የቴዲ አፍሮ ምኞቶች

ከያሬድ ኃይለማርያም

ዘረኝነትና ጥላቻ በመንግሥት ደረጃ በሚሰበክበት አገር፣ ድንቁርና እጅግ በተጫናቸው የወያኔ ቱባ ባለሥልጣናት ሕዝብ በሚዘለፍበት፣ ታሪክ ተጣሞ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪን የሕብረተሰብ ክፍል በሌላው ላይ ለማነሳሳት ሌት ተቀን የሚደክሙና ጉርጓድ የሚምሱ ቡድኖችና ግለሰቦች ባሉበት አገር፣ ፍርሃትና ጥርጣሬ በነገሱበትና አፈና በበረታበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር እንደ ቴውድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ‹ ያሉ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በማሕበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ሚና በዘፈን ሕዝብን ከማዝናናት እጅግ ያለፈ ነው፡፡ የቴዲ ዘፈኖች ታሪክን ለሚክዱና ለሚያጣምሙ ማስተማሪያዎች ናቸው፡፡

በጥላቻ ጭንቅላታቸው ለናወዘና በጎጠኝነት በሽታ ለሚማቅቁም ፍቱን መድሃኒቶች ናቸው፡፡ የማንነት ቀውስ ለገጠማቸውም ጥሩ አስታዋሾች ናቸው፡፡ በፍርሃት ለሚማቅቁም ብርታት ናቸው፡፡ ከእውነት ለተጣሉም አስታራቂዎች ናቸው፡፡ በሥልጣን መባለግ ለሚናውዙም የማስጠንቀቂያ ደውሎች ናቸው፡፡ በፖለቲካ ቁርሾ ደም ለተቃቡም ፈዋሾች ናቸው፡፡ በፍቅር ለናወዙም የሃሳብ ሰረገሎች ናቸው፡፡ ቴዲ በዘፈኖቹ አገራዊና ግላዊ ሕይወታችንን የሚመለከቱ በርካታ ጉዳዮችን ዳሷል፡፡ ብዙዎች ያልደፈሯቸውን ጭብጥች ስሜትን በሚነካ መልኩ እያነሳ ውይይቶችን አጭሯል፡፡

በቁጥር ለመገመት የሚችግር አፍቃሪ ያለውን ያህል ስሙ ሲነሳ ወባ እንደነደፈው ሰው የሚያንዘፈዝፋቸውን ተቃዋሚዎችንም አፍርቷል፡፡ ይህም ነው ቴዲን ከዘፋኝነት አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ እንዲል የሚያደርገውም፡፡ ብዙ ዘፋኞች አንጋፋዎቹንም ጨምሮ ታሪካቸው በአድናቂ የተሞላ ነው፡፡ ምክንያቱም ቴዲ ያዜመባቸውን ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኃይማኖታው ጭብጦች ፍጹም ሳይነኩና ሳይደፍሩ እድሜያቸውን የሚፈጁት ሁሉንም ለማስደሰት ነው፡፡ ሁሉንም ለማስደሰት ከራስ ጋር መፋታትን የግድ ይላል፡፡ ሕሊናን እንዳይነቃ አድርጎ ማስተኛትን ይጠይቃል፡፡

እራስን ሳይሆኑ ከሁሉም ጋር መስሎ የማደርን ወይም አድር ባይ የመሆን ክህሎትን ይጠይቃል፡፡ ከዛ በኋላ በልቶና ጠግቦ የሚያገሳውን እና ቁራጭ ዳቦ አሮበት በርሃብ ቁንጣን የሚሰቃየውን፣ ፍትሕ አጥቶና ነጻነቱን ተነፍጎ የሚማቅቀውንና በንጹሃን ደምና ስቃይ ኑሮውን የሚያደላድለውን፣ ዘመኑን የራሱ ብቻ ያደረገውንና አመታት ቢቀያየሩም ዘመን የራቀውን ሁሉ እኩል ማየት ይጀመራል፡፡ ቴዲ ከዚህ በሽታ በጊዜ ከተላቀቁ ጥቂት የኪነ-ጥበብ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ እውነት በሁለት ተቃራኒ ጫፎች ላይ ለቆሙ ሰዎች እኩል አትመችም፡፡ የግድ ከሁለቱ አንዱ ለዛ እውነት በተቃሮኖ የቆሙ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሞጋቾች ተከታታይ ድራማ ክፍል 59...

የቴዲ ዘፈኖችም ሁሉንም የማያስደስቱት ለዚህ ነው፡፡ ግፍ ይብቃ ብሎ የሚያዜመው ቴዲ ግፍ ፈፃሚዎቹንና ግፉአኑን እኩል ሊያስደስት አይችልም፡፡ ለዚህም ነው የተወሰኑ ዘፈኖቹ እየተመረጡ በሕዝባዊ መድረኮች እንዳይቀርቡ በወያኔ ባለሥልጣናት እገዳ የሚጣለው፡፡ ቴዲ ለእውነት፣ ለፍትህና ለፍቅር መቆም የሚያስከፍለውን ዋጋ እየከፈለ ያለ ብርቱ ሰው ነው፡፡ ስለሆነም በየማሕበረ ድረ-ገጾች ከአዲስ አመት ጋር ተያይዞ ስሙ ተደጋግሞ መነሳቱና መሞካሸቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በዚህም የሚናደዱ ይኖራሉና መጪው ዘመን ልቦና የሚገዙበት ይሁን!

የቴዲን “ፍቅር ፈራን” ተጋብዛችኋል፡፡

መልካም አዲሰ አመት!!

ዘመኑ ቴዲ በዜማዎቹ የተመኘልን የፍቅር፣ የሰላም፣ የፍትህ፣ የአንድነትና የመተሳሰቢያ ይሁን!!!

Share