ተገፊዎች የባህሪ ለውጥ ኣምጡ እንጂ! ከገለታው ዘለቀ

ከ ገለታው ዘለቀ

ልትታተም ካሰበች ኣንዲት ልቦለድ ጽሁፍ ላይ ኣንድ የምናብ ሰው ከተገረመበት ነገር ተነስተን ኣጭር መልእክት ለማቀበል እንሞክራለን። ይህ የምናብ ሰው ወደ ኣንድ ሃገር ይሄድና በዚያ በኣንድ ሆቴል ውስጥ ተቀምጦ ናሽናል ጂኦግራፊ የተሰኘውን የ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ያያል። በወቅቱ ይተላለፍ የነበረው ፕሮግራም የዱር እንስሶች ኑሮ ነው። ይህ የምናብ ሰው ከኣልጋው ጫፍ ላይ ቁጢጥ ብሎ ረጃጅም ጢሙን ቁልቁል እየላገ ይህን ፕሮግራም ያያል። የሚያማምሩ የሜዳ ኣህያዎች መንጋ ረጋ ብሎ ሳሩን ይግጣል። ጥቂት ሳይቆይ ከረጃጅሙ ሳር ውስጥ ሲሹለከለኩ የነበሩ ሶስት ጅቦች መጡ። ኣንዱን ጅብ ቀድሞ ያየው የሜዳ ኣህያ ሩጫውን ሲቀጥል ሌላው ነገሩ ያልገባው ሁሉ ተከትሎ ይሰግር ጀመር።

የሜዳ ኣህያዎቹም ተፋፍገው ሲሮጡ ኣንድ ወደ ሁዋላ ቀረት ያለ የሜዳ ኣህያ  ነበርና ኣንዱ ጅብ ከሆዱ ቆዳውን ሊዘነጥል ይጥራል። ይህ የሜዳ ኣህያ እግሮቹን እያወራጨ ለማምለጥ ይጥራል። ትግሉ ከሚሮጡት ጋር ሩጫውን ለመቀጠል እንጂ የሚነክሰውን ጅብ ለመጉዳት ኣይደለም።

ሌሎቹም ጅቦች ተጋገዙና ምን ዋጋ ኣለው ይህን የሜዳ ኣህያ ሆዱን ዘረገፉት።

ያ የምናብ ሰው ተገረመ። ኣየ ኑሮ…………

ወደ ሌላ ኣንዲት ወንዝ ስር ጥሙን ሊያረካ ውሃ ከሚጠጣ ሌላ ያማረ የሜዳ ኣህያ ጋር ካሜራው ወሰደው። ይህ የሜዳ ኣህያ ሁለት የፊት እግሮቹን  ፈርከክ ኣርጎ እንዴው እግዜር የሰጠውን ውሃውን በፍቅር ይስባል። ጥቂት ሳይቆይ ኣንድ ሌላ ጅብ ከሁዋላው ዘሎ ከሆዱ ቆዳውን ሊዘነጥል ትግል ጀመረ። ይህ የሜዳ ኣህያ ከወራጁ ወንዝ ጫፍ ላይ ተክሎት የነበረውን ኣፉን ነቀል ኣረገና ወደ ሁዋላ በቅጽበት ዞረ። የሚታገለውን ጅብ እንደሌሎቹ የሜዳ ኣህያዎች በርግጫ ብሎ ለማምለጥ ኣይጥርም። ኣንገቱን ጠምዝዞ ኣንድ ሁለቴ ዞረና ወደ ሆዱ ገብቶ ቆዳውን ሊዘነጥለው የሚታገለውን ጅብ ጉሮሮ ኣስግጎ ኣገኘውና በዚያ ላይና ታች ክችም ባለ ጥርሱ የጅቡን ጉሮሮ ቀርጥፎ ይዞ ትግል ተጀመረ። ኣሁን ጅብ ማጥቃቱን ትቶ ራሱን ለማዳን እየታገለ ነው። ነገር ግን ኣልሆነም።  ይህ የሜዳ ኣህያ የዋዛ ኣልነበረም። ጥቂት ደቂቃዎች ከታገሉ በሁዋላ ጅቡ መታገሉን ሲያቆም የሜዳው ኣህያ ሙሉ በሙሉ ከሜዳው ላይ ኣንጋለለውና ያየው ጀመር። ጥቂት ኣሸተተውና ጥሎት ለመሄድ ርምጃ ሲጀምር ኣንድ ሌላ ጅብም መጣ።  ያ  የሜዳ ኣህያ በሃይል ወደ ጅቡ መሮጥ ሲጀምር ጅቡም ቂጡን ጥሎ ሮጠ።

የምናቡ ሰው ይህን ነገር እያየ ተገረመ። ለካ ይሄ የሜዳ ኣህያ ብቻውን በዚህ ጠራራ ጸሃይ በዚህ ወንዝ ሥር የሚያንቀባርረው የባህሪ ለውጥ ኣምጥቶ ነው። እየተራገጡ መሮጥን ኣቁሞ መናከስ ጀምሩዋል። ይህ የባህሪ ለውጡም ከተጠቂነት ወደ ኣጥቂነት ኣሸጋግሮታል እያለ ይደነቃል…………

በኣንድ ሃገር የሚኖሩ ህዝቦች ኣንዳንዴ ጅብ በሆነ ስርዓት ይጠቃሉ። ጥቂት ቡድኖች ያለውን የሃገሪቱን ሃብት ተቆጣጥረው ኣብዛኛውን ሰው ጦሙን ያሳድሩታል። የኢኮኖሚው ሰፊ ልዩነት ሌሎች የህይወት ዘርፉን ሁሉ ያጠቁትና ያልተመጣጠነው እድገት በፍትህ ፊት፣ በባህልላዊ ቡድን፣ በኣጠቃላይ በኑሮ ዘየ ሁሉ ከባድ የእኩልነት እጦትን ይስብበታል።

ዛሬ ኢትዮጵያ ቢሊየነር ሁሉ ያላት ኣገር ናት። በሌላ ጥግ ደሞ የ ዓለምን የመጨረሻ ድህነት የሚኖሩ ብዙ ህዝቦችም ኣሉባት፣ ይህ ሰፊ ያልተመጣጠነ እድገት በተወሰነ ደረጃ ቢሳለጥ ኣሁን ያለው የድህነት ገጽታ መልኩን ይቀይር ነበር። የገቢ ኣለመመጣጠን ስንል ሁሉ እኩል ይካፈል ማለታችን ኣይደለም። ሁላችን እኩል በመካፈላችንም ፍትህ ኣይሰራም። ግን ደሞ ለሃብታሙ ህንጻ የሚሰራው ወዛደር ቢያንስ ቤት ኣከራይቶ የቀን ኑሮውን የሚገፋበትን ሊከፍለው ይገባል። ቀን ቀን ኣሸዋና ሲሚንቶ ሲያቦካ ውሎ ለምን ጎዳና ላይ ይወድቃል? መንግስትስ እንዲህ ያለውን ኣስከፊ ስርዓት ለምን በተወሰነ ደረጃ ኣያጠብም? ለምን ፖሊሲ ኣያወጣም?። የካፒታሊዝም ጽንሰ ሃሳብ እኮ እንደዚህ ኣይደለም።  ካፒታሊዝም ፍትህ ኣለው። ዜጎች ባላቸው የሥራ ኣቅም እየሰሩ የተለያየ የገቢ መጠን መኖሩ ትክክል ነው። ይሁን እንጂ ድሃውን ያለልክ ጎድቶ ሃብታሙን ያለልክ ማበልጸግ የካፒታሊዝም ስርዓት ልብ ኣይደለም።

የሚገርመው ስርዓቱ ፍትሃዊ ባይሆንም እነዚህ ዜጎች ኣይናከሱምና ኑሮኣቸው ሁሉ የሚያሳዝን ይሆናል::

ደሞ መንግስት ሥራ ጠፋ ሲሉት ሥራ ንቃችሁ ነው ኣይነት ይናገራል። ተናቀ የተባለው ስራ ምንድን ነው? ብላችሁ ብትጠይቁ ያው የወዛደርነት ሥራ ነው። የመጀመሪያው ጥያቄ ታዲያ ኣሁን ይህ ሚሊዮን ሥራ ኣጥ በቃ ሥራ ኣንንቅም እሺ ወዛደርነቱን እንሥራ ብሎ ቢወጣ ይህንን የሚያስተናግድ ኢንዱስትሪ ወይም የኮንስትራክሽን ስራስ የታለና ነው? የትኛው የፋብሪካ ስራ ወይም የኮንስታራክሽን ስራ በወዛደር እጦት ስራ ኣቆመ?

እውነቱን ለመናገር ኣንዳንድ ሰው ወደ ወዛደርነት ስራ የማይሳበው ገቢው ስላነሰ ወይም ስለማያኖረው ነው። በሃገራችን ውስጥ የሲቪል ኤንጂኔር ስራ ስለምን ተከባሪ ሆነ? ባህላዊው ሲቪል ኤንጂነር (ኣናጺው) የተከበረ ነበር ወይ? ብለን ብንጠይቅ ኣልነበረም:: “ኣናጢ መናጢ” ነበር የሚባለው። ምንም የሌለው ድሃ ማለት ነው መናጢ ማለት። ሁዋላ ላይ ታሪክ ተቀየረና ዘመናዊ ትምህርት ተምረው የመጡ ኣናጺዎች (civil engineers) ገቢያቸው ዳጎስ ያለ በመሆኑና የነሱን ኑሮ ብቻ ሳይሆን የቤተሰባቸውን ህይወት የሚቀይር ገቢ ስላላቸው ተወደዱ።

በድሮ ጊዜ፣

“የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ

ወሰደሽ ኣስተማሪ…” ይባል ነበር ኣሉ።

በኔ ጊዜ ኣስተማሪ ለትዳር የማይመረጥበት ጊዜ ስለምን ሆነ? ያው ከኑሮው ጋር ከገቢው ኣቅም ጋር ተያይዞ ነው።

ያ የሜዳ ኣህያ ዘይዱዋል። የባህሪ ለውጥ በማምጣቱ ተከብሮ ከተባራሪነት ወደ ኣባራሪነት ተሸጋግሩዋል። የተባረከ ነውና የጅቡን ስጋ ግን ኣይበላም። እነዚህ እንስሳት እንደዚህ የሜዳ ኣህያ የባህሪ ለውጥ ቢያመጡ ያ ጅቡም ቅጠላቅጠል መብላት ይጀምርና የነዚህ እንስሶች መንደር ሰላም ይወርድበታል።መከባበር፣ መተሳሰብ ይመጣና ኣብረው ይኖራሉ። ጅብና የሜዳ ኣህያ ሳይጠራጠሩ ተቃቅፈው ያድራሉ::

ድሆች በኢትዮጵያ ውስጥ የባህሪ ለውጥ ሊያመጡ ይገባል። እነዚህ በሙስና የከበሩ ሚሊየነሮችና ቢሊየነር ኢትዮጵያ ውስጥ  ስንት ፊላንትሮፒክ ወይም ሰባዊ የሆነ ድርጀት እንዳላቸው ወይም እንደሚረዱ  ኣላውቅም። ርሃብ ሲመጣ ኣለማቀፍ ድርጅቶች ናቸው ስንዴና ዘይት ለማቅረብ ሲሮጡ የሚታዩት።

ዛሬ ሃገራችን ባልተመጣጠነ እድገት ጎዳና ላይ እየነጎደች ነው። ያለው እየጨመረ፣ የሌለው የሚበላው እያጣ ወጣቱ ጢሙን ኣንዠርግጎ የጡረታ ኣባቱን ቤት ሳይለቅ እየኖረ ነው። ካልተናከሰ እንዲሁ ይኖራል።መናከስ ከጀመረ የባህሪ ለውጥ ካመጣ ግን ተከብሮ፣ መብቱ ተጠብቆ ይኖራል።

ኣንድ ጊዜ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ የ ኢትዮጵያ ጦር ላይቤሪያ ዘምቶ ነበር። በዚያ ቆይታው ዩናይትድ ኔሽን (UN) ዳጎስ ያለ ኣበል ያስብለት ነበርና ይህንን ኣበሉን የኢትዮጵያ መንግስት እኔ ኣከፋፍላለሁ ብሎ ነው መሰለኝ ይቀበላል። ተቀብሎ ለወታደሮቹ ማካፈል ነበረበት። ይሁን እንጂ ይሄ የጅብ ባህሪ ያለው ኣሰራራቸው ባህሪ ሆኖባቸዋልና ያንን ገንዘብ ቆይ ዛሬ ቆይ ነገ እያሉ ያቆዩባቸዋል። መንግስትን የሚያህል ትልቅ ነገር የነዚያ የድሃ ወታደሮች ኣበል ኣጓጉታው ኣልሰጥም ብሎ ቆየ። ከተዘራፊዎቹ ኣንዱ መንግስት ዘረፈኝ ብሎ ኣስቆናል። እንግዲህ ይታያችሁ ዩናይትድ ኔሽን ለሰጠው መንግስት ቀንቶ እነዚያን ድሆች ቀማ። ሁዋላ ላይ ግን እነዚህ ወታደሮች ኣምጸው እንደነበር ዜና ሰምተናል። መንግስትም ደንግጦ እሰጣለሁ ብሎ ነበር መሰለኝ። መናከስ በመጀመራቸው እንጂ መንግስት የልፋት ዋጋቸውን ነጥቆ ኣፍንጫችሁን ላሱ ብሎ ነበር።በጠራራ ጸሃይ መንግስት እንዲህ ኣድርጎ ድሆችን የሚቀማባት ኣገር ናት ኢትዮጵያ።

ቸሩን ያሰማን ጃል!

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ

geletawzeleke@gmail.com

1 Comment

  1. ገለታው ውስጠ ወይራ የሆነች አፃፃፍህን አድንቂለሁ::እንዳልከው የባህሪ ለውጥ ስላላመጣን ነው መራመጃ መቆሻመጃ ያጣነው::”ሊነጋ ሲል ይጨልማል”!

Comments are closed.

berhan hailu
Previous Story

የፍትህ ሚ/ሩ ብርሃን ኃይሉ ከስልጣናቸው ተባረሩ

piremier legue
Next Story

የ2012/2013 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አስሩ መጥፎ የተጫዋች ዝውውሮች

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop