የባሕታዊው ማስታወሻ (ክፍል አንድ)- በገ/ ክርስቶስ ዓባይ

May 20, 2013

በገ/ ክርስቶስ ዓባይ 
ግንቦት 10 ቀን 2005 ዓ/ም
ክፍል አንድ

አባ ወ/ ሥላሴ ይባላሉ፤ ይህን ዓለም ንቀው ዕድሜ ልካቸውን የለፉበትን የሥጋቸውን ድሎት ከምንም ባለመቁጠር ወደ ገዳም ገብተው ማንነታቸውን ደብቀው ይኖራሉ። አባ ወ/ ሥላሴ የዓለም ስማቸው ማን እንደሆነ ባይታወቅም፤ በወጣትነት ዕድሜአቸው ትጉህ ተማሪ እንደነበሩ አንዳንድ ጊዜ በጨዋታ መካከል ሳይታወቃቸው ከሚሰነዝሩት አስተያየት ለመረዳት ይቻላል።

በትምህርት ቤት ዘመናቸው ሁለተኛ እንኳ ሆነው እንዳማያውቁ ሁልጊዜም በአንደኝነት ማዕረግ ከክፍል ወደ ክፍል ሲሸጋገሩ እንደቆዩ በጣም ለሚያቀርቧቸውና ጓደኛቸው ለሆኑት መነኩሴ እንዳጫወቷቸው ይታወቃል።

የአባ ወ/ ሥላሴ ወላጆች ሐኪም እንዲሆኑ ቢገፋፏቸውም እርሳቸው ግን የአገራቸውን የሺህ ዓመታት ኋላቀር የአስተራረስና የግብርና ምርት ለማሻሻል ከፍተኛ ፍላጐት ስለነበራቸው  ሐረር ወደሚገኘው ዝነኛውና ብቸኛው የአገሪቱ የግብርና ዩኒቨርስቲ ዓለማያ ይገባሉ። በዚያም ከነበሩት ፋኩሊቲዎች ውስጥ በዕጽዋት ሣይንስ ሲማሩ ቆይተው በከፍተኛ ማዕረግ ይመረቃሉ።

ቀጥሎም በወቅቱ የነበረው የደርግ አስተዳደር ሠፋፊ የመንግሥት እርሻዎችን የማቋቋም ዕቅድ ጋር ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ከመንግሥት እርሻዎች በአንዱ፤ በዋና ሥራ አስኪያጅነት እንዲሥሩ በኃላፊነት ይመደባሉ። ከዚያም አመመኝ፤ ሰለቸኝ፤ ደከመኝ ሳይሉ ቀን ከሌት ተግተው በመሥራትና በማሠራት ከፍተኛ የሆነ የምርት ውጤት በማስመዝገባቸው የማበረታቻ ሽልማትና ጉርሻም ይሰጣቸዋል። አያይዞም ሌሎች የግብርና ምሩቅ ባለሙያዎች በረዳትነት ይመደቡላቸዋል።

አባ ወ/ ሥላሴም የአሠራራቸውን ሁኔታ በዘርፍ በዘርፉ ለይተውና አጥንተው ለእያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራ ተግባር (Job Discription) አዘጋጅተው ሁሉም የሥራ ድርሻውን በሚገባ አውቆና ተረድቶ እንዲሠራ ኃላፊዎችን ይመድቡና፤ ሁሉም ነገር ሥርዓት ባለው መንገድ መተግበር ይጀምራል።

በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሁኔታውን ለማየትና አስፈላጊም ከሆነ አንዳንድ ጉዳዮችን አጥንተው በመንግሥት እርሻዎች ኃላፊ በኩል ለሊቀመንበሩ ለኰሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሪፖርት ለማቅረብ በድንገተኛ ጉብኝት ወደቦታው ይሄዳሉ።

ባለሥልጣናቱ በእርሻ ልማቱ መ/ቤት ሲደርሱ ባዩት ነገር ሁሉ እጅግ በጣም ይደነቃሉ። ምክንያቱም  አባ ወ/ ሥላሴ  ሁሉንም በየዘርፉ የመደቡትን የሥራ ክፍፍል፤ በቻርት አስደግፈው  ግልጽና ቁልጭ ባለ መንገድ ከማስቀመጣቸውም በላይ ፤ የእርሻና ዝግጅት፤ የዘር፤ የአረም፤ የተባይ መከላከያና የሰብል አሰባሰብ፤ ተጨማሪ የሰው ኃይል ወቅቶችንና መደረግ ከሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ጋር በቅድሚያ ዘርዝረው ማስፈራቸውን ያያሉ።

የልዑካን ቡድኑ በሌሎች የመንግሥት እርሻ ልማት ጣቢያዎች ተዘዋውረው ያላዩትን ሁሉ በአባ ወ/ሥላሴ ሥር በሚመራው የእርሻ ልማት ቢሮ በማየታቸው እጅግ በጣም መርካታቸውን እና ወደፊት ምን ዕቅድ እንዳላቸውና ከመንግሥትስ የሚጠብቁት ጉዳይ ካለ በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት ከእርሻ ልማቱ ጎን ለጎን የእንስሳት መኖን በተመለከተ ምርምር ለማድረግ እንደሚፈልጉና ለዚሁ አገልግሎት የሚሆኑ ቢያንስ ከአምስት እስከ አሥር የሚደርሱ የውጭ አገር ላሞች እንዲፈቀዱላቸው ይጠይቃሉ።

እንግዶቹም ጥያቄያቸውን መዝግበው በመያዝ ለበላይ አካል እንደሚያቀርቡ ገልጸውላቸው አመስግነው ይሄዳሉ። ነገር ግን ከጊዜ በኋላ አባ ወ/ሥላሴ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል። ይኸውም መቀመጫቸውን አዲስ አበባ አድርገው ሁለት የመንግሥት እርሻዎችን፤ የበላይ ኃላፊና ተቆጣጣሪ ሆነው እንዲሠሩ የተወሰነ መሆኑን፡ ነገር ግን የእንስሳት መኖን ምርምር አስመልክቶ ያቀረቡት ጥያቄ በሂደት የሚታይ መሆኑ ይገለጽላቸዋል።

አባ ወ/ሥላሴም እርሻ ልማቱን በጊዜያዊነት ሊመራ ይችላል ያሉትን ሰው በመወከል  በእጃቸው የሚገኘውን ማንኛውንም የመንግሥት ንብረትና  ሀብት እንዲሁም በጅምርና በዕቅድ ላይ ያሉ ሥራዎችን አስረክበው በውሳኔው መሠረት ወደ አዲስ አበባ በመሄድ አዲሱን ሥራቸውን ይጀምራሉ።

በአዲሱ ምደባቸውም በተሻለ ሁኔታ ሙያቸውን የተመለከቱ መጻሕፍትን ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ መጽሔቶችን የማግኘት ዕድል ያገኛሉ። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ በምህፃረ ቃሉ ኢልካ (ILCA) በመባል ከሚታወቀው የምሥራቅ አፍሪካ የዓለማቀፍ የእንሥሳት ምርምር ማዕከል በወጣ ሙያቸውን የሚመለከት ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ያመለክቱና ይቀጠራሉ። በዚያም ሲፈልጉት የነበረውን የእንስሳት መኖ ከወተት ሀብት ጥናትና ምርምር ጋር በተጎዳኘ መሥራት የሚያስችል ዕድል ይከፈትላቸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደቡብ ሸዋ ወላይታ አካባቢ ማዕከሉ ባቋቋመው የምርምር ጣቢያ አለቃቸው ሆኖ ከተመደበ እንግሊዛዊ ጋር ሆነው የ6 ዓመት የጥናት ፕሮጀክት ይመራሉ። ይሁን እንጂ ምንም እንኳ ጥናቱ ለስድስት ዓመት የታቀደ ቢሆንም በአራተኛው ዓመት ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ በዚሁ እንዲያበቃ ይደረጋል።

በዚህ አጋጣሚ ወቅት አንዳንድ የምርምር መላምቶችንና ጠቋሚ ሥራዎችን በዓለም አቀፍ የወተት ሀብት መጽሔቶች (Dairy Magazines) ሐሳባቸውን ያጋሩ ኖሮ የጻፏቸውን ሲመለከቱና ሲከታተሉ ከነበሩ የውጭ ሀገር ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የጀርመኑ እስቱትጋርት ዩኒበርስቲ ለሦስት ወራት የሚዘልቅ የተጋባዥ አስተማሪነት (Guest Lecturer) ጥሪ ያደርግላቸውና ሔደው ይመለሳሉ።

በኋላም ይመሩት በነበረው የምርምር ጣቢያ በጊዜያዊነት ተቀጥረው ሲሠሩ የቆዩት ወደ ሰላሳ ሰባት የሚደርሱ ዝቅተኛ ሠራተኞች ከሥራ እንዲባረሩ በእንግሊዛዊው አለቃቸው ይወሰናል። አባ ወ/ሥላሴም “ምንም እንኳ እኛ በኃላፊነት ደረጃ ላይ ሆነን ምርምሩን ብናካሂድም ውጤቱ የተገኘው በእነዚህ ሠራተኞች ቀና ትብብርና ትጋት ጭምር በመሆኑ እንደየደረጃቸው በሚመጥን ሌላ ሥራ ተፈልጎ መመደብ አለባቸው እንጂ መባረር የለባቸውም” የሚል አቋም ይይዛሉ።

እንግሊዛዊው አለቃቸውም ምን ዓይነት ሥራ ብሎ ይጠይቃል። አባ ወ/ሥላሴም “አንዳንዶቹን በአትክልተኛነት፤ አንዳንዶቹን በዘበኝነት፤ አንዳንዶቹንም የመኪና መንጃ ፈቃድ እንዲያወጡ አድርገን በሾፌርነት፤ ሌሎችንም በጽዳት ሠራተኛነት መመደብ ይቻላል” በማለት ይገልጻሉ። እንግሊዛዊው አለቃቸው ግን የእርሳቸውን ሐሳብ ሊቀበል አልፈለገም።

አባ ወ/ሥላሴም በሆዳቸው እውነቱን ነው፤ እርሱ እንግሊዛዊ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ይላሉ። ስለሆነም የወገኔ ችግር ችግሬ ነው፤ በማለት በጣም ያዝናሉ። ቀጥሎም ከጥቂት ቀናት በኋላ እነዚህ ሠራተኞች ትዳር አላቸው ልጆች ወልደዋል ስለዚህ ሁኔታውን በጥሞና እንዲመለከተው መልሰው እንደገና ይጠይቁታል። እንግሊዛዊው አለቃቸውም ፈጽሞ ሊሆን እንደማይቻል ያረጋግጥላቸዋል።

 

እርሳቸውም እንግዲያውስ የምሰናበተው እኔም ጭምር ነኝ ይላሉ። እንግሊዛዊውም በሁኔታቸው ተገርሞ “ እንዴት?” ይላቸዋል ።

“ሰው ስለሆንኩ! በታማኝነትና በትጋት ሲያገለግሉኝ ቆይተው በእነርሱ ቀና ትብብር ውጤት ላይ በመድረሴ አልከዳቸውም” ይላሉ። አለቃቸውም “አስብበት”ይላቸውና ይለያያሉ። በሦስተኛው ቀን ኮሪዶር ላይ ይገናኙና ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ እንግሊዛዊው ሰው አባ ወ/ሥላሴን “እንዴት ወሰንክ?” ይላቸዋል። እርሳቸውም በቀድሞው ውሳኔያቸው መጽናታቸውን ያረጋግጡለታል።

 

ከዚያ በኋላ ለዚህ አረመኔና ጨካኝ ዓለም ተባባሪ አልሆንም በማለት ወደ ገዳም ይገባሉ። ገዳም ከገቡ በኋላም በሁሉም ዘርፍ  በትጋት በመሳተፍ ደጅጥናታቸውን ይጀምራሉ። አረጋዊ አባቶችን በማገልገል፤ በምግብ ዝግጅት፤ በጉልበት ሥራ፤ በጾም በጸሎት ሁሉ በርትተው ተጋድሎአቸውን ይቀጥላሉ።

በመጨረሻም አንድ ቀን አበምኔቱ ማለትም የገዳሙ አስተዳዳሪ ይጠሯቸውና “ እንግዲህ ይበቃዎታልና የሥላሴ ዕለት  ሥርዓተ ምንኩስና ስለምናደርግ እርስዎም ይዘጋጁ አሏቸው። ምን አድርጌ ምን ሠርቼ እያሉ፤ ለዚህ ማዕረግ ገና አልደረስኩም በማለት ሊከራከሩ ሞከሩ፤ ግን በማኅበሩ የተወሰነ ስለሆነ እኔ አልቀለብሰውም  በማለት አስረድተዋቸው ወደ ባዕታቸው ገቡ።

አባ ወ/ሥላሴም ለረዥም ጊዜ ባሉበት ሳይነቃነቁ ከቆዩ በኋላ ወደሚጠብቃቸው ሥራ ተጓዙ።  ሥራቸውን ጨርሰው ወደ ባዕታቸው ከገቡ በኋላ የተለመደውን ጸሎታቸውን አድርሰው ድካም ስለተሰማቸው አረፍ እንዳሉ፤ ወ/ ሥላሴ ሆይ! አሁንስ መንኩስ በአንተ ጸሎት ብዙ ሰው ይማራልና በአበ ምኔቱ የቀረበልህን ትዕዛዝ ፈጽም የሚል ራዕይ ታያቸው።

በመጨረሻም አባ ወ/ሥላሴ ተብለው መነኰሱ። በኋላም ስጦታቸው ጸሎት ስለሆነ በተለይ በኢትዮጵያ ላይ የሠለጠነው የወያኔ መንግሥት በሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር፤ ሰቆቃ፤ አድልኦ፤ እስርና ግድያ ምክንያት በማድረግ ሕዝቡ ሁሉ ዓይንህ ላፈር እያለ ሲረግም፤ አባ ወ/ሥላሴ ግን ለባለሥልጣናት አስተዋይ አእምሮ እንዲሰጣቸው፤ ሕዝብና መንግሥት ተስማምቶ እንዲኖር፤ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ሁሉ የሰው ልጅ ተፋቅሮና ተግባብቶ በሰላም እንዲኖር ሁልጊዜ መጸለያቸውን ሥራዬ ብለው ተያያዙት።

ይሁን እንጂ አንድ ቀን መልአክ ተገልጾ “የምወድህ ፤ያከበርኩህ ወ/ሥላሴ ሆይ ከእንግዲህ ወዲህ ስለመለስ ዜናዊ በፍጹም አትጠይቀኝ፤ ይኸው በአንት ጸሎትና ልመና ይመለሳል እያልኩ ለንሥሐ ዕድሜ ሰጠሁት። ነገር ግን አይደለም በየቀኑ በየሰዓቱና በየደቂቃው ተንኰል ሲያስብና ሤራ ሲያውጠነጥን  ውሎ ያድራል። ሕዝቤን አስጨንቋል፤ ለእናቴ በአስራትነት በሰጠኋት ሀገር ፍትሕ አሳጥቷል፤ ንፁሐን ሰዎች ያለአግባብ እየታሠሩ፤ እየታንገላቱ፤ የለፉበት፤የጣሩበት ፤የጋሩበት፤ ላባቸውን ያንጠፈጠፉበትን፤ አንጡራ ሀብታቸው እየተወረሰ፤ ዕትብታቸው ከተቀበረበት፤ ከአያት ቅድመ አያታቸው በዘር ሐረግ ከወረሱት ቀያቸው በገፍ እያፈናቀለ ነው።

የሰዎች ዕንባ፤ ጩኸት፤ ዋይታና እሪታ ሁልጊዜ በፊቴ ነው። እሱ ሥልጣንና ገንዘብ አይጠግብም። ለብዙ ሺህ ዓመታት በእንግዳ ተቀባይነትና አስተናጋጅነት የሚታወቀው፤ ሰውን በሰውነቱ ብቻ ልዩ ከበሬተና ፍቅር እያሳዬ እርስ በእርሱ ተግባብቶ ይኖር የነበረውን፤ ምንም የማያውቀውን ሕዝቤን፤ በዘርና በጎሣ እየከፋፈለ መረዘው። እህል እያለ በመጋዝን አሽጎ ሕፃናትን እያስራበ ነው። የእነዚህ ሕፃናትና የእናቶች ዕንባ በፊቴ እንደ ጎርፍ ይፈሳል። ዕድሜአቸው ለአቅመ አዳምና ሔዋን ያልደረሱ ልጆች በዚህ አሰቃቂ አገር ከመኖር ወደ ሌላ ሀገር ሔደን ዕድላችንን እንሞክር በማለት ሳይወዱ በግድ ሲሰደዱ ለከፍተኛ ችግር፤ እንግልትና፤ ለድንገተኛ ሞት ተዳርገዋል። ይህ ሁሉ የመለስ ዜናዊ አረመኔያዊ አስተዳደር ውጤት ነው። እኔ ግን ቁጣዬ በፊቴ እየነደደ ታገስኩት፤ ከእንግዲህ ወዲህ ስለመለስ ዜናዊ አትለምነኝ። አንት ነህ እንጂ እርሱ እኔን አያውቀኝም” ተብለሃል ይላቸዋል።

አባ ወ/ሥላሴም ወደ ሰማይ አንጋጠው  “እግዚአብሔር እኮ ፈጣሪ አምላክ ነው። አሁንም አጥብቄ እለምናለሁ፤ አብዝቼም እማጸነዋለሁ። ልቡን መልሰው፤ የማስተዋል አእምሮ አድለው። አንተ እኮ ተወዳዳሪ የማይገኝልህ ቸር አምላካችን ነህ፤ አንተ እኮ ፍቅር ነህ፤ አንተ ከተውከን ማን ይታደገናል? ጌታዬ ሆይ እንደ ፈቃድህ ይሁን! በማለት ጸለዩ። መልእክት ይዞ የመጣው መልአክም ከፊታቸው ተሠወረ።

ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራት በኋላ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዓለም ምግብ ድርጅት በተዘጋጀ ሴሚናር ተጋብዘው በአሜሪካ ሬገን አዳራሽ እንዳሉ እግዚአብሔር ሊገሥጻቸው አንድ ሰው ያዘጋጃል። እኒህ ሰው ሐሳቡ በአዕምሮአቸው ሲጸነስ ፍርሃት ፍርሃት ብሎአቸው ነበር፤ ግን የጌታ መልአክ  በአጠገባቸው ሆኖ አደፋፈራቸው ድምፃቸውንም በአዳራሹ ከተዘጋጀው ድምፅ ማጐያ በላይ እንዲሆን አደረገ።

እግዚአብሔር ይህንን ያደረገው ሰውየውን (አቶ መለስን ) ለመመለስና ባለፈው ተጸጽተው ንሥሐ እንዲገቡ ለማድረግ ነበር። በአንፃሩም በአቶ መለስ ዜናዊ ጐን በመሆን ከልጅነታቸው ጊዜ ጀምሮ በሜንተርነት (በአሠልጣኝነት)  ለረዥም ጊዜ ሲያሳስታቸው የነበረው ከዲያብሎስ ከፍተኛ ባለሥልጣንናት አንዱ የሆነው እስከማዕዜኑ የተባለ ሠይጣን የእርሳቸው ንሥሐ መግባት ማለት፤ ከማኅበረ ዲያብሎስ ተማርከው ወደ ማኅበረ ቅዱሳን መግባት ስለሚሆን ተሽቀዳድሞ መቅሪያቸውን በመምታት ለቅስፈት የሚያበቃቸውን ደዌ ሲያስተላልፍባቸው እኒህ ባህታዊ መነኩሴ አባ ወ/ሥላሴ በጸሎት ላይ እንዳሉ በመንፈስ ያዩና ሳይታወቃቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ምርር ብለው ያለቅሳሉ።

ከዚያም በአካባቢው ያሉ የገዳሙ መነኰሳት ሁሉ ተሰብስበው ምነው ምን ሆኑ በማለት ይጠይቋቸዋል። እርሳቸውም እርሷን ለማዳን ለሃያ  አንድ ዓመታት የተጋደልኩላትን ነፍስ ተማረክሁ ይላሉ። ቀጥሎም ወደ ጸሎታቸው ተመልሰው ምግብ ላለመብላትም ይወስኑና ተጋድሎአቸውን እስከመጨረሻው ይቀጥላሉ። ይሁን እንጂ የጌታ መልአክ እንደገና ወደ እርሳቸው ይላካል። ልጄ ወዳጄ ወ/ሥላሴ ሆይ ጸሎትህን ሰምቻለሁ ነገር ግን ያች ነፍስ ከምርጦቼ ወገን አይደለችም። ምድቧ ከከሃዲዎች ወገን ስለሆነ ከእንግዲህ ወዲህ ራሥህን አትበድል ስለአንተ ሐዘንና ልመና፤ ሌሎችም የሚረግሙትን አንተ ግን ለማዳን የሚገባህን አድርገሃልና የተሰበረው ልብህ ይጠገንና ይጽናና ዘንድ ነፍሱ ከሥጋው በተለየች ጊዜ መዳረሻዋን እንድታይ አደርጋለሁና፤ ልጄ ወዳጄ ወ/ሥላሴ ሆይ ዕረፍት አድርግ፤ ተብለሃል አላቸው።

 

ባህታዊውም ዓይናቸውን ወደ ሰማይ አቅንተው “አምላኬ ሆይ እኔ የማልረባ ሰው ስሆን አክብርኸኛልና፤ ልመናየንም ሰምተሃልና ክብር ምስጋና ላንተ ይገባል ዛሬም ነገም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ፤ ለአዛኝቱ እናታችን ለቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን  ድንግል ወላዲት አምላክም ምስጋና ይገባል። ሁሌም ቸርነትህ ወሰን የለውምና አመሰግንሃለሁ። አምላኬ ሆይ እንድቃልህ ይፈጸምልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” በማለት ሲጸልዩ መልአኩ ከፊታቸው ተሠወረ።

ይህ ከሆነ ከጥቂት ቅናት በኋላ አባ ወ/ ሥላሴ ቆመው ሲጸልዩ  ሳለ እንደተለመደው የዕለቱን መቅኑናቸውን የሚያቀብሏቸው ሌላው መንኩሴ አባ ከሰተ ብርሃን፤ ወደ ባዕታቸው ሔዱ።

እርሳቸውም ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ጸሎታቸውን እንዳያሰናክሉ በማሰብ ገርበብ ያለውን በር በታላቅ ጥንቃቄ ገፋ አድርገው ገቡ። እርሳቸውም “እንደምን ዋሉ አባቴ ይባርኩኝ” አሉ፤ ግን ምንም መልስ አላገኙም። ሌላ ጊዜ “እግዚአብኅሔር ይመስገን፡ በሰላም ዋሉ አባ ከሰተ ብርሃን?” ይሏቸው ነበር። ዛሬ ግን ምንም መልስ አልሰጡም። ቀና ብለው ሲያዩአቸው በመቋሚያቸው ተደግፈው ዳዊታቸውን እንደያዙ ናቸው። ይሁን እንጂ በሕይወት ያሉ አይመስሉም። እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በገዳም ውስጥ አልፎ አልፎ እንድሚፈጸም ይታወቃል። በመሆኑም አባ ከሰተ ብርሃን በነበሩበት ሳይንቀሳቀሱ በትዕግሥት መጠበቅ ጀመሩ።

በአዕምሮአቸውም ራዕይ እያዩ ይሆን? ወይስ በጸሎት ብዛት ከድካማቸው የተነሣ አሸልቧአቸው ይሆን? በማለት ከኅሊናቸው ጋር እየተሟገቱ መጨረሻውን ለማየት በመጓጓት ይጸልዩ ጀመር።

 

የሆነው እንዲህ ነበር፤ …………. ይቀጥላል!

 

     

3 Comments

  1. ፅሁፉ በጠቅላላው ጥሩ ነው። ቢሆንም አንዳንድ ግድፈቶችን አስተውያለሁ። ለምሳሌ የሥራ ተግባር ያሉት የሀሳብ ድግግሞሽ ያለበት ነው። በቅንፍ ባሰቀመጡት የእንግሊዝኛ አቻ መሠረት የሥራ መዘርዝር ቢባል የተሻለ ይሆናል እላለሁ። ሌላው ደደግሞ የገረመኝ ይሄ ራዕይ ተገለጠላቸው ያለከው ነገር ነው። ትንሽ ተዓማኒነት ይጎለዋል። በራዕይ የሚያናግራቸው መንፈስ ዐቅም ያጣ ተቃዋሚ እንጂ ሁሉን ማድረግ የሚችል ፈጣሪ አይመስልም። ለዚያውስ ፈጣሪ እኛን የሚወደን ከሆነ ይህ ሁሉ ግፍና መከራ ሲደርስብን ለምን እስካሁን ሳይረዳን ቆየ?

  2. ብዙም ተአማኒነት የለውም::ግን ባይደላኝም አልከፋኝም::እንደ እኔ በዚህ መድረክ ላይ ለልብ ወለድ ቦታ ያለው ሰው ይኖራል ብየ አላስብም::ልብ ወለድ የጋሀዱ አለም ነፀብራቅ ቢሆንም በእንደዚህ አይነት ቦታ ሲገኝ ዋጋ አይኖረውም:: ያውም በ21ኛው ክ/ ዘመን::

Comments are closed.

Tekelmichael Abebe 1
Previous Story

የኛ ነገር፡ የኔም ነገር፤ አንድ – (ከተክለሚካኤል አበበ)

3404
Next Story

የሚኒሶታውን ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ በማስመልከት በKfai Radio የተሰጡ የሕዝብ አስተያየቶች

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop