ከ፡ ነሲቡ ስብሐት (አሉላ) ቨርጂንያ ሰሜን አሜሪካ (nhsibhat@gmail,com) 7033004302 ቀን፦ ነሐሴ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. (July 13,2023)
በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬን አቀርባለሁ።
ነሐሴ 02 ቀን 2015 ዓ.ም. “የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የውጭ ድጋፍ ሰጪ አስተባባሪ ኮሚቴ”ን በመወከል እንደ ሊቀ መንበርነቶ በABC TV አማራ ሚድያ ከጋዜጠኛ መልካም መላ ጋር ያደረጉትን ውይይት መነሻ በማደረግ ያለኝን ቀና አስተያየት ልገልጽልዎ ወደድኩ። ውይይቱን እዚህ በመጠቆም ማድመጥ ይቻላል
https://youtu.be/k6ldn3gXt24
በአሁኑ ወቅት የ “አማራ ፋኖ” እያደረገ ያለው ሀገር የማዳን ተጋድሎ አግባብና ተደጋፊ ነው ስል በራሴ በኩል ነው። ስለ አማራው እልቂትና ስለ ፋኖ መሳሪያ ትግል አስፈላጊነት ትንታኔ ውስጥ ሳልገባ በሰላማዊ መንገድ ሲጨፈጨፍ የኖረው አማራ ወቅቱን ጠብቆ በትንሹ ለ32 ዓመት ሲሰደድ፣ ሲታሰር፣ ሲደበደብ፣ ሲገደል፣ ሲታረድ የነበረው ስቃይና መከራ እንደ ውሃ ፍላት ሞቆ፣ ሞቆ የመጨረሻው የሙቀት መጠን 100 ድግሪ ሴንቲግሬድ እንደሚፈላ ተፈጥሮአዊ ሕግ የአማራው ፍልሚያ ተወደደም ተጠላ ፈልቷል። ይህ ፍላት ደግሞ በድል ሳይጠናቀቅ ወደ ኋላ መመለስ አይደለም መቀዝቀዝ ካሳየ ሊከሰት የሚችለው፣ ቀደም ሲል የነበረው የእልቂት መጠን ጨምሮ የአማራ ዘር እጅጉን ማለቅ ብቻ ሳይሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ ልትበታተን እንደምትችል መናገር ይቻላል።
የጦርነትን አስከፊነት፣ ሕይወት ቀጣፊነት፣ ንብረት አውዳሚነት ብንረዳም ዜጎች መሳሪያ አንግበው ሚፋለሙት ሰላምን ጠልተው ሳይሆን አምባገነንና ገዳይ አገዛዞች የግድያና የጭፍጨፋው መጠናቸው እያየለ፣ ይባስ ብሎም የሰላም በራቸውን ዘግተው በእብሪት ከመግዛት አልፈው ሕዝብን አላስቀምጥ ሲሉ፣ ሕዝብና ልጆቹን ከመተንኮል አልፈው ሲያሳድዱ፣ ሲገድሉ፣ በኑሮ አድቅቀው ሲያስርቡ፣ ለበሽታ ሲዳርጉ እየተንገላታ ያለው ሕዝብ ለመብቱ መሳሪያ ቢያነሳ ተው ሊባል አይገባውም።
አማራውም እየተካሄደበት ካለው የዘር ጭፍጨፋ ከመከላከል አልፎ አሁን ላይ እንደምናየው ማጥቃት ደረጃ መድረሱ እሰየው ያሰኛል። በዚህ ሂደት ላይ ይህን እቅስቃሴ እንመራለን ወይም ያገባናል ለሚሉ “ታዋቂ” ግለሰቦች፣ ምሁራን ያለኝን አስተያየት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።
በተለይ በቅርቡ የ “አማራ ሕዝባዊ ግንባር የውጭ ድጋፍ ሰጪ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር” ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በABC አማራ ሚድያ ባስተላለፉት ውይይት ላይ በድጋፍ ሰጪነት አልፎ እንደ አመራር የሚሰጡት መግለጫ ላይ ያየሁትን ቅሬታ ላጋራ ፈለግሁ።
በእኔ አመለካከት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ይህንን ንቅናቄ እየመራሁ ነኝ ቢሉ አይጨንቀኝም። ዋናው ፍላጎቴ በቅድሚያ የዶክተር ዐብይ መንግሥት ተወግዶ ሌላ ተረኛ መንግስት መተካት ላይ ሳይሆን በጥቅሉ ኢትዮጵያችን ከዘረኛ አገዛዝና በዘርና ቋንቋን መሠረት አድርጎ ለ32 ዓመታት ከተጫነባት የዘር ሕገ መንግሥት ተላቃ ሁሉንም ያማከለ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞ፣ ዘረኝነት ለኢትዮጵያዊነት ቦታውን ለቆ ማየት ነውና አካሄዳቸው በዚህ ከሆነ ድጋፌ ከዚህ አንጻር መሆኑን ልጠቁም እወዳለሁ።
“መነሻችን አማራ መዳረሻችን ኢትዮጵያ” ብሎ የተነሳው “የአማራ ሕዝባዊ ግንባር” ይዞ የተነሳው ስምና መፈክር ቀላል አይደለም።
“መነሻችን አማራ” ሲል እንቅስቃሴው በአማራው ዘር የተጀመረ “አማራ ፋኖ” እንደሆነ ሲያመለክት መዳረሻው አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ አፋር፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላ፣ ወላይታ፣ ወዘተ. በጥቅሉ ከደቡብ ሰሜን፣ ከምዕራብ ምሥራቅ በአራቱም አቅጥጫ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘረኛው የብልጽግና አገዛዝና ከወያኔ ዘርንና ቋንቋን ተገን ያደረገ ሕገ መንግሥት አላቆ በልጆቿ ለልጆቿ የሆነች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መመስረት ሲሆን እውነትም “መዳረሻችን ኢትዮጵያ” የሚለው ይሰምራል። መስመር ብቻ አይደለም ይህ አካሄድ በዚህ ጉዞው ሌሎች ዘሮችን ሁሉ እያካተተ ይጓዛል። በቀጣይነትም በብልጽግናው ሸኔ ንብረታቸው እየተዘረፈ መከራ ላይ ያሉትን የኦሮሞ ወገኖችን፣ በነጌታቸው ረዳ ወያኔ ሥር እየማቀቁ ያሉትን የትግራይ ወገኖቻችንን ከነኚህ ሁለት “ዘመነ ዳቢሎስ” ኃይሎች በማላቀቅ “መዳረሻው ኢትዮጵያዊነት” ላይ ይሆናል። በአረመኔው የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ሊጠፉና ተዳክመው ለአገዛዙ እንዲያጎበድዱ እየተዘመተባቸው ያሉትን ሁለት ታላላቅ ሃይማኖቶቻችን ላይ እየተደረገ ያለው ዝርፊያና ውድመት ይቆም ዘንድ፣ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩትን የኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምህመናንን በማካተትና በማቀፍ የሚጓዝ ግዙፍ ኃይል በመሆን ለድል የሚበቃው “አማራ ፋኖ” እውን ይህን ሲያደርግ ኢትዮጵያ ላይ ደረሰባት እንላለን። እውነትም የፈሰሰው ደምና የተከሰከሰው የልጆቿ/የአማራው አጥንት ኢትዮጵያን በማዳን ታሪክ ተሠራ እንላለን። የዚህ ጊዜ በወሬና በጉራ ሳይሆን በተግባር አማራ የኢትዮጵያ መሆኑን በኩራት ቢናገር ቢፎክር አይደንቅም። በሆነው ባልሆነው እየተባላ ያለውና እራሱን አጠንክሮ አንድ ኢትዮጵያዊ ኃይል በዚህ 32 ዓመታት ጉዞ ሊገነባ ያልቻለው የአንድነት ኃይል እስከዛሬ ቢጠበቅ የሚታይ ኃይል ሁኖ ከመውጣት ይልቅ “ወሬ ብቻ” በመሆኑ ትግሉና ኢትዮጵያን የማዳን ሂደት እንደ ጊዜው ፖለቲካ አማራው ላይ ሊወድቅ የተገደደው ለዚህም ነው።
“አማራ ሕዝባዊ ግንባር” ሲል እጅግ በጣም “አማራ ግንባር” ከሚለው ይለያንና ሕዝባዊነትን በስሙ ሲያካትት ሌሎች ኃይሎችንም በሂደት እንደሚመለከት፣ እንደሚቃኝ ያመለክታል። አዎ! ያለውን የዘር ፖለቲካ ሥርዓት ከሀገራችን ለአንዴም ለመጨረሻም ለማስወገድ አማራው ታሪካዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛልና ጠንክሮ ይጓዝ እላለሁ። እየተዋጋ ያለውን የመንግሥት ሠራዊት ለመከፋፈልና በተለይ በኢትይጵያዊነቱ የሚኮራው የሠራዊቱ ክፍል ከመንግሥት ኃይል እየከዳ ወደ ፋኖ ሲቀላቀል ቀጣይ ጉዞ ሊሠምር የሚችለው “መዳረሻ
ኢትዮጵያዊነት” ላይ መሆኑ ምንጊዜም መዘንጋት የለበትም። ለዘመናት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያችን ለእነሱ በሚያመች መንግስታዊ መዋቅር ተካታ እንደፈለጉ ሊያዙን፣ ሊገዙን፣ “እፍኝ ቆሎ ይዘህ ወደ አሻሮ ተጠጋ” እንዲሉ በእርዳታ ስም ገና ያልተነካ የሀገራችንን ሀብት ሊዝቁ የሚቋምጡ የውጭ ኃይሎችን ጉዞ ገትተን ኢትዮጵያችን በራሷ ለራሷ/ለልጆቿ ትሆን ዘንድ “መዳረሻችን ኢትዮጵያ” ሲሆን የሚታይ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በመሆኑም “መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ” ዳጎስ ያለ መርህ፣ መፈክር እንደሆነ ልንረዳ ይገባናል።
“አማራ ፋኖ” እያስመዘገበ ያለውም ድልና በሌላ አንጻር ያለውን አገዛዝ እንዴት እያርበተበተው እንዳለ ከሚሰጡ የመንግስት የመጨረሻ ሰዓታት መግለጫዎች መረዳት ይቻላል።
ይህ የ “አማራ ፋኖ” ተጋድሎ በድል ተጠናቆ ትልቋ ሥዕል ኢትዮጵያ እንድትሆን ከተፈለገ በተለይ ድጋፍ እንበለው አመራር ሰጪ ከሆኑት ዘንድ እጅግ ከባድ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል። አለን ከሚሉት ተመክሮ አንጻር በርካታ ነገሮችን ማገናዘብ ይጠበቅባቸዋል።
ለምሳሌ፦
ኢትዮጵያችን የበርካታ ነገድ/ጎሳ ሀገር መሆኗን፣
ኢትዮጵያችን ዋና ዋና የእስልምናና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ሀገር መሆኗን፣
እምነት ባይኖራቸውም ኢትዮጵያን የሚያፈቅሩ፣ የሚወዱ፣ የሚሞቱላት በርካታ ዜጎች መኖራቸውን፣
በኢትይጵያችን በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ የሲቪክ ማህበራት እንዳሉ ማገናዘብ፣
በርካታ ማኅበራት የሠራተኛ፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ወዘተ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር መኖራቸውን፣
ምሁሩን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ታዋቂዎችና አክቲቪስቶች ያሏት ለሀገርና ሕዝብ ተቆርቋሪዎች መኖራቸውን፣
በውጭው ዓለም ተበትኖ ያለው ዴያስፖራ ሀገሩን እንደሚፈልግና እንደሚወድ ዋናው ማሠሪያው ኢትዮጵያዊነት መሆኑን መገንዘብ፣
ወዘተ. እነኚህንና መሰል ጉዳዮችን ማገናዘብ እጅግ አስፈላጊ ነው።
በዚህ ሁኔታ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ለሚያደርጉት መልዕክት እጅግ ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ ሀሳቤን ላካፍል ወደድሁ።
“ትግላችን የመከላከል ነው” አሁን የ“አማራ ፋኖ” ከመከላከል አልፎ ማጥቃት ሂደት ላይ ነው። እንደውም እንዲህ በአፋጣኝ መንግሥትን እያናጋ ሲንቀሳቀስ ይህንን ማጠናከርና በዚህ ስሜት የማጥቃት ጉዞውን እንዲገፋበት መገፋፋት እንጂ መከላከልን መደጋገም ጥሩ አይመስለኝም። አራት ኪሎም ሊገባ የሚችለው እኮ የመንግሥትን ሠራዊት እያጠቁ ሲጓዙ ነውና ምንም የሚያስጨንቅ ጉዳይ የለም በአጭሩ “አማራ ከደረሰበት የበርካታ ዓመታት ስቃይና ፍጅት አንጻር በሰላም ሲከላከል፣ ሲታሰር፣ ሲደበደብ፣ ሲገደል ኖሮ ዛሬ ግን እራሱን ከመከላከል አልፎ ይህን ዘረኛ ሥርዓት ለመናድ ፋኖ ተሰማራ ብሎ መሳሪያውን ከፍ አድርጓል፣ ይህ መሳሪያ ደግሞ ዝቅ የሚለው አማራው የጀመረውን የመሳሪያ ትግል በድል ሲያጠናቅቅ ነው።” ቢባል ያምራል።
“አራት ኪሎ ገብተን እኛ በምንፈልገው መንገድ ሥርዓት እንመሠርታለን” ትልቅ ስህተት!!!
ወያኔ፦ አዲስ አበባን እየከበበ ሲቃረብ “እኛ ቤተ መንግሥት ስንገባ ኤርትራ የራሷን ባንዲራ ታውለበልባለች፤ እኛ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ እንመሠርታለን”
ኦሮሙማ፦ በለውጥ ስም የሚያተራምሰው የዐብይ አሕመድ አገዛዝ እራሱን አደላደልኩ ካለ በኋላ “ለኦሮሚያ አመቺ የሆነች፣ እኛ የምንፈልጋት “ኢትዮጵያን” እንገነባለን፣ አማራን ደብረብርሃን እንከተዋለን”
እያሉ ሀገር ምን ላይ እንደደረሰች አይተናል።
ከዚህ አቀራረቤ አንጻር ሻለቃ ዳዊት ከአሎት ተመክሮ አንጻር እጅግ መሠረታዊ የአባባል ስህተት ይታያል። ምን አይነት ሀገር ነው የሚፈልጉት? በአማራው ዘር የበላይነት የምትመራ? ሌላ ተረኛ ዘር የሚመራት ሀገር? ሌላም ሌላ ጥያቄ ቢነሳ በአሉት ጥቅል ምላሽ ላይ ነውና መቀበል ይኖርቦታል።
“አማራ ፋኖ አራት ኪሎን ተቆጣጠረ ማለት የመንግሥት ስልጣንን ጨበጠ ማለት ነው። ከዚህ በቀጣይነት አማራው ያደረገውን ክቡር ተጋድሎና የከፈለውን መስዋእትነት በታሪክ መዝገብ በማስቀመጥ፣ አማራው ለኢትዮጵያ የተጋደለ ኃይል መሆኑን ለማስመስከር፣ ያለው የዘረኝነት አገዛዝ ያበቃ ዘንድ በቅድሚያ በወያኔ ተረቆ ለ32 ዓመታት ኢትዮጵያ የተጫነባት የዘር ሕገ መንግሥት አክትሞ፣ ዘርና ቋንቋን ተገን ያደረገ አከላለል ያበቃ ዘንድ ሥልጣኑን ከዘረኛው የዐብይ አሕመድ አገዛዝ የሚረከበው አማራ ፋኖ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ፣ የሲቪክ፣ ታዋቂ ኃይሎች፣ ምሁራን ወዘተ. ጋር በመምከር ወደ ሽግግር መንግሥት ለመመሥረት የሚያመራንን መስመር በመዘርጋት ሕዝባዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመሥረት ጥርጊያ መንገድ በማሳየት አቅጣጫ ለመጠቆም እንጥራለን” በዚህ መልክ ቢቀርብ የመላው ኢትዮጵያን ሕዝብ ልቦና በሳቡት ነበር።
ጠያቂ መልካም ካሳ ያነሳችው አንድ መሠረታዊ ጥያቄ አለ በሚገባ መብራራት ያለበት ሻለቃ ዳዊትም በጥሩ ሁኔታ ቢያስቀምጡትም ይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል።
“ሌሎች ኃይሎች የትግራይ ወያኔ እና የኦሮሙማ ኦሮሚያ ኃይሎች ከእናንተ ጋር አብሮ መኖር አንፈልግም ቢሉስ?” የሚል ጥያቄ አቅርባለች። “አማራው በትግራይና በኦሮሚያ ተከቦ ሊኖር አይችልም” በሚል ጥቅል ምላሽ ሰጥተዋታል። መልካም ነው። በተጨማሪም መጠቀስ ያለበት “አማራው እየተዋጋ ያለው አማራ የሚለውን ክልል ለመያዝ ሳይሆን የዚህን የዘረኝነት አገዛዝ ቁንጮ መንግሥት ገርስሠን ያለውን የዘረኝነት ሕገ መንግስት ለትውልድ ተሻጋሪ በሆነ ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ሕገ መንግሥት ተተክቶ ኢትዮጵያን እንደሀገር ማስቀጠል በመሆኑ የ “አማራ ፋኖ” ተጋድሎ በድል ተጠናቀቀ ማለት የወያኔም ሆነ የኦሮሙማ ዘረኛ አገዛዝ እስከ ሥርዓቱ አበቃለት ማለት ነው። ለዚህም በኢትዮጵያዊነቱ የማንጠራጠረው የትግራይ ሕዝብም ሆነ የኦሮሞ ሕዝብ ወደ ሀገራዊ ስሜታቸው እንደሚመጡ አንጠራጠርም። ለዚህም ዶር ዐብይ ለስልጣን ብቅ ብቅ ያለ አካባቢ “ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ” ሲል እንኳን ሌላውን ዘር ይቅርና ኦሮሞና ትግሬው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ ጀምረው ነበር። ይህ የሚያሳየው ዳር እስከዳር ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት የዘር አገዛዝ እንዳንገፈገፈው ነውና ይህ ደግሞ በመተባበርና በፈቃደኝነት እንደሚመለስ ተስፋ አለኝ።” ምላሹን ለማጠናከር።
በሌላ በኩል ይህን የ“አማራ ፋኖ” የተቃወመ ሁሉ የወያኔና የኦሮሙማ ዘረኛ ብቻ አድርጎ መፈረጁ ስህተት መሆኑን እየጠቆምሁ በዚህ እንቅስቃሴ “መሃል ሰፋሪ” ሊኖር አይችልም የሚለው ድምዳሜ የሰዎችን መብት መጋፋት ይመስለኛል። ደርግ በአብዮቱ ወቅት “መሀል ሰፋሪ” በራሱ ጠላት ነው እያለ ስንቱን ንጹሐን እንደፈጀ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። አንድ ንቅናቄን ወክሎ የሚናገር ሰው ከስሜታዊነት ገለል ቢል ይመረጣል።
በሌላ በኩል ሻለቃ ዳዊት የኤርትራን ጥያቄ እንደ ቅኝ ግዛት የተያዘች እንደነበረች ምስክርነት ሲሰጡ ምን ያህል እንደሚያጠያይቅ ዝርዝር ባልገባም ልገልጽሎት እወዳለሁ። እውን ኢትዮጵያ ናት ኤርትራን ቅኝ የገዛች? ይህንን ወደፊት ልንመለስበት እንችላለን።
ለማጠቃለልም ሻለቃ ዳዊት “የአማራ ሕዝባዊ ንቅናቄ” ብዙ አጋሮችን ይዞ ይጓዝ ዘንድ ካስፈለገ እጅግ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ልገልጽልዎት እወዳለሁ። እንደማንኛውም ታዋቂ ግለሰብ ሀሳቦን ገልጸው ቢሆን በርካታ የሚቀባዥሩ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ስላሉ ከነሱ ደርቤዎት አይጨንቀኝም ነበር። ግና ቀጣይ የሀገሪቷ መንግሥት ሊሆኑ ሲንደረደሩ እና ብልጽግና/ህወሓት ሥርዓት ለመናድ የሚፋለመውን “አማራ ፋኖ” ወክለው ሲናገሩ የሚሰጡት ትንታኔና መግለጫ ሀገርና ሕዝብን ይመልከታል፤ እኔም ሆንኩ በርካታዎች ስህተትም ቢኖርብን ስለሀገራችንና ሕዝባችን እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማችን ድምጽ የምናሰማ እንዳለን ሊገነዘቡ ይገባል እላለሁ።
አማራ በኢትዮጵያዊነቱ ጥርጣሬ ባይገባንም በብዙ ሚሊዮን የሚገመተውን ኦሮሞ እና የትግራይ ሕዝብ እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ዜጎችን የት አድርገን ነው “ኢትዮጵያ የአማራ ናት” የሚል ዱላ ለሌሎች የሚያቀብሉት? ይህ ሁሉ በተለያየ መድረክ በመቅረብ ውይይት ሲሰጡ ጥሩ ልምድ ካሎት፣ የተለያዩ ጽሁፎች ካስነበቡን እንዲሁም መጽሐፍት ከጻፉ፣ እርሶም እንደነገሩን በተለያየ አህጉራት የሰሩና የሌሎች ሀገሮች በተለይ የዘር ፍጅት ከተካሄደባቸው በርካታ ልምድ ካካፈሉን ሻለቃ ዳዊት የዚህ ዓይነት ስህተት ባይጠበቀም ሁኗልና አይመለስም። ለዚህም ይመስለኛል በተደጋሚ አጭር ማብራሪያ ለመስጠት የተገደዱት።
ሌላው ላሰምርበት የምፈልገው እኔም ሆንኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎቱ ሀገሩ ኢትዮጵያ እንጂ ሌላ አይደለም እና ይህንን ሕዝብ ለረዥም ዓመታት ከደረሰበት መከራና ስቃይ በእግዚሐብኤር ረዳትነት ለማላቀቅና ለጥሩ ዘላቂ ሀገር ግንባታ ለመዘጋጀት ከሆነ የተሰራውን ስሜታዊ አገላለጽ በማረም ለመጓዝ መጣሩን ላሳስብ እወዳለሁ። ዐብይ አሕመድ “አታሎና ሸውዶ” ሀገር ሊበታትን የተጓዘበት አሳፋሪ አካሄድ የትም አላደረሰውም፤ አያደርሰውምም እና የሩቁን እንተወውና ከአሁኑ፣ ከትላንቷ ታሪክ ሌሎች ከሰሩት ስህተት ትምህርት በመውሰድ ትግሉን እንምራው ሀገርና ሕዝብ እንዲወዱን እንሁን። ካልሆነም ትግል ያልተለየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመታገል አዲስ አይደለምና ትግሉ ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጉቱ ግለሰብ ሳይሆን ሀገሩ ነችና ለራሳችን ስንል እንጣፍጥ።
ከምስጋና ጋር
ነሲቡ ስብሐት (nhsibhat@gmail,com) 7033004302