July 13, 2024
30 mins read

መፍትሔ ለኢትዮጵያ ፥ ጊዚያዊ ወይስ አዋላጅ መንግሥት?

መሳይ ከበደ

ልብ ይባል 

ይህ በቅርብ በእንግሊዝኛ የደረስኩትና ያሰራጨሁት፣ “Shifting from Moralization of Power to Containment: The Idea of Caretaker Government in Ethiopia” በሚል ርዕስ የቀረበው የእንግሊዝኛ ፅሁፍ ትርጉም ነው። መካሪዎቼ እንዳሉት፣ በብዙዎች ዘንድ በተለመደ ቋንቋ መጠቀም የአንባቢያን ቁጥር ይጨምራል፤ ስለ አዋላጅ መንግሥት በብዛት የተነሱቱን አለመግባባቶችንም ይቀንሳል።

አስፈላጊው የአስተሳሰብ ለውጥ 

የዓፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከወደቀ በኃላ ኢትዮጵያ ሶስት የተለያዩ ቅርጾች ባላቸው ጊዚያዊ ወይም የሽግግር መንግሥታት ውስጥ አልፋለች። ግን ውጤቶቹ ተመሳሳይ ናቸው። ሶስቱም ኢዴሞክራሲያዊ የሆኑ መንግሥታት ወልደዋል፤ ሶስቱም በአንድ ግለሰብ ፍጹማዊ አገዛዝ ሥር ወድቀዋል። በአብዮቱ ጊዜ ደርግ የመጀመሪያውን ጊዚያዊ መንግሥት ሥልጣን አስፍቶ ወደ አንድ ግለሰብ ቋሚ አምባገነናዊ መንግሥት ቀይሮታል። በተመሳሳይ መንገድ ሕወሃት ሁሉን የመንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኃላ፣ ለአንድ ግለሰብ ሙሉ ሥልጣኑን በማስረከብ፣ በተራው ወደ ቋሚ መንግሥትነት ተቀይሯል። እሱን የተካው የአብይ መንግሥት በመርህ ደረጃ እንደ ጊዚያዊ መንግሥት ነበር የተቆጠረው። ምክንያቱም ብዙዎች ደጋፊዎቹ ቀደም ንግግሮቹን ይዘው፣ የአሰራርና ሕገ መንግሥታዊ ለውጦችን እንደሚያመጣ ተስፋ አድርገው ነበር። አቢይ ግን የተናገራቸውን አንዱንም ሳይፈጽም የበፊት መንግሥታትን ፈለግ ተከትሎ ወደ አምባገነናዊ መሪ ተቀየረ።

አሁንም ከግራም ከቀኝም የምንሰማው አዲስ ጊዚያዊ መንግሥት ይመስረት የሚለውን ጥሪ ነው። መቼ ነው ኢትዮጵያውያን የጊዚያዊ መንግሥት ፈለግ ለአገሪቱ ጥሩ ነገር አያመጣም ብለው ከታሪክ የሚማሩት?

መቼ ይሆን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ለሥልጣን የሚታገሉት ተፎካካሪዎቻችውን ለማስወገድ መሆኑ ገብቶአቸው የእርምት እርምጃ የሚወስዱትና ለሥልጣን መጋራት የሚበቁት? ዘመናዊነት ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ የፖለቲካ ውድድር ወደ ዜሮ ድምር ጨዋታ እንደተቀየር ለኢትዮጵያውያን ለምን ተሰወረ? ያንኑን ስተት በመደጋገም አዲስ ውጤት መጠበቅ፣ አንድ ታላቅ ሰው እንዳለው፣ እብደት ነው።

ኢትዮጵያውያን ከዚህ ተደጋጋሚ ሽንፈት አስፈላጊውን ትምህርት ወስደው ቢሆን ኖሮ፣ ከጊዚያዊ መንግሥት አማራጭ በመውጣት፣ በምን መንገድ ብንሄድ ነው አዲሱ መንግሥት  ከቁጥጥራችን እንዳይወጣ ማደረግ የምንችለው ብለው  በተመራመሩ ነበር። መመራመሩ ስለ መንግሥት ሥልጣን ያላቸውን ግንዛቤ ይቀይር ነበር። ማለትም መንግሥት እንዲያገለግለን ሙሉ ሥልጣን እንስጠው የሚለውን አቋም ትተው፣ ከቁጥጥራችን እንዳይወጣ ምን ማደረግ  ይኖርብናል ባሉ ነበር። ይህ አጠያየቅ ደግሞ ወደ የአስተሳሰብ አቅጣጫ ለውጥ ይወስዳል። መንግሥት ሥልጣኑን እንዲያከማች ከመተባበር ይልቅ ሥልጣኑን ለመቆጣጠር የሚይስችሉ ዘዴዎች የቶቹ  ናቸው ብሎ መጠየቅን ያስከትላል። ዴሞክራሲ ሌላ ፍች የለውም፥ ሥልጣንን፣ በተለይም የመንግሥት ሥልጣንን፣ የመቆጣጠር መብት ነው።

የሥልጣን ተፈጥሯዊ አውሬነትጠባይ

የዚህ ግንዛቤ መሠረት፣ ሥልጣን በተፈጥሮው እራሱን የማገድ ወይም የመቆጣጠር ባህርይ የለውም የሚለው በተመክሮ የተረጋገጠ እውነታ ነው። በአጠቃላይ ሰዎች ሥልጣን ሲይዙም ሆነም ይዘው ሲቆዩ፣ የትም ሆነ መቼም እንዲገደብባቸው አይፈልጉም፡፡ ይህ እውነታ የሚነግረን፣ ዴሞከራሲያዊ የሆኑ አገሮች ሥልጣንን ለመወሰን የቻሉት፣ ተፈጥሮአዊ ከሆነ ጠባዩ ጋር በመታገል ነው፡፡ ለዚህም ነው ዴሞክራሲን ለመመስረት መጀመሪያውኑ አስቸጋሪ የሆነው። ከተመሰረተ በኋላም ለማስቀጠል የማያቋርጥ ጥንቃቄና ትግል የሚጠይቀው። እንደሚባልው ተፈጥሮን መደምሰስ አይቻለምና። ሰዎች በተፈጥሮ ማህበራዊ ናቸው የሚለው ንድፈ ሃሳብ የሚጠቁመው፣ የማዘዝና የመታዘዘ ግንኙነት ለሰው ተፈጥሮአዊ መሆኑን ነው። በተጨማሪም ለፖለቲካ ሥርዓት በውድ መገዛት ለግለሰቦች ብቻ የማይተው ጉዳይ በመሆኑ፣ ግንኙነቱን አስገዳጅ ማድረጉ ከተፈጥሮ የሚጠበቅ ነው።

ታድያ ተፈጥሮን መደምሰስ ካልተቻለ፣ ሥልጣን እራሱን እያስፋፋ፣  ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንዳያይል ለማድረግ፣ ሰዎች ያላቸው ብቸኛ አማራጭ አጥር በመገንባት ሊተላለፍ የማይገባውን ወሰን ማስቀመጥ ነው። የሥልጣን ወደ ፍጹማዊነት ማዘንበልን ለመግታት የዓለማችን ባህሎች በአገኙት መንገድ ሁሉ ሞክረዋል።  የክርስትናንና የአይሁድ እምነቶችን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ የሥልጣን ገደብ ማጣት እግዚአብሔርን በመዳፈር የአዳም የመጀመሪያው ኃጢያት መሆኑን ይናገራሉ። እግዚአብሄር አዳምን የመሬት ንጉሥ ቢያደርገውም፣  ይህ በቂ ስላልመሰለው፣ ፈጣሪውን ማከል ፈልጎ፣ የተሰጠውን ትእዛዝ ተላለፈ። የእግዚአብሄር እኩያ ለመሆን ከመነሳት የበለጠ የሥልጣንን ገደበ ቢስነት የሚያስረዳ ምን አለ?

እግዚአብሔር በአዳም ላይ የወሰደው ቅጣት፣ በነገሥታትና መኳንንት ዘንድ ፍርሃት በመፍጠሩ የሥልጣንን አውሬነት አቀዝቅዟል። ቢሆንም ፍርሃቱ ከጥንት ጀማሮ ማህብረሰብ ላይ የሚደርሰውን በደል ለማቆም በቂ አልሆነም። የምናገረው ትክክል ላልመሰላቸው ሁሉ፣ በባሪያ ሥርዐት ጊዜ የሥልጣንን ጭካኔ መጠን እንዲያስታውሱ እጠይቃለሁ፣ በተለይም ቀረብ ከሚለው በአሜሪካ በተፈጸመው የጥቁር ዘር የባርነት ቀንበር ታሪክ ጋር በማነጻጸር። ሌላ ማረጋገጫ፣ ደግ የሆኑ ሰዎች ሥልጣንን የማለስለስ ዝንባሌ አላቸው የሚለው የተሳሰተ እምነት ነው። ማለስለስ ቀርቶ ሥልጣን ደጉን ሰው ሲያበላሸው ነው ታሪክ የሚያሳየው። ብዙዎቻችን ትዝ ይለናል፣ በአብዮቱ ጊዜ ለቀበሌና ለከፍተኛ የተመረጡ የተከበሩ ዜጎች ብዙም ሳይቆዩ ወደ አረመኔነትና ነፍሰ ገዳይነት ሲቀየሩ አይተናል። ሥልጣን ገደብ እንደማይፈልግ የሚያሳይ ሌላው ማረጋገጫ ዴሞክራሲያዊ ማህበርሰባችን እንኳን ለአምባገነናዊ አገዛዝ ተመልሶ መምጣት ሁሌም ተጋላጭ መሆናቸው ነው። ለዚህ ምስክር የሚሆነው አልፎ አልፎም ቢሆን፣ አምባገነን አገዛዞች በዴሞክራሲያዊ አገሮች ውስጥ ጭምር ብቅ ማለት መቻላቸው ነው፣ ለምሳሌ በጀርመን የሂትለር መነሳት።

ሥልጣን ተፈጥሮአዊ ገደብ የለውም ከተባለ፣ የሚከተለው ወሳኝ ድምዳሜ አንድ ብቻ ነው።  እሱም ሥልጣን ላይ የተቀመጠ ሰው፣ ማንም ይሁን ማን፣ ደግ ወይም መጥፎ፣ የሚያመጣው ለውጥ የለም።  መደረግ ያለበት ትልቁ ቁም ነገር፣ የሥልጣንን ወሰን በማስቀመጥ የሕዝብን የመቆጣጠር ኃይል ማዳበር ነው። ምክንታያቱም ሥልጣን ማንንም ቢሆን ያባልጋል፣ ይበክላል። በዚህም የተነሳ የዜጎችን መሠረታዊ መብቶች በየጊዜው እንዲረገጡ ያደርጋል። ልክ የእንሰሳ መገራት እንስሳነቱን እንደማይደመስስ ሁሉ፣ የፖለቲካ ሥልጣንም መገራት ያለበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ተገርቶም አውሬነቱ መቼም እንደማይጠፍ መዘንጋት የለበትም።

 

የአዋላጅ መንግሥት ንድፈሃሳብ

ሥልጣንን ለመግራት ለኢትዮጵያ አመቺው መፍትሔ የትኛው ነው ብለን ስንጠይቅ፣ በመጀመሪያ ዋናው ችግር የቱ እንደሆን በትክክል ለይቶ ማወቅ አለብን። ከላይ እንደተጠቆመው፣   በእኔ አስተያየት ትልቁ እንቅፋት አምባገነንነት በተደጋጋሚ መከሰቱና እሱን ለመጣል በኃይል መጠቀም ማስፈለጉ ነው። ይህን ሁኔታ ስንተነትን፣ የችግሩ ምንጭ ያለው መንግሥት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳይኖሩ በማድረግ፣ ቢኖሩም በነፃና ፍትሃዊ መንገድ እንዳይወዳደሩ እክሎችን በመፍጠር፣ እራሱን ሥልጣን ላይ ለማቆየት የሚከተለው  አሠራር ነው። ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ አለመቻሉ የአገሪቷ ዋና የፖለቲካ ማነቆ ነው። ሀገሪቱ ያሏት የአንድነት፣ የኢኮኖሚና ምህበራዊ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ ያጡት ከአምባነን ሥርዓት መላቀቅ ባለመቻሏ ነው።

ታዲያ ለዚህ መድኃኒቱ ምንድን ነው?

በጣም ጎልቶ የሚሰማው መፍትሔ፣ ተወዳዳሪዎችን ሁሉ ሚያካትት ጊዚያዊ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚለው ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው ይህ መንገድ ከዚህ በፊት ተሞክሮ አልሠራም። እንዲያውም ቋሚ አምባገነንነት እንዲከሰት አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል። ለምን ቢባል በደርግም ሆነ በወያኔ ጊዜ የሽግግር መንግሥትን በበላይነት የመራው በጦር አሸንፊ የሆኖው ወታደራዊ ኃይል ወይም ፓርቲ ስልሆነ፣ ወደ አምባገነንነት ቢለወጥ ሊገርመን አይገባም። ደግሞስ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት የከረሩ ልዩነቶችና ክፍፍሎች ወደ ስምምነት መጥተውና በአንድ መንግሥት ሥር ተጠቃለው ለአገሪቷ ተስማሚ የሆኑ የጋራ ውሳኔዎች ላይ ይደርሳሉ ማለት አሳማኝ ነው ወይ?

በጦር አሸናፊ በሆነ ኃይል የሽግግር መንግሥት መመራት የለበትም የምንል ከሆነ፣ የሚቀረው አማራጭ ተፎካካሪዎች ሁሉ እንወክላለን ወደሚሉት ሕዝብ ሄደው፣ የእሱን አብላጫ ድምጽ በነፃና ፍትሃዊ ውድድር ይዘው እንዲመጡ የሚያደርግ አሠራር ብቻ ነው። እስካሁን በኢትዮጵያ የነገሠው መርህ፣ በጦር አሸናፊ መሆን ለሥልጣን ያበቃል የሚል ነው። ይህ መርህ ተሽሮ የሕዝብ አብላጫ ድምፅ ብቻ ለሥልጣን ያበቃል በሚለው መተካት አለበት። ተፎካካሪዎች ሁሉ በነፃ ውድድር የሕዝብን ድምፅ የሚያገኙበትን አሠራር የቱ ነው ብለን ብንጠይቅ፣ ወደ አዋላጅ መንግሥት ፅንሰ ሃሳብ በቀላሉ እንደርሳልን። በዚህ አሠራር መሠረት፣ ተፎካካሪዎች የሽግግር መንግሥት መሥራቾች ሳየሆኑ ለመንግሥት ሥልጣን የሚያበቃቸውን ሕዝባዊ ውክልና በቅድሚያ ማግኘት አለባቸው።

የሕዝብን ድምፅ ማስቀደም የአዋላጅ መንግሥትን አስፈላጊነት ማረጋገጥ ነው።  ከላይ የተባለውን ለማድመቅ፣ የሽግግር መንግሥት ለሥልጣን በሚፎካከሩ ኃይሎች ከተመሠረተ የሚጠበቅበትን ውጤት በምንም ተአምር ሊያስገኝ አይችልም።  ይህ መንገደ የሚጠበቀውን ውጤት ስለማያስገኝ ለሕዝብ የመጨረሻውን ዳኝነት የሚሰጥ አሠራር መከተል የግድ ነው። በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የምርጫ ክንዋኔ አልተጀመረም፤ ምርጫ የሚባለው ሕዝብ የቀረበለትን እንዲያፀድቅ ማድረግ ነው። ማለት እውነተኛ የሆነ ፉክክር ቀርቦ በነፃ የሚበጀኝ ይህ ፓርቲ ወይም መሪ ነው ብሎ ሕዝብ በአብላጫ ወስኖ መንግሥት የተመሠረተበት ጊዜ የለም። የአዋላጅ መንግሥት ሃሳብ እውነተኛ የሕዝብ ምርጫን የሚያስጀምር አሠራር ቀያሽ ነው።

ግጭት ሲነሳ ጠበኞቹ እንዳይገዳደሉ ገላጋይ ጣልቅ እንደሚገባ ሁሉ፣  በፖለቲካውም የአዋላጅ መንግሥት አስተሳሰብ ሕዝብ እንደ ገላጋይ ቀርቦ ጠቡን እንዲያቆም የሚያደርግ ዘዴ ነው። በዚህ  መንገድ ብቻ ነው ገላጋይም ዳኛም በማድረግ፣ ትክክለኛ ቦታውን  ሕዝብ ሊያገኝ የሚችለው። የአዋላጅ መንግሥት ሥራውና ሃላፊነቱ አንድ ብቻ ነው፤ እሱም ገለልተኛ በመሆን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ አስፈላጊ የሆኑትን አስተዳደራዊና የአፈፃፀም ሁኔታዎችን ማሟላት ነው።

ከዓላማው ውሱንነት የተነሳ፣ የአዋላጅ መንግሥቱ በጊዚያዊንት ከ3 እስከ 6 ወር ለማይበልጥ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል ይሆናል። ነፃና ፍትሃዊ የሆነ ምርጫ እንዲኖር ከማድረግ ወጪ ሌላ ኃላፊነት የለውም። በፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሥልጣን በሚታገሉ ኃይሎች የሚቋቋም መንግሥት ባለመሆኑ፣ አዋላጅ መንግሥት ከጊዚያዊ የሽግግር መንግሥት በጣም ይለያል። እንዲያውም፣ እነሱን በጊዚያዊንት የሚያገል አሠራር ነው። የሚገለሉትም በሁለት ምክኒያቶች ነው፥ 1) ስለማይስማሙና ሥልጣንን ለመጋራት ዝግጁ ስላልሆኑ፤ 2) ገለልተኛ ሆነው ትክክለኛ ምርጫ እንዲደረግ የማይተባበሩ በመሆናቸው ነው። እነሱን የሽግግር መንግሥት አካል ማድረገ የሁለት የኳስ ቡድኖች ተወካዮችን የግጥሚያው ዳኞች እንደማድረግ ነው።

ሌላው መጠቀስ ያለበት የአዋላጅ መንግሥቱ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ከሚያስፈልገው ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት ድንጋጌ ወይም መመሪያ ሊያወጣ አለመቻሉ ነው። ትክክለኛ ምርጫ መካሄዱ ከተረጋገጠ በኃላ ለተመረጠው ፓርቲዎች ወይም የፓርቲዎች ኅብረት የመንግሥት ሥልጣን ያስረክባል። ይህን ከባድ ኃላፊነትና አደራ የአዋላጅ መንግሥቱ ሊወጣ የሚችለው ገለልተኛ ሊሆኑ በሚችሉ፣ ታማኝና ለሰላም የቆሙና ከሁሉም ማህበራዊ ክፍሎች፣ ማለት ከሃይምኖቶች፣ ከዘውጎች፤ ከሙያ፣ ከትምህርት፣ ከወታደራዊ ፣ ከሠራተኛ ክፍሎች፣ ወዘተ፣ የተወጣጡ አባላት ሲኖሩት ነው። በተጨማሪም፣ ማንኛውም የአዋላጅ መንግሥቱ አባል የአንድ ፓርቲ አባል ሊሆን አይችልም፤ በሚካሄደው ምራጫ ውስጥም በእጩነት ሊቀርብ አይችልም።

የቀረበው ሃሳብ አዲስ አይደለም። ቱኒዚያና ባንግላዴሽ የተባሉት ሀገሮች በሚመቻቸው መንገድ በሃሳቡ ተጠቅመዋል። ከኢትዮጵያም ሳንወጣ  ተመሳሳይ አሠራር በታሪክ ተመዝግቦ እናገኛለን።  አንድ ወዳጄ እንዳስታወሰኝ፣ በዙፋኑ ተወዳዳሪዎች መካከል በተለምዶ የሚነሱ አጥፊ ግጭቶችን ለማቆም ዓፄ ምኒሊክ ራስ ተሰማ ናደውን የልጅ ኢያሱ ሞግዚት ብለው እንደሾሙ ታሪክ ይናገራል። ይህም የሆነው ልጅ ኢያሱ በዚያ ጊዜ የ12 ዐመት ልጅ ስለነበሩ፣ እድሜአቸው ለሙሉ ሥልጣን እስከሚያበቃቸው ድርስ በሳችው ስም ራስ ተሰማ መንግሥትን በጊዚያዊነት እንዲመሩ ነው።  በተጨማሪም ቀረብ ብሎ ላጤነ ሰው፣ የተሰነዘረው ሃሳብ በአንድ የውጪ አገር አደራዳሪነት ለመወያየት ዝግጁ ነን ከሚለው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይንት ያለው ቅድመ ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል።  ዋናው ልዩነቱ ግን አዋላጅ መንግሥት ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት ይችላሉ የሚለውን የሉዐላዊነትን መሰረታዊ መርህ በመከትል ከአገሪቷ በተውጣጡ ዜጎች የተቀነበረ መሆኑ ነው።

ያቀረብኩት መፍትሄ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ መሆኑን በደንብ እገነዘባለሁ፣ በተለይም ተግባራዊነቱን በተመለከተ።  ሆኖም ጥያቄዎቹ ሁሉ ክብደት የሚያገኙት ለአንድ ጥያቄ መልስ ሲኖራቸው ነው።  እሱም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲይዊ መንገድን የዘጋውን እንቅፋት ለማንሳት ሌላ ምን ዘዴ አለ የሚለው ነው። ነፃና ፍትሃዊ ምርጭ ካልተደረገ፣ እንዴት ነው ቋሚና ሁሉን የሚወክል ፖለቲካዊ ሥርዓት ተመሥርቶ ከልሂቃን ፖለቲካ ፅንፈኝነት አገሪቷ መላቀቅ የምትችለው ? ወደ ሕዝብ በመመለስ በሕዝብ አብላጫ ድምፅ አገሩ ካልተዳኘ፣  ከልሂቃን አጥፊ ፉክክር ማምለጥ አይቻልም። በአንድ ቋሚ መንግሥት ሥር ሃቀኛ ምርጫ ማካሄድ ካልተቻለ፣ ያለው አማራጭ የመንግሥትን ፖለቲካዊ አካል ከአስተዳደራዊ አካሉ በጊዚያዊ መልክ ለይቶ በማገድ ነጻ የውድድር ሜዳ ማመቻቸት ነው። ወደዚህ መንገድ ኢትዮጵያውያን ሊመጡ ይችላሉ ብዬ እንዳስብ ያደረገኝ፣ ተደቅኖ የሚታየውን ሁሉን የሚጎዳ የእርስ በርስ ጦርነት አደጋ ለማምለጥ ብቸኛው አማራጭ ነው የሚለው እምነቴ ነው። አደጋው ሲከርና ወደ መኖር ወይም አለመኖር ሲለወጥ ሰዎችን ከፍ አድርጎ ወደ አስፈላጊው መፍትሔ እንዲመጡ ያነቃቃልና።

 

የአፈጻጸም መንገድ

ኢትዮጵያ ችግሮቿን ልትፈታ የምትችለው በድርድር ብቻ መሆኑ ለብዙዎች ግልፅ ይመስለኛል። ይህን ድርድር ያመቻቻል የምለው አዋላጅ መንግሥት እንዴት ተግባራዊ ይሆና? በመጀመሪያ ደረጃ የታጠቁ ኃይሎችና ፖለቲካ ፓርቲዎች (ያለውን መንግሥትን ይጨምራል) ሥልጣን ለመያዝ የሚያደርጉትን እሽቅድምድም አቁመው እርሳቸውን ነፃና ፍትሃዊ ለሆነ ሕዝባዊ ምርጫ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። በሌላ አባባል መሳሪያ ይዘው የሚፋለሙ ኃይሎች በአሉበት ረግተው፣ ያለው መንግሥትም ወታደሮቹን ከጥቃት አካባቢዮች አስወጥቶ፣ የተኩስ አቁም ሁኔታ በቅድሚያ መፈጠር አለበት።

በኃይል የሚፋለሙት ለጊዜው ገሸሽ ካሉ፣ የአዋላጅ  መንግሥት ምስረታ ሊከናወን ይችላል።  እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ሁሉም የሚፈልገውን እንደሚያገኝ ነው። መሳሪያ ይዘው የሚታገሉ  ኃይሎች ከመንግሥት ጥቃት ይከለላሉ፤ ለነጻ የምርጫ ውድድር እራሳቸውን ያቀርባሉ።  መንግሥትን የሚቆጣጠረው ፓርቲም በነጻ ይንቀሳቀስል፤ የሚያጣው ነገር ቢኖር ለመመረጥ በመንግሥት ኃይል መጠቀም አለመቻሉ ነው። በዚህ እጦት ሊከፋ አይገባም፣  ምክንያቱም ያለው መንግሥት ደጋግሞ እንደሚናገረው ለሥልጣን ለመብቃት በሕዝብ መመረጥን ይጠይቃል። በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎችም ከቀረበው ሃሳብ የሚያገኙት ሁሌም የሚመኙትን የነጻና ፍታዊ ምርጫ ዕድል ነው።

በማያሻማ ሁኔታ የቀረበው ሃሳብ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ነው።  ሃሳቡን የማይቀበል ማንኛው ኃይል፣ የሕዝብ ነፃ ምርጫ ብቻ ለሥልጣን እንደሚያበቃ ይልተቀበለ ኢዴሞክራሲያዊና ጽንፈኛ ስብስብ መሆኑን ያረጋግጣል።  ይህም ገፅታ ለሕዝብ ነቀፌታ ስለሚያጋልጠው ተደማጭነት ሊያሳጣው ይችላል። ምክነያቱም በቀረበውን ሃቀኛ የነፃ ውድድር ዕድል አልሳተፍም ማለት፣ ተወዳዳሪው ቡድን ከኳስ ሜዳው ካልወጣ አልጫወትም እንደማለት የሚቆጠር ነው።  የቀረበውን ሃሳብ ምን ስኬታማ ይደርገዋል ብዬ ብጠይቅ ይህ በነፃ አልወዳደርም የሚለው እምቢተኝነት በበቂ የሚመልስ ይምስለኛል።

ለቀረበው ሃሳቡ አመቺ ሁኔታ የፈጠረው የፋኖ መነሳትና ማየል ነው እላለሁ። አንድ እርግጠኛ ነገር ቢኖር የፋኖ እዚህ ደረጃ መድረስ የኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ላይ የሚያመጣው አደጋ ካለመኖሩም በላይ፣ የአማራ ሕዝብን ያለአግባብ ተጠቂ ያደረገውን ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ያመጣል። ውጤቱ የአማራ ሕዝብ የሚገባውን ሥፍራና ሚና እንዲጫወት ያደርጋል።  በኦሮሞ ሕዝብ በኩልም ተመሳሳይ ሁኔታ እየመጣ በመሆኑ፣ በጦር አንዱ ሌላውን አሸነፎ የበላይ የሚሆንበት ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳበቃ ያበስራል።  ይህ ሚዛኑን የጠበቀ የኃይል አሰላለፍ በሥልጣን መጋራት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመዘርጋት መንገድ ይከፍታል። ሚዛን እንዳይፈጠር የሚያውከው ኃይል መንግሥትን የሚቆጣጠረው ፓርቲ በመሆኑ፣ እሱን ከምርጫ አስፈፃሚነት የሚያገለው የአዋላጅ መንግሥት ንድፈሃሳብ የእውነተኛ ለውጥ ብቸኛ መንገድ መሆኑ ፈጦ የሚታይ ይመስለኛል።

 

Shifting from Moralization of Power to Containment: The Idea of Caretaker Government in Ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop