ብቻውን ሆኖ ከጥግ ቆሞ ይቆዝማል። ጸጉሩን እየፈተለ ይናደዳል . . . ብቻውን ያልጎመጉማል። ትንሽ ቆይቶ ያለቅሳል። ለጉድ! ያነባዋል። ሰው እንዳለ እንደሌለ አካባቢውን ይቃኛል። ገና ወደዚህ አካባቢ እንደመጣ ሲብስበት በሰው ፊት ያለቅስ ነበር። አሁን አሁን ግን ሲያለቅስ ሰው ሲያየው አይወድም። መጀመሪያ አካባቢ ጎረቤቶቹ ሲያለቅስ ሲመለከቱ ያጽናኑት ነበር። በኋላ ግን ቀውሷል ብለው ደመደሙ። እንዲያው በደፈናው ግማሾቹ ፍቅር ይዞት ነው ሲሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ የሳሃራ በረሃ ጋኔል አግኝቶት ነው. . . ወይም የባሕር ጂኒ ተጠናውታው ይሆናል ማለት ጀመሩ። በየሄደበት ሁሉም እብድ ነው፣ ቀውሷል ብለው ደምድመዋል። ስለሚናገረው ነገር ግን ማንም ልብ ብሎ ያስተዋለውም፣ የጠየቀውም የለም። እሱም መናገር አይወድም። በእርግጥም ስለሱ የሚያውቅ ማንም የለም።
ብቸኝነቱን ሲያስብ፣ የውስጥ ሃዘኑ የአዕምሮውን ጣሪያ ሲነካበት ከቤት ተነስቶ ውልቅ ይላል። ባቡር ይሳፈርና ወደ ፍራንክፈርት ይሄዳል። መሄጃ እንደሌለው የሚያውቀው ግን ፍራንክፈርት ሲደርስ ነው። ለምን ከቤቱ እንደወጣ ግራ ይገባዋል። ባቡር ጣቢያ ከሚገኘው ማክዶናልድስ ይገባና ቁጭ ይላል። እዛም ሆኖ በሃሳብ እንደገና ይወረሳል። ወዲያው ደግሞ እንባው ድቅን ይላል። የጸጋዬ ገብረ መድህንን ወንድ ልጅ ተደብቆ ነው የሚለቅሰው የሚለውን ግጥም በቃሉ ይወጣዋል።
ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ፣
አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ፣
ተሸሽጎ ተገልሎ ተሸማቆ ተሸምቆ፣
ከቤተሰብ ተደብቆ፣
መሽቶ የማታ ማታ ነው፣ ሌት ነው የወንድ ልጅ እንባው ።
እውነት ነው! ወንድ ልጅ በቀን አያለቅስም ብሎ ራሱን ያሳምናል።
በእንባ የጠበቡ ዓይኖቹን እየደጋገመ ጠረግ ጠረግ ያደርጋቸዋል። ጭንቅላቱ ግን በሃሳብ እንደተወጠረ ነው። እዬ! ዬ! ብሎ . . . አልቅሶ ቢወጣለት ምንኛ በወደደ ነበር። አካባቢውን ዞር ዞር ብሎ ይቃኛል። የሚያውቀው ሰው የለም። ማልቀስ እችላለሁ። ማን እንዳይታዘበኝ? ከማን ነው የምደበቀው? እዚህ አበሻ የለም . . .ቀውስ የሚለኝ የለም . . . እያለ ራሱን በራሱ በሚጽናኑ ቃላት ማባበል ይጀምራል። ብቻው ሲያለቅስ አበሾች አይተው ቀውሷል እንዳይሉት መፍራቱን ግን አልተወም።
ቁጭ ባለበት በሃሳብ ይነጉዳል። እንቅልፍ እንደያዘው ሰው በመሃል እንደገና ከሃሳቡ ይባንናል። በቀስታ ድምጽ ማዕበል፣ ማዕበል ፣ ማዕበል ይላል። አጠገቡ ያሉት ሰዎች ቋንቁው ባይገባቸውም በትዝብት ይመለከቱታል፤ በመቀጠልም ጮክ ብሎ እጄን ያዢኝ ፣ እጄን ያዢኝ ፣ እጄን ያዢኝ እያለ ይጮኻል። ሁሉም ሰው ወደ እሱ ይመለከታል፣ እሱ ግን ሰው እንደሚመለከተው ከቶ አያስተውልም። ለምን ለቀቅሽኝ ፣ ለምን?. . . ለምን ለቀቅሽኝ ብሎ ይጮኻል። ከዚያም ወዲያው ፈቱን የእንባ ዘለላ ያርሰዋል። ያለቅሳል ፣ ይንሰቀሰቃል. . . በጉንጩ ላይ ከሚፈሰው ይልቅ ደረቱን ሰንጥቆ ወደ ውስጥ የሚገባው እንባ ይብሳል ።
ጥቂት ቆይቶ ራሱን የጸጋዬን ግጥም ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል። እሱም አልመች ሲለው ግጥሙን እያሰላሰለ ማን ነው . . . ወንድ ልጅ ተደብቆ ነው የሚያለቅሰው፣ የሚንሰቀሰቀው ያለው? . . . ስህተት ነው ፀጋዬ! ወንድ ልጅ የሚያነባው አደባባይ ላይ ነው እንጂ! . . . ፀጋዬ ተሳስተሃል! ግጥምህን አርመው! ባንተ ዘመን ይሆናል በምሽት ተደብቆ የሚያለቅስው፣ በእኛ ዘመን ግን ተቀይሯል። በእኛ ዘመን ወንድ ልጅ ሲደላው ብቻ ነው ተደብቆ በምሽት የሚያነባው፣ እንደዚህ ቀይረነዋል፣ አንተም ቀይረዋ!
ጣሩ ሲበዛበት ግፍ መከራው፣
በቀን በጠራራ ፀሐይ አደባባይ ሕዝብ ፊት ነው፣
ወንድ ልጅ የሚያለቅሰው፣ የሚንሰቀሰቀው።
ማንነቱ የተደፈረበት፣
እሱነቱን ያጣበት፣
ብሶቱን የሚገልጽበት፣
ቁጭቱን የሚያሳይበት፣
ብቸኝነቱን የሚወጣበት።
ቀን ነው የሚያነባው፣
ሰው ፊት ነው የሚያለቅሰው፣
አደባባይ ነው ስቅስቅ የሚለው፣
ሕዝበ አዳም፣ የሃበሻ ዘር ብሶቱን እንዲያይለት ፣
አይቶም እንዲያላግጥበት . . . ።
ፀጋዬ ግጥምህን ቀይረው። . . . ይላል።
ወዲያው ቀና ብሎ ላፍታ ሰውን ሁሉ ከገላመጠ በኋላ፣ የአዳም ልጅ ሁላ አላግጥ . . . እኔን እያየህ ተዝናና ብሎ ከማክዶናልድ ይወጣል። ነገር ግን፣ ውጭ ወጥቶ የሚሄድበትን አያውቀውም። መሃል መንገድ ላይ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ቆሞ፣ እንደገና ለራሱ ብቻ በሚገባው ቋንቋ ማልጎምጎም ይቀጥላል፡፡
ከዚያም ፈጠን ፈጠን እያለ በርካታ እርምጃዎች ይራመዳል ። ወዲያውም ዘው ብሎ አንዱ አበሻ ቡና ቤት ይገባል። እዚያም ላፍታ አይቆይም። ይወጣል። እንደገና ሌላው ጋ ይገባል። ከዚያም ይወጣል። ከረንቦላ መጫወቻ ቤት ይሄዳል። . . . እዚያም እንደደረሰ፣ ተጫዋቾቹንና የከረንቡላ መጫወቻወን ጠረንጴዛና ኳሶች ትኩር ብሎ ቆሞ ያስተውላል።
ይኽ ትዕይንት ለሱ የዕለት ተዕለት ኑሮው ነው።
ከእነዚህ ቀናት በአንዱ ግን፣ እንዲህ ሆነ። …. በዚው በለመደው ቤት የከንቡላ ጨዋታ እያስዋለ ሳለ፣ ድንገት ሳይታሰብ . . . “ማዕበል ! ማዕበል ! እጄን አትልቀቂ ! . . . ጀልባውን ይዤዋለሁ እጄን አትልቀቂ ! ሲል አንቧረቀ። በአንድ እጁ ጀልባውን፣ በሌላኛው እሷን እንደሚጎትት ያህል ሰውነቱ ተወጣጠረ። ጮኸ ! ተጣራ ! ከረንቦላ ቤቱ ላፍታም ቢሆን በጸጥታ ተሞላ። ሁላችንም በአንክሮ ወደ እሱ ተመለከትን። በአዕምሮው አንድ ነገር እንዳስታወሰ ዓይኖቹ ፈጠጡ። እንባው በፊቱ ላይ ቦይ ቀዶ ቁልቁል መንዠቅዠቅ ጀመረ። . . . በከረንቦላው ጠረቤዛ ላይ ያሉትን ድንጋዮች በታተናቸው። ጨዋታውን ተረበሸ። ተጫዋቾቹ ጮኹበት። “ይህንን ቀውስ አስወጡት” ብሎ አንዱ ጮኸ ። ባለቤቶቹ “ውጣ! እንግዳ አትረብሽ” ብለው ገፍትረው አስወጡት።
የእሱን እግር ተከትሎ፣ በከረንቦላ ቤቱ ውስጥ የጦፈ ክርክር ተነሳ። “ይህንን ሰውዬ መምህር ግርማ ቢያገኙት ያድኑታል” አለ አንዱ። “እባክህ ተወን! በዓለም የታወቀው የጀርመን ሃኪም ያላዳነውን እንዴት ነው መምህር ግርማ የሚያድኑት?” አለ ሌላኛው። ክርክሩ ከእሱ አለፈና ወደ መምህር ግርማ ሥራና ተዓምር ተቀየረ። አንዱ የእሳቸው አድናቂ ሌላው ደግሞ ጽኑ ተቃዋሚ ሆነው ይከራከሩ ጀመር።
እኔንም በውል የማላውቀው ስሜት ገፍትሮ ከውስጥ አስወጣኝ። ተከተልኩት። እንደተለመደው ለማጽናናት ሞከርኩ። “ፀሐፊ ነኝ ትል የለም እንዴ?” ሳላስበው ጠየቀኝ። መልሱን ሳይጠብቅ ቀጠለ። “እስቲ ጻፈውና እንይህ? እስቲ ንገርልን ምን እንደደረሰብን ? አቦ ጀግና ሁና ! እውነቱን ጻፈዋ ? ቀውሷል እያሉ ከየአበሻው ቡና ቤት ከሚያባርሩኝ የደረሰብኝን ንገራቸው። ሳሃራን አየሁት. . . ባህሩን አየሁት ብለኸኝ የለም እንዴ ? ጻፈዋ እናንብበው ? ወይስ ሰሃራ ድረስ የሄድከው የአሸዋውን ማማር፣ የቴምሩን ጣእም፣ የፀሃዩን ግለት፣ የሙቀቱን ትእይንት ለማያውቁት ልታሳውቅ ነበር? ወይንስ ዕረፍት አምሮህ ነው ? …. ጉድ እኮ ነው! የኛ ስቃይ ለእናንተ መዝናኛ መሆኑ አይገርምህም ! ” በማለት ሳላስበው በጥያቄ ላይ ጥያቄ እአደራረበ ጠየቀኝ።
“ለመሆኑ ኩፍራን ታውቀዋለህ ? ከሱዳን ተነስተን እስከ ሊቢያ ኩፍራ ድረስ ምን ያህል የሰው ልጅ ስቃይና መከራ እንዳለ ታውቃለህ ? ሳሃራን አቋርጠህ ሰዎች የሚኖሩበት ቦታ ስትደርስ የሚሰማህን ታውቃለህ ? አንተ አታውቅም ! መች ይህን ጉድ ቀመስክና ! አንተ ኤር ኮንድሽን ባለው መኪና ውስጥ ተቀምጠህ አይደል እንዴ ሳሃራን የጎበኘኸው ? እሱንም እንኳ ቢሆን ጻፍና አስረዳቸው. . . መቀወስ ይነሰኝ እንዴ ? ቀውስ ነው እያሉ የሚያሽሟጥጡኝን በውል አስረዳቸው እንጂ ? ዳሩ አንተ ብትጽፈው መች አንብበውት፤ ለእሱ መች ጊዜ አላቸውና፤ አንዳንዶቹም ማንበብ አይችሉም። መታወቂያቸው ላይ ያለውን ስማቸውን እንኳ በውል አያውቁትም እኮ ! . . . እኔ ግን ቀውስ አይደለሁም። እነርሱ ናቸው አውቆ አበዶች። ሙሉ ቀን ድንጋይ ሲያፋትጉ የሚውሉ፣ ቤት ሞልተው በባዶ ሁካታ ሲንጫጩ የሚውሉ፣ ጫት እንደ ከብት እያመነዥኩ በቅዠት ምናብ የሚደሰኩሩ፣ በቁማር ፍቅር ሲነዱ ለሚያድሩ፣ የቡና ቅራሪ ሲጋቱ የሚውሉ፣ እነርሱ ናቸው እንጅ ቀውሶች። …. ህ’ ህ ! …. የህሊና ሚዛናቸው የተዛባ፣ አዙሮ የሚያይ አንገት የሌላቸው፣ የመጡበትን የረሱ፣ የሚሄዱበት ካርታ የጠፋባቸው።” መድረሻቸው ከከንቱ የሆነ ። “ሰው መሳይ በሸንጎ ማለት እነሱ ናቸው።”
“ደግሞ ንገራቸው. . . በሳር ውስጥ ተሸሸጎ፣ ታፍኖ፣ ከኩርፋ ትራቫሎስ ድረስ ያለውን መከራ። ስለ ባሕሩም፣ ስለ ጀልባውም ንገራቸው ለእነዚህ አረመኔዎች። እኔን ቀውሷል እያሉ ከየቡና ቤቱ የሚያባርሩኝን ። ቀውስ ነው በላቸው። በፍቅር ነው ያበደው ይሉ የለም? አዎ በፍቅር ነው የቀወሰው በላቸው። ስለ ፍቅር ምን ያውቃሉ? በሃሳብ የሚገለሙቱ፣ በሥራ ቦዝነው ከረንቦላ የሚጫወቱ፣ ጫት እያመነዠኩ በከንቱ ፍልስፍና ለሚሟገቱ፣ የመንፈስ ድኩማኖች፣ ሲመሽ አንቡላ እየጋፉ በየጎዳናው ለሚጣለዙ ግብዞች፣ አስረግጠህ ንገራቸው። እኔ ሰው ወድጄ ስለሰው ነው ያበድኩት . . . እነርሱ ግን የራሳቸውን ጠልተው ሰለ ሆዳቸው አብደዋል። አዎ አሁን በእኔና በእነሱ መካከል ልዩነት አለ። ይኸውም እኔ ሰው ወድጄ ስለፍቅር እራሴን ሰጥቻለሁ፣ እነሱ ደግሞ ሞራል አጥተው ለሱስ ስብዕናቸውን ጥለዋል።”
“አይገርምም! ለሴት ፍቅር እንዴት ታለቅሳለህ ብሎ ጠየቀኝ እኮ አንዱ። እንዴት አላለቅስም? አለቅሳለሁ እንጂ! ሱዳን ነበር የተዋወቅነው። እዚያ ነው ያፈቀራት በላቸው።”
ሻይ የምትሸጥበት ቦታ ነው የተዋወቅነው። ገንዘብ አልነበረኝም። ርቦኝ ነበር ። ምንም ሳልፈራ መራቤን ነገርኳት። ዳቦና ሻይ ሰጠችኝ። እንደ እናቴም እንደ እህቴም ታየችኝ። ደግነትዋ እንድቀርባት አደረገኝ። በልቼ ስጨርስ ሲርብህ ሁል ጊዜ ና አለችኝ። እኔም ከእሷ አካባቢ መጥፋትን አልደፈርኩም። ስቀርባት ወደድኳት ። ስቀርባት ወደደችኝ ። ተዋደድን። እኔ ገንዘብ አልነበረኝም። ከውጭ ይልኩልኛል ብዬ የተማመንኳቸው ወንድሞቼና እህቶቼን በቃላቸው አላገኘኋቸውም። ታሪኬን ነገርኳት። አዘነችልኝና እኔ አለሁልህ አለችኝ። ገንዘብ ሠርተን አውሮፓ እንደርሳለን አይዞህ አለችኝ። ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ያጣሁትን የሰው እምነት እንደገና የሰጠችኝን ካላፈቀርኩ ማንን ላፍቅር?”
“ንገራቸው ለእነዚህ ብኩኖች! ሻይ ሽጣ ነበር ወደ ሊቢያ የምንሄድበትን የከፈለችው። ያንን ሁሉ መከራ አልፈን አብረን ነበር ሊቢያ የደረስነው። ካንተ አልለይም ብላ አብራኝ የተሰቃየችው። ሳጣ ያጣችው፣ ሳገኝ የተደሰተችው፣ የፍቅር ማጀቴ ነበረች እኮ ። አንድ ለእኔ የተፈጠረች፣ ውብ ቆንጆ፣ ደግ ለሰው አዛኝ፣ ጠይቅ ድፍን ሱዳንን፣ ጠይቅ ድፍን ሊብያን፣ ማን እንደነበረች ይነግሩሃል። . . . እርጉዝ እኮ ነበረች፣ የመጀመሪያው ልጄ እናት፣ አውሮፓ እናሳድጋለን ስንል ነው እኮ ጥላኝ የሄደችው፣ እንዴት አላብድ? እንዴት አልቀውስ፣ እንዴት አላለቅስ፣ ለእሷ ያልታበደ ለሌላ ለማን ይታበድ?”
“እነዚህ ስለ ፍቅር ምን ያውቃሉ? እነዚህ ከልጃቸው አፍ ቀምተው ለቁማር የሚገብሩ እብዶች እኔን እንዴት ቀውስ ይሉኛል? እነሱ አሉ አይደሉም እንዴ ጨርቃቸውን ያልጣሉ በቁም ሙቶች። ይህንን ቀውስ አስወጡት ሲሉ በጫት አፋቸው ሲለፈልፉ አያፍሩም እኮ።”
ነገሩን ለማወቅ ቸኩዬ “. . .ታዲያ ለምን ተጣላችሁ? የትነች ያለችው? እናስታርቃችሁ እንጂ. . .?” ብዬ ጠየቅኩት። ዓይኑን ፈጠጥ አድርጎ አይቶኝ ። ቀጠለ።
“እኔ ጠቤ እንደነሱ ከሰው አይደለም። እኔ ጠቤ ከተፈጥሮ ነው። ከበረሃው ነው በልልኝ፣ ከማዕበሉ ጋር ነው በልልኝ። ያንን የሳሃራን በረሃ አቋርጠን ሊቢያ ስንደርስ ደስታችን ብዙ ነበር ። መለያያችን መድረሱን መች አስብንና። ሁለት ወር ሊቢያ ውስጥ ተደብቀን ኖርን። በተለይ እሷ ራሱዋን ደባብቃ አስቀያሚ ለመምሰል ትጥር ነበር። የእሷን ቁንጅና ያዩ ሊቢያኖች እሷንም እንደማይለቋት እኔንም እንደማይለቁኝ አውቀን ነበር። ለነገሩ ሁላችንም ተደብቀን አልነበረም የምንኖረው? እዛ ነበር እርጉዝ መሆኗን የነገረችኝ ። የመደንገጥም፣ የመደሰትም፣ የማዘንም ስሜት ተሰማኝ። እንደ ምንም ገንዘቡ ተከፍሎ፣ ጀልባው ተዘጋጀና ጉዞ ጀመርን። የሊቢያን የባሀር ክልል ስንወጣ ጀልባው ላይ ችግር እንዳለ ተረዳን። ከአንድ ወገን ያሉ ሰዎች በተፈጠረው ግርግር ወደ እኛ አካባቢ መጡ ። ጀልበዋ ተገለበጠች። ብዙዎቹ ሰመጡ። እኔ እጇን እንደያዝኳት እሷም እጄን እንደያዘችኝ ነበር ጀልባው መስጠም የጀመረው። በአንድ እጄ እሷን በሌላው ጀልባውን እንደያዝኩ፣ እሷ ደግሞ በአንድ እጇ እኔን በአንድ እጇ ባዶውን ጀርካን እንደያዘች ነበር። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሳይታሰብ ማዕበል ተነሳ። ይህንን ጊዜ ስትጸልይ ነበር። ፈጣሪ ላልተወለደው ልጃችን ብለህ ማረን፣ ማዕበሉን አቁምልን እያለች ነበር የምትጸልየው፣ ማርያምን ነበር የምትማጸነው።”
“በአንድ እጄ እሷን በአንድ እጄ ጀልባውን ይዤ ነበር ማዕበሉን ለመቋቋም የታገልኩት። በከፍታ የተነሳው ማዕበል ውሃውን ፊታችን ላይ ስለረጨን አፈነን። እጄን ለቀቀችው። ለመያዝ ሞከርኩ አልቻልኩም። እሷም ታገለች። ስሜን እየጠራች ጮኸች። ከአጠገቤ ድምጿ ራቀኝ። ድምጿ በአራቱም ማዕዘን ይሰማኝ ጀመር። ወዴት ልሂድ? ዋና አልችል። እዚህ ነኝ ብዬ መለስኩ። አበድኩ፣ በዚያ ጨለማ ምን ላድርግ፣ አበድኩ፣ ጮኩ፣ ምን ልሁን? ሌሊቱን ሁሉ ተጣራሁ፣ ድምጿ እየራቀ መጣ። እንዲሁ እንዳበድኩ ምሽቱ እየነጋ መጣ። ጠዋት ላይ የለችም፣ ትልቅ መርከብ መጥቶ እኛን አዳነን፣ ጀሪካኑን በሩቅ አየሁት። ፈለኳት ነገር ግን ላገኛት አልቻልኩም፣ የለችም። ከዚያ ቀን ጀምሮ መንፈሴ ታወከ፣ ህሊናየ ተነካ፣ ሰላሜና ፍቅሬ አብሮ በማእበል ዳግም ላይመለስ ተወሰደ፣ እኔም የሰውና የመንፈስ ደሃ ሆንኩ። አበድኩ፣ ቀወሰኩ። ንገራቸው ለምን እንደቀወስኩ። መቼም አይሰሙህም። ቁማር ተበልቶ አበደ ብትላቸው ነበር የሚሰሙህ!”
“ለእነዚህ ሃይማኖት ለሌላቸው ግብዞች። ለእሷ ያላበድኩ ለማን ልበድ?. . . ለማን ልቀውስ? እንደነርሱ ለቁማር፣ ለጫት፣ ለዝሙት . . . ? ጂኒ ባሕር ላይ መታው አይደል የሚሉህ? አዎ! የባህር ነውጥ ጭካኔና የሰው ፍቅር ማዕበል፣ የሳህራ በረሃ አባዜና የሰው ልጅ ውዴታውና ውለታው ነው እሱን ያቀወሰው በላቸው። እንደ እናንተ በየመሸታ ቤቱ ከበርቻቻና ጫት ቁማርና አደንዛዥ ዕጽ አይደለም እኔን ያሳበደኝ ብሏል በላቸው። መቼም ስለደነዘዙ አይሰሙህም እንጅ፣ ንገራቸው። ሰው ለሰው እንደ ተፈጠረና እንደሚኖር ሁሉ፣ ሰው ለሰው እንደሚሞትም ይወቁ።”
ካለኝ በሁዋላ፣ ጥሎኝ እያለቀሰ ሄደ። እያነባ፣ እየጮኸ፣ እያጉተመተመ፣ ሄደ . . . የባህሩ ጂኒ፣ የባሕሩ ጋኔል ነው ፍቅሬን የወሰዳት እያለ ሄደ። ቀን ከሌሊት አነባለሁ፣ አለቀስሳለሁ፣ ለእንባና ለሃዘን ቀጠሮ የለውም ጸጋዬ አንተም አልተረዳኸውም እያለ ፈጠን ፈጠን እያለ ሄደ።
መከራ ሲመጣ አይነግርም አዋጅ ፡
ሲገሰግስ አድሮ ሌት ይደርሳል እንጅ
እንዲሉ፣ ጸጋዬ ተሳስተሃል፣ እኔ ዛሬም ነገም አነባለሁ፣ ዓይኔ እስከሚከዳኝ አነባለሁ። የሰው ልጅ አሳር ፍፃሜ እስከሚያገኝ፣ ፍቅር፣ ደግነት ልግስናና ርህራሄ ሚዛን እስከሚደፋ፣ ፣ የሰውልጅ ሃብቱ ሰው መሆኑ እስኪታወቅ ድረስ ዛሬም ነገም አነሆ አለቅሳለሁ.፣ማዕበሉ ፀጥ እስከሚል አነባለሁ . . እያለ እያጉተመተመ፣ ከዓይኔ ራቀ።
ተፈጸመ
(ግንቦት፡ 2015 ዓ.ም)
- በፍራንክፈርት ከተማ የሊቢያንና የደቡብ አፍሪካን ሰማዕታት ለማስታወስ በተዘጋጀው የሐገር ፍቅር ሥነ ጥበብ ዝግጅት ላይ የቀረበ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ልብ ወለድ።