ከደረጀ ተፈራ፣
እንደሚታወቀው የአማራ ህዝብ ከግማሽ ክ/ዘ በላይ በኦነግ፣ በህወሃት፣ በኢህአዴግ አሁን ደግሞ በብልፅግና መንግስት ተቆጥሮ የማያልቅ መከራና በደል ደርሶበታል። ሽመልስ አብዲሳ ሰበርነው ያለውን የአማራ ህዝብ ኦነግ ሸኔ እያሳደደ ይገድላል፣ የሃገሪቱ የስልጣን መንበር ላይ የሚገኘው ጠ/ሚ አብይ አህመድ እንደ መንግስት ህዝቡን ከጥቃት ከመከላከል ይልቅ በአማራ መቃብር ላይ ዛፍ እንተክላለን እያለ ያላግጣል። ከአራት ኪሎ እስከ ጫካ ድረስ እየተናበቡ የአማራን ህዝብ ከምድረ ገፅ ለማጥፋት እየተረባረቡ ይገኛሉ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የደግነት እና የሰብአዊነት ምሳሌ ተደርጎ የተገለፀ የአንድ የሳምራዊ ሰው ታሪክ በሉቃ 10፥ ከ25 – 37 ላይ ተጽፎ እናገኛል። በአንድ ወቅት አንድ ሳምራዊ ሰዉ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲጓዝ በመንገድ ላይ ወንበዴዎች አገኝተውት ገንዘቡን ዘረፉት፤ ልብሱንም ገፈፉት፣ በህይወት እና በሞት መሃል ደብድበዉ በሜዳ ላይ ጥለውት ሄዱ።
በዚያ መንገድ አንድ ካህን ሲሔድ የወደቀውን ሰው ቢያየውም፤ ምንም ሳይረዳዉ አልፎት ሔደ፡፡ ከካህኑ ቀጥሎም አንድ ከሌዊ ወገን የሆነ ሰው በዚያ መንገድ ሲጓዝ በወንበዴዎች ተደብድቦ የወደቀዉን ሰዉ ቢያየውም እርሱም ሳይረዳዉ ዝም ብሎ ጥሎት ሄደ።
ነገር ግን አንድ ሳምራዊ በዚያች መንገድ ሲያልፍ፤ አይቶም አዘነለት፤ ልቡም ስለራራ በሰብአዊነት የቆሰለውን ሰው ቁስል ጠራርጎ፣ ቁስሉም እንዲያደርቅለት ወይን አደረገለት፤ እንዲያለሰልስለትም ዘይት አፈሰሰለት፡፡ ሩህሩህ ሰው በዚህም ሳያበቃ ቁስለኛውን ደግፎ እንግዳ ማረፊያ ቤት ከፍሎ አስቀመጠው። የቤቱ አከራይንም በመጥራት ወጪህን ሁሉ እከፍልሃለሁ ይህንን ሰው አስታምልኝ በማለት የተደበደበውን ሰው አደራ ሰጥቶ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔርን አመልካለሁ፣ አገለግላለሁ ከሚለው ከካህኑ እና ህግ አውቃለሁ ከሚለው ከሌዋዊዉ ይልቅ እምነቱን በምግባር ያሳየ፣ ሰብአዊነት የተሰማው፣ በወንበዴዎች ተደብድቦ ለወደቀዉ ምስኪን ሰው የደረሰለት ደጉ የሰብአዊነት ምሳሌ የሆነው ሳምራዊው መንገደኛ ነው።
ስለዚህ በዘመናችን በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈፀም፣ እንግልት፣ በደል፣ ወረራ፣ ግድያ፣ ዝርፊያ፣ ከተማ ማውደም፣ ህዝብን ማፈናቀል፣ የዘር ማፅዳት እና ጭፍጨፋ ባጠቃላይ በሰብአዊ ፍጡር ላይ የሚፈፀምን ወንጀል አይቶና ሰምቶ የማይቆረቆር፣ በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ የሚገኝ አረማዊ ድርጊትን አቃሎ የሚመለከት፣ የሚያድበሰብስ፣ በራስ ላይ ወይም በቅርብ ቤተሰቡ ላይ ሊፈፀም የማይፈልገውን አስነዋሪና ጨካኝ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈፀም እያየና እየሰማ በምንቸገረኝነት ወይም በሌላ ምክንያት በግፉአን ሞትና መከራን አንዳላየ የሚሆን ወይም የሚያላግጥና የሚያቃልል ቅድም ሆነ ሼክ ወይም የትኛውም ዜጋ ሁሉ ከዚህ በላይ የተገለፀው የካህኑና የሌዋዊው ምሳሌ ለእነሱም የተነገረ መሆኑ መረዳት ይገባዋል።
በውዳሴ ከንቱ ተሸንፋችሁ አረመኔ ገዢዎችን ለማስደሰት ወይም ለማባበል ስትሉ የተገፋውን እና የተበደለው የአማራ ህዝብ እንደ መስዋዕት በግ ማቅረብ የምትፈልጉ፣ በግል ጥቅምና ክብር ለተሸነፋችሁ ከንቱዎች ይህ መልዕክት ይድረድልኝ።