እዉን መዘክር ለተስፋየ ገብረአብ?

ከመኮንን አሻግሬ (ታህሳስ 2016 ከቨርጂኒያ አሜሪካ)

ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋየ ገብረአብን ለመዘከር መርሐ ግብር መያዙን ሰማሁ። በርግጥ ዝርዝር ፕሮግራሙ በምን መልኩ እንደሚካሄድ መረጃዉ የለኝም፡፡ አንድ ሰዉ ለሠራዉ መልካም ሥራ ማስታወሻ የሚሆን ዝግጅት መደረጉ እንደዉም ይበል የሚያሰኝና የሚበረታታ ነዉ። ተስፋየን በሚመለከት በእእምሮዬ ዉስጥ ያቃጨለዉ ጥያቄ ግን በርግጥ ሊዘከርለት የሚገባ ጸሐፊ ነወይ የሚለዉ ነዉ።

 

ተስፋየ የተዋጣለት የልብ ወለድ ደራሲ መሆኑ አይካድም። የአጻጻፍ ስልቱ መሳጭና ስሜትን ለመኮርኮር ብቃት እንዳለዉም አምናለሁ። በጽሑፎቹና በቃለ መጠየቆቹ የሚያሰተላልፋቸዉ መልዕክቶች ግን እጅግ መርዛም ናችዉ። ያንን የመሰለ የሥነ ጽሑፍ ቸሎታዉን እርስ በርስ ለማናቆርና ሊበታትነን ለሚችል እኩይ ለሆነ ዓላማ ተጠቅሞበታል። ድርጊቱ ስለመፈጸሙ በታሪክ ያልተረጋገጠን ክስተት እዉነት አስመስሎ በማቅረብ በሰዎች አእምሮ ጥላቻን ፈጥሮ ለጭፍን በቀል እንዲነሳሱ በማብቃት ደረጃ ወደር የለዉም። በሃያ ሚሊዮን ብር “አኖሌ የጡት ቆረጣ” የሚል ሐዉልት ለማቆም መሠረት የሆነዉ “የቡርቃዉ ዝምታ” በሚል ያሳተመዉ መጽሐፍም የሚያረጋግጠዉ ይህንኑ ነዉ።

 

በአሁኑ ጊዜ የጎጠኝነት ስሜት ዜጎችን አንቆ አላላዉስ ባለበት፣ በማንነት ላይ ተመስርቶ የዜጎች ሕይወት እንደቀልድ በየቀኑ በሚቀጠፍበት፣ ተወልዶ ባደገበት ቀየ ”መጤ“ እየተባለ በሚሳደድበት፣ ለዘመናት የተፈራን ቤትና ንብረት በሠዐታት ዉስጥ በሚወድምበት አገር ላይ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባዉን ግለሰብ መዘከር ምን ማለት ነዉ?  ይህ ሁሉ ሰቆቃና ዉርጅብኝ በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለዉ ትናንትና ተስፋየና መሰሎቹ የዘሩት ዘር አይደለም ወይ? ለማንኛዉም የተስፋየ ጽሑፎች ምን ያህል መርዛሞች እንደሆኑና ግለሰቡም እኩይ ዓላማ እንዳለዉ ለመረዳት እንዲቻል ቀደም ሲል በ2009 ዓ.ም. “በጥላቻ የተጋረደ ሐቅ” በሚል ርዕስ የጻፍኩትንና በበርካታ ድህረ ገጾች ላይ ተሰራጨቶ የነበረዉን ጽሑፍ ለዚህ እንዲመች በማድረግ እንሚከተለዉ ይቀርባል።

 

ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) ነዉ የተወለደዉ። በዘር ሐረጉ ኤርትራዊ ነዉ። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ፕሬስ መምሪያ ኃላፊ ነበር። ሌሎች ኃላፊነቶችም ነበሩት። ጥሩ የመጻፍ ችሎታ አለዉ።  ሆኖም ግን በቂ የታሪክ ዕዉቀት ያለዉ አይመስልም። በሥነ ጽሑፎቹ ዉስጥ አርሲ ላይ የኦሮም ሕዝብ በአጼ ምኒሊክ አሰቃቂ ዕልቂት እንደተፈጸመባቸዉ፣ ኦሮሞ ለም መሬቱን በነፍጠኛ/በአማራ እንደተነጠቀ፣ ኦሮሞ ተወላጆች በስማቸዉ በማፈር ስማቸዉን ለመቀየር መገደዳቸዉን፣ ኦሮሞዎች በማንነታቸዉ እንዲያፍሩና በባሕላቸዉ እንዲሸማቀቁ እንደሚደረጉ … ወዘተ በመስበክ ይታወቃል። ይህንንም ለማሳየት የጻፋቸዉን ጽሑፎችና ያደረጋቸዉን ቃለመጠይቆች ማጤን ተገቢ ነዉ። ከዚያ በፊት ግን ይህ ሰዉ እንደሚለዉ በኦሮሞ ብሔረሰብ መካከል ስላደገ ለእነሱ ካለዉ ፍቅር የመነጨ ነወይ የሚለዉን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል። ለኔ ግን አይመስለኝም። ምክንያቱም የሚወድ ሰዉ ጥላቻን አይዘራም። ጥላቻ መርዝ ነዉ። ከነቀርሳ የከፋ ጉዳት ያስከትላል። አስተሳሰብን ያዛባል። ለክፋትና ለበቀል ይዳርጋል። ፍቅር ግን ምኅረትን ያወርዳል። በማኅበራዊ እንቅስቃሴም ሰላምንና መቻቻልን ያሰፍናል። ስለሆነም የሚወድ ሰዉ ፍቅርን፣ ይቅርባይነትንና መቻቻልን መስበክ ቀዳሚ ዓላማዉ ያደርጋል እንጂ በአሉታዊ መልኩ አይንቀሳቀስም።

 

ተስፋዬ ገብረአብ ይህንን የሚያደርግበት የራሱ ዓላማ የነበረዉ ይመስለኛል። የቀድሞዉ ዳኛ አቶ ወልደሚካኤል መሸሻ “ጊዜ መስተዋቱ! ተስፋዬ ገ/አብ ማነዉ” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ድረ ገጽ ላይ ሰፊ ዘገባ አቅርበዉ ነበር። በራሱ በተስፋዬ እጅ ጽሑፍ የተጻፉ በርካታ ሰነዶችም ቀርበዋል። ዋናዉ ነጥብ ጽሑፉም ሆነ ሰነዶቹ የሚያመላክቱት ተስፋዬ ገብረአብ ተራ ጸሐፊ ሳይሆን ከኤርትራ ደኅንነት ጋር በቅርበት የሚሠራ ግለሰብ እንደነበር ነዉ። የሚጽፈዉም እየታዘዘና እነሱን እያማከረ ከዚያም በላይ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገለት እንደሆነ መረዳት ይችላል። ታዲያ ከእንደዚህ ዓይነት ሰዉ ምን ልንጠብቅ እንችላለን? ለምንስ አንዳንድ ሰዎች ይህ ሰዉ በሚነዛዉ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ ሆኑ? ለማንኛዉም እስኪ ወደ ጽሑፎቹ እንመለስ፡-

 

  • የቡርቃ ዝምታ

 

ይህ መጽሐፍ ታሪካዊ ልብ ወለድ በሚል በ1992 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ነዉ የታተመዉ። በአወዛጋቢነቱ ግንባር ቀደም ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል። በመሠረቱ ይህ መጽሐፍ በምንም መስፈርት “ታሪካዊ ልብወለድ” ሊባል አይችልም። ሲጀመር መነሻ ያደረገዉ በጽሑፍ የተደገፈ ታሪክን ሳይሆን ፖለቲከኞች የራሳቸዉን አጀንዳ ለማስፈጸም ሲሉ አንድን ሕዝብ በሌላዉ ላይ ለማነሣሣት የሚነዙትን ፕሮፖጋንዳ ነዉ። ታሪክን በቁንጽል በመዉሰድ፣ እዉነታዉን በማጋነንና አንዱን ወገን እጅግ ጨካኝ ብሎም ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ድርጊት እንደፈጸመ ለማስመሰል በተጓዳኝ የፈጠራ ትረካዎች የተገነባ መጽሐፍ ነዉ።

 

“ታሪካዊ ወይም ታሪክ ቀመስ ልብወለዶች” ለአገራችን ሥነ ጽሑፍ አዲስ አይደሉም። ኢትዮጵያዊ ጀግንነት፣ አይበገሬነት፣ ላገሩ የነበረዉን ፍቅር የገለጸበትን ተጋድሎ የሚተርኩ በልብ ወለድ መልክ የተጻፉ እንዲሁም ከጊዜዉ የቀደመ ላገራቸዉ ትልቅ ራእይ ስለነበራቸዉ ስለአጼ ቴዎድሮስ በልብ ወለድ መልክ የሚተርኩ እንደ ታንጉት ሚስጥር (በብርሃኑ ዘሪሁን)፣ አንድ ለእናቱ (በአቤ ጉበኛ) … ወዘተ መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም ግን እነዚህን ልብ ወለዶች አንብበን ከሚሰማን የአገር ፍቅር፣ የአገር ኩራት፣ ወኔ … አንጻር የተስፋዬን “የቡርቃ ዝምታ” ስንመዝነዉ ጥላቻን የሚዘራ፣ አለመተማመንን የሚፈጥር፣ ለቁጭት የሚዳርግ እንዲሁም ከሌሎች መሰል መርዘኛ ንግግሮችና ጽሑፎች ጋር ተዳብሎ አንዱን ብሔር በሌላዉ ላይ ለማነሣሣት ጉልበት ያለዉ ሆኖ እናገኘዋለን።

 

 

  • ጫልቱ እንደሄለን

 

የ“ደራሲዉ ማስታወሻ” በሚለዉ መጽሐፉ ላይ “ጫልቱ እንደሄለን” የሚል ትረካ ከገጽ 66 – 100 ድረስ አቅርቦልናል። አዉቶብስ ዉስጥ በመጓዝ ላይ እያለ አንድ ግለሰብ ያጫወተዉን ታሪክ ተመርኩዞ እንደጻፈዉ ገልጿል። በተጨማሪም “ … እዉነተኛ ቢሆንም የደራሲ ብዕሬን በመጠቀም ምናባዊ ገጸ ባሕሪያት ጨምሬበታለሁ” በማለት አስፍሯል። ለማንኛዉም የታሪኩ ዋና ፍሬ ነገር እንደሚከተለዉ ነዉ።

 

ጫልቱ በትዉልድ አካባቢዋ የቱለማ ታሪክ ላይ ከወንዶች ጋር ተወዳድራ በማሸነፏ ፈረስ በመሸለሟ ዝነኛ ነበረች። በዚያ ላይ ቆንጆና ፈረስ ጋላቢ በመሆኗ ዝናዋ ሊንር ችሏል። በአስራ አምስት አመቷ ብትዳርም ኮብልላ አዲስ አበባ ከአክስቷ ጋር መኖር ጀመረች።  አማርኛ መስማትና መናገር ካልቻለች ትምህርት ቤት ልትገባ እንደማትችል አክስቷ ስለነገረቻት ከመጀመሪያዉ ቀን ጀምሮ አማርኛ መማር እንደጀመረች ተጠቅሷል። እንዲሁም አማርኛ ፈጥና ለመልመድ ኦሮምኛ መናገር ማቆም እንደሚገባትም አሳስባታለች። በመቀጠልም ጫልቱ ሚደቅሳ የተባለዉ ስም ከቁመናዋና ከቁንጅናዋ የማይስማማ በመሆኑ ስሟን ከነአባቷ ስም መቀየር እንደሚገባ ነግራት ሄለን ጌታቸዉ (ጌታቸዉ የአክስቷ ባለቤት ስም መሆኑ ነዉ) ተብላ ልትጠራ በቅታለች። እንደዉም ቃል በቃል አክስቷ ያለቻት “ … ይህንን መልክና ቁመና ይዘሽ ጫልቱ ተብለሽ መጠራት ይጎዳሻል። ንቅሳት ባያደርጉብሽ ጥሩ ነበር። ግን አንድ ጊዜ ሆኗል። ምንም ማድረግ አይቻልም። አባትሽ መልክሽን አበላሽቶታል። ይህንን የመሰለ ዉበት እንዲህ ማበላሸት በጣም ያሳዝናል። ቢሆንም ግን አማርኛሽን ካስተካከልሽ ምንም አይደለም … ” (ገጽ 73 ይመለከቷል።) ይህም በመሆኑ ሄለን ስትወደስበትና ስትኮራበት የነበረዉ ስም ከነአባቷ ስም ጭምር በመቀየሩ እንዲሁም የዉበት መለኪያ የሆነዉ ንቅሳት በመንቋሸሹ ግራ እንደገባትና አእምሮዋን እንደረበሻት መጽሐፉ ያትታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የድል አጥቢያ አርበኛ - አገሬ አዲስ

ብሩሕ አእምሮ አላት ተብሎ ስለተገመተና የአማርኛ ቋንቋዋም ስለተሻሻለ ትምህርት ቤት እንድትገባ ተወሰነ። ሆኖም ግን ኑሮ ዐልጋ በዐልጋ አልሆነላትም። ለምሳሌ አንድ ጊዜ የአቴቴን መዝሙር ስታዜም የሰሙት የአክስቷ ልጆች እናታቸዉ ፊት ያንኑ ደግመዉት ነበር። ያኔ የአክስቷ ዐይኖች በድንጋጤ ፈጠዉ “ጥንቆላ ታስተምሪያቸዉ ጀመር?” በማለት አንባርቃባታለች (ገጽ 76 ይመለከቷል።) በተጨማሪም የአክስቷ ባል ጣልቃ ገብቶ ስለትርጉሙና ቤተ ክርስትያን ዉስጥስ ምን ብለዉ እንደሚዘምሩ ለጠየቃት ጥያቄ የሰጠችዉን መልስ በመመርኮዝ “ … እኛ ክርስቲያኖች ነን። አንቺም ክርስቲያን ነሽ። ቃልቻ፣ ጨሌ የሚሉት የሰይጣን ልማድ ነዉ። ሰይጣን እንዲህ ያለ ቀዳዳ እየፈለገ ገብቶ ንጹህ መንፈሳችንን ያቆሽሻል … ላንቺም ለሁላችንም የቃልቻዉን ጸሎት ከግቢያችን ማራቅ ይሻላል … ” ብሏታል (ገጽ 76 እና 77 ይመለከቷል።) ሌላ ጊዜ ደግሞ ለምን የዋሬና ኦኮሌ ሥርዓት እንደማይደርግ ስትጠይቅ “ … ቆፍቱ ሳለሽ የምታዉቂዉን ሁሉ እንደሌለ እርሽዉ … እዚህ እሬቻ አናደርግም። ዋሬ የለም! ኦኮሌ የለም። ኢብሳ ኦሮሞ የለም። አቴቴ የለም …. ” በማለት አክስቷ በቁጣ መልሳላታለች (ገጽ 78 ይመለከቷል።) በመሆኑም እነዚህ በምስጋና መልክ የሚቀርቡ የከበሩ በዓላትና ስታደንቃቸዉ የነበሩ “የአስተሳሰቧ ወጎች” አዲስ አበባ ዉስጥ ተንቋሸዉና ነዉር ሆነዉ በመገኘታቸዉ ፍርኅት እንደለቀቀባት ተጠቅሷል።

ትምህርት ቤት ስትገባ ደግሞ ሁሉም ሰዎች የተመካከሩ ይመስል “ … ቆንጆ ነበርሽ! የሆንሽ ንቂሳ ጋ  ሆንሽ እንጂ … ይህን የመሰለ ዉበት ቸክችከዉ አበላሹት … ” ስለሚሏት ገንብታዉ ከኖረችዉ ኩራት ጋር ፍጹም እየተጋጨና መንፈሷን እንዳናወጠዉ ገጽ 80 ላይ ተጠቅሷል። በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ጽጌ የሚባሉ የእንግሊዘኛ መምህር ተማሪዎቹ በሄለን ላይ በቋንቋዋና በንቅሳቷ እንዳይስቁባት እንዲሁም ሁለት ቋንቋ በመናገሯና በትምህርቷም ጎበዝ በመሆኗ ከሁሉም እንደምትበልጥ በመመስከር “የሚያንቋሽሿትን ተማሪዎች” እንደገሰጿቸዉ ገጽ 87 እና 88 ላይ እናገኛለን።

 

በዚህ ዓይነት ሁኔታ አዲስ አበባ ዉስጥ ቆይታ አንድ ወቅት ወላጆቿን ለመጠየቅ ወደ ቆፍቱ ሄደች። ከመሄዷ በፊት ግን አክስቷ  “ … ኦሮምኛ ካወራሽ አማርኛሽ ድርግም ብሎ ነዉ የሚጠፋብሽ። ስለዚህ ‘ኦሮምኛ ረሳሁ’ ብለሽ በአማርኛ ብቻ አዋሪያቸዉ። ከእናትሽ ጋር ሳይቀር በአማርኛ አዉሪ። ጫልቱ የሚለዉን ደግሞ መልሰዉ እንዳያስለምዱሽ ሄለን መሆንሽን ንገሪያቸዉ። ጫልቱ ብለዉ ቢጠሩሽ መልስ አትስጪ … ” በማለት እንደመከረቻት ገጽ 90 ላይ ተወስቷል። በዚህም የተነሣ ገበያ መዉጣት ችግር እንደሆነባትና ዘመድ ለመጠየቅ በየመንደሩ ስትሄድ ስሟን በመለወጧ ጥያቄ እንደሚቀርብላትና በአማርኛ ብቻ መልስ በመስጠቷ እንደዚያ በነገሠችበት መንደር ትርፉ መናቅን እንዳተረፈላትና ‘አባቷ ሸገር ልኮ ገደላት። ያችን የመሰለች ልጅ እንዲህ ሆና ቀረች’ በሚል ሊዘበትባት እንደበቃ ገጽ 96 እና 97 ላይ እናገኘዋለን።

 

ከዕረፍት ቆይታዋ ብትመለስም ወደ አዲስ አበባ እንዳልተመለሰችና እንደዉም ባል አግብታ ለመኖር እንደሞከረች ሆኖም ግን ባሏ በመሞቱ እንደተቸገረች መጽሐፉ ያትታል። በማንነቷ ላይ የተፈጠረባት ዉዥንብር ግን የደርግ ሥርዓት ወድቆ  ኢ.ሕ.አ.ዲ.ግ “የነፍጠኛ ሥርዓት በብሔር ብሔረሰቦች ላይ ያደረሰዉ በደል” በሚል በከፍተኛ ደረጃ በሚስተጋባት ጊዜም በማንነቷ ላይ የተፈጠረባት ዉዥንብር እንደቀጠለ መጽሐፉ ይተርካል። በመሆኑም ሄለንነቷ በኖ ቢጠፋም ወደ ጫልቱነቷ በቀላሉ መመለስ ባለመቻሏ ምን መሆን እንዳለባት ግራ ተጋብታ እንደነበር በመጨረሻም በ1994 ዓ.ም. ወደ ቆፍቱ በመመለስ እናቷን ይቅርታ ስለመጠየቋ ተወስቷል (ገጽ 99 ይመለከቷል።)

 

ወዳደገችበት ቀየ ብትመለስም ሕይወት ለጫልቱ ጥሩ አልነበረም። ብቸኛ ሆና እንደሰነበተች፣ ከእናቷ በስተቀር ማንንም ለማነጋገር ፈቃደኛ እንዳልነበረች፣ እያደርም ምግብ መዉሰድ እንደቀነሰች፣ ወደገበያ መሄድ ጨርሶ እንዳቆመችና በአጠቃላይ ከቤት መዉጣት እንደማትፈልግ ደራሲዉ ለመግለጽ ከሞከረ በኋላ በስተመጨረሻ አንድ ቅዳሜ ቀን ቡና ጠጥታ ጋደም እንዳለች በዚያዉ እንዳሸለበች ጽሁፉ ይደመድማል። የመሞቷ ምክንያትም አከራካሪ ሊሆን እንደሚችል መግቢያዉ ላይ ተገልጿል። ምናልባትም በደረሰባት “በደል” በሁኔታዎች በመገፋፋት ራሷን ያጠፋች (መርዝ ጠጥታ ሊሆን ይችላል) እንዲመስል ጽሑፉ የሚገፋፋ መንፈስ አለዉ።

 

ታሪኩ ዕዉነት ነዉ ወይስ ሙሉ ለሙሉ የፈጠራ ነዉ የሚለዉን ለጊዜዉ ወደ ጎን ትተን ለማስተላለፍ የተፈለገዉ መልዕክት ላይ ማተኮር ይሻላል። ደራሲዉ በዚህ ጽሑፍ ማስተላለፍ የፈለገዉ መልዕክት የሚከተለዉን ነዉ። ጫልቱ የሚል የኦሮሞ ስም ይዛ አዲስ አበባ ዉስጥ መኖር ስለማትችል ስሟን ለመቀየር መገደዷ፣ በግድ አማርኛ እንድትናገር መገደዷ፣ በንቅሳቷ እንድታፍር መደረጓ፣ ያደገችበትና ትኮራበት የነበረዉ ባሕል አዲስ አበባ ዉስጥ ዋጋ አለመሰጠቱና ከዚያም በላይ መንቋሸሹ፣ ወደትዉልድ ቀየዋ ስትመለስ ስሟን በመቀየሯና ኦሮምኛ ረሳሁ በማለቷ መሳቂያ እንደሆነች … በመጨረሻም እንደሄለን መሆንም ሆነ ወቀደድሞ ጫልቱ ማንነቷ መመለስ ባለመቻሏ ለሞት እንደተዳረገች ይተርካል። ታዲያ ለዚህች ልጅ ሞት ተጠያቂዉ የአማራ ብሔር ወይስ ብሔረሰቦች በማንነታቸዉ እንዳይኮሩ “የአማራ ገዥ መደቦች” የሚሏቸዉ የፈጠሩት አስተሳሰብ ወይም ባሕል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ኦሮሞ ሙስሊም ይሆናል የሚል ግምት አለኝ" - የፓርላማው አባል አቶ ግርማ ሰይፉ

 

ጫልቱ ስሟን የቀየረችዉም ሆነ ኦሮምኛ እንዳትናገር ተጽዕኖ ያሳደረችባት የገዛ አክስቷ እንጂ ሌላ የዉጭ አካል አይደለም። የምትኮራበትን ባሕል ያጣጣለችባትና ከጥንቆላ ጋር ያያዘችዉም ይህችዉ አክስቷ ነች። በንቅሳቷም ማፈር የጀመረችዉ ገና ከቤት ነዉ። እንደዉም አባቷ እንደዚያ በማድረጉ አክስቷ እንደበደለኛ ቆጥሯዋለች።

 

ቋንቋ መግባቢያ ነዉ። አማርኛ የአገሪቷ የሥራ ቋንቋ ነዉ። ስለሆነም ኦሮምኛ እንዳለ ሆኖ አማርኛ ማወቅ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም። ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዉስጥም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ መጠቀም የሚከለከልበት ሥርዓት ወይም አካባቢያዊ ተጽዕኖ መኖሩን አላዉቅም። በደርግ ጊዜ የነበረዉን በሚገባ አስታዉሳለሁ። እንደዉም ደርግ ሲወድቅ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበርኩ። በዚያ ሥርዓት ወቅት ሰዎች በኦሮምኛ፣ በትግሪኛ፣ በጉራጊኛ … ወዘተ ሳያፍሩ ዘና ብለዉ ሲያወሩ አስታዉሳለሁ። ከስድስተኛ እስከስምንተኛ ክፍል ድረስ የቀድሞ አምሃ ደስታ እና የአሁኑ እንጦጦ አምባ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስለተማርኩ የአካባቢዉ ሰዎች ሳይሸማቀቁ በዶርዝኛ ሲያወሩ እንሰማ ነበር። በወቅቱ የሚያሾፍ ሰዉ አጋጥሞኝ አያዉቅም።

 

መጠሪያ ስሞች እንደአካባቢዉ ባሕልና ልማድ ይለያያሉ። አንዱ አካባቢ የሚወደዱ ስሞች ሌላ አካባቢ እምብዛም ጥቅም ላይ ላይዉሉ ይችላል። እንዲሁም ከጊዜ ጋር እየቀሩ የሄዱ ስሞችም ይኖራሉ። ከተማ ዉስጥ የማይዘወተሩ ስሞች ሲያጋጥሙ ተማሪዎች ለመቀለድ ወይም ለማብሸቅ ሙከራ ሲያደርጉ ይታያል። ይህ ግን ካለመብሰል የመነጨ ነዉ። የሆነዉ ሆኖ ከብሔር ጋር የተገናኘ አይመስለኝም። ምክንያቱም በርካታ የገጠሩ ኅብረተሰብ የሚጠቀምባቸዉ የአማራ ስሞች በከተማ ተማሪዎች ዘንድ ለማብሸቂያነት ወይም ለተረብ ምንጭ ሆነዉ ሲያገለግሉ እናዉቃለን።

 

ንቅሳት በኢትዮጵያ ዉስጥ በስፋት ይታወቃል። በርግጥ በአሁኑ ሰዓት በተለያየ ምክንያት እየቀነሰ የመጣ ይመስላል። የሆነዉ ሆኖ በተለይም በአማራ፣ በትግራይና በኦሮምያ ገጠራማ አካባቢዎች ራስን ለማስዋብ ግንባር፣ ጉንጭና አንገት ላይ ንቅሳት ማየት የተለመደ ነበር። የከተማ ባሕል ስላልሆነ ልክ እንደስሙ በትምህርት ቤት አካባቢ ልጆች ሊቀልዱበት ይችላሉ።  እነዚያን ልጆች ሊያሸማቅቅ ስለሚችል አግባብ አይደለም። ሆኖም ግን ልጆቹ መሳቃቸዉን እንጂ በሌላዉ ላይ ሊደርስበት የሚችለዉን የሞራል ዉድቀት ስለማይረዱ ማንም ከተረብ ሊያመልጥ አይችልም። የእንደዚያ ዓይነት ልጆችን ሞራል ለመጠበቅና እንዳይሸማቀቁ ለማድረግ የቤተሰብ፣ የአካባቢ ማኅበረሰብ እና በዋንኛነት የመምህራን አስተዋጽዖ ወሳኝ ይመስለኛል። በዚህ ረገድ ደራሲዉ የጠቀሳቸዉ መምህር ጽጌ በጫልቱ ንቅሳት ተማሪዎች እንዳያሾፉባት በመገሰጽና እሷም በማንነቷ እንድትኮራ ያደረጉት እገዛ በመልካምነት ሊጠቀስ የሚገባ ነዉ። እንዲሁም የገዛ አክስቷ ከጅምሩ ሊያፈርሱት የተነሱትን ማንነቷን ለመጠገን ሙከራ ሲያደርጉ ከነበሩት መካከልም የአክስቷ ባል ተጠቃሽ ናቸዉ። እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ደራሲዉ በአማራነት የሣላቸዉ ናቸዉ። ዓላማዉ ማጥላላት ሆኖ ሳለ ለምን እንደዚህ ዓይነት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ እንዳደረጋቸዉ አልገባኝም። ምናልባት ሐቅ ተናንቆት ይሆን? ለማንኛዉም በማናቸዉም ኅብረተሰብ ላይ ሊደርስ የሚችለዉን አጋጣሚ ጫልቱ ላይ በኦሮሞነቷ እንደደረሰባት በማስመስል ለማቅረብ የሞከረዉ ፍጹም አግባብ ያልሆነና ከእዉነታዉ የራቀ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል። እስኪ አስቡት። እንደነዚህ ዓይነት ጽሑፎችን አዲሱ ትዉልድ በሚያነቡበት ጊዜ ምን አይነት ስሜት ሊያድርባቸዉ ይችላል?

 

ከተጠቀሰዉ መጽሐፍ ሳንወጣ ከገጽ 216 ጀምሮ “ናደዉ እና ታሪኩ” በሚል ርዕስ የቀረበ ጽሑፍ እናገኛለን። ይህ ጽሑፍ የሚያወሳዉ ስለናደዉ ጦርና ስለጄኔራል ታሪኩ አገዳደል ነዉ። የእኔን ትኩረት የሳበዉ በገጽ 220 ላይ የተጠቀሰዉ አባባል ነዉ። ይኸዉም “ … መንግሥቱ (የቀድሞዉን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ለማለት ነዉ) ከደርዘን ንግግሩ መካከል ጄኔራል ታሪኩን ለመግደል ያበቃዉ ምክንያት ማቅረብ አልቻለም። ለአብነት የነጋዴነት ዝንባሌ ነበረዉ በማለት ያጣጥለዋል። ይህንንም ከጉራጌነቱ ጋር እንዲያያዝለት ፈለገ … አስረጂ ሲያቀርብ … ‘ሰላሳ ሳንቲም የሚሸጠዉን ለስላሳ መጠጥ ለሠራዊቱ በአንድ ብር እየሸጠ፤ ከአንድ ለስላሳ ሰባ ሳንቲም አትርፎ ወደኪሱ ይከት ነበር’ ይለናል …” በሚል ተቀምጧል። ፕሬዚዳንቱ ስለብሔር አላነሱም። ሁላችንም እንደምናዉቀዉ እንደዚያ አስበዉ ቢሆን ኖሮ ሳያሽሞኖሙኑ ፊት ለፊት ይናገሩት ነበር። ደግሞም ነጋዴነት ከጉራጌነት ጋር የሚያያዝበት ምክንያት አይታየኝም። ለማንኛዉም ግለሰቡ ሰዎች ባላሰቡት መንገድ ሁሉንም ነገር እንዴት ወደ ብሔር ጠምዝዞ የመዉሰድ አባዜ እንዳደረበት በግልጽ ያሳያል።

 

 

  • ቃለ መጠይቅ

 

ተስፋዬ ገብረአብ በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ በኩል ከጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ ጋር ቃለ መጠየቅ አድርጎ ነበር (እ.ኤ.አ. በNov. 2014 ይመስለኛል)። ቃለ መጠይቁ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰ ሲሆን የእኔን ትኩረት የሳበዉ ግን ስለዕዉቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ የጠቀሰዉ ክፍል ነዉ። “ … በዓሉ ግርማ በረቀቀ ዘዴ የኦሮሞን ጥያቄ ያነሣ ነበር” ይልና በመቀጠልም “በኢትዮጵያ ደራስያን ታሪክ ዉስጥ የኦሮሞን ጥያቄ በቅድሚያ ያነሳዉ በዓሉ ግርማ ነዉ … ቀጥሎ ኦሮማይ ላይ አነሣ። የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ላይ እንዳለ ፍንጭ ሰጠ። ታደሰ ቆሪቾ የሚባል ሰዉ አመጣ። የሉሊት ታደሰን አባት አመጣዉ … ” በማለት ያጠናክረዋል።

 

የበዓሉ ግርማ የመጀመሪያ ድርሰት የሆነዉ “ከአድማስ ባሻገር” ላይ ሉሊት ታደሰ የምትባል ገጸ ባሕሪ አለች። ቀደምት ስሟ ጫልቱ ቶሎሳ ነበር። ስሟን የቀየረችዉ ራሷን እንደጠይም ጣዖት ስለምትመስል “ጫልቱ” የሚለዉ ስያሜ ለዚያ የሚስማማ ባለመሆኑ እንደሆነ እዚያዉ መጽሐፍ ላይ ተጠቅሷል። ተስፋዬ ገብረአብ ግን በማንነቷ በማፈሯ ራሷን ለመደበቅ ስትል ያደረገችዉ ለማስመሰል ሞክሯል። ሌላዉ የሚገርመዉ ይህንን ታሪክ ከ“ኦሮማይ” መጽሐፍ ጋር ለማያያዝ መሞከሩ ነዉ። እንደሚታወቀዉ “ኦሮማይ” የበዓሉ ግርማ የመጨረሻ ድርሰትና ሕይወቱን ያጣበት መጽሐፍ ነዉ። እዚህ መጽሐፍ ላይ ሻለቃ ታደሰ ቆሪቾ የሚባል ሰዉ ተጠቅሷል። የአርሚ አቬሽን ትራፊክና ስምሪት ኃላፊ ነበር። ይህ ሻለቃ በስዉር ለሻዕቢያ ይሠራ ከነበረና ዕቁበ ሲላ ከሚባል መካኒክ ጋር በመተባበር ወደ አዲስ አበባ መሣሪያ ሲልክ ነበር። እንዲሁም “የኦሮማይን ተልዕኮ” በቅጥረኛነት ከሚያስፈጽሙ ሰዎች ዝርዝር ዉስጥም ነበር። ለማገናዘብ እንዲረዳ ሻለቃዉ የተጠቀሰበት ክፍል ገጽ 32 -33፣ 182- 184፣ 242 – 244 እና 367 ናቸዉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እውን ውሳኔው ከዘላቂ የነፃነት፣ የፍትህና የሰላም አርበኝነት የመነጨ ነው? - ጠገናው ጎሹ

 

ዕቁበ ሲላ በትዉልድ ኤርትራዊ ነዉ። የሻዕቢያን ዓላማ በመደገፍ በስዉር ቢተባበር አያስደንቅም። ሻለቃ ታደሰ ቆሪቾ ግን ሲተባበራቸዉ የነበረዉ ዓላማቸዉን ደግፎት አልነበረም። ዕድሜዉ ለጡረታ ቢደርስም ምንም ቅሪት አለመያዙ ይሰማዉ ስለነበር ለገንዘብ ጥቅም ሲል ብቻ እንደነበር ከገጽ 33 እና 244 መረዳት ይቻላል።

 

ለጊዜዉ ብሔሩን ትተን ሻለቃ ታደሰ ቆሪቾ ኢትዮጵያዊ ነዉ። በመሆኑም የሻዕብያን የመገንጠል ዓላማ ከልቡ አምኖበት ሊደግፍና ሊተባበር የሚችልበት ምክንያት አይኖርም። በዚያ ላይ ለአገሩ አንድነትና ዳር ድንበር መከበር ሕይወቱን ለመሰዋዕት ቃለ መሐላ የገባ ወታደር ነዉ። በዚህም የተነሣ የፈጸመዉ ድርጊት ከአንድ ወታደር የማይጠበቅ ከፍተኛ የአገር ክሕደት ወንጀል ነዉ።

 

ተስፋዬ ገብረአብ ግን በዓሉ ግርማ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ላይ እንዳለ ለማሳየት የሉሊት ታደሰን አባት “ኦሮማይ” ላይ በሻለቃ ታደሰ ቆሪቾ አስመስሎ እንዳቀረበዉ በድፍረት ይናገራል። በመጀመሪያ ደረጃ በየትኛዉም የተለጠጠ አተረጓጎም ብንሄድ የሉሊት አባትና ሻለቃ ታደሰ ቆሪቾን የሚያስተሳስራቸዉ አንዳችም ነገር ማግኘት አንችልም። በዚያ ላይ ከላይ እንደተገለጸዉ “ታደሰ” የሚለዉ ስም የሉሊት ፈጠራ ስም እንጂ የእዉነተኛ የአባቷ ስም አይደለም። ሻለቃ ታደሰ ቆሪቾ ደግሞ አባትና እናቱ ያወጡለትን ስም ስለመቀየሩ የተወሳ ነገር የለም። በመሆኑም ደራሲ በዓሉ ግርማ ባላሰበዉ መንገድ ለራሱ ዓላማ እንዲስማማ ሲል ብቻ እንደዚያ ዓይነት ትልቅ ድምዳሜ ላይ መድረሱ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነዉ።

 

በሁለተኛ ደረጃ ሻለቃ ታደሰ ቆሪቾ የሉሊት አባት ነዉ ብለን ብንቀበል እንኳን ከተስፋዬ ገብረአብ መሠሪ መልዕክት ጋር የሚሄድ አይደለም። የኦሮሞ ሕዝብ ኩሩና አገሩን የሚወድ ነዉ። ከጥንት ጀምሮ የአገሩን አንድነትና ዳር ድንበር ለማስከበር ሲዋደቁ የነበሩ በርካታ ጀግኖችን ያፈራ ሕዝብ ነዉ። በኢትዮጵያና በሻዕብያ መካከል በተደረገዉ ጦርነት እንኳን በርካታ አንቱ የተባሉ የኦሮሞ ብሔር የሆኑ ጄኔራሎች ተሳትፈዉበታል። ለምሳሌ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ፣ ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ፣ ጄኔራል ረጋሳ ጅማ … ወዘተ እያሉ መሄድ ይቻላል። በርግጥ እንደማንኛዉም ሕዝብ የኦሮሞ ሕዝብም መንግሥትንና አገዛዝን በመቃወም እንቅስቃሴ ዉስጥ በስፋት ተሳትፏል። የሆነዉ ሆኖ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ለተራ የገንዘብ ጥቅም ሲል አገሩን ክዶ ለሻዕብያ የጦር መሣሪያ ሲያሻግር ከነበረዉ ሻለቃ ታደሰ ቆሪቾ ጋር ለማመሳሰል መሞከር የኦሮሞን ሕዝብ የሚያዋርድ እንጂ የሚያኮፍስ አይሆንም። የደራሲ በዓሉ ግርማንም ክብር የሚነካና ዉድ ሕይወቱን የከፈለበትን መጽሐፍ የሚያጠለሽ ነዉ።

 

በዓሉ ግርማ በእናቱ ኦሮሞ እንዲሁም በአባቱ ሕንዳዊ ነዉ። ይህ ዕንቁ ደራሲ ከአድማስ ባሻገር፣ የሕሊና ደወል፣ የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ ደራሲዉ፣ ሀዲስ እና ኦሮማይ የተሰኙ ስድስት መጽሐፍትን ለንባብ አብቅቷል። በአጻጻፍ ስልቱ ብቻ ሳይሆን ጽሑፎቹ በሚይዟቸዉ ጥልቅ መልዕክቶች ጭምር ለማንበብ የታደለ ሁሉ የሚመሰክረዉ ነዉ። ከነዚህ መጻሕፍት ዉስጥ የኦሮሞን ሕዝብ ነጥሎ ወገንተኛነት ያሳየበት አንድም ቦታ የለም። ተጀምሮ እስከሚጨረስ ድረስ ሲጽፍ የኖረዉ እንዳንድ ኢትዮጵያዊ ነዉ። መጨረሻም ኦሮማይን የጻፈዉ ለእናት አገሩ ካለዉ ፍቅርና ተቆርቋሪነት ነዉ። እኔ በበኩሌ ከእሱ መጽሐፍ ዉስጥ ኦሮሞ መሆኑን የጠቆመበትን/ያንጸባረቀበትን ክፍል አይቼ አላዉቅም። ተስፋዬ ገብረአብ ግን የመሠሪ ዓላማዉ አጋር አድርጎ ለማቅረብ ሲታክት ይታያል። ይህ በፍጹም ተገቢ ያልሆነና የጽሑፉንም ዓላማ የሚያዛባ ነዉ። ሕይወቱንም ያጣበትንም ትልቅ መስዋዕት ጠበብ ተደርጎ እንዲታይ የሚያደርግ ነዉ። እንደጀመረዉ ራሱን ችሎ ቢሄድ ይሻል ነበር።

 

በነገራችን ላይ በዚያ ቃለ መጠይቅ ወቅት ሎሬት ጸጋየ ገብረመድኅንም የኦሮሞ ብሔርተኝነት ስሜት እንዳለዉ ለማሳየት በግጥሙ ዉስጥ የተጠቀመባቸዉን የኦሮምኛ ስያሜዎች በማጣቀስ ለማያያዝ ሙከራ አድርጓል። በሥነ ግጥም ላይ ጎበዝ ባልሆንም የእሱን ግጥሞች ለማየት እንደሞከርኩት ኢትዮጵያን በአራቱም ማዕዘን ከጫፍ እስከጫፍ የሚነካ ሆኖ ነዉ ያገኘሁት። አንድም ቦታ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን የሚያሳይ ነገር አላየሁም። ይህ ማለት ኦሮሞ አይደለም ማለት አይደለም። ወይም በኦሮሞነቱ አይኮራም ለማለት አይደለም።  በጽሑፉ የምናዉቀዉ ግን በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ነዉ።

 

ቀደም ሲል ስለደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋየ ገብረአብ ያቀረብኩት ጽሑፍ ከሞላ ጎደል ይህንን ይመስል ነበር። እናስ የእንደዚህ አይነት ጽሑፎች ባለቤት የሆነን ሰዉ ስንዘከር ምን አይነት መልዕክት እያስተላለፍን ነዉ? በጽሁፎቹ ያስተላለፋቸዉን መርዘኛ፣ ከፋፋይና አጋዳይ መልዕክቶችን እንጋራቸዋለን? ቆም ብለን ማሰብ የሚገባን ይመስለኛል፡፡

 

 

ቸር ይግጠመን     

የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ለማግኘት ለምትፈልጉ፡- mekonnen_ashagre@yahoo.com  

4 Comments

  1. ወዳጄ የተስፋዬ ገ/አብን ተረት ለሚመጥናቸው በእውቀት ለተጎዱ ተከታዮቹ ተውላቸው፡፡ እኛ ከ10ኛ ክፍል ተማሪ ተረት እንጅ እውቀት ልንገበይ አንችልም የተስፋዬን ታሪክ ለሚመጥናቸው ትቶ በመውደቅ ላይ ያለችን አገር ተጋግዘን እናንሳ፡፡ ይልቅስ በአውሮፓ በሚኖርበት አገር አንድ አገር ወዳድ ጀግና ተስፋዬን ጉድ ያደረገው ፋኖ እዚህ ላይ ሊታወስ ይገባል ተስፋዬ መርዛማ ተረቱን ለሆዳም አሳታሚዎች ልኮ ሌላ ደም ከማፍሰሱ በፊት የመጻፉን ረቂቅ በመውሰድ የገዛ ተስፋየን ደም አገንፍሎ እንደ መለስ ላይመለስ የሸኘው ወንድማችን በዚህ አጋጣሚ ሊታወስ ይገባዋል አለማየሁ መለስ መሰለኝ ስሙ፡፡

  2. Wow, it is so articulative and worth reading. I appreciate the writer’s patience amd commitment to discredit such a guy.

  3. የሰለለት አገር ይዘክረው እንጅ እነዚህ ምን ሊባሉ ነው ሲጻፍ ይፈታተናል እንጅ የምን ማቃጠር ይሉታል? በዚህ አይነት የሞሶሎኒን የልደት ቀን የኢሳይያስን የልደት ቀንም አብረው ያክብሩ እነ ነውር ጌጡ። እነ ጃገማ ኬሎን፣ጎበና ዳጨ ሳይዘከሩ እነ ህዝቅኤል ጋቢሳ፣ጁዋር መሀመድ፣ዳውድ ኢብሳ፣ዲማ ነገዎ አሁን ደግሞ ተበድረው ተስፋዬ ገአብን ይዘክራሉ።

  4. መኮንን አሻግሬ አንተም ለአቅመ ንባብ አልደረስክም ማለት ነው በእውነት ይህ አስተያየት ለተስፋዬ ይገባዋል “ተስፋየ የተዋጣለት የልብ ወለድ ደራሲ መሆኑ አይካድም” ታዲያ ዘካሪዎችስ ምን አጠፉ? ሃሳባቸውን እኮ ነው ያጠናከርክላቸው፡፡ነገ ደግሞ መለሰ ዘራዊ የተዋጣለት መሪ ነው ልትለን ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share