አልፎ መስተዋል ጀምሯል እየተባለ አይደል፡፡ ይታያችሁ የለበስኩት ልብስ ቀላል የሚባል ነዉ ፤ ማለቴ ከላይ ቲሸርት ነገር ከታች ጅንስ ሱሪ ፤ ይህ አለባበስ ደግሞ የጦርመሳሪያ ሊደብቅ አያስችልም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ እንዲያ መዳበሱ ፤ የሰዉን ጭን ማፍተልተሉ ለምን አስፈለገ!!!!!!!

የሆነሆኖ ኋላ ላይ ነዉ የፍተሻዉ ዉስጠ ሚስጢር የገባኝ፡፡ ጓደኞቸ እንዳስረዱኝ መሰል ፍተሻ በይበልጥ የሚደረገዉ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን ለመጠየቅ በሚመጡ ሰዎች ላይ ብቻ ሲሆን ፤ ይህ የሚደረገዉም ሰዎች እንዲሸማቀቁና ዳግመኛ ለመጠየቅ እንዳይመጡ ታስቦ ነዉ፡፡ እዚህ ላይ አንድየሰማሁትን ታሪክ ጣል ላድርግ፡፡ ሰዉየዉ በሀገራችን በጣም የተማሩ ከሚባሉትና ከተከበሩት ምሁራን መካከል አንዱ ናቸዉ፡፡ እናም አንድ ቀን እኒህ ሰዉ የህሊና እስረኞችን ለመጎብኘት ወደ ማረሚያ ቤቱ ይመጣሉ፡፡ ከዚያም አንድ ወጣት ልፈትሽዎ ብሎ ጠጋ ይልና ያንን ዳበሳዉን ይጀምራል፡፡ሰዉየዉም ግራ በመጋባት ከአሁን አሁን ያቆማል ብለዉ ሲጠብቁ እንዲያዉም ይባስ ብሉ ከጭናቸዉ ከፍ በማለት እንትናቸዉን እንደለመደዉ ጨበጥ ያደርጋል፡፡ ይህኔ በልጁ ተግባር በጣም የተበሳጩት ሰዉ እየተሳደቡ ወደ መጡበት ተመለሱ፡፡

“እንዳያልፉት የለ ፤ ያ ሁሉ ታለፈ” ሲል አምባገነኑ ኢህአዴግ እንዳቀነቀነዉ ሁሉ እኛም ይህን ሁሉ ዉጣ ዉረድ አልፈን ዞን 2 አንዱአለም አራጌ ወደሚገኝበት ግቢ የሚያስገባዉን የቆርቆሮ የዉጭ በር ከፍተን ገባን፡፡ ከዚያም ከፊት ለፊታችን ሰዉ ወደ ዉስጥ አልፎ እንዳይገባ ታስቦ የተሰራን የእንጨትአጥር ተደግፈን ከጠባቂዎቹ አንዱን አንዱአለምን እንዲጠራልን ጠየቅን፡፡ እርሱም በፊቱ ላይ ምንም ትህትና ባይታይበትም ወደ እስረኞቹ መኖርያ የምታስገባን ሌላ ትንሽ የዉስጥ በር ከፍቶ ከአይናችን ተሰወረ፡፡ ከእርሱ በላይ በኩል በረጅም ማማ ላይ ክላሽንኮቭ የታጠቀ ጥቁር ልጅ እግር ወታደርአጠቃላይ እንቅስቃሴዉን ይከታተላል ፤ መሳሪያዉን ከፍ አድርጎ በመያዝ በተጠንቀቅ አንዴ ወደ እስረኞች ግቢ አንዴ ወደ እኛ በአንክሮ ይመለከታል፡፡ በዚህ መሀል አንድ ጥርሰ ፍንጭት በፊቱ ላይ የሀዘን ስሜት የሚነበብበት ግን ደስተኛ ለመምሰል የሚሞክር እስረኛ ትንሽቱን የዉስጥ በር ከፍቶ ብቅአለ፡፡ ከዚያም ስሜት አልባ ፈገግታ ፈገግ እያለ አንዱአለም እየመጣ መሆኑን በመጠቆም እራሱን በርቀት አስተዋዉቆ ተሰወረ፡፡ ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ያችዉ በር ዳግም ተከፍታ በናፍቆት የምንጠባበቀዉ ወጣት ፖለቲከኛ በቱታ ነጠላ ጫማ ተጫምቶ በፈገግታ ወደ እኛ ገሰገሰ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮ/ል መንግስቱ ስለማንዴላ ተናገሩ (አዲስ ቃለምልልስ)

እንግዲህ ምንም እንኳ ሁሉንም የህሊና እስረኞች በገጠመን ችግር ምክንየት ለመጎብኘት ባንችልም አንዱአለም አራጌንና እስክንድር ነጋን በእንዲህ ያለ ሁኔታ ለመጠየቅ ቻልን፡፡ እቅዳችን ከእስክንድር ነጋ በመቀጠል ርዕዮትን ከዛም ሌሎችንም ለማየት የነበር ቢሆንም በመጨረሻ ሰዓት ላይ ከእስክንድር ጋርየጀመርነዉን ሞቅ ያለ ዉይይት አቋርጠን ከማረሚያ ቤቱ እንድንወጣ ተደርገናል፡፡ ምንም እንኳን እዛዉ በመቆየት የመጣንበትን አላማ ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ብንጥርም አልተሳካልንም ፤ ከመዉጣት በቀር ምንም አማራጭ አልነበረንም፡፡ ያም ሆኖ ግን ከእስክንድር ነጋ እና ከአንዱአለም አራጌ ጋር በነበረንአጭር ቆይታ ብዙ መረጃ ተለዋዉጠናል ፤ በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ብዙ ብዙ ለመጨዋወት ችለናል፡፡ ሁለቱም ወጣት ምሁራን ፊታቸዉ በደስታ እያበራ በወንድማዊ ስሜት ያላቸዉን አስተያየትና ምክር ለግሰዉናል፡-በተለይም እየተቀጣጠለ ካለዉ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የወደፊትአቅጣጫ አመላክተዉናል፡፡ ከዚህ ባሻገር እስክንድር ነጋ “በቃ! ተበተኑ” የሚለዉን የማያቋርጥ የጠባቂዎች ቁጣ እና የነሱን ግልምጫ ተቋቁሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም ለዲያስፖራዉ መልክዕክት አስተላልፏል፡፡

በእስክንድር ነጋ እንዲሁም በአንዱአለም አራጌ ላይ በተወሰነ መጠን የመክሳት ነገር አስተዉያለሁ፡፡ ሆኖም ያ የሰላ አንደበታቸዉ ፣ ቁርጠኝነታቸዉ ፣ የመንፈስ ጥንካሬያቸዉ ከእነርሱ ጋር ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸዉ ጥልቅ ፍቅር ፣ ክብር እና ታማኝነት ጠንካራና የማይናወጥ መሆኑንተገንዝቤአለሁ፡፡ እዚህ ላይ እስክንድር የተናገረዉን እንደምሳሌ መጥቀስ በቂ ነዉ፡፡ “እኔ ንፁህ ነኝ፡፡ ለመንግስት መቼም ቢሆን ይቅርታ አልጠይቅም ፤ አመክሮ እንኳን ቢሆን አልሞክረዉም፡፡ ይህን ስል ሚስቴና ልጄ አይናፍቁኝም ማለት አይደለም ፤ እነርሱን የማጣት ህመም ሁሌም በልቤ ዉስጥይሰማኛል ፤ ሆኖም ይህ ለምወደዉ ወገኔ ስል የግድ ልከፍለዉ የሚገባ መስዋትነት ነዉ፡፡” ነበር ያለዉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አቶ ገዱ በምክር ቤቱ ያደረጉት የተቃውሞ ንግግር

በማረሚያ ቤቱ ቆይታዬ እንደተረዳሁት አሁንም አንዱአለም አራጌም ሆነ እስክንድር ነጋ በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የተለያዩ ተፅዕኖዎች ይደረጉባቸዉዋል፡፡ ይህም በርዕዮት እንዲሁም በሌሎች የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ላይ ተመሳሳይ ስለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ከእነዚህ ከሚደርሱባቸዉ ተፅዕኖዎችመካከል አንዱ መፅሀፍ እንዳያስገቡና እንዳያነቡ መከልከል ነዉ፡፡ ይህ ምናልባት በጣም ቀለል ተደርጎ ሊታይ ይችላል ፤ ሆኖም መታወቅ ያለበት ይህ በእንዲህ ከቀጠለ በእነዚህ የሀገራችን ፈርጦች ላይ የሚያስከትለዉ አዕምሮአዊ ጉዳት ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡

ከማረሚያ ቤቱ ስንወጣ የብዙዎቻችን ስሜት ደፍርሶ ነበር—በተለይም ከእስክንድር ነጋ ጋር የጀመርነዉ የጦፈ ዉይይት እንደዚያ በመሰናከሉ ፤ አንዳንዶቻችንም ላለማልቀስ እንታገል ነበር፡፡ እስክንድርም ቢሆን ተመሳሳይ ስሜት እንደተሰማዉ ማስተዋል ችያለዉ፡፡

Share