ፍርድ ቤቱ ባለፈው ውድቅ ያደረገውን ጉዳይ ዛሬ ያለምንም ይግባኝ ማፅደቁ ተሰማ

ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. የነበረው የፍርድ ቤት ውሎ አዲስ ክስተትን ይዞ ብቅ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ባለፈው ሚያዚያ 2006 ዓ.ም.ተጠርጥረው ከታሰሩ 3 ጋዜጠኞች እና 6 ብሎገሮች መካከል ዛሬ እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ የነበራቸው በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ እና ማህሌት ፋንታሁን ቀደም ሲል የማዕከላዊ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት የክስ ጉዳይ ለመውሰድ የጠየቀው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ በሌላ ተቀያሪ ወንድ ዳኛ እዛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ባለፈው በነበረው ቀጠሮ ውድቅ የተደረገው በፀረ-ሽብርተኝነት ክስ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎ የነበፍቃዱ ፣ አቤል እና ማህሌት ሂደት ለሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ተከላካይ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን፤ ከህግ አኳያ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት ጠይቆ ውድቅ ተደርጎበታል፣ ስለዚህ በነበረው ውሳኔ ፖሊስ ቅር ከተሰኘ ይግባኝ ማለት እንጂ በተመሳሳይ ችሎት እና ጉዳይ ላይ በፍርድ ቤቱ ውድቅ የተደረገ ጉዳይ እንደገና ቀርቦ የፖሊስ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ እና ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ በሚል መፈቀዱ ከህግ አግባብ ውጭ ነው፤ ይሄንንም ለፍርድ ቤቱ ብናቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፤ ስለዚህ የህግ አካሄድ (procedure) ስህተት ታይቶበታል ሲሉ የነበረውን ሂደት ተናግረዋል፡፡ ይህን የክስ ሂደት ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት ለመውሰድ ውድቅ ያደረገችው ዳኛ ሴት እንደነበረች አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ በላይ ማናየ ፖሊስ ፍርድ ቤት ያቀረባቸውን እስረኞች ሲያወጣ፤ ለተወሰነ ጊዜ በጠበቂ የፀጥታ ኃይሎች ለጊዜው ታግቶ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ፤ ለነገ ማዕከላዊ እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ተለቋል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገው የጋዜጠኛው እገታ ምክንያት እስካሁን አልታወቀም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአባይ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር እየተነጋገርኩ ነው አለች

(Bisrat Woldemichael/Addis Ababa)

 — with Izedine Yahya.

Share