April 27, 2014
20 mins read

ብቸኛው ሰው (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም)

ፀሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
——–
ፕሮፌሰር መስፍንን በአካል ያየሁት ሁለት ጊዜ ያህል ብቻ ነው፡፡ በነዚህም ጊዜያት ከመጨባበጥ በቀር ሌላ ነገር ማውጋት አልቻልንም፡፡ ብንጨዋወት እንኳ በፖለቲካ አመለካከታችን የምንግባባ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ እሳቸው “ኢትዮጵያ ውስጥ ነገዶችና ጎሳዎች እንጂ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የሉም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንድ ብሄር ብቻ ነው” ነው የሚሉት፡፡ እኔ ግን “በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አሉ፤ ነገድና ጎሳ የብሄር ቅርንጫፎች እንጂ ራሳቸውን የቻሉ ህዝቦች አይደሉም” ነው የምለው፡፡ በሌላ በኩል ፕሮፌሰር መስፍን “የብሄረሰቦችን መብት ለማስከበር በብሄር መደራጀቱ ለሀገር አንድነት አደጋ አለው” የሚል እምነት አላቸው፡፡ እኔ ግን “ለመጥፎ ዓላማ እስካልሆነ ድረስ በብሄር መደራጀቱ መጥፎ አይደለም” የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሌላም ብዙ ልዩነት ማስቆጠር ይቻላል፡፡

ይሁንና በፖለቲካ እንዲህ የተለየኋቸውን ምሁር ለአንድም ቀን እንደ ጠላት አይቼአቸው አላውቅም፡፡ በተቃራኒው ህሊናን በሚያምራምሩ ብዙ ባህሪያቶቻቸው በጣም ያስቀኑኛል፡፡ “እኛስ መቼ ነው እንደርሳቸው ሆነን ለሀገራችንና ለህዝባችን ክብር የምንቆረቆረው” እላለሁ፡፡ ከዚህ ፈቅ የሚሉት አንዳንድ አድራጎታቸው ግን በነቢያትና በቅዱሳን ካልሆነ በቀር ከኛ ዘመን ሰው የሚጠበቁ አይደሉም፡፡

በእርግጥ እላችኋለሁ! ፕሮፌሰር መስፍን በብዙ አጋጣሚዎች “ሰው ማለት… ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ ዕለት” የተሰኘውን ብሂል በተግባር ከውነው ያሳዩን ብሄራዊ ጀግና ናቸው፡፡ እኝህ ታላቅ ሰው ሀገራችን ሰው በምትፈልግበት ልዩ ልዩ አጋጣሚዎች በልዩ ድፍረትና ልበ ሙሉነት በከወኗቸው ድርጊቶቻቸው የህዝብ ልጅ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ለብቻቸው ሆነው የፈጸሟቸውን በርካታ ገድሎች መዘርዘር እንችላለን፡፡ ለዛሬው ግን በጣም ጥቂቶቹን ብቻ እንዲህ እንዘክርላቸዋለን፡፡

=== የትግራይና ድርቅና ረሃብ===

ብዙዎቻችን በ1965 ስለተከሰተው የወሎ ረሃብ በቂ መረጃ አለን፡፡ ከዚያ አስቀድሞ በ1950ዎቹ ስለተከሰተው የትግራይ ረሃብ ግን ብዙም ሲጻፍ አላነበብኩም፡፡ ችግሩ የተከሰተው የያኔው ረሃብ እንደ 1965ቱ ረሃብ በቂ የሚዲያ ሽፋን ባለማግኘቱ ይመስለኛል፡፡

በርግጥም ያ ረሃብ ከፍተኛ እልቂት የታየበት ነበር፡፡ የንጉሡ መንግሥት የረሃቡ ወሬ ታፍኖ እንዲቀር በማድረጉ በልዮ ልዩ ክፍለ ሀገራት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለትግራይ ወገኑ ሊደርስለት አልቻለም፡፡ መኳንንቱና መሳፍንቱ ከድሮም ጀምሮ የደሃው ህይወት ስለማያሳስባቸው የረሃቡን ጉዳይ ከቁብ አልቆጠሩትም፡፡ በዚያ ወቅት ድምጹን ያሰማው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ መስፍን ወልደማሪያም ነበር፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን የረሃቡን ወሬ የሰሙት ከተማሪዎቻቸው ነው፡፡ ረሀብ በትግራይ መኖሩ ሲነገራቸው ለንጉሡ መንግሥት ባለስጣናት አቤት አሉ፡፡ ሆኖም መንግሥቱ ለወሬው ደንታ አልነበረውም፡፡ በመሆኑም ፕሮፌሰር መስፍን የነበራቸው ብቸኛ አማራጭ ከተማሪዎቻቸው ጋር እየዞሩ ከህዝቡ እርዳታ መለመን ነው፡፡ በዚህም የተፈለገውን ያህል ውጤት ለማግኘት ባይችሉም የተወሰኑ ዜጎቻችንን ህይወት ለመታደግ በቅተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በወቅቱ ድምጻቸውን ያሰሙ ብቸኛው ሰው ሆነው በታሪክ ተመዝግበዋል፡፡

===የአጣሪ ኮሚሽን===

የቀዳማዊ ሃይለ ሥላሤ መንግሥት ሲንኮታኮት በርካታ ባለስልጣናት በስልጣናቸው አላግባብ በልጽገዋል በሚል ታስረው ነበር፡፡ የነዚያን ባልስጣናት ጉዳይ አይቶ ለፍርድ የሚያቀርብ አጣሪ ኮሚሽንም ተቋቁሞ ነበር፡፡ የዚያ ኮሚሽን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መስፍን ነበሩ፡፡

አጣሪ ኮሚሽኑ ምርመራውን በከፍተኛ ሃላፊነትና በሰከነ መንፈስ ማካሄድ ጀመረ፡፡ ይሁንና የኮሚሽኑ አካሄድ ተናዳፊዎቹን የደርግ መኮንኖች ሊያረካ አልቻለም፡፡ በመሆኑም የደርጉ ም/ሊቀመንበር የነበረው ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማሪያም በኮሚሽኑ ስራ ጣልቃ ገብቶ ማወክ ጀመረ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንንም “ቶሎ ቶሎ መታ አድርግና ጨርስ እንጂ! እስከመቼ ነው እነዚህን አሳማ ባለስልጣናት የምንቀልበው” አላቸው፡፡ ይሁንና ፕሮፌሰር መስፍን ለጓድ መንጌ ጫና አልተበገሩም፡፡ እንዲህ የሚል የድፍረት መልስ ሰጡት፡፡

“ጓድ ሊቀመንበር! የሀገር መሪ ለታሪክ ጭምር ማሰብ አለበት፡፡ ታሪክ ማለት ዛሬ ስለናንተ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚጻፈው እንዳይመስልዎት፡፡ ታሪክ ጊዜው ሲደርስ እውነቱ ከሐሰቱ ተጣርቶ የሚቀረው ቅሪት ነው”

ሻለቃ መንግሥቱ በፕሮፌሰር መስፍን አነጋገር ተናደደ፡፡ ወዲያኑ አጣሪ ኮሚሽኑን በመበተን በባለስልጣናቱ ላይ የሞት እርምጃ እንዲወሰድ አደረገ፡፡

=== የብሄራዊ እርቅ ጥያቄ===

ደርግ ከሻዕቢያና ከህወሐት ጋር የሚያደርገው ጦርነት እየተጠናከረ በመጣበት ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጭንቀት ውስጥ ወደቀ፡፡ ብዙዎች “ሀገራችን እንደ ሶማሊያና ላይቤሪያ ልትሆን ነው” በማለት ተወጠሩ፡፡ ይሁንና አንድም ሰው ጦርነቱን ለማስቆም ይበጃል ያለውን ሀሳብ ለመሰንዘር አልቻለም፡፡ በተለይም የጊዜው መሪ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም የርሳቸውን ሃሳብ የሚጻረረውን ሁሉ ያጠፋሉ እየተባለ ይነገር ስለነበር ሁሉም ኢትዮጰያዊ በቤቱ ከትቶ ፈጣሪውን መማጸኑን ነው የመረጠው፡፡

አንድ ሰው ግን አላስቻለውም፡፡ “ሀገሬ በጦርነት አዙሪት ከምትጠፋ የመሰለኝን ሃሳብ ልሰንዝርና የሚሆነውን ልጠብቅ” በማለት የመሰለውን እርምጃ ለመውሰድ ተነሳ፡፡ “ጦርነቱን ለማቆም ብቸኛው መፍትሔ ብሄራዊ እርቅና ማድረግና የሽማግሌዎች ባለአደራ መንግሥት ማቋቋም ነው” በማለት ለፕሬዚዳንቱ ግልጽ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ በሚቋቋመው መንግሥት አወቃቀር ላይ በሂልተን ሆቴል ማብራሪያ ሰጠ፡፡

ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ “የባልና የሚስት ጥል እንጂ የኢትዮጵያ ጉዳይ በሽማግሌ አይፈታም” በማለት የሰላም ፎርሙላውን አጣጣሉት፡፡ በታሪክ አጋጣሚ የተሰጣቸውን የመጨረሻ እድል አበላሹት፡፡ በመሆኑም መንጌ በወሰዱት የጀብደኝት እርምጃ ለዘልዓለሙ የታሪክ ተወቃሽ ሆነው ቀሩ፡፡ የሰላም ፎርሙላውን ያቀረበው ሰውዬ ግን በታሪክ መዝገብ ስሙን በደማቁ አስጻፈ፡፡
እንግዲህ ያ ሰውዬ ማለት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ናቸው፡፡ ሰው በጠፋ እለት ሰው ሆነው የተገኙ ደፋር ሰው!!

===የለንደን ኮንፈረንስ===

በግንቦት ወር 1983 የተካሄደው የለንደን ኮንፈረንስ አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ ከአዲስ አዙሪት ጋር ሊያመጣ እንደሚችል ብዙዎች አስቀድመው ገምተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል በማለት በኮንፈረሱ ቦታ የተገኘ ሰው አልነበረም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ግን ስምንት ያህል ምሁራንን በማስተባበር ከኮንፈረንሱ ቦታ ሄደው ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡ በተለይም “የኢትዮጵያና ኤርትራ ፍቺ የሁለቱን ህዝቦች ፍላጎት ያገናዘበ ካልሆነ በስተቀር በሁለቱ ህዝቦች መካከል መቃቃርን ይፈጥራል” በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ያ አነጋገር ከሰባት ዓመታት በኋላ እውነት ሆኖ ብዙዎችን አስደንቋል፡፡

በዚያ ኮንፈረንስ ላይ በጣም አስገራሚ ሆኖ የተገኘው ሌላኛው ነገር ፕሮፌሰር መስፍን ከሻዕቢያው ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የነበራቸው ቆይታ ነው፡፡ ከኢሳያስ ጋር እንደ ወንድማማች ሆነው ሲጨዋወቱ ያዩዋቸው ሰዎች “ሁለቱ ሰዎች ከዚያ በፊት ይተዋወቁ ነበር እንዴ?” የሚል ጥያቄ አጭረዋል፡፡ ከአቶ ኢሳያስ ጋር ያወሩትን ያህል ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር አለመቀራረባቸውም ሌላኛው አስገራሚ ነገር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

=== የሰብዓዊ መብት ጉባኤ===

በሰኔ 1983 የተመሰረተው የሽግግር መንግሥት ያጸደቀው ቻርተር በኢትዮጵያ ውስጥ የሃሳብና የመደራጀት ነጻነት መፈቀዱን አብስሮ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚያ በፊት ባልታየ መልኩ እንደ አሸን ፈሉ፡፡ ህብረ ብሄራዊና ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተመሰረቱ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ “ሰብዒ መብት” የሚል ለብዙዎች እንግዳ የሆነ ጽንሰ-ሃሳብ በሚዲያ መንሸራሸር ጀመረ፡፡

አብዛኛው ምሁር ከአንዱ የፖለቲካ ቡድን ጋር ራሱን አቆላለፈ፡፡ የዘመኑ እንግዳ ደራሽ የሆነውን የሰብዓዊ መብት ጽንሰ-ሃሳብ የሚያብራራ ሰው ግን ጠፋ፡፡ በዚህ መሀል ነው ታላቁ ኢትዮጵያዊ ምሁር ብዙዎች የረሱትን የሰብዓዊ መብት አጀንዳ በማንሳት ለህዝቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማስረጃ ለመሞገት የተነሱት፡፡ እርሳቸው ያቋቋሙት ድርጅትም ባለፉት ሀያ ሁለት ዓመታት የሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠበቃ በመሆን ያሳለፈው ውጣ ውረድ እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡

ስለ ሰብዓዊ መብትና መከራከርና በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥ በዋነኛነት በመንግሥት መፈጸም የነበረበት ስራ ነው፡፡ በመሆኑም ፕሮፌሰር መስፍን በሰሩት ስራ መንግሥት ከፍተኛ ሽልማት ሊያበረክትላቸው ይገባ ነበር፡፡ ይሁንና የተደረገው የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ የመንግሥት ካድሬዎች ከኢትዮጵያዊ ባህልና ስነ-ምግባር ውጪ ፕሮፌሰር መስፍንን በአጸያፊ ስድቦች ሲያብጠለጥሏቸው ነው የሰነበቱት፡፡ እርሳቸው ግን ስድቡንም ሆነ እስሩን ችለው ለህዝቡ መከራከራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ለህዝባቸው ሲሉ ሁሉንም የተጋፈጡ ጀግና ምሁር!

===የኤርትራዊያን መባረር===

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በተከሰተበት ወቅት “የዐይናቸው ቀለም አላማረንም” የሚል ያልተለመደ ምክንያት እየተሰጠ በርካታ ኤርትራዊያን (በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ) ተባረዋል፡፡ ታዲያ የመንግሥት እርምጃ ከተቃዋሚዎችም ሆነ ከሌሎች ወገኖች ብዙም ተቃውሞ አልገጠመውም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ግን አላስቻላቸውም፡፡ “ሻዕቢያ ወረረን ተብሎ ኤርትራዊያንን በጅምላ ማባረር ታሪካዊ ስህተት መፈጸም ነው፤ ሰዎቹ ከተባረሩም እንኳ የሰብዓዊ መብታቸውን በማይነካ መልኩ መሆን አለበት” በማለት ድምጻቸውን አሰሙ፡፡ ታዲያ በዚያን ጊዜ የተፈጸመው ነገር እስከ አሁን ድረስ ለብዙዎች እንግዳ ነው፡፡ ለወትሮው ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር በሃሳብ የሚጣጣሙት የግል ጋዜጦችም እንኳ በእርሳቸው ላይ ጀርባቸውን አዙረው የሚበቃቸውን ያህል አብጠለጠሏቸው፡፡ አንዳንዶቹ ጭራሽ ከሻዕቢያ ጉቦ የተቀበሉ አስመሰሏቸው፡፡

ጥቂት ወራት አለፉ፡፡ ኤርትራዊያንን በጅምላ ማባረር ስህተት መሆኑን ሁሉም አመነ፡፡ መንግሥት ካባረራቸው መካከል ጥቂት የማይባሉት እንደገና ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደረጉ፡፡ በ1997 እንዲያውም “ኖርማላይዜሽን” የሚል እቅድ በተግባር ላይ እንዲውል ተደረገና “በጣም ድንቅ ሃሳብ” ተብሎ ተሞካሸ፡፡ ይሁንና ሁሉንም አስቀድመው የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን ነበሩ፡፡ ሌሎች የርሳቸውን ሃሳብ ቀምተው ተወደሱበት፡፡ እንዲህ ነች የኛ ኢትዮጵያ!
————————
ፕሮፌሰር መስፍን ማለት በዚህች አጭር ጽሑፍ የሚገለጹ ሰው አይደሉም፡፡ ብዙ ድርሳናትን የሚያስጽፉ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ እኝህ ደፋርና ለህሊናቸው ታማኝ የሆኑ ምሁር በቅርቡ ሰማኒያ ሁለተኛ ዓመታቸውን ያከብራሉ፡፡ ታዲያ አንድ የሚያሳዝነኝ ነገር አለ፡፡ ብዙዎች ግለ-ታሪካቸውን እየጻፉ የህይወት ልምዳቸውን በጥቂቱ እንድንመለከት እያደረጉን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር መስፍን እጅግ ዘግይተዋል፡፡ የ20ኛውን ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን ጥልፍልፍ የታሪክ ጉዞ ሊያስተምሩን የሚችሉት ሰው ዝም ብለውናል፡፡

እነ ልደቱ አያሌውን የመሳሰሉ ትንንሽ ፖለቲከኞች እንኳ “ታሪኬን እወቁልኝ” እያሉ በሚነዘንዙበት ዘመን መስፍንን የመሰለ “አንድ ለእናቱ” የሆነ ሰው ዝም ማለቱ አግባብ አይመስለንም፡፡ ስለዚህ እኝህ የሀገር ቅርስ የሆኑ ታላቅ ሰው በቀሪው የህይወት ዘመናቸው በዚህ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል እላለሁ፡፡
—–
አፈንዲ ሙተቂ
መጋቢት 6/2006
ሸገር -አዲስ አበባ

The writer Afendi Muteki is a reaserchr and author of the ethnography of the peoples of east Ethiopia. You may get some of his articles on the following page.
https://www.facebook.com/afendimutekiharar?ref=hl

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

Go toTop