(ዘ-ሐበሻ) ሕወሓት መራሹ የኢትዮጵያ አስተዳደር በሃገሪቱ ውስጥ የሕወሓት ነጋዴዎች ካልሆኑ በስትቀር ሌሎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው በሃገራቸው ነግደው እንዳይበሉ ከፍተኛ ምቀኝነት እንዳለበት በተደጋጋሚ መዘገቡ አይዘነጋም። ከዚህ ቀደም በንግድ ብልጠት የሕወሃት የንግድ ድርጅቶችን እርቃናቸውን በኪሳራ አስቀርተው የነበሩት የስታር ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤቶች የሕወሓትን ክፍፍል ተከትሎ በተፈጠረ ድንጋጤ በሙስና ሰበብ ታስረው ከንግዱ ዓለም እንዲወጡ መደረጉ አይዘነጋም።
– የኮካ ኮላ ከፍተኛ ባለ አክሲዮን አቶ ንጉሴም ከአቶ ታምራት ክስ ጋር ተያይዘው በኪሳራ ከሕወሃት ድርጅቶች ተፎካካሪነት ወጥተዋል።
– የሃግቤስ ኢንተርናሽናል ባለቤት ሚ/ር ህራየር ቤንሰን (አርመናዊ ናቸው) እርሳቸውም በሙስና ሰበብ ከአቶ ስዬ አብርሃና ወንድሞቻቸው ጋር እንዲታሰሩ በመደረግ ከሕወሓት ንግዶች ጋር እንዳይፎካከሩ ተደርገው ግማሽ ደርዘን ዓመታትን እስር ቤት እንዲያሳልፉ ተደርገዋል።
– የመስቀል ፍላወር ባለቤት አቶ እስክንድርም በሕወሓት ተመትተዋል
– እነ አቶ ክቡር ገና በተፎካካሪነት ላይ አይደሉም
– በአቢሲኒያ ባንክ ላይ የደረሰውን ከአንባቢዎቻችን እንተወዋለን
– እንደ አቶ ብርሃነ መዋ ያሉ ነጋዴዎች ንግዳቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል
– ጣይቱ ሆቴልን የገዙትና የዘሞኒተር የ እንግሊዘኛ ጋዜጣ አዘጋጅ አቶ ፍጹም ዘ-አብ አስገዶም እህታቸው የአቶ ስዬ አብርሃን ወንድም አቶ አስፋ አብርሃን ስላገቡ ብቻ ሕወሃት ለሁለት ሲሰነጠቅ “አቶ አሰፋ በአምቻ ጋብቻ ተይዘው ጣይቱ ሆቴልን በቅናሽ ለአቶ ፍጹም እንዲሸጥ አድርገዋል” በሚል ተከሰው ከገበያ እንዲወጡ ተደርጓል
ምን ይሄ ብቻ? ሌላም ሌላም
አዲሱ የወያኔ ሰለባ ደግሞ ኤርሚያስ አመልጋ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ቡሬ የተሰኘውን ውሃ በጎጃም ክልል ውስጥ ፋብሪካ ከፍተው ሲያቀርቡ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ “በደረቅ ቼክ ማጭበርበር ወንጀል” ታስረው ተፈትተዋል። መለስ ሞተዋል የሚል ዜና በኢሳት በተነገረበት ወቅት “አልሞቱም አዲስ አበባ ገብተዋል” እያለ በማስተባበል ሥራ ላይ የከረመው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ኤሚያስ ታሰሩ ብሎ በሰበር ዜና ቢዘግብም ሪፖርተር ደግሞ ታስረው ተፈቱ ብሏል። የሪፖርተር ዜና እንደወረደ ይኸው፦
የዘመን ባንክና የአክሰስ ሪል ስቴት መሥራች የሆኑት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከደረቅ ቼክ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው አንድ ቀን በቁጥጥር ሥር ውለው ባለፈው ዓርብ ተለቀቁ፡፡
አክሰስ ካፒታል ግን በአቶ ኤርሚያስ ላይ የተጀመረው ምርመራ መቋረጡን አስታውቋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ካዛንቺስ (ስድስተኛ) ማዘዣ ጣቢያ አንድ ቀን ካደሩ በኋላ ተለቀዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ችግሩ የተፈጠረው ባለመግባባት መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ግን ምርመራው ተቋርጦ ወደ ሥራ መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ የተጠረጠሩበት ምክንያት የአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ አንድ ደንበኛ ኩባንያው እሠራለሁ ያለውን ቤት ሠርቶ በወቅቱ አላስረከበኝም በማለት ገንዘባቸው እንዲመለስ ሲጠይቁ፣ አቶ ኤርሚያስ የ350 ሺሕ ብር ቼክ ይፈርሙላቸዋል፡፡
እኝህ ደንበኛ ዘመን ባንክ ሄደው በቼክ የተጻፈላቸውን ገንዘብ ማግኘት ባለመቻላቸው ወደ ክስ በመሄዳቸው ነው አቶ ኤርሚያስ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተብሏል፡፡
ምንጮች እንደሚገልጹት ግን፣ አካውንቱ ውስጥ ገንዘብ ነበር፡፡ ነገር ግን ሌላ የሪል ስቴቱ ደንበኛ አካውንቱን በፍርድ ቤት በማሳገዳቸው ገንዘቡን ማንቀሳቀስ አልተቻለም፡፡ አክሰስ ካሉት አካውንቶች ውስጥ በአንደኛው ከ1.7 ሚሊዮን ብር በላይ እንደነበር ሪፖርተር መረዳት ችሏል፡፡ ይህም መረጃ ለመርማሪዎቹ ቀርቦ የይከፈለኝ ጥያቄ ላነሱት ግለሰብ ገንዘቡ ተከፍሏቸዋል፡፡ ግለሰቡም ወዲያው ክሱን በማንሳታቸው ምርመራው ተቋርጦ አቶ ኤርሚያስ ተለቀዋል፡፡
አክሰስ ሪል ስቴት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በአካውንቱ ውስጥ በቂ ገንዘብ መኖሩን አረጋግጧል፡፡ የተፈጠረው ክስተትም በቢዝነስ እንቅስቃሴ ውስጥ በየጊዜው የሚያጋጥም መሆኑን የገለጸው አክሰስ፣ መርማሪዎቹ ይህንኑ ተረድተው ምርመራውን ማቋረጣቸውን አስታውቋል፡፡
በዘመን ባንክ በአካውንቱ ውስጥ ገንዘብ መኖሩን ተረጋግጦ፣ ችግሩ ሊፈጠር የቻለው በአካውንቱ ውስጥ ገንዘብ ባለመኖሩ ሳይሆን በፍርድ ቤት ውሳኔ በመታገዱ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡
ችግሩ የተፈጠረውም በዘመን ባንክ ስህተት መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ ባንኩ በጉዳዩ ሳይጠየቅ እንደማይቀር ተናግረዋል፡፡ የባንኩን ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ እሸቱን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ብንሞክርም፣ ‹‹በባንኩ ፖሊሲ መሠረት በደንበኞች ጉዳይ ላይ አስተያየት አንሰጥም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ወደተለመደው የሥራ ገበታቸው መመለሳቸውን ያስታወቀው አክሰስ ሪል ስቴት፣ በቀጣይ ሳምንታት ሥራውን አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃዎችን ለደንበኞቹ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
አቶ ኤርሚያስ በኢትዮጵያ ቢዝነስ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ሰዎች ተርታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም አሜሪካ ውስጥ በተለያዩ ባንኮች ውስጥ በመሥራት የሚታወቁት አቶ ኤርሚያስ ኃይላንድ በመባል የሚታወቀውን ውኃ፣ ዘመን ባንክን፣ አክሰስ ሪል ስቴትና ሌሎች ተዛማጅ ቢዝነሶችን በመመሥረት ይታወቃሉ፡፡