(ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር 86 ሚሊዮን 613 ሺህ 986 (43,715,971 ወንዶችና 42,898,015 ሴቶች) መድረሱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ ይህ የሕዝብ ብዛት በ2009 ዓ.ም 94 ነጥብ 4 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኤጀንሲው አስታውቆ የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር በ1999 ዓ.ም 73 ነጥብ8 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ ከስድስት ዓመት በኋላ በተደረገው ጥናት በ12ነጥብ 1ሚሊዮን እድገት መታየቱን አረጋግጫለሁ ብሏል።
በዚህ ጥናት መሠረት፦
– የኢትዮጵያ ሕዝብ 15 ነጥብ 9 ሚሊዮኑ በከተማ ይኖራል
– በ1999 ዓ.ም በከተማ ይኖር የነበረው ህዝብ ብዛት 11ነጥብ9 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ በ2005 ትንበያ መሠረት የህዝብ ቁጥሩ ወደ 15 ነጥብ 9ሚሊዮን እድገት አሳይቷል፡፡ ይህም ከ19ነጥብ1 በመቶ ወደ 18 ነጥብ7 በመቶ ማደጉን የትንበያው መረጃ ያመለክታል፡፡
– በ2005 በአጠቃላይ በሀገሪቱ 15ነጥብ 9ሚሊዮን ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ የፈለሱ መሆናቸውን ጥናቱ ያመለክታል፡ ይህም በ1999 ከነበረው የፍልሰት መጠን በ4ነጥብ 1ሚሊዮን እድገት እንዳለው ጥናቱ ያሳያል። በ2009ም የፍልሰቱ መጠን 19ነጥብ 1ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ተተንብዩዋል።
መንግስት ይህን ይበል እንጂ ታዛቢዎች ይህን አሃዝ አይቀበሉትም። በተለይም በ2005 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ ፈልሰዋል ያለው መንግስት የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛትን 3 ሚሊዮን 122ሺህ ብቻ አድርጎ ማስቀመጡና ከ1999ኙ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ውጤት ጋር ሲነጻጸር የ386 ሺህ ቁጥር ብቻ ብልጫ ማሳየቱ አነጋጋሪ ነው። የአዲስ አበባ ሕዝብም 3 ሚሊዮን 122ሺህ ብቻ ነው ማለት ቁጥሩን ሆን ብሎ ለማሳነስ የተደረገ ነው ተብሏል። ታዛቢዎች አሁንም የአማራውን ሕዝብ ቆጠራ ውጤት ቁጥሩን አንሷል አይቀበሉትም። ከዚህ ቀደም በ1999ኙ ምርጫም እንዲሁ ታዛቢዎች የአማራው ሕዝብ ቆጠራ አንሷል በሚል ላቀረቡት ትችት የመንግስት ባለስልጣናት “አማራው በበሽታ እንዳለቀ” አድርገው ማስቀመጣቸው የሕዝብ ቁጣን ቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።
ሰንጠረዡን ይመልከቱና የእናንተን አስተያየት እንካፈል
(የሰንጠረዡ ምንጭ፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ነው)