July 20, 2024
20 mins read

ድርጅታዊ መዋቅርና የጠራ መርሃግብር የሌለው ትግል ለአምባገነኖች በር ይከፍታል

ለውጤታማ ትግል ድርጅታዊ መዋቅርና መርሃግብር ወሳኝ ነው

ladershipሃምሌ 13ቀን 2016ዓም(20-07-2024)

በታሪክ እንደታዬው ከሆነ የአንድ አገር ሕዝብ ጭቆናና በደል ሲፈጸምበትና በአንባገነኖች አገዛዝ ስር ሲወድቅ ችሎ ችሎ ማመጹ የማይቀር ሃቅ ነው።ይህንንም በአገራችን ላለፉት ሃምሳ ዓመታት አይተነዋል።በዘውዳዊ የባላባታዊ ስርዓት ወቅት በነበረው ፍትህ አልባና የአገር ባለቤትነት እጦት ሕዝብ ለድህነት ለርሃብና ለበሽታ በመጋለጡ ያም ለአመጽ እንደቀሰቀሰው አይካድም።ከብዙ መስዋእትነትና ውጣ ውረድ በዃላ ዘውዳዊ ስርዓቱ ተገርስሶ በቦታው በሕዝቡ ስም የሚናገር ግን በሕዝቡ ባልተመረጠ የወታደር አምባገነን አገዛዝ ስር ለመውደቅና ለ17 ዓመት የስቃይ ኑሮ ተዳረገ።ይህም የሆነው ሕዝቡን የሚወክል፣ችግሮቹን ለመፍታት የተደራጀና ብቃት ያለው የፖለቲካ ድርጅት አለመኖሩ ነበር።ባዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል ቁጥር አንድ !

ለዓመታት ሲታገል የነበረው የተማሪው ንቅናቄና የአምባገነኑ ወታደራዊ አገዛዝ በከፈተው ቀዳዳ አገራችን ለቀጣዩ አደጋ ተጋለጠች፣ያም በጎሳ ማንነት ኢትዮጵያን ለመበታተን ለተነሱ ስብስቦች የተከፈተው በር ነው።የወታደራዊ አምባገነኑን አገዛዝ ለማሶገድ የተደረገው ትግል ጎራ ለይቶ እርስ በራሱ ሲባላ ለገዢውና ለተገንጣዮቹ ዓላማ ማዳበሪያ ሆነ።አንድ ወጥ ዓላማና ግብ ያለው ሕዝብ የተካፈለበትና የሚቆጣጠረው ድርጅት ባለመኖሩ የሕዝቡ ትግል ተጨናግፎ ለጸረ ሕዝብ ሃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸው በሕዝቡ የተጠላውን ወታደራዊ አገዛዝ በምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካኖቹ ድጋፍ ገልብጠው ስልጣኑን ተቆጣጠሩ።ባዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል ቁጥር ሁለት!

የሕዝቡን ጥያቄ በመቀልበስ የጎሳ ጥያቄ አድርጎ የተነሳው ይህ ጎሰኛ ቡድን አገዛዝ የሕዝቡን ችግር መፍታት ቀርቶ በድህነቱ እንኳን አብሮ እንዳይኖር አደረገው።የሃይማኖትና የጎሳ ማንነት የሕዝብ መለያ ሆኖ እርስ በርሱ እዬተባላ እንዲኖርና በመጨረሻውም አገር ተገነጣጥላ እንድትፈርስ በሕግ ደንግጎ ለ27 ዓመት በልዩነት ፣በጥቅም ሽኩቻ ፣በዘረፋ፣በመግደልና በማፈናቀል የስቃይ አገዛዙን አስፍኖ ኖረ።

ሁል ጊዜ ጭቆናና በደል ባለበት የሕዝብ የተቃውሞ ትግል መነሳቱ የማይቀር በመሆኑ ሕዝቡ በሚችለው መጠንና በተበታተነ መልኩ ሲታገልና መስዋእት መክፈሉን አላቆመም ነበር።የወያኔ የበላይነት ከሚሸከሙት በላይ ሲሆንባቸው፣የስርዓቱ መበስበስና ውስጣዊ የጥቅም ሽኩቻው ጣራ ሲነካ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቃል የገቡት በኢሕአዴግ ስም የተሰበሰቡት ጎሰኞች የዬራሳቸውን ሃይል ውስጥ ውስጡን ሲያደራጁ ኖረው ከውጭ ድጋፍ ጋር ተዳምሮ የኦነግ ክንፍ የሆነው ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የሚለው ስብስብ የሥልጣኑ ባለቤት ሆነ። ለእውነተኛ አገራዊ ለውጥ የተደራጀና ሕዝቡን ያደራጀ መዋቅርና መርሃግብር ያለው ሕዝባዊ ድርጅት ባለመኖሩ ጨዋታው በጎሰኞቹ መሃል ሆነና ተረኛው ስልጣኑን ጨበጠ።ባዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል ቁጥር ሶስት!

ይህንን የሥልጣን ግብግብ ተከትሎ በኦሕዴድና በወያኔ መካከል በተደረገው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ተጨፈጨፉ፣ቆሰሉ፣ተፈናቀሉ፣ የአገር ሃብትና ንብረትም ወደመ።በጦርነቱ ማግስት የኦሕዴድ መጠናከር ያስከተለው ቀውስ በወያኔ አገዛዝ የተማረረው ለውጥ ፈላጊ ሕዝብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የደረሰበት በደልና ግፍ ያለፈበትን የስቃይ ኑሮ የሚያስንቅና የሚያስመኘው ሆነ።ጥላቻው፣ ድንቁርናው፣ ጭካኔው፣ መፈናቀሉ፣ዘረፋው፣ሙስናው፣መለኪያ ቢስ ሆነ።የአገር መበታተን አደጋው ፈጦ መጣ።ይህም ለዳግም ትግል ሕዝቡን በተለይም በሁሉም ተገንጣዮች እንደ ጠላት የሚቆጠረው የአማራውን ተወላጅ ለትግል ቀሰቀሰው፤ሆኖም ግን በቅጡ የተደራጀ መዋቅርና መመሪያ ፍኖተካርታም ሆነ መርሃግብር የሌለው በየከባቢው በጎበዝ አለቆች የሚመራ የፋኖ ታጣቂ የሚመራው ትግል ለመጀመር ተገደደ።ትግሉ እዬተጠናከረ ሲመጣ በአገዛዙ በኩልም የሚወሰደው እርምጃ እንዲሁ በእጥፍ ጨመረ።በመሬት ብቻም ሳይሆን በአዬር የማጥቃቱን እርምጃ ተያያዘው።ሁሉም ነገር ለጦር ሜዳ ፍጆታ ሆነ።በዚህ የጭካኔ እርምጃ ንጹሃን አርሶ አደሮች፣ የቤተክርስቲያንና የመስጊድ አገልጋዮችና ምዕመናን ከነአማልኮት ቦታቸው በቦምብ ጋዮ።የደሃው ደሳሳ ጎጆ ነደደች።ከብትና ህጻናት አብረው ተቃጠሉ።በከተማም የኑሮ ውድነት፣የሥራ ማጣት፣የሰላም መናጋት፣መታገድና መዘረፍ በየአካባቢው የስርዓተ አልበኝነት የሽፍታ መናኸሪያ ተስፋፋ፣ወንጀል የኑሮ ዘይቤና የገቢ ምንጭ ሆነ።ያሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ የሚለው አባባልም በመሬት ላይ በግልጽ ታዬ።አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ በሆነበት አገር ፍትሕና ሰላም፣እኩልነትና እድገት ድራሻቸው ጠፈቶ ሁሉም በስጋት ከቤቱ ወጥቶ መግባቱን መጠራጠር ጀመረ።አገዛዙና ደጋፊዎቹ ግን ገሃነሙን ገነት አድርገው መቀደዳቸውን ያለሃፍረት ቀጠሉበት።በሃያ ብር ኩንታል ጤፍ ተገዝቶ ይበላባት የነበረች አገር አሁን እንደ ሄሮይን በጥቁር ገበያ 15 ሽህ ብር ያውም ከተገኝና ገንዘብ ካለ የሚገዛበት አገር ሆናለች።ጥቂቶች በሚያማርጡባት አገር ብዙሃኑ ቆሎ በልቶ ለማደር የቢሮ ሰራተኛ ሆኖ ገቢ ያለው መሆን አለበት።ሌላውማ አይነሳ በሁለት ቀን አንድ ጊዜ በልቶ ማደር የሎተሪ ያህል የሚቆጠር ዕድል ሆኗል።

ይህ ሁሉ በመሬት ላይ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ ግፍና በደል የሥርዓት ብልግናና ጭካኔ በሰፈነባት አገር አብዛኛው ሕዝቡ ብሶቱን ውጦና ደንዝዞ የባሰ አታምጣ እያለ በቤተክርስቲያንና በመስጊድ ደጀ ሰላም ተኮልኩሎ ፈጣሪውን ያስቸግራል።የእምነት አባቶችም የሥርዓቱ ደጋፊ በመሆን ተከፋፍለው የፍርሃትና የጥቅም ቆፈን እዬለበለባቸው ነው።የእዬሱስንም ሆነ የነብዩ ሞሃመድን አስተምሮና ትእዛዝ ከመቀበልና ከመፈጸም ይልቅ ጆሯቸው የሚከፈተው ለአገዛዙ ትእዛዝ ለቤተመንግሥቱ ሆኗል።ሁሉም በሚባል ደረጃ ለአንድነቱና ለእኩልነቱ መሰናክል የሆነበትን የጎሰኝነት ታርጋ ተሸክሞ በጋራ ጠላቱ ላይ ማተኮር አቅቶታል። የወንዜ ጅብ ይብላኝ ብሏል።በሽታው ሁሉንም ለክፎታል፤ተማረ የተባለውም የዚያው ወረርሽኝ ሰለባ ሆኗል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራው ማህበረሰብ በፋኖ ስም የተጀመረው የሽምቅ ውጊያ ሌላው ቢቀር ለአማራው መብትና ከጥቃት ተከላከሎ ያድናል ተብሎ ብዙ ድጋፍና ተስፋ የተጣለበት ትግል በጥቂት ጊዜ ውስጥ ብዙ ድሎችን ያበሰረ ሲሆን የአገዛዙም ዋና ጠላት ሆኖ ተመድቧል።አገዛዞች ሁሉ እንደሚያደርጉት ኦሕዴድ/ ኦነግም የወያኔን ስልት በመጠቀምና ወያኔንም በመደለል የተቃዋሚውን ጎራ ብሎም ፋኖን ለመከፋፈል ጥረት ከማድረግ አልተቆጠበም።ደካማውን በጥቅም ለመደለል ጠንካራውን በቤተሰቡ ላይ ጥቃት በመፈጸም ለማንበርከክ ብዙ ሙከራዎችን አድርጓል።ከዚህ ሁሉ ፈተና አልፎ ለወሳኙ ውጤት ሲታሰብ ፋኖ በራሱ ችግር ውስጥ ገብቶ ትግሉን ከሚቀለበስበት አደጋ ጠርዝ ላይ አድርሶታል።መታገል አንዱ ሲሆን የሚታገሉበትን ዓላማ አለማወቅ ወይም መዘንጋትና የግለሰቦች የሥልጣንና የጥቅም ማስከበሪያ ማድረግ ከተጀመረ ውጤቱ ለውጥ ሳይሆን የበለጠ ነውጥ ይሆናል።

የፋኖ ትግል የአማራውን ማህበረሰብ ለመታደግ እስከሆነ ድረስ በዚያው ዓላማ መጽናት ይኖርበታል።አገራዊ ለውጥ ለማምጣትም ከሆነ ለውጡ ምን እንደሚሆንና የወደፊቱ ስርኦት ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ፍኖተካርታና መርሃግብር መያዝና ለሕዝቡም ማስረዳትና ሕዝቡም አስተያዬቱን እንዲሰጥበት ማድረግ ይገባል።በትግሉም ውስጥ የሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ መኖር አለበት፤ ከአማራነት ወደ ኢትዮጵያዊነት እርከን መሻገር ይኖርበታል።ለአማራውም ሆነ ለኢትዮጵያዊነት ለሚደረገው ትግል የፋኖ ሃይል የግድ መዋቅራዊ ቅርጽና መአከላዊ አመራር ሊኖረው ይገባል።ያም ባለመሆኑ ነው ሰሞኑን የታዬው የስልጣን ሽኩቻና መከፋፈል ጎልቶ የወጣው።ይህ መከፋፈል በጊዜው ካልተወገደና ዋና ተጨዋቾቹ አደብ ካልገዙ በስሙ የሚንቀሳቀሱበት ሕዝብ አደብ ሊያሲዛቸው ይገባል። ብዙሃኑ የፋኖ አባላት በጥቂቶቹ መሪ ነን በሚሉ ግለሰቦች ምክንያት እርስ በርስ የሚዋጉበት ዕድል እንዳይፈጠር ሁሉም ለውጥ ፈላጊ ድምጹን ሊያሰማ ይገባዋል።ሕዝብ ያልተቆጣጠረው ትግል የአምባገነኖች የሥልጣን መሰላል ይሆናል። አገር ወዳዱ በጎጥና በቡድን ባህር ውስጥ መስመጥ አይኖርበትም።የተጀመረው ትግል በዚህ መልኩ ከተዳከመ ወይም ከተደናቀፈ ለጎሰኞቹ አገዛዝ ጥንካሬና አገር የማፈራረሱን ሴራቸውን እንዲቀጥሉበት መፍቀድ ይሆናል።ያም ባዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል ቁጥር አራት ይሆናል።ካለመደራጀትና መርህ አልባ መሆን ለቁንጫ መራባት እንደሚጋለጠው ቤት መሆኑ ታውቆ የቁንጫ መርቢያ የሆነውን ቤት በንጽህና መያዙ ይጠቅማል።ንጹህ ቤት ሲባልም ሁሉም የሚሳተፍበት ግልጽና አመራር ያለው የትግል ተቋም ወይም ድርጅት ማለት ነው።የፋኖ አባላት ወታደራዊ ተልእኮ እንጂ የፖለቲካ ተልእኮ እንዲኖራቸው ከተፈቀደላቸው ሥልጣኑ በምርጫ ሳይሆን በጡጫ የመያዙ አደጋ ከፍተኛ ይሆናል፤ያም ለዳግም ትግል ለዳግም ጫካ መግባት ይዳርጋል።ጠመንጃ ተሸክሞ መንከራተት ባህላችን ሆኖ ይቀራል ማለት ነው። የዴሞክራሲ ለውጥ በሩ ከተዘጋ ከድህነት ከበሽታ፣ ከርሃብ፣ ከኽላቀርነት ለመውጣት የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል ትኩረት እንዳያገኝ ያደርጋል።

ወታደራዊ ትግሉ የአገዛዙን ጭፍጨፋ ለመከላከልየተቋቋመ ሲሆን የፖለቲካ ድርጅት መኖርም ለፖለቲካው ትግል መሪ ይሆናል።በወታደራዊው ዘርፍ ብቻ ተንጠልጥሎ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ለውጡ የፖለቲካ የኤኮኖሚና ማህበረሰባዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት መሆን ስለሚገባው ያንን እራዕይ ያነገበ የፖለቲካ ድርጅት መኖር አለበት።ብልጽግና ተብዬው የሚመራበትን አገር አጥፊ መመሪያ ተቀብለው ተሳትፎ በማድረግ እራሳቸውን ያከሰሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ለተሰራው ወንጀልም ተጠያቂዎች ናቸው።አማራጭ ሊሆኑ አይችሉም።የአሁኑንና የወደፊቱን ችግር ለመፍታት በአገር ወዳዶች ህብረት ላይ የቆመ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት መፈጠር አለበት።ለውጡ የሥርዓት ለውጥ ስለሆነም በአብይና በጥቂት ወንጀለኞች መወገድ ላይ ብቻ ማተኮርና መቆም የለበትም።

አሁን በፋኖ ውስጥ የተከሰተውን ችግር ለማሶገድ የግድ የጋራ አመራር(ማእከላዊ እዝ) መፍጠር ተገቢ ነው።ለንትርኩም ዋና በር የከፈተው የዚሁ አካል አለመኖሩ ነው።ማእከላዊ አመራሩ የሚከተለው የትጥቅ ትግሉ ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ የሚመራበት ፍኖተ ካርታ ሊኖረው ይገባል፣ስልቱ በዬጊዜው ሊለዋወጥ ስለሚችል የግድ ይህ ነው ብሎ ለማስቀመጥ ያስቸግር ይሆናል።የስንቅና ትጥቁ ማእከልም በዚሁ ስር መሆን ይገባዋል።ብክነትና መነጣጠቅን ያሶግዳል።አመራሩን በበላይ ተጠሪነት የሚያገለግል በወታደራዊ ልምድና ብቃቱ የታወቀ ሰው ከመካከላቸው ቢመደብ የጎረምሶቹን ግብግብ ሊያሲቆም ይችላል።ክፍተቱ ሳይወገድ ጊዜ ከተሰጠው ልዩነቱን ተጠቅመው የውጭ ሃይሎችና ገዢው ቡድን ሰርገው ለመግባት ያመቻቸዋል።ገንዘብና ሥልጣን የሚይማልለው አይኖርም አይባልም፤የልዩነቱም ምክንያት ይኸው ነው።የዓላማ ልዩነት ኖሮ አይደለም።ጄነራል ተፈራ ማሞ ምንም እንኳን ደካማ ጎኖች ቢኖሩትም፣በሥርዓቱም ውስጥ የነበረና ወታደራዊ ቁመናውንም ስለሚያውቅ፣ ከጎጥና ከቡድናዊነት የተላቀቀ ሰው ከሆነ ባለው ልምድና ዕድሜ ለቦታው ተገቢ ይመስለኛል።ካልሆነም የተሻለ ሰው ካለ ቢመደብ መልካም ነው። ወሳኙ ለትግሉ የሚሰጠው ጥቅም ብቻ ነው። የቀሩት የከባቢ ፋኖ መሪዎች ባሉበት የከባቢ ፋኖዎች ከተመረጡ የከባቢ አዛዦች(Regional commanders) እንደሆኑ ይቀጥላሉ ማለት ነው።የፈለጋቸውን ለማድረግ ግን የእዝ ሰንሰለቱና ወታደራዊ ሕግና ስነስርዓቱ አይፈቅድላቸውም ፤ሁል ጊዜ ለበላይ አካል ማለትም ለማእከላዊው እዝ ታዛዥ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል። ይህ ግለኝነትን ብሎም አምባገነንነትን ይከላከላል።ትዕዛዙን የጣሰ ተገቢው ቅጣት ይጣልበታል።ይህ ዓለም አቀፋዊ የወታደር ስነስርዓት መመሪያ በሁሉም ዘንድ መከበር አለበት።

ግለኝነትንና ቡድናዊነትን በጋራ እንታገለው!

ለጋራ ድል የጋራ ትግል!

አገሬ አዲስ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop