(ይህ ጽሁፍ በአዲስ አበባ ታትሞ የሚወጣው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ታትሞ የወጣ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን)
የለውጥ ድምፆች
ማኅበራዊ ሚዲያ ፕሬሱን እየተካ ይሆን?
“ስለሰው ልጅ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ጥቅም ሳስብ ወደአዕምሮዬ የሚመጣው የተወጠረ ፊኛ ነው” ብሎ ይጀምራል የአዲስጉዳይ ዘጋቢ ያነጋገረው ተሾመ ምናላቸው የተባለ ከኢንድራጋንዲ ዩኒቨርሲቲ በሶሲዮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪውን ያገኘ ወጣት። “የሰው ልጅ እንደተወጠረ ፊኛ ነው። በአዕምሮው የሚያሰላስለውን ሐሳብ ካልተነፈሰው ይፈነዳል። ማኅበራዊ ተራክቦው ዝቅተኛ ሲሆን፤ ወይም ከነአካቴው ሲዘጋ ‘እኔን መሰል ሌላም አለ’ ብሎ ማሰብ ያዳግተዋል። መሰሉን ማግኘት ያልቻለ ሰው ደግሞ ብቸኝነትና መገለል እንዲሁም ያለመፈለግ ስሜት ያድርበታል። ከፍተኛ ጭንቀትና ድብርት ሲነግሱበት ያለጥርጥር በውስጡ አብዮት ይነሣል። ይህ አብዮት ሰውን እንዲጠላና እንዲርቅ፣ ወይም በራሱ ላይ እስከሞት የሚያደርስ እርምጃ እንዲወስድ ይገፋፋዋል። ይህ በጤናው ላይ የሚከተለው መዘዝ ነው። ከዚህ ጋር ተዛማጅ በሆነ መልኩ ማንም ሰው የፈለገውን የመናገርና በነጻነት የማሰብ ተፈጥሮአዊ መብቱ የተከለከለ ጊዜም ልክ በጤናው ላይ እንደሚፈጠረው ያለ አብዮት ነው የሚያስነሳው። ለለውጥ ይቀሰቀሳል። መተንፈሻ ቀዳዳ ለማግኘት በሚያደርገው ፍትጊያ ቁጣና እልህ የተሞላበት ጥፋት ይፈጽማል። በየትኛውም መንገድ ስሜቱን ለመግለጽ ከመሞከር አይቦዝንም። ይህ የሰው ተፈጥሮአዊ ባሕሪ ነው። ሰውን ከመናገርና ሐሳቡን ከመግለጽ መከልከል ብዙ ጊዜ የሚያስከትለው ውጤት መልካም የማይሆነውም ለዚህ ነው” ይላል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው ሐሳብን በነጻነት የማንሸራሸሪያ መንገድ እጅግ ጠባብ እየሆነ መጥቷል የሚሉ ወገኖች በተለይ የነጻ ፕሬስ መዳከምንና መረጃም ከአንድ ወገን ብቻ በብዛት መፍሰሱን እንደጤነኛ አካሔድ አይመለከቱትም። ኢትዮጵያ ውስጥ አልፎ አልፎ የሚከሰቱትን እንደ 1997 ዓ.ም ዓይነት ግብታዊ ትግሎችም ከሐሳብ በነጻነት አለመንሸራሸርና ልዩነትን በመግባባት ተቀብሎ የመራመድ ባሕል መዳበር አለመቻል ጋር ተያይዞ ከዚህ አፈና ለመውጣት ከሚደረግ ትግል ጋር ያያይዙታል። በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያሉት የኅትመትና የብሮድካስት ውጤቶች በአብዛኛው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆናቸው፣ ጥቂት የሚባሉት የግል ሚዲያዎችም የብዙኀኑን ሐሳብ ለማንጸባረቅ በሚያስችል መልኩ በኅትመት ሥርጭትም ሆነ በይዘትና ጥራት በሚፈለገው መጠን ያለመደራጀታቸው የሀገሪቱ የፕሬስ ዕድገት ‘እንደካሮት ቁልቁል’ እንዲሰርግ አስገድዶታል ይላሉ። ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርጉት ደግሞ መብቱን በወረቀት ሰጥቶ በተግባር የነሣውን መንግሥት ነው። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ዛሬ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ፕሬሱን ተክተው አንዳንዴም ቀዳሚ ሆነው እየመሩ ተመራጭ የሐሳብ መለዋወጫና የአዳዲስ አስተሳሰብ መግለጫ መድረኮች የሆኑት።
የዛሬው ዐብይ ጉዳይ ዓምዳችን “ማኅበራዊ ሚዲያዎች ፕሬሱን እየተኩ ነውን? ለተዘጉት አንደበቶችስ እንደለውጥ ድምፆች አገልግለው ይሆን?” የሚሉትን ጥያቄዎች ይፈትሻል። እግረ መንገዱንም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ማኅበራዊ ችግሮቻችንን ተከፋፍለን እንድንሸከማቸው እንዴት እንዳገዙ ማሳያዎችን ያቀርባል።
ኢንተርኔትና ኢትዮጵያ
እንደ አንዳንድ መረጃዎች በኢትዮጵያ የበየነመረብ (ኢንተርኔት) ተጠቃሚዎች ቁጥር በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት እጅግ ከፍተኛ በሆነ ቁጥር ጨምሯል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት 500 ሺሕ የማይሞሉ ተጠቃሚዎች የነበሩት በይነመረብ ዛሬ እንደ መገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል ገለጻ 2.5 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የግል ኮምፒዩተር ኖሯቸው ለኢንተርኔት ግልጋሎት በኢትዮ ቴሌኮም ደንበኝነት ከተመዘገቡት ኢትዮጵያውያን የላቀ ቁጥር ያላቸው ኢንተርኔት ካፌ ውስጥ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ። ጥንቃቄ የታከለበት ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ቅሉ፤ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የበይነመረብ ተጠቃሚ ስለመሆናቸው ግን ‘ወርልድ ኢንርተኔት ስታትን’ ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡
የሁሉም ገጸበረከት
በይነ መረብ /ኢንተርኔት/ ለሰው ልጆች ካበረከታቸው መልካም ዕድሎች መካከል አንዱ ማኅበራዊ ሚዲያ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ በመላው ዓለም ሰፊ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም ለውጦች እንዲከሰቱ መንስኤ ለመሆን የቻለ፣ በሌላ ቋንቋ የዓለምን የመረጃ ቅርጽ እየለወጠ የሚገኝ ድንቅ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ገፀ በረከት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አዝጋሚ ቢሆንም ሕዝቡ የሱታፌው ተካፋይ እየሆነ ነው። ከሦስት ዓመታት በፊት ከ134 ሺሕ የማይበልጥ የነበረው የኢትዮጵያውያን የፌስቡክ አውታረ መረብ ተጠቃሚዎች ቁጥር የዓለም ሀገራትን የበይነመረብ ተጠቃሚነት በስፋት በመዳሰስ መረጃ በሚሰጠው ‘የሚኒዋትስ የጥናት ግሩፕ’ ሪፖርት መሠረት ከ902 ሺሕ እንደሚልቅ የተገለጸው በታኅሣሥ 2005 ዓ.ም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ዓይነተኛ መገለጫ የሆነው ፌስቡክን የተቀላቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ እንደሚጠጋ ይገመታል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፅዕኖ የማሳደር አቅሙ እያደገ የመጣው ማኅበራዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ ለመቃኘት የጦማርያንን፣ የቴክኖሎጂ ሙያተኞችን፣ በጥቅሉ የድረ ዜጎችን እና የሌሎችን ምሁራንን አስተያየት መካፈል ግድ ነው፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያ ትንግርቶች
ማኅበራዊ ሚዲያ ሰፊ ተቀባይነትን ባገኘው ፌስቡክ ብቻ የተገደበ ባይሆንም፤ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ አባላትን ያሰባሰበውን ይህንኑ አውታረ መረብ የሚስተካከለው አልተገኘም፡፡ በአሁኑ ወቅት ትዊተር፣ ማይስፔስና ሊንክድኢንን ጨምሮ ከ500 በላይ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዳሉ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የጡመራ መድረክ (blog)፣ ዌኪስ (wikis)፣ የበየነ መረብ የውይይት መድረክ (Internet forums)፣ የድምፅና ምስል መጋሪያዎች (podcasts and Utube) ከማኅበራዊ ሚዲያ መገለጫዎች መካከል በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያ ‘አይ-አዎ’
በተለያዩ ወገኖች የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ እና አዎንታዊ ፋይዳ ሁሌም ቢሆን የጦፈ ክርክር እንዳስነሳ ነው፡፡ “ታማኝ የመረጃ ምንጭ ሊሆን አይችልም፤ ሰዎችን ለማታለል ሊውል ይችላል፤ ሰዎች በአካል እንዳይገናኙ እንቅፋት በመፍጠር ላልተገባ የሥነ ልቡና ቀውስ ይዳርጋል” ወዘተ. በማለት ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያላቸውን ቅሬታ ከሚያሰሙት ጀምሮ አንድሪው ኪንን የመሳሰሉ ጸሐፊያን “The cult of the amateur writing” የሚል መጽሐፍ በማሳተም ማኅበራዊ ሚዲያውን በስፋት ተችተዋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያን የሚተቹ ወገኖች እንደ ማስረጃ ከሚያወሷቸው ነጥቦች አንዱ በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ይፋ የሆነውንና “ማኅበራዊ ሚዲያን አዘወትሮ መጠቀም ሱስ ያስይዛል፡፡” የሚለውን ግኝት መሠረት ያደረገው ጥናት ነው፡፡ በተለይ በተመራማሪዎቹ ስም የወጣለት “FOMO” (fear of missing out) /በአማርኛው የመረሳት ፍርሃት/ ጥናቱ በተካሔደባቸው ብዙ ተማሪዎች ላይ መታየቱ የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ጎን ጎልቶ እንዲታይ አድርጎታል፡፡
በአንጻሩ በርካቶች ማኅበራዊ ሚዲያን በእጅጉ በማወደስ የብዙ ለውጦች መንስኤ መሆኑን ያወሳሉ፡፡ “መድኃኒት አሉታዊ ጎኖች አሉት ተብሎ አልወስድም እንደማይባለው ሁሉ ማኅበራዊ ሚዲያም ከአጠቃቀም ጉድለት በሚያስከትለው ችግር ሳቢያ በደፈናው መወገዝ የለበትም፡፡” በማለት ይከራከራሉ፡፡
የተጋመሰው የጎርጎርሳውያኑ የዘመን ቀመር ሲገባደድ በመላው ዓለም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ሁለት ቢሊዮን አካባቢ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ሰፊ ጥቅምን ያበረክታል ተብሎ የሚጠበቀው ማኅበራዊ ሚዲያም “እልፍ” አዎንታዊ ፋይዳዎች ያሉት መሆኑን የተለያዩ ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡ ሰዎች በነጻነት ሐሳባቸውን ለመግለጽ፤ የተደራጀ እንቅስቃሴን በቀላሉ ለማስተባበር፤ የተለያዩ ዕውቀቶችን ለማግኘት፣ የሥራም ሆነ ሌሎች መልካም ዕድሎቻቸውን ለማሳደግና፣ በጣም ጠቃሚ መረጃዎችን በፍጥነት ለመለዋወጥ ማኅበራዊ ሚዲያው የላቀ ጥቅም እንደሚሰጥ የሐርቫርድ፣ ጆን ሆፕኪንስ፣ ኮሎምቢያ እና ስታንፎርድ የመሳሰሉ የአሜሪካ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች ምሁራንን አሳምኗል። ከዚህም ባሻገር ለተማሪዎቻቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ዘላቂ ጥቅምን ሊያገኙ የሚችሉበትን ልዩ ኮርስ አዘጋጅተው የ”ምርጥ ሶሻል ሚዲያ ተሞክሮ” ትምህርትን እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት በሄይቲ የደረሰው እጅግ ከፍተኛ የሆነ የመሬት መናወጽ ለ220,000 ሰዎች ሞት እና 30 ሺሕ ሕንፃዎች መደርመስ ምክንያት ሆኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በጊዜው የአሜሪካ ቀይ መስቀል ለዚህ ዘግናኝ አደጋ እርዳታ ለማሰባሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በዋነኝነትም በትዊተር ባደረገው ቅስቀሳ በ24 ሰዓታት ብቻ ከ126 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማሰባሰብ በቅቷል፡፡ በግብጽ ለተከሰተው አብዮት ብሎም በዐረቡ ዓለም ለታየው መነሣሣትም ማኅበራዊ ሚዲያ በተለይ ፌስቡክና ትዊተር የላቀ ሚና መጫወታቸው ይታወሳል፡፡ በአሜሪካዋ ቦስተን ከተማ በቅርቡ የተካሔደውን የማራቶን ሩጫ መሠረት አድርጎ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት አድራሾች ማንነት ለመለየት ከምንም በላይ የላቀ ሚና የተጫወተው የፍሎሪዳው ነዋሪ ዴቪድ ግሪን በማኅበራዊ ሚዲያ ያሠራጨው የፍንዳታውን ክስተት የሚያሳይ የሞባይል ፎቶ ነበር፡፡ ኤፍ ቢ አይም በሶሻል ሚዲያ የተገኘውን ፎቶ ‘የቦንብ ጥቃቱን አድራሾች ለመለየት ያስቻለ ምርጥ መረጃ’ ሲል ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡ በዚህ መልኩ በመላው ዓለም ማኅበራዊ ሚዲያ በሰው ልጆች በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሆነ ሌሎች የሕይወት መስተጋብሮች ውስጥ አቻ የሌለው ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
ነገረ ፌስቡክ በኢትዮጵያ
ፌስቡክ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ዋነኛው ነው፡፡ ኤሪክ ኩልማን የተባሉት የቴክኖሎጂ ጸሐፊ “ፌስቡክ ሀገር ቢሆን ኖሮ ሦስተኛው የምድራችን ትልቁ ሀገር በሆነ ነበር፡፡” በማለት ፌስቡክን ያካተታቸውን ሕዝቦች ብዛትና በሰው ልጆች ላይ ለማሳደር የቻለውን ተጽዕኖ በአጭሩ አውስተዋል፡፡ በኢትዮጵያም ይህ ማኅበራዊ ሚዲያ ለተለያዩ ኩነቶች በጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ ሕይወት ወንድምአገኝ በፌስቡክ ላይ የተለያዩ ሓሳቦችን በመሰንዘር ትታወቃለች፡፡ አንድ ቀን ምሽት ሕይወት አልጋዋ ውስጥ ሆና ዝናቡ ይዘንባል፡፡ ሁለት ብርድ ልብስ ብትለብስም ቅዝቃዜውን መቋቋም አቅቷት ጋቢ ደረበች፡፡ በድንገት በዚያ የምሽት ዝናብ በየመንገዱ የተቀዳደዱ ልብሶችን ለብሰው ለብርድ የተዳረጉ ሰዎች ወደአዕምሮዋ መጡ፡፡ ይሄኔም ሕይወት ካላት ልብሶች ለእነዚህ ወገኖች ልታካፍል ወሰነች፡፡ ነገር ግን የእርሷ ብቻ አስተዋጽዖ በቂ አለመሆኑን በማሰብ የቻሉ ሰዎች ያገለገሉ ጫማዎችንና አልባሳትንም ቢሆን እንዲለግሱ በፌስቡክ ገጿ ላይ ጥያቄ አቀረበች፡፡ በእርሷ ጥያቄ በርካቶች ስለተስማሙ ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ከ335 በላይ ለሚሆኑ ችግረኛ ተማሪዎች እና በጎዳና ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ልብስን እና ጫማ ለመለገስ ተቻለ፡፡ ባሕር ማዶ ያሉ የፌስ ቡክ ጓደኞቿም ‘እኛ ልብስ መላክ ባንችልም ብር መላክ ይቻለናል’ በማለት የአቅማቸውን ረዷት፡፡ “ወደ 11 ሺሕ ብር እጃችን ላይ ነበር፡፡ በዚህ ብርም ከ35 ለሚልቁ ለደጃዝማች ዑመር ሰመተር ተማሪዎች አዳዲስ ዩኒፎርም፤ አዲስ ጫማና ቅያሬ ሹራብ ገዝተን አስረከብን፡፡” በማለት በአጭር ቀናት ውስጥ በፌስቡክ አማካኝነት ለማሳካት የቻለችውን ፋይዳ ያለው ማኅበራዊ ሓላፊነት ተናግራለች፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኘችውና ሁለተኛ ዲግሪዋን በዓለም አቀፍ ግንኙነት የሠራችው ሕይወት ወንድምአገኝ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲህ ላለ በጎ ሐሳብ ጭምር ከፍ ያለ ጠቀሜታ ማበርከት እንደሚቻልበት ትናገራለች፡፡
ኢዮብ ምሕረተአብ በማኅበራዊ ሚዲያ ሰፊ እንቅስቃሴን ከሚያደርጉ የበይነመረብ ተጠቃሚዎች መካከል ይደመራል፡፡ በፌስቡክ ለበጎ ምግባር የተነሳሳበትን አጋጣሚ እንዲህ ሲል ያወሳል፡፡ ‹‹ሁል ግዜ ባገኘሁት ቁጥር አንድ ብር የምሰጠው የአእምሮ ውስንነት ያለበት የኔ ቢጤ አለ፡፡ ብሩን ሲቀበለኝ መንጭቆ ነው፡፡ ቀና ብሎም በቅጡ አያየኝም፤ እኔም ቅር አይለኝም፡፡ ለረጅም ግዜ ከአዲስ አበባ ውጪ ቆይቼ ስመለስ ግን ለዚሁ ሰው እንደተለመደው አንድ ብር ሰጠሁት፡፡ ይሄኔም ቀና ብሎ አየኝና “ጠፋህ በሰላም ነው?” አለኝ ደንግጬ “ሰላም ነኝ” አልኩት፡፡ አሁንም እደጋገመ “ጤናህ ግን ደህና ነው ወይ? በጣም ጠፋህ እኮ?” አለኝ… በዚህ ነገር ልቤ ተነካ! ከተቻለና ፈቃደኛ ከሆነ አማኑኤል ሆስፒታል ወስጄ ላሳክመው፤ ካልሆነም ብርድ ልብስና ለዝናብ ጊዜ የሚሆን የላስቲክ ልብስ ልስጠው ብዬ አሰብኩኝ፡፡” ይላል። ይሄን ክስተት ተከትሎ ኢዮብ ፌስቡክ ላይ ላሉ ጓደኞቹ ጉዳዩን በመግለጽ “የአሥር ብር የሞባይል ካርድ ቁጥር በፌስቡክ ሳጥኔ ላኩልኝ” አላቸው፡፡ ያገኘው ምላሽ ከጠበቀው በላይ ነበር፡፡ ከሀገር ውጪ ያሉ ጓደኞቹ ሁሉ “ብር በኋላ እንላክልህ” ብለውት እንደነበርና ደግነታቸው ከብዶት እንደማይፈልግ ቢያሳውቃቸውም አንዲት ጂዳ የምትኖር ልጅ ግን በግድ 500 ብር እንደላከችለት ይናገራል። “ፌስቡክ በዚህ ሁኔታ በቀላሉ አንድ ሰው መርዳት ያስቻለኝን በጎ ሥራ እንዳከናውን አድርጎኛል” ብሏል።
የፌስቡክ ዘመቻዎች
በሀገራችን ውስጥ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደው የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ መብት በእጅጉ ተሸርሽሮ ተግባራዊ መሆን አልቻለም። ከወራት በፊት በጣሊያን ሀገር ለግራዚያኒ የቆመውን ሐውልትና ሙዚየም በመቃወም ለተቃውሞ የወጡ ዜጎች አላግባብ መታሰራቸውና በዋስ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ ራሱን “ዞን 9” ብሎ የሚጠራው የአራማጆች (አክቲቪስት) እና ጦማሪዎች (ብሎገር) ኢ-መደበኛ ቡድንም “የሰላማዊ ሰልፍ መብት ይከበር” በሚል መርሕ ሦስተኛውን የበየነ መረብ ዘመቻ (ካምፔይን) አካሂዷል፡፡ ይህኛው የዞን ዘጠኝ አራማጆች እና ጦማሪዎች ዘመቻ በሀገር ውስጥ እና በውጭ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ ሲሆን አልጀዚራን የመሳሰሉ ሚዲያዎችንም ቀልብ ለመግዛት በቅቷል፡፡ ይህ ቡድን ከዚህ ቀደም ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ይከበር እና ሕገመንግሥቱ ይከበር የሚሉ በከፍተኛ ቁጥር የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተሳተፉባቸው ሁለት ዘመቻዎችንም አካሂዶም ነበር።
በግል ተነሳሽነትን ከ335 በላይ ሰዎችን ለማልበስ ያስቻለው የሕይወት ወንድማገኝ የማኅበራዊ ሚዲያ በጎ አድራጎትም ሆነ የዞን ዘጠኞች የሠላማዊ መብት ይከበር ሦስተኛ ዘመቻ በሀገራችን በአሁኑ ወቅት ያለውን የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም ከእንቶፈንቶ ወደቁም ነገርና የጋራ ጉዳይ መሸጋገሩን ለማሳየት ጥቂቱ ምሳሌ ነው፡፡
‘የዞን ዘጠኝ’ ትግሎች
ዞን ዘጠኝ ለሀገራቸው ጉዳይ ተቆሪቋሪ በሆኑ ዘመኝ ወጣቶች የተመሠረተ ነው፡፡ በቅርቡ አንደኛ ዓመቱን ያከበረው ይህ የአራማጆች እና ጦማሪዎች ኢ-መደበኛ ቡድን ማኅበራዊ ሚዲያን ለፖለቲካ፣ ለማኅበራዊ፣ ለስፖርትም ሆነ ሌሎች ዘርፎች በሚገባ በማዋል እንደ ዓይነተኛ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በምጣኔ ሀብት ላገኘው ኤርሚያስ ታዬ “ዞን ዘጠኝ የፌስ ቡክ አዋዋሌን (አጠቃቀሜን) በጥሞና እንዳስብበት እና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች ላይ እንዳተኩር ያደረገኝ ልዩ ስብስብ ነው፡፡” በማለት አድናቆቱን ሲገልጽላቸው በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ውስጥ ፕሮጀክት ማናጀር ሆና የምትሠራው ኢየሩሳሌም በበኩሏ ‘ወጣቱ ለሀገሩ አያስብም ሱሰኛ ነው’ እየተባለ በሚወነጀልበት በዚህ ወቅት በራስ ተነሳሽነት በተለይ ፖለቲካዊ ርእሶችን በጡመራ መድረካቸው ያለፍርሃት በማንሣት ለውይይት ማቅረባቸው ያስመሰግናቸዋል ትላለች፡፡
የዞን ዘጠኝ አባላት በቀዳሚነት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከኢ- መደበኛ ቡድኑ አባላትም ሆነ ሌሎች ጸሐፍት የደረሳቸውን መረጃዎችና ጽሑፎች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታይ በታገደው ጦማራቸው በየጊዜው ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ ውጪም በየሦስት ወሩ የበየነ መረብ ላይ ዘመቻን በማካሔድ የአራማጅነት ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ ቡድን በተመሠረተ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በትምህርት፣ በመጻሕፍት፣ በሃይማኖት እና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በድምሩ ከ150 በላይ ሰፊ ትንታኔ የታከለባቸው ጽሑፎችን ለንባብ አብቅቷል፡፡ በዞን ዘጠኝ ድረ ዓምባም ሆነ በአባላቱ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተለቀቁትን መረጃዎች በአማካይ ከ300 ሺሕ በላይ ሰዎች ጋር ለመድረስ የቻለ ነበር፡፡
ከዞን ዘጠኝ አባላት መካከል አንዷ የሆነችው ማኅሌት ፋንታሁን ከአዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ተመርቃ ሥራ ላይ ትገኛለች፡፡ “በዞን ዘጠኝ ውስጥ የተሰባሰብነው አባላት ከተለያዩ የትምህርትና የሙያ ዘርፎች የተውጣጣን በመሆናችን አንዳችን ከሌላችን የተማማርነው ብዙ ነገር አለ፡፡ በተለይ በግሌ የማላውቀውን ለማወቅ፣ የማልችለውን ለመቻል ምን ማድረግ እንዳለብኝ ተረድቻለሁ፡፡” ትላለች።
ጆማኔክስ ካሣዬ የተባለው ሌላኛው የዞን ዘጠኝ መሥራች በበኩሉ ‹‹ዞን ዘጠኝ በግሌ ምናባዊ የነበረውን ነገር መሬት ላይ እንዳወርደው፣ እንዲሁም በፍርሐት በተጠፈርንበት ሰዓት ከሚደፍሩ ልበ ሙሉዎች ጋር አንድ መሆን፣ ከምንም በላይ ከማንም ጋር ካልወገኑ ነገር ግን ያገባኛል ባዮች ጋር መጎዳኘቴና ይሄም የእኛ ስሜት ወደሌሎች እንዲጋባ ማድረግ መቻሌ ያስደስተኛል” ብሏል።
ሁለተኛ ዲግሪውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ሕግ በመሥራት ላይ የሚገኘው ሌላኛው የዞን ዘጠኝ አባል ዘላለም ክብረት በበኩሉ “የዞን ዘጠኝ አባል በመሆኔ ሐሳቤን በተደራጀ መንገድ የምገልጽበት መድረክ አግኝቻለሁ፡፡ በተጨማሪም ከቡድኑ አባላት ጋር በማደርገው ውይይት ሐሳቤን አዳብር ዘንድ አግዞኛል” በማለት ያገኘውን ጥቅም ይገልጻል፡፡
የዞን ዘጠኝ እና ሌሎችም ጦማሮች መታገድ
የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ባገኙ እና በመሥራት ላይ በሚገኙ ወጣቶች የተመሠረተው ዞን ዘጠኝ በተቻለ አቅም ጽንፍ የያዙ ሐሳቦችን ላለማስተናገድ ጥረት ቢያደርግም በሀገር ውስጥ እንዳይታይ መታገዱ (block) መደረጉ አልቀረም፡፡ ማኅሌት ፋንታሁን “መንግሥት በሀገራችን እንዲዘጉ የሚያደርጋቸው ብሎጎች ወይም ድረ ዓምባዎች በፖለቲካ ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑም መንግሥት የሀገራችን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ማኅበረሰቡ በነጻነት እንዲወያይ፣ መረጃ እንዲያገኝና ብሎም እንዲያካፍል አለመፈለጉን ያሳያል፡፡” በማለት ሐሳቧን ስትገልጽ ጆማኔክስ በበኩሉ “በራስ ፍቅር መውደቅ በራስ ብቅል እንደመስከር ነው፡፡ በፕሮፓጋንዳ ከሚያደነቁረው ኢቴቪ ውጭ እንዳይታይና እንዳይሰማ ማድረግ ሕዝብን ከመናቅና በራስ ካለመተማመን የሚመነጭ ነው፡፡” በማለት የመንግሥትን እርምጃ ይኮንናል፡፡ ሌላኛው የቡድኑ አባል ዘላለም ደግሞ “ጦማራችን መዘጋቱ በሀገር ውስጥ ያለንን ተደራሽነት በጣም እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡” በማለት የዕገዳውን ቅጽበታዊ ውጤት ካወሳ በኋላ በተለይ በመንግሥት በኩል ድረ ገጾችንና የጡመራ መድረኮችን በምን መልኩ እንደሚዘጋ ግልጽ ፖሊሲ የሌለው መሆኑ “እስከ አሁን ድረስ ወደ አምስት የሚጠጉ የቡድኑ የጡመራ መድረኮች ተዘግተዋል፡፡” በማለት ቅሬታውን ይገልጻል፡፡
በሕግ ሁለተኛ ዲግሪውን የሚሠራው ዳንኤል ብርሃነ የተባለ ጦማሪ ደግሞ ‹‹በየትም ሀገር የጡመራ መድረክን መዝጋት የተለመደ ነው፡፡ የእኛ ሀገሩን የተለየ የሚያደርገው ዘጊው አካል በግልጽ አለመታወቁ ነው፡፡››በማለት ከጡመራ መድረኮቹ መታገድ ይልቅ አዘጋጉ አሳሳቢ መሆኑን ያወሳል፡፡ ለአብርሃም ደስታ ግን የጡመራ መድረኮችን ማገድ ዜጎችን ማፈን ነው፡፡
የ ‘ድምፃችን ይሰማ’ ድምፆች
ድምፃችን ይሰማ የተሰኘው የፌስቡክ ቡድን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በበርካታ ክፍለ ሀገራት እና በውጭ ሀገራትም ጭምር ከ20 በላይ ቡድኖች አሉት፡፡ የቡድኑ አባላት “ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የመንግሥትን የሃይማኖት ጣልቃ ገብነትን የምንቃወምበት ድምፅ” በሚል የሚገልጹት ይህ የፌስቡክ ገጽ ከተመሠረተ ከአንድ ዓመት በላይ ሲሆነው፤ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ ሰፊ መረጃዎች እየቀረቡበት ይገኛል፡፡ የተጀመረው የሰላማዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴ መረጃዎችና ትእዛዛት በፌስቡክ የሚተላለፉ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይ በክልሎች ሰፊ ቅርንጫፎች አፍርቷል። ድምፃችን ይሰማ ከወልዲያ፣ ድምፃችን ይሰማ ከጅማ አባጅፋር፣ ድምፃችን ይሰማ ከመቂ በሚሉት የፌስቡክ መለያዎች ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሠላማዊ መንገድ ድምፃቸውን በስፋት በማሰማት ላይ ናቸው መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ የቡድኑን አባላት በፌስቡክ ገጻቸው አማካኝነት ለማናገር ያደረግነው ሙከራ ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ የቡድኑ እንቅስቃሴ ግን በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚካሔዱ የአራማጅነት እንቅስቃሴ ዓይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሳ የሚችል ነው፡፡
ፌስ ቡክ ከእንቶፈንቶ ወደ ቁምነገር
ዳንኤል ብርሃነ የሶሻል ሚዲያ ዋናው ፋይዳ በሀገራችን የሌለውን የመወያየት ባሕል ለማሳደግ መርዳት ነው ይላል፡፡ “በእኛ ሀገር በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዲሞክራሲያዊ መስተጋብር የለም። በሶሻል ሚዲያ አማካኝነት ግን አንድ ተራ የሃይስኩል ተማሪ ትልቅ ማኅበራዊ ቦታ ከሚሰጠው ሰው ጋር በእኩልነት ሲመላለስ ታያለህ፡፡” በማለት በሶሻል ሚዲያው አማካኝነት የመጣውን አዲስ የውይይት ዕድል ይጠቁማል። ‘አንተ አታውቅም ዝም በል’ የሚል ዓይነት ያልተገባ አካሔድ ባለበት ማኅበረሰብ እንዲህ ዓይነቶቹን አካሔዶች በመግታት የባሕል ለውጥ ለማምጣት ማኅበራዊ ሚዲያ የላቀ ሚናን ለመጫወት እንደሚችልም ይናገራል፡፡
አብርሃ ደስታ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ዩንቨርስቲ (ዩኒሳ) የሦስተኛ ዲግሪውን (ፒኤች ዲ) እየተከታተለ የሚገኘው አብርሃ በተለይ ህወሓትን በፌስቡክ ገጹ በመተቸት ይታወቃል፡፡ “እኔ ፌስ ቡክን ከመቀላቀሌም በፊት በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ የማነሳው ለየት ያለ ሐሳብ አይወደድም ነበር፡፡” በማለት የፌስቡክ ተጠቃሚ ስለሆነ ብቻ በመንግሥት ላይ የተቃውሞ ሐሳቦችን መሰንዘር እንዳልጀመረ የሚናገረው አብርሃ “የማነሳቸው ሐሳቦች የተለዩ በመሆናቸው በውድድር ለጓደኞቼ የሚሰጠውን ዕድልን እኔ ስነፈግ ቆይቻለሁ” ይላል። በፌስቡክ መለያው የሚያንጸባርቃቸው ሐሳቦችም ከዚሁ እውነታ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ በግሉ ሶሻል ሚዲያው የፈጠረለትን ዕድል ሲያወሳም “እኔ በፖለቲካ ስብሰባ ላይ የማነሳቸው ሐሳቦችን ስለማይወደዱ የመናገር ዕድል እንኳን አይሰጠኝም፡፡ ከዚህ ባለፈም የተለየ ሐሳብ በማንጸባረቄም ‘ተማሪዎችን ያበላሻል’ እየተባልኩ እወቀሳለሁ፡፡ አሁን ግን ያመንኩበትን ሐሳብ የማንንም ፍቃድ መጠየቅ ሳያስፈልገኝ በሶሻል ሚዲያው በነጻነት ለማራመድ ችያለሁ፡፡” ይላል።
የዞን ዘጠኝ አባሏ ማኅሌት በበኩሏም “ማኅበረሰቡ ከሚነቃባቸው መንገዶች አንዱ ሐሳብን መግለጽ እና መወያየት መቻል እንዲሁም መረጃን በወቅቱ ማግኘት ነው፡፡ በሃገራችን ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በተለያዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩና ሃሳባቸውን መግለፅ እንዲችሉ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም መረጃዎችን በፍጥነት ለኅብረተሰብ በማድረስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡” በማለት የማኅበራዊ ሚዲያ ጥቅምን ትገልፃለች፡፡
ዘላለም በበኩሉ “ማኅበራዊ ሚዲያ በራሱ ለውጡን ካለበት ይዞልን ይመጣል ማለት ከባድ ቢሆንም እንደ የለውጥ መድረክነት በመሆን ግን ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡” በማለት የማኅበራዊ ሚዲያውን የለውጥ እርሾነት ይናገራል፡፡ “የተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮችና ብዙ የፖለቲካው ተዋናዮች ፌስቡክን በመሳሰሉ የማኅበራዊ ሚዲያዎች በብዛት መታየታቸውና ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው ሚዲያው የለውጡ አጋዥ መድረክ በመሆን እንዲያገለገል አድርጎታል የሚል እምነት አለኝ፡፡” ብሏል።
“የመንግሥት እርምጃ አፈና ነው”
በኢትዮጵያ በየነ መረብ ላይ ያለውን የመንግሥት ቁጥጥር በስፋት ያጠናው “ኦፕን ኔት” የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም በተለይ ፖለቲካዊ ሐሳቦችን በበይነ መረብ መግለፅ በሀገሪቱ ውስጥ በስፋት የሚገደብ መሆኑን ያትታል፡፡ ኦፕን ኔት ኢኒሺየቲቭ በመስከረም ወር ለጥናቱ ተሳታፊ ፍቃደኞች በልዩ ሁኔታ የተዘጋጁ ሶፍትዌሮች በማከፋፈል ባደረገው ጥልቅና ቴክኒካዊ ተግባራዊ ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ድረ ዓምባዎች ሆን ተብለው እንዲዘጉ መደረጋቸውን ደርሶበታል፡፡ በተለይ እንደ ethiox.com ያሉ ነፃ ሐሳቦችን የሚያንሸራሽሩ ድረ ዓምባዎች መዘጋታቸው ይህን ተቋም በእጅጉ ማስገረሙ አልቀረም፡፡
የግንቦት 7 አባላት ፎቶዎች ለስለላ ሶፍትዌሮች
የኢትዮጵያን መንግሥት በበየነ መረብ ነፃነት ረገድ ክፉኛ እያሳማ ያለው ጉዳይ የተለያዩ የፖለቲካ አስተያየት መሰንዘሪያ የሆኑትን የጡመራ መድረኮችና ድረ ዓምባዎችን መዝጋቱ ብቻ ሳይሆን ባልተጠበቀ መልኩ የግንቦት 7 አባላትን ፎቶዎች በመጠቀም የስለላ ሶፍትዌር (ስፓይዌር) በበየነ መረብ ተጠቃሚ ሰዎች ኮምፒዩተር ላይ በድብቅ ያስቀምጣል ይባላል፡፡ ‘Finspy’ የሚል መጠሪያ ያለው የስለላ ሶፍትዌር በኢትዮጵያ በጥቅም ላይ መዋሉን ይፋ ያደረገው “ሲቲዝን ላብ” የተሰኘው ተቋም ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ሶፍትዌር አለመገዛቱ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው፡፡ በጀርመን ሀገር የሚሠራውን ይህንኑ ሶፍትዌር የተቃዋሚ ድምፆችን ለማዘጋት ሆን ተብሎ በጥቅም ላይ መዋሉን የሚናገሩት ቶሮንቶ እና በርክሌይን በመሳሰሉ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች የሚገኙ ምሁራን ግን ድርጊቱን በጽኑ አውግዘውታል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ለውጥ ይመጣ ይሆን?
በሀገራችን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ከፍ እያለ መምጣቱ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ማኅበራዊ ሚዲያ ምን ዓይነት ለውጥን ሊያመጣ ይችላል የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ነው፡፡ ዳንኤል ብርሃነ ‹‹በማኅበራዊ ሚዲያ የሚከሰቱ ለውጦች አሉ፡፡ ነገር ግን እንደ ግብጽ ዓይነት አብዮት በኢትዮጵያ በጭራሽ የሚሆን አይደለም፡፡›› ሲል ይደመድማል፡፡ ማኅሌት ፋንታሁን በበኩሏ ‹‹ማኅበራዊ ሚዲያ በእርግጥም ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ እስካሁን የተጠቃሚው ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም የተለያዩ ሐሳቦች እየተነሡ እየተንሸራሸሩበትና መረጃዎችም እየተሰራጩበት ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ የተጠቃሚው ቁጥር ሲበዛ አሁን ከምናየው የበለጠ የነቃ ማኅበረሰብ መፈጠሩ አይቀሬ በመሆኑ ለውጥ ይኖራል፡፡›› ትለለች፡፡ ጆማኔክስ በበኩሉ ‹‹ከነውጣ ውረዱም ቢሆን በማኅበራዊ ሚዲያ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡›› ሲል ይደመድማል፡፡ ‹‹ፌስቡክን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች እንደ ተወስኦ መድረክ (Discourse Sphere) በመሆን የለውጡ አካል መሆን እንደሚችሉ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን የኢንተርኔት ተጠቃሚነት (Internet Penetration) ደካማ መሆን የዚህ ለውጥ ዋነኛ ማነቆ ሊሆን ይችላል፡፡›› በማለት ሐሳቡን የሚገልጸው ዘላለም በበኩሉ ‹‹አሁን ካለው ትንሽ የተጠቃሚነት ቁጥር ላይ መንግሥት ያለምንም ግልጽ ፖሊሲ ድረ አምባዎችንና ጦማሮችን ሲብስም ማኅበራዊ ድረ ገጾችን መዝጋቱ የለውጡን ሂደት እጅግ ያከብደዋል፡፡ ነገር ግን የማኅበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሚ ቁጥር እየጨመረ መምጣት ሰዎች በተለያየ መንገድ ሐሳባቸውን የሚገልጹበት ሁኔታ በመፍጠሩ ብሎክ በማድረግ ሐሳብን ማሰርና ለውጥንም ማዘግየት እንደማይቻል እያሳየ ነው፡፡›› ሲል ሐሳቡን ደምድሟል፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያው የመተንፈሻ ቀዳዳ በመሆን ፕሬሱን እየተካው ነው የሚለው የሚዲያ ባለሙያው መስፍን ኅሩይ “በሀገሪቱ የሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔቶች በመንግሥት ጫናና በኅትመት ዋጋ ውድነት ከገበያው ሲወጡ አዘጋጆቹን ጨምሮ ብዙዎቹ በዚያ ያጡትን መድረክ በማኅበራዊ ሚዲያው በማግኘት በተሻለ ተደራሽነት ስሜታቸውን እንዲገልጹ አስችሏቸዋል” ብሏል። እንደመስፍን ገለጻ መንግሥት ጠንከር ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን እየተከታተለ መዝጋቱ የምትከፈተዋን ማንኛዋንም የመተንፈሻ ቀዳዳ በመድፈን ውጥረቱን ከማባባስና ከማፈንዳት በተለየ የሚያመጣለት ጥቅም የለም” ይላል።
በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በሀገሪቱ በልማት፣ በማኅበራዊም ይሁን በፖለቲካ ረገድ በጎ ለውጦችን ማምጣት ይቻላል፡፡ አሁን አሁን የእነዚህ ለውጦች ምልክቶች በአደባባይ እየታዩ ነው፡፡ ይሄን መልካም ዕድል በሚገባ ለመጠቀም በነጻ ሐሳብ መንሸራሸር የሚያምን መንግሥት ያስፈልጋል፡፡ እንዲያ ካልሆነ ግን የተገፉት የለውጥ ድምፆች የመጨረሻ ማረፊያቸው አይታወቅም፡፡
አዲስ ጉዳይ መጽሔት፡ ማኅበራዊ ሚዲያ ፕሬሱን እየተካ ይሆን?
Latest from Blog
ሀገሪቱ እኮ የለችም…. የጄነራሎቹ ጉድ…. የአብይ አህመድ ነገር…
ሀገሪቱ እኮ የለችም…. የጄነራሎቹ ጉድ…. የአብይ አህመድ ነገር…
ዓለም ሁሉ ያስደነቀው ሚልዮኖች የተመለከቱት አስደናቂው ቪድዮ| Ethiopian Orthodox Mezmur
ዓለም ሁሉ ያስደነቀው ሚልዮኖች የተመለከቱት አስደናቂው ቪድዮ| Ethiopian Orthodox Mezmur
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤ 15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን
ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር
የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!” አቶ ቡልቻ ደመቅሳ
ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ
ሀገሪቱ እኮ የለችም…. የጄነራሎቹ ጉድ…. የአብይ አህመድ ነገር…ሀገሪቱ እኮ የለችም…. የጄነራሎቹ ጉድ…. የአብይ አህመድ ነገር…ሀገሪቱ እኮ የለችም…. የጄነራሎቹ ጉድ…. የአብይ አህመድ ነገር…
ሀገሪቱ እኮ የለችም…. የጄነራሎቹ ጉድ…. የአብይ አህመድ ነገር…
ቴዲ አፍሮና ጃዋር መሐመድ፤ ”ንጉሥ አንጋሹ ፖለቲከኛ” የዘመኑ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆነው ጃዋር መሐመድ ‘አልፀፀትም’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን መጽሐፍ 🔴What separates Jawar and Abiy is their measure of how much non-Oromos
ቴዲ አፍሮና ጃዋር መሐመድ፤ ”ንጉሥ አንጋሹ ፖለቲከኛ”
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ
ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )
“ገብርዬ ነበረ የካሳ ሞገሱ…..” በጋዜጠኛ እና መምህርት መስከረም አበራ አብይን የሚያንዘፈዝፉት የእንስቷ ንግግሮች አድምጡት