May 24, 2013
6 mins read

የቶሮንቶ ኢትዮጵያዊያን የዜጎችን መፈናቀል አወገዙ፤

Toronto ethiopian 3

By Tekelmichael Abebe

ብሄርን መሰረት ያደረጉ መፈናቀሎችንና ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ ሰብአዊ ግፎችን ለመዋጋትም ቃል ገቡ

በቶሮንቶና አካባቢዋ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን፤ በኢትዮጵያ በተለያየ ስፍራ የሚደረገውን ብሄርን መሰረት ያደረገ መፈናቀልና ሀይማኖትን የዘመረኮዘ የሰብአዊ መብት ገፈፋ በጽኑእ አወገዙ።
ባለፈው እሁድ ሜይ 19 ቀን ብሉር መንገድ ላይ በሚገኘው በትሪኒቲ ቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን አዳራሽ፤ በሁለቱ ዋና ዋና ሀይማኖት መሪዎች አስተባባሪነት በተደረገው ስብሰባ ላይ፤ ተሰብሳቢዎቹ በያዝነው ግንቦት ወር ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግና ጉዳዩን ለአለም መንግስታት ለማሳወቅም ወስነዋል።
በዚህ፤ ከአጼ ሀይለስላሴ ዘመን ጀምሮ በሕዝብ እንደራሴነትና በተለያዩ ሀላፊነት ኢትዮጵያን ሲያገለግሉ የቆዩት ሀጂ መሀመድ ሰይድ በምክትል ሊቀመንበርነት፤ እንዲሁም በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ ቃል አቀባይ፤ ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ፤ በሊ/መንበርነት የሚመሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮችን የያዘው ስብስብ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ፤ የስብስቡ ምክትል ሊ/መ ሀጂ መሀመድ ከህመማቸው እንዲፈወሱ ጸሎት በማድረግ ተጀምሮ፤ ሶስት ሰዓታት ያህል በመምከር፤ በወቅቱ አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሀሳቦችን አሳልፏል።
የስብሰባው ሊቀመንበር ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ባደረጉት የመግቢያ ንግግር፤ ፖለቲካ ውስጥ አንገባም የሚሉ ሰዎች ሰዎች መሆናቸውን እንደሚጠራጠሩ፤ ክርስትናም ከፖለቲካ ጋር ተቃርኖ እንደሌለው፤ እንዲያውም፤ ክርስቶስም ይሁን ነቢያትና ሀዋርያት ነጻነትን እንደሰበኩና፤ የዚህ ዘመን ክርስቲያኖችም ነጻነታቸውን ለማስከበር ከመታገል ወደሁዋላ ማለት እንደሌለባቸው ተናግረዋል።
ሊቀ ካህናት ጨምረውም፤ ቤተክርስቲያን የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ እንደማትታገል፤ እንዲሁም ማናቸውንም የፖለቲካ ቡድኖች ወይንም ፓርቲዎች ለይታ እንደማትደገፍ፤ ይሁን እንጂ ለነጻነት የሚደረግን ትግል የመምራት የሞራል ግዴታ እንዳለባት፤ ለነጻነት ትግል የሀይማኖት ተቋማትና ተከታዮቻቸው ቀዳሚ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ወደወቅታዊው አንገብጋቢ የአገር ጉዳይና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማድረግ ስለሚገባቸው ነገር ሲናገሩም፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር የሚቀረፈው የስርአት ለውጥ ሲመጣ እንደሆነና ሁላችንም ለዚያ ዓላማ መሳካት በትጋት መስራት እንዳለብን አሳስበው፤ እስከዚያው ግን ይሄንን የመከራ ግዜ በድርጅትና በሀይማኖት በብሄርና በግል ጸብ ሳንለያይ በአንድነት መጋፈጥ አለብን ሲሉ መክረዋል።
ከረጅም ውይይት በሁዋላም ከክርስቲያኖችና ከሙስሊሞች፤ ከሴቶች እንዲሁም ከፖለቲካ ድርጅቶች የተወጣጡ 13 አባላት ያሉበት የቶሮንቶ ኢትዮጵያዊያንን የሚያስተባብር ግብረ ሀይል ተቋቁሟል።
ተሰብሳቢው ህዝብ፤ ይህ ግብረ ሀይል፤ በቀጣዩ አንድ ወር ውስጥ፤ ሶስት አበይት ስራዎችን እንዲያከናውን ሀላፊነት ሰጥቶታል። አንደኛ በካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ የሚካሄድ የተቃውሞ ስልፍ እንዲያዘጋጅ፤ ሁለተኛ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ለካናዳ መንግስት የሚቀርብ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያሰናዳ፤ ሶስተኛም ለተጎዱት ወገኖች የገንዘብ ማሰባሰብ የሚደረግበት መንግድ እንዲጠና ወስኗል።
ከአፋር እስከቤኒሻንጉል፤ ከጅጅጋ እስከ ጉራፈርዳ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰውን መፈናቀልና ሰቆቃ በጽኑ ያወገዘው ስብሰባ፤ በሜይ 25 በኢትዮጵያ የሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ ለጠራው ሰልፍ ጥቁር ልብስ በመልበስ አጋርነቱን ለማሳየትም መግባባት ላይ ደርሷል።

ከቶሮንቶ ካናዳ ለተጠናከረው ዘገባ፤ ሀብታሙ ስለሺ

Previous Story

ግልጽ ደብዳቤ ለዶ/ር በያና ሱባ (የኦዴግ አመራር) – ከዶ/ር ፍቅሬ ቶለሳ ጂግሳ

Next Story

አባ መላ ልብ ሲበላ ! በእንግዳ ታደሰ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop