የኛ ነገር፡ የኔም ነገር፤ አንድ – (ከተክለሚካኤል አበበ)

እንደመግቢያ፤ አሸዋና አለት

 

 

 

Tekelmichael Abebe

1. እስኪ ደግሞ ትንሽ ልረብሽ። ጽሁፍ ተሸፋፍነው የተቀመጡ ሀሳቦችን ካልገለባበጠ፤ ያንቀላፉትንም ካልረበሸ አይመቸኝም።
2. አንዳንድ ጠንካራ ምሳሌያዊ አባባሎች በአንድ ሀይማኖት ውስጥ ቢነገሩም፤ መልእክታቸውን የሀይማኖት ድንበር አይወስነውም። ጠቀሜታቸውን ሳይንስና ስልጣኔም አይሽረውም። በአሸዋ ላይና በአለት ላይ ስለሚገነባ ቤት ጽናት ልዩነት ቅዱስ መጽሀፍ የተናገረውን መጥቀስ ይቻላል። ቃል በቃል አላስታውሰውም፤ ግን እምነታችን በጠንካራና በማይናወጽ አለት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን፤ በፈተናና በጥርጣሬ፤ እንዲሁም በጽናት እጥረት እንዳይበረዝ ሲያስጠነቀቅ፤ መጽሀፍ ቅዱስ “በአለት ላይ የታነጸ ቤት በአሸዋ ላይ እንደተገነባ ቤት ንፋስና ወጀብ አያናወጠውም” አይነት ነገር ይላል።
3. ከዚያ የኛ “ትግል” ትዝ አለኝ። የኛ “ትግል”፤ ትግል ካለን፤ በአሸዋ ላይ የታነጸውን ቤት መስሎ ይታየኛል። በአህያ ቆዳ የተሰራ አይነት ቤት፤ ጅብ በጮኸ ቁጥር የሚንቀጠቀጥ። ዛሬ ስለዚያ ነው የምጽፈው። ስለዚያም ብቻም አይደለም፤ እኛንና ጠላቶቻችንን ስለሚለያዩን ወይም አንድ ስለሚያደርጉን ነገሮች እጠቅሳለሁ።
4. ለምሳሌ፤ ጠላቶቻችን ርኩስ መሆናቸው፤ እኛም የነሱን ርኩሰት ነቅሰን ማውጣታችን፤ እኛን ደርሶ ጻድቅ አያደርገንም። አንዳንዶች እነደዚያ የሆንን ሊመስላቸው ይችላል። ለምሳሌ ግንቦት ሰባት ወይንም መድረክ፤ ኢዴፓ ወይንም ኢህአፓ የኢህአዴግን ጉድ አጋለጡ ማለት እነዚህን ድርጅቶች በርግጠኝነት ከኢህአዴግ የተለዩ ያደርጋቸው ይሆናል እንጂ ያለቅድመ ሁኔታ የተሻሉ አያደርጋቸውም። ኢሳትም ለኛ ግሩም ሆነ ማለት፤ በርግጠኝነት ከኢቲቪ ይለየዋል እንጂ፤ ያለአንዳች ቅድመሁኔታ ከኢቲቪ የተሻለ ያደርገዋል ማለት አይደለም። (ይሄ፤ ለምሳሌ ያህል ነው እንጂ፤ ኢሳትንና ኢቲቪን አላወዳድራቸውም፤ ስለዚህ አንዳንዶቻችን ይቺን ሀረግ መዘን ወደ መደምደሚያ እንዳንከንፍ ወይም በኢሳት ላይ የተነሳሁ አይነት አድርገን እንዳንተረጉመው)። በአጠቃላይ፤ ከጠላቶቻችን የተሻልን ክፉዎች ልንሆን እንችላለን፤ ነገር ግን ተራችንን የምንጠብቅ መጥፎዎችም ልንሆን እንችላለን ነው ሁለተኛው ነጥቤ። እንጂ፤ የኢህአዴግን ክፋት ስላጋለጥንና ስለተቃወምን ብቻ የተሻልን ነን ማለት አይደለም። ባለፈው ሰሞን እንደቀልድ በወረወርኩት ጽሁፍ የመጣው ጣጣ ያንን ያሳያል። እኛም ከጠላቶቻችን የተሻልን ላንሆን እንደምንችል ይጠቁማል።
እንደማስታወሻ፡ ካለፈው የቀጠለ
5. ለማስታወስ ያህል፤ ያለፈው ጽሁፌ ሁለት ሀሳቦች ብቻ ናቸው ያሉት። አንደኛ፤ በህዝብ ዘንድ እየተወደደ እየታወቀ ተደማጭነት እያገኘ የመጣው ኢሳት የሚያደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ፤ በህዝብ ዘንድ አሉታዊም አዎንታዊም ውጤት ስለሚያመጣ፤ ጥንቃቄ ያድርግ የሚል ነው። ለምሳሌ፤ ከስድስት ከተሞች ውስጥ በአምስቱ ላይ የአንድ ሀይማኖት ብቻ ተወካዮችን መጋበዝ ብልህነት የጎደለው አካሄድ ነው የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፤ ከኢሳት ጊዜያዊ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅትም ባሻገር፤ ሀይማኖታዊ ጉዳዮችን የምንመለከትበት ቋሚ መንገድ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል የሚል ነው። ከዚያ ባሻገር ግን የመንግስትና ሀይማኖትን መለያየት በተመለከተ የቅንጦት የሚመስል ነገር ግን አስፈላጊ የሆነ ውይይት ለመጫር ነው ጽሁፉ ሙከራ ያደረገው።
6. የተሰጡትን ምላሾች ሁሉ ለማንበብ ግዜ አላገኘሁም፤ የተወሰኑትን ግን አለፍ አለፍ ብዬ ተመልክቻቸዋለሁ። አብዛኞቹ ስድቦች ናቸው። ብዙዎቹ አስተያየቶች ደግሞ አስፈግገውኛል። ከጨዋዎቹ ተቺዎቼ ውስጥ አባዛኞቹ ያተኮሩት “ይሄንን አደባባይ ይዘህ ባትወጣ ይሻል ነበር” የሚል ሲሆን፤ በጣም ጥቂት ጨዋዎች ደግሞ “እንዴት ኢሳትን ትነካለህ? ትደፍራለህስ?” የሚሉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። እንደትልቅ ድፍረት፤ ራስን ከገደል ጫፍ እንደመወርወር፤ ራስን እንደማጥፋትም የቆጠሩትም አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ግጭት የተፈጠረ፤ “የከዳሁ” ሁሉ የመሰላቸው አሉ።
7. ካለፈው የፖለቲካ ልምዳችን እንደምናውቀው፤ ሰው ካልተቀየመ ወይንም ካላኮረፈ ወይንም ካልከዳ ራሱንና የራሴ የሚለውን ስለማይተች፤ የበሰሉ፤ የተማሩ፤ በዚህ በምእራቡ ዓለም ለረጅም ግዜ ኖረው የሀሳብን በነጻነትና ያለፍርሀት መግለጽ ፋይዳ ተረድተዋል የተባሉት ሁሉ ያልጠበቅኩትን ተግሳጽ ሰንዝረዋል። በእውነቱ አንድን ጽሁፍ ብቻ መሰረት አድርገን፤ እዚህ ሁሉ ስጋትና ተግሳጽ ውስጥ መግባታችን የሚያሳየው፤ “ጸረ-ኢህአዴጉም ጎራ (የኛ ጎራ ማለት ነው)፤ መንግስት በሚማቅቅበት፤ “ከመንጋው የተለየ ሀሳብን የማስተናገድ ባህል እጦት እንደሚሰቃይ ነው።” ይሄ አደገኛ ነው። እነሆ ቃና ቀይሬ እንደ ንጉስ ላስረዳ ነው።
የትችት ትችት ትችት
8. ባለፈው ሰሞን ወዳጃችን ልጅ ተከሌ ማለፊያ ግሩም ጽሁፍ አንደጻፈ ሰማን። ጽሁፉም ተነበበልን። አሰላሰልነውም። አንዳንድ ሰዎች ለጽሁፉና ለጸሀፊው የሰጡት ምላሽ አላስደሰተንም። ቢሆንም አልገረመንም። ያንዳንዶቹ የተጻፈም ያልተጻፈም ምላሽ ግን አሳስቦናል። የልጅ ተክሌን ሀሳብ ከመተቸትና ከመበለት ይልቅ፤ ልጅ ተክሌን ወደመንቀፍና ወደማጠየፍ አዘንብለዋል። የጽሁፉን ፍሬ ነገር ሳይሆን የጸሀፊው ቁመትና ውፍረት ወርድና ክብደት ላይ የሚወያይ መብዛቱ አጅግ አሳስቦናል። ሀሳቡን ተችተው አስተያየት ለመስጠት የፈቀዱትም ቢሆኑ፤ ያተኮሩት፤ “የራስ ተቋም በአደባባይ አይተችም፤ ለጠላት ደስ ይለዋል፤ ንፋስም ይገባልና” የሚል አይነት ስሜት ይጎላበታል። አንዳንዶች ከቶም የጸሀፊውን ነገር የተገነዘቡ አይመስልም።
9. ቀድሞ ነገር፤ ልጅ ተክሌ የአገራችንንና የህዝባችንን ጥቅም የሚነካ ጽፉህ ይጽፋል፤ አገራችንን የሚጎዳ መንገድ ይሄዳል ብለን አንሰጋም። ይሄ እምነታችን ጥንትም ነበረ፤ አሁንም አለ። በርግጥ ልጅ ተክሌ ብዙም ባልተለመደ መልኩ አፈሙዙን፤ ወደወገን/ወደራሱ ማዞሩ ለብዙዎች ግርታን ቢፈጥር አይደንቀንም። ይሁን እንጂ፤ አንደኛ ልጅ ተክሌ ይሄን ሲያደርጉ የመጀመሪያው አይደለም። ሁለተኛ፤ የኛ የሆነውንና በኛ ምድር ላይ የተተከለውን ልጅ ተክሌ ከሀሳቡ አልፈን እሱን መጠራጠራችን በጎ ሆኖ አላገኘነውም። ስህተትም ነው። ይሄ ጽኑ የተለየ ሀሳብን የመፍራት ደዌም ነው። እስከመቼ የተለየ ሀሳብን እንሸሻለን? እስከመቼስ በራሳችን ድጋፍና ሰልፍ ጫጫታ ተውጠን እንኖራለን የሚል ጥያቄም ፈጥሮብናል? አንዳንዴ ወጣ ብሎ ማየት ያሻል።
የሀሳብ ነውር የለውም፡ የድርጊት እንጂ
10. የተለየ ሀሳብን መፍራት የለብንም። መጋፈጥ እንጂ። ሰው ነፍስ ካወቀ፤ የሀሳብ ነውር የለውም። የሀሳብ ጸያፍም የለውም። የሀሳብ ወንጀልም የለውም። ስለማይናገረው እንጂ ማንስ በጭንቅላቱ የሚያስበውን፤ በልቡም የሚመኘውን እንደምን እናውቀዋለን? ማንም ሰው፤ እንወያይበት፤ እናስበበት፤ እናድግበትም ዘንድ፤ ስህተትም ከሆነ እንዲታረምና እንዳይደገምም ብሎ ባደባባይ በስሙ በጻፈው ጽሁፍ ሲሆን ሲሆን ሊሸለም እንጂ ሊጎሸም አይገባውም። በርግጥ ልጅ ተክሌ ሲጎሸምና ሲዘለዘል የኖረ ወዳጃችን ስለሆነ፤ በአመታት ትችትና ነቀፋ የደነደነው ቆዳው በዚህ ይሰነጠቃል ብለን ከቶም አንሰጋም። የሰዎቻችን ከተለመደው የተለየ ሀሳብን ለማስተናገድ የመፍራትና የመቅፈፍ ነገር ግን ረብሾናል።
11. ደግሞስ በዚህ በምእራብ የነጻነት አጥቢያ የምንኖር ሰዎች ስለምን ትችትን እንፈራለን። ስንት ነገርስ እንፍራ? ስንት ነገርስ ያሸብረን? ኤደን ባህረሰላጤንና ሳህል በረሀን፤ አባይንና ጎጀብን ተሻግረን ተሰደን፤ በንጽጽርም ቢሆን የተሻለ ነጻነት ካለበት ዓለም መጥተንም፤ የተለየ ሀሳብን የመፍራት ሰቀቀን ይከተለን? እንግዲያውስ እላችሁዋለሁ፤ ነጻነታችንና ዴሞክራሲያችን በአለት ላይ እንጂ በአሸዋ ላይ መገንባት እንደሌለበት ህዝባችን ሊያውቀው ይገባዋል። “ይሄን ሀሳብ አንሸራሽር፤ ይሄንን ሀሳብ ግን ከቶም አታንሳው” የሚል ማእቀብና ምክር፤ በአገራችን እንዲሰፍን የምንመኘው ዴሞክራሲና ነጻነት ጸር ነው። ይሄ እስክንድር የታሰረለት፤ ርእዮትም የታጎረችበት፤ ሲሳይም የተሰደደበት ራእይ አይደለም። ደግሞስ፤ ይሄንን የሚፈቅደውስ ማነው? ህሊናችን አይደለምን? ከህሊናችን በላይ የተሻለ ከልካይስ፤ ፈቃጅስ ከወዴት ይገኛል?
12. ለዚህ ነው እኛ ሰው ህሊና ይስጥህ ሲባል እንጂ ልቡና ይስጥህ ሲባል የማይረዳኝ። ህሊና ያለው ሰው ደግሞ ህሊናው የፈቀደውን እንዲናገር፤ ህሊናውን የደረሰበትን ግኝት እንዲመሰክር ልናበረታታው ይገባል እንጂ፤ ልናከላክለው አይገባም። ካልሆነም ደግሞ የጸሀፊውን ሰብእናውን ሳይሆን ሀሳቡን ልንመትረው፤ እይታውን ልንተቸው፤ አመለካከቱን ልንተረክከው እንችላለን። እንጂ የጸሀፊውን ሰብእና ለማጥቃትና ጸሀፊውን ትልቅ ሀጢያት እንደፈጸመ በማነጣጠር የምንናገረውም የምንጽፈውም እኛ የታገልንለትንና ለህዝባችን ልናወርሰው የምንምለውንና የኛን ህልም የሚያንጸባርቅ አይደለም።
የማይጠየቅ ተቋም፤ የማይተች እውቅና
13. ወዳጃችን ልጅ ተክሌ ከዚህ ቀደምም ብዙዎቻችን የምንሸሻቸውን ሀሳቦች ለመናገር የሚጀግን፤ ብዞዎቻችን የምናፍራቸውን ሀሳቦች ለመጻፍ የሚተጋ የስደት ወዳጃችን ነው። ባለፈው ጽሁፍ ያነሳውም ሀሳብ፤ ምንም የሚጣል የለበትም ብለን ባንመሰክርም፤ በራሱ የሚተማመንንና በአለት ላይ የተገነባ ዴሞክራሲን ለመገንባት የሚተጋን ቡድን የሚያስደነግጥ ነገር አላገኘንበትም። ያለበለዚያማ በሚጻፈውና በሚወራው ጠላታችን መደንገጡ፤ የሚናገሩና የሚጽፉትንም ወደእስር ማጋዙ ስህተት አይደለም ማለት ነው። እኛ መንግስትነትን አጥተን በተለዩ ሀሳቦች መንሸራሸር ይሄን ያህል ከበረገግን፤ የመንግስትነትን ስልጣን የያዘው አካል በተቺ ሀሳቦች መንሸራሸር ቢጨነቅና መንገደኛውን ሁሉ ቢያስር ምን ያስደንቃል?
14. በርግጥ፤ ወዳጃችን ልጅ ተክሌ በሰዎች ዘንድ ታምኖ የተነገረውን ምስጢር ያባከነ፤ ወይንም እሱ ለድርጅቶች ባለው ቀረቤታ ያገኘውን መረጃ የተጠቀመ ባሪያችን ቢሆን እኛም ይከፋን ነበር። አንለቀውምም። ለጥፋቱ እንቀጣው ነበር። ይሁን እንጂ ልጅ ተክሌ የተጠቀመው መረጃ ሁሉ አደባባይ በህዝብ ዘንድ በግልጽ ያለ እንጂ፤ የተተቸው ተቋም ጋር በሚሰራበት ግዜ ያገኘው መረጃ አይደለም። ደግሞስ የማይተች እውቅና፤ የማይጠየቅ ተቋም ለመመስረት ነው እንዴ የምንታገለው? እንግዲያውስ ያለፉትን አስር አመታት ብቻ ብንገመግም፤ ትልቁ የጎዳንና እንዳናንሰራራ ቀስፎ የያዘን ጥፋት የምንክባቸውን ለመተቸት፤ የምንቆልላቸውን ለመጠየቅ አለመድፈራችን፤ “ዝም በሉ፡ ጠላት እንዳይሰማ፡ በቃ ይሁንላቸው ይደረግላቸው” የሚለው የተለማማጭነትና የሰቀቀን ባህርይ ነው።
አደባባይ ወይስ ወደጓዳ?
15. በልጅ ተክሌ ላይ ከተሰነዘሩት ትችቶች መካከል፤ “ትችቱ ለምን በአደባባይ ሆነ? ውስጥ ለውስጥ አይሻልም ነበር ወይ” የሚሉት ጥያቄ-ተኮር ትችቶች መልካም እንደሆኑ ይሰማናል። የኛም ሀሳብ ይኸው ነው። ይሁን እንጂ፤ ያ አንድ መንገድ ነው። ብቸኛው መንገድ አይደለም። ልጅ ተክሌም የተከተለውን መንገድ ለመከተሉ ጥሩ ምክንያት ይኖረዋል። ልጅ ተክሌ እንዲህ ያለውን ትችት ይዞ ወደአምባ ሲወጣ፤ ግራ ቀኙን አላየም፤ በቅጡም አላሰላም ለማለት አንደፍርም። መጠየቅ ያለብንን በአደባባይ ባለመጠየቃችን፤ መናገር ያለብን በአደባባይ በግዜ ባለመናገራችን ምክንያት እነሆ ቅንጅት እንደብጉንጅ ውስጥ ውስጡን አብጦ፤ በመጨረሻ አይፈርጡ አፈራረጥ ፈረጠ። ከቅንጅት ቁስል እስካሁንም አላገገምንም። እንደልደቱ አያሌው ያሉ እስካሁንም ያልተካናቸውን ትንታግ ፖለቲከኞች አጣን። (በዚህ ሀሳብ ብቻ የምንበሳጭ እንኖራለን፤ ይሁን እንጂ ልጅ ተክሌ “ልደቱ ናፈቀኝ” የሚል ጽሁፍ እየጻፈ እንደሆነ ጠቁሞናልና ከዚህ ለሰላውም ትችት እንዘጋጅ)።
16. በመሰረቱ በአደባባይ የሚነሱና ውስጥ ለውስጥ የሚነገሩ ሀሳቦች ውጤታቸው አንድ አይደለም። በአደባባይ የሚነገር ነገር ትኩረት ይሰጠዋል። ሰዎች ይወያዩበታል። ተወቃሾችና ተከሳሾች ካሉም ለወደፊቱ ያርሙታል። ተጠያቂ አካልም ወደፊት እጋለጣለሁ ሲል አግባብ ካልሆነ ስራ ይታቀባል። ውስጥ ለውስጥ የሚደረጉ አስተያየቶችና እርማቶች ከስራ ላይ ይልቅ ወደ ቆሻሻ ቅርጫት እንደሚዶሉ የልጅ ተክሌ ምስክርነት አያሻንም። እንጂ፤ የጋዜጠኞቹ ትጋትና ፍጋት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በየአካባቢው የሚገኙ የኢሳት ደጋፊዎች አስተዳደራዊ ምሬትና ስሞታ ቢጻፍ፤ “ይሄ ድርጅት እስካሁንስ እንደምን ቆመ?” ያሰኛል። “ወደፊትስ ይቆማልን?” የሚለውም ጥያቄ የሰይጣን ጆሮ አይስማው በማለት ብቻ የሚጠፋ አይደለም። እንደ ኢሳት ያለ ህዝባዊና ተስፋ የተጣለበት ተቋም እንዲያድግ የአደባባይ ውይይት፤ የግንባር ትችት፤ የፊት ለፊት እርማት ያስፈልገዋል። የምንፈልገው ተቋም በአደይና በጸደይ (የሰዎች ስም ናቸው) ላይ የቆመ ሳይሆን በአለት ላይ የተተከለ መሆን ነው ያለበት። እስካሁንም ሰዎች መካብ እንጂ ድርጅቶች/ተቋማት መገንባት አልቻልንምና።
በአደባባይ የሚሰራ በአደባባይ ይጠየቃል
17. ደግሞስ ኢሳት በአደባባይ የሚሰራ የአደባባይ መገናኛ ብዙሀን እንጂ የህቡእ ጋዜጣ አይደለም። ሰለዚህ ኢሳት ለሚሰራው የአደባባይ ስራ በአደባባይ መጠየቅ አለበት። ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት “የእንወያይ፡” ዝግጅታቸው ላይ ወዳጃችን ፋሲል የኔዓለምና አፈቀወርቅ አግደው ያንጸባረቁትን ሀሳብ በአደባባይ እንጂ በውስጥ ተቹ ማለት ስህተት ነው። ምክንያቱም እነሱ ስህተት ቢሆንም ባይሆንም ሀሳባቸውን በአደባባይ የማንጸባረቅ እድል ሲያገኙ፤ የነሱን ሀሳብ የሚቃወመው ሰው ግን በውስጣዊ አስተያየት ብቻ መወሰኑ፤ የነፋሲልን ሀሳብ የሰሙት ሰዎች፤ የተለየውን ሀሳብ እንዳያዳምጡ እድል መንፈግ ነው። ይሄ ኢሳት የቆመለት ኢሳት የቆመበትም መሰረት አይደለም።
18. የሰማያዊ ፓርቲ በመጪው የአፍሪካ አንድነት/ህብረት 50ኛ አመት ምስረታ በዓል ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርቷል። ከአገራችን ያላግባብ የተነቀልን ተቃዋሚዎች ነን የምንል ሰዎችም ድርጅቶችም፤ እንዲህ ያለውን ሰልፍ፤ ጠሪዎቹ ለምንም ዓላማ ይጥሩት “በርቱ ግፉበት፤ ብቻ እንዲህ ብታደርጉት መልካም ነው፤ ይሄንንም ብታክሉበት ሸጋ ነው” ማለት ነው ያለብን። እንጂ ዓላማቸውን ሙሉ በሙሉ ማራከስ፤ አግባብ አይደለም። ልጅ ፋሲል ግን የሰዎቹ የሰልፍ ጥሪ ሀቀኛ መሆኑን እንደሚጠራጠርና እንዲያውም ትኩረት ለማግኘት ያደረጉት አይነት ጥሪ እንደሆነ ነው የተናገረው። ያ ብቻም አይደለም፤ ይሄ አይነቱ ሰልፍ ቢደረግም እንኳን፤ ስርአቱን በምእራባዊያን ዘንድ ሰልፍና ተቃውሞ ፈቃጅ ሊያስመስለወም ይችላል የሚል ፍራቻ አንጸባርቋል። በርግጥ ልጅ ፋሲል ሀሳቡን የሰጠው በግሉ እንደሆነ ቢናገርም፤ እሱ የኢሳት ዋና ማኔጂንግ ኤዲተር እንደመሆኑ መጠን አንድን ነገር ተናግሮ በግሌ ነው የተናገርኩት በማለት ብቻ ሊያመልጥ፤ ኢሳትንም ነጻ ሊያደርገው አይችልም።
19. በሀላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ብዙውን ግዜ ይሄንን በግሌ ነው ያልኩት የድርጅቱ አቋም አይደለም የሚል ብልሀት ይጠቀማሉ። ልጅ ፋሲል በአስተያየቱ ላይ ከዚህ ቀደም ኢሳት የሰራቸውን ተመሳሳይ የሰልፍ ጥሪ ዘገባዎች እንደምሳሌ አቅርቧል። ከተቀመጠበት የሀላፊነት ወንበር አንጻርም የሚሰነዝረው እያንዳንዱ ሀሳብ የኢሳት ሊመስል፤ ሊሆንም እንደሚችል መረዳት አለበት። እንዲህ ያለውን በአደባባይ የተነገረ ሀሳብ መተቸት ያለብን፤ ኢሳት አንዳንዴ ፈንገጥ ያለ ሀሳብ አይመቸውም እንጂ ሲሆን ሲሆን በራሱ በኢሳት ላይ፤ ያለበለዚያ ግን በተገኘው መድረክ ነው። የለም እንቶኔን አትንኩ የሚለው አስተያየት፤ ለራሱ ለእንቶኔም አይበጅም።
ለነገሩ የኛ ችግር፡
20. ለነገሩ በስደት የምንገኝ ድርጅቶችና ተቃዋሚ ግለሰቦች፤ በአገር ቤት የኛን ስደትና ሚና የሚቀንስ፤ የኛን መኖር ምክንያት የሚያሳጣ እንቅስቃሴ የሚጀምር ሲመስለን፤ ያንን እንቅስቃሴ ለማጣጣልና ለማራከስ እንፈጥናለን። ይሄ እኛም በስደት ወደኬንያ ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ፤ ላለፉት 12 አመታት በኢህአፓም በመኢሶንም፤ በቅርቡ ደግሞ በነግንቦት ሰባትም በነከበደም በነገመቹም ላይ ያስተዋልነው በሽታ ነው። ልክ የዛሬ አስራሁለት አመት ተሰደን ወደናይሮቢ ስንገባ የተቀበሉን ደግ ድርጅቶች ከነገሩንና እስካሁንም ከትውስታችን ካልወጣው ነጥብ አንዱና ዋንኛው “አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች መኖር፤ በምእራባዊያን ዘንድ፤ አገር ቤት ዴሞክራሲ ያለ ያስመስላል” የሚል ነጥብ ነው። እነሆ ታሪክ ራሱን እንዳይደግምና፤ እኛ ከአመታት በፊት እንከሰሰስበት የነበርነውን፤ ማለትም የአገርቤቱ እንዲህ ነው የሚለውን ክስ፤ እኛም በተራችን እንዳንደግም መጠንቀቅ አለብን። ከፖለቲካ ወንጀሎች ሁሉ የከፋው ሌሎችን የከሰስንበትን ጥፋት ወይም በሌሎች በስህተት የተከሰስንበትን ጥፋት እኛ ስንፈጽም ነው።
21. ይቀጥላል።
እኛው ነን፤ ግንቦት ልደታ፤ 2005፤ ተረንቶ፤ ከናዳ

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሁሉም አከባቢዎች ያሉ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኞች ሃገር የቆመበትን ምሰሶ የሚቦረቡሩ ቅንቅኖች ናቸው!!!

3 Comments

  1. በጣም ግሩም ሀሳብና ጥልቅ ትንታኔ ነው ያቀረብከው። አንተ እንዳልከው የኢህአዴግ መጥፎ መሆን ብቻ ተቃዋሚዎቹን ጥሩ አያደርጋቸውም። የኢቲቪ መጥፎ መሆን ብቻ ኢሳትን ጥሩ አያደርገውም። የተሻለ መጥፎ ብቻ ሳይሆን የባሰ መጥፎ መሆንም አለ። ተቃራኒ ሀሳብን ስለማስተናገድ የሰነዘርከው አስተያትም ድንቅ ነው። ከሁሉም ግን ነጥብ ፳ ላይ ያቀረብከው ሀሳብ ተመችቶኛል።

  2. አበበ በመጀመሪአ፡ትሩ አመለካከት ነው”ወንድሞቸሀ ናቸውና፡ባደባባye:ayhune shtete kale be terebeza ye feta’.1 weyna ante ya wetahwene temelkto aysmamume alalkuhme alge .yhe democracy aserare new alkute .malet yefelkute ,le hzbe yemetay sayhone be fit le fit be mengager yefeta

Comments are closed.

Share