March 18, 2015
28 mins read

የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካና የአድዋ ድል – ሚንጋ ነጋሽ

የካቲት 23 2007 (ማርች 2, 2015) የ119ኘዉ የአድዋ ድልና የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ነዉ። አከባበሩ በሃገር ዉስጥ ቢቀዘቀዝም፤ በተዘዋዋሪዉ በአሉን የሚያከብረዉ በዉጭ ሃገር የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። በሰሜን አሜሪካ የድል በአሉ ቀን ከአፍሪካ አሜሪካዉያን ታሪክ መዘከሪያ ወር ጋር መያያዙና የየካቲት 12 ሰማእታትን መታሰቢያ ቀን ደግሞ ከሰላሳ በላይ በሆኑ ያለም ከተሞች መዘከሩ፤ በዉጭ  የሚኖሩ ኢትዮጰያዉያን ትኩረት የሰጡት ስለሀገር አቀፍ ድልና ስለአፍሪካዊነት (Pan Africanism) መሆኑ ራሱን የቻለ መልዕክት አለዉ።

በዚህች አጭር ጽሁፍ ለማስገነዘብ የምሞክረዉ አድዋንና መሰል የሃገራችንን እሴቶች በብሄር-ብሄረስብና ወይም በሃይማኖት ዘመም  የፖለቲካ  መነፅር (ethnocentric paradigm) መመልከትና በብዙሃን ዘመም (diverse, multi-ethnic) መነፅር መመልከት የሚየስከትሉትን እደምታዎች ለማሳየት ነዉ። ሁለቱም አመለካከቶች የሚያዩት አንድ ነገር ቢሆንም የሚሰጡት ትርጉም ግን የተለያየ ነዉ። ሃገር አቀፍ ፖሊሲ ሲነደፍ ሁለቱ መነፅሮች የሚያሳዩትን ልዩነትና አንድነትን በቅጡ መረዳት ይጠይቃል። እኔ የታሪክ ወይም የፖለቲካ ስነልቦና ሳይንስ ተማሪ አይደለሁም። ሰለአድዋ ድልም የማዉቀዉ በጣም ዉሱን ነዉ። ቢስማርክ ከጠራዉ እ.ኤአ 1884/85 የበርሊን የአፍሪካ ቅርጫ ኮንፍረንስ (the conference for the scramble of Africa) ጀምሮ እንዴት ኢትዮጵያ እንደሌላዉ የአፍሪካ ክፍል የዚህ ቅርጫ ሰለባ አለመሆንዋ ብዙ የታሪክ ምሁራንን አስረገርሞዋቸዋል። ይህንን ታሪክ አፈወርቅ ገብረየሱስ፡ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፡ ራይመንድ ጆናስ፡ ሪቻርድ ፓንክረስት፡ ዶናልድ ሌቢን፡ ኤድዋርድ ክሬሚ፡ ሃሮልድ ማርከስ፡ ጆን ሰፔንሰር፤ ታደስ ታምራት፡ መርእድ ወልደአረጋይ፤ ብርሃኑ አበበ፤ አለሜ እሽቴ፤ ባህሩ ዘውዴ፡ ሽፍራዉ በቀለ፡ ሹመት ሲሻኝ፡ ዘዉዴ ገብረስላሴ፤ ጌታችዉ ሃይሌ፤ጳዉሎስ ሚለኪያስ፤ ጳዉሎስ ኞኞ መስፍን አርአያ፤ ጌታቸዉ መታፈሪያ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የጻፉትንና የተናገሩትን የማንበብ እድል ነበረኝ፡፡

ከፊልም፤ሙዚቃና ግጥም ስራዎች ደግሞ እነ ቦብ ማርሌና ራሰ ተፈሪያኒዝም፤ የሃይሌ ገሪማን፤ የአለምፅሃይ ወዳጆን፤ የፀጋዮ ገብር መደህን፤አዲሰ አለማየሁ እጅጋይሁ ሽባባዉና የቴዎድሮስ ካሳሁንን ስራዎች መስማትና ማየቱ ተጨማሪ ሰሜት  ፈጠሮልኛል።። ከታላላቅ የፖለቲካ መሪዎች ጽሁፎችና ንግግሮች መካከል ደግሞ፡ እነ ማርከስ ጋቢ፡ ማርቲን ሉተር ኪንግን (የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግብዣ ጨምሮ)፤ የአፍሪካ የነፃነት መሪዎች ማለትም እነ ሙዋሊሙ ኔሬሬ፡ ኬኔዝ ካዉንዳ፤ጆሞ ኬንያታ፤ ኔልስን ማንዴላ፡ ታቦ እምቤኬ፡ ክዋሚ ንክሩማ፤ በደቡባዊ አፍሪካ በ1880ዎቹ የተፈጠሩትና እስከዛሬ ያሉትን በኢትዮጵያ ስም የሚጠሩትን ቤተ ክርስቲያኖች ታሪክን በተመለክተ የፐ/ር ማሞ ሙጬን የቅርብ ጊዜ ፅሁፎች ሳነብ፤ አሜሪካም በተለይ በሁለተኛዉ እ..ኤ.አ የ1933 የጣሊያን ወረራ ጊዜ ስለነበረዉና ስለአነ መላኩ በያን ሥራና ስለአፍሪካ አሜሪካዉያን ወዶ ዘማቾች ምልመላ ሳነብ፤ የተረዳሁት አድዋ የአድዋዉያንና የኢትዮጵያዉያን የድል ታሪክ ብቻ አለመሆኑን ነዉ። የሃይቲን የነፃነት ትግልና በልጅነቴ እሰማ የነበረዉን የአፄ ምኒልክን የደስታ የተኩስ ሩምታ ምክንያት ያስታዉሰኛል። እነዚህ ምሁራን የነፃነት መሪዎችና አርቲስቶች የተከተሉት በአብዛኛዉ የብሄረሰብና የብሄር መነፅር የታሪክ ትርጉም አልነበረም ብሎ መደምደም ይቻላል።

በአንፃሩ አዲስ ህይወት (የብዕር ሰም): ቦኒ ሆልኮምብና ሲሳይ ኢብሳ፤ ማሩ ቡልቻ፤ በ 1990ዎቹ በ Red Sea Printers ና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኩራዝ አሳታሚ የታተሙ መጻህፍትና ገድል መሰል ጽሁፎች የፖለቲካ ትንታኔያቸዉ በአንዳንንድ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የሚታየዉን ብሄረ ተኮር ጥናቶች (ethnography and ethnic studies) ተደግፈዉ ማርክሳዊ መሰል ትንታኔና ትርጉም ሊሰጡ ይሞክራሉ። ጎልቶ የሚወጣዉ መልዕክታቸዉ ኢትዮጵያ የሚለዉን የፖለቲካና የሶሺያል መሰረቶች የሚንድ (de-legitimize) ነዉ። የሀገር ዉስጥ ግጭቶችን በብሄር መነጽር ያይዋቸዋል። የአድዋ ጦርነትን ዋና መሪዎችን ከሌሎች ግጭቶች ጋር እያጣቀሱ ሲወቅሱ ይሰማሉ። ብሄር ተኮር ድርጅቶችም ግጭቶቹን የአንድ ወገን በማስመሰል ከዛሬ ፖለቲካ አገናኝተዉ ቢቻል አዲስ ነፃ ሀገር ባይቻል ደግም አሁን ካለዉ የተሻለ የፌዴራል አስተዳደር እንመሰርታለን እያሉ ቃል ይገባሉ። የድሮዋ ኢትዮጵያም ልዩ የብሄረሰቦች እስር ቤት ነበረች የሚል ትረካም አላቸዉ። አዲሲትዋ ኢትዮጵያም የብሄረስቦች (nations, nationalities, peoples, volks) ድምር ነች ወይም ትሆናለች ይላሉ። በዚህም የተነሳ የፖለቲካ የአስተዳደርና የትምህርት ወዋቅሩ ይህንኑ ተከትሎዋል። ይህ አካሄድም ሀገሪቱዋን ከመበተን አድኖዋት በኢኮኖሚም እየተራመደች ነዉ ብለዉ ይከራከራሉ።

የፖለቲካ መሪዎች ይመጣሉ-ይለወጣሉ። ስርአቶቹን የሚመራዉም ርአዮተ አለም እንዲሁ ይቀያየራል። ይህ ደግሞ በብዛት የሚታየዉ አፍሪካ ዉስጥ ባሉ ከቀኝ ግዛት በሁዋላ በተፈጠሩ ሀገሮች (post colony states) ነዉ። አንድ ቲዎሪም ሁሉን ነገር (phenomenon) ሊያብራራ አይችልም። ይህ እንኩዋን በኩዋሊቴቲቭና በፊኖሚኖሎጂ የምርምር መንገድ የሚጠኑ ስራዎችን ቀርቶ በኢምፒሪካል  የምርምር መንገድ ላይም በየጊዜዉ የሚታይ ሁኔታ ነዉ። ታሪክንም በተለያዩ መነፀሮች መመርመር በራሱ ችግር የለዉም። እንዴዉም ይህ አካሄድ በተ;ለይ በፖሊሲ ንድፊያ ጊዜ የተሻለ አካሄድ ሊሆን ይችላል። በእኔ እድሜ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሶስተ ያስተዳደር መርሆዎችን አይቻለሁ። ባለፉት 40 አመታት ዉስጥ ብሄር ዘመምና የግራ ዘመም የታሪክ ትርጉዋሜዎች የመንግስትን ዋና ዋና ፖሊሲዎች ሲመሩ አይተናል። ሁለቱም ህብረተስብን በመደብ በብሄርና ወይም በሃይማኖትና በጾታ መክፈልና ልዩነቶች ላይ ማተኮርን ይወዳሉ። አንድን ህብረተሰብ በዴሞግራፊ መርሆዎች ከፍሎ ማጥናቱ ችግር የለዉም። ልዩነታቸዉ ብዙሃንነት (diversity) እንዴት እንደሚስተናገድ ነዉ። ሰለ ከአንድ በላይ ማንነት (dual & multiple identities) በሃገራችን ብዙ አይነገርም።

ብዙዎቹ የዛሬ የብሄር ንቅናቄ መሪዎች በአንድ ወቅት የማርክሲስት ርአዮተ አለም ተከታዮች እንደነበሩ ይታወቃል። አስተዳደር ላይ የሁለቱ ልዩነት ማርክሲሰቶች ሀገር አቀፍ፡ አህጉር አቀፍ፤ከዚያ አልፎ ኢንተርናሽናሊዘምን ሲያወድሱ፤ በተቃራኒዉ ብሄር ተኮር አካሄድን የሚመርጡ ደግሞ ጭንቀታችዉ ቆመንልሃል ለሚሉት የህብረተሰብ ክፍል ሲሆን ግራ ዘመምነታችዉ ስታሊን በስራ ላይ ያላዋለዉን የመገንጠል መንገድ እንዲያቀነቅኑ አድርጎዋቸዋል። ግራ ዘመም ያልሆኑት ብሄር ተኮር ድርጅቶች ደግሞ ተግባራቸዉ ወደ ፋሽዝምና አፓርታይድ፤በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ ሲያቀርባቸዉ ይታያል። የሶቪየት ህብረትና የይጎዘላቪያን አፈጣጠር፤ አፈራረስና ዉጤቱን ማጤን ይረሳሉ። ስለሆነም አንድ ብሄር ተኮር የፖለተካ ሃይል የተለያዩ ብሄሮች ባሉበት ሀገር ላይ የበላይነት በያዘበት ቦታ ገዢዉን ብሄር ለመጥቀምና ለማሞገስ ተብለዉ የሚደረጉ ሙከራዎች ትክክለኝነታቸዉና ትረጉዋሜያች በቅጡ ሳይፈተሹ በህገ መንግስት ላይ ይሰፍራሉ። የመንግስትም ስራዎች በብሄር ተኮር ፖሊሲዎች ይመራሉ። የብሄር ድርጅቱ ካናሳ ወግን ከመጣ የአናሳዎችን  ህብረት በመፍጠር የብዙሃኖችን ግፊት ለመቁዋቁም ይሞክራል። ማንነት (identity) የምርጫ አጀንዳ ሆኖ ዜሮና አንድ ወይም እድገትና ድህነት፤ባርነትና ነፃነት፤ እኛና እነሱ፤ ሰይጣንና መልአክ፤ወዘተ ተብሎ ይቀርባል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ አካሄድ በሃይማኖት (bigotry) በመታጅብ ላይ ይገኛል።  ከዚህ ባሻገር ደግሞ ሊበሪቴሪያኒዘምን ማለትም ግለሰብ መብት ላይ የሚያተኩር  የፖለቲካ አስተሳሰብን የሚያራምዱ አሉ። ሁሉም ማለትም የግራዉም ብሄር ተኮሩም ሆነ ሊበሪቴሪያኑ “ዲሞክራሲያዊ” የሚል ታፔላ አላቸዉ።

ሰለዚህ ኤትኖሼንትሪዝም በሃገራች ሲታይ ልዩነትን (diversity) ለማስተናገድ እ.ኤ.እ በ1993 የሰራዉ ህገ መንግስት መፍትሄ እንዳልሆነና ሀገር አቀፍ መግባባት ለመፍጠር አለመቻሉ በቅጡ ተፈትሾአል። የ1991 ዱም ቻርተር ማለትም የህገ መንግሰቱ አዋላጅ የተፃፈዉ ከግጭት በሁዋላ ስለነበር ያመለከተዉ የጊዜዉን የሃይል አሰላለፍ ነበር። ጸሃፊዎቹም እርስ በርሳቸዉ ይጣሉ እንጂ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ከ25 አመታት በሁዋላም ቢሆን መሰረታዊ ልዩነት አይታይባችዉም። በትምህርት ቤቶችም የሚሰጡ ትምህርቶች የብሄር ተኮር መሰረት ስላላቸዉ ከፍተኘ ትምህርትም በብሄር በመዋቀሩና በክልል አሰተዳደር ስር መሆናቸዉ፤ በምሁሩም ቅን ልቦናዊነት (bona fide, honesty and integrity) ላይ ለመተማመን አስቸጋሪ እየሆነ መጥቶዋል። ሃገሪቱ የተማረ ህዝቡዋን በተለያዩ ምክንያቶች ስታጣና፤ አብዛኛዉ ወጣት የሆነዉ ህዝብ የስራ አጥነት፤የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስደት ሰለባ ሲሆን፤ በባህር ላይ ሲሰምጥና በየስደተኛ ካምፖችና እስር ቤቶች ሲታጎር፤ የምርምር ተቁዋሞች መሰረታዊ ምርምር ማደረግ አለመቻላቸዉ፤ ዮኒቨርሲቲዎችም ከጥራት ይልቅ ወደ ብዛት አተኩረዉ በየክልሉ ሲረጩ፤ በብሄር ተኮር ሹማምንት ሲመሩ፤ ዉጥረቶቹንም በፍትሃዊ ምርጫዎች ለማስተንፈስ አለመቻሉ፤ ብሄርና ሃይማኖት የፖለቲካ ማማ (platform) ሆነዉ መቀጠላቸዉ፤ በግጭት ቀጠና ዉስጥ ያለችዉን የሀገራችንን ችግሮች እጅግ ዉስብስብ አድርገዉታል።

ስለዚህም በሀገራችን ዛሬ በስልጣን ላይ ያለዉ ብሄር ተኮር መንግስት እንደ ቀድሞዎቹ የማርክሲሰትና የንጉሳዊ መንግስታት ሁለት ችግሮች ገጥመዉታል። በአንድ በኩል ሌሎች ብሄር ተኮር ተፎካካሪዎቹ የማዕከላዊ መንግስት ስልጣኑን ሊወስዱብትና ለራሳችዉ ብሄር ሊተኩ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ካልሆነላቸዉ ደግም ሃብት ወደ አሽናፊዉ ብሄር ብሄረሰብ እንዳይፈስስ ሲሰተሙን ለማፍረስ ይጥራሉ። ይሀ ጥረት በራሱ በመንግስትና ፓርቲ ዉስጥ፡ በምርጫና በጠመንጃም እየተሞከረ ይገኛል። የብሄር ድርጅቶች መሪዎችም ለሁለተኛ ድል (second breakthrough) እየተዘጋጀን ነዉ ይላሉ። ሁኔታዉ በሶቪየት ህብረትና በዩጎዝላቪያ የኮሚኒስት ፓረቲዎች ዉሰጥ የብሬዥኔቭና የቲቶን ሞት ተከትሎ የተፈጠረዉን ክስተት በገዥዉ የብሄሮች ግምባር ዉስጥ አይከሰትም ብሎ መናገር አይቻልም። እሰከ አሁን በድርጅቱ ዉስጥ የነበረዉ  የሃይል አሰላለፍ ለማስቀጠል ርብርቦሽ ያለም ይመስላል። በሌላ በኩል ደግሞ ከብዙሃኖችና ከዲሞክራሲ ሃይላት ክፉኛ ዉድድር ገጥሞታል። በነፃና ፍትሃዊ ሀገር አቀፍ ምርጫ እንደማያሸንፍ ተረድቶታል። ስለሆነም ተፎካካሪዎቹን ስልጣን ከማካፈል ይልቅ ማፍረስንና አሽባሪዎች ብሉ መሰየሙን መርጦዋል። በ2005ቱ ምርጫ ያኮረፉም ጠመንጃ አንሰተዉ ከቆዩት ጋር የታክቲክ ወዳጅነት የፈጠሩ ይመስላሉ። የሰላም መንገድ መጥበብና መዘጋት አመፅ ተቀባይነት እንዲያገጘ እያደረገ ይገኛል። ከዚህም አልፎ ሰለሰላማዊና የመሳሪያ ትግሎች (armed & peaceful resistance) ተጉዋዳኝነት የሚያሳዩ ፍልስፍናዎች እየቀረቡ ይገኛሉ። ይህንንም ሁኔታ ጎረቤት ሀገሮች ለራሳቸዉ በሚጠቅም መንገድ ሂደቱን ሊቃኙት እንደሚፈልጉ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነዉ። በቀጠናዉ ያለዉን አጠቀላይ በሃገሮች መሃል ያሉትን ዉጥረቶችን ወደጎን አድርገን የሃገሪቱን የዉስጥ ዉጥረት ብናይ የመጪዉ ግንቦት ምርጫ ወይም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ጥገናዊ የህገ መንግስት መሻሻል እዚህ ግባ የሚባል ፋይዳ እንደማይኖራችዉ ግልፅ ነዉ።

ሰለዚህ በሀገራችን ያሉትንና እየተፈጠሩ ያሉትን ዉጥረቶች ለመፍታት ወሳኝ እርምጃዎች መዉሰድ ያስፈልጋታል። ለዚህም  ቁልፉዋ የምትገኘዉ በአብዛኛዉ የማእከላዊ መንግስትን ስልጣን በሚቆጣጠረዉ ብሄር ተኮር ድርጅት እጅ ቢሆንም   ድርጅቱ ይህንን ሊሰራ የሚችል መሪ ከዉስጡ ለማዉጣጥ እስካሁን አልቻለም። ብሄራዊ አንድነትንና እኩልነትን የሚገነባ፤እሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት የፖለቲካ አስተሳሰብና አስተዳደር መመስረት የዛሬዉ የሃገሪቱ ፈተናዎችዋ ሲሆኑ፤ እነዚህ ፈተናዎች ግን የዛሬ 119 እመት በፊት እነ አፄ ምኒልክን፡ እቴጌ ጣይቱን፡ ራሰ አሉላን፤ ፊታዉራሪ ሃብተ ጊዎርጊስን፤ ራስ ጎበናንና ሌሎቹን በሺህ የሚቆጠሩትን የአድዋን አርበኞች ገጥመዋችዉ ከነበሩት ፈተናዎች ጋር የሚወዳደሩ አይደሉም። እ.ኤ.አ ከ1937ቱ ፈተናዎች ጋርም የሚወዳደሩ አይደሉም። በእነዛ ከባድ ፈተናዎች ጊዜ ብዙ መስዋእትነት ተከፍሎዋል።  እነዛን ፈተናዎችን ስንመረምር የእኛ ትዉልድ ፈተና የኤትኖሴንሪክ የታሪክ መነጽር ወዴት እየወሰደን መሆኑን መገንዘብና በቅን ልቦና ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን መንገዶች መሻት ነዉ። ችግሮችን መካድ ወይም መደበቅ ሳይሆን፤ በእዉቀት በዉይይት በዲሞክራሲና በፍትሃዊ ካሳ (restorative justice) የሚፈቱትን የታሪክ ጠባሳዎች እያጎሉ ጣት መቀስሩ ለማንም ጠቃሚ እንደማይሆን ማወቅ ነዉ። የዛሬ ተሽናፊዎች ነገ አሸናፊዎች ለመሆን እንዳይሰሩ፤ ይህንንም በር በጊዜዉና በቅጡ በብሄራዊ እርቅና መካካስ መዝጋት እንጂ፤ እንዴዉ በደረቁ የርስ በርስ ጦርነት ሂደቶችን እንደ ገድል እየቆጠሩ፤ ከበሮ መምታቱ፤ በግብር ከፋዩ ገንዘብ ስርግና ምላሽ መደገሱ፤ ለአንድነትና ለብሄራዊ መግባባት ጠቀሚ ርምጃዎች ሊሆኑ እንደማይችሉ፤ ከድግሱ በሁዋላ ቢሆንም፤ ግንዛቤ መዉሰድ ያስፈልጋል።

ከዚህም በላይ ኤትኖሴንትሪዝም የማእከላዊ መንግስትን ስልጣን ቢይዝም ሆነ ባይዝ የሚያልመዉ ስለ አንድ ንፁህ የጠራ የተቀባ፤ወርቃማና እግዚአብሄር ስለመረጠዉ ጭቁንና ስለተጎዳ ወዘተ ማህበረሰብ ስለሚኖርባት ቅኖናዊት ሀገር  (utopian state) መሆኑ መረሳት የለበትም። በዚህም የተነሳ የተረጋጋ የብዙሀን ብሄር ብሄረሰቦች ሀገርን ማስተዳደር ከባድ ፈተና ይሆንበታል። በብዙ ክልሎችም በነፃ ምርጫ ማሽነፍ ያስቸግረዋል። ቀልፍ የአስተዳደር የማከላከያ የኢኮኖሚ አዎታሮችን ቃል እንደሚገባዉ ማስተዳደር ይሳነዋል። አዲሲቱ ኢትዮጵያ መሆን ያለባት ከብሄርና ብሄረስቦች (nations, nationalities, ethnic groups, volks) የተዉጣጡ ስብስቦች (የህገ መንግስቱን መግቢያ ይመልከቱ) ተስማምተዉ የሚፈጥሩት ሀገር ናት የሚለዉም ምርጫ መር ከሆነ ዲሞክራሲ ጋር ማጣጣም አስቸግሮታል። ስምምነቱም ካልሰራ ደግሞ አንቀፅ 39ን ተጠቅሞ መሄድ ይቻላል የሚለዉን መፈፅም ቀላል አለመሆኑን ተረድቶታል። የሚሄደዉም ክልል ምንም እንኩዋን በአፍሪካም ሆነ በአወሮፓ ለጊዜዉ የሚታየዉ ብሄረሰብና ሃይማኖት ተኮር የሆነዉ የፖሊቲካ ምህንድስና ዉጤት አሉታዊ ቢሆንም፤ የተሻለ/ች አባት/እናት ሀገር መመስረት ይቻላል የሚሉ አሁንም አልጠፍም። ይህንን አካሄድ መፋትሄ ነዉ ብሎ ሀገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ለህዝብ በሬፈርነደም ማቅረብ ግን ሃላፊነት የጎደለዉ አካሄድ ነዉ። የጋራ እሴቶችን፤ ክፉም ይሁኑ ደግ መኖራቸዉን መርሳት፤ ሰዎች ከአንድ በላይ ማንነት (dual or multiple identity) እንደሚኖራቸዉ፤ የሀገራት አመሰራረት ሁል ጌዜ ያለችግር አለመሆኑን በቅጡ አለመመርመርና የወዲፊቱን ጉዞ በቅጡ ማለም አለመቻልን ያመለክታል።

በመጨረሻም በዉጭ የምንኖር ኢትዮጰያዎያን ባንፃራዊ ነፃነት ስለምንገኝና ከጊዜ ወደጊዜ ቀጥራችንም እየበዛ ስለሄደ፤ እንደ አድዋ አይነት ሃገር አቀፍ የሆኑ እሴቶች ከማክበር የሚከለክለን ነገር መኖር የለበትም። በሃገራችንም የሰላም ድምፅ ከፍ ብሎ እንዲሰማ መሞከር ይኖርብናል። በመሬትና በአንዳንድ ጥቅሞች መደለልና የገዛ ጥላችንን ሳይቀር መፍራት የለብንም። ራሳችንን ከፍርሃት ነፃ ማዉጣት ይገባናል። ስለ አሀጉራዊ ስለአፍሪካ ዲየስፖራ፤ ስለአፍሪካ አሜሪካዉያን ሰለሃገር አቀፍ እሴቶች ዉርስና ቅርሶች መናገር መጻፍ፤ ማክበርና መዘክር ይኖርብናል። በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን የታሪክ አሻራዎች (historical footprints) በምንችለዉ ዘዴ መረዳት፤ማሰባሰብና የተዘረፉት ቅርሳ ቅርሶች እንዲመለሱ መሞከር ይገባናል። የአክሱም ሃዉልት መመለስ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ መሆን የለበትም። ከበስተሁዋላም ሆነ ከፊት ሆነዉ የሚሰሩትንና የሚረዱትን ማመስገን ይገባል። ዶ/ር አበራ ሞላና አቶ ኪዳኔ አለማየሁ በመካከላችን መገኘታቸዉና እየሰሩ ያሉትንም ልናዉቅላቸዉና ልናበረታታቸዉ ይገባል። በብሄር ተኮር ፖለቲካ ዉስጥ ራሳችንን አጥረን፤ ታሪካችን የግጭት፤የረሃብ፡ የቸነፈርና የስደት ብቻ እንዳይሆን፤ዛሬ አፍሪካ አሜሪካዉያን የገቡበትን ራስን ያለማወቅ ቀዉስ (identity crisis)፤ ሌሎች አፍሪካዉያን ወገኖቻችን ያለባቸዉን የራስ መተማመን ችግር፤ ልጆቻችን በአዉሮፓ እንዳሉት አናሳ ኮሚኒቲዎች፤ የኢኮኖሚዉ፤የፖለቲካዎና የዕዉቀት ጭራ፤በሁዋላም የአሀገሮቹ ባዐዳን እንዳይሆኑ፤ ከወዲሁ ማስብና ዘዴ ማግኘት የእኛ የመጀመሪያ ትዉልድ ፈላሾች (immigrants) ፈተና ነዉ።

 

[1] አ.ኤ.አ በማርች 15, 2015 በዴንቨር ኮሎራዶ የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ላይ የተደረገ ንግግር;;

Latest from Blog

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

Go toTop