አቶ አብርሃም ያዬህ የምላስዎትን አፈሙዝ በአቶ ገ/መድኅን አርአያ ላይ አያዙሩ!

ሸግዬ ነብሮ

የዚህ ጽሑፍ መነሻ በቅርቡ አውራምባ ታይምስ የተባለው ድረ-ገጽ ከአቶ አብርሃም ያዬህ ጋር ያደረገው ቃለ-ምልልስ ነው።
ወደ አቶ አብርሃም ቃለ – መጠይቅ በዝርዝር ከመግባታችን በፊት “ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ” የሚለውን የሀገራችንን ብሂል በማጤን አቶ አብርሃም ያዬህንም ሆነ አቶ ገ/መድኅን አርአያን በተመለከተ በቅርብ የማውቀውን አቀርባለሁ። በዚህ አጋጣሚ አቶ አብርሃም ወደ ሀገር ቤት በገቡበት ጊዜ የነበሩ እማኞች በሙሉ በሕይዎት የሉም፤ ወይም ቢኖሩም እንኳን ምንም አይሉም ብለው አስበው ከሆነ መሳሳታቸውን አስቀድሜ ልጠቁማቸው እወዳለሁ።
አቶ አብርሃምያዬህ የመለስ ዜናዊ፣ ስብሃት ነጋ፣ ስዩም መስፍንና አባይ ፀሐዬ የሕወሓት ማፊያ ዘራፊ ቡድን ቁንጮ አባላት የቅርብ ጓደኛና የአንዳንዶቹም የሥጋ ዘመድ ናቸው። ግለሰቡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ዓለም በቆዩበት ዘመን ምንም በደል ያልደረሰባቸውና የተደላደለ ኑሮ የነበራቸው ሲሆን፣ ግብር እየከፈለ ያስተማራቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በመክዳት እንደ ዘመዶቻቸው የጎጠኝነት ህመም (Narrow Tribal Mentality) ተጠናወቷቸው ትግራይን ከኢትዮጵያ ለማስገንጠልና የትግራይ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከተመሠረተ በኋላ የአመራር ቦታ እይዛለሁ በሚል ቀቢፀ ተስፋ ሀገር ጥለው የፈረጠጡ ደካማ ፍጡር ናቸው። (እንደ ቀድሞ ታጋዮች፣ የአሁን ሀገር ዘራፊዎች የናጠጠ ዲታ እሆናለሁም ብለው ሊሆን ይችላል።)
አቶ አብርሃም እጀ ለስላሳ፣ ባለረጅም ምላስ፣ ለሜዳ ትግል የማይበቁና የወንድነት ሀሞት የሌላቸው በመሆናቸው ከመከረኛው የትግራይ ሕዝብ በሚገኘው የድርቅ እርጥባን ፍርፋሪ ካርቱም ውስጥ እየተንደላቀቁ የኖሩ ቅምጥል “ታጋይ” ናቸው። የአቶ አብርሃም የውጭ የሥራ ተልዕኮ ከዚህ በፊት እርሳቸው ለማናፈስ እንደሞከሩት የሕወሓት የመረጃ መኮንንነት አይደለም። የመረጃ መኮንንነት መለፍለፍን ሳይሆን ማዳመጥንና ማመዛዘንን የሚጠይቅ እነ ምን ይዤ ልቅረብ ብለው የሚሠሩት ሞያ ሳይሆን፣ የሰከነ አዕምሮ የሚጠይቅና በተክለፈለፈ የአብርሃም ያየህ ዓይነት ፍጡር የሚከናወን ተግባር አይደለም። ስለሆነም የግለሰቡን ፀባይ የተረዱት ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው የአብርሃም ምላስ ይጠቅማል ባሉት የአገናኝነት (Laison Officer) ተግባር ላይ መደቧቸው። ለግል ጥቅም የቆሙ የሱዳን ባለሥልጣኖችን በገንዘብ በመያዝ ድጋፍ ማስገኘት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባንኮች ወያኔ በዘረፈው ገንዘብ የምዕራቡ ዓለም ሆዳም ጋዜጠኞችን በመደለል በየሆቴሉ በመጋበዝና ውስኪ በማጠጣት የድለላ ሥራ በመሥራት ትግራይ ገብተው ድርቅን በተመለከተ ቪዲዮና ፎቶ በማንሳት በድርቅ ዕርዳታ ስም ለወያኔ እኩይ ተግባር የሚውል ገንዘብ የሚያስገኝ የፕሮፓጋናዳ ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ነው።
በሌላ በኩልም የዛሬ የሕወሓት መኳንንቶች ወደ ሱዳን ብቅ ሲሉ ማረፊያና ቆነጃጅቶችን በማዘጋጀት፣ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት ይላላኩ እንደነበር ከጤፍ የማይቆጥሩዋቸውና የሚንቁዋቸው ዛሬ በሸራቶን ልዩ ክፍል ተዘጋጅቶላቸው የሚንደላቀቁት የሕወሓት ማፊያ ቡድን ዘራፊ ቢሊዬነሮች ሁሌም የሚሉት ነው። አቶ አብርሃም የትግራይን በረሃ ያልረገጡና የስሚ ስሚ ከሌላ ያዳመጡትን ሽንኩርትና ቅመም ጨምረው አጣፍጠው የሚያቀርቡ ጥሩ የሸክላ ድስት ናቸው። የአቶ አብርሃም ምላስ ረዥም ከመሆኑ የተነሳ መቋጠሪያ ሸምቀቆ ስለሌለው እነ ስብሃት ነጋ ወደ ሚስጥሩ ጓዳ ሳያስገቡ በጥንቃቄ በገደብ በሩቅ የያዙዋቸው አገልጋያቸው (Servant) ነበሩ።
ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) ሲመሠረት አቶ አብርሃም በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ቀርቶ በተራ አባልነት እንኳን ያልታጩ ጀሌ መሆናቸውን ሲገነዘቡ ነው “እኔ ከማን አንሼ ነው” በማለት ተቆጥተው እና መለስና ስብሃት ጋ ካልቀናኝ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ልብ እሰርቃለሁ፤ የናቀኝንም እበቀላለሁ ብለው በማስላት ነበር ወደ አዲስ አበባ የገቡት።
አቶ አብርሃም ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ የተቀበላቸው የመረጃ መሥሪያ ቤቱ ቢሆንም የግለሰቡን ፀባይ በመረዳቱ ያሠማራቸው በፕሮፓጋንዳ ሥራ ብቻ ነው። አቶ አብርሃም ስለሕወሓት ወያኔ የሆነውን ታሪካዊ መረጃ ከማነብነብና ከተለያዩ ጽሑፎች ካገኟቸው መረጃዎች በስተቀር ትግራይ በረሃ ውስጥ ስላለው ሁኔታ የሚያውቁት የስሚ ስሚ ካልሆነ በስተቀር አንድም ነገር የለም። ስለትግራይ በረሃና ጓዳ ጎድጓዳ የእጃቸውን መዳፍ ያክል የሚያውቁትና ለመረጃው መ/ቤት እጅግ ጠቃሚ መረጃ የሰጡት ግን አቶ ገ/መድኅን አርአያ ነበሩ። ሆኖም ግን ሚስጥሩ ያልገባቸውና የአብርሃም ያየህን ንግግር በቴሌቭዥን መስኮት ያዳመጡና አሁንም ወያኔ በሀገራችን ላይ ከሚፈፅመው ጋር እያዛመዱ ሰውየውን እንደትንቢተኛ የሚያዩዋቸው አሉ። ሀቁ ግን በመረጃ መሥሪያ ቤቱ ቢሮ አብርሃም ያየህን ተዋናይ አድርጎ የተሠራ ድራማ ነው። መረጃው የተገኘው ከአቶ ከአቶ ገብረ መድኅን አርአያና ከመረጃ መ/ቤቱ ነው።
ወያኔ ኢትዮጵያን ሲወር አቶ አብርሃም የፈረጠጡት ወደ ዩጋንዳ ነው። በዩጋንዳ ቆይታቸውም ወያኔን እታገላለሁ በሚል ከኮሎኔል መንግሥቱ ገንዘብ ለመቦጨቅ ያደረጉት ሙከራ ባለመሳካቱ ግለሰቡ ባላቸው የሲጋራ፣ የመጠጥና የሴሰኝነት ባህሪ ገንዘብ ስለማይበቃቸው ወደ ተራ ሌብነት በመዝቀጥ በንጉሡ ጊዜ የፖሊስ ጄኔራል የነበሩትን የጄኔራል ጋሻው ከበደን ሴት ልጅ ለመዝረፍ ሲሞክሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘው አራት ዓመት ተፈርዶባቸው ካምፓላ ውስጥ ሉዚራ ወደተባለው ወህኒ ቤትና ከባድ ወንጀለኞች በሚታሰሩበት Block A ተወርውረው ሳለ በዩጋንዳ፣ አሜሪካና መላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከእሥር እንዳስፈቷቸውና ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለሱ እንደረዷቸው ይታወሳል።
ውለታ ቢሱና በልቶ ካጁ አብርሃም ያዬህ ግን በዴንማርክ ኑሯቸውን ካደላደሉ በኋላ ቅንጅትንና የረዷቸውን ኢትዮጵያውያን ለምን እኔን በትግል አመራርነት አላቀፉኝም በሚል በተለያዩ ጊዜያቶች ሲያንቋሽሹና የመለስ ዜናዊን ታላቅነት ሲለፍፉ የወያኔ ድረ-ገጽ በሆነው በአይጋ ፎረም ሳይቀር ተስተውለዋል።
በቅርቡም በለመደ አፋቸው አውራምባ ታይምስ በተባለው ድረ-ገጽ ላይ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ በጊዜው የነበሩት ሰዎች ያለቁ መስሏቸው “ላም ባለዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ እራሳቸውን አዋቂ አድርገው አቶ ገብረ ምድኅን አርአያን አንቋሽሸዋል። በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በቀረበው ቃለመጠይቅ ላይ አቶ ገብረ መድኅን ለመሳተፍ ፈቃደኛ እንዳልነበሩና እንዲያውም ፊታቸውን ለማሳየት እንዳልፈለጉ፣ ወደ መገናኛ ብዙሐን ያመጧቸው እርሳቸው እንደሆኑ፣ ሰዎች ከአቶ ገ/መድኅን ጋር በአንድ ላይ መቅረብ እንደሌለባቸውና ነገርም ስለሚያበላሹ እንደመከሯቸው፣ አቶ ገ/መድኅን ከእርሳቸው በፊት ሁለት ዓመት ቀድመው የገቡ ቢሆንም ጠቃሚ ሆነው ባለመገኘታቸው ተጥለው እንደተቀመጡ፣ በሐውዜን ጉዳይ ላይ የተናገሩት ሁሉ ሀሰት እንደሆነና እንዲያውም ሐውዜን ሲደበደብ አዲሰ አበባ እንደነበሩ፣ አብርሃም ያዬህ ዓይናቸውን በጨው አጥበው ቀባጥረዋል።
አቶ ገ/መድኅን አርአያ የወያኔ በጅሮንድ ወይም ገንዘብ ያዥ የነበሩ፣ ሕወሓት ሲመሠረት ጀምሮ አብረው የነበሩ፣ የወያኔን ገመና ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ከካርቱም መሸታ ቤት ሳይሆን ከትግራይ በረሃ የመጡ፣ የረጋ መንፈስ ያላቸው፣ አስተዋፅዎአቸው (ክሬዲታቸው) በከፊል በአፈ-ጮሌው አብርሃም ያዬህ የተሰረቀባቸው ሀቀኛና ጥሩ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ናቸው። ከላይ እንደተገለፀው በአቶ አብርሃም አፈ-ጮሌነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቀረበው ገለፃ መረጃው የተገኘው ከአቶ ገ/መድኅንና ከደኅነነቱ መ/ቤት የመረጃ ዘገባ (Intelligence Analysis) ነው።
በእንግሊዝ ሀገር በለንደን ከተማ የወያኔ የመረጃ ሠራተኛ ተባባሪ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው ኃይለ ሥላሴ ግርማይ የተባለው ቅጥረኛ እየተከፈለው አቶ አብርሃም በኢትዮጵያ ቴሌቨዥን ሲለፈልፉ ከጀርባ ሆኖ መረጃ ሲያቀብልና ጽሑፍ ሲሰጥ የነበረ ነው። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ኃይለ ሥላሴ ግርማይ የአቶ ገ/መድኅን አርአያ የእናታቸው ልጅ ታናሽ ወንድማቸው ሲሆን፣ በተለያዩ ጉዳዮች በተለይም እነ ተክሉ ሐዋዝ በእነ ስብሓት ነጋ በመገደላቸው ተጣልቶ እየተከፈለው ለደኅንነቱ መ/ቤት መረጃ ሲያቀብል የነበረ ግለሰብ ነው። ሮም ላይ በጣሊያን መንግሥት አማክኝነት የደርግና የወያኔ የእርቅ ስብሰባ በተደረገበት ወቅት የአውሮፕላን ቲኬትና የልዩ ልዩ ወጭ ተልኮለት ከለንደን ወደ ሮም በመሄድ ከረጅም ዓመታት በኋላ ከአቶ ገ/መድኅን ጋር እንዲገናኝ ተደርጓል። (አቶ አብርሃም አዲስ አበባ በቴሌቭዥን ሲለፈልፉ የአቶ ገ/መድኅንን የሮም ጉዞ እንኳን አያውቁም ነበር።)
ህምባባ ሼዊት በተባለ ኦፕሬሽን ወያኔ አቶ ገ/መድኅንንና አቶ አብርሃም ያዬህን ለማጥፋት ያደረገው ዝግጅት ተደርሶበት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሲነገራቸው መሬት ተቀድዳ በዋጠችኝ ሲሉ የነበሩት አቶ አብርሃም ስንት ማደሪያ እንደቀያየሩና ያሳዩት የባህሪ መለወጥ ማንነታቸውን አስመስክሯል። በአንፃሩ ግን አቶ ገ/መድኅን በመገናኛ ብዙሐን ከመቅረባቸው በፊት በአንድ የመንግሥት መ/ቤት እንደ ማንኛውም ሰው ሳይፈሩ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩና እንኳን ሸፍኑኝ ሊሉ ግምባር ቀደም ሆነው ደረታቸውን ሰጥተው ወያኔን ፊት ለፊት የመፋለም ቁርጠኛ አቋማቸውን እጃቸውን ለመንግሥት ከሰጡ ቀን ጀምሮ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ያስመሠከሩ ሀቀኛና ቀጥተኛ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
አቶ ገ/መድኅን አርአያ አቶ አብርሃም እንደሚሉት ከእርሳቸው በፊት ሁለት ዓመት በኢትዮጵያ ካለሥራ ተጥለው የቆዩ አይደሉም። አቶ ገ/መድኅን ከአቶ አብርሃም በፊት ኢትዮጵያ ውስት የቆዩት ለዘጠኝ ወራት ሲሆን ስለ ሕወሓትም ሆነ በትግራይ በረሃ የውሃ ኩሬ ሳይቀር የት እንዳለ የማስታወስ ከፍተኛ ችሎታ ስለነበራቸው ሳይጋለጡ ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ሲሠሩ የቆዩ እንጅ በሬዲዮና በቴሌቭዥን የሚያቅራሩ የድል አጥቢያ አርበኛ ወይም የከተማ ፋኖ አልነበሩም።
ለመሆኑ አቶ አብርሃም ቀን በቴሌቭዥን ሲጮሁና ማታ ማታ ደግሞ ከአዲስ አበባ እስከ ናዝሬት በሚገኙ መሸታ ቤቶች “አሆይ ላሎዬ” ሲሉ፣ ጀግናውና ሐቀኛው አቶ ገ/መድኅን ግን ትግራይ በረሃ ድረስ እንደገና ገብተው አመርቂ ሥራ ሠርተው መውጣታቸውን ብነግረዎት ምን ይላሉ!? አቶ አብርሃም ያዬህ የት እንደነበር ሊያውቁት ቀርቶ ምንነቱን እንኳን ሰምተው የማያውቁትና የወያኔ ሬዲዮ ጣቢያ የነበረበት ክሳድ ግመል የተባለ ተራራማ ቦታ ድረስ በመሄድ ገ/መድኅን አርአያ ኢትዮጵያዊ ግዴታቸውን ተወጥተው የተመለሱ ጀግና መሆናቸውን በሕይዎት ኖሬ ስመሠክርላቸው ክብርና ኩራት እየተሰማኝ ነው። ይህንና ሌሎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሊነገርላቸው የሚገባቸውን ድንቅ ሥራዎች አንድ ቀን በሕይዎት ያለን ምሥክሮች በአካል ቀርበን የመንመሠክረው ሀቅ ስለሆነ አቶ አብርሃም ዛሬ አፍዎ እንዳመጣ መዘላበዱ ነገ ትርፉ ውርደት ይሆናልና ቢታቀቡ እመክረዎታለሁ።
በዚህ አጋጣሚ ዕውነታውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወደፊት ሊያቀርቡ የሚችሉ ብዙ ሰዎች ስላሉ አቶ አብርሃም ያዬህ የምላስዎትን አፈሙዝ ከጀግናውና ሀቀኛው ገ/መድኅን ይልቅ ወደ ሀገር አጥፊው ወያኔ እንዲያዞሩ ስመክር፣ ሌሎችም እበላ ባይ ሆድ አደሮች ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ስማቸውንና ታሪካቸውን ባይለውጡ መልካም ነው እላለሁ።

4 Comments

  1. Merrejaws balkefa. rasewon medebeq min ametaw? Betekikilegna simewo yetsafu. yalebeleza alubalta yihonal!

  2. Dear Azalu,
    How do you know that Shegye Nebro has not used her/his real name? I think there is nothing here that shows the writer didn’t use his/her real name.

Comments are closed.

Menelik II ethiopia
Previous Story

ገብረኪዳን ደስታ በትግርኛ “አጼ ምኒልክን ለሸዋ እንጂ ለኢትዮጵያ አልቆሙም ነበር” በሚል በጻፉት መጽሐፍ ላይ የሕዝብ አስተያየት ይፈለጋል

Next Story

አንድነት ፓርቲ ለመድረክ ምላሽ ሰጠ፤ የተደበቀውን አፍረጠረጠው

Latest from Blog

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የውጪ ግንኙነት የቤተክርስቲያኒቱን የሺሕ ዘመናት ታሪክ እና እሤቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርባታል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) እንደመንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ- ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የተካሄደው፤ ‹‹የአፍሪካ  መንፈሳዊ ቀን/The African Spiritual

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |
Go toTop