September 22, 2023
9 mins read

ለምንገኝበት እጅግ መሪርና አስከፊ እውነታ ተገቢውን ትኩረት እየሰጠን ካልተራመድን …

T.G

September 21, 2023

ማነኛውም ሰው ዘመን ያፈራውን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ በመጠቀም ከገሃዱ ዓለም አንፃር የሚታዘበውንና የሚረዳውን ጉዳይ ለህዝብ በማቅረብ እና ጠቀሚታ እንዲኖረው በማድረግ የድካሙን ዋጋ የማግኘቱ (የመጠየቁ) ተገቢነት አያጠያይቅም።

በዚህ ተጠቃሚ የሆነ ወይም የሚሆን ህብረተሰብም (ትውልድም) ይህንን መልካም አስተዋፅኦ ሰምቶና ታዝቦ የጊዜያዊ ስሜቱ ማርኪያ (amusement) ማድረግ ሳይሆን ይበልጥ እያዳበረ የሁለንተናዊ ሰብእናውና ደስታው (real sense of humanity and happiness) መሠረትና ዋልታ ሊያደርገው ይገባል።

በአሁኑ ጊዜ እየታዘብነው ያለነው ግን ይህንን አይነት አስተሳሰብና አካሄድ ሳይሆን በመሬት ላይ እየሆነ ያለውን እጅግ መሪርና አደገኛ የትውልድ ቀውስ እየሸሹ በየአዳራሹ፣ በየአደባባዩና በየሚዲያው የሚደረግን አያሌ ሚሊዮኖች ተከታዮችን (ያውም ከአድናቆት በስተቀር የራሳቸውን ነፃና ሚዛናዊ ህሊና ተጠቅመው ሂሳዊና ገንቢ አስተያየት የሌላቸውን ወገኖች) ለማፍራት የሚካሄድ “የታዋቂነት” ተውኔትን ነው።

በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ከሆኑት የዚህ ትውልድ አባላት አንዱ የዶንኪ ቲዩቡ እሸቱ ነው። በተወሰነ ተሰጥኦና ችሎታ የህዝብ እውቅና ማግኘት በሁሉም ነገር አዋቂ መሆን ማለት እንደሆነ አድርጎ ከመቀበልና ከማስተጋባት በሚመነጭ እጅግ ደካማ ወይም እጅግ የተንጋደደ አስተሳሰባችን ምክንያት እሸቱና መሰሎቹ ለምንና እንዴት ተደፈሩ በሚል አካኪ ዘራፍ የሚሉ ወገኖች እንደሚኖሩ በሚገባ እረዳለሁና አይገርመኝም።

እሸቱን በሚዲያው ላይ በሚያቀርባቸው ማህበረሰባዊ ጉዳዮችን እና ሃይማኖታዊ እምነትን (ገዳማትን) በሚመለከቱ ዝግጅቶች እንጅ በአካል ወይም በሌላ አጋጣሚ አላውቀውምና ከግሉ ምንነት፣ ማንነት፣ ባህሪ፣ ህይወት፣ እምነት፣ አስተሳሰብ፣ ወዘተ ጋር ፈፅሞ ጉዳይ የለኝም።

አስተያየቴ ፖለቲካ ወለድ ከሆነው የዘመናት መከራና ፍዳ የመውጫ በር አጥቶ የመቃብር እና የቁም ሞት ሰለባ በሆነ ህዝብ መካከል እየኖሩ ምንም እንዳልተፈጠረ በሚያስመስል ሁኔታ በየአደባባዩ፣በየአዳራሹና፣ በየቤተ እምነቱ (በየገዳሙ) እና በየሶሻል ሚዲያው ድንቅ፣ አስገራሚ፣ ተአምረኛ፣ አስቂኝ፣ አዝናኝ፣ አስተማሪ፣ ሰማዕት፣ ቅዱሰ ቅዱሳን፣ ጥዑመ ልሳን፣ ፍኖተ ፅድቅ፣ ትንቢተ ፅድቅ ፣ ወዘተ በሚል በራስ ዓለም ውስጥ መሸሸግ ቢያንስ ከሞራላዊ እሴት አንፃር ፈፅሞ ትክክል አይደለም ከሚለው መሠረታዊ እሳቤና እምነት የሚነሳ ነው።

በየአዳራሹና በየአደባባዩ አጨብጭቦ፣ እልልታውን አቅልቶ፣ በአግራሞት ተደምሞ፣ ወዘተ ሲወጣ ምን ተማርክበት? ከነማን ተማርክ? ለምንና እንዴት ተማርክ? የምትኖርበትን ገሃዱ ዓለምክንና የአዳራሽ ውስጥ/ የአደባባይ ላይ አድናቆትክንና ፈንጠዝያህን እንዴት አነፃፀርከው?  ምንስ ልታደርግና ልትሆን አስበሃል? ወዘተ ተብሎ ሲጠየቅ ያንኑ የአዳራሽ ውስጥና የአደባባይ ላይ ስሜታዊነት የተጫነው እርሱነቱን መልሶ የሚተርክ ትውልድ ፈፅሞ የትም ፎቀቅ ለማለት አይቻለውም።

የዚህ ዘመን ወጣት ትውልድ የአገሩ ህዝብ በዘመን ጠገቡና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድን አገዛዝ ምክንያት  ሰብአዊ ማንነቱና ክብሩ  መግለፅ በሚያስቸግር ሁለንተናዊ መከራና ውርደት ውስጥ በሚገኝበት በዚህ እጅግ አስከፊና አስፈሪ ወቅት ምንም እንዳልተፈጠረ  ወይም አገር በሰላም ውሎ በሰላም እንደሚያድር እና የእነርሱን የመድረክ ላይ ተውኔት በጉጉት እየጠበቀ “ዘመነ ፍስሃን” ማጣጣም እንደሚኖርበት  ሊነግሩትና ሊያሳምኑት የሚሞክሩ አባላቱን ቢያንስ አደብ ግዙ ሊላቸው ይገባል።  

በሰላም ተወልደው፣ አድገው፣ ተምረውና ተመራምረው ከራሳቸው ህይወት አልፎ ለአገራቸው (ለህዝባቸው) አያሌ ታላላቅ ሥራዎችን ሊሠሩ የሚችሉ በአያሌ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህፃናት የፈጣሪ እና የወገን ያለህ እያሉ እጅግ ለመግለፅ የሚከብድ የሰቆቃ ድምፅ (ጩኸት) እና በአያሌ ንፁሃን የደም ጎርፍና የቁም ሞት ዋይታ በተከበበ አዳራሽ ውስጥ  እየተሰየሙ ምንም እንዳልተፈጠረ በሚያስመሰል ሁኔታ በአግባቡ ቢያዙ ከነድንቅነታቸው ሊያድጉ የሚችሉትን  ህፃናት በስሜት፣ በጭብጨባ፣ በእልልታ፣ በመውረግረግ እና በአጠቃላይ ለእነርሱ በማይመጥን የጥያቄና የትርክት ጋጋታ እያጀቡ የማህበራዊ ሚዲያ ንግድ መነገጃ ማድረግ ቢያንስ የሞራል ጎስቋላነት ነውውና ከምር ቆም ብለንና ትንፋሽ ወስደን ማሰብ ይኖርብናል።

ልብ በሉ ወገኖቼ! እንዲህ አይነት ህፃናት ከተገቢው የሙያ እገዛ ጋር ባልተያዙበት ሁኔታ በየአዳራሹ  እየሰየሙና እያሰየሙ በስሜታዊነት ማጨብጨብ፣  እንኳን እነርሱን አ ቂንም እጅግ በሚፈታተን ልክ የሌለው አድናቆት አዳራሹን ማናወጥ፣ በጭብጨባና በእልልታ ከሚቀልጠው አዳራሽ ውጭ ሌላ ዓለም የሌለና የሚኖር እስኪመስላቸው ድረስ ማደናገር፣ ወዘተ በወደፊት የእድገትና የሙሉ ሰብእና አቋማቸውና ቁመናቸው ላይ ሊያሳድር የሚችለውን አላስፈላጊ (አሉታዊ)  ተፅዕኖ (retardation) በእውን ልብ ማለት ያሻልና ልብ ያለው  ወገን ልብ ይበል!!

የትኛውም የሙያ ተሰጥኦና ችሎታ ለዘመናት  የመጣንበትንና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንኳንስ ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝበትን እጅግ  መሪርና አስፈሪ ሁኔታ ቢያንስ ግምት ውስጥ የሚያስገባ ካልሆነ  የእሴትነቱ ትርጉም ጎደሎ ነውና ሊያሳስበን ይገባል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

የኦህዴድ መራሹ ብልፅግና  መንግስት  በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በንጹሀን  ዜጎች ላይ እየወሰዳቸው ያሉ የነፃ እርምጃ  ግድያዎች  መንግስት ያሰበውን የፖለቲካ ግብ ያሳካለታል  ወይ ? በኔ አመለካከት እነዚህ የንፁሃን ዜጎች  የጅምላ ግድያዎች  በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላዎ (double edge sword) ናቸው:: ፩- መንግስት እያሰላው

 የኦህዴድ መራሹ ጅምላ ግድያዎች ስሌት (ሸንቁጥ- ከምዕራብ ካናዳ)

January 24, 2025
እነዶ/ር ደብረፅዮን እና በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መሪዎች እነጌታቸው ረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ሰራዊቱን ወደውግንና አስገብቷል። የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት ባወጡት መግለጫ ውግንናቸው ከእነዶ/ር ደብረፅዮን ጋር መኾኑን አስታውቀዋል።

በትግራይ የተፈጠረው ምንድነው?

January 23, 2025
የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ ምግቧንም ተጋርቶ ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ ማን ይኖራል ከቶ? በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት

ሰው በሰውነቱ – ከ ይቆየኝ ስሜ

Go toTop