May 25, 2013
16 mins read

አባ መላ ልብ ሲበላ ! በእንግዳ ታደሰ

በእንግዳ ታደሰ

Aba Mela (Ato Birhanu Damte)
አባ መላ ልብ ሲበላ ! በእንግዳ ታደሰ 1

ተረት ሲጀምር ከዕለታት አንድ ቀን ተብሎ አይደል የሚጀመረው ? በኔ እና በአባ መላ የወጣትነት ዘመን  አንድ ድምጻዊ ዘፋኝ ነበር ፡፡  በሃይሉ እሸቴ የሚባል ፡፡  « ገሳጭ እንበለው ? ወይስ  ነቃፊ ዘፋኝ ? »  ብቻ ልማታዊ ዘፋኝ አልነበረም ፡፡ ምጸተኛ ዘፋኝ ብለው ይሻላል ፡፡ ውሻን ወደ ግጦሽ … የዋኋን እንስሳ ደግሞ ወደ ሊጥ ቡሃቃ ያስጠጋ ፡፡ አባ መላ ደግሞ እንደሰማሁት ከሆነ ትውልዱ መርካቶ ዙርያ ስለነበር ፣ ኮልፌ አካባቢ ያለውን የፖሊስ ሠራዊት ሙዚቃ ሰፈር ጠንቅቆ ስለሚያውቀው በሃይሉ እሸቴንም ያውቀዋል የሚል እምነት አለኝ ፡፡

በሃይሉ በዘፈኑ ሲሸነቁጥ የተሰደቡትም ሳይቀር  በዘፈኑ እየሳቁ እንደገናም ከምር ይጠሉት ነበር ፡፡ አባ መላ ልክ እንደ በሃይሉ እሸቴ ፣ ከሰሞኑ የወያኔን ሰፈር ፣ በብላኔ*  ይሁን ወይም በዉነት ስላደበላለቀው ፣ እንስሶቹ ሰፈራቸው ሁሉ ተደበላልቆባቸው የግጦሹ እንስሳ ወደ ሊጥ ወረዳ ፥ የሊጡ እንስሳ ደግሞ ወደ ግጦሽ መንደር ገብተው እየተተራመሱ፣ አንዴም በአባ መላ የአራዳ ቋንቋ ሲስቁ ፣ በሌላም በኩል በጥላቻ እየወረዱበት ይገኛሉ ፡፡ ብላኔ የመርካቶ ቋንቋ ናት- ዕውነተኛ ያልሆነች ሲሉ የሚጠቀሙባት ፡፡

አንድ የቡሽ ጥቅስ ትዝ አለኝ ፡፡ የአባትየው ሳይሆን ፣ የጀርጀራው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ፡፡ ልክ እንደ አገራችን ቀዳማዊት እመቤት አፉ እንዳመጣለት የሚዘባርቀው ጆርጅ ቡሽ ፣ ሁሌም ባይሆን አንዳንዴ ፣ ጥሩ ጥቅሶች ተብለው ከተመዘገቡለት ውስጥ የመስከረም አስራ ሃንድን የሽብርተኞችን ጥቃት አስመልክቶ የተናገረው ንግግር ነበር ፡፡

« ሽብርተኞች ላይ ርምጃ በምወስድበት ወቅት ፣ አስር ዶላር ለሚያወጣ ባዶ ድንኳንና  በድንኳን ውስጥ ለተጎለቱት ግመሎች  ስል የሁለት ሚልዮን ዶላር ሚሳይል እንዲተኮስ አላደርግም ፡፡ ወሳኝ የሆነ ርምጃ ነው የምወስደው ብሎ  ነበር » ፡፡ ”When I take action, I’m not going to fire a $2 million missile at a $10 empty tent and hit a camel in the butt. It’s going to be decisive.”

በጥሩው ፍቅራቸው ጊዜ ፣ ከአቶ መለስ ጥሩ አቀባበልና ፣ መስተንግዶ ይደረግለት ነበር የሚባለው አባ መላ ፣ አሁን ፥ አሁን ግን በአስር ብር ድንኳን ውስጥ ለተጎለቱት የመለስ ግመሎች ሚሳይሌን ከማስወነጭፍ ፣ ከትላልቆቹ ልጀምር ብሎ የጀመረው ሚሳይል የማስወንጨፍ ርምጃ – ከገዛ ተጋሩ እስከ እነ ግርማ ብሩ ኤምባሲ ግቢ ውስጥ ያሉ ወያኔዎችን ሁሉ አበሳጭቶ ፣ አባ መላን ይሄ ከሃዲ እያስባለው  ነው ፡፡

ከአባ መላ ጋር ያደጉና ቅርሌ የለጉ አብሮ አደጎቹ ፣ አባ መላ ከልጅነቱም ጀምሮ ፣ ባህላተ ቃላት ያለው ወይም አፈ ቀና እንደሆነ ይመሰክሩለታል ፡፡ አባ መላንም ፣ በቦታ ፥ በጊዜ ፥ እንደሁኔታው መሆን የሚችልም ነው ይሉታል ፡፡ እሱም አልካደ ! በአራዳ ቋንቋ ፖለቲካን ማን ነው እንደተርኪስ ባቡር አንድ ቦታ ላይ ያቆመው ? ተለዋዋጭ ነው ብሎናል ፡፡አባ መላ ይህን እንደ ተርኪስ ባቡር  ማን ነው አንድ ቦታ ያቆመው ያለውን ፖለቲካ ፣ አቶ መለስ ከሞቱ  በኋላ ማድረጉ ነው አጠያያቂው ጉዳይ ? አራዳ ሁሌ ሲወሳ ! ያውም ፒያሳ- ያውም ፒያሳ የሚል ዘፈን የሰማሁ ይመስለኛል ፡፡ ዉነቱን ነው አባ መላ ! በአቶ መለስ ለሳኝነት በአህያ ቆዳ የተሰራው ቤት ፣ ጅብ ሲጮኽበት ፈረስኩ ፣ ፈረስኩ ሲል እያየ ! ማን አብሮ እዚያ ቤት ይከርማል ? አራዶቹ እነ አባ መላ ድሮ « ላስ እንደ አየር ላንስ ይሉ አልነበር መርካቶ ! »

ግን አባ መላ ! ይህ ፖለቲካ ተለዋዋጭ ነው ! አንቀጹ መሻሻል አለበት ! የዘር ፖለቲካውም ጦዘ ! በየኤምባሲዎቻችንም አንገቱ ላይ ከረባት ያንጠለጠለ ገበሬ በዛበት ፥ ሻንጣ ተሸካሚውም በዛ ፣ የተባለውን ፊልም ያየውና የባነነው አቶ መለስ ከሞቱ  በኋላ ነው ወይስ ድሮም በብልጥጤ አይ ነበር ሊለን ነው ? ዉነቱን ነው አራዳው ሁሉ ወረዳ በሆነበት ዘመን ! አባ መላ ፊልም ቢሠራብን ሊደንቀን አይገባም ፡፡

ባለፈው ፕሮፌሰር መስፍን ፓል ቶክን በሚመለከት በጻፉት ጽሁፍ ላይ ያላስተዋልኩትን ነገር እንደገና ሄጄ እንዳይ አድርገውኛል ፡፡ የዚህ ፓልቶክ ሰለባ የሆኑት የምስራቅ አፍሪቃ አገሮች ሰዎች ሲሆኑ ፣ ከፍተኛውን ቁጥር ሱማልያ ስትዘግን ሁለተኛውን ደግሞ ኢትዮጵያ ታፍስና ፣ ሶስተኛውን ደግሞ ኤርትራ ትቆነጥራለች ያሉትን በትክክል አየሁ ፡፡

ናይጄርያ በአፍሪቃ ከፍተኛውን የህዝብ ቁጥር ያላት አገር የከፈተችው የፓልቶክ ክፍል አንድ ነው ፡፡ እሱም ሙዚቃ ብቻ ነው የሚያሰማው ፡፡ ከዚያም ከዘለለ ምናልባት ቢያስተዋውቅ የፉፉ ዱቄት ሊሆን ይችላል ፡፡ እንደ አፍሪቃ ቀንዱ የፖለቲካ ዲዲቲ አይረጭም ፡፡

ከዘጠና ሰባት ምርጫ ወዲህ ፓልቶክ የሚባለውን ጣቢያ ከኮምፒዩተሬ ውስጥ አውጥቼ  በሰላም እኖር ነበር ፡፡ ከሰሞኑ አንድ ጸሃፊ ለዚህ ፓልቶክ ጥሩ ስም አውጥቶለት አንብቤአለሁ – ቡል ቶክ ! ብሎታል ፡፡ አንድ ወዳጄ ኧረ እባክህ አባ መላን ግባና አድምጠው ብሎ ቢጨቀጭቀኝ ፣ ይህን ፓልቶክ የሚባል ጭነት ኮምፒዩተሬ ውስጥ ጭኘ  እንደ ቦኖ ወሃ ጠባቂ ሴት ተራዬን ጠብቄ ውዬ ፥ ውዬ እድሉን አገኘሁና አባ መላ ድንኳን ጎራ አልኩ ፡፡

ዉነትም አባ መላ ! አፉ እንደ አሜሪካን ዶላር ነው ፡፡ ይለዋል ! ይመነዝረዋል ፡፡ አበባ ይረጭለታል ! በርታ የሚልም የጅ ጠአት ይቀሰርለታል- ኧረ ስንቱ ! እጅግ የገረመኝ አባ መላ የማረከው የሚመስል የእጅ ምስል ለመናገር ተራ እየጠበቀ እጁን የሰቀለው ሰው መብዛቱ እጅግ ድንቅ የሚል ነው ፡፡ በዚህ መሃል አንድ እጅግ ከልቤ ያሳቀኝ አንድ ተረበኛ ሰው ከጽሁፍ ገበታው ላይ አንድ የሚያስቅ ጽሁፍ ከተበ ፡፡ አቤት ! አቤት ! ይሄ ሁሉ እጅ ፣ አንዳንድ ጠብመንጃ ቢይዝ ኖሮ ወያኔ የሚባል አይኖርም ነበር ፡፡ ወሬኛ ሁላ አለ ! አባ መላም የሚስቅ ምስል ለቀቀለት ፡፡ አባ መላ ውነትም የፓልቶክ አባባ ታምራት ገለታ ነው ፡፡

እጅግ የሚገርመው እዚያው አዲስ አበባ ላይ ሆኖ  ወያኔን በተባ ብዕሩ እንቅልፍ የሚነሳውን ፣የተመስገን ደሳለኝን ጽሁፍ የማያነብ ዲያስፖራ ! አሳጥረህ ብቻ አንቆርቁልኝ የሚል ብዙ ሰው በአባ መላ ተሞለቀቀ ፡፡ ሞለቀቀ በከሳቴ ብርሃን መዝገበ ቃላት ብዙ ትርጉሞች ቢኖሩትም ፣ በዚህ አግባብ ግን ብዙ ሰው በአንድነት አብሮ ሄደ ነው ትርጉሙ ፡፡ እስከዛሬ ግንባራቸውን ሳያጥፉ የወያኔንን ካምፕ ሲያራውጡ የነበሩ የፓልቶክ ክፍሎች ሁሉ ሳይቀር ቀፎአቸውን ነቅለው አብረው ሊቀላቀሉ እስኪመስል ድረስ ቤታቸውን አቀዘቀዙ ፡፡ አባ መላም አለ ! በሶስት ክፍል የከፈትኩትን ክፍል ለወደፊት በሬድዮ ጣቢያም አጎለብተዋለሁ አለ ፡፡ ማን ያውቃል ፟? ቀጥሎም ኢሳትን የሚገዳደር ቴሌቪዥንም ሊከፍት ይችላል ፡፡

ይህን ሞገደኛ የዲያስፖራ ኃይል በአራዳ ስልትና በወያኔ ቆረጣ ለመሰንጠቅ ፣ የሚደረግም ጨዋታ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመትም የዋህነት አይመስለኝም ፡፡ በእባብ የደነገጠ በልጥ ሆኖብን ብንጠራጠር  አባ መላ ይቀየመን ይሆን ?

ልደቱ ሸዋ ሮቢት ታስሮ ወያኔ  በአይነ ምድር ላይ በባዶ እግሬ እንደ ጭቃ ረጋጭ አስረገጠኝ ሲለን አዝነን ማንዴላችን አልነው ፡፡ ቀጥሎም በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት ወያኔ ቢሮዬ ውስጥ ቆልፎብኝ ፣ ይኽው ሶስተኛ ቀኔ ብሎ ፣በአሜሪካን ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም በስልክ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግ ! እንዴት ወያኔ ስልኩን ሳይቆርጥበት ባዶ ቢሮ አስቀመጠው  ብለን ሳንጠይቅ ልደቱ ልባችንን በላው ፡፡ ይህ ሁሉ ደርሶብን ! አባ መላ አንተንም እንደ ታምራት ገለታ ብንጠረጥር ትቀየመን ይሆን ?

 

ግምቴን ላስቀምጥ ፡፡ አባ መላ አሁንም የኢሃዴግ ደጋፊ ነኝ ይለንና ፣ የተማረኩት በወያኔ ፎቅና መንገድ ነው ይለናል! እኛም እንለዋለን ! ጥልያንም ጣዝማ በርንም ፥ ጅማንም ፥የቀበና ድልድይንም ገንብቶልናል እና ጥላያን ተመልሶ ይግዛን ማለትህ ነው እንለዋለን ? ፡፡ ስለ ሃብት ክፍፍሉ ፍትሃዊ አለመሆንና ፣ ባዶ አንገታቸው ላይ ክራባት ያሰሩ የአንድ ክልል ተወላጅ  ገብሬዎች ፣ ኤምባሲያችንን ሞልተውታል እያለን ፣ በዘረኝነትና በሙስና የተበከለን መንግስት እደግፈዋለሁ ሲለን ሃሳቡ አይጋጭም  ?

 

አባ መላ! ምናልባት አቶ መለስ ያዋቀሩት በአህያ ቆዳ የተለበጠው ቤታቸው ከርሳቸው ህልፈት በኋላ እንደማይቆይ ቀድሞ ነቄ ስላለ ፣ፖለቲካ ዳይናሚክ ነው ፣ መገለባበጥ ነው በሚልም እሳቤ ይህን ርምጃ እንደወሰደ በገሃድ ነግሮናል ፣የአባ መላን አመል ለማወቅ ራጅ ወይም ኤክስሬይ እስካላገኝንለት ድረስ ከአባ መላ ጋር አብሮ ለመሥራት ከሌሎች ፓልቶክ ቤቶች የአድሚንነት ስራ ለማግኘት cv ያቀረቡ አድሚኖች የአባ መላን ዘላቂነት የት ያህል ተረድተዉታል ?

 

አባ መላ እንደሚለው ብዙ ሰነዶች በእጁ እንዳሉና ፥ በራሱ በኢሃዴግም ውስጥ ጥገናዊ ለውጥ የሚፈልጉ አመራሮች እንዳሉ ስለነገረን ፣ ይህን ነውጠኛ የዲያስፖራ ህዝብ ፣አባ መላ ከሚያውቀው የጥገና ለውጥ አቀንቃኝ የኢሃዴግ መስመር ጋር ለማዛመድ የሚወሰድ ርምጃ እንደሚሆን መገምት ቢቻልስ ፥

 

በመጨረሻም በወያኔያዊ ቆረጣ ፣ ይሄ አልበገር ያለውን ፣ የአባይ ቦንድን ገንዘብ አትበሏትም ብሎ ባዶ አቁማዳዎቻቸውን ይዘው እንዲመለሱ ያደረጋቸውን የዲያስፖራ ህዝብ ፣ በሚጥመውና ፥ ደስ በሚለው አራዳዊ ቋንቋ እንደ ታምራት ገለታ አነሁልሎ ፣ የወያኔን ቀላል ሚዛን ቦክሰኞች እና የገዛ ተጋሩን ሰዎች አስደንብሮ ከክፍሉ ካስወጣ በኋላ ! ኑ የሌሎች ፓልቶክ ቤት አድሚኖች ፣ እንደውም ታላቅ የፈውስ ኮንፍረንስ ለመጀመርያ ጊዜ ፣ በሳይበር አለም ከአዲስ አበባና ክምድረ አሜሪካ ያሉ ታዋቂ ተቃዋሚዎችን ስለጋበዝኩ  ዛሬና እሁድን ከኔ ጋር አሳልፉ የሚለው ግብዣ ስንቱን ጠርጎ ይወስደው ይሆን ፟? ጠርጥር ከጥህሎም አይጠፋም ስንጥር ሆኗል ተረቱ ተቀይሮ አባ መላ ! ለማንኛውም ፖለቲካ ዳይናሚክስ ነው ! አባ ድሉን ግን ትወዳቸዋለህ እንጂ ! እሳቸው እንኳ የሚከረበቱ አይመስለኝም…ለቀልድ ነው

ከአንተ ቀጥሎ በፓልቶክ ንግግር የምወዳቸው አባት ናቸው ፡፡ በተለይ ከግዕዙ ጋር ሲያዋዙት አቤት ደስ ሲል፡፡

 

እንግዳ ታደሰ

 

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop