የኢሕአዴግ የአ.አ ወጣቶች ማህበር 15 አመራሩን አገደ

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በጉባኤው
ዋዜማ ላይ እየተወዛገበ ነው

‘‘የማህበሩ አመራር በኪራይ ሰብሳቢነት ተዘፍቋል’’
ከማህበሩ የታገዱ የም/ቤት አባላት
‘‘በኪራይ ሰብሳቢነት የተዘፈቁት የታገዱት አመራሮች ናቸው’’
የማህበሩ አመራር

በዘሪሁን ሙሉጌታ

የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታየአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ የአመራር ምርጫ ያካሂዳል። ማህበሩ ጉባኤ ከማካሄዱ በፊት ወደ 15 የማህበሩ ም/ቤት አመራር አባላትን ማገዱን ተከትሎ ከታገዱት አባላት ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቷል።
70 አባላት ካሉት የማህበሩ ም/ቤት መካከል ወደ 23 የሚሆኑ አባላት አለአግባብ ‘‘ተባረናል’’ ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት ማህበሩን እየመራ ያለው የአመራር አካል በኪራይ ሰብሳቢነት መዘፈቁንም አመልክተዋል። በቅርቡ ለሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤም 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የተጋነነ ገንዘብ መመደቡንም ገልፀዋል። የተመደበውም ገንዘብ በአብዛኛው ‘‘ለተሃድሶ’’ ወይም ለመዝናናት የሚውል ከመሆኑም በላይ የገንዘብ አሰባሰብ ሂደቱም ግልፅነት የጎደለው እንደሆነም ተናግረዋል።
ማህበሩ ጉባኤውን ለማካሄድ የጠየቀውን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ከአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተሞች፣ ከአዲስ አበባ ገቢዎችና መንገዶች ባለስልጣን እና ከሌሎች መንግስታዊ ተቋማት የሚሰበሰብ እንደሆነም አመልክተዋል።
በማህበሩ አመራር አለአግባብ ታግደናል የሚሉት እነዚሁ ወጣት አመራሮች በተጨማሪ እንደገለፁት የጉባኤው መሪ ቃል (ሞቶ) ‘‘የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመለስን ራዕይ እናሳካለን’’ የሚል መሆኑ ማህበሩ ነፃነት የሌለውና በኢህአዴግ ካድሬዎች የሚሽከረከር መሆኑን ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
‘‘አለአግባብ ተባረናል’’ የሚሉት ወጣት አመራሮች የተባረሩበት ምክንያት በማህበሩ አካባቢ ኪራይ ሰብሳቢነት መስፈኑን በማጋለጣቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በሕገ-መንግስታዊ መብታቸው መሠረት በሌላ ነፃ ማህበር ውስጥ አባል በመሆናቸው ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።
ማህበሩ ለስሙ 80 ሺህ አባላት እንዳሉት ቢነገርም በትክክል የማህበሩን ስራ የሚያከናውኑ ከሁለት ሺህ እንደማይበልጡ ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የገለፁት። የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወጣት ዮሐንስ ጣሰው ማህበሩን ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም በኢህአዴግ ካድሬዎች ተፅዕኖ እንደሚደረግበትም ቅሬታ አቅራቢዎቹ አያይዘው ገልፀዋል።
በማህበሩ አመራር ላይ በተነሱ ቅሬታዎች ላይ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወጣት ዮሃንስን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረግን ቢሆንም ከስራ መብዛት ጋር በተያያዘ ልናገኘው አልቻልንም። ሆኖም የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ወጣት መድሃኔ መለሰ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፀው ከአንድ ሳምንት በፊት ስብሰባ ተካሂዶ እንደነበር እና 15 የማህበሩ የም/ቤት አባላት ለጊዜው መታገዳቸውን አምኗል። በማህበሩ ሕገ-ደንብ መሠረት የአመራር አባላት የሚባረሩት በጠቅላላ ጉባኤው መሠረት እንደሆነ አስታውቋል። 15ቱ የአመራር አባላት የታገዱት ከክፍለ ከተማ በመጣ ግምገማ መሠረት እየሰሩ አለመሆኑ በተጨባጭ ማስረጃ በመረጋገጡ ከክፍለ ከተሞች ለአስፈፃሚው በመጣ የግምገማ ሪፖርት መሆኑን አመልክቷል። ሦስቱ የአመራር አባላት ደግሞ በገዛ ፈቃዳቸው ከምክር ቤቱ እራሳቸውን በማግለል ሲሆን፤ የቀሩት አምስቱ ደግሞ ከሀገር በመውጣታቸው እንደሆነም ገልጿል።
ለጉባኤው የወጣው የገንዘብ መጠን በተመለከተ ወጣት መድሃኔ ተጠይቆ ትክክለኛው የገንዘብ መጠን 1 ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ ሳይሆን አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ብር መሆኑን፤ ከዝግጅት ጋር በተያያዘም ጠቅላላ ጉባኤው መካሄድ ከነበረበት ጊዜ መዘግየቱን በመጪው ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ የወረዳ ም/ቤት ጉባኤዎች ከተካሄዱ በኋላ በሳምንቱ ደግሞ በከተማ ደረጃ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚካሄም አመልክቷል።
ለጉባኤው ወጪ የተደረገው የገንዘብ መጠን በ116 ወረዳዎች ውስጥ ለሚካሄድ ጉባኤ በመሆኑ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን የጠቀሰው ወጣት መድሃኔ በ116 ወረዳዎች ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ የተጠቀሰው ገንዘብ ቢያንስ እንጂ አይበዛም ብሏል።
ማህበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ የገንዘብ ምንጩ በመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚደገፉ በመሆኑ ከመንግስታዊ አካላት በአይነት መደገፉ ወይም ስፖንሰር መደረጉ ችግር የለውም፤ የሚለው ወጣት መድሃኔ ገንዘቡ ለተሃድሶ (ለመዝናናት) ይውላል መባሉ በተጨባጭ እቅድ ላይ የሌለ ነገር ነው ሲል አስተባብሏል። ከመንግስት አካላት በገንዘብ ከሚሰጠው ድጋፍ በበለጠ በቲሸርት፣ በኮፍያና በአዳራሽ መልክ የሚደረጉ ድጋፎች እንጂ በካሽ አለመሆኑን አያይዞ ገልጿል።
የማህበሩ የአባላት ብዛት በተመለከተ ቀደም ሲል 80 ሺህ አባላት አሉት ይባል እንደነበር የጠቀሰው ወጣት መድሃኔ፤ ነገር ግን በተደረገው የማጥራት ስራ በአሁኑ ወቅት በማህበሩ እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት የሚሳተፉ የአባላት ቁጥር 32ሺህ መሆኑንም አስረድቷል።
የጉባኤው መሪ ቃል በተመለከተ ‘‘በመለስ ሌጋሲ የወጣቱን ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን’’ መባሉ ከማህበሩ ነፃነት አንፃር ስላለው ፋይዳም ተጠይቆ፤ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስተዳደር ወቅት ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፓኬጆች በመቀረፃቸው፣ በህገ-መንግስቱ ወጣቱ በነፃ በመደራጀቱና ወጣቱ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ተጠቃሚ መሆናቸውን መነሻ በማድረግ የተወሰነ ነው ሲል መልሷል።
በማህበሩ ስም ከሚከራዩ ተቋማት ገቢ ጋር በተያያዘ ምዝበራ ስለመኖሩም ወጣት መድሃኔ ተጠይቆ ከአመራሩ ይልቅ በም/ቤቱ ከታገዱ ወጣቶች ላይ ይሄ ችግር መኖሩን ከታገዱበት ሦስት ምክንያቶች መካከል የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር አንዱ እንደሆነ በመግለፅ በአንፃሩ ማህበሩ አመራሩን የሚቆጣጠርበት ስርዓት መቀየሱን፤ በአሁኑ ሰዓት ሦስት የአመራር አባላት ከኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤት ተከሰው ጉዳያቸው በሕግ መያዙን በመጥቀስ አመራሩ ኪራይ ሰብሳቢነት እየተዋጋ መሆኑን አመልክቷል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በ1990 ዓ.ም የተቋቋመ ማህበር መሆኑ ይታወቃል።n

ተጨማሪ ያንብቡ:  Breaking News: በአማራ ክልል አዊ ዞን ፌደራል ፖሊስ እና ሕብረተሰቡ ወጊያ ገጠሙ፤ ሰዎች ሞተዋል

(ምንጭ ሰንደቅ ጋዜጣ የዛሬ ሜይ 22 ዕትም)

2 Comments

  1. NO WONDER ABOUT THESE JUNTAS,BECAUSE THEY LEARN EVERY EVIL ASPECTS FROM weyanes NO SURPRISE AT ALL. YEAHYA LIJ AHYA NEWA.

Comments are closed.

Share