ከትም አግሳ አንበሳ!

ሊነክሱህ ሲመጡ ውሾች ተጅብ ጋራ፣
የጥንብ አንሳ ወሬ መስማቱን ተውና፣
ከትም አንበሳ ሆይ ነፋስ ሳታስገባ!

ራስህን ጠልፈህ ወጥመድ እንድትገባ፣
ያልሸረቡት ሴራ ያልደረቱት ደባ፣
በቆምክበት ምድር አይገኝምና፣
መገፋፋት ትተህ ተቃቀፍ አንበሳ!

የዱር አውሬ ጨቋኝ ብለው ስንቱን ሰብከው፣
ግልገል ቡችላውን መንፈሱን በርዘው፣
ያዝ ብለው ለቀዋል እንዲያደሙህ ነክሰው፣
አንበሳ ሆይ ከትም አንድነት ኃይል ነው፡፡

እርጉም ልጆችህን በጣፊያ ደልለው፣
ከፍለው እንዳይጥሉህ ጥርሳቸውን ስለው፣
ወርችህን እንዳይቆርጡት ገዝግዘው ገዝግዘው፣
አንድ ላይ ከትመህ በኃይል እርመዳቸው፡፡

አገሪቱ ምድሩ ስትሆን ደም አበላ፣
ቆፍጣናው አንበሳ አራት ዓይኖች አውጣ፣
ጥበብ ተአንድነት ጋር ነፍስ አድን ነውና!

አንበሳ ሆይ ይግባህ የትግል ጥበቡ፣
ጅቦች ተኩላዎች ሊነክሱህ ሲመጡ፣
አራት እግሮችህም አንድ ላይ ይቁሙ፣
መጠላለፍ ትተው ወጥመድ እየገቡ፡፡

ቃሉን ይስጥ ጫካው ይመስክር ተራራ፣
ጎምለል ጅንን ብለህ አንዴ ስታገሳ፣
ምድር ይንቀጠቀጣል እንኳንስ ተኩላ!

ሰላም እንዲሰፍን ዳር ተዳር ተጫካ፣
ሥርዓት እንዲመጣ ተፍጥረታት ዘንዳ፣
ጨቅላ መብላት እንዲተው ጅብና ተኩላ፣
ሞረሽ ተጠራርተህ ከትም አግሳ አንበሳ!

በላይነህ አባተ ((abatebelai@yahoo.com)
ታህሳስ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም.

ተጨማሪ ያንብቡ:  በነቀምት ሆስፒታል 10 እናቶች በወሊድ ምክንያት ህይወታቸው አለፈ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share