ትርጉም – ይነጋል በላቸው
ዶር. በያን አሶባ
ውድ ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሣ /ቶለሣ
በስሜ አድራሻ የላኩት ግልጽ ደብዳቤ በበርካታ ድረ ገፆች በወጣበት ወቀት እኔ ጉዞ ላይ ነበርኩ፡፡ በዚያም ምክንያት ወዲያውኑ መልስ መስጠት በምችልበት ሁኔታ ላይ አልነበርኩም፡፡ በዚህ በምጽፍልዎ የደብዳቤዎ ምላሽ እኔን ስለሚመለከቱ ነጥቦች ብቻ አነሳለሁ፡፡ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግምባር ስለአጠቃላዩ የደብዳቤዎ ይዘት መልስ ይሰጥዎታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ውድ ዶክተር ፍቅሬ
አስተያየቴን መጀመር የምፈልገው በዚህ ግልፅ ደብዳቤዎ የአያትዎን ስም እንዴት ሊጨምሩ እንደፈለጉና ይህ ያልተለመደ አካሄድ ያጫረብኝን ስሜት በማስቀደም ነው፡፡ አቅም በፈቀደ በርካታ የጽሑፍ ሥራዎችዎን ለመመልከት ሞክሬ ሁሉም ‹ፍቅሬ ቶሎሣ› እንደሚሉ አረጋግጫለሁ፡፡ ይህም አያትዎን ያለመጨመር የአጻጻፍ ይትበሃል እ.አ.አ በ1983 በብሬመን ዩኒቨርስቲ ለዶክትሬት ዲግሪዎ ማሟያ ያቀረቡትን ጹሑፍ ጨምሮ በሌሎች በርካታ ተከታታይ ጽሑፎችዎ አልተስተዋለም፡፡ በፌስቡክዎም የአያትዎ ስም አልተገለጸም፡፡ .እኔ እስከማውቀው ድረስ የራስዎን ስም ፍቅሬ ቶላሣ (Tolassa, not ከዚህ በፊት ይጠቀሙበት ነበር እንደሚባሉት Tolossa!) ብለው መጻፍ ብቻ ሣይሆን ‹ጂግሣ› የሚለውን የአያትዎን ስም ተጠቅመው የጻፉት በዚህ ግልጽ ደብዳቤዎ ብቻ ነው፡፡
እርስዎም እስካሁን ወደጎን ትተዋቸው እንደነበረው ሁሉ አሁን ‹ጂግሣ›ን ባሉበት እንዲያርፉ ለቀቅ እናድርጋቸውና አዘውትረው በሚጠቀሙበት ቶሎሣ/ቶለሣ በሚለው የአባትዎ ስም ላይ ትኩረታችንን እናውል፡፡ ‹ቶሎሣ› የሚለው ስም ‹ቶሎ› ከሚለው የአማርኛ ቃል ተወስዶ ኦሮምኛ እንዲመስል ‹ሣ›ን በመጨመር የተበጀ ቃል ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ በሌላ በኩል ‹ቶላሣ› ከኦሮምኛው ‹ቶላ› የተገኘ እንደሆነ በርግጠኝነት ዐውቃለሁ፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ስምዎን በሁለት መንገድ እየጻፉ ሁለት ተቃራኒ ማንነቶችን ለመላበስ መፈለግዎን መረዳት አይገድም፡፡ ይህን በማድረግ በአማራነትና በኦሮሞነት የማንነት አጥር ላይ ፊጥ ማለት ተመኝተው ከሆነ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልዎ፤ በአራዶች አነጋገር ‹ይመችዎ!›፡፡ ሊሆኑት ወይም ሊጠሩበት በሚፈልጉት ስምም ይሁን ማንነት የመጠራት መብትዎን ሙሉ በሙሉ አከብራለሁ፡፡
የኔ ጥያቄ ይሄውልዎ፡- እኔ የርስዎን የፈለጉትን የመሆንና በፈለጉት የመጠራት መብት ሳከብርልዎ ለኔስ ይህን መብት ለምን ይነፍጉኛል? ስሜ Bayyanaa Suba አይደለም፡፡ ስሜን ‹Beyan Asoba› ከሚለው ውጪ በሌላ መልክ በፍጹም ጽፌ አላውቅም፡፡ ይህ የሰጡኝ አዲስ ስያሜ አባል የሆንኩበትን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግምባርን በአንድ ወይ በሌላ መልክ ለመንካት ካልሆነ በስተቀር እኔን በተመለከተ ያወጡልኝ ስም ሊሆን ይችላል ብዬ መቀበል ያቅተኛል፡፡ በግልጽ እንደሚገባኝ ለፖለቲካዊ ዓላማዎ ሲሉ ይህን አዲስ ስም ፈልስፈው ለኔ የሰጡኝ ይመስለኛል፡፡
ለፍጡሮቻቸው ስም ማውጣት የሚቻላቸው ፈጣሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ወላጆች ለልጆቻቸው የተለያዩ ስሞችን እንደሚያወጡ ሁሉ የመኪና ፋብሪካዎችም ለምርቶቻቸው የተለያዩ ስሞችን ይሰጣሉ፡፡
እንደመጥፎ ዕድል ሆኖ ለኛ ለኦሮሞ ሴቶችና ወንዶች ልጆች የስቃይና የውርደት ምክንያት ሆኖ አበሣና መከራ ያሳየን የነበረው የሕይወት መሪር ተሞክሯችን ስማችንን እንድንቀይር ትምክህተኞች (አማሮች?) ያደርጉብን የነበረው ጫና ወይም የማስገደድ ተግባር ነው፡፡ ኦሮሞ የሚለው ብሔራዊ መጠሪያችን ከማንኛውም መዝገብ ተፍቆ በርካታ አንቋሻሽ የፍካሬ ትርጉሞች በተለጣጠፉለት ስያሜ እንድንጠራ ተገድደን ነበር፡፡ ተማሪ ልጆቻችን ሳይቀሩ የተዋጣለት ኢትዮጵያዊ መሆን ይችሉ ዘንድ ስሞቻቸውን (ወደ አማራ ስሞች) እንዲቀይሩ በመምህሮቻቸው የሚገደዱበት ሁኔታም ነበር፡፡
በዚያች ሀገር ውስጥ ዋናው የፖለቲካ ማጠንጠኛ ግለሰቦች በቅድሚያ ኦሮሞነታቸውን፣ ሲዳማነታቸውን፣ ወላይታነታቸውን፣ ከምባታነታቸውን፣ ሃዲያነታቸውን ወዘተ. እንዲገድሉና በውጤቱም ኢትዮጵያዊ የሚባል የጋራ ማንነት መገለጫ እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኦሮሞነትና ኢትዮጵያዊነት አብረው ሊሄዱ ካልቻሉ ምርጫው ሁለት ነው፤ አንድም የእርስዎን ኢትዮጵያዊነት ባፍንጫችን ይውጣ ብለን መተው፣ አለበለዚያም በነበረው አካሄድ ነጻነትን ተነጥቀን እንደጥንቱ እያለቀስንና እየተሰቃየን መኖር፡፡
ለእርስዎና መሰሎችዎ በሚገባ ግልጥ አድርጌ ልነግራችሁ የምፈልገው አንድ ነገር አለኝ፡፡ ያም ኦሮሞዎች ማንነታቸውን ክደው በሚጣልባቸው የራሳቸው ያልሆነ ማንነት የሚንበረከኩበት ጊዜ አልፏል ወደፊትም አይመጣም፤ በዚህ ዕርማችሁን አውጡ፡፡ ኦሮሞነትን የሚጋፋ ኢትዮጵያዊነት አንቀበልም፤ ይህ ኢትዮጵያን ከኦሮሞ የማስቀደም አካሄድ እስካልቀረ ድረስም ትግላችን ይቀጥላል፡፡ ምርጫው የእርስዎና የቢጤዎችዎ ነው፡፡ እኛን ከነኦሮሞነት ማንነታችንና ከሌሎች ተዛማጅ መብቶቻችን ሙሉ በሙሉ መከበር ጋር ትቀበላላችሁ ወይም ከአደንቋሪ የኢትዮጵያዊነት ስብከታችሁና ከኢትዮጵያ አንድነታችሁ ጋር ጥንቅር ብላችሁ ልትቀሩ ትችላላችሁ፡፡ በኦሮሞዎች መቃብር ላይ፣ በሲዳማዎች መቃብር ላይ፣ በወላይታዎች መቃብር ላይ፣ በከምባታዎች መቃብር ላይ፣ በሃዲያዎች መቃብር ላይ፣ ወዘተ. የኢትዮጵያን አንድነት ለመገንባት ሲቋምጡ አንድ ዓይነት የሞራል ጉድለት አይታየዎትም ይሆን? ይህ ዓይነቱ ጉዞ መጨረሻው የማያምርና ከቆመለት ዓላማ የተለዬ መጥፎ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል መገንዘብ እንዴት አቃተዎት? ይህ ዓይነቱ ኢምክንያታዊና ኢሞራላዊ የጥፋት መንገድ በመጨረሻው ስክነትንና ማስተዋልን ተላብሶ የሁሉንም በግዛቲቷ የሚኖሩ ወገኖች ፍላጎት ባማከለ ሁኔታ ሁሉንም የሚወክል ማንነት እንደሚያብብ ታላቅ ተስፋ አለኝ፡፡
በመጨረሻም በዚህ ራስ ምታት የሚለቅ አስቸጋሪ ጉዳይ ዙሪያ ይህ የአጸፋ መልሴ የመጀመሪያየም የመጨረሻየም እንደሆነ ልገልጽልዎ እወዳለሁ፡፡
በያን ኤች አሶባ (Beyan H. Asoba 5/29/13)
ከ‹ተርጓሚው› የተሰጠ አጭር አስተያየት
1. በአማርኛ ለተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ በእንግሊዝኛ መልስ መጻፍ ምን ማለት ነው? ዶክተሩ ከጋና ነው ወይንስ ከእንግሊዝ የተገኙት? እዚሁ ከቅኝ ገዢዋ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተፈጠሩ ይሆን? (ኢሣይያስና መለስ ነፍሳችሁ አይማር – ጥቁር ውሻም ውለዱ!) ዶክተር በያን ከአማርኛና ከእንግሊዝኛ የትኛውን አጣርተው ሊናገሩ ዌም ሊጽፉበት እንደሚችሉ በእንግሊዝኛ በጻፉት መልሳቸው በውል ተረድቻለሁ፤ ታዲያ አማርኛ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ለመግለጽ አውሮፓና አሜሪካ ድረስ ሄደው ለምን ትዝብት ውስጥ ይገባሉ?
2. የኢሣት የተለያዩ ባንዲራዎችን በኢትዮጵያ ስም ማስተናገድ ምን ማለት ነው? በጣም ይታሰብበት፤ በልክ ያልተያዘ ፍቅርና ጥላቻ መዘዝ አለው፡፡ ስንወድም ስንጠላም፤ ስንቀርብም ስንርቅም በምክንያት ይሁን እንጂ በስሜት አይሁን፡፡ የኢትዮጵያ ባንዲራ እንኳንስ ለአንድ ሕዝብ ለመላው ዓለም በቅቷል – የሌሎች ሀገራትን በተለይም የአፍሪካውያንን ባንዲራዎች ተመልከቱ፡፡ እኛ የምንጸየፋትን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ባንዲራ ከእኛ እየኮረጁ በተለያየ አቀማመጥ ይጠቀሙባታል፤ ነፈዞች ደግሞ የገዛ ባሏን የጎዳች መስሏት ገላዋን በጋሬጣ እንደሸነተረችው ሞኝ ሚስት እየሆኑ ያስቁን ይዘዋል፡፡ አትለማመጡዋቸው፤ ይልቁንስ የራሳችንን ሥራ እንሥራ፤ እውነትና ግልጽነት ያልተገባ ይሉኝታንና ፍርሀትን ያስወግዳሉ፡፡ እውነቱን ልባችን እያወቀው አንደበታችን በሀሰት ማባበልን ይተው፡፡ ለየትኛው ጊዜ…
የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁንልኝና በዚህ ጉዳይ ሰፋ ባለ ሁኔታ እመጣበታለሁ፡፡ በየወንዙ እንደሚማማል የማይተማን ጓደኛ ለማያዛልቅ ስትራቴጂ አንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በአካል የተቀመጡ መስለው በምናብ ግን ተራርቀው መቀመጥ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ እያፈረሱ ግንባታ የለም፤ እየጠሉ አንድነት የለም፤ የሚጸየፉህን ልመናና ልምምጥ የለም፡፡ የደነዘ አስተሳሰብ በምንም ዓይነት ሣሙና ቢታጠብ አይነጻም፡ ዐውቆ የተደበቀን ቢጠሩት አይሰማም፡፡ በጠላት ተቀፍቅፎ በበጎች ጋጣ ውስጥ የመሸገ ቀበሮና ተኩላ በልምምጥና እውነትን በመሸፈን በሚደረግ ልመና በረቱን ለቅቆ አይወጣም፤ የነገ ሰው ይበለን፡፡