August 13, 2023
13 mins read

ለኢትዮጵያ መንግሥት “ራሱን እንዲመረምር” የቀረበ አቤቱታ

Oromo Tergnaw 1 1 1

በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ይህ መልእክት የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንደሚደርሳቸው እምነት አለኝ። በሙያ ሥልጠናዬ የነገረ ግጭት ትንታኔ እንዲሁም የነገረ መለኮት ትምህርት ሙያተኛና በመስኩም የበኩሌን አስተዋጽኦ ያደረግሁ ነኝ። ቀደም ባሉት ሁለት ዓመታትም “ዐብረን ሰው እንሁን” በሚል የግጭት ልውጠት መሰረታዊ ግንዛቤን የሚሰጥ መጽሐፍ ለእትመት በማብቃት አቅም በፈቀደ መጠን በፖለቲካው ወሳኝ ሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች ዘንድ ጭምር ለማሰራጨት ጥረት አድርጌአለሁ። ይህንንም የምለው የምሰጠው አስተያየት መነሻው ከምን አንጻር እንደሆነ ለማሳወቅ ብቻ ነው።

ከአምስት ዓመት በፊት አንስቶ በኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካዊ ጕዳዮች ላይ ተመሳሳይ ሐሳብና ማሳሰቢያ በየጊዜው ከመስጠት አልተቆጠብኩም። አሁንም በአንድነት ውስጥ ለዘመናት ቆይቶ፣ ነገር ግን ልዩ ልዩ ለሆነው የአገሪቱ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ የወቅቱ (2018-2023) ሁኔታ ዘላቂ ሰላምና ፍትህ እንዲያመጣ እጅግ የጠለቀና በራስ ላይ የጨከነ “የራስ ምርመራ” ስራ ከአገዛዙ እንደሚጠበቅ ለመናገር እገደዳለሁ።

ምንም እንኳ ይህን መናገር ለመፈረጅ ለወሰኑ ወገኖች አንዳች ለውጥ ባያመጣም፣ የምሰነዝረው አስተያየት ወገንተኛነት የሌለውና ከነባራዊ ሁኔታና ከሙያ አንጻር እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። አሁን ኢትዮጵያ እየተጋፈጠችው ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ፣ አገርም ሆነ የሚያስተዳድራት አካል እንዲቀጥሉ፣ ከወደፊቱም አይቀሬ ግርሻ ለመዳን እውነቱን መነጋገር ማንም ሊሽሸው የማይገባ ነገር ነው።

አገሪቱ አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ አይደለችም፣ የማይመረጠውን መንገድ መርጣ በረጅሙ ተጕዛበታለች። የደረስንበትም ስፍራ ውስብስብ የተግዳሮት ድር ከመፍጠሩ የተነሳ ከኢትዮጵያ መንግሥት አጠቃላይና ራስ ተኮር የሆነ፣ ከተለመደው ምላሽ የተለየ ምላሽ ሊያሰጥ የሚያስችል ፈጣንና ጥልቅ ምርመራ በራሱ ላይ ማድረግ የሚገደድበት ምኅዳር ላይ ይገኛል። ይህ የተያዘው የፖለቲካ እልህ ሊለወጥ ይገባል!

በግልጽ እንደሚታወቀው፣ የተገባው የማህበራዊ ትስስር፣ የኢኮኖሚ ርካታ፣ የፖለቲካ መረጋጋት ተስፋ ሊፈጸም ካለመቻሉም ባሻገር፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ፈጽሞ ተቃራኒ የሆኑ ክስተቶች ያለማሰለስ ቀጥለዋል። በሕዝብና በመንግሥት መካከል የማመንና የመተማመን ሁኔታ ከማዘቅዘቅ ወደ መጥፋት ስለደረሰ ተገቢውን የልውጠት መሰጠት ከህዝብ ማግኘት አልተቻለም።

አገሪቱ በእጇ ላይ ያለው መልከ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ፣ ቁጥሩ እያሻቀበ የመጣው የታሳሪ (በአፈሳም ጭምር) ብዛት፣ የውስጥ አገርም ሆነ የዳር አገር ድንበርና ወሰን ውጊት፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ብዛት፣ የአስተዳደር በደል እና የመሳሰሉት መንግሥትን ትንፋሹን ውጦ ወደ ራስ ያተኮረ ልባዊና መድኅናዊ ግለ ምርመራ እንዲያደርግ ግድ ይሉታል። የአገሪቱ አቅጣጫ የውስጣዊ መከፋፈል፣ የሲቪል ኑሮ ረብሻ፣ ከብሔር ወሰን የዘለለና የሚያሻቅብ የኅይል እንቅስቃሴ ሁሉ፣ ግለሰቦችንና ማህበረሰብን እድል ፈንታቸውን የተመሳቀለ አድርጎታል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ አገርን ለልማትም ሆነ ለመረጋጋት አያስችልም።

በመንግሥት ፍላጎትና የፖለቲካ ግብ ተጽእኖ ሥር ያልዋለ፣ ኅላፊነት በሚሰማቸው ሹማምንት፣ ምሁራን፣ የእምነት መሪዎች፣ የቀጣይ ትውልድ ተወካዮች፣ ጕዳት ደርሶብናል የሚሉ ቡድኖች፣ እና ዋና ዋና ባለድርሻዎች የሚሳተፉበት የለውጥ ጥረት ዛሬ ነገ የማይባል፣ እንደ ተለመደው ከይስሙላ እና ከ ”ረጋ ሰራሽ” የተረፈ መፍትሒ ያስፈልጋል።

በግልጽ እንደሚታወቀው፣ የፖለቲካው ርእዮተ ዓለም ምን ዓይነት እንደሆነ ግራ የሚያጋባው የጽንሰ ሐሳብ ብዥታና የመንግሥት የአመራር ብቃት እጅግ አናሳነት ለዚህ ሁሉ የአገሪቱ ቀውስ ምክንያት ሆኗል፣ ይህ ማንም ሊሰስተው የማይገባና ለሚፈለገው ለውጥ መጀመሪያ አሜን የሚባል እውነት ነው። አገሪቱ ካለፈ ታሪኳ ጋር የተያያዘ ችግር የነበረባት ቢሆንም፣ በለውጡ ጅማሬ ራሷን ለህክምና ገልጣ የሰጠችው ቀዳሚ ዕድል በአመራር ብቃት ሊፈወስ ወይም ሊሻለው ይችል ነበር እንጂ እንዲህ አሁን እንደሚታየው ሊብስበት አይገባውም ነበር።

የመንግሥት ባለ ሥልጣናት መገደልና መገዳደል፣ የመረጃ መሸፋፈን፣ የባለ ሥልጣኖች ቶሎ ቶሎ ከሥልጣን መልቀቅ፣ በየመዋቅሩ መለዋወጥ፣ የውስጣዊ ግጭት ማሻቀብ፣ የሰላም ስምምነት መፈረካከስ፣ የሃይማኖት ቤተ ሰዎች በፖለቲካ መነካካት፣ እና ሌላ ብዙ ጉዳዮች ሁሉን የሚያጠቃልል ፈውስና የእርቅ አቀራረብ በአስቸኳይ እንዲፈጸም ግድ ሊል ይገባል። በእንዲህ ዓይነቱ ጎዳና ራስን መመርመር ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን ባለ ድርሻ ነኝ በሚለው ሁሉ ዘንድ ሊተገበር የሚገባ ጉዳይ ነው።

ለዚህም የሚከተሉትን የመነሻ መፍትሒ እነሆ እላለሁ፣ ሐሳቦቹ የሚሰነዘሩት ከሰላም ግንባታ ሙያ አንጻር እንደሆነ ልብ ይባልልኝ።

ለግጭት ልውጠት ዋቤ እንደሆነ ሰው፣ የሚከተሉትን የመፍትሒ መንገዶች እነሆ እላለሁ።

የመንግሥት ተጠያቂነትና ግልጽነት

 

የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያደርጋቸውን መንግሥታዊ ተግባራትና አገራዊ ውሳኔዎች፣ በፍጹም ግልጽነትና በተጠያቂነት ሊያደርግ ይገባል። ግልጽ የሆነ ተግባቦት/ኮሚኒኬሽንና ኃላፊነት የሚታይበት መንግስታዊ አስተዳደር፣ ህዝባዊ አመኔታን ለመገንባት እጅግ አስፈላጊና ቀዳሚ የመንግሥት ባህርይ ሊሆን ይገባል።

 

የብሔራዊ እርቅና አገራዊ ፈውስ

 

ሁሉን አቀፍና አጠቃላይ የሆነ፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ በጉዳዮች ላይ የመግባባት፣ እንዲሁም ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር የይቅርታ መርሐ ግብር መመስረት፣ በዚህም የበደለና የተበደለ የሚገናኝበትን ዘመናዊና ባህላዊ የህዳሴ ፍትሕ ሥርዓትን መመስረትና መዘርጋት።

 

ሁሉን አካታች የአመራር እቅድ

 

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የብሔር ስብጥር ባሉባቸው አገር፣ ደግሞ ደጋግሞ በመፈተሽ የአገዛዙ መዋቅር ሁሉን አካታች እንዲሆንና ትርጉም ያለው ተሳትፎ በሁሉ ዘንድ በመንግስትነት ደረጃ እንዲኖር ማድረግ ብሔራዊ ውሳኔዎች የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ሰፊ የባለቤትነት መሰረት ያላቸው እንዲሆኑ ያደርጋል።

 

ዓለም አቀፋዊ ሶስተኛ ወገን ድጋፍ

 

ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን፣ ለማኅበራዊ መረጋጋትና ስለ ሰላም ግንባታ ሲባል፣ ለሶስተኛ ወገን አገልግሎት ዓለም አቀፍ ተቋማትን እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን ባለሙያ ግለሰቦችን መጠቀም። የግጭት መፍትሒና የመፍትሒ አገባብ ባለሙያዎች፣ የእርቅ ሒደት ድጋፍን እንዲያደርጉ የብሔራዊ ውይይትንም እንዲታዘቡ ማድረግ።

 

አገር አቀፍ የሰላም ትምህርትና የስብራት ፈውስ መርሐ ግብር

 

በዓመታት መካከል ባለ ማቋረጥ በየስፍራው የተከሰቱ ግጭቶች ያስከተሏቸው የስሜት ስብራቶችና የስነ ልቡና ቁስሎች እንዲድኑ፣ ተካታችና አጠቃላይ የሆነ የሰላም ትምህርት መርሐ ግብሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል። መንግስትና የመንግሥት አካላትም የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ በሚሆኑበት መልኩ እነዚህ መርሐ ግብሮች በጥንቃቄ ከተፈጸሙ አንድ አካላዊ ህመም ታክሞ እንደሚድን ያህል በግለ ሰቦችና በማህበረሰብ ላይ ብዙ ፈውስ ያመጣሉ።

 

እንግዲህ መጽሐፍ እንደሚል “ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” ሚኪያስ 6:8 ነውና፣ ኢትዮጵያ እየተጋፈጠች ያለችው ወቅታዊ ችግር አሁንም በመንግሥት አካላት ብቻ ይፈታል ብሎ ማሳብ ስህተት መሆኑን መንግሥትም ሆነ ህዝብ ተገንዝቦ በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት የስካሁኑ ጕዞ ራሱንም ሆነ ህዝብን የት እንዳደረሰ ተመልክቶ ወደ ራሱ ምርመራና ማስተዋል በመመለስና ከኃይል አማራጭ ይልቅ የተለየ መፍትሒ እስካሁን በየምክንያቱ እየተኮላሹ፣ እየተድበሰበሱ እየታፈኑ ያሉትን ሁሉም የሚሳተፍበት የሰላም ግንባታ መፍትሒ ይሰጥ ዘንድ ይገባል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop